የሰላም ሃሳብም፤ የሰላም እርምጃም #ሊደፈር እንጂ #ሊፈራ ወይንም #ሊሸሽ አይገባም። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ #ስልክ ደውለው ለምን አያናግሯቸውም?? ከፋን ያሉትንም፧

 

የሰላም ሃሳብም፤ የሰላም እርምጃም #ሊደፈር እንጂ #ሊፈራ ወይንም #ሊሸሽ አይገባም። 
 
ደፋር ዕይታ ነው። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ #ስልክ ደውለው ለምን አያናግሯቸውም??
በተመሳሳይ ሁኔታም ለልጅ እስክንድር ነጋ፦ ለልጅ ዘመነ ካሴ፤ ለልጅ ምሬ ወዳጆ፤ ለሻለቃ መሳፍንት ተስፋ እና ለጃል መሮ ስልክ ደውለው ለምን በቅንነት አያነጋግሯቸውም። በዓለም የሌለ የሰላም ሚር የፈጠሩ፤ "የዓለም የሰላም አባት"፤ የሰላም ሎሬት ተሸላሚ ለሆነ ሰብዕና የራሱን አገር ችግር መፍትሄ #አማጭነት እንደምን ይቸግረዋል? አፈሙዝ ስለምን ይናፍቀዋል???? ተራርቆ --- መራራቅ ነው። ተቀራርቦ ግን መቀራረብ ነው።
 
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"
 
 May be an image of 3 people and dais
 
ጤና ይስጥልኝ ክብረቶቼ እንዴት ናችሁልኝ????
 
 
ኢትዮጵያ ከሱማሌ ጋር የምታደርገው ሰላማዊ ግንኙነት ጅምሩ የሚያበረታታ ነው። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ወጥነው ካልተውት። በሱማሌ በኩልም ወጣ ገብ ነገር ስለማይ ጽናቱን ከሰጣቸው ጠብ፤ ጥላቻ፤ ቂም ለአዲሱ ትውልድ ማስረከብ የአስተሳሰብ ድህነት ነውና በጀመሩት ሰላማዊ ጎዳና እንዲቀጥሉ ምኞቴ ነው።
 
እኛ አፍሪካውያን ለአፍሪካ ችግር የመፍትሄ ግንባር ቀደም ተሰላፊወች ልንሆን ይገባል። ድጋሚ በሁለቱ አገሮች መሃከል እልቂት እንዳይኖር ማድረግ #ቸር ጎዳና ነው። የቱርክ አገረ መንግሥት ለወሰደው ተነሳሽነት እና መልካም ሂደት ሊመሰገን ይገባል፤ ፈጣሪ አላህ ይጨመርበት ነው እንጂ መልካም አስበው አገሮችን የሚያቀራረቡ ቅኖች ለእኔ ብፁዓን ናቸው። ሰላም #ሊፈራ አይገባውም። ሰላም #ሊደፈር ይገባል።
 
 
የወደብ ጥያቄ ጎልቶ መቼ ወጣ? የወደብ ጥያቄ በኢትዮጵውያን ውስጥ #ጽንስ ነው። የማይወለድ ግን በውስጥ #እዬተገላበጠ ጊዜ #የሚጠብቅ። በቀደመው በዘመነ ህወሃት እራሱ ስለወደብ ማንሳት "በሽብር ወንጀል" የሚያስጠይቅ ነበር። አሁን ይፋዊ የመወያያ አጀንዳ ሆኗል። ይህ ጥሩ ነገር ነው። 
 
#የአብይዝም የወደብ ጥያቄ፤ የባኽር በር የማግኜት ፍላጎትን በሁለት መስመር ለይተን ማዬት የምንችል ይመስለኛል።
 
1) የባህር በር መውጫ የቀደመ የአብይዝም ህልም ይመስለኛል፤ ከኽር ኃይል ምስረታ ጋር አገናዝቤ ሳዬው። ቀድመው እንዳደራጁ ዜና አዳምጫለሁኝ። የባህር ኃይል እኮ የተለዬ ክብር እና ልዩ ማንነትም ነበር። የሚያሳሳ የሚናፈቅም ነበር ከአለባበስ ጀምሮ ተልዕኳቸውም ሁለገብ ነውና። 
 
2) የወደብ ጥያቄው ግን #የፋኖ ንቅናቄ ጎምሮቶ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ማዕበሉን ሲቀዘፍው ያን ጊዜ አቅጣጫ ለማስቀዬር፤ ያው አባ ገራገሩ አማራ ኢትዮጵያ ሲባል ቀዳሚ የለውም እና የእሱን መንፈስ #እንደማግኔት ለመሳብ ታልሞ የተወጠነ ነው ብዬ አምናለሁኝ።
 
እርግጥ ነው ውስጥ ለውስጥ የቀደሙ ተግባራት ቢኖሩም ፍሰኃው የተበሰረው በፈረንጆች አቆጣጠር ጥር 1/2023 ነበር። ለዛውም እንደ አገር ገና ዕውቅና ካላገኜች ነገር ግን እጅግ በሚደንቅ ሥልጣኔ፦ ሥልጣንን በሙሉ ዴሞክራሲያዊ ዲስፕሊን ከምትከውን ሱማሌላንድ ጋር ነበር። 
 
ኢትዮጵያ ይሁን፤ ውጭ የሚኖሩ የአብይዝም ደጋፊወች በተለይ የፖለቲካ ሳይንስ ሙሁራን ሰፊ ትንታኔ ሰጥተውበታል። ብዙ አቅም ፈሶበታል። አዲስ ቅራኔም አፈንድቶ ነበር። ያ ሁኔት ባለህበት እርጋ በል ያለው የአንካራው ዲክላሬሽን ነበር። እስከ አሁን ባለው ሁነት ደህና ይመስላል። ነገር ግን የሁለቱ አገር መሪወች የአቋም እና በውሳኔ የመጽናት አቅም በምን ሁኔታ ሊቀጠል እንደሚችል አይታወቅም። ለለቱ ግን ውጥረቱ ረግቧል።
 
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተንታኞችም የተሰጣቸውን አዲስ አጀንዳ እንደ ተለመደው ያቆላምጣሉ። ሚዲያወችም እንዲሁ። ለክብራቸው፤ ለሞገሳቸው፤ ለተቀባይነታቸው ግን ፈታኝ ይመስለኛል። በማይጸና ስምምነት መንግሥታቸውን ወግነው መተንተን፤ እንደ ገና ደግሞ እንደ ጆንያ ሽንብራ መገልበጥ። ቀዝቃዛም፤ በረዶም፤ ፍልም ሲቀርብ ማዕደኛነት??? ህም። ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ለምን? እንዴት?--- የተከለከለ መንገድ ነው።
 
የሆነ ሆኖ በሱማሌላንድ በኩል ተንጠልጥሎ የቀረው አመክንዮም በምን ሊቋጩት እንደሚችሉ የአብይዝም መንግሥት ሌላው ትልቁ የቤት ሥራው ይመስለኛል። ለሱማሌላንድ ግን ትልቁን የዕውቅና ምዕራፍ ከፍቷለኝ - አቤቶ አብይዝም። በሌላ በኩል ሱማሌላንድ በምርጫ አዲስ አመራሯን አግኝታለች። አዲስ አመራር ደግሞ አዲስ የአመራር የማንነት ዘይቤ ይኖረዋል። ጠንከር ያለ ዕይታም ቢቢሲ አማርኛው ፔጅ ላይ አንብቤ ነበር። ጊዜ የሚጠብቅ ጉዳይ ነው።
 
#በዚህ ውስጥ ………
 
የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አቅም በእጅጉ #ተፈትኗል። በእጅጉ #ታሽቷል#አዳልጦታል ማለት ይቻላል። በእጅጉ ውስጡ ተጋልጧል። ይህ የሆነበት ምክንያት የመሪ እና ተመሪ የምክክር ዓውድ ልልነት፤ ወይንም የመብት እና የግዴታ ዝግነት ያመጣው ጣጣ ይመስለኛል።
በተለይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስተር እና፤ የደህንነት አካላት ጥንቅቅ ያለ ተግባር ሊከውኑ ይገባል። 
 
ሰሞኑን የሰማሁት የመቋዲሾ የአዬር ማረፊያ ጥቃት እርምጃም ቢሆን ከዚህ ገርበብ ያለ የመሪ እና ተመሪ ግጥምጥሞሽ ምክንያት ይመስለኛል። ለነገሩ ጠሚር አብይ እራሳቸው ከስለላ ተቋም ምስረታ እና መሪነት የቆዩ ሆነው፦ ሰርክ እንዲህ ዓይነት ለዓለም ሚዲያ የተጋለጠ ግድፈት መታዬት አይገባውም ነበር። በመንግሥት አስተዳደር ለቆዬ ሰብዕና እንዲህ እንደ ጀማሪ በዬውጥኑ መፍረክረክ ጥሞና ወስዶ እራስን ማጥናት የሚገባ ይመስለኛል። ለነገሩ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ከአቶ ጃዋር መሃመድ (ሃጂ) በስተቀር ጥሞና ጋር ተገናኝተው አያውቁም። ብንናገርም ላም እረኛ ምን አለ ከመጤፍ አይቆጥሩትም። አንሰማም። 
 
ጥሞና አይደለም ለአፍሪካ አንከሯ ኢትዮጵያን ለሚመራ፤ ወይንም እመራለሁ ብሎ እራሱን ለዛ ያጬ ቀርቶ እኛ ለግል ህይወታችን፤ በዚህ አገራዊ ጉዳይ ምስቅልቅል ሲልም ጥሞናን ፈቅደን እና ወደን እንወስዳለን። ሙሉ አቅም፤ ሙሉ እርጋታ፤ ሙሉ ማስተዋልን ጥሞናው ይመግበናል። ለስህተታችን እርምት፦ ለውስጣችንም ትጉህ ቡርሽ እናገኛለን። ጠቃሚ ብልህነት ነው - ጥሞና። የፈጣሪ ከአላህ ጋርም ያገናኛል።
 
#ነገረ - ቅንነት በግልጽነት።
 
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ለአቻቸው ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ስልክ ደውለው ቢያነጋግሯቸው ምርጫዬ ነው። ስልኩ ላይነሳ ቢችል እንኳን፦ ደጋግመው ደውለው የዓለም "የሰላም አባትነታቸውን" ድርሻ መወጣት ይኖርባቸዋል ባይ ነኝ። እርግጥ ነው መታመንን እንደ መጀመሪያው ዙር በቀላሉ ለማግኜት አይቻል ይሆናል። ግን ለሰላም ደግሞ፤ ደጋግሞ መጣር በእጅጉ ያስፈልጋል። ይህን ወርቃማ ጊዜ ጭቃ ውስጥ ዘፍቆ ወደ እርስበእርስ እልቂት ማምራት ሥልጣኔ አይደለምና። የወኔ መፈታተኛ ጉዳይም አይደለም። ብልህ ጎዳና ነው በቅርበት ፈቅዶ መነጋገር። በዚህ አሳቤ ፕሮ ኤርትራ እና ፕሮ ኢትዮጵያ ወገኖቼ ወይንም ሚዲያወች ሊበግኑ ይችላሉ። ግን ከቋያ ነዲድ እሳት፤ ከፍምና ከቀጣይ ቃጠሎ ይሄኛው መንገድ ቀላል እና ወጪአልባም ስለሆነ ነው ሃሳቡን ያነሳሁት።
 
በዕድሜ፤ በተመክሮ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፤ ጠቅላይ ሚር አብይን አሳምረው ይበልጣሉ። ይህ ባይሆን፦ ዝቅ ብሎ ለትህትና፤ ለትዕግሥት፤ ለመቻቻል እራስን ማስገዛት ቢያስከብር እንጂ የሚያስንቅ አይደለም። ደፍረው ኤርትራ በ2010 ዓም ዶር አብይ ሲሄዱ እኮ ያን የግርዶሽ መጋረጃ በድፍረት ቀደው ነው። አሁንም ይህን ቢያደርጉ አይዋ ቀውስ፤ እታታ ድቀት፤ መርጉ ሞት ቢከፋቸው እንጂ ሰላም ወዳድ የዓለም ህዝብ ደስ ይለዋል። ይህ ማለት ግን ለይስሙላ፤ ጀምሮ ለመተው፤ ለውዳሴ ከንቱ እንዳለፈው ጊዜ ከሆነ ትርፋ ከድቡሽት ላይ ቤት እንደ መሥራት ይሆናል። 
 
በፌድራሉ እና በህወሃት በጦርነቱ ውስጥ የጎላ ሚና የነበራባቸውን አማራን፥ አፋርን፤ ኤርትራን በሙሉም በከፊልም ያገለለው የደቡብ አፍሪካ ስምምነት ጦሱ ጥልቅ የሆነ አሳታፊነትን ያገለለ ነበር። ጉልሁ ለጊዜው ጦርነቱ መቆሙ ነው። ሌላው ጉዳይ እንደተንጠለጠለ ነው። ውልብልቢቱ ንፋስ በለጋው አቅጣጫ እዬተወዛወዘ ይገኛል። ሌላም ጦስ አስከተለ።
 
የሆነ ሆኖ እርቅም፤ ምህረትም፤ ይቅርታም ለሁለቱም ወገን ያስፈልጋል። የሰከኑ ሰዋዊ ዕሳቤወች ሊፈልቁ ይገባል። ቅንነትን ምራን ማለትም ይገባል። ሙሉ 7 ዓመት ቀውስ፤ ጦርነት፤ ሰቀቀን፤ ስጋት፤ ጭንቀት፤ መፈናቀል፤ ጥቁር ልብስ፤ መራራ ስንብት፤ የአካል ጉድለት፤ የተቋማት ውድመት፤ የመኖር መስተጓጎል መቆም አለበት። ጦርነት በቃ! 
 
በሌላ በኩል ትናንት አንድአፍታን ሳዳምጥ ነበር። ልጅ አማኑኤል መንግሥቱ ሁሉም የሰላም #አማራጭ ተሞክሮ እንዳልተቻለ የሚገልጽ ዕድምታዊ ዕሳቤ ሲያነሳ አዳመጥኩተኝ። እዛውም ጽፌለታለሁኝ። ልጅ አማን የሚያውቀው እኛ የማናውቀው የሰላም ጥረት ነበር ወይ? ምን ዓይነት? መቼ? የት? የፋክቶቹ ጭብጥ ይዘት ምን ነበሩ? ይህን ልጅ አማን ቢያስረዳን ጥሩ ነው። ይህን ያክል ያልወለዱት፤ ያላአሳደጉት ልጅ ለማገዶነት ለማቅረብን መናፈቅ ሰዋዊ አይመስለኝም። #ጭካኔ ነው። 
 
#ነገረ ፋኖን በሚመለከት ………
 
ፋኖ አንድ እስኪሆን መጠበቅ አያስፈልግም #ለቅናዊ ንግግር። አንድ ለመሆን የማያስችሉ የፋኖ ተፈጥሮን በሚመለከት ዩቱብ ቻናሌ ላይ በአውዲዮ ሠርቸዋለሁኝ። ስለሆነም ወደዛ አልገባም። አሁን ባለው ሁኔታ ፋኖ እንደ አባት አደሩ በጎበዝ አለቃ ስለሚመራ የጎበዝ አለቆች ጋር በተናጠልም፤ በጋራም ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ሊወያዩ ይገባል። ይህን መስመር ሊደፍሩት ይገባል። የአንድ አገር ልጆች እኮ ናቸው።
 
ጠሚር አብይ የነገረ አማራን ጉዳይ ከግምት በታች እንደሚንቁት አውቃለሁኝ። ይህ ግን አይጠቅማቸውም። በተለይ ኢትዮጵያን ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ሊመሩበት አይችሉም። ከሁሉ በላይ ሳይለንት ማጆሪቲው ስለፋኖ ኃይሎች ምን እያሰበ እንደሆነ ዳታው አልተሠራም። እሳቸው ወደ ሥልጣን ሲመጡ አይተውታል። ያ ሁሉ የድጋፍ ዌብ ምን ያህል ግዙፍ እንደነበር። ሚሊዮኖች ተስፋ ያደርጉት የነበረው ግንቦት ሰባቶች እስኪደነግጡ ድረስ፤ ጃዋሪዝም እስኪደነግጥ ድረስ፤ የአማራ አክቲቢስቶችም እስኪገርማቸው ድረስ ፍቅር በቅንነት በገፍ ---- ተለገሰ። 
 
ያ ኃይል አሁንም አለ በዝምታ ውስጥ። ንቀተወት እንደ አንድ የህዝብ መሪ የተገባ አይደለም። መታበይ ይጥላል። ህወሃትን የጣለው የአቶ አባይ ወልዱ ከልክ ያለፈ መታበይ ነበር። እርስወም ፈጥረዋል አቶ ሽመልስ አብዲሳን። ግን አይጠቅምም።
 
#ነገረ የጫካው ኦነግ አቶ ጃል ማሮ ……
 
ወጣት ነው። ቁጥብ ነው። ብዙ ሚዲያ ላይ አይታይም። ዕውቅና ሰጥታችሁ በሦስተኛ ወገን ውይይት ጀምራችኋል። ግን ተቋርጧል። ዶር አብይ አቶ ጃል መሮን ደውለው ቢያገኟቸው ጥሩ ነው። ይህቺ ጊዜ ወርቅ ናት ለእርስወ። እናም ይጠቀሙበት። የኢትዮጵያ ህዝብ ሙሉ 7 ዓመት ሰላሙን ተዘርፏል። በሃይማኖት ማንነቱ፤ በዞግ ማንነቱ፤ በዕውቀት ማንነቱ፤ በትጋት ማንነቱ፤ በመኖር ፍላጎቱ ላይ የፍርኃት ናዳ ነው የወረደበት። ካለ አጽናኝ። ካለ አይዞህ ባይ።
 
#መታመንን እና አብይዝም።
 
እስከ አሁን አብይዝም ታማኝ የሆኑበት መስመር ከኢዜማ ጋር ያለው ውህድነት ካልሆነ፦ በሌሎች ጉዳዮች መታመንን አላይም። ዛሬ በስብሰባ የገለፁት አቋም ነገ ይሻራል። ዛሬ ያመሰገኑት ነገ ይወገዛል። ዛሬ ያደነቁት ነገ ይቀላል። ከሁሉ የሚገርመኝ ጉዳዩን በቀጥታ አይናገሩትም፦ ታኮ ይፈልጉለታል። አስታከው በአሽሙር፤ በማጣጣል፤ በማቅለል ይገልፁታል። ይህ መንገድ ለሚሊዮኖች መሪነት? ሁሉንም የመኖር ሂደት ሁልጊዜ አንጠልጥለው ይተውታል። ለዚህ ነው እኔ አሳቻ ዘመን በአሳቻ መሪ የምለው። 
 
ነገሩ ሲከሰት ያቀሉታል። ብዙ አቅም ከፈሰሰበት በኋላ ይከልሱ እና መፍትሄም መንገድም ይሆናሉ። 7 ዓመት ተሞከረ። ግን የተረጋጋ አገር ለመምራት ጋዳ ሆነ። ስለሆነም መታመንን እርግጥ የሚያደርግ አዲስ ዕውነተኛ መንገድ ሊጀምሩ ይገባል ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ። ሙሉ የፖለቲካ እስረኞች ሁሉ ከእስር ሊለቀቁ ይገባል። አገር ቤት ገብተው መታገል ለሚፈልጉ ዜጎች የቢዛ ዕቀባ ሊጣልባቸው አይገባም። ማን ዜግነት ሰጪ? ማን ነሺስ? ---- ዕውቀቱ፤ ዕሳቤው ካለ ድፍረቱን አምጦ መውለድ ይገባል።
 
#ፖለቲከኞችን ታግሶ ስለማሳተፍ።
 
ተፎካካሪ፤ ተቃዋሚ የሚባሉት እንደ ብልጽግና ተጠማኞች ወይንም እንደ ተዋህጂወች እኩል ሊታዩ ይገባል። ያደለው ሌላ ይናፍቃል። ያለን አልይህ ግን ተፈጥሮኛ አይደለም። ስለ ኢትዮጵያ የሚታሰብ ከሆነ የሚበልጠው አቅም አገር ይረከብ ዘንድ መድረኩ ሊበጅ ይገባል። ህዝብ ይዳኜው ዘንድ በግልጽ መስክ ዕድሉ ሊመቻች ይገባል። ዴሞክራሲ አፈ ያለው መቃብር አይደለም እና። ነፃነትም እሮቦ እና ሲሶ የለውምና። ዜግነትም የክት እና የዘወትር ሊኖረው አይገባም። 
 
ለአንድ ዓለም ዓቀፍ የኖቤል ተሸላሚ ሰላም እንጂ ጦርነት፤ ፍቅር እንጂ ጥል፤ ይቅርታ እንጂ ቅሬታ፤ ምህረት እንጂ በቀል፤ አብሮነት እንጂ መነጣጠል ሊናፍቀው አይገባም።
 
#የሚፈራው። እንደ ማሳረጊያ። 
 
ከእርቀ ሰላም በኋላ መሰወር፤ መታገት፤ በምግብ ብክለት መሸኜት፤ በፊት ለፊት ግድያ፤ መኖር በካቴና ሊሆን ይችላል ተብሎ ይፈራል። ምልክቶች ከዚህ ቀደም ታይተዋል እና። ፋኖ አቶ አሰገድ የት ነው ያሉት???? ስለዚህ ከዚህ መሰል የሴራ አረንቋ አጽድቶ እንደ መሪ በራስ ተማምኖ በሁለት እግሩ መቆም የሚችል ቁመና እና ሰብዕና አፍሪካም፤ ኢትዮጵያም ያስፈልጋቸዋል ብዬ አምናለሁ። 
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን፤ አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
01/03/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?