መረጃ ከመዋለ ንዋይ በላይ ልዩ #አቅም ነው። መረጃ ተቋምም ነው ብቁ መሪ ከሰጠው። ማሸነፍ አህዱ የሚለው ከመረጃ አቅምም #ንጥርነትም ነው። ስለሆነም ይህን ቃለ ምልልስ አቃሎ ማየት አዲስ ገብነትን ያመለክታል።
"እግዚአብሄር በአንድም በሌላም
ይናገራል ሰው ግን አያስተውለውም።"
እንዴት አደርን ማህበረ - ቅንነት?
ክፍል ሁለት ትናንት ማምሻ ላይ ነበር የተለቀቀው። እኔ ያዳመጥኩት ዛሬ ነው። በነገራችን ላይ ይህ የመጀመሪያ ውይይት የተካሄደበት ስቴዲዮ ቀለሙ የዩቱብ ቻናሌ #ቋሚ ቀለም ነው። እኔ ቀለም ስለምውድ ዩቱብ ቻናሌን ሳዥጎረጉረው ባጅቼ አንድ ቀን ግን ወሰንኩኝ። የቤት ውስጥ ቀለሜም ወደ ዩቱብ ቻናሌ ቀለም ይጠጋል። ይህ ቀለም ወደ 15 ዓመት ይሆነዋል ምርጫዬ ውስጥ ከታደመ እንደማለት።
ቀለሙም ግጥሜ ነው። የተጠጋጋ ወደ ዓመት ለሚሆን ጊዜ ለቴስት፤ #ውሳኔየ ወደ 8 ወር አስቆጥሯል ለዩቱብ ቻናሌ ቋሚ ቀለም ሲሆን። ትናንት Eurovision Song Contest የ2025 በሲዊዝ ባዝል ከተማ ላይ ሥርዓቱ ሲከፈት ከነበሩት ሞደሬተሮች፤ አንዷ ሞደሬተርም የክብር ልብስ ምርጫዋ ይህ ቀለም ነበር። ቀለሜን ስላገኜሁም ይመስለኛል ጓጉቼ ያደመጥኩት ልበል ይሆን? ክፍል ሁለትንም ሁለት ጊዜ አዳመጥኩት።
ይህ ቃለ ምልልስ ከህወሃት እጮኝነት ተስፋ ጋር እንዳይቆራረጡ ጭራሽ አጀንዳቸው ያልሆነ ሚዲያወች አይቻለሁኝ። #ኮሽታን እዬለቀሙ የሚያስተጋቡ ልማርበትም፤ ልወቀውም የሚያሰኜው ይህ መግለጫ አጀንዳቸው አልነበረም። ምክንያት ትናንት ያወግዙት የነበረ ህወሃት መጋለጡ የኮሰኮሳቸው ይመስለኛል። ምኞታቸው እንደ ሰይጣን ያዩት የነበረው ህወሃት አቅሙ ጎልብቶ #ብጥበጣውን ቢቀጥል ተስፋችን በአንድም በሌላም ይሳካል ብለው ስለሚያምኑ ይመስለኛል።
በተለይ ለአማራ ህዝብ ከህወሃት የሚገኝ የተስፋ #ስንጣሬ የለም። የህወሃት ፖለቲካ ሲፈጠር ጀምሮ ለአማራ ህዝብ ቤርሙዳ ትርያንግል ነው። ተቋማቱ መሠረታቸው የአማራ ህዝብ ጥላቻ ነው። በዚህ ብዙ አጋር እንደ ችግኝ አፍልቶ የአማራ ህዝብ አሳሩን አይቷል። ይህ ይቀጥልልኝ መቼም ሰውነትን የሚገለብጥ ክስተት ይመስለኛል።
ህወሃትን መደገፍ፤ አቅምን ከእሱ ጋር ማዳበል ህወሃት ሆዬ ድጋሚ ዕድል አግኝተህ በሳለ #በቀልህ ጎራርደን የሚል ይለፍ ካልሆነ በስተቀር ህወሃት የአማራ ተስፋ ውስጥ ሊጠነሰስ አይገባም። ዕውነተኛ የጎንደር ፋኖወች ይህን "በሞኝ ክንድ ዘንዶ ይለካበታልን" እንዳትሞክሩት በትህትና ላሳስባችሁ እሻለሁኝ።
ህወሃት በለስ ቀንቶት በቀደመው ጦርነት ዳባትን፤ አንባ ጊዮርጊስን ኮሶዬን አልፎ ተሻግሮ ጎንደር ከተማን ቢያገኝ ኖር በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ በቀሉን ያወራርድበት ነበር። ዕውነተኛ የጎንደር ፋኖወች ልታስተውሉት የሚገባ በኽረ ጉዳይ በአብይዝም ዘመን የፈኩት የዩቱብ ሚዲያወች የተሰወረው መሻታቸው #ህወሃት ለምን መንበረ ሥልጣኑን ለቀቀ ነው። ተጠቃሚወች ናቸውና። ለዚህ አቅም ማዋጣት …………?????
ስለሆነም በቃለ ምልልሱ ፕሮ ህወሃት የሆኑ ዩቱበሮች ክፍትፍት ብሏቸዋል። ጭጋግ ለብሰዋል። ለብልጽግና እጅ መስጠት አድርገው አይተው ቅርጫ ላይ አውለውታል ቃለ ምልልሱን። 120 ሚሊዬን ህዝብ ልሰደድ ቢል #አቅም አለውን??? ቢችልስ የት ሊሰደድ ይችላል? ይህን በጥልቀት ማገናዘብ ይጠይቃል ሰው ሆኖ፤ ስለሰው አስባለሁ ከተባለ። አንድ አመት ቀርቶ አንድ ወር የሚሞላ መሃያ ለአንድ ቤተሰብ የመደበ ይኖር ይሆን? ህዝባችን መንፈሱ ባይባክን ምርጫዬ ነው። ህልሙ እና አቅሙ አይመጣጠንምና።
በዚህ አጋጣሚ በትህትና እማሳስበው በድጋሚ ህዝብ ጠቀም ተብለው የሚታሰቡ ሚዲያወች ከፋኖ #የአንድነት ዘመቻ ወደ የሃኪሞች ፍትሃዊ ጥያቄ አጀንዳቸውን የቀዬሩትም ቢሆኑ፤ ለሃኪሞችን ጥያቄ #ነፃነት ቢሰጡት ምርጫዬ ነው። ዕውነተኛው የሃኪሞች ጥያቄ ይጎሳቆላል፤ ሃኪሞችም አላስፈላጊ መስዋዕትነት እንዲከፍሉ ያደርጋል። ይህ ደግሞ ጭካኔ ነው።
አርቲስት ወ/ሮ አዜብ ወርቁ ውስጧን በቅንነት ስትገልጥ ባልተገባ የሚዲያ ወከባ ቅንነቷ ተከቶ እንደነበር አስታውሳለሁኝ። እኔ ምንም አልሰራሁበትም። ምክንያት የወገኖቻችን ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ ነፃነት #ስለሚጫን፤ እና መከፋት #ቧንቧ እንዳያገኝ #ስለሚያፍን። ቅንጣቱም ይሁን የገዘፈውም ጉዳይ ፖለቲካዊ ገጸባህሬ ከሰጠነው አደጋው የከፋ ይሆናል። #ስኬትም አይደለም። ወገኖቻችን ጥያቄ እያላቸው እንዲታመቁ እዬተበየነባቸው ነው። ስንቱን ጫና ያስተናግዱ ወገኖቻችን? በዚህ ቃለምልልስ ውስጥ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት እና ስኬቱን ወይንም ውድቀቱን ያመሳክራል። ፖለቲከኞች፤ የሚዲያ ባለቤቶች ተደጋጋሚ ግድፈት እንዳንፈጽም ይረዳል። ብልህ ……?
አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የተማረም ይሁን ያልተማረ፤ ሊቅም ይሁን ሊሂቅ አቅሙን፤ ክህሎቱን ኢትዮጵያ ላይ ኢንቤስት አደርጋለሁ ብሎ ሲወስን፤ ውጭ የሚኖር ኢትዮጵያዊም ወደ አገሬ ገብቼ የበኩሌን ድርሻ እወጣለሁ ብሎ ሲበይን ከሌላ ክስ ነክ ጉዳዮች ጋር #ማናከስ ሰዋዊም ተፈጥሯዊም አይደለም።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ካለፈው ድክመቱ እራሱን ሊያርም ይገባል። ለነፃነት እዬታገልክ ከአንተ ሲደርስ ገቢር ላይ ለመዋል ከቸገረህ፦ ህልምህ እና መባተልህ መዳረሻቸው የማይታወቅ ይሆናል። ወይ ገደል ወይንም አሜኬላ ሊያመርት ይችላል መባተልህ። የአቅም ብክነቱ የሰው ልጅ መስዋዕትነትን ሊቀንስ ይገባል። የወገንን የነፍስ ወከፍ ጥረት እና አቋም ላይም ተጽዕኖ ሊያሳድር አይገባም። ስለሆነም አቶ ጌታቸው እረዳ ከብልጽግና ጋር ለመሥራት የወሰኑበት ሁነት መብት ነው ብለን መቀበል ይገባል። ግልብ ውሳኔም አለመሆኑ ከቃለ ምልልሱ ፋክት ገብ ጭብጦች መረዳት ይቻላል። ቀላል ፖለቲከኛ አይደሉም አቶ ጌታቸው እረዳ።
ለዴሞክራሲ የሚተጋ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የወገኖቹን የውሳኔ ሂደት በቅንነት ሊያው ይገባል። ስደት ድሎት ሊኖርበት ይችላል። ግን አገር ደግሞ ከድሎት በላይ ቅዱሱ የሆነ የመንፈስ ምግብ አለው። ስለሆነም ስደትን የማያልሙ፤ ወይንም ስደትን በቃኝ ያሉ ወገኖች ጉዳይ በቅንነት ሊታይ ይገባል ብዬ አስባለሁኝ።
ለምሳሌ አባይ ሚዲያ ከገባ ጀምሮ ስንት አዲስ ትንታግ ወጣቶችን አፈራ? በትውፊቱ ልክ ምን ያህል ውስጡን አለመለመ ብሎ ስኬቱን መገምገም ይገባል። እራሱ የፕሮግራሞቹ መጠሪያ ይገርሙኛል። የሚስብ፤ የሚመስጥ አቅም አላቸው። (እንዝርት፤ ፈትል፤ መሰንቆ) ስለሆነም ቀና እርምጃወች ሊጣጣሉ አይገባም እንደማለት። ዊዝደምም ነው ብልህነትን መሰነቅ።
በሰባዕዊነት ዘርፍም እንደ አባይ ሚዲያ በአካል ተገኝቶ #ያጽናና፤ አይዟችሁ ያለ፤ መጠጊያ ላጡ ድምጽ የሆነ የግል ሚዲያ የለም። ይህ የተገኜው ኢትዮጵያ በምትዳደርበት ህገ - መንግሥት እና አመራር ሥር ሆኖ ለመኖር በመፍቀዱ ነው። ዴሞክራሲ እና ፈተናውን ማስታረቅ አንድ የሥልጣኔ #አህጉር ይመስለኛል። ስለሆነም መሰደድ እየቻሉ ያባካንኩትን ጊዜ ሆነ የበደልኩትን ህዝብ እራሴን ወቅሼ፤ በተሰጠኝ ድጋሚ ዕድል ልካስ ያለን ወገን #እንቶኔን ይመስላል ብሎ መፈረጅ የፖለቲካ ጀማሪነት ማጣፈጫ ነው - ለእኔ።
በዚህ ክፍል ሁለትም ይሁን ክፍል አንድ ውይይት የህወሃትን ሆድ ዕቃ ከምናውቀው በላይ አውቀን እራሳችን እንቀርጽበት ዘንድ ብዙ ቁምነገሮች ተገኝቶበታል። ሰው ነን እና እኛም በየፌርማታው ስለምንገድፍ። በህወሃት የፖለቲካ ሂደት የሰው ንግድ፤ የሃብት ሽሚያ፤ ገፋዊ የትውልድ ማገዶነት እና ቀጣይ ዕጣው፤ ኢትዮጵያዊነት፤ ወዘተ ብዙ የዕውነት ዘለላወች ቃለ ምልልሱ ለቀጣዩ ትውልድ የፖለቲካ ግንዛቤ መረጃ ይሰጣል።
ሁለቱም ክፍል በመረጃ የታጨቀ ነው። መረጃ የውጪ ኃይል ትንተናም ፕሮፖጋንዲስትም አያስፈልገውም። ባለሙያም ተቋምም አለው።
/// መረጃ አቅም ነው።
///መረጃ ሚስጢር ነው።
///መረጃ ማሸነፍ ነው።
/// የጦርነት ድል ሚስጢር የመረጃ አቅም በመቅደም ይወስነዋል።
የአስተዳደር፤ የአቅም ግንባታ እና የተስፋ ትልም የመረጃ መዋለ አቅም የአስተዳደር ክህሎትን ይጠይቃል፤ ጉዞውንም ይፈውሳል። መረጃ በፍፁም ሁኔታ #ፕሮፖጋንዳ ሊሆን አይችልም። በሌላ በኩል መረጃ ፖለቲካዊ ተንታኝም አያስፈልገውም። ያገኜኽውን መረጃ እንዴት ለቀጣይ ተግባር ቆጥቤ ጥቅም ላይ ላውለው፤ ከዚህ የመረጃ ፍሰት ለእኔ የትግል ጉዞ የቱ ጠቃሚ መስመሬ ሊሆን ይችላል ብሎ የአገኙትን መረጃ ብልህነትን መመገብ ያስፈልጋል።
አንድ ምሳሌ ላንሳ ዘመናይ ጦርነት እና የድል መሻት በባህላዊ መንገድ መሞከር ሽንፈት እንደሚያስታጥቅ፤ በዚህ መንገድ መጓዝ መራራ መሆኑን አጠይቋል ውይይቱ። ይህ ትጥቅ ትግል ላይ ላሉም፤ ወደፊትም ለሚያስቡ የሚረዳ ከልምድ የተገኜ ክህሎት ይመስለኛል። መማር ለፈቀደ የስትራቴጂ እና የታክቲክ ሂደት ከዘመን ሥልጣኔ ጋር እንደምን በልቀት ሊታይ ይገባል የሚለውን መንገድ ከፍቷል ባይ ነኝ። የተረጋጋ መንፈስ ላለው ፖለቲከኛ፤ ለስኩን የሚዲያ ሰብዕና።
#ቁልፍ የመረጃ ቋቶች።
1) "ህወሃት ሃሳብ #ያለቀበት መሆኑ።"
2) ህወሃት አሻግሮ እና አሻቅቦ የሚያያቸው ያድኑኛል ብሎ የሚያስባቸው የትጥቅ ትግሎች #ጥገኛ ስለመሆኑ።
3) 90 ኪሎሜትር እርቀት ላይ አክተሮች ተቀምጠው በዳባት ግንባር፤ ሸሽታችኋል ተብለው በግፍ የተረሸኑ የትግራይ ወጣቶች። መኖራቸው እንደ ሰው ሊሰቀጥጥ ይገባል። ነገም ይህ አለመደገሙ እርግጠኛ የሚያደርግ የፖለቲካ አዬር አለን ትግራይ ላይ????
4) "መኖራችን አኑሩት" የሚለው የትግራይ ሰው ጥያቄ፤ በቃን! በእኛ ማገዶነት ኢትዮጵያ ማዳን ፍልስፍናን አንሻም። የሚል ድምጽ መኖሩ ማድመጥ ታላቅ የምሥራች ነው ለእኔ። ቸር ዜና።
5) ስምምነቱ ቀድሞ ተካሂዶ ቢሆን ሊያተርፍ የሚችለውን የቤተሰብ አባል አንክሮዊ ፀፀትን የሰነቀ ስለመሆኑ። አክተሮች ተርፈው አንጋቾች፦ የፕሮሚ ጠባቂወች ወጣትነታቸው #አፈር መሆኑ? ጎምዛዛ ሃቅ ነው። ወደፊትስ??? ይህ አይደገምን???
6) ማዕከላዊው የህወኃት መሪ ቁንጮ ብቻ የሚያውቁት ሚስጢር ኬኒያ ላይ ለሚዲያ ታድሎ የሰላም ስኬት መስተጓጎሉ፤ ሚስጢርና የመሪነት አቅምን በአስተውሎት እንመረምረው ዘንድ ነግሮናል። አድካሚው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዕለታቱ ቀራንዮ መሆኑን ያገናዝባል። አቋም የለሽ መሪወች እና የኢትዮጵያ ፍዳን ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል።
7) የተከበሩ አንባሳደር ማይክ ሃመር ከማዕከላዊ መንግሥት ውክል ተወያዮች ነጥለው ለሁለቱ የህወሃት ተደራዳሪወች ለጄኒራል ፃድቃን እና ለአቶ ጌታቸው ያነጋገሩበት ሁነት እንደነበር አዳመጥን። የዕለቱ አወያይ #ምን ነበር ብሎ ሳይጠይቅ ዘሎታል። እጅግ አዝናለሁኝ።
8) የአብይዝም መንግሥት ከደቡብ አፍሪካው በፊት እያተደራደረ ግን የካደበት ሁነት ነበር ለዛውም በፓርላማ። ምን ያህል አዘናጊ ፖለቲካ እንደሆነ እሰቡት። በአንፃሩ አሁንም ከፋኖ ጋር መሰሉ እዬተከወነ ሊሆን ይችላል ብሎ ለማሰብ ፍንጭ ሰጪ ነው። ተደራደሩ የሚባሉት ስለሚወገዙ። በጥልቀት ፋኖን እንመራለን የሚሉ ሁሉ ይህን ግንዛቤ ሊሰጡት ይገባል። ከጸጸት በፊት። ከመስዋትነት በፊት። አቅምን ከማባከን በፊት።
9) የህወሃት ፋንታዚ #ፕላን የለሽ መሆኑ። ይህ እጅግ አስደሳች መረጃ ነው። ቀለም የለሽ እስክርቢቶ። ከህወሃት ጋር ፍቅር ለያዛቸው፤ አብረው ለመሥራት ዱብ ዱብ ለሚሉትም ሆነ በማገርነት ለተሰለፋት የማስጠንቀቂያ ደወል ነው።
10) የአብይዝም ሥርዓትን አቃሎ የማዬት ጉዳዬ። "ሦስት ወር ቀርቶታል፤ ትርምስ ላይ ነው ያለው" ወዘተ
11) አቶ ጌታቸው ረዳ ቢመርም፤ ቢጎመዝዝም ባለው ሥርዓት በህግ ሥር ሆኖ መሻትን ማሳካት የወሰኑበት አግባብ።
12) የቅድስት ተዋህዶ ልጆች እና ኢትዮጵያዊነት በነበሩበት የዓድዋ ቀጠና እጅግ መሳጭ እና ሁልአቀፍ ዕይታ ሊመጣ ይገባል የሚል አዲስ ጎዳና ቀያሽነቱ። እምናዬው ሚዲያ ላይ የኢትዮጵያኒዝም ሰንደቅ ዓላማ አይደለም። የህወሃት ዓርማ እንጂ። ዲያስፖራ ላይ ያለው የህወሃት ደጋፊም ይህን ሃቅ ማስታረቅ እንዳለበት ያመሳጥራል። ለህዝብ ሲታገሉ የህዝብን ዕውነተኛ ፍላጎት አጥርቶ መነሳት ይገባል።
13) ከትግራይ ክልል ውጪ ስለሚኖሩ የትግራይ ልጆች ጉዳዬ በአጀንዳነት ከህወሃት መሻት ጋር እንደምን ሊታይ እንደሚገባ የቀረበው ሃሳብም በሳል ሆኖ አግኝቸዋለሁኝ። ጉዳታቸውን ሆነ ትፍስህታቸውን በውስጥነት የማስተናገድ አቅም መፍጠር እንደሚያስፈልግ። ይህ ለአማራ ፋኖ የትግል አቅጣጫም ጠቃሚ ይመስለኛል።
14) ለስምምነት እንደምን ጉዟቸው እንደተደራጄም ከዚህ ቀደም የተከበሩ የማይክ ሃመር የኃላፊነት ዝውውር ጋር ኢትዮ ፎረም ሐተታ ሰርቶበት የነበረ ቢሆንም የጉዞ ቤተኛ በአንደበታቸው ሲገልጡት የሚሰጠው የስሜት ሂደት ቃናው የተለዬ ነው።
#በጠያቂው ያልተነሱ እኔ ያልገቡኝ ……?
1) "የትግራይ ዜጋ።" ደነገጥኩኝ ቃሉን ሥሰማ። በኋላ አሻሽለው የትግራይ ሰው በሚል ገርተውታል። የሆነ ሆኖ ስሜቱ ለብም፤ በረድም፤ ሞቅም እያደረጉ በቴርሞሜትር ይለካ ባልልም፤ ይህን የህሊና ቀለም እንደ አልባሌ ላየው አልፈቀድኩም።
2) ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ በወንጀል የሚጠየቁ የህወሃት መሪ አካላት ከፈለጉ ከአገር እንዲወጡ የፈቀዱበት አግባብ። ይህም አስደንግጦኛል። ይቅርታ ሳይጠይቁ። ንስኃ ሳይገቡ። ሳይናዘዙ። የበደሉትን ወገን ሳይክሱ።
የፈፀሙትን በደል ዝርዝር መረጃ ሳይሰጡ እንዴት? ለምን? የአገር መሪነት ማለት ቸለልተኝነት ማለት አይደለም። ያ የመከራ ዘመን የጋራ ታሪክ ነው። ግን በአግባቡ በፈፃሚው አንደበት ሊተነተን፤ ሊሰነድም ይገባል። ሰው እና አገር የተቃጠሉበት ሂደት እንዲህ እንደ አልባሌ??? ከቂም፤ ከጥላቻ፤ ከበቀል ወጥቶ ፋክቱ ግን ሊገለጥ የሚችልበት መንገድ ተስቶ እንዲዳፈን ይለፍ መስጠት ለምን ተፈለገ??? የኢትዮጵያ ወጣቶች በዬዘመኑ የሚከፍሉት ግብር ከንቱ ሊሆን አይገባም። ለትምህርት፤ ለማረሚያ ሊውል ይገባል።
3) "ትግራይ ትስዕር" ይህ ሞቶ ህወሃት ጦርነቱን የመራበት ነበር። ጠያቂው ይህን ሲያቀርብ አቶ ጌታቸው ረዳ መልስ የሰጡበት አግባብ ግን ፈጽሞ አልገባኝም። "ኢትዮጵያ ትቅደም ማለት ኬንያን ትቅደም፤ ሱዳን ይዳከም ማለት እንዳልሆነ" የተነፃጸረበት ሁነት ለእኔ ኦድ ነው። በውስጣቸው ያለው የመሻት አቅጣጫ በሚገባ ሊብራራ ይገባ ነበር። ትግራይ እኮ ጥንት አንድ ክፍለ አገር፤ ዛሬ ክልል ናት። እና ጠያቂው ምንም ሳይል እንደ ተከደነ ቃለምልልሱ ተጠናቋል። መጠዬቅ ማድመጥን ይጠይቃል።
ክወና።
የገረመኝ የቃለ ምልልሱ መቋጫ ምዕራፍ ሦስትን ያጨ ነበር። ትክክለኛው ቦታ ላይ ምዕራፍ ሁለት የተጠናቀቀ አይመስለኝም። በሌላ አገላለጽ ማሰሪያ አንቀጽ የሌለው ዐረፍተ ነገር መስሎ ነው የተጠናቀቀው ቃለ ምልልሱ።
የአብይዝም መንግሥት በመረጃው የመጠቀም አቅሙን አላውቅም። የአብይዝምን ሥርዓት በሃሳብ በሚሞግቱ፦ ወይንም በትጥቅ የሚፈትኑ ኃይሎችም ከዚህ ቃለምልልስ በኋላ ጎዳናቸውን አጥርቶ ለመቀዬስ ምን ያህል እንደሚጠቀሙበት አላውቅም። እኔ በግሌ የብዕር ሞጋች ነኝ። ብዙ በጣም ብዙ ረቂቅ መረጃወችን አግኝቸበታለሁኝ። ለዚህም ነው ሁለቱንም ክፍል ደግሜ ያዳመጥኩት። የፃፍኩበትም።
አቶ ጌታቸው ረዳ አንደበተ ርትዑ ናቸው፤ ፖለቲከኛም ናቸው። ተጽዕኖ ፈጣሪም ናቸው። እላፊም ይናገራሉ። በእላፊ ንግር ሁለት ሊቃናትም ኢትዮጵያ አሏት። አቶ ጌታቸው ሦስተኛ ናቸው። አቶ ጌታቸው ረዳን በህወሃት ሥልጣን ላይ እያለ አንድ ጊዜ ሞግቻቸዋለሁኝ። ከዛ በተረፈ እንደዛሬ አተኩሬ አዳምጬ አስተያዬት አልፃፍኩም።
ምክንያቴ የትውልድ መንፈስ ረፍት ያስፈልገዋል የሚል የውስጥ መሻት ስለአለኝም ነው። የትውልድ መስዋዕትነት መቀነስ አለበት የሚል የጸና አቋም አለኝ። ኢትዮጵያ ትርታዋን ለማስቀጠል ስክነት፤ እርጋታ፤ አስተውሎት፤ መደማመጥ፤ እራስን መገሰጽ፤ ለራስም ቡርሽ ወይንም ላፒስ መፍቀድ፤ ክህሎት እና የበዛ ቅንነት በገፍ ሊቀርብላት ይገባል የሚልም ቋሚ እምነት ስለአለኝ ነው።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፦ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
14/05/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት ጋራጅ የለውም።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ