የጤና ባለሙያወች #የራሳቸው #ጉዳይ ነው በህብረት ያስነሳቸው። ሌላ ገፊ ኃይል ያላቸው አይመስለኝም።

 

የጤና ባለሙያወች #የራሳቸው #ጉዳይ ነው በህብረት ያስነሳቸው። ሌላ ገፊ ኃይል ያላቸው አይመስለኝም።
 
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"
May be an image of 1 person and text that says 'k ann annydebol BBc Focus on Africa ቃለ መጠይቅ ስለ ኢትዮጲያ የጤና ባለሙያዎች የኑሮ ሁኔታ ለአለም አቀፍ ሚድያ ድምፃ ድምፃችንን ያሰማችው Anatomic Pathologist ዶ/ር ማህሌት ጉሽ ገብረወልድ በፀጥታ ሀይሎች ታፍና ተወስዳለች፡ ቤተሰቦቻ ጭንቅ ላይ ናቸው። የኛን ድምፅ ትፈልጋለች! ሀሳብን በነፃነት የመናገር ሰብአዊ መብትን ማፈን አምባገነንት ነው። ኢሰማኮ ዝምታውን ሊሰብር ይገባል! ፍትህ ለስራ ባልደረቦቻችን።'May be an image of 1 person and hospitalMay be an image of 1 person, smiling and hospital 
 
 
May be an image of 4 people and hospital
በዘመነ አብይዝም የ፯ ዓመታት የአገዛዝ ሂደት ኢትዮጵያ ውስጥ ያልታዬ የፈተና፤ ያልተሞከረ የቀውስ፤ ያልተመለከትነው የሴራ ድንኳን የለም። 100 ቀናት ሳይሞላ ገና በልጅነት ዕድሜው ከሰኔ 16 ጀመሮ በመላ ኢትዮጵያ ያልታዬ የፈተና ቡፌ የለም። ደቡብ ምን ያህል ህዝብ ነው የተፈናቀለው። የገዴወ፤ የጋሞ ህዝብ ምን ዋጋ ከፈለ። ቡራዩ ለገዳዲ አዲስ አበባ ፦ ብቻ ፈተና ኢትዮጵያን ፈተናት።
 
ቀውሱ በመንግሥትም ታቅዶ፤ መንግሥት ውስጥ ባሉትም ተመስጥሮ እንዲሁም በፊት በምን አቅሙ እል የነበረው #ህወሃት መራሽ ሴራም በሚችለው ሁሉ በቀውስ አምራችነት ላይ ተሳትፎ እንደ ነበር ዛሬ ባለው የህውሃት የትርምስ ማሳቸው ለመገንዘብ ችያለሁኝ። ከዚህ ጋር ተያይዞም የህወሃት ሆነ የኢህዴግ #ተስፈኞችም ተመሳሳይ ትጋት እንደ ነበራቸው ቢዘገይም ምልክቶቹ ዛሬ ይፋ ናቸው። በምን መሥፈርት ህወሃት እንደሚናፍቅ ባይገባኝም። 
 
የሆነ ሆኖ በህወሃት እና በብልጽግና #ልግዛህ እና #አልገዛም ጦርነት፤ በብልጽግና እና በአማራ ትጥቅ ፍቱ፤ አንፈታም የነፍጥ ተጋድሎ፤ በኦነግ የጫካው እና በብልጽግና፤ በኦነግ መንፈስ እና በአማራ ህዝብ የደረሰው ሰቆቃ ውስጥ የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያወች #ቤተ - ሳይለንት ማጆሪቲው ውስጥ ነበሩ። እርግጥ መጀመሪያ ላይ ከጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ጋር በነበራቸው የጋራ ቆይታ ጥያቄያቸውን ከሞላ ጎደል ማንሳታቸውን አስታውሳለሁ። ይህም #በራሳቸው #ጉዳይ ላይ ብቻ ነበር።
 
የኢትዮጵያ የህክምና ባለሙያወች በየትኛውም ሁኔታ፤ በማናቸውም ጊዜ የሙያቸውን ግዴታ ከመወጣት ውጭ ጉልህ የሆነ የፖለቲካ ተሳትፎ አልነበራቸውም። አልነበሩም። እነሱ ንግግራቸው ውይይታቸው ከሙያቸው ጋር ብቻ ጋር ነበር። እራሱ በቅድስት ተዋህዶ የነነዌ የሱባኤ ወቅት እንኳን ቀዝቃዛ ነበሩ። ይህ ማለት ሙያቸውን ከየትኛውም ንቅናቄ ጋር ለማዛመድ #ፈቃደኛ #አልነበሩም ማለት ነው።
እና ታዲያ "ዛሬ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ" ለምን አስፈለገ ነው የጹሁፌ ጭብጥ። ኃይል ለሊሂቃን????
 
የሆነ ሆኖ ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላ ዓለም ጭራሽ በኮረና ጊዜ በምን ሁኔታ እንዳሳለፋ የሚታወቅ ነው። #ትንፋሽም #ፈውስም ናቸውና። አንድ ጣሊያናዊ ዶክተር ይህ ሲያልፍ #ትረሱናላችሁ ብለው እኔ አውድዮ ሠርቸበታለሁኝ። በኢትዮጵያ ባለው የፖለቲካ ሙቀት ባለሙያወቹ የቀጥታም፤ የተዘዋዋሪም ተሳትፎ አልነበራቸውም።
 
ኢትዮጵያ በአንድም በሌላም በዕንባ ውስጥ ነው የባጀችው። የመጨረሻው የዕውቀት ደረጃ የሚገኙት የጤና ባለሙያወች፤ ኢትዮጵያ በሊቃውንት የምትመራ መሆኑ እዬታወቀ ይህ የሙያ ዘርፍ ግን ሳይለንት ማጆሪቲው ውስጥ ቤተኛ ነበር። ስለሆነም ከምንም የፖለቲካ ጉዳይ ጋር ተለጣፊ ሊሆን አይገባም ንቅናቄው። 
 
ይህን ዕንቁ ሃቅ ይዘን ዛሬ ያለውን ብሄራዊ የሃኪሞች ንቅናቄ ስንመዝነው #በራስ #ችግር #ገፊነት እንጂ የማንም፤ የምንም ፖለቲካዊ ፍላጎት ንቅናቄው #አንጋች እንዳልሆነ እንረዳለን። ስለሆነም የአብይዝም መንግሥት አቅሙን ያዋለበት መሥመር #ብክነት ነው። ከዕውነት፤ ከፋክት፤ ከብልህነት፤ ከዊዝደም ጋር የተራራቀም ነው።
 
መንግሥት የደህንነት ግራ ቀኝ ተቋማት አሉት። ቀደም ባሉት ከፋኝ ንቅናቄወች፤ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፤ በገፍ የተከወነው የአገር ውስጥ የመፈናቀል አሳዛኝ ተውኔት፤ የንጹኃን ግድያ፤ የንጹኃን እገታ፤ ህፃናትን ጨምሮ የሴት ልጆች ተገዶ #መደፈር፤ የገፍ እስር እና ወከባ፤ የዜጎች ተገዶ #መሰወር፤ የንጹኃን የግፍ ግድያ እንደ ሰው የሚፈትን ቢሆንም የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያወች ኮሽ አይል ነበሩ።
 
እና ታዲያ ዛሬ በምን ሂሳብ፤ በየትኛው ቀመር በአሸባሪነት፤ በሥልጣን ነቅናቂነት፤ በመንግሥት ቅየራ እና ወዘተ ፋንታዚ መንፈስ ጋር ንጹሁ የሃኪሞች የመኖር ዋስትና ጥያቄ ሊያያዝ ይችላል? ወኪላቸው ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ ሥም ጠርተው ሁሉ ፖለቲከኞችን "ተውን፤ እጃችሁን ከእኛ አንሱልን" ብለው ጠይቀዋል።
 
እኔም ከቀን አንድ ጀምሮ ይህን ንቅናቄ ታከው አቅም ሻሞ ላይ ትጋት እንዳይኖር አብክሬ አስገንዝቤያለሁኝ። ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያ የህክምና ባለሙያወች ማህበር ነፃነቱን እንዳይሻሙ፤ ነፃነቱን እንዲሰጡት፤ ንጹሁ ፍትኃዊ ጥያቄ ለጥቃት እንዳይጋለጥ አስገንዝቤያለሁኝ።
በጣም እየከረረ ከመጣ አደጋው አስጨናቂ ነው። ይህ ንቅናቄ ከሳይለንት ማጆሪቲው ቤተኝነቱን ጥሎ የወጣ ስለሆነ የጨመተው የማህበረሰብ ክፍል ከታከለበት የአብይዝምን የተስፋ ጉዞ ሊገታ ይችላል። ሌላም ያልተጠበቀ ክስተት ተፈጥሮ ብዙ ነገር ሊመሰቃቀል ይችላል። ችግሩንም ማስተዳደር ከማይቻልበት ሁኔታ ሊደረስ ይችላል።
 
ለመፍትሄ መታበይ አይስፈልግም። መንግሥት የህዝብ ሎሌ ነው። ይህን ደረጃውን መርሳት የለበትም። ነገ ከቀናውም ምርጫ ይኖራል። ድምጽ የሰጠን ቅን ወገን ቁራሽ እንጀራ ከነሳኽው አድብቶ ግን ተደራጅቶ የሚጠብቅ ኃይል ባለ ሙሉ ሲሳይ ባለቤት ሊሆን ይችላል። የማይጠበቅ የምርጫ ውጤት ሊመጣ ይችላል። በሁሉም ዘርፍ እርካታም መረጋጋት የለምና።
 
ህዝባችን በድህነት ሰላሙን ቢያገኝ ምንኛ በታደለ ነበር። ከአዲስ አበባ 100 ኪሎ ሜትር መጓዝ የማይቻልበት ሁነት ነው ያለው። ለትንሹም ለትልቁም፤ ለአጭሩም ለረጅሙም ጉዞ አውሮፕላን ተመራጭ ነው። ለዛ አቅሙ የሌለው ቤተ ዘመዳሙ ተቆራርጦ መቅረት ነው። ጉዞ በአፈና እና የሰው ሽያጭ ተኮር ሆኗል። ይህ ሁሉ መዛባት የጠቅላይ ሚኒስተሩ ወንበር ተቀምጦ የሚሠራበት በመጥፋቱ ነው። ብዙ ቅብ ብልጭ ድርግም የሚሉ አርቲፊሻል ትዕይንቶች ናቸው። ይህ ደግሞ ለትውልድ ፋይዳው እንብዛም ነው።
 
ሁሉም ያለውን ቅንነት እና ቀናነት አዋጥቶ የህዝብ መረጋጋት፤ በልቶ ማደር፤ መጠለያ፤ ከፈን፤ ንፁህ ውሃ የተሟላ ማህበራዊ ሰላም እና አገልግሎት ወዘተ ህዝባችን የሚገኝበትን ምህንድስና እራሱን አሸንፎ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል። የአብይዝም ይለፍ ቢገኝ። ኢትዮጵያ በቃት!
 
ተጋሩ የሆነን ባለሙያ ከህወሃት መንፈስ ጋር፤ ኦሮሞ የሆነን ከኦነግ መንፈስ ጋር አማራ የሆነን ከፋኖ መንፈስ ጋር አገናኝቶ ማሰብ በራሱ ትክክል አይደለም። ሙሉ ፯ ዓመት ኢትዮጵያ ለአንዲት ቀን ሰላም አልነበራትም። ሞት ያልሰማንበት፤ ሰበር ዜና ያላስተናገድንበት ማዕልት አልነበረም። የሃኪሞች መንፈስ በዚህ ሁሉ የቀውስ ሁነት በዝምታ ውስጥ ጨምቶ ነው የነበረው።
 
ይህን የሃኪሞች ንቅናቄ የመፍትሄ ጎዳና ማድረግም ይቻላል። ንጹሁን የኢትዮጵያ የሃኪሞች ጥያቄ ለጥቃት፤ ለበቀል መጠቀም መንግሥታዊ ትዕይንት ሊሆን አይገባም። ሙያተኞችን መንግሥት #ሊያቄማቸውም አይገባም። ልጅ ራበኝ ሲል ምግብ እንጂ ለካቴና፤ ለዱላ ሊዳረግ አይገባም። ምን ዓይነት ድፍረት ይሆን በፈውስ ላይ፤ በአዳኝ ላይ የዱላ ክንድ የሚሰነዝር። ድፍረትም ነው። ሥረዓተ አልበኝነትም ነው። የደሙ ባለሙያወችን ሳይ ሰቀጠጠኝ።
 
እርግጥ ነው በአደባባይ የተገደሉ ዘመን ለመተካት ብዙ ዋጋ መክፈል ያለበት ሃኪሞችን በቅርቡ ኢትዮጵያ በተከታታይ አጥታለች። ማለት ከሞት መደብደቡ ሲመዘን። 
 
#ማሸነፍ #በመሸነፍ ውስጥም ይገኛል። ጥያቄያቸው የመግሥት ይቀየርልን፤ የሽግግር መንግሥት እንፈልጋለን አይደለም። መኖርን ለማኖር የምንችልበት ሁነት ይመቻች ነው። #መፈጠር #ለመኖር ነው። መኖር #ኮንፓስ ነው። መኖር #ካንፓስም ነው። መንግሥትም የሚመረጠው መኖርን ለማኖር ነው። ሙያተኞች የመረጡትን መንግሥት ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ጠይቀዋል።
 
የመረጡትን መንግሥት ኃላፊነት እና ተጠያቂነትህን አልተወጣህም ስለሆነም ሌላ መምረጥ አለብን ብለው የመጠየቅ ሙሉ መብት አላቸው። ሥልጣኑ የህዝብ ከሆነ። አብይዝም የሚፈራው ነገር እንዳይፈጠር ከተቃዋሚወች በብዙ ልቆ እና ተሽሎ መገኜት አለበት። #ከአነጋገሩ ጀምሮ። መንግሥት ግዑዝ ሊሆን አይገባም። የትኛውም የኮንስትራክሽን ዓይነት ከህዝብ የመኖር ዋስትና በላይ ሊሆን አይገባም። ለአንድ ግንባታ የሚሰጠው አትኩሮት ለአንድ ሰው ህይወት መቀጠል አይውልም በአብይዝም ትልም ውስጥ። የየክልሉ መስተዳድሮች ሥራ ሳይሆን በጉብኝት ነው ጊዜያቸው የሚባክነው። 
 
#ሰው #ይቅደም! ህንፃ ሰው ዓልባ ወና ነው።
 
ተፈጥሯይነት ይቅደም! ተፈጥሮ የሰው ልጅ ሐሤቱን ካልሰጠው ምን ያደርግለታል። 
 
ሁሉም ነገር ለሰው ልጅ የመኖር ዋስትና ይሁን። ቅድሚያ ለሰው ልጆች #የዳቦ ጥያቄ። 
 
#የተደበደቡ የጤና ባለሙያወች ፎቶ ደርሶኛል። መለጠፋን አልፈቀድኩትም። አክሰሱ ላላቸው ታዳጊ ወጣቶች አብነት የለውም። ሥነ ልቦናቸውም ይጎዳብኛል። የአብይዝም ሥርዓት ድፍረቱ ግን ገርሞኛል። የመረጠን እጅ መስበር ምን ይባላል? 
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እንዴት አረፈዳችሁ ክብሮቼ።
ኑሩልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
21/05/2025
መኖራችን ኮንፓሳችን!
መኖራችን ካንፓሳችን!
ዕውነት ጋራጅ አያስፈልገውም።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?