#የዳነ #ሃሳብ #ቀድሞ ራስን #ያድናል፤ #ትውልድን #ያድናል፤ #አገር #ያድናል #ቅዱስ #ነውና!

 

#የዳነ ~ሃሳብ ለእኔ ሰማዕትም ነው።
#የዳነ ~ ሃሳብ ብዙ ይፈተናል።
 
#የዳነ ~ ሃሳብ በወጀብ፤ በብዙ ጦሮ፤ በብዙ ማዕበል ይፈተናል። ግን ህውከቱን ጸጥ አድርጎ ብስጩውን አየር ሳይቀር #ፈውሶ ያሸንፋል። 
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
ምዕራፍ ፲፯
 
 May be an image of one or more people, braids and people smiling
 
የሥርጉትሻ ቤተ - ቅንነት ውድ ቤተኞች እንደምን አላችሁልኝ? እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ በጣም ደህ ነኝ። ዕለተ ሰንበትን #ከዳነ ~ ሃሳብ ፍልስፍናዬ ጋር እንወያይ ዘንድ ፈቀድሁኝ። የዳነ ~ ሃሳብ ጋር ስሆን የሚኖረኝ የማሰብ አቅም እና የጤናዬ ሁኔታ፤ ከብስጩ ሃሳብ ጋር ስቆይ የሚገጥመኝ የጤና እክልን ለረጅም ጊዜ በህይወቴ መረመርኩት። 
 
እርግጥ ነው የሚያበሳጨኝ ነገር እኔ ዕውነት ሲንገላታ ነው፤ መርኽ እክል ሲገጥመው። ዕውነትም መርኽም እንደ አቅርቦታችን ስለሚለያይ እኔ መርህ ዕውነት በምላቸው ጥሰት ተፈጽሟል ብዬ ሳስብ ነው በሰጨኝ የሚመጣው። ሙሉ ዕድሜ ላይ እንኳን ስክነቱ በራሱ ይቆጣጠራል። የተፈጥሮ ጸጥታ አስከባሪ ስለሚሆን አይቸግርም። እኔ አብዛኛውን ጊዜየን እማሳልፈው በአገራዊ ጉዳይ ነው። በመፃፍ፤ ሌሎችን በጥሞና በማድመጥ እና በትጋትም በመሞገት። 
 
እራሱን #አንቱ ያለ፤ ወይንም በሌላው አንቱ የተባለ ዕውነት በሆነ አቅም ላይ ምስክርነት ለመስጠት ይሳነዋል። ቆጥቋጣ ነው። ሌላውን ሲያስተልቅ እሱን የሚያሳንስ ይመስለዋል። ደፍሮም አስተያዬት በሚታወቅ ሥሙ ለመስጠትም ራድ የሚይዘው ይመስለኛል። በሌላ በኩል ከክብሩ ዝቅ ያለም ይመስለዋል። በእኔ ቤት ይህ የለም። ላይክም፤ ሸርም የሌላውን ለማድረግ ገደብ አልባ ነኝ። ለሰው ስማገድም ቅድመ ሁኔታ የለኝም። መመስከር ላለብኝ ዕውነት ይሁን ሰብዕና #በልግሥና ነው እምከውነው።
 
ዛሬ …… ዛሬ ልጓሙ ያዝ የተደረገው ስንት ዋጋ የተከፈለለት ሰብዕና በተለዋዋጩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምክንያት በተማገድኩለት ልክ ስለማላገኘው የአቅም ፍሰቱን በሥርዓት ማስተዳደርን መረጥኩኝ። ደግሞም ይገባል። ከዚህም በላይ የተመሰከረላቸው ሰብዕናወች አመሰግናለሁን ደፍረውት አያውቁም። አያደምጡም። ይህ ብቻ አይደለም ያ ሁሉ ሺህ ህዝብ እየተከተላቸው የሚያቀርቡት መንፈስ ልሙጥ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። 
 
እነሱ ዕውቅና ሲሰጡ የሌላው ሥም ይገናል ብለው ስለሚያስቡ በጣም ቁጥቦች ናቸው። ይህ ግን ዝበት ያለበት ምልከታ ነው። "በማን ላይ ቁመሽ እግዜሩን ታሚያለሽ" ነው። አልፈው ተርፈው ልዕልት ኢትዮጵያን የሚዳፈሩበት ልክ የእንብርክክ ያስኬዳል። ይሉኝታ የላቸውም።
የሆነ ሆኖ #በማረተ ይሁን #በዛገ ሃሳብ ዙሪያ የሚከቡት ጥውልግ የሃሳብ አዟሪቶች ናቸው። በደጋጎች ሃሳብ ዙሪያ ደግሞ በጣት የሚቆጠሩ መልካም ሰወች ናቸው ሊኖሩ የሚችሉት። 
 
በጣም የናቀ፤ እጅግም ያጣጣለ፤ #የዘለፈ ሃሳብ ብዙ አድናቂ ያገኛል። ብልሹ ሃሳብ የበለጠ የመበከል አቅም አለውና። ለምሳሌ አንድ ንጹህ እራፊን ውሃ ላይ ንከሩት፤ እዛው ላይ በመቀስ ቆርጣችሁ ከአጎረፈ ውሃ ንከሩት። የበለጠ ጎልቶ የሚወጣው በአጎረፈው ውሃ ላይ የተነከረው እራፊ ነው። እኔ ይህን ሞክሬዋለሁኝ።
 
#ከእኛ ባለፈም ………
 
ይህ ጉዳይ ግን የእኛ ብቻ ችግር አይደለም። ከእኛም ባለፈ ነው፤ የአህጉራት፤ የግሎባል ችግርም ነው። የእኛ ብቻ ችግር እየመሰለን እንበሳጫለን እንጂ አጠቃላይ የዓለምን ሁኔታ ስትከታተሉት ድውይ ሃሳብ ለእኛ ብቻ እንደመርገምት የተሰጠን አይደለም። ክፋ ሃሳብም አብሮን አልተፈጠረም። የትም ብንወለድ። ብራዚል ይሁን ኒዊዝላንድ ላይ ተጸንሰን ብንፈጠርም ክፋ ሃሳብ አብሮን ለማደግ የለማ ሁኔታ አለው በየትኛውም አገር ላይ። 
 
ምክንያቱም የሰው ልጅ ሁሉ ይህችን ዓለም ስንቀላቀል የሚቀበለን ክፋ ሃሳብን መቋቋም የሚችል ተቋም የለም። ለዚህ ነው እኔ ዓለማችን አንገት የሌለው ሰው ትመስለኛለች የምለው። ለምን? ስንፈጠር የዳነ ~ መንፈስ ይዘን #ጸድቀንም ነው የምንወለድ። ጸድቀን የሚለው ሃሳብ አይክበዳችሁ። ዕውነት ስለሆነ። ግን ነገር ግን ያን ጸድቆ የተፈጠረን ድኖ የተወለደን ~ መንፈስ የሚያስቀጥል ተቋም ዓለማችን የላትም። ስለሆነም በቅይጡ፤ በተዥጎረጎረው፤ በሸካራው፤ በጓጎለው፤ በአጎፈረው ብቻ ሳይሆን በአጎረፈውም ዕሳቤ ውቅያኖስ ውስጥ አቀባበሉ ይጸናል። በዚህ ቅጥ መጠኑ በጠፋበት ዝንቅንቅ ውስጥ የዳነ ~ ሃሳብን ኮትኩቶ ለማሳደግ #ጋዳ ነው። 
 
ቤት መልካም ቤተሰቦች ኖረው ቢሞከር ውጭ ይበከላል። በሃይማኖት ተቋማት ጥረቱ አለ። ግን ምን ያህል የሰው ልጅ ለሃይማኖት ዶግማና ቅኖና ተግባራዊነት ዝግጁ ይሆናል? እያንዳንዳችን የመፍቀድ አቅማችን እራሳችን እንለካው። ከአንድ ቤት ተወልደን አድገን። ዕድል ባሰማራን በአገርም፤ በውጭም ኖረን ስንገናኝ መደማመጡም፤ መጣጣሙም ፈተና ላይ ይወድቃል። ይህንንም እኔ እራሴ ሪሰርች ሠርቸበታለሁኝ። 
 
ደግሜ ደጋግሜ እምገልጸው #አለሁ የምትለው ዓለማችን መኖሯ በዳነ ~ ሃሳብ ውስጥ ወይንስ በተበከለ? በገደፈ ወይንም በዛገ ሃሳብ ውስጥ? ---- በቅይጥጥ ይሆን የተቀመረው? አንዱን ክስተት ጦርነትን ስታስቡት በሰው ልጅ ህይወትን በመቀማት፤ ሥልጣኔን በማውደም ነው የአቤቱ ጦርነት ታሪኩም ሆነ ሪከርዱም። ለምን ጦርነት ይነሳል? ስለምንስ በጦርነት ተፈጥሮ ይነዳል? ምክንያቱ ባልዳነ ~ ሃሳብ ብክልነት ነው።
 
ዓለማችን ለጦርነት መመከቻ ሥልጡንነት ብዙ በጣም ብዙ በጀትን ትመድባለች። የዳነ ~ ሃሳብ መነሻው የፍቅር ተፈጥሮ ነው። ይህን የፍቅር ተፈጥሮ አቅም ያለው ለማድረግ የትምህርት አካል ሊሆን ይገባል ብላ አትሞግትም ልዕልት ዓለማችን። አጀንዳዋም አይደለም።
 
/// ዓለማችን ስለትህትና አጀንዳ ይዛ ተወያይታ ታውቃለችን?
/// አለማችን ስለ ታማኝነት ወርክሾፕ አዘጋ ጅታ ታውቃለችን?
/// ዓለማችን ስለ ታጋሽነት ያዘጋጀችው የማስተማሪያ ሰነድ አላትን?
/// ዓለማችን ስለ ምስጋና የሚመራመር ማዕከል አላትን?
/// ዓለማችን ስለ መቻቻል በመደበኛ የሚያስተምር ኮሌጅ አላትን?
/// ዓለማችን የፍቅር ተፈጥሮ ኤክስፐርት፤ ፈላስፋ አላትን?
/// ዓለማችን በፍቅር ተፈጥሮ ብቻ የሚተጋ የሚዲያ አውታር ቴሌቪዥን፤ ራዲዮ፤ ፖድካስት፤ ፓንፕሌት፤ መጋዝን፤ ጋዜጣ አላትን?
 
#ይህን በሚመለከት በቁጥር ሁለት Sergute Selassie ሥርጉተ ሥላሴ ዩቱብ ቻናል በግራፊክ ለአረዳድ እንዲመች በከበቡሽ ሚዲያ ለመነሻ የሆኑ ሃሳቦችን ሠርቼበታለሁኝ። በቁጥር አንድ ዩቱብ ቻናሌ Sergute Selassie ሥሜ በእንግሊዘኛ ብቻ በተፃፈው ደግሞ ለአዌርነስ የቃላት ፖስተሮች ሠርቸበታለሁ።
 
ለአሰራር እንዲያመች በኽረ መሪ ሃሳቦችን በየዘርፋ ለማቅረብ ሞክሬያለሁ። ትዝ የሚለኝ የፍቅር ልዑካን የሚል አንድ ማዕቀፍ ነበረው፤ የሆነ ሆን አንድ ብሩክ ቀን ይህን ሃሳብ የሚያራምድ፤ አቅም ያለው ተጽዕኖ ፈጣሪ ትውልድ ከመጣ ሃሳቡን ወርሶ ሊያስቀጥለው ይችላል የሚል ሙሉ ዕምነት አለኝ። ይህን ሃሳቤን ተመድም፤ የአውሮፓ ህብረትም፤ ሲዊዝ በታተመ የ193 አገሮች የገጽ ስብስብ መጸሐፍ ላይም አቅርቤዋለሁኝ። 
 
#የእኔ እና እኔ ዘለግ ያለ ተከታታይ ሙግት። 
 
እኔን በሃሳብ እራሴን ይሞግተኛል። ህግን ያልተማረ ሰው ወንጀለኛ ሊባል ይችላል ወይ? ብየ ስጠይቅ መልሴ ሊባል አይገባም ነው። ግዴታውን የማያውቅ ሰው እንደምን ግዴታውን ሊወጣ ይችላል? ግዴታህን አልተወጣህም ተብሎስ እንደምን ሊጠየቅ ይችላል? መብቱን ሳያውቅ ሰው እንደምን መብቴ ይከበር ብሎ ሊጠይቅ ይችላል? 
 
ስለዚህም ዓለማችን ህግን የጥቂት ባለሙያወች ብቻ ሳይሆን የማህበረሰቡ የማድረግ ግዴታ አለባት ብየ አምናለሁኝ። ማህበረሰቡ ስለ አገሩ ህግ እና ስለ ታህሳስ 10/1948 ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌወች ሊያውቅ ይገባል ባይ ነኝ። ልጆችም እንደ ዕድሜያቸው ልክ በመደበኛ ከህፃናት መዋያ ጀምሮ ሊማሩት ይገባል። ይህ እስካልሆነ ድረስ ወንጀለኝነትን ሊቀንስ አይችልም። 
 
በዳነ ~ ሃሳብ ዙሪያም የፍቅር ተፈጥሮ ካሪክለም ተነድፎለት እንደ ተፈጥሮ ሳይንስ፤ እንደ ማህበራዊ ሳይንስ በመደበኛ ትምህርት ቤት በሁሉም የዓለም ክፍል በመደበኛ ትምህርት ቤቶች ሊሰጥ ይገባል ባይ ነኝ። ለእኔ የፍቅር ተፈጥሮ ሳይንስ ነው። የፍቅር ተፈጥሮ ፍልስፍና ነው። የፍቅር ተፈጥሮ ሙያም ነው። የዳነ ~ ሃሳብ በዓለማችን በጥቂት ሰወች ሊቀነቀን ይችላል። ይህ በቂ አይደለም። የዓለምን አብዛኛውን ህዝብ የህሊና አሳምኖ አጋሩ፤ ተከታዩ ሊያደርግ ይገባል ባይ ነኝ። ለዛ ደግሞ ዕውቅና ያስፈልገዋል።
 
የዳነ ~ ሃሳብ አሁን ያለው አቅሙ ውስን ብቻ ሳይሆን የበረደውም ነው። ውርጬ በደመመን እያገላበጠ የሚቀጣው ነው። ጥቂቶች አሉ ግን በቂ ቢሆን ኖሮ ፩ኛው የዓለም ጦርነትን፤ ፪ኛው የዓለም ጦርነትን ያየች፤ በተጨባጭ የዳሰሰች ዓለማችን ለሦስተኛው የዓለም ጦርነት አትሰናዳም ነበር። 
 
ፋክክሩ ሮኬቱ፤ ሚሳኤሉ፤ ተዋጊ ጀቱ አልበቃ ብሎ ገዳይ እና አውዳሚ ሰው አልባ #ድሮን ደግሞ የዲጅታሉ ዓለም የሥልጣኔ መለኪያ ሆኗል። ለዚህም ነው ዕለታት በደም የቀለሙ ~ በዋይታ የወረዙ፤ ቀናት በመከፋት ~ የጨቀዩ፤ ወራት #በጠቀራ ረግረግ የሚማስኑ፤ ዓመታት በአፈር እና ድንጋይ የተኳኳሉት የሚማስኑትም፤ ሰዓትታ በዕንባ የዘለቡ፤ ሰከንዳት በአካል መጉደል የሚዋከቡት፤ መኖር እና ተስፋ በመራራ ስንብት የሚታለቡ ባልሆኑ ነበር። ዕለታት ~ ወቅታት ~ ዘመናት የጦርነት ትውፊት ሃራም ማለት እንዲችሉ የዳነ ~ ሃሳብን የሚያራምዱ፤ የሚያበረታቱ ድምፅች ላይ አተኩረን ልንሰራ ይገባል ባይ ነኝ።
 
/// የሰው ልጅን የሰው ልጅ ስለምን ያገለዋል?
/// የሰው ልጅን አምሳያው የሰው ልጅ ስለምን ይጠላዋል?
/// የሰው ልጅን የሰው ልጅ ስለምን ይበቀለዋል?
/// የሰውን ልጅ የሰው ልጅ ስለምን ይጫነዋል?
/// የሰውን ልጅ የሰውን ልጅ ስለምን ይገድለዋል?
መልሱ ----- የዳነ ሃሳብ ስደት ላይ ስለሆነ። አዳኝነት በመታደል የሚሰጥ ጸጋ ነው። 
 
#ጥቂት ስለ ዳነ ሃሳብ ቅንነት ……… ሃሳብ ላዋጣ እስኪ ………
 
* አዳኝ ጠብቆ ሲነበብ ወይንም ሲነገር አድብቶ መያዝ ይሆናል። ገደል አፋፍ ላይ ያለን ዕንቡጥ ሃሳብ አደጋ ሳይደርስበት ቢያድን ጀግንነት ነው። ምርቃትም ነው። ክፋ ሃሳብ ጥልቅ ገደል ነውና።
 
** #አዳኝ እኔ ጠብቆም ላልቱ ሲነገር ወይንም ሲነበብም ነው። ፈዋሽ የሚለው ሁለተኛ ትርጉሙ ነው። ፈዋሽ ከሚለው ኃይለ ቃል ጋር በቅርበት ይገናኛል፤ አደግ ሳደርገው #ማህሪ የሚለውን ይወስዳል። መዳን እኮ በምህረት ነው። ለታመመ ሰው እግዚአብሄር ይማርህ ስንል ዳንልን ማለት ነው። ከእዮር ጋን የሚያገናኝ ድልድይም ነው - ሥንኙ። በውስጥ ፈጣሪን የመማጸን፤ በጸሎት ህመምተኛውን የማገዝን ጥልቅ የተደሞ ሚስጢርም ነው። የሆነ ሆኖ ……/
 
የዳነ ~ ሃሳብ እራሱን አዳኝ ጀግና ብቻ ሳይሆን ሌላውንም አዳኝ ነው። እራስን በንጹህ ሃሳብ ማዳን ቆራጥ ውሳኔ ይጠይቃል።
የዳነ ~ ሃሳብ የፈጠረውን አምላኩን አስፈቅዶ፤ አስቀድሞም ይነሳል።
የዳነ ~ ሃሳብ እሱን የሰጠውን ፈጣሪውን በፍጹም ልቦናው ያከብራል።
የዳነ ~ ሃሳብ የምስጋና ልግሥናው ደንበር የለውም።
 
የዳነ ~ ሃሳብ ምስጉን ነው።
የዳነ ሃሳብ ያሸተ ነው፤ ፣ሁሌም እሸት።
የዳነ ሃሳብ መልካም ምኞትም ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ምሩቅ ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ውስጥን ያረጋጋል።
የዳነ ~ ሃሳብ ቅልጡፍ ሥልጡን ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ አዳጊ ነው፦ የዳነ ~ ሃሳብ የዕውቀት ዘርፍ ነውና - ለእኔ።
 
የዳነ ~ ሃሳብ የተስፋ አጋፋሪ ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ የመኖር ሊጋባ ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ሁልጊዜም ለምለም ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ዘወትር ያዘመረ ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ እርጅና ትውር አይልበትም። 
 
የዳነ ~ ሃሳብ ብርቱ አጽናኝ ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ታታሪ ገበሬ ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ የአይዟችሁ አርበኛ ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ድንግል ነው፤ ያልባለቀ።
የዳነ ~ ሃሳብ ትናትን አክብሮ፤ ዛሬን አመስግኖ፤ ነገን በንጽህና ይጠባበቃል።
 
የዳነ ~ ሃሳብ ውርሱም፤ ቅርሱም ርትህ ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ባህሉ ከነፃነት ይነሳል።
 
የዳነ ~ ሃሳብ ሰፊ ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ግልጽ ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ቀጥተኛ ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ለማዳን ጊዜ አጥሮት አያውቅም።
የዳነ ~ ሃሳብ ድካም አያውቅም።
የዳነ ~ ሃሳብ ለማዳም፤ አላማጅም ነው። ተናካሽ ስላልሆነ። 
 
የዳነ ~ ሃሳብ ህሊናን ያጸዳል። የወጣለት የተፈጥሮ #ቡርሽ ነው፤ ለፈቀደ።
የዳነ ~ ሃሳብ ተወሳካዊ ምግባሮችን በትህትና ይገራል።
 
የዳነ ~ ሃሳብ ገረጭራጫ አይደለም።
የዳነ ~ ሃሳብ ውርግርግ አይደለም።
የዳነ ~ ሃሳብ የወጣለት አድማጭ ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ስኩን ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ጥዱፍ አይደለም።
የዳነ ~ ሃሳብ ብክንክን አይልም።
የዳነ ~ ሃሳብ እሮ አይደለም።
የዳነ ~ ሃሳብ ምሩቅ ነው፤ በረከት የተንሰራፋበት።
 
የዳነ ~ ሃሳብ ትዕቢተኛ አይደለም።
የዳነ ~ ሃሳብ #መስቀኛ አይደለም።
የዳነ ~ ሃሳብ ሳቂተኛ ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ #ፏ ፍንትው ያለ ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ለማዳን ቅድመ ሁኔታ አይፈልግም።
 
የዳነ ~ ሃሳብ ተመስገን ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ #አሜንም ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ የበጎ ሃሳብ #እሺ ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ፍጹም የሆነ አወንታዊም ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ደህና ነኝ ለማለት አይፈራም፤ ፈውሱ በእጁ ነውና ያለው።
 
የዳነ ~ ሃሳብ ሟርትን ይጠየፋል።
የዳነ ~ ሃሳብ ጽኑ የምሥራች ዜና ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ያድናል። አዳኝ ነውና።
የዳነ ~ ሃሳብ ጥሞና ግጥሙ ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ለአርምሞ ምቹ ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ጥድፊያን ይጠየፋል።
 
የዳነ ~ ሃሳብ ፈውስ ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ንጹህ ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ቅን ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ሩህሩህ ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ሰላም ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ከፍትህ በላይ #ርትህ ነው።
 
የዳነ ~ ሃሳብ፤ ከደስታ በላይ #ሐሤትኔ ይመግባል።
የዳነ ~ ሃሳብ ሲያጽናና ከውስጡ ውስጥነትን ለግሶ ነው።
 
የዳነ ~ ሃሳብ ተፈጥሯዊ ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ሰዋዊ ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ስዋሰው ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ መስተዋድድ ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ቅጽል አይደለም፤ ሥርዕወ ግሥ እንጂ።
 
የዳነ ~ ሃሳብ የህይወት ትርጉምን ያውቃል።
የዳነ ~ ሃሳብ ፍልስፍናው #ምህረት ነው።
 
የዳነ ~ ሃሳብ ፍቅር ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ማመዛዘን ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ መርኃዊ ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ደመግቡ ነው።
 
የዳነ ~ ሃሳብ ሁልጊዜ ሙሽራ ነው።
የዳነ ~ ሃሳብ ሟተቱ ዕውነት ነው።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
 
ኑሩልኝ። አሜን።
 
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
12/10/2025
 
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ክፋ ሃሳብ #ትውልድ አጥፊ አረም ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?