አላዛሯን ኢትዮጵያ የእኔ የማለት።
የመቻቻል እጬጌዊቷ፤ ሉላዊቷ እናት ጠ/ ሚር አንጌላ ሜርክል ለኢትዮጵያ! „አቤቱ አሳቦችህ በእኔ ዘንድ እንደምን እጅግ የተከበሩ ናቸው! ቁጥራቸውም እንደ ምን በዛ! ብቆጥራቸው ከአሽዋ ይልቅ ይባዛሉ፤ ተነሳሁም፤ እኔም ገና ከአንተ ጋር ነኝ።“ መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፻፴፰ ቁጥር ፲፯ እስከ ፲፰ ከሥርጉተ©ሥላሴ 28.08.2018 ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ። · የልብ አድርስ ዜና። ውዶቼ የማከብራችሁ ትንሽ የልብ አድርስ ዜና አለችኝ። ያው የጹሑፌ ታዳሚዎች እንደምታውቁት እኔ በጀርመኗ መራሂተ መንግሥት በጠ/ ሚር አንጌላ ሜርክል ልዩ የሆነ ተመስጦ አለኝ። የ21ኛውም ምዕተ ዓመትም የሉላዊ የመቻቻል እናት ናቸውና። ሶርያ ያን ጊዜ እንደዛ በሁለገብ ችግር ስትናጥ፤ ስደተኛ እንደ ጎርፍ አውሮፓን ሲያጥለቀልቅ በነበረበት ወቅት ከስደቱ ግዝፈት አንፃር ሁኔታው ለአውሮፓው ህብረት ከአቅም በላይ ሆኖ ነበር። በዛ ላይ የሽብርተኝነት አደጋው ደግሞ መጠነ ሰፊ ነበር። ብዙም ተከታታይ አደጋ ነበር በፈረንሳይ እና በቤልጄየም። በሌሎች አውሮፓ አገሮችም ስጋቱ ይህ ነው አይባልም ነበር። ስለሆነም የአውሮፓ ህብረት አገሮች የሚችሉትን ሁሉ አድርገው፤ ሸክሙ ሲባዛ በበቃኝ ፊታቸውን ሲያዞሩ እንሂ የዓለማችን ድንቅ ጽድቅ ግን ሁሉንም ነገር ተቋቁመው ያን የመከራ ጊዜ ተጋፈጡ። የርህርህና ጉልላቷ ዶር አንጌላ ሜርክል በሚመሩት በፓርቲያቸው በCDU አባላት፤ በደጋፊዎቻቸው፤ በአጋር እህት ድርጅቶች ሳይቅር ተዘርዝሮ የማያልቅ ፈተና ውስጥ ነበሩ። ተጨማሪ አዲስ የናዚ መንፈስ አራማጅ ፓርቲ አስከ መፈጠር የተደረሰ...