የሳጅን በረከት የምክር አገልግሎት በአፍንጫዬ ይውጣ። ...

ግልግሉ መቼ ነው?
 „ጠፈርን በህዋው ላይ አጸናት፤ ሰማይንም ማዬት በጸሐይ ብርሃን ነው።“
መጽሐፈ ሲራክ ምዕራፍ ፵፫ ቁጥር ፩

ከሥርጉተ©ሥላሴ
 28.08.2018 
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።


 ግልግሉ መቼ ነው?


·         መነሻ።
Ethiopia: ሰይፉ ፋንታሁን ከአቶ በረከት ስምዓን ጋር ያደረገው ቆይታ

ውዶቼ እንዴት ናችሁ ደህና ናችሁን። ዛሬ ነፋሻማ አዬር አለ ተዚህ ከጋዳማዊቷ ውቢት ቆንጂት ሲዊዝሻ። ስለሆነም ዞር ዞር ብዬ ተመለስኩኝ። ደስ ይላል ሁለመናው።
ሳጅን በረከት ስምዖን በርካታ ዲስኩሮችን እያሰሙን ነው። ባለፈው ሰሞናት ዶር አብይ አህመድ ድምጻቸው ጥፍት ባለበት ወቅት ከጠ/ ሚር ቢሮ የወጣ መግለጫ ይሁን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕከት ይህስ ጹሁፍ የሳጅን በረከትን ነው ጠረኑ ብዬ ነበር። እኔ የዶር አብይ አህመድን የጸሁፍ ጣዕም፤ የቃላት ይዘት እና ምቱን ስላጠናሁት ያ ጹሁፍ ሊገጥም ስላልቻለ ነበር እንደዛ ያልኩት።

መልክዕቱ የጠ/ ሚሩ ነው ተብሎ ነበር የቀረበው፤ ነገር ግን መንፈሱ ደግሞ የሳጅን በረከት ነበር። በሰሞናቱ የሳጅን በረከት ስምዖን ቃለ ምልላሳቸውም ከጠ/ ሚር አብይ አህመድ ጋር በቅርበት እንደሚገናኙና የማመከር ተግባራቸውም እንደ ቀጠለ ተነግሮናል። ያው ነው በግል የቤት ሥራ እንደሚሰጣቸው እና የቀጥታ የስልክ ግንኙነትም እንዳለ አዳምጠናል። መቼ ነው ከሴራው ቸረቸራ ሀርድ ዌር አላዛሯ ኢትዮጵያ መቼ ነው የምትገላገለው አሰኝቶኛል። 

እኔ እንደ ሌሎች ሰዎች አይደለሁም በይቅርታ እና በመቻቻል መንፈስ ጽኑ እምነት አለኝ። ሰው ባይፈቅደውም ጥሩ ሆነ መገኘት አትራፊ ስለመሆኑ አውቃለሁኝ። ጥርግርግ አድርጎ ዋ! ከ እከሌ ጋር የምለው ለምህረታዊ ጉዞ አይበጅም። ስለሆነም ጠ/ ሚር አብይ አህመድ እና የሳጅን በረከት ስምኦን መገናኘቱ መልካም ነው።

 ሰው ለመምራት ከሰው ተነጥሎ አይሆንም። ከሰው ጋር መገናኘትም ሰውኛ ነው። ይቅርታ ምህረት ቸርነት ትህትና ደግነት ቢበጅ እንጂ አክሳሪ አይደለም፤ በሰላም ተገናኝቶ እንዴት ሰነበትክ መባባል መልካምነት ነው። ነገር  ግን ዛሬም በሴራው ቸረቸራ ቅሪተ አካል በዛ ክፉ መንፈስ ኢትዮጵያ ትመራ ግን የውነት ለመደመሩም - ለመቀነሱም - ለማከፈሉም - ለመባዛቱም ክፍሉ አይደለም።

የቀድሞው ጠ/ ሚር አቶ ሃይለማርያም ደስአለኝ ከቢኒ ጋር በነበራቸው ቆይታ „እኔ ከአቶ መለስ ጫማ ስር ነኝ ብለውን ነበር።“ አሁንም እኔ የሚታዬኝ የኼው እንዲምስል ነው የቃለ መልልሱን ሆድ ዕቃ ስመረምረው። መቼ ነው ከዛ የሙት መንፈስ ጋር ፍቺ የሚፈጸመው ያሰኛል?

አሁንስ እዛው መትበስበስስ ስለምንስ አስፈለገ? አብሮ መሥራት ከሳጅን በረከት ስምዖን ጋር?! በስመ አብ ወወልድ ወምንፈስ ቅዱስ አታሰመኝ ያሰኛል? በሴራ በሸር በክፉ ነገር ሥልጣና ጠ/ ሚር አብይ አህመድ አስፈለጋቸውን? ስለምን? እንዴትስ? ሊቋረጥ የሚገባው መስመር ነው። 

መልካምነት ከነጠፈበት ጉድጓድ ስብዕና ጋር አብሮ ለመሥራት ማሰብ በራሱ መርግ ነው። የፈለገ ዓይነት መስፈረት በዚህ መስመር ኢትዮጵያ አትድንም።  

ይህን መስማት እንዴት እንደሚያቅለሸልሽ እና እንዴት እንደሚያንገሸግሽ እኛን ሆኖ የጠ/ ሚር ቢሮ ቢያው መልካም በሆነ ነበር። በፍጹም ሁኔታ ያማል። በፍጹም ሁኔታ ይገለማል። ህዝብ ሆ! ብሎ የደገፈው እኮ ከሴራው ቸረቸራ ሳጅን በረከት ሃርድ ዌር ጥገኝነት ተላቀቅን ብለን እንጂ እዛው ለዛው ከሆነ ታጥቦ ጭቃ ነው። ቀላል የማይባሉ ሰዎች እኮ ስጋት አለን ሲሉ በፍጹም ይህ መስመር ከሴራ ጋር ቤተኛ አይደለም ነበር ሙግቱ …

እውነት ለመናገር አስገዳጅ ሁኔታ ገጥሞ ካልነበረ፤ ምንም ከሳጅን በረከት የዛገ መንፈስ ጥገኝነት ግፋፎ ለቀማ፤ አስር ልቃሚ ፍለጋ መሄድ አያስፈልግም ነበር። ምን አጥቶ የአብይ መንፈስ? መመካት ባይሆንም የአብይ መንፈስ የሚያጣው አንዳችም ነገር የለውም። ሁሉም አለው። 

አሳታፊ ለማደርግ ደግሞ አሁን የጀመረው፤ ተገለው፤ ቦታ አጥተው፤ የኖሩትን ሊሂቃን ሆነ ቅን ዜጎችን የማሳተፉ ተግባርን በስፋት መቀጠሉ አዋጪም ነው እኛዊነትም ነው። እርግጥ ነው አግላይነትን ላለመከብከብ ሊሆን ይችላል ግን ኤክስፓዬርድ ያደረገ ባትሪ እኮ አያገለግልም። የሳጅን በረከት ስምዖን መንፈስ የተቀጠለ ካርቦን ነው።

ብዙ ሰው በኢትዮጵያ በአገሩ ባይተዋር ሆነ የኖረበት ዘመን ማክተሙ ሊረጋገጥ የሚችለው አሁን ጠ/ ሚር አብይ አህመድ በብሮድካስት ባለሥልጣን ሆነ ከፊሉ ወደ ግል ለማዛወር የታሰቡት ተቋማትን በሚመለከት ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው የሄዱበት መንገድ ይበል የሚያስብል እንጂ አሁን እነ የሴራ ቸረቸራዎች ይምሯችሁ፤ የእነሱም የምክር አገለግሎት ያስፈልጋል ከሆነ እዬሞቱ ተስፋን የመጠበቅ ያህል ነው ለእኔ። ለዚህ እንጥፍጣፊ ትዕግስት የለንም።

አዲስ ሰውኛ ለውጡ በዚኸው በተነገረን ልክ መቀጠል አለበት። በምናዬው የቸርነት አንበል ልክ መቀጠል ይኖርበታል፤ እንጂ ከዛ የክፉዎች አፍ ወደ አለው የ27 ዓመት የመከራ መቃብር እንደገና ምልስት ማድረግ የድግምት ወይንም የአዚም መሆን አለበት። ከሆነ ከተደረገ?

እንዳልኩት አስገዳጅ ሁኔታ ከኖረ፤ እገታ እና አቅባ ከኖረ ደግሞ ለህዝብ በይፋ ይነገር። አሁን ከሰሞናቱ ያዬኋዋቸው የሙሃይ አዱኛ ቤት ግንባታ እና የዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ልጆች ጋር የነበረው ቆይታ የነበረብኝን ሥጋት ቀርፎልኛል።  

የፈለግኩትን የአብይ መንፈስ አግኝቻለሁኝ። ግን አሁንም ከሳጅን በረከት ስምዖን የሴራ ትራፊ ጥገኝነት፤ ጥውርነት ከታሳበ ወዬልሽ አንቺ አላዛሯ ኢትዮጵያ ነው … ግራጫማ መንፈስ ወረራ ይሆናል …
   
በፍጹም የሳጅን በረከት ስምዖን መንፈስ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያዊነት አትራፊ ሳይሆን ካንሰር ነው። የሚበጅ ስለመሆኑ እና ስላልመሆኑ እኮ ታዬ ሙሉ 27 ዓመት። የበሰበሰ እንቁላል፤ ድንጋይ ይወረወርበት የነበረው የኢህአዴግ አመራር አካል በስሜን አሜሪካ  ደረቱን ነፍቶ፤ እልል ኩልል ተብሎለት፤ እንኳን ደህና መጣህልን ተብሎ ያን ያህል ለማዬት፤ ለመገናኘት ወረፋው ግብግቡ ሁሉ እኮ አብያዊ መንፈስ የገዛው፤ ፍቅሩ ያስተዳደረው፤ ትህትናው የነዳው እንጂ የሳጅን በረከት ስምዖንን መንፈስን ለማቀሰስ ያ ክፉ ዘመን ናፍቆት አይደለም አለነበረም። ይሄ ሆኖ ከሆነ መቼም ትልቅ አገራዊ ግድፈት ብቻ ሳይሆን ክህደትም ነው።

ለለማ፤ ለአብይ፤ ለገዱ፤ ለአንባቸው አሁን ከዘገዬም ለደመቀ መንፈስ የተሰጠው ሙሉ የነፍስ ፍቅር እኮ የሳጅን በረከት ሀርድ ዌር ይምራን አይደለም። ይህን ተጠይፎ ተሰዶ የነበረው ዜጋ እና አካል ነው አሁንም አገር እዬገባ ያለው። ስለሆነም የምልዕቱ ፍቅርን በታማኝነት የማስቀጠል ልዩ ሃላፊነት አምስቱም አላባቸው።

ታማኝነት ሲጓደል ከህመም በላይ ነው። ታማኝነት ሲቆስል ከእሳተ ጎመራው ከጎርፉ ከላርባ ረመጥ በላይ ነው። ታማኝነት አልጋ ላይ ሲውል ከስቃይ በላይ ነው። ታማኝነት ሲቃጠል ከነዲድ በላይ ነው።

ታማኝነት ጥገኛ ሲሆን ከቋያ በላይ ነው። ለእኔ ለሥርጉተ ሥላሴ በዬትኛውም የግንኙነት መስመሬ ትልቁ መለኪያ ብቻም ሳይሆን ሰው ነው የምለው አንድን ሰው ፍጹም ታማኝ ከሆነ ብቻ ነው። ለእኔ ለሥርጉተ ሥላሴ የአስተሳብ ድህንት አለመኖር እና ፍጹም ታማኝነት የደም ዝውውሬ አዛዥ ነው።

ታማኝነት ስልም ተማላውን አይደለም። ፍጹም ታማኝነት ነው። በሁሉም መስመር ፍጽምና አይቻል ይሆናል። ታማኝነት ላይ ግን ፍጹም ታማኝ ያልሆነ ማናቸውም ሰብዕና ሆነ ሃሳብ ከእኔ ጋር የተጀመረ ግንኙነት ከኖረውም ይቆማል። ቀጥ ነው የማደርገው። ድርድር የለም።

እኔ ዶር አብይ አህመድን እምለምነው በአጽህኖትም ላሳስባቸው እምሻው ህዝብ ለሰጣቸው፤ ፈጽሞ ታይቶም ተስምቶም ለማያውቀው ፍቅር እና እክብሮት ፍጹም ታማኝ መሆን ግድ ይላቸዋል። ስለ ፍጹም ታማኝነት በተለያዩ ንግግሮች በዛሬዎቹ ሳይሆን በቀደሙት ላይ እንደሆኑበት ስለማውቅ እኔ ጥርጣሬ የለኝም።

የሆነ ሆኖ የኢትዮጵያን ተስፋ ከሳጅን በረከት ጫማ ሥር ተንበርክኮ እንዲለምን አለማድርግ የመጀመሪያው የእርምጃቸው ቁልፍ ጉዳይ ሊሆን ይገባል። የኢትዮጵያ ህዝብ ከሄሮድስ መለስ ዜናዊ ሌጋሲ እና ከሳጅን በረከት ስምዖን መንፈስ ጋር መገናኘትም መዋደድም አይሻም - በፍጹም።

የዚህ አምልኮት ያላባቸው መቀጠል የሚሹት ያድርጉት ግን እኔ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በልዩነት ለበከተው የሄሮድስ መለስ ዜናው ከቅርብ አማካሪ ከነበሩት፤ አሁንም ለዛ የሙት መንፈስ አደግዳጊ ከሆኑት ለሳጅን በረከት ስምዖን የሃርድ ዌር ክርፋት እና ደጅ ጥናት ቀጣይነት በዬትኛወም ድርድር ልቀበለው የማልችለው ጉዳይ ነው።

ሰው ራሱን ደብቆ - ራሱን ሽሽቶ - ራሱን ፈርቶት - ረሱን ስግቶበት - ራሱን ርዶበት፤ ራሱን ከዜግነቱ ነጥሎበት ለኖረ ለዛ የልዩነት ማግር እና ወጋግራ የጨለማ ዘመን እንደ ገና ደጅ ጥናት፤ ጥገኝነት ተፈላጊ አይደለም።
እነሱ ይህን የሚያደርጉበት መሰረታዊ ምክንያት የአብይ መንፈስ ገኖ በመውጣቱ ያን ጥላሽት ለማስቀባት እና ጥርጣሬ እንዲኖረን ለማስደረግ ሆን ብለው እንደ ስልት ነው የሚጠቀሙበት።

ሌሎችም ቢሆን ባልፉት ሰሞናት የምንሳማቸው መግለጫዎች፤ ንግግሮች ሁሉ „እኛም አብይንም እዬመራነው ነው።“ የአብይ መንፈስ የሚወስዳቸው መርሃዊ ግንኙነታዊ ጉዞዎች ሁሉ የእኛ ቡራኬ ነው እዬተባለ ነው፤ ሸራፈውም፤ ሾላኪውም፤ ቁመ ቀሩም የሚለን ይህንኑ ነው።

አብይን መንፈስ ለመምራት አቅሙ ወርዱ ቁመናው አለን የሚሉ ሁሉ እያደመጥ ነው። ይህ ማለት አብይ መንፈሱ በሦስት በአራት ምርኩዝ ተደግፎ የቆመ ነው ዓይነት ነው። ግን ሁሉም ለሁሉም ዛሬ አስተርጓሚ አያሻም።

ከተፎካካሪ ሆነ በአውራ ፓርቲ ከቆዬው የሳጅን በረከት ሀርድ ዌር ውስጥ በሚሰጠው የቀመር እገዛ ነው የአብይ ሌጋሲ  እዬተንቀሳቀሰ ያለው ለማለት ነው። ይህ ለአብይ ሌጋሲ ራሱን ችሎ መውጣት እና ለቀጣይ መንገዱም አደገኛ ዝንባሌ በመሆኑ ጥርት ያለ መስመር መከተል ብቻ ሳይሆን ልቅ የሆኑ የግለሰብ ግንኙነቶች መልክ ማስያዝ፤ መቀጣትም ያለባቸው ይመስለኛል ጠ/ ሚር አብይ አህመድ።

እኔ እንደ ሥርጉተ ሥላሴ አብይ መንፈሱን ቀድሜ ባላጠናው ኖሮ ሊመስል የሚችል ነገር አለ ማለት ይቻላል። ነገር ግን እኔ ቀድሜ ሥራዬ ብዬ፤ ጉዳዬ ብዬ እንደ አንድ የትምህርት ሌሰን ስላጠናሁት፤ ስለሞገትኩበትም አብይ መንፈሱ የእኔ የሚለው ብቁ፤ ብልህ፤ ክውን ያለ፤ ልቅም ያለ፤ ጥርት ያለ ያልበለዘ የማያልቅ የሃሳብ ልቅና አቅም አለው ብዬ አምናለሁኝ።

አይደለም አላዛሯን ኢትዮጵያን አፍሪካን የመምራት ብቁ ጸጋ አለው ብዬ አምናለሁ። ይህም ብቻ አይደለም ሙሉዑ ሞራላዊ ስብዕናው የተባበሩት መንግሥታትን የጸሐፊነት ደረጃ ቀጥ አድርጎ ለመምራት የሚያስችል ክህሎቱ ብቻ ሳይሆን ርህርህናው እና ለምህረት ያለው ታላቅ አክብሮት፤ ለፍቅራዊነት ያለው ቅርበት፤ ለመቻቻል ያለው የህልውና አቅም ያበቃዋል ብዬ አስባለሁኝ።

ስለሆነም እኔ ዶር አብይ አህመድን ጥርት ልቅም ባለው ሌጋሲያቸው ውስጥ ማዬት ነው እኔ የምሻው። ቅይጡ፤ ስብጥሩ፤ ዝንቁ አይመቸኝም ለእኔ። አብይ የእኔ የሚለው ሌጋሲ ሊኖረው ግድ ይለዋል። ግልጽ መስመሩን፤ የመሰመሩን አቅጣጫ፤ ዓለማ እና ግቡን ጥርት ባለ ሁኔታ ቀርፆ ለህዝብ ይፋ ማድረግ ይኖርበታል።

ይሄ የኮፒ ራይት የይገባኛል ችግር እኮ እዬመጣ ያለው በዚህ ምክንያት ነው። እርግጥ ነው ድርጅቱ ኦህዴድ፤ ግንባሩም ኢህአዴግ መሆኑ ይታወቃል። ፈንጋጣ ግን ጠቃሚ ህዝበ ጠቀም መስመሮችም የአብይ ሌጋሲ እዬሳዬ ነው። ድጋፉም የመነጨው ከዚኸው ነው።

ሰውኛ - እኛዊነት - ተፈጥሯዊነት እነዚህ ከግንባሩ የቆዩ መስመሮች ያልነበሩ ናቸው። ይህ የነጻነት አሰጣጡ ዘዬ እና የአብሮነት የህልውና ትርጓሜውም እንዲሁ አዲሳዊነት ነው። ይህ መልክ ባለው ሰነዳዊ ነገር መታገዝ ይኖርበታል።

ያልተደመሩ፤ ያለተቀነሱ፤ ለመደመር ተነሳሽነት የሌላቸው፤ ለመደመር ጊዜ የሚሹ ነፍሶችም አሉ። እነሱም ዜጎች ናቸው። ግልጽነቱ ይፋዊ ከሆነ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል።
በሌላ በኩል የመደመር ፍልስፍና በራሱ የተገባውን ያህል ተብራርቷል ማለትም አይቻልም። ሁሉም እንዳሰኘው ነው የሚተረጉመው። ለዚህ ነው ጋዜጠኞች ከጠ/ሚሩ ጋር የነበራቸው ቆይታ ጠርዝ ለጠርዝ ሲኳትን የታዬው። እነሱም እራሳቸው አልገባቸውም። እንሱም እራሳቸው የህዝብ ማህበረዊ ንቃተ ህሊና ከደረሰበት ደረጃ የመድረስ አቅም አንሷቸው ነው እኔ ያዬሁት።

ዶር አብይ አህመድ ሰዎችን ሲያቀርቡም፤ ሲያነጋግሩም በጣም መጠንቀቅ አላባቸው ብዬ አስባለሁኝ። ለህዝብ ግልጽ ያላደረጓቸው ፓተንቶች፤ በግል ከሊሂቃኑ ጋር ከሚያደርጉት ግንኙት ላይ ከተወሳ ያ ግለሰብ ሚሰተር ኤ የራሱ ሃብት፤ የራሱ ንብረት፤ የራሱ ድርጅት ፈጣራ አድርጎ እንደሚጠቀምበትም ማወቅ አለባቸው። ግልጽነታቸውን ልጓም ሊያበጁለት ይገባል።

ብዙ ሰው ያለዬው፤ ያላስተዋለው የዶር አብይ አህመድ ጸጋ ችሎታቸውን፤ ብቃታቸውን፤ ሳይስቱ ውራሽ ናቸው። ይህ እንግዲህ በፖለቲካ ሊሂቃን ያልተለመደ ጉዳይ ነው። ቆጥበው ሥልጣን ስይዝ ብለው ለዛውም ከኖራቸው ነው ደብቀው ወይንም ሰውረው የሚያቆዩ አሉ። በዶር አብይ አህመድ ግን ይሄ የለም። ያላቸውን ሳይሰቱ፤ ሳይንቆጣቆጡ ዘርግፈው የማስተላልፍ ልዩ ችሎታ ያላቸው ሰው ናቸው። ይህ ቀጥተኝነት ግልጽነት ቅንነት ዛሬ ብዙ ሰው ኦንላይን ላይ ብዙ ነገር እንዲያውቅ ረድቶታል።

ነገር ግን በዚህ የግልጥነት እና የቀጥተኝነት ባህሪያቸው በግል የሚያናግሯቸው ሊሂቃን ጋር ፓተንቶቻቸው ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። መረጃ በመስጠትም እረገድ እንዲሁ። ህዝብ ከሚያውቀው ከተለመደው ውጪ የሆነ ነገር ንግግር ማድረግ የተገባ አይደለም፤ ይሁን ከተባለ ደግሞ ንግግሩ ለሚዲያ ክፍት መሆን ይኖርበታል።

ህዝብ እዬዳመጠ ከሆነ ግን ችግር የለውም፤ ይህንማ ከአብይ አንደበት በዚህን ቀን ሰምተነዋል፤ ምንጩ አብይ ነው ማለት እንችላለን። ተወራራሽ የሆኑ ጉዳዮችን በማንሳትም ዝበቱን ማስተካከል ይቻላል። ስለሆነም ስርቆቱን ማስቆም ይቻላል። ይህ ጥረቱም ውጤቱም የአዲሱ ካቢኔ ነው ማለት ይቻላል።  

ኮፒ ራይቱም የአብይ ሌጋሲ ነው ለማለት እንደፍራለን። ማለት እንደ እኔ ላለ ሥራዬ የአብይ መንፈስ መከታትል ለሆነ ሰው ማለት ነው። ይህ ዝግ ስብሳባዎች ከግለሰቦች ሆነ ከተፎካካሪ ሊሂቃን ታዛቢ በሌለበት ከሆነ አጅግ ጎጂ ነው። ለአላዛሯም ኢትዮጵያ ፖሊሲም ሆነ ለአብይ ሌጋሲም ጠቃሚ መንገድ አይደለም። ታሪክ እኮ ነው። የታሪክ ስርቆት ደግሞ ወንጀል ነው። ከስርቆት ታሪክ እንዲድን ደግሞ የጠ/ ሚር ቢሮ ለታሪኩ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል።

ውሸት እኮ የፖለቲካ ሳይንስ ነው ለተኖረበት ዘመን። ማፈር የለም፤ የትናንት ውሸት ቅጣት ሳይበዬንበት ወይንም ምህረት ሳይጠዬቅበት ዛሬም ደግሞ ሌላ ውሸት ፈጥሮ ራስን ማኮፈስ ልማድ ነው።

ንግግሩ ለህዝብ ይፋ ከሆነ ወይንም ታዛቢ ከኖረ ግን መለዬት ይቻላል፤ ማንዘርዘሪያው፤ ዳኝነቱ ከህዝብ ዘንድ አለና። የሽምያ ጉዳይ ለፖለቲካ ፉክክር ሌላ ማስረጃ ነው የሚሆነው። „ሁሉ ተፈቅዶልኛል፤ ሁሉ ግን አይጠቅምም“ ሁሉን ገልጦ ማሳዬት አስፈላጊ አይደለም እንደማለት። መቆጠብ ጥሩ ነው ለሙሴነት።
  
ለማንኛውም የሳጅን በረከት የአሁን እርምጃ የአብይ መንፈስን እኔ እዬመራሁት ነው የሚለን ሙሉ ተሳትፎ አለኝም ነው የሚለን። ይህ ጣማራ ተልዕኮ ያለው ስለመሆኑ ዶር አብይ አህመድ ከማናቸውም ሊሂቃን ጋራ በሚያደርጓቸው ግንኙነቶች ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው በትህትን ላስገነዝባቸው እሻለሁኝ።  ምክንያቱም ተስፋ እንዳይጠወልግ ስለምሻ። 

በሌጋሲ ጉዳይ ደግሞ የኮፒራይቱ ህገ ደንብ የለሽ፤ ልቅ የሆነ መስመር ነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ስለሚመራም …

ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!

የኔዎቹ ፌስ ቡክ ያላችሁ እባካችሁን ሸር አድርጉልኝ። የዶር አብይ ቅንነት ልጓም ሊበጅለት ይገባል። ከሳጅን በረከት ስምዖን ጋር እንዳሻቸው ግንኙነታቸውን ማድረግ ቢችሉም እንደገና የነፃነት መንፈስ ለእሱ ያደግድግ ግን ግፍ ነው የውነት ... 

የኔዎቹ ኑሩልኝ፤ መሸቢያ ጊዜ። መሸቢያ ጊዜ። 
·         

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።