የድጋፍ ሰልፍ አዲስ አባባ ላይ ጦሱ መከራ ነው።
ፍቅር የልብ እና የውስጥ እንጂ የፖስተር አይደለም?
ከሥርጉተ ሥላሴ 18.06.2018 ከገዳማዊቷ ሲወዘርላንድ።
„ … ከዚህም በላይ ደግሞ የአምላኬን ቤት ስለወደድሁ ለመቅደሱ ካዘጋጀሁት
ሁሉ ሌላ የግል ገንዘቤ የሚሆን ወረቅና ብር አለኝ እና ለአምላኬ ቤት ሰጥቼዋለሁኝ።"
(መጽሐፈ ዜና መዋዕለ ቀዳማዊ ምዕራፍ ፳፱ ቁጥር ፫ - ፬)
እኔ ለጠ/ ሚር አብይ አህመድ የድጋፍ ሰልፍ አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንም፤፡ ምክንያቱም አጋጣሚውን የሚጠብቁ የሰለጡኑ እኩይ የግራ ዘመም መንፈሶች ስላሉ። ይልቅ እኔ የማስበው ዕድሉ ያለችሁ እንደ እኔ ማዕቀብ የማይጣልባቸው ወገኖቼ በቴሌቪዥን፤ በጹሁፍ፤ በራዲዮ ለወያኔ ሃርነት ትግራይ የስንቅ ቋት የሆኑ ሃሳቦችን ወጥቶ መሞገት ሰፊው ድርሻ ይሆናል።
አዋሳ ላይ እኮ የሆነው ይሄው ነው። አድብተው ጠበቁ፤ ሲቆሰቁሱ ካራረሙ፤ አጋጣሚው ሲገኝ ግራቀኙ እኩይ መንፈስ ህውከቱን ፈጠሩት። በሰው ልጅ መከራ የአብይ አስተዳደርን ለማስወቀስ ሄዱ። ዋሽንግተን ፖስት የጻፈበት ፊርማ ሳይደርቅ ነው ይሄ የተከናወነው። ለጠ/ ሚር አብይ አህመድን እኮ አቀባበል ሲያደርግ የደቡብ ህዝብ ብሄራዊ ቀን ነበር። ደረጃው ታይቶም ተሰምቶም አይተወቅም። ልክ የኬኒያ መንግሥት ያደረገውን ነው አዋሳ የፈጸመው። ያን ቀን እኮ ሥራ ሁሉ ዝግ ነበር ብዬ አስባሉሁኝ። አክብሮቱም፤ ደስታውም ልክ አልነበረውም የውስጥም ነበር፤ ሥርዓቱም አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ነበር። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶው አባት "ከነፍሴ አዳምጥኩዎት" ነበር ያሉት፤ ሌላው የስብሰባው ተሳታፊ "እንቅልፍ የተኛሁት የእርስዎን ሹመት ካዳመጥኩኝ በሆዋላ" ነበር ያሉት። ሌላውም አቶ አባተ ደግሞ ፡በሰላም ቤቴ ገብቼ እንደማድር ተስፋ አለኝ" ነበር ያሉት። ያ ድንቅ የህዝብ ሐሤት፤ የህዝብ ሳቅ፤ የህዝብ ብሩህ ተስፋ፤ የህዝብ ትስስር አይፈለግም ነበር፤ ቁርሾ ቅናት ተከለ የሆነው ሆነ።
አሁንም በዝምታው ውስጥ የከረመውን የአዲስ አባባን ህዝብ ለዳግም እልቂት ለመዳረግ ካልሆነ በስተቀር አትራፊ አይደለም። በመንፈሱ ሚሊዮን ደግፎታል የአብይን ቅዱስ መንፈስ። በእኛ ብቻ ሳይሆን በግብዣ በሄዱባቸው፤ አቅደውም በተጓዙባቸው የውጭ አገር መንግሥታት ሁሉ ተቀባይነቱ ከሚጠበቀው በላይ ነው። ሽልማቱም፤ ክብሩም የምድር ነው ለማለት አይቻልም። ስለዚህ አሁን ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ አስፈላጊ አይደለም። ያ የታይታ ነው። በላተረገጋጋ ጸጥታም የሚታሰብ አይደለም። ፍቅር እኮ የልብ እና የውስጥ እንጂ የፖስተር ጉዳይ አይደለም። ይሄ የታይታ ነው። ራሱ አቤቱ ሰማያዊ ፓርቲ ደስተኛ ነውን? አይደለም?
መከራ የባጀበት የጎንደር ህዝብ በተደሞ ጸሎት ላይ ነው። ጸሎቱ አብይን ጠብቅልን ነው። እንዲህ ዓይነት ስክነት በ27 ዓመት ውስጥ ታይቶ አይታወቅም ነው እኔ ከወደ አሜሪካ መረጃው የደረሰኝ። አሁን ኮ/ ደመቀ ዘውዱን እኔ አላውቃቸውም። ግን እጅግ የምመሰጥባቸው ሰው ሆነዋል። ስክነታቸው። እርጋታቸው። ጥልቅ ጥንቃቄያቸው ልዩ ነው። ዕዳ አለማስቀመጣቸው ትውልድን ይገነባል። ለሁሉም ነው ያሰተማሩት ፖለቲካዊ ሰብዕናን ሆነ ወታደራዊ ዲስፕሊን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለዚያውም በጸጥታ ውስጥ። ውደዱኝ፤ አክብሩኝ፤ ደግፉኝ ብለው አለቀሰቀሱንም፤ ፕሮፓጋንዲስት አላሰለፉም ግን በተግባራቸው ማሳ ህሊናችን በመልካምነት አነጹት። አሁን እኔ የጎጃምን ያህል ይናፍቁኛል ኮ/ ደመቀ ዘውዱ። ስለምን? ሰብዕናው ትውልድን ስለሚገነባ። ህይወታቸው ተቋም ሆኗል። ተመስገን!
ስለዚህ ለክብሩ ጠ/ ሚሩ አብይ አህመድ የአመራር ዘመን የፖስተር ፕሮፖጋንዲስት አያስፈልገውም። አቅም የለሹ ልግመኛው ፓለቲካ፤ ሰነፉ ፖለቲካ ነው ፕሮፖጋንዲስት የሚያሰፈለግው። የባለቅኔው ጠ/ ሚር ብቃት፤ ብልህነት፤ ጥበብ በራሱ ጊዜ ራሱን እዬገለጠ ነው ያለው። ነገም የሚታይ ይሆናል። ፈጣሪ ከጠበቀልን።
ይህ አቅም ስለተፈራ ነበር እኮ ከአንድ ዓለም አቀፍ መድረክ ነው በዲሞሽን ኦሮምያ ላይ የተመደቡት። ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚ/ርነት እኮ ሉላዊ መድረክ ነው። ከዛ ወርደው ነው ክልላዊ የከተማ ልማት … የሆኑት። ግን የለማ መንፈስ ብቁ ስለሆነ፣ አብቃይ ስለሆነ፣ የሰለጠነ ስለሆነ፣ ግራ ዘንበል ስላልሆነ፣ ዘመናይ ስለሆነ አስተዋለ - አዬ - አዳመጠ - ከራሱ በላይ ለሆነ ሃላፊነት አጨ። ለኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዕንቁውን ሸለመ። ስለዚህ እነኝህ የዘመን ፈርጦችን የሚደግፋቸው ህሊና፤ ቅዱስ መንፈስ ፈጣሪም እንጂ ፖስተር አይደለም። ፈተናቸውን የሚሻገሩበት ጥበብ እኮ እኔ ነኝ ያለ ጋዜጠኛ፤ ፖለቲካ ተንታኝ፤ የቀደመ ሊሂቅም እኮ ሊደርስበት ያልቻለው ለዚህ ነው … ሁሉም ጅራት ተከታይ ነው የሆነው።
አብረው የሚሰሩትም አንዳንድ ጊዜ እንደነግጣለን ነው ያሉት … ባልተለመደው የሰብዕና ዓይነት የአረብ ኢሚሬት አልጋ ወራሹን ሹፌር እኮ ክብር ጠ/ ሚሩ ነው የነበሩት። አዲስ አባባንም አዟዙረው ያስጎበኙ ክብሩነታቸው ናቸው። እሳቸውንም ክብሩ አልጋወራሹ የተቀበሉም ሹፌራቸው እንደነበሩ ሁሉ አዳምጫለሁኝ። ይህን የመሰለ ተዋዳጅነት በሽልንግ አይገዛም። ከሰማይ ቅብዕ በስተቀር …
የሆነ ሆኖ አዲስ አበባን ላልታወቀ ወንጀል የሚያጋልጥ ስለሆነ በፍጹም ሁኔታ መካሄድ የለበትም። ይህን ያሰቡት ቅኖች ናቸው ግን ዛሬ አንድ ሰው ብቻ ይበቃል ህውከት ለመፍጠር። ያደቡ ጉዶች አሉ። ባህርዳር ላይ እኮ አንድ አጋዚ ነው 50 ነፍስን ያጠፋው በደቂቃዎች ውስጥ የፈጀው ወይንም የረሸነው ለዛውም ከተማ ላይ፤ በወገን ላይ የማይፈቀድ ባሩድ። በዬስብሰባው እኮ የሚቀርቡ ሃሳቦች በድርጅታዊ ሥራ ሁሉ የሆኑት የትኞቹ እንደሆኑ መለዬት ይቻላል። አሁን ሰሞኑን ህዝባዊ ስብሰባ አለ ተብሏል። በዬወገኑ ድርጅታዊ ሥራውን አጠነቀዋል። ሰው አዘጋጅተዋል እኩዮች መቼም አያልቅባቸውም እና። ይህን ታዩት አላችሁ። ጠብቁት።
ስለሆነም የታሰበው የድጋፍ ሰልፍ አዲስ አበባን ላልታሰበ መከራ የሚያጋልጥ ስለሆነ የትም ቦታ የድጋፍ ሰልፍ አያስፈልግም። ሌላ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅንም መናፈቅ ነው። በሌላ በኩል መልካም ነገር እያዩ፣ እያዳመጡ እንኳን ያን መቀበል ለተሰናው ሰይጣናዊ አዬር ሌላ ብርንዶ አቅርቦ የሰው ግብር በገፍ ከማሰናዳት በስተቀር በፍጹም ሁኔታ ሊበረታታ አይገባም።
ይልቅ መንፈስ ለሌላቸው የተንሳፈፉ ግን የተፋለሱ ጹሁፎች ነው በዬጊዘው የሚበተኑት፤ አቅሙ ብቻ ሳይሆን ይለፍ የታደሉት በዛ ላይ ይሠሩ ተግተው። በግብታዊነት ተነስቶ ከመቃወም መታቀብ አንዱ ድጋፍ ነው። በጸሎት መርዳት ሌላው ጉዳይ ነው። ራስን ከቂም እና ከበቀል ማጽዳት ሌለው አቅም ነው። ራስን ከሚያውኩ ነገሮች መታቀብ ሌላው እረዳታ ነው። መስከን ሌላው ድጋፍ ነው። አላምጦ መዋጥ ሌላው እገዛ ነው።
መልካም ነገሮችን ለማዬት መናፈቅ፤ ለማድመጥ መፍቀድ ሰላማዊ እገዛ ነው። ቀድሞ ነገር በቀደመው ጊዜ ይናገሯቸው በነበሩት ዩቱብ ላይ ባሉ ዕይታዎች የትግራይ ልጆች እራሳቸው በጣም በስክንት ነው ሲከታተሉት እማዬው የነበረው። ያን ጊዜ ታዋቂም አልነበሩም። የወል እይታ የማነበው በህዝባዊ ስብሰባ ላይ እንግሊዘኛ አይቀለቅሉ የሚል ብቻ ነው። ይህም ገንቢ ነው እኔም የማምንበትም ነው። ስለምን? የንግግርን ውበቱን ይዳፈራዋል። በሌላ በኩል ውስጡን በተከታታይ ለመከታተል የጭብጡን ፍሬ ነገር ላይ ተጽዕኖ ያሳርፋል። ስለዚህም እይታው ቅናዊ ወንድማዊ ወገናዊ ነው። ከዛ በተረፈ አንድም በተቃርኖ የበከተ ሃሳብ አንብቤ አላውቅም። ምክንያቱም እኔ በየተወሰነው ወቅት የአድማጩን መጠን ስለምቆጣጠር። መልካምነት የህሊና መስኖ ስለሆነ አጀንዳዬ ነው።
በተረፈ እባካችሁን ይህን የህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በሌላ ቀይሩት። በማህበራዊ ሚዲያ የአብይ ቀን፤ የአብይ ሳምንት፤ የአብይ አቅጣጫ ስንኞች ቀን በማለት ፍሬ ሃሳቦችን ለቅሞ በማውጣት መትጋት ይቻላል። አስፈላጊ ከሆነ። እኔ ሙዚቃ እራሱ በሳቸው ሆነ በኦቦ ለማ መግርሳ ሥም የወጣው ብዙም አይሰብኝም። ሌላ የመንፈስ ስጦታ ይበልጥብኛል። አይዞህ አለንልህ ማለት። አቅዶ የህብረት ጸሎት ማድረግ። አቅዶ ሱባኤ መያዝ። እግዚአብሄር አምላክ መሬት ላይ ኑረን ይህን ቀን ስላሳዬን ማመስገን። ልብ ያጡትን ወደ ልቦናቸው መልሶ እንዲስቁ አብረውን ለእነሱም መጸለይ።
አንድ ቀን ወይንም ለሳምንት የዘለቀ ስለመልካምነት የተጉትን ፕሮ ፋይል ፎቶ በመጠቀም የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ማድረግ ይቻላል። ለዚህ ተኩስ የለውም፤ ሰው አይሞትም፤ ሰው አይታሰረም። ስጋትም ፍርሃትም የለውም። ሉላዊም ተጽዕኖውም እጅግ የገዘፈ ነው። በዚህ መትጋት ያስፈልጋል። ከዚህ ውጪ ግን ህዝብን በሚማግዱ ጉዳዮች ላይ ጊዜ ማባከን አይገባም። እሳቸውን ማሳጣት ይፈለጋል። ምክንያቱም የቡኒት መሬት እንዲህ ዓይነት አቅም ታመጣለች ተብሎ ታስቦ ስላልነበር። አቅሙን ለማንበብም፤ ለመተርጎምም፤ ለማመሳጠረም አቅም የለም። ሁላችንም አልተሰናዳንም፤ ዳጡ እና ምጡም ይሄው ነው።
ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው ዓራት ዓይናማው መንገዳችን ነው።
የኔዎቹ ለነበረን ልስሉስ ጊዜ ሁሉን ቻይ አምላክ መንፈሳችሁን እንደ ሸለማችሁኝ የልቦናችሁን ይስጣችሁ። አሜን!
መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ