ለእስር ጊዜ ሦስት ዕጥፍ ቀረጥ መክፈል።
ሌላ ግፍ ለእስር ጊዜ ሦስት
ዕጥፍ ቀረጥ
መክፈል ግድ ነው።
ከሥርጉተ ሥላሴ 17.08.2018
(ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።)
„ህልም ከመሆን ወዳለመሆን ይሄዳል በዬምሳሌውም እዬራሱ ያሳያህል።“
(መጽሐፈ ሲራክ ምዕራፍ ፴፩ ቁጥር ፫)
መቼም ተችሎ የተኖረው ጉድ ምን ይባል? ማን ይባል? አይታወቅም? ያው የደብረታቦር እና የባህርዳር ጉባኤ እጅግ የተመሰጥኩበት ስለሆነ ዛሬ ደግሜ ማድመጥ ፈልጌ አማራ ቴሌቪዥን ላይ አገኘሁት። ለካንስ ትናንት ከተለጠፈው የተቆራረጠ ስለነበር ነው መሰል ዛሬ ደግሞ ሙሉውን አገኘሁት። ግርም ብሎኛል። ለካንስ የእስር ጊዜም ቀረጥ በሦስት እጥፍ መክፈል አለበት አንድ እስረኛ። ያ ቀረጥ እዚህ እስር ቤት አልነበርኩም። እንግልትም አልደረሰብኝ ብሎ ነው።
- ወዲህ ነው ነገሩ
አንድ እስረኛ አንድ ዓምት ከስድስት ወር ከታሰረ ሲፈታ ታስሮ ነበር ተብሎ የሚሰጠው የእስረኝነት ማረጋገጫ የፍዳ ዲግሪው የሦስት ወር ብቻ ነው። ሦስት ወር ታስሮ ነበር የሚል ምስክር ወረቀት ብቻ ነው የሚሰጠው። የደገምኩት እንድታምኑት ነው። የአንድ ዓመት ከሦስት ወሩ የቆጥ የበረከቱ ለወያኔ ሃርነት ትግራይ መሳፍንታት ቆሌ መቋደሻ ነው። እዚህ እስር ቤት አልነበርኩኝም ሰማይ ላይ አርጌ ወይንም ገሃነም ውስጥ ነበርኩኝ ግን በእናንተ አልነበርኩም ብሎ መፈረም አለበት። አስራ አንድ ወርም ከሆነ የሦስት ወር ብቻ ነው የሚሰጠው። ቀሪው ሰባት ወሩም እንዲሁ ለጥቁሩ ጭራቅ ለወያኔ ሃርነት ትግራይ መሳፍንታት ሥርዕዎ መንግሥት ቆሌ የአርቲ የቡክብካው መግዣ ነው … መቋደሻ …
ምን ዓይነት ጉድ ነው? ምን እንበለው ይህን የደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ለማለትም አይገልጸውም። 10 ወር ከሆን 10 ወር 6 ኣመት ከሆነ 6 ዓመት ስለሚባል። ከዛም የከፋ ስለሆነ። ለነገሩ አንድ ጊዜ ደጉ አቤ ቶኬቻው አፓርታይድ መባል የተገባ አይደለም ብሎን ነበር።
- እንግዲያሳ ማን እንበለው?
የዲያቢሎስ አፓርታይድ እንበለው። ለእስር ጊዜ ለ18 ወር እስር መረጃ የለሹ ሌላ የ15 ወር እስር የመከራ ቀረጥ መገበር አለበት። ይሄ ደግሞ በኪራይ ሰብሳቢ፤ በጉቦ፤ ሙስና በምን የሊስት ዝርዝር ይያዝ። በምንስ ሰንጠረዥ ይወራረድ። በዚህ 15 ወራት ውስጥ ያለውን ስቃይ የጨለማ ኑሮ ሰው እጁን ዘርግቶ መቆም ከማይችልበት ጥብቆ፤ ዓይን ብርሃን ከተነፈገበት እጅግ በረዶ ከሆነ ቦታ። እንግዲህ ይህ የግዞት ዘመን ህጋዊ ዕውቅና እና ተቀባይነት የተሰጠው ስሌት ውስጥ የገባው በሦስት ወር ብቻ ነው። 15 ወሩ ዋቢ፤ ባሊህ አልባ ነው። ምን ሥም ይውጣለት? ምን ይባል? ማን ይባል? ከእኛ ቀድመው ያለፉት ምንኛ ታድለዋል።
ግን ኢትዮጵያ ሃይማኖት አላትን? የእምነት አባት አላትን? የህግ ተቋም አላትን? በዘመነ የትግራይ መሳፍንት ምንድን ናት ኢትዮጵያ አገር ናት ወይንስ ሃጢያት ወይንስ መርገምት? እንጦርጦስ ትባል? ሲኦል ትባል? ገሃነብ ትባል? ምንድናት? ወይንስ የሰው መኖሪያ አገር? በዚህ ሁሉ የሰቆቃ ዘመን ትግራይ ዘምና ዘንከት ብላ የሰላም ጊዜ አሳልፋለች።
ሌላው የሚገርመው እኔ የተወሰነው ሰው ብቻ ይመስለኝ ነበር፤ ለካንስ የሁሉም መከራ ነው። እስረኛ ምን እንደሚወጋ አይታወቅም መርዝ መወጋት ግድ ይለዋል። ይህን ገመና ተሸክመው ነው የትግራይ መሳፍንት አሁንም እንቀጥል የሚሉት? ዕብኖች።
አርበኛ ገመቹ ማዕከላዊ ላይ እንደ ሰልክ እንጨት ተሰቅሎ ውሎ ያድራል። አድሮ ይውላል። ውሎ ያድራል። አድሮ ይውላል። እሱ ደግሞ በኦነግ ነው። አሁን እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ገና ተጠናክረን፤ ተመዝግበን እንቀጥላለን፤ እንታገላለን፤ እንፎካከራለን ሊሉ ነው? እኔ እነሱ ብሆን ገዳም ገብቼ እመነኩሳለሁኝ። አንድ ቢሸፍቱ የተወለደ ደልደል ያለ ብሩክ ወጣት „የቢሸፍቱ ተወላጅ ኢትዮጵያዊ አማራ ነኝ“ ብሎ ነው ራሱን ያስተዋወቀው። ጎረቤቱ አካላቸው የጎደለ፤ ትክሻቸው በድብደባ ብዛት ወልቆ፤ ከሰሞናቱ ተፈተው ቤት ውለዋል። ያው ለግንቦት 7 ቀረመት የዋለው ጎንደር ብቻ ነው። ትካሻቸው ወልቆ ቤት መቀመጣቸውን በጎረቤት ስላዬ ያለው „ብአዴን ንስሃ ይግባ፤ ይቅርታ መጠዬቅ ብቻ ሳይሆን ለተጎዱት ካሳ ይከፈል“ ብሏል።
- እኔ ደግሞ እላለሁኝ …
ግንቦት 7ስ ለጎንደር ህዝብ ምን ካሳ ሊከፍል ይሆን? ማሰልጠኛ ከፈትኩ እያለ ሪፖርተሮቹን አሜሪካ አስቀምጦ ግደል፤ እሰር፤ ስቀል፤ ያገኘህውን ጎንደሬ እያሰደድክ አሰቃይ እያለ ሲያሰውጅ የነበረው? ካሳ አለው ለዚህ? አለሁ፣ እቀጥላለሁ፣ እወዳደራለሁስ ሊል ይሆን ግንቦት 7? በምን ሞራሉ? በምንስ የህሊና አቅሙ? በዬዕለቱ የሚሰማው ነገር እጅግ ይሰቀጥጣል።
ሌቦቹ ተፈቱ ተብሎ ኡኡታው ሲደቃ ይህን ገማና ማን ይካሰው? በማን ሥም ነው ጎንደሬ እንዲህ እዬተፈለፈ የታጨደው? ይህን መከራ በግንቦት 7 ሥም የትኛው ኢትዮጵያ ቀዬ እና መሬት ላይ፤ ቦታ ላይ ተከናውኗል? ለግንቦት 7 ጎንደሬ ሰው „ሰዉ“ አይደለምንም? የጎንደር አማራ ለግንቦት 7 ከእንሰሳት፤ ከእሳር፤ ከእንጨት ይሆን እንደ ተፈጠርን አድርጎ የሚያዬን? ሰዎች አይደለንም ጎንደሬዎች? ግን ግንቦት 7 ጎንደር ምን አደረገው፤ ምን በደለው? የእውነት አዝኛለሁኝ። ከበፊቱ በላይ …
መናገር እያቃታቸው ስቃዩ እያደከማቸው በሲቃ ሲናገሩት ማልቀስም፤ ማዘንም ውስጤ አይገልጸውም። ወገኖቼ በሌሉበት፤ ባልነበሩበት፤ በሞኝ ክንድ ዘንዶ ተለካበት። በሰው ቁስል እንጨት ቢሰዱበት ነው የሆነው ነገሩ። እነሱ እማ ወገኖቻቸውም ምናቸው ተነካ? … ግንቦት 7 ጎንደርን ይቅርታ የሚጠይቀው መቼ ነው? ውሸታም ስለመሆኑስ መቼ ነው በአደባባይ ራሱን የሚገልጸው? ካሳስ የሚከፍለው መቼ ነው? በውሸት ዘጋቢ አገር ሲያሳጭድ መኖሩን መቼም አሊ አይልም? ይሄ ነው ነፃነት የክት እና የዘወትር ልጅ አዘጋጅተህ በሌለ ነገር ህዝብህን አሳጭደህ? የራስህን ወገን ከለላ ሰጥተህ እና ሞሽረህ? ይሄ ነው ዴሞክራሲ? ይሄ ነው ትንሳኤ … ወያኔማ የተፈጠረበትን ነው የሠራው?
ግንቦት 7 ከሻብያ ጋር ተመሳጥሮ ጎንደሬን እንደ ጥንቸል መሞከሪያ ጣቢያ አደረገው። መከራው ከተፈታም በኋዋላ ይቀጥላል። በእድገት፤ በመገለል፤ ሩቅ ቦታ በመመደብ፤ በኑሮው ስጋትን በመልቀቅ። አጅባር ደብረታቦር ከተማ ያለ ሜዳ ነው። እዛ የታሠረ የክሱ ጭብጥ ደግሞ ሁመራ ወደ ግንቦት 7 ሊሄድ ሲል ተብሎ ነው የሚወነጀለው። ይህ እንግዲህ ግንቦት 7 ኤርትራ ላይ ተቀምጦ ሸህዲን ነዳጅ ማደያ ቦቲ አጋዬሁ እንደሚለው መሆኑ ነው። ከአንድ ወንዝ የተቀዱ ነው የሚመስሉት ሁለቱም።
አንዱ የውሸት ጥሬ ዕቃ አምራች፤ ሌላው የቀረበውን የውሸት ጥሬ እቃ ወደ የሰው ልጅ መቆራራጫ ማሽን የሚያሰገባ ማለት ነው። ጎንደር በዚህ መሰሪ ስውር የቅብብሎሽ ሸር ነው በግራ እና በቀኝ የታረደው። አንዱ አቀባይ ሌላው ጎል አግቢ ጨዋታው የጎንደር አማራ ብርንዶ፤ ድውለት፤ ቅቅል፤ ጥብስ፤ ለብለብ፤ ዝግን ባለተወለደ አንጀት ታራሰ … ይህ ልጅ ያወጣልን? ለግራ ቀኙም አያወጣም። ፍርዱን እዮር ይስጥ።
ለሌላ የትግል ዘመን መዘጋጀት እጅግ ይሰቀጥጣል። የሰው ስጋ በልቶ ዓይነት ነው የሚሆነው … በንሰሃም የሚሆን አይደለም … እጅግ የሚዘገንን ነገር ነው። እንዴት ተብሎ ነው ከህዝብ ፊት የሚቆመው። ለጠላት ወገንህን በተሳሳተ መረጃ አሳልፈህ ሰጥተህ። ለጅብ መንጋ ሸልመህ። ሰው መሆንን ይፈትናል። እኔ የግንቦት 7 መሪዎቹ ይህን እዬሰሙ እንቅልፍ ወስዷቸው ማደራቸው ብቻ ሳይሆን፤ ልጆቻቸው ወጥተው እስኪገቡ ድረስ አቅል እንዴት ሊኖራቸው ይችላል? የሰው ግብር ባልተወለደ አንጀትህ አቅርበህ፤ አሳርደህ፤ አሳጭደህ፤ አሁንም ከረባትህን ለብሰህ ገበርዲን አስረህ መንጎራደድ? ከባድ ነው። ቀና ብሎ ለመሄድም አያስችልም። ደብቁኝ የሚያሰኝ የሰው ልጅ እርድ ነው የተፈጸመው - በግፍ። ሃላፊነት የጎደለው እርምጃ ነው። ከአራዊቱ የተሻልኩ ሰው ነኝ ለማለት ከበድ ነው።
አቤቱ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ሆይ! አደብ ግዛ! አዲስ ብርንዶ ለማቅረብ አትክለፍለፍ። ለማገዶነት አማራውን ማዘጋጀት አይኖርብህም። ሰማያዊ ማልያ መለሰቡሰን ሁሉ እኔ አልወደድኩትም። ምን ማለት እንደሆነም አልገባኝም?
ሌላው የሚገርመው ነገር አደባባይ ላይ በሚዲያ ነው አማራ ሥራ ምደባ ላይ ሌለው 100% ዕድል ሲሰጠው አማራ ግን የተቀነሰ ድርሻ ሊሰጠው ይገባል ተብሎ የአማራው ተወካይ በቴሌቪዥን በይፋ እና በአደባባይ መግለጫ የሰጡት። አሁንም ሹም ናቸው አሉ።
አማራ ተኝቷል። ተኝተህ በለኝ በማለቱ ነው የዚህ ሁሉ ግፍ መሞከሪያ ጣቢያ የሆነው። ለወደፊቱም በማስተዋል ሊራመድ ይገባል። ለሰዎች ሥም እና ዝና ከመኳተን ህልውናውን ለማስጠበቅ ቢተጋ መልካም ነው። አሁን አማራ መተኛት የለበትም። ህሊናውን አንቅቶ እያንዳንዷን እርምጃ መከታተል አለበት። ቆቅ መሆን አለበት አማራ። ዬዘመኑ ማገዶ አቅራቪነቱ በአስቸኳይ ማቆም አለበት።
ይህ የነፃነት አዱኛቸው የሰፋ እና የተንሠራፋ የነበሩት አርበኛ አባቱ ቤት ንብረታቸው በእሳት ጋይቶ በብስጭት እንደ ተቃጠሉ አልፈዋል። ይህቺ አናት ኢትዮጵያ አሁን ደግሞ ከሰውም እናት የሆነ መሪ ሙሴ አዛኝ ሲመጣ ደግሞ በተሸረበ ሴራ ጠልፎ ለመጣል ላይ ታች ይባላል። ለ አማራ ህዝብ ከ ኦህዴድ የተሸለ ድርጀት የለውም። ይህን ልብ ሊለው ይገባል። ኦቦ ለማም ዶር አብይም ቅኖች ፈርሃ እግዚአብሄር ያደረባቸው ሰውኛ ናቸው። መንፈሳዊ ናቸው። ከአረመኔነት ወደ ሰውነት ሽግግር ተደረገ ተብሎ ነው አሁን ያዙኝ ልቀቀኙ በዬምድጃው የሚደመጠው። ኢትዮጵያ ሳቀች ተብሎ። ወደውን ነው እነ ኦቦ ለማ መግርሳ ወደ ቀያችን የመጡት። ፈልገውን። የጠሉንማ በአዬር ላይ ውግያ ምክንያት ሆነው አስፈጅተውናል።
አሁንም የሆነው ሆኗል። በኢትዮጵያ ሰላም ተውሎ የሚታደርባት አገር እንድትሆን አይፈለገም። በዚህ ላይ የሊቆች ሊቅ ደግ መሪ አዋቂ መሪ ስሚ ሲመጣ ደግሞ ሌላው ምጥ እና ዳጥ ነው ... አቅም ተፈርቶ፤ ለውጥ ተፈርቶ ህውከት ተጠምቶ ይሄው ነው ... የልግመኛው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጧት ማታ ...
በደቡብ ጎንደር ዞን ደብረ ታቦር ከተማ የተካሄደው ክፍል 2 የወጣቶች ውይይት
"አማራነት ይከበር!"
የአማራ ማገዶነት በአስቸኳይ ይቁም!
የኔዎቹ በጽሞና አዳምጡት ሰው መሆንን ይፈትናል ይፈትላልም። ሰው … ግን ሰው?
መሸቢያ ጊዜ!
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ