ሐምሌ አምስት የአማራ ተጋድሎ ቅዱሱ ቀን!

ገናናው የአማራ ተጋድሎ የጎንደር ጎጃም አብዮት በሁለገብ ትጋቱ በአጭር ጊዜ ለድል የበቃ ክህሎቱ ስለትንግርት ነው።
„ልጄ ሆይ ሕጌን አትርሳ ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ።“
(መፅሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ ፫ ቁጥር ፩)
ከሥርጉተ ሥላሴ 12.07.2018
(ከገዳማዊቷ ሲዊዘርላንድ።)



  • ·       መነሻ።
  • ሐምሌ አምስት አቦዬ ናቸው አነባበሮ የሚዘጋጅበት። አነባባሮ በኑግ አና በተልባ የሚዘጋጅ ነው። እንደ እሙሃይ ቂጣ ወይንም እንደ ዳቤ ያለ። አቦዬ ከጎነደር ለተማ በርቀት ስለሚገኙ ጉዞው አድካሚ ነው። ስንመለስ ግን ከትንሿ ገብያ ጉዝጓዟን ገዛዝትን ጠበላችን ይዘን ስነገባ ቤቱ ደግሞ እልባብ ባልባብ ሆነ ይጠብቅናል። ያው የሐዋርያት ፆምም መፍቻ ነው። አንድ ሐምሌ አቦ ግን ሌላ ፈተና፤ ፈተናውም ታምር ይዞ መጣ ያም እንዲህ ሆነ።
  • ዘመናይነት። 

ሰሞኑን የአቶ አባይ ወልዱ ባለቤት በአውስትራልያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አንባሳደር ወ/ሮ ትርፏ ኪዳነማርያም ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ አንድ ቃለ ምልልስ ከSBS አድርገዋል። ለውጥ ስለ አመጣው ሃይል የተለመደውን ቧልታቸውን አስደምጠውናል።

ለውጡ በኦሮሞ ንቅናቄ ብቻ እንደመጣ አድርገው ነበር ያቀረቡት። እንደ መልካም መግለጫም ታይቶላቸው በዬቦታው ተለጥፎላቸው አይቸዋለሁኝ። ይሄ በአንድ እጅ ማጨብጨብ ጭቆናም ነው። 

ወያኔ ሃርነት ትግራይን ለማትረፍም ሆነ ሥልጣናቸውን ሊያቆይላቸው ይችላል። በዚህ ቦታ ተቀምጦ ከእውነት ጋር ተጣልቶ ከእውነት ጋር ተፋልሶ፤ ከእውነት ጋር ተቃቅሮ ግን ከሆነ ነፍስን የመፋረዳት እዮር አለ። 

ቦታው እራሱ የህሊናን ስልጡነንት ይጠይቃል። እሳቸው የኢትዮጵያ ተወካይ እንጂ የባለቤታቸውን ሴራ ሸፋኝ እንዲሆኑ አልነበረም ይህ ታማኝት የ100ሚሊዮን ነፍስን እንዲጠብቁ የተሰጣቸው።

እሳቸውም ያውቁታል ይህን ለወጥ የወያኔ ሃርነት ትግራይ በችሮታ የሰጠው እንዳልሆነ። ሁለቱ ገናና አብዮቶች ማለትም የአማራ እና የኦሮሞ ተጋድሎ ያመጡት 50ሺህ ወጣቶች ለእግር ብረት የተዳረጉበት ጥርት ያለ ዕውነት ነው። በአካል ጉዳቱን ዓለምም እዬዘገበው ነው። ይህን የተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ሚደያዎችም፤ ዓለምዓቀፍ ድርጅቶቸም ያውቁታል። እሳቸው በዚህ ሉላዊ ሥልጣን ተቀምጠው ይህን መሰል ታች የወረደ የነጣይነት አስተሳሰብ ማራመድ በፍጹም አይጠበቅባቸውም ነበር። ያሳዝናልም ከማህብራዊ ንቃት ህሊናም ዝቅ ያለ መንፈስ ስለመኖሩ ያሳጣል። 

እርግጥ ነው የተዘረፈው የወልቃይት እና የጠገዴ መሬት የነፍሳቸው ኩላሊት ስለመሆኖ ቀደም ባለው ጊዜ ቃለ ምልልሳቸውን አዳምጫለሁኝ። እንዲህ ዓይነት ታሪክን፤ ትውፊትን፤ የከዳ ሰብዕና አህጉርም አገርም ለሆነችው አውስትራልያ አንባሳደርነት ያበቃል ለማለት ጋዳ ነው። ሌብነት ሲባል እኮ የገንዘብ ብቻ አይደለም፤ የሥነ - ልቦናም፤ የመንፈስም፤ የባዕትም፤ የማንነትም ነው። ስርቆት ደግሞ ጸያፍ እና ቀፋፊ ነገር ነው። ሌባ መባልም ይጎፍንናል። አብሶ ይህን ለቀጣይ ትውልድ ቅንዲወወርሰው ማድረግ ደግሞ ነፍስን ከግድግዳ ጋር ያጣብቃል። ለዛውም አውስትራልያን ያህል ስልጡን አገር ተቀምጦ ... 

ትንሽዬ አገር ለኮታ ማሟያ ቢኮን እንኳን ያስኬዳል። ለነገሩ በራስ ላይ ያልጀመረ ታማኝነት ዘረፋን የሚንከበካብ ሃላፊነት ባይፈጠር ይሻለዋል። ገና ሲፈጥር የሞተ በድን ነውና።
 

It’s Time: Ambassador Tirfu Kidanemariam - SBS Amharic


ለውጡን ያመጣው መሠረታዊ አምክንዮ ደግሞ የሁቱንም ተጋድሎዎች ጥያቄዎች ሳይመልስ መቆም እንደማይችል ይታወቃል። ቀድሞ ነገር ሁለቱም ክልሎች የህዝባቸውን የልብ ትርታ ለማድመጥ ባይፈቅዱ ኖሮ የሚተርፍ ዘርም አይኖርም ነበር። እሳቸው የተቀመጡበት ወንበር ሳይቀር ማዕበሉ ይንጠው ነበር። እንዲህ በተደላደለ ወንበር ተቀምጦ  መዘመን አይገኝም ነበር።

የገዱ መንፈስ የለማን ባያደምጥ እንሱማ ለዘር አንዲትም ድምጽ ለመስጠት ፈቃደኞች አልነበሩም። የተካሄደው የተጋድሎ መስመር እጅግ ፈታኝ እና ብዙ ህሊናዊ መንፈሶች የፈሰሱበት ነው።

እነሱ ተደላድለው በሴራቸው ሲታመሱ እኛ ደግሞ ሌት ተቀን የምንችለውን ሁሉ አድርገንበታል። መሬት ላይ ያሉትም የለማ እና የገዱ መንፈስም እንዲሁ … ስለዚህ የአቶ አባይ ወልዱ ባላቤት ክብርት አንባሳደሯ ወ/ሮ ትርፏ ኪዳነማርያም አሁንም በአማራ ተጋድሎ ላይ ያላቸውን ቀልድ ቢያቆሙ ይመረጣል።

ህዝብ ከተቆጣ ከባድ ነው። ከእንግዲህ የሚቆይበት ወንበር ህዝብ ከፈቀደ ብቻ ነው። አውስትራልያም ቢሆን አማራዊ መንፈሶች ጉዳያቸው አጀንዳቸው የሆኑ ዜጎች አሉ። ኢትዮጵያውያን በዬትኛውም ሁኔታ ከእንግዲህ መንፈሳቸው ከሚሰበርበት ሁኔታ አንባሳደሮች መቆጠብ ግድ ይላቸዋለው።

27 ዓመት እኮ ዜጎች አልነበርነም። ቢያንስ አሁን … ከመሼ … እንደ ዜጋ ተቆጥራቸሁ እዬተባልን ነው። ስለዚህ ቀጥ ብለን እናመለክታለን። 
ከዚህ በላይ ለአማራ ወጣት የተጋድሎም አርበኞች የሥነ - ልቦና ግድያ ቢቆም የተሻለ ነው። ዘመቻ ከተጀረመ ወንበርን መነቅነቅ ይቻላል። ቀልድ የለም 27 የኖረው ቀንበር ይበቃል።

በሌላ በኩል ላይ የተንጠለጠሉበት ትምክህትም ለነገ የትግራይ ህጻናት መንፈስ ህጻጽ ማብቀል ነው። እንደ እናት፤ እንደ ሴት፤ እንደ ስልጡን ሰብዕናም ሰው ለመሆን ማሰብ መልካም ነው። ዶሮ አይደለም አንባ ጊዮርጊስ 26 ህጻናት ባህርዳር ላይ 50 ነዋሪ የተረሸነው።


  • ·       ንስኤ።

የአማራ ተጋድሎ አብዮት ስለምን ተነሳ ስለሚለው? የአውትራልያዋ አንባሳድር የክብርት ወ/ሮ ትርፏ ኪዳነማርያም ባለቤት ትዕቢተኛው የአቶ አባይ ወልዱ ካቢኔ ዘረፋውም፤ ወረራውም፤ ስርቆቱም፤ ሌብነቱም፤ ጥጋቡም አላስችለው ብሎ፤ ክልል ጥሶ፤ በርት እንደ ለመደበት ገልብጦ ለዛ ወንበር ያበቃውን የጀግና ቤት የኮ/ ደመቀ ዘውዱን ደፍሮ ለመግባት፤ ለማስር ሲሞክር ነበር የአማራ ነፍስ ከጸጥታዊ - ተደሟዊ - እዮባዊ ባዕቱ ብቅ ብሎ የጀግነትነት ጠሐዩ ቦግ ያደረገው። 
  • አማራ ባለ አቅል ነው።

አማራ በተመስጦው ውስጥ ያለውን ብቃት ጠገብ ትእግስቱን የፈተነውን የወያኔ ሃርነት ትግራይ የማን አለብኝነቱን ቅስም እንኩት በማድረግ የመታበይ ቱባውን እንዲተረትር ያስገደደው የሀምሌ 5ቱ የአማራ ታገድሎ ፍንዳት ነጎድጓዳማ ጎመራ ነበር።


ትቅማጥ እንደ ያዘው የወያኔ ሃርነት ትግራይን ስበስባ በስብበሰባ ያጣደፈው፤ ከወዲህ እና ከወዲያ ያወራጨው፤ ከጉድጓድ ተቀብሮ እንደኖረ አራዊት ያገኘውን ሁሉ ሲያርድ፤ ሲደበድብ፤ ሲያፈናቅል ያባጀው፤ ሁለት ጊዜ ሙሉ አስቸኳይ ጊዜ እንዲታወጅ ያስደረገው፤ መላቅጥ አሳጥቶ ዕብኑን ቀፎውን እንዲቀር ያደረገው፤ በሥነ - ልቦናው ከተንጠራራበት ተራራ ወረድ ብሎ መሬት እንዲረግጥ ያስገደደው የመጀመሪያው ደወል የተደወለው አማራ መሬት ጎንደር ላይ ነበር። መነሻው ደግሞ የተሰረቀው ማንንትን ማስምለስ ነው። የተዘረፈውን ታሪካዊ ዕትብታዊ ባዕት ማስመልስ ነው።

ይህ እንቋዊ  ተጋድሎ ዓለምዓቀፍ ተልዕኮን ሰንቆ የተነሳው ህዝባዊ አብዮት ምክንያታዊ የሆኑ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ይዞ የተነሳ፤ በወጉ በመንፈሱ ድርጁ የነበረ፤ ታቦት ሊቀረጽለት የሚገባ ገናና ህዝባዊ አብዮት ነበር። አማራ በ66ቱ የማርክሲስት ሌኒኒስት ፖለቲካ ሰውር ሴራ ጫኝነት ከተፈረደበት ግለት እና መከራ እራሱን ለማለቀቅ፤ የታሰረበትን እግር ብረት በጣጥሶ የወጣበት፤ ግማዱን አሸንቅጥሮ ጥሎ „አማራነት ይከበር“ ብሎ የታሪክም የትውልድም መቅድመ ብጡል የጀግኖች ውሎ ያወጀበት የድንቆች ድንቅ አብዮት ነበር።

አማራ አንገቱን ደፍቶ መሬቱን፤ ሰብዕናውን፤ ማንነቱን፤ አንጡራ መንፈሱን ተቀምቶ አጎንብሶ ሲድህ የነበረበትን ዘመን ማክተሚያውና ዋዜማ ያወጀበት የድል መባቻው ዕለት ነበር ያ የቁርጥ ቀን ውሎ። አማራ ቀርፆ፤ ደሙን ገብሮ፤ ፈጥሮ ሁኖባት በኖረባት መሬቱ፤ ባድማው፤ በአገሩ በኢትዮጵያ መሬት ላይ ከዘሩ ተነቅሎ፤ በመጤነት ተፈርጆ ከገብያ እንደገባ ውሻ ሲንከለከል የኖበረበትን ያን የመከራ ጥቁር ዘመን መጋራጃ በበቃኝ የቀደደበት ታሪካዊ ዕለት ነበር ሀምሌ 5 ቀን የቅዱሱ አቡዬ ዕለት።

ይህ ቀን ለአማራ ትውልድ እንደ ገና መፈጠር የወያኔ ሃርነት ትግራይን ሥርዕዎ መንግሥት ኢ- ሰብዕዊ የግፍ፤ የጭቆና፤ የበረድ፤ የመከራ ዘመን ከጫንቃው አሽቅንጥሮ ለወገኖቹም „የኦሮሞ የጋንቤላ ደምህ ደሜ ነው፤ ድምጽህ ለተነፈገውም ድምጽህ ነኝ“ ለአንተም እኔ መገበር ካለብኝ ተገብሬ አዲሱን የእኩልነት መንፈስ በአብሮንት አስመጣልሃለሁ ብሎ፤ የኢትዮጵውያንን ሙሉ ብሶት እና ሰቆቃ እንደ እናት በባለቤትነት ያሰተናገደ እጹብ ድንቅ፤ በአፍሪካ ለነፃነት የተደረገ የተጋድሎ አዲስ ፈር ቀዳጅ እርምጃ ነበር።

የመንፈስ ልዕለናው እጬጌ ነበር። ያ ሞቱንም፤ በታቀደ ሁኔታ መሬቱ ቅርሱ፤ ተቋማቱ መንደዱን ሁሉ ችሎና ታግሶ አዲስ የተስፋ ችቦ ያበራ የገድሎች አውራ ነበር የአማራ ታጋድሎ የማንነት የህልውና አብዮት ራዕይ።
  • ·       ጃም ምሩቅ ነው።  

በዚህ ሂደት ቅኔው ጎጃም አማራነትነት ያነበበት፤ የተረጎመበት፤ ያመሰጣረበት በደሙ ደሙን ከፍሎ እራሱን ያሰከበርበትን ጉልልታዊ እርምጃውን ወስዶበታል። በዛ የጭንቅ እና የመራራ ዘመን፤ በዛ የጨላማ ዘመን፤ በዛ ጉማም ዘመን ጎጃም ማቄን ጨርቄን ሳይል ራሱን ገብሮ፤ ቤቱን፤ ትዳሩን፤ ልጁን ሰጥቶ፤ ኑሮውን አፍርሶ ያደረገው የቀራኒዎ ውሎ ፈጣሪ አምላካችን ለሰው ልጆች ከሰጠው ፍቅር ጋር የሚተካከል ፍጹም ቅዱሳዊ የሆነ ታላቅ ሰማያዊ ስጦታ ነበር። 


ይህን ተጋድሎ መንፈሱን ለመውረር የዘመቱትን ሁሉ እርቃኑን ያስኬደበት የጎጃም ስልታዊ ተከታታይነት ያለው የተጋድሎ ሂደትም ራሱን ያቻለ የገደል ትንግርት ነው። ጎጃም የተፈጥሮን ዕድምታ በቅኔ ያማሳጠረ የመሆን አድባር ነው። ጎጃም ለመሆን ያለወላወለ ጀግና እና ደፋር ህዝብ የተፈጠረበት ቅዱስ ባዕት ነው። ጎጃም የመወስን አቅሙ እና አቋሙ የማያወላዳ፤ በአማራነቱ የማይደራደር ንጹህ ህዝብ ነው።  

ጎጃም የፍቅር ቃልኪዳን ማህተም ነው። አማራነትን መርሳት ማለት የጎጃምን የደም ግብር መዳፈር ማለት ነው። የጎጃምን መስዋዕትነት መርገጥ ማለት ነው። ጎጃም እራሱን ሲሰጥ፤ እራሱን ሲገብር አልሳሰለትም። ቅደመ ሁኔታ አላበጀለትም።

ጎጀም የደጎች አውራ ነው። ጎጃም ህሊና ነው። ጎጃም ነፍሱን የሰጠ የነፍስ አባት ነው ለአማራ ማህበረሰብ። ጎጃም ሰውኛ ነው። ጎጃም ተፈጥሮኛ ነው። ጎጃም የሰብዕዊ መብት መረገጥን ከልቡ ያዳመጠ ህግ አዋቂ ህዝብ ነው። ጎጃም በዬትኛውም ሁኔታ እና አጋጣሚ ያለውን ያወቀ፤ ያለውን ያከበረ፤ ያለውን የእኛ ያለ የመሆን ጉልላት ነው።

አማራነት ለእኔ ሰጠኝ የምለው የሞራል ስጦታ ቢኖር የጎጃም ነፍስ በማህጸኔ መጸነሱ ነው። ኦዎን! ጎጃም ነፍሴ ነው። አዎን! ጎጃም ይናፍቀኛል፤ አዎን! ጎጃም ክፉ አይንካብኝ። ስበሰባ አለ በተባለ ቁጥር ይጨንቀኛል ይጠበኛል፤ አዎን! ጎጃም ዕውነት ስለሆነ እሳሳለታለሁኝ። ጎጃም ንጹህ ነው።


ጎጃም የሴራ ትብትብ አያውቅም። ጎጃም ጻዕዳ ህሊና ነው ያለው። ስለዚህም ጎጃም ታቦቴ ነው። ለጎጃም ህይወቴን ብሰጥለትም አልሳሳለትም፤ በስፖርት ሜዳ፤ በሙዚቃ ኮንሰርት፤ በመደበኛ ህዝባዊ ስብሰባ ሁሉ አማራነቱን በውስጡ ያተመ፤ ስለ እኛ እኛን የሆነ ድርብ ሃላፊነትን የተሸከመ የዘመን መሪያችን ነው ጎጃም።

ጎንደር በዬዘመኑ አንድምስ እኳን አጋዥ አግኝቶ አያውቅም። ጎንደር የሚፈለገው ለማገዶነት ብቻ ነው። ጎንደር በጥርስ የተያዘ ቦታ ነው። ጎንደር ከሁሉም ነገር የተገለለ ነው። ጎንደር ኩርማንነቱ ነው በዬዘመኑ ሲሰላ ሲመነዘር የተኖረው። ጎንደር ተደቁሶ በባይታዋርነት ነው የኖረው። ጎንደር አቧራ ለብሶ አቧራውም ተቀንቶበት ሰላሙ ታውኮ ነው የኖረው።

ጎንደር የልጅ ግብር ለሥምኞች ሲያቀርብ ነው የኖረው። መንገድ ዘዴ አለኝ ያለ ሁሉ ጎንደርን የሙከራ ጣቢያ ከማድረግ ፈጽሞ ተቆጥቦ አያውቅም። ጎንደሬም በዬተገኘበት ሲሳደድ ነው የኖረው። ተሰደንም ዕጣ ክፍላችን ለግዞት ነው። መክሊታችን ለግዞት ነው። ኑሯችን ለግዞት ነው። ነፍሳችንም …

ለጎንደሬ ዬይፍታህ ምህረት አግኝ ሲለው አማራነትን አመጣለት። እናም ታሪክ፤ ዘመን ፈጣሪ ነውና ጎጃምን መረቀለት። ጎንደርን ዳግም የወለደው ጎጃም ነው። ይህ በሚዲያ፤ በማህበራ ሆነ በፖለቲካ ህይወት በጎንደር ላይ ካለው ሰፊ የተጽዖኖ ቀንበር ይላቀቅ ዘንድ የጎጃም ከጎኑ መሰለፍ በመንፈስ፤ በሥነ - ልቦና የሰጠን፤ ያቀዳጀን ያወረሰን ዕሴት ዲካ የለውም።
  • ክውና፤

አሁን የትም ቦታ፤ በዬትም ሁኔታ እኔ ስለጎንደር አልጨነቅም። ስለምን? የጎጃም መንፈሱ ስላለት። ጎጃም ደም መላሽ ነው። ጎጃም ጥቃታችን ያወጣ ምራቁን የወጣ ህዝብ ነው። ጎጃም ፍቅር ነው! ጎጃም ቃልኪዳን ነው! ይህን ቀን ሳስበው ጎጃምን በሻማ አብርቼ ክፉ እንዳያሰማኝ፤ ልጅ እንዲያወጣለት አምላኬን በመማጠን ነው።

በዚህ አጋጣሚ ለአማራ የህልውና ተጋድሎ አብዮት ቅድመ ሁኔታ ሳታበጁ ዕውቅና ለሰጣችሁ ጸሐፍት እና ሚደያዎች ልባዊ ምስጋናዬ በያላችሁበት ይድረሳችሁ። ትጋታችሁ ያስገኘውን ሰብል ደግሞ ያላችሁበት ስለሆነ መዘርዘር አያስፈልገኝም።
Freedom! ነፃነት! 05.22.2018

https://www.zehabesha.com/amharic/archives/92836#respond

የአማራ ተጋድሎ የተጀመረበትን ቀን በማስመልከት ኮል ደመቀ ዘውዱ ዛሬ ጎንደር ላይ ያደረገው ምርጥ ንግግር


ጎጃምን ለጎንደር የፈጠርክለት አምላክ የተመሰገንክ ሁን!
"አማራነት ይከበር!"
ሐምሌ አምስት የክብር ቀኔ!
በአማራነታችን በንመካባትም አናፍርበትም ያሳጣን አንዳች ነገር የለምኛ!
የኔዎቹ ዕለቱ በዚህ መልክ ተዘከረ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ!

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።