ምክትል ጠ/ ሚር አቶ ደመቀ መኮነን ሥልጣናቸው ላይ ናቸውን?

አቶ ደመቀ መኮነን ምን ይሠራሉ?
ለዚህ እንኳን አይሆንም?

„ሕዝቡን ግን እንደ በጎች አሰማራቸው፤
እንደ መንጋም በምደረ በዳ መራቸው።“
አማራ ፍዳ ይሄ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።
(መዝሙር ምዕራፍ ፸፯ ቁጥር ፶፪)
(ከሥርጉተ ሥላሴ 18.07.2018)
(ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።)


  • ·       እግዚዖ የፍትህ ያለህ?!

ዐቃቤ ሕግ በአርበኞች ግንቦት 7 የተከሰሱት ክስ ሊቋረጥ አይገባም ሲል ተከራክሯል (ጌታቸው ሺፈራው)

ትናንት ቀን ላይ ይህን መረጃ ሳተናው ላይ አገኘሁት፤ ግርም ብሎኝ ዝም ብዬ ተመለከትኩት። እርዕሱን ብቻ። ቀድሞወንም ቢሆን አማራ ከዛ ጣጠኛ ግንቦት 7 ጋር ምንም ግንኙነት የለውም ነበር። ምኔ ብሎ?

የወያኔ ሃርነት ትግራይ የበቀል ቁርሾውን በምን ያወራርደው። ዕንባ ትውልድን ካበረከተ፤ መሬት እንደ ተባረከች ከቀጠለች እዬር እራሱ ተጠያቂ ይሆናል። ምክንያቱ ፈጣሪ ስለፍጥረቱ ቀናተኛ ስለሆነ።

የወያኔ ሃርነት ትግራይ  አማራን ለማራድ ምን ድርሰት ይምጣለት? በአማራ ሥም የተደራጀ የለም ማለከኪያ። ስለዚህ ህብረ ብሄረ ከሆኑትም አማራን ምርጥ እያደርጉ የግንቦት 7 መለዮ አለበሱት። እናም አማራ በሌለበት፤ ባልኖረበት ጉዳይ አካሉን ገበረ፤ ወጣትነቱን ገበረ፤ ተፈጥሮውን ገበረ፤ ሥነ ህሊናውን ገበረ፤ ትውልድን ገበረ። 

ይህ ድርጅት ግንቦት 7 ማለቴ ነው ባይፈጠር ከቶ በማን ተመካኝቶ አማራ የልዑል እንግዚአብሄርን የቀራንዮን መከራ ወይንም የዘመነ ሂትለርን ኦሾትዝ ፋሽታዊ ጭካኔ በምን ስበብ ይሟሽ ነበር።

የሚገርመው ከፍተኛው የግንቦት 7 ዋና ጸሐፊ አንጎልም ማለት ይቻላል አርበኛ አርበኛ አንደርጋቸው ጽጌ ከእስር ተፈተው፤ ከጠቅላይ ሚ/ር አብይ አህመድ ጋር ሰፊ የውይይት ክፍለ ጊዜ እንደነበራቸው ሚደያ ላይ አዳምጫለሁኝ። በተጨማሪም ከሳቸው ባለነሰ በናፍቆት ሰቀቅን የተገረፉት፤ በስጋት አሳር ፍዳቸውን የከፈሉት፤ በጋ በሐሩር ክረምት በአውሮፓው በረዶ ፍትህን ፍለጋ ሲንከራተት ከነበረው ቤተሰባቸው እና ወዳጆቻው ጋር ለንድን ይገኛሉ።

በቅንጅት ጊዜ እንዲሁ መሪዎቹ ተፈተው፤ እስካሁን አካሉ የጎደለ መከረኛ እዛው እስር ቤት እንዳለ ዶር መራራ ጉዲና ከእስር እንደ ተለለቀቁ አዳምጠን ነበር። ባለቤት ያጣ ትውልድ። አሁንም ለግብር ራሱን ሲያዘጋጅ ይገርመኛል። ጎንደር ላይ አብን ለሚባል ድርጅት ስብሰባ እንደነበር አዳምጫለሁኝ። ይደንቀኛል ሞትን ስቃይን በቃኝ የማይል ሞኝ ህዝብ ቢኖር አማራ ነው። ሌላ ቦታ እንዲህ ቀልድ የለም። 

አሁን ደግሞ ግንቦት 7 ከሁሉም ነገር ከአሸባሪነት ክሱም ነፃ ሆነ፤ በአዋጅ ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ተሞሸረ እዬተባለ እያደመጥን ነው። ጉልቻውን ያጥና ብለናል። የመንግሥት ሚዲያም ዕውቅናውን እንዲሁ በስፋት ሲሳጥ ተመልክተናል። 

የሁለት ጊዜ የሞት ፍርደኛው የድርጀቱም ሊቀመንበር፤ ሚዳያቸው ኢሳትም ነፃነቱ ታውጆለታል፤ ኑ እና ሞግቱንም እዬተባሉ ነው ሁለቱም።
እና አማራ ባልበላበት ባልኖርበት ደግሞ ተከሳሽ ሆነ፤ ያን ሁሉ ግማድ ተሸከመ፤ አሁን ደግሞ ምን አድርግ ተብሎ ነው የማይፈታውስ? እንዲህ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚባለውስ? አሁን እንኳን በዘመነ አብይ ፍትህ ልመና የት ይኬድ? 

ለመሆኑ አማራን እውክላለሁ የሚሉት ምክትል ጠ/ ሚር አቶ ደመቀ መኮነን ይህን እንኳን ማስፈጸም እንዴት ይሳናቸዋል? የሚገርም ጉድ እኮ ነው የዓለም ሚዲያ ይህን ጉድ ቢሰማው ምን ሊል ነው? ድርጅቱ ነፃ ነህ ተብሎ የሌሉበት ደግሞ ታስረው ፍዳቸውን ይከፍላሉ። አሉን ለመሆኑ አቶ ደመቀ መኮነን ከወንበራቸው? ትንሽ ወኔ ቢጤ የላቸውንም? ትንሽ አይነሽጣቸውንም?

አሉን ለመሆኑ ዶር ገዱ አንዳርጋቸው ከወንበራቸው ላይ? ስለምን ነው አሁን እነዚህ የእኔ ቢጤ ዳሃዎች ፍዳቸውን የሚከፍሉት፤ ስቃዬቸውን የሚያዩት፤ እኔም በዚህ ጉዳይ ሰፊ አቤቱታ አቅርቤ ነበር ለጠ/ ሚር አብይ አህመድ፤ እስከመቼ ነው አማራ በግንቦት 7 ስም ፍዳውን የሚከፈለው? እስከመቼ ነው በዚህ ጦሰኛ ድርጅት ሰብብ አሳሩን አማራ የሚከፍለው? እኮ እስከ መቼ? 

ግፉ አልበዛም ወይ፤ አድሎው አያንገሸግሽም? ኧረ በዛ! የሠራዊት ጌታ የተቆጣ ዕለት ምን ሊያመጣ እንደሚችል የሚችል ይችለዋል?

አሁንም ለዚህ ነው ሸር ጉድ እዬተባለ ያለው ሰሞኑን፤ ለዳግም ሞት፤ ለዳግም ፍዳ፤ ለዳግም እንግልት፤ ለዳግም በጥርስ ለመያዝ? መቼ ነው ኢትዮጵያ መሬት ላይ ዜግነት እኩል ፍትህ የሚያገኘው? መሪውን ፈተህ፤ መሪውን ነፃ አድርገህ፤ ድርጅቱን ና እና ታገል ብለህ ፈቅደህ? 

ቁልፍ መሪውን ፖለቲካ አቋሙን አዋያይተህ በቤተ መንግሥት በክብር ተቀበልህ፤ ስለምንድ ነው አማራ ለዚህ ላለተወለድበት ድርጅት ፍዳ እና አሳሩን የሚያይበት?አማራ አንድ ወገን እንዴት ያጣል? አንድ ዋቢስ እንዴት አይኖረውም? ግን ዶር ለማ መገርሳስ ምን ይሉ ይሆን? ምክንያቱም የመርህ ሰው መሆናቸውን አሳምሬ አውቃለሁ እና?

ሰው ያለው ያግባሽ ሆነ እኮ? እጅግ ያሳዝናል፤ ታሪክንም ያጠቁራል። እንዲህ ምንም የሚቋጥር ዓላማ እና ግብ ላለነበረው፤ እንዲህም ይህ ሁሉ ሰው ባክኖ ለቀረበት፤ ያ ሁሉ ድካም እና የህሊና ሃብት መቅኖ ፈሶ ለቀረ የግንቦት 7 የሞገድ፤ የኔት፤ የሞባይል ትግል፤ የአማራ እናት ግብር ስትከፍል መባጀቷ አልበቃ ብሎ፤ አሁን ደግሞ መሪዎች በሰላም ውለው እያደሩ አማራ ተነጥሎ ፍዳ ከፋይ ሆነ። ምን አጋባቸው እነሱ? ነገም እርድ ፈላጊዎች ናቸው። ነገም ጥላ ያዥ ፈላጊዎች ናቸው።
  
በሌላ በኩል ድርጅቱ ከመሸገበት፤ በጀትም ሰጥቶ ሲያዝመነምነው ከነረበው ከኤርትራ መንግሥት ጋር የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለምን ያነጋገረ የፍቅር ደርሶ መልስ እዬተከወነ ምን አለ አማራ አሁንም ግብር ከፋይ ይሁን? እንዴት ነው አማራን በሚመለከት የህሊና ዳኝነት ለመስጠት አቅም ሁሉም የሚያንሰው? ግን ሰውነት በምን ይለካ? በምንስ ይመዘን? ለዚህ ፍቺ ምን ቅደመ ሁኔታ ያስፈልገዋል። 

የድርጅቱን ከፍተኛ መሪ የፈታህ ዕለት ነበር እኮ ያለምንም ቅደመ ሁኔታ በዚህ ጦሰኛ የመከራ ድርጅት ሥም የታሰሩ የአማራ ልጆች ከይቅርታ ጋር መለቀቅ የነበረባቸው? ወያኔ ሃርነትም ያውቀዋል ምንም ያልነበረው ድርጅት እንደሆነ ግንቦት 7፤ የሥም ንግሥና ብቻ፤ አሁን እንኳን መቆሚያ ብትን አፈር ሲጣ ነው ለአዬር ላሉ የመንፈስ አምላኪዎቹ ማጣፊያው ሲያጥረው ሞገድ ላይ የተዋህድነ መግለጫ እንዲሰጥ የተደረገው ... ይሄ ብቻ በቂ አይሆንም ለፖለቲካ ሊሂቃን ውሳኔ ... 

ነው አብዩ ቤትም የክት እና የዘወትር፤ የሰው አዬነት ምደባ ተጀመረን?  
ምንድነው ይሆን የሚፈለገው? ይህ ፍቅር የሚባለው ነገር አማራን ከቶ አይጨምርምን? አማራ ላይ ሲደርስ የቁርሾ እና የመከራ ተሻካሚነቱ ብቻ ይሆን የሚወሰነው? ጊዜም - ታሪክም - ትውልድም ይፍረደው?! ልዑል እግዚአብሄርም ፍርድና ዳኝነቱን ይሰጠው።

ለአማራ የሚሆን ቀን ፈጣሪ ያምጣ! አሜን!

የኔዎቹ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ!



አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።