ብርሃነ ትንሳኤ በወርሃ ክረምት!



ባረኮተ ተመስገን።
v      
በስም አብ ወወልድ ወምፈስ ቅዱስ አህዱ አምላክ፤ አሜን!
ከሥርጉተ©ሥላሴ
22.07.2018
(ከገደማዊቷ ሲዊዘርላንድ።)

„የእግዚአብሄር ህግ ፍጹም ነው። ነፍስን ይመልሳል፤ የእግዚአብሄር ምስክር የታመነ ነው፤ ህፃናትን ጠቢባን ያደርጋል። የእግዚአብሄር ሥርዓት ቅን ነው፣ ዓይንንም ያበራል። የእግዚአብሄር ፍርሃት ንጹህ ነው ለዘላለም ይኖራል፤ የእግዚአብሄር ፍርድ እውነት እና ቅንነት ነው። ከወረቅ ከክቡር እንቁ ይልቅ ይወደዳል፤ ከማር እና ከማር ወለላ ይጣፍጣል። ባርያህ ደግሞ ይጠብቀዋል፤ በመጠበቁም እጅግ ይጠቀማል።“ (መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፲፰ ከቁጥር ፯ እስከ ፲፩ ቁጥር)

v  ቅድመ ሃሳብ።

እግዚአብሄር ደግ አምላክ ነው። እግዚአብሄር የፍቅር አምላክ ነው። እግዚአብሄር የመዳን አምላክ ነው። እግዚአብሄር የመቻቻል አምላክ ነው። እግዚአብሄር የመፍትሄ አምላክ ነው።

እግዚአብሄር የሰላም አምላክ ነው። እግዚአብሄር የመተሳሰብ አምላክ ነው። እግዚአብሄር የእርቅ አምላክ ነው። እግዚአብሄር ለፍጡራን የሚያዝን ቸር እና ደግ አምላክ ነው።

እግዚአብሄር የተበተኑትን ልጆቹን አይረሳም። እግዚአያብሄር በመከራችን ሁሉ መንገዳችን ቀያሽ ነው። ፈጣሪ የነባቢታቸን መንፈሳዊ መሃንዲሳችን ነው።

v   የተስፋ ጵጵስና!
እንሆ ቀኑ ደረሰ። እንሆ ብርሃን በራ። እንሆ ተስፋ ወደ እኛ መጣ። ባርኮ ሰጥቶን እና ግን ቆልፍን የያዝነውን ይቅርታን በልቦናችን ውስጥ እንጠቀምበት ዘንድ ፈቀደለን። ውስጣችን ጠረገልን። ተመስገን! እንሆ ቀድሞ የሰጠንን ማስተዋል ካለበት ፈትሸን እንቀርበው ዘንድ ፈቃዱ ሆነ።

እሱ የሁሉ ጌታ፤ የሁሉ ሉዕል፤ የሁሉ ንጉሥ እንሆ ቀኑን ወሰነ። ነገ ብሩክ ቅዱስ ቀን ናት ለቅዱስ ተዋህዶ አማንያን ብቻ ሳይሆን ለመለ ሰላም ወዳድ ህዝብ ሁሉም።

በቅድስት ቤተክርስትያናችን የቅኖና አፈጸጸም ምክንያት ተለያይታ የኖረችው ቅድስት ተዋህዶ አህቲ የምተሆንባት ዕለትን በፀሎት፤ በፆም፤ በሱባዬ ልንቀበላት የሚገባ ያቺ ብሩክ ቀን ወደ እኛ እንሆ ገሰገሰች።

መንፈስ ቅዱስ እኛን የቀረበባት ሰሞናት አድዮ! ነገ ዴያቢሎስ አፍሮ የሚደበደብበት ዕለት ነው። ነገ ፀላዬ ሰናይ በቤተክርስቲያናችን ሊሂቃን ተቀጥቅጦ የሚወገደበት ዕለት ነው፤ ነገ ተበትነን መንፈሳችን ስክነት አጥቶ፤ መጠጊያ አጥተን ለኖርን ማህበረ ምዕመናን ልዩ ዕለታችን የልደተ ክርስቶስ ዕለት ናት። ለእኔ ረዘመብኝ።

ብዙ ሰው በቁሳዊ ጉዳዮች ላይ ይደክማል ልክ ባድመ ላይ እንደነበረው። እኔ ግን እንደዛ አይደለም የምመለከተው።

v   ገሃዱ ዓለም ቤርሙዳ!
 አፈጸጻም እና ህይወት በአንድነት አጣማሬ አላያቸውም። አፈጸጻሙ ሰውኛ ነው። ህይወት ግን መንፈስኛ ነው። ማን ይቀጥል? ማን ይሁን የእኔ ጉዳይ አይደለም። ያ የፈጣሪ ጥበብ ነው። 

ሁሉን ሸከም ያቃለለው አምላክ እኮ የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት እንዴት ስምረት አንዳደረገው ይታወቀል። ሰውኛው ሙሁር ቤት ከሁለት ይነጣቃል ወዘተ ወዘተ እያሉ ሲፈላሰፉ ፈጣሪ ግን ሌላ ታምር ሠርቱ ስንጥቁን ሰፍቱ ሳይሆን በውህደት አንድ አደረገን።
ለደቂቃ ስለኖርነበት የልዩነት፤ የመከፋፋት፤ የእልህ ዘመን እንዳንስብ አደረገን። ተመስገን። 

በትግራይ ልጆች እና በኢትዮጵውያን መሃከል የለውንም የልዩነት ግድግዳ እንዲህ አንድ ቀን የምህረት ቀን ያምጣ። ሁሉም በህሊናው ሰንቆ የያዘው ገመና ስላለ።
የሆነ ሆኖ አፈጻጸም አጀንዳዬ አይደለም። 

ሰይጣናዊ ከሆነው አስተሳብ ውጪ መንፈሳዊ ህይወት ላላቸውም ሉላዊ ዜጎች ሁሉ የሆነው እንደሚሆነው ሆኖ ነው የተከወነው። በቅድስት ቤተክርስትያናቸውም የሆነው እንደሚሆነው ሆኖ በመንፈስ ቅዱስ ሃይል የመንፈስ ድል ብቻ ነው እኔ አትኩሮት የማደርግው።

v   ስለምኞት።
ሊቃውነት ቤተክርስትያን ለመሬታቸው ይብቁ። የተከፈለው መንፈሳችን ወጥ ይሆን። ዕንባችን በሲቃ ይፍሰስ፤ ባረኮት ትንሳኤ በምድራችን ዕውን ይሁን። 

ከተዋረድንበት ረግረግ ወጥተን ወደ ክብራችን መመለስ ነው ለእኔ ቁም ነገር የምለው ይሄን ነው። እኔ የቅብ፤ የዲኮረሼን፤ የለበጣ ጉዳይ አይደለም፤ የመንፈሳዊ የሊቃውንት ቢተክርስትያን ጸሎት ወደ ላይ በአንድ አህቲ ልቦና እንዲያርግ ነው ምኞቴ። 

በአንድ ማህሌት በመንፈስ እንዲቆም። በአንድ የቅዳሴ ልዑካን ሥርዓት ቁርባን፤ ሥርዓት ተክሊል፤ ሥርዓት ምንኩስና ሥርዓት ጥምቀት መንፈስ እንዲከውን ነው ህልሜ።

ለዚህም ነው በመከፈል ውስጥ እራሴን አባል፤ ቤተሰብ ለማድረግ ሳልፈቀድ ቤቴን ቤተመቅደሴ አድርጌ የኖርኩትኝ። ከማከብራቸው የተዋህዶ ቤተሰቦቼም የተለዬሁት። ይህች ቀን ሥርጉተንም አብረው ይተረጉሙባታል። 

ምን ቢረዘም ያ የመከራ ሌሊት አሁን በሁሉም ዘርፍ የእኔ የውስጥነት ንባብ ለቅኖች ይገለጣል። ደስታዬን፤ ሐሤቴን የገበርኩበት የዕድምታዬ ሚስጢርን ይረዱታል። አዎን ሥርጉተ ሥላሴ ፈንገጥ ትላለች። 

ይህ ከፍልስፍናዋ፤ ከህይወት መርኋዋ የፈለቀ ነው። ወደ ፈጣሪዬ ቤት ስሄድ ልበ መንታነትን ተሸከሜ አይታሰብም ነበር።

ሰሞናቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ብቻ ሳይሆን በአንድም የቅኖና እና የዶግማ ዕድምታ የማትለዬን የሁለማችን አካል የሆነችው ከኤርትራ ቅድስት ተዋህዶ ጋር በህሊና ሃዲድ በመንፈስ ወደ ቀደመው የተመለስንበት ፍጹም ጽድቃዊ፤ ጸደያዊ የመባቻ ሰሞናት፤ የሰናይ ሰሞናት ነበር።

በስደት የኖሩት አባቶቻችን ወደ ቅድስት አገራቸው ሲገቡ የሁለቱም ቅደስት አበያተ ቤተክርስትያናት ሊቃውነተ ጉባኤ ልዑል እግዚአብሄር ከፈቀደላቸው ቦታ ተገናኝተው ስላደረግልን መልካም ነገር ሁሉ ፍጹም ልዩ አድርጎ መርቆ ስለሰጠን ጸጋ ሁሉ በህብርነት በወረብ፤ በቅዳሴ፤ በአቋቋም፤ በዜማ፤ በማህሌት፤ በቅኔ ያን የጥንት የጥዋቱን ለኤርትራ እና ለኢትዮጵያ ለእኛ የተሰጠንን ቅዱስ መንፈስ ወደ ባዕቱ የሚመለሰበት ዘመን ሩቅ አይሆንም። 

ዓውዷ አማታትን፤ የንግሥ ሥርዓትን ካሻችን ማከበር ይቻል ዘንድም በሩ ተከፍቷል። ኤርትራ ውስጥም ቅዱሳን ቦታዎች ሃብታችን አሉን፤ ኢትዮጵያም ውስጥ ቅዱሳን ቦታዎች ሃብታቸው አለ።

v   ማታዳላው አድዮ ድንገቴ ዜና፤
አድዮ ዘንድሮ ተሰናድታለች፤ አዳዲስ የምሥራችን ልታበሥረን … አዎን በዓመት አንድ ቀን ብቅ የሚለው የመስቀል ወፍም እንዲሁ … አድዮ አታዳላም፤ አድዮ የሁላችንም ናት።

ኤርትራም መሬት ወቅቷን ሳታዘባ ብቅ ትላለች ሚስጢር አላት እና፤ ናፍቆት አለባት እና … የመሰቀል ወፍም እንዲሁ … ለእኛ የሰጠውን ለማን ሰጣ? ፈተናችንም ቢሆን የተሰጠንን እናውቅበት ዘንድ ለትምህርት ነው። ይህ ይሆን ዘንድ ግድ ነው .. አሁን እንደ ገና አክፉ መከራ እንዳይመጣ፤ መለያዬትን እጅግ አድርገን ፈራናው … ተመስገን!

v   ታደልን በምለሰት።
እንደ እኔ የታደሉ አባቶች ከማህሌት መልስ በእልፍኝ ሲያወጉ ጸጥ ብሎ ለሚያደምጣቸው ሌላ ዓለም ሳልም ነበር የኖርኩት።

እኔ በጥር ሥላሴ ክብረ ባዕላት ላይ ሊቃውንተ ቤተክርስትያንት ከአያቴ ቤት መጥተው እልፍኙ ውስጥ ሆነው በቅኔ እዬተተራረቡ ሲወዳደሱ አይቶ ላደገ የተዋህዶ ልጅ ይህን ሁሉ ይንፍቀኛል።

በገዳማት፤ በሊቃውነት ዩንቨርስቴዎች በእንተ ስለማርያም ያፈራቻቸው ሊቀ ሊቃውንተ ቤተክርስትያንት ያ ለዛ፤ ያ አንደበት፤ ያ ቤተሰባዊ ልሳናዊ  ጭውውት አሁን አይደለም ኢትዮጵያ ላይ ኤርትራም ተጨምራ ታምራቱን የምናይበት፤ ያን የተነጠቅነውን ሙሉ ደስታ የሚመለስበት ቀን መጣ እንሆ ወደ እኛ ቀረበ ገሰገሰ … እጃችን ዘርግተን እንቀበለው … ልባችን ከፍተን እናስተናግደው።

አዝናለሁኝ ይህን ዘመን በቁሳዊ ትርጓሜ እዬሸነሸኑ ለሚታመሱ የገህዱ ዓለም አርበኞች። የቀጨር መጬሬ ሁነኛዎች። አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት መንፈስ የተለዬ መሆኑ አልገባቸውም።

ይህ ዘመን የምርቃት ዘመናችን ነው። ካላከበርነው፤ ካልፈቀድነው ይወሰዳል። እናም ብለሆች ከእጃችን እንዳያመልጥ ልክ እንደ አራስ ልጅ እንጠንቀቅለት!
 አቅም ያለውም ይጸልይበት … ይህ ዘመን አይደለም ኢትዮጵያ ዓለም ከኖረችበት የትርምስስምስ የፖለቲካ ቋንቋ ሁሉ የተለዬ ነው በተለይ ለአፍሪካ። 

ሁሉ የሚቻለው ኤልሻዳይ አምላክ በመረጣት አገሩ ላይ ታማራቱን ሊገልጥ ግድ ብሏል።

ገና ዓይናችን በገድላት የምህረት ዝናብ ይራራል፤ ውስጣችን በታማራት የሐሤት ፍሰኃ ይረሰርሳል … አሜን! ይሁንልን! ይደረግልን!

…. እንደ ወትሮው ሲሆን ብዙ ነገር ለዛዛ ነው፤ ብዙ ነገር ዝግምተኛ ነው። ብዙ ነገር ዳተኛ ነበር። ሰውኛ ስለነበር። አሁን ግን ፍጥነቱም ውጤቱም ስኬቱም ከፈጣሪ ዘንድ ስለሆነ „እንሆ ሁሉ በእርሱ ሆነ ያለ እርሱ አንዳችም የሆነ ነገር የለም።“

ኢትዮጵያ እግዚአብሄር የፈቀደው ብሩህ ሊቀ ሙሴ ሲመጣ እንዲህ ነው እንደ እናት በመንፈሱ ጸንሶት የነበረውን ኢትዮጵያን ቁም ነገር የማድረግ ዓላማ ላይ አተኮረ፤ ሆነለትም።

አሁን ያለውን ቅጽበታዊ ታማራት እንደ ሰው ለመተርጎም ለመተንተን አይቻልም። ፍጹም ከሰው የሂሳብ ስሌት፤ ከሳይንቲስቶች ቀምር፤ ከሰው የማሰብ አቅም በላይ ላይ ነው፤ የሆነውም የሚሆነውም ሁሉ። አሁን አሁን ልዑል እግዚአብሄር ራሱ መሬት ላይ ወርዶ የሚፈጽመው ይመስለኛል።
  • ሊቃውነት ዘመናት!

ዘመኑ የታምር ነው። ዘመኑ የገድል ነው። ዘመኑ የብርሃን ነው። ዘመኑ የተስፋ ነው። ዘመኑ የኛዊነት ነው። ዘመኑ የሁመናዊነት ነው። ዘመኑ አታምልጠን ተብሎ የሙጡኝ የሚባልበት ነው።

አብሶ እንደ እኔ ላለ ከሁሉም መንፈስን ላለማባክን ራሱን ቀጥቶ ለቆዬ የተዋህዶ ልጅ ትንሳኤ ነው። ትንሳኤ የመንፈስ የምለው ይሄንኑ ነው።

አብይ ተንሳኤ ነው። ለረጅም ጊዜ በተደሞ በተዘጋ ገዳማዊ ህይወት የኖርኩት እኔ የማውቃት ያደግኩባት አባቶቼ ያገለገልሉበት ቤተ እግዚአብሄር አንድ ስለሆነች፤ መንፈሴን ሳላናውጽ ፈተናውን ታግሼ ሰብሰብ ብዬ ተቀመጥኩኝ።

አሁን ግን ችዬ እንኳን በአገልግሎቱ ተጠቃሚ ባለሆንም ግን አቅጣጫዬ ሳይበትን  በአህቲ ልቦና ጸሎቴን አቅርባለሁ ደስታዬም ሙሉ ይሆንልኛል። ተመስገን!

v   ትንሽ ስለአንድአቤት።

አንዳቤት በደብረታቦር አውራጃ በእስቴ ወረዳ የምትገኝ የገጠር ባዕት ናት። አንድአቤት ምሩቅ ቦታ ናት። አንድአቤት ለምለም ቦታ ናት። አንዳቤትን ለተደጋጋሚ ጊዜ ለጉብኝት ሄጄ አይቻታለሁኝ። የአንድአቤት እርጎ ቅቤ ነው።

እርጎው ሲጠጣ የጓጎለ ቅቤ ከውስጡ ይገኛል። ሙሉው ግሬራ ወተትን ተጠጥቶም አይጠገበም። ጣዕሙ ልዩ ነው።  የዛን የመሰለ እርጎ አርሲ ክ/ ጢቼ አውራጃ ጠና ወረዳ ላይ ገጥሞኛል፤ ከዛ ውጪ የአንዳቤትን የመሰለ እርጎም ወተትም ገጥሞኝ አላውቅም።
እኔ ከገበሬ ጋር ስለሰራሁኝ የገበሬው ህይወትን የማጣጣም ዕድሉ ስለነበረኝ መመዘን የሚያስቸል ተመክሮም አለኝ።

አንዳቤት መንፈሱ ከጎጃም ይልማና እና ዴንሳ ጋር እንደሆነም እናቴ አጫውታኛለች። አስከ ጋብቻ የደረሰ ግንኙነት እንዳለው ነግራኛለች።

ታላቅ እህቷ ወ/ሮ አልጋነሽ እርቅይሁን ከዛ እንደምትኖር ነግራኛለች። እናቴ እንደ ነገረችኝ በቀድሞው ጊዜ ሹማምንት ወደበዬቦታው ሲንቀሳቀሱ ሰው አቤቱታ በአቤቱታ ነበር አሉ።

ተበድልኩ የሚለው ብዙ ነበር አሉ። ልክ አሁን ነብዩ ጠ/ሚር አብይ አህመድ በዬሄዱበት እንደሚገጥማቸው ማለት ነው። ሁሉም ተበደልኩኝ፤ ሁሉም ተጎዳሁኝ። ሁሉም ፍትህ አጣሁ እንደሚለው ማለት ነው። ይህን ሲያዳምጡም መንፈሳቸው ጭልም ሲል አስውላቸዋለሁኝ።

ለስለስ ያሉ ጉባኤዎች ላይ ደግሞ ገፃቸው ለምለም ሲሆን አስተውላለሁኝ። አሁን አሜሪካን አገር ለምስግና ተጠርተዋል። እንዳያስከፏቸው ሁሉ አስባለሁኝ። ይህ ገራራ የሆነ ሆምጣጣ አስተያዬት ባይቀርብ እመኛለሁኝ።

የሆነ ሆኖ ዶር አብይ አህመድ አላገጠማቸውም እንጂ አንድአቤት ቢሄዱ ደስ ከሚሰኙበት „ፊታችሁ ያስደስተኛል“ ከሚሉት አንዱ ምን አልባትም መንፈስ ቅዱስ ያለበት ቦታ ሊሉት የሚገባ ይመስለኛል።

እኔ መጀመሪያ ጊዜ አንድአቤትን አይቼ ከተመለስኩ በኋዋላ ነው እናቴን ከጎበኘኋቸው ቦታዎች አንዳቤት ልዩ እንደ ነበር ስነግራት ያስረዳችኝ፤ ቀድም ብዬ እንደገለጽኩት ችግር - መከራ  - ፈተና ቢገጥመው እንኳን አንዳቤት መከራውን ቻል አድርጎ የእግዚአብሄር እንግዳ በሰናይ እንደሚአስተናግድ ስታስረዳኝ ሥሙ አንድአቤት የተባለውም …

 „ሹማምንቱ በሄዱ በመጡ ቁጥር አንድም ሰው ቅሬታ የማያቀርብበት፤ እግዚአብሄር ያሳዬዎት፤ ክርስቶስ ያመልክተዎት የሚል ቅሬታ አመልካች የሌለበት ቅዱስ ቦታ ስለሆነ፤ ሥሙን የዘመኑ ገዢ ነው የሰጠው።

አንዲያውም አንድ አቤት የሚል የማይገኝበት፤ ክስ የሚያቀርብ የሌለበት የተባረከ የምህረት ቤት፤ የምህረት ባዕት ስለሆነ አንድአቤት ብለው ያወጡለት የቀደሙት ገዢዎች ናቸው “ ብላ አጫውታኛለች።

ወላጅ አባቷ አንዳቤቴ ነበሩ ግ/ እርቅይሁን አብተው ይባሉ ነበር፤ የወጣላቸው ዓራት ዓይናማ አርበኛ ነበሩ እሷም የአርበኛ ልጅ ተብላ እንክብካቤ ይደረግላትም ነበር። የአዳሪ ትምህርት ቤት ዕድል ሁሉ አግኝታ ቤተሰቦቿ ነው ያሰቀሯት። የማደጎ ልጅ ልጃችን አትሆንም ብለው።
  
አገር ቤት ለለገዳዲ የመዝናኛ ፕሮግራም ለመጽሄት፤ ለጋዜጣም ወጎቼን ጽፌ ስልክም ያን ጊዜ ሥርጉት እርቅይሁን በሚል የብዕር ሥም የነበረውም በዛ ምክንያት ነበር።

ከትናንት በስትያ ዘሃበሻ ላይ አንድ ጹሁፍ ሳነብ ለካንስ እሰከ ዛሬዋ ዕለት አንድአቤት ላይ የቅዱስ ወብዕጹ አባታችን የአቡነ መርቀርዮስ ሥም አንድም ቀን ሳይሰተጓጎል ይጠራ ነበር አሉ።

ግርም ነው ያለኝ። ይህን ያክል ዘመን ግማድን ፈቅዶ መሸከም። እጹብ ድንቅ ጽናት! አሁን ከሰሞኑ አፈርኋናት እንደ ተጨመረ ሰምቻለሁኝ። ሚስጢሩ አንድአቤት የሰላም የእርቅ ቤት ስለሆነ ነው በዚህ ጽናቱ የቆዬው።

v   ጽናቱ ሐዋርያዊ ተደሞ!

ጠብ ጭቅጭቅ የማይፈቅድ ስለሆነ። እኔ ቅዱሱ እጬጌው አባታችን አጅግ አድርጌ አምናቸዋለሁኝ። በከፋኝ ዕለት ሻማዬን አብርቼ ሁሉ እለምናለሁኝ። ጭንቁ እንደጓጓሁኝ ሳላያቸው ወደ አገር ቤት ስለሚገቡ  ነው። ለእኔ ሃዘን ተፍሰሃ ነው። ላገኛቸው እጅግ አድርጌ እፈቅድ ስለነበር።

 ምክንያቱም ሌላ ሳይሆን የጥሞና ጊዜ አያያዛቸው እጅግ ይመስጠኛል። አባቴ እንድላቸው አድርጎኛል። ቁጥብ ናቸው። በቀን አንዲት ጊዜ ብቻ ነው እህል የሚቀምሱት። ኢትዮጵያም ዕድለኛ ናት።

የጽናት ሐዋርያው ብጹዑነታቸው በህይወት እያሉ ምድሪቷን ይረግጡ ዘንድ ተፈቀደላት። ከልባቸው ሰማዕት ናቸው። እርጋታቸው ፍጹም እዮራዊ ነው። ባረኮታቸው እዮራዊ ነው።

ንዑዳዊ ቅንነታቸውን ዘመን ይተርጉመው በእኔ አቅም የሚሞከር አይደለም። መቼም መላ የኢትዮጵያ ህዝብ እስላም ክርስትያኑ ፍሳሃው ይሆናል ብዬም አስባለሁኝ። መሬቷን ሲረግጡ የተፈጥሮ መስኮቶች ተከፍተው ኮለል ይላሉ በሲቃ …


v   ቃ ናፈቀኝ በተዋህዶ፤
v   አንዳቤት ላይ ልዩ የተስፋ ሆስዕና!
  
እናም ልዑል እግዚአብሄር ፈቅዶ አገር ቤት ሲገቡ ብጹዑ አባታችን እንዲያው በኤሌኮፍተርም ቢሆን ያን የምህረት፤ የጽናት፤ የመቻል ቦታ አንድአቤትን ተገኝተው ቢባርኩት፤ ተገኝተው ቢቀድሱብት እንዴት ትልቅ ነገር በሆነ ነበር። እዛውም ባዕት አቡነ መርቀርዮስ ታቦት ቢቀረጽላቸውም ምኞቴ እና ፈቃዴ ነው።

እኔ እስከ አሁን በሚካሄዱት የእርቅ እና የሰላም ጉባኤ ቢሆን ብዬ ጓጌቼ አላውቅም። ምክንያቱም ለአባቶቼ አገር ሲገቡ የሚገጥመውን ፈታና ስለማስበው።
አሁን ግን ልክ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር አዲስ ግንኙነት ስትፈጥር የተሰማኝን ያህል መታመን በጠ/ ሚር አብይ አህመድ አስተዳደር ሰላም ስለሚሰጠኝ እምነቴ ጽኑ ስለሆነ ምን ይሆኑ ብዬ አልሰጋም። በፍጹም።

እነዛ ሁለት ሰማዕታት ሰኔ 16 ቀን ሁሉንም መከራ ተቀብለውበታል፤ እነዛ የቁም 154 ሰማዕታትም ሁሉንም ፈተና አስተናግደውታል።

ስለሆነም ነገ ተስፋ ብቻ ነው የሚታዬኝ። ሌላው ውጪ ሥጋቸው የቀሩ ሰማዕታት አባቶቻችንም አጽማቸው ፈልሶ ለአጋሩ መሬት ይበቃል። ቀን ጥሩ ነው እንዲህ ይክሳል።

ከቶ ይህ ዘመን ማን ይባል? ያችን ቀን ስናገኛት ማን እንበላት የሚል አንድ ግጥም ለህትምት የበቃ አለኝ። ከዬትኛው የግጥም መድበሌ እንደሆን አላስታውሰውም፤ አፈላልጌ እልጥፍላችሁአለሁኝ  ለአዱኛዎቼ።

አዎን ይህችን ቀን ማን እንበላት መጋቢት 24 ቀን 2010ን። እኮ የቀለበት ቀን እንበላትን? የባረኮት ቀን እንባላትን? የሰውኛ ቀን እንበላትን? የተፈጥሮ ቀን እንበላት? ወይንስ የትንሳኤ? ለነገሩ እኩለ ሌሊት ላይ ነበር የምሥራቹ የተደመጠውም። የግጥሜን ጭብጥ ሳገኘው ዕዬታዬን ምን እንደነበር ጭብጡም ምን እንደሚል አካፍልአለሁኝ።

   v     ቱ።
በተረፈ ሳይገባን እና ሳንመቼው ይህን ቅዱስ የምህረት - የመቻቻል ዘመን ላመጣልን፤ ለሰጠን፤ ለፈቀደልን አምላካችን ልዑል እግዚአብሄር ክብር ምስጋና ይግባው! አሜን። ቸር ወሬ ያሰማን አማኑኤል፤ አሜን!

የራስ ባለደራ ሥነ - ግጥም። (29.04.2018)
ኢትዮጵያን ቁምነገር የማድረግ ዓላማ!
ወስብሃት ለእግዚአብሄር።


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።