ስለምንፈልገው ነፃነት ዝግጁነት አይነሰን።
ዝግጁነት።
„ፌዘኞች ከተማቸውን ያቃጥላሉ፤
ጠቢባን ግን ቁጣን ይመልሳሉ።“
መጸሐፈ ምሳሌ ተግሳጽ ምዕራፍ ፳፱ ቁጥር ፰
ከሥርጉተ ©ሥላሴ
06.08.2018
ከገዳማዊቷ ሲዊዘርላንድ።
- · መቅድመ ሃሳብ።
ተወዳጇ ፆመ ፍልስቲት መጣችልን። ፆመ ፍልሰቲት ቀኗ አጭር ግን እጅግ የተመስጦ እና የሱባኤ፤
የምህላ እና የሰጊድ፤ የተደሞ እና የትሩፋት ጾም ናት። ፍልሰቲት የውስጥ ሰላም ማስፈኛ ወቅትም ናት።
አማና ይህን ጊዜ፤ ታች አምና ይህን ጊዜ፤ ከዛም በፊት ይህን ጊዜ ሃይማኖታዊ በሆኑ ጉዳዮች
የሱባኤ ወቅቱን ውስጣችን ጥቁር ለብሶ ነበር የተከወነው። ተስፋችን በልዑል እግዚአብሄር ብንጥልም ከቀን ወደ ቀን እዬጠነከረ በመጣው
ጭካኔ ምክንያት ተስፋችን፤ እምነታችን፤ ጽናታችን የፈተኑ እጅግ አስቸጋሪ ጊዜን አሳልፈናል።
እነሆ ዘንድሮ በልዑል እግዚአብሄር ቸርነት እና ፍቃድ ብጹዕን አባቶቻችን፤ ሊቃውነት ቤተክርስትያን
በአኃቲ ልቦና ሆነው ሱባያቸውን የሚይዙበት የተባረከ፤ የተቀደሰ ጊዜ ላይ እንገኛለን። ተመስገን!
በውስጣችን ትፍስህት፤ ተስፋ፤ ማግስትን አስበን፤ መኖራችን የፈቀድንበት ወቅት ላይ ነን። ስለሆነም
የ2010 ጾመ ፍስቲት ከወትሮው በተለዬ በውልዮሽ ማዕዶተ ፍቅር፤ በውልዮሽ ማዕዶተ መተሳሰብ፤ በወልዮሽ ማዕዶት መከባባር ፍለስቲት
በጥልቅ የተመስጦ መንፈስ አምሮባት ትከወናለች ማለት ነው። ተመስገን!
ሳይሽ እወላለሁ ከልቤ አስቀምጬ
ሳይሽም አድራለሁ አቅፍ አንተርሼ
አወሳሳሻለሁ አድርሽኝ ለብሼ
አንቺን እዬሳሳሁ ጀግንነት ወርሼ
እንደ ወጣሁ አልቀር አይቀር እንደ መሼ፤
„አድርሽኝ“ ግጥም ለህትምት የበቃ ነው፤ ሁልጊዜም በጸጋዬ ራዲዮ ላይ እንደ ድርሳን
የመግቢያ መዝሙሬ ነበር።
አድርሽኝ የሚባል የ16 ቀን የሱባኤ ቀናት የጎንደር ከተማ ብቻ ይመስለኛል ሃይማኖታዊ ትውፊት
ስለለ ያን በማሰብ ነበር የጻፍኩት። ስለ አድርሽኝ ትውፊት በተለያዬ ሁኔታ ስገልጠው ኑሬያለሁኝ። አድርሽኝ ለሚቀጥለው ዓመትም በሰላም
በጤና ሳንጎደል አድርሽን ድንግልዬ ማለት ነው።
ዘንድሮ እንደ ወትሮው፤ እንደ አባት አደሩ የውጪው ስደተኛው ህጋዊ ቅዱስ ሲኖዶስ፤ የአገር ውስጡ ቅዱስ
ሲኖዶስ፤ የገለልተኛው የሚለው ተወግዶ በአኃቲ ልቦናና መንፈስ ነው
ሱባዔውን የጀመርነው። እንኳን ለዚህች ብሩክ ቀን አደረስን አደረሳችሁ። ተመስገን።
- · ልሳነ ወስጤ።
እንሆ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሰሞናቱ አዲስ ምዕራፍ ውስጥ ትገኛለች። ይህን አስመልክቶ
የጀርመን ድምጽ ከቤተክርስትያኒቱ ሊቀ ሊቃናት አቦው ጋር ስለ ወደፊት ተስፋዋ እና ስለ ስምምነቱ አፈጸጻም ቃለ ምልልስ አደርጓል።
እጅግ እማከብራት እና ስኩን የሆነችው ጋዜጠኛ ነበረች ተግባሩን የከወነችው። ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በትውፊቱ ልክ በታላቅ አክብሮታዊ ሁኔታ ነበር
ቃለ ምልልሱ የተከናወነው። የዛሬ ልጆች ይመቻል እንደሚሉት ማለት ነው። ቃለ ምልልሱ እዬተካሄደ የተነሱትን ጥያቄዎች አንድ በአንድ
በመንፈሴ እኔ በግሌ አወርድ እና አወጣ ነበር።
የአልጀርሱ ስምምነት ወሳኔን ወደ ተግባር ለማሸጋገር ቁሞ ቀር የሆነውን
ውሳኔ አዲሱ የኢትዮጵያ ጠ/ ሚር አብይ አህመድ ወደ ተግባር የማሸጋገር ኮስታራ፤ ደፋር እርምጃ ለመወሰድ የሚያስችል አቋም ላይ
እንዲደረስ መንግሥታቸውን ሲያስደርጉ የሙሁራኑ ውይይት አገር ቤት ተካሂዶ ነበር፤ ያን ነበር በምልሰት ስቃኛው የነበርኩት።
አብሶ የዓለም አቅፉ የህግ ባለሙያ የዶር. ያዕቆብ ኃይለማርያም ምልከታ አፈጻጻም ተኮር ነበር።
ቁሳዊ ላይ አትኩሮት ነበረው። እኒያ በሁለመናቸው ተመስጥነባቸው፤ የባሳ የከፋ ቀን ቢመጣ እንኳን የአሮን በትርን ሚና ይጫወታሉ
ብለን ያሰብናቸው ሊቀ ሊቃውንት እዛ ታች ወርደው ሲቀረቅሩ እንደገና በምልሰት ያልፍንባቸውን የትግል አርንቋዎች እና በቅንነት ያዬናቸውን
ፖለቲካዊ አቋሞች መፈተሽ ግድ ብሎን ነበር።
ብልሁ ጠ/ ሚር አብይ አህመድ ደግሞ የሄዱበት መንገድ እና የኤርትራ መሪ ፕ/ ኢሳያስ አፈወርቂም
ዕድልን በአግባቡ መጠቀምን አወቁበት እና በታሰበው ቀርቶ ባልታሰበው መንገድ ሁሉንም አጀብ ያስኝ እጅግ አስደሳች እርምጃ ወሰዱ።
መቼም የአንድ ጥሩ የለውም። ሰላም የሁለትዮሽ ፈቃድን በውል ይጠይቃል።
እርግጥ ነው ይህም ያልተማቻቸው ወገኖች ያን የህዝብ ደስታ እና ፍስሃ እያዩ እንኳን ማክሰል
የለመደባቸው ስለሆኑ፤ ከአዎንታዊነት ጋር በፍጹም ሁኔታ በተፃራሪነት የቆሙ ስለሆኑ በዛው የቁፋሮ አካፋቸው ያሉትን አሉ፤ ግን ሴራቸው
አምላካችሁ አለ ፍግም ብሎ ቀረ።
የሰው ልጅ ሰውን ደስ በሚያሰኝ ነገር ሲተጋ ያስመሰግናል እንጂ አስወቃሽም አስነቃሽም አልነበረም።
ሰው የሚጨነቀው ክሬዲት ተቆጠረለት ዓይነት ነበር። ይህም እኮ ሲታደሉት እንጂ እንኳንስ ኢትዮጵያዊ
የውጪውም ሞክሮ ሞክሮ ያልተሳከ ጉዳይ ነበር፤ በቀናት ታምር በታምር የተነባበረው። የሚገርመው የነበረው የቁርሾ ጣጣ ሁሉ ለቅኖች
አጀንዳቸው አልነበረም በፍጹም።
ያን የሳቅ ሰሞናት እንዳያመልጥ ከመትጋት በስተቀር ስለ ቀደመው ጉዳይ አስታዋሽ አልነበረውም።
ከበላያችን ብን አድርጎ ያጠፋው የእኛ መፍቀድ እና አለመፍቀድ አልነበረም። በፍጹም። እሱ ኃያሉ አምላክ የሠራው ትንግርት ነበር።
እኔ ስላለፈው ነገር ሰከንድ ማጥፋት አልፈልግም።
ይህን የተቀናቀኑ ቆሽቋሽ ዛቢያዎ ሰይፋቸውን ሳሳሉ፤ ያሰቡትም መቀብር ተልኮ ትቢያ ሆነ። ስለምን
ነበር ያ የሆነው? የዕምነት ዝግጁነት ማነስ ነበር። ለሁሉም ነገር እራስን ክፍት አድርጎ
በቅንነት፤ ለሚጠቅም ከሆነ አንተው ባለቤቱ አለህ፤ እና እንደሚሆን አድርግልን፤ ለበረከት ለሰናይ አድርግው ብሎ የልብ መሰናዶ ከፈጣሪ
ጋር ከተደረገ እጅግ መርግ የሆነው ነገር እንኳንስ አልፎ ተርፎፈ ሌላውን ሊያውክ ቀርቶ ለራስም የውስጥ ሰላምን ያጎናጽፋል።
እጅግ የሚያሳዝነው አምላክን አምናለሁ ማለቱ ለበጎ ነገር ወታደር መሆን ካላስቻለ ዕምነቱ ከዬት
ላይ ነው? ያው ማንበብ ስለምወድ ብዙ አነባለሁኝ። ቅንነቱ የጭብጭባ
ብዛት ሲኖር የአጀብ ብዛት ሲኖር ብቻ ነው።
ዛሬ ዛሬ እኔ ሳስበው አይደለም የሰው የልዑል እግዚአብሄር ፍቅርም በውስጣችን
በፍጹም ሁኔታ አለ ለማለት የሚያዳግቱ ጉዳዮች ይገጥማሉ። እምነቱ
ጽናቱ ቢኖር አንድ ሚሊዮን ህዝብ መንገድ ላይ ፈሶ ያን ያህል ጉጉስ ባልገባን ነበር። የእኔ ቤተሰብ ቢሆን ብለን ማሰብ ተሰናን
እና የሆነው ሲሆን ባጀ።
አሁንም ያሉት ጠ/ሚር ዶር አብይ አህመድ ናቸው፤ ከሦስት ወር በፊትም የነበሩት እሳቸው ናቸው
አሁን ደግሞ የሚሆነውን እያዬን ነው። ስለምን? ስለምንፈልገው ነገር ዝግጁንት ስለሚያነስን ነው።
ዝግጁዎች አይደለንም ለበጎ ነገሮች። እንኳንስ ብዙኃንን አሰለፍን ወደ ተፈለገው አቅጣጫ ለመምራት ቀርቶ እራስን ለመምራትም እጅግ
ብዙ ነገሮች ይቀራሉ።
የቅድስት ተዋህዶ እንደዛ አቅሟ መበተን ከልብ ቆርቁሮን ከሆነ ለማህበረ ምዕመኑ አፈጸጻም ላይ የሚወሰድን
ምንም ነገር የለም። በመንፈሱ ለተሰነዳ አማኝ ዋናው ቁም ነገር ቅድስት ቤተክርስትያናችን ዲያቢሎስን አሸንፋ፤ ሳጥናኤልን ረትታ እረታ በአንድነቷ
ጸንታ መቆሟ ነው። ከዚህ ውጪ ዓላማ ተልዕኮ ካለ አማኝነት እራሱ ፈተና ውስጥ ነው ማለት ነው። የተዋህዶ ልጅነትም አያሰጥም፤ የተሰጠም
ካለ ይነሳል።
ቀድሞ ነገር ቅደስት ተዋህዶ እኮ ሂደን ነው እምናመልከት እንጂ ቤታችን መጥታ ቀስቅሳ፤ ፕሮፖጋንዲስት
እንደ ገሃዱ ዓለም አሰለፍ፤ ከእንቅልፍ አስነስታን አይደለም። ልዩ የሚያደርጋትም እኛ ነን ወደ እሷ የምንሄደው። ይህ የሚያደረገው
ደግሞ የተሰጣት ፈጽሞ የማይመረመር ጸጋዋ ነው።
ስለዚህ በዚህ መንፈስ ውስጥ ላለ ትክክለኛ የኦርቶዶክስ አማኝ በአባቶቻችን እንግልት፤ ስደት፣ መከራ፣ መከፋት ምክንያት
ከፍቶን፤ እርር ብለን፤ ስናለቅስ ከኖርን ዛሬ አባቶቻችን ወደ ባዕታቸው ሲገቡ፤ ያቺ የመከራ፤ የደም መሬትም የአባቶቻችን ቡራኬ
ስታገኛልን፤ የቀረባትን ሙሉ መንፈስ ሲኖራት እኛ በአባቶቻችን ተልዕኮ
ሥራ ገብተን እምናምስበት፤ እምንፈተፍትበት ምንም ጉዳይ ሊኖር አይገባም። አይችልምም። ድርሻ ድርሻ አለን።
ዕምነት እኮ የጠረጴዛ ልብስ አይደለም። እምነት ከውስጥ መቀበልን ማጽደቅ ነው። ስጋት የሚሆነው
እርግጥም የተዋህዶ ልጅነትን ሳንቀበል ኖረን ከሆነ ብቻ ነው። ከዚህ በሰተቀር ያን ሐሤታችን የሚቀሙ ነገሮችን ሁሉ አሸንፍን አባቶቻችን
የጀመሩትን ሃይማኖታዊ ተጋድሎ እንዲቀጥሉ አቅም ማዋጣት፤ ቢያንስ በጸሎት መርዳት ይጠበቅብናል።
ሱባኤያችንም ይሄ ተኮር መሆን አለበት። የቅድስት ተዋህዶ አንድነት መቀጠል መሠረት እንዲይዝም
የኢትኦጵያን መንግሥት ሰላሙን እንዲጠብቅልን መጸለይ አለብን። ደስታ ረቂቅ ስለሆነ፤ አብሶ መንፈሳዊ እርካታ እጅግ ረቂቅ ስለሆነ
ስለማይጨበጥም አለካነውም እንጂ እንደ ገና የመወለድ ያህል የትንሳኤ ሰሞናታችን ነው። ከገድልም፤ ከታምርም በላይ ነው ክንውኑ።
አፈጻጻሙ እራሱ እሱ ልዑል እግዚአብሄር አንድዬ ቀጥ ብሎ ቁሞ እንዳስፈጸመው ማመን ይኖርብናል። ማተቡ ካለን።
ስንት መንፈስ ተብትኗል። ስንት ቤተሰብ ተለያይቷል፤ ስደቱ አልባቃቸው ብሎ ስንት ስደት ላይ
የተወለዱ ልጆች ተስፋቸውን ከፍለነዋል። ብንጠነክር ስንት ነገር መርታት ስንችል ትርፋችን ማክሳት ሆኖ ኖሯል።
ለትክክለኞቹ አማንያኖች ትልቁ ነገር ያ የጥል ግድግዳ ፈርሶ ቅድስ ተዋህዶ አንድ መሆኗ፤ ቅድስት
ተዋህዶ የተገለለችበት ዘመን አክትሞ የአላዛሯ መሪ ጠ/ ሚር አብይ አህመድ ጉዳያቸው ሆና፤ ምክንያት ሆነው፤ ተግተውበት፤ አሜሪካን
አገር ድርስ ሄደውበት፤ በራሳቸው አውሮፕላን ብፁዑ ቅዱስ አባታችን ፓትርያርከ ዘኢትዮጵያን አቡነ መርቅሪዮስ እና ሙሉውን የብዑንን
ልዑክ ይዘው አገር ቤት የገቡበት ሚሰጢረ ሥላሴ ገሃድ የሆነበትን የቅድስና ተልዕኮ፤ የምርቃት ዘመን ከእጃችን እንዳያመልጥ ልንደግፈው፤
ልናበረታታው ይገባል። አውሮፕላኑ እኮ እንደ አውቶብስ ደጃቸው ድርስ ነው የሄደው። ክብሩ ራሱ፤ ማዕረጉ ራሱ ልዩ ነው። አዲስ ታሪክ አዲስ ዘመን ላይ ነን። ትጋቱ ታቦት ያስቀርፃል አብዩ ዘመን ተብሎ።
ስለሆነም ካለሥራችን፤ ከለድርሻችን፤ ከለ ተሰጥዖችን ቅድስት ቤተክርስቲያን ከእንግዲህ ልናውካት ፈጽሞ አይገባም። እጃችንም፤ አንደበታችንም፤ ቀልባችንም
መሰብሰብ ይኖርብናል። እግዚአብሄር በሠራው ድንቅ ነገር፤ እሱ በከወነው ታምራት ላይ ምንም ዓይነት የመንፈስ ማዕቀብ
ብንጥል ተጎጂዎች እኛው እራሳችን ነን። እንቀሰፋለን።
አዬችሁት አይደል? ፈተናዋን ጅጅጋ አካባቢ በተነሳው ቀውስ ማነው የጥቃት ኢላማ የሆነው፤ ትግራይ
ላይ ያሉ አቨው ተቃዎሙ የብጹዕኑን ወደ አገር መመለስ፤ ትግራይ ላይ ጥፋት አይታሰብ በሞኞቹ መንደር ሙከራ ተካሄደ ጅጅጋ እና አካባቢዋ
ቤተክርስትያናችን ነደደ፤ ሰማዕቱም አብረው ነደዱ።
ይህን መሰል ሰው ሠራሽ ፈተና፤ ሰው ሰራሽ ክፉ ነገር ነው በጸሎት አማላካችን በመጠዬቅ ፍርዱን ይሰጥ ዘንድ መማጸን ያለብን እንጂ በአባቶቻችን በጀመሩት የብጽዕና ተግባርማ እጃችን መሰብሰብ ነው የሚኖርብን።
ውዴቼ ፈተናችን ብዙ ነው። አሳራችን ብዙ ነው። መከራችን አላለቀም። ፈተናችን ያቀለለውን መንገድን
መርጦ መጓዝ ደግሞ የራሳችን ምርጫ ነው …
የኔዎቹ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።
ወስብሃት ለእግዚአብሄር።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ