መርህ ራሱን ስላማይጥስ ያክመኛል።

መርህ የሚመራት
አገር ትናፍቀኛለች።
„መተላለፉ የቀረችለት ሃጢአቱ
የተከደነችለት ምስጉን ነው፤“
መዝሙር ምዕራፍ ፴፩ ቁጥር ፩
ከሥርጉተ©ሥላሴ
24.09.2018
ከጨምቷ ሲዊዘርላንድ።



አዱኛዎቼ እንዴት አላችሁልኝ? አማን ነውን? ዛሬ ዛሬማ ለመርዶ መንፈሴን አዘጋጅቼ እዬጠበቅኩኝ ነው። ድንገተኛ አደጋ ወይንም በሰው እጅ የተሰራ መከራ … ባጀብን>>  

አገር ህዝብ፤ ህዝብም አገር ነው። አገር ትውልድ፤ ትውልድም አገር ነው። ታሪክ አገር፤ አገርም ታሪክ ነው። ትውፊት አገር፤ አገርም ትውፊት ነው። አገር ትሩፋት፤ ትሩፋትም አገር ነው። አገር ነባቢት፤ ነባቢትም አገር ነው። ወገን አገር ነው፤ አገርም ወገን ነው። ማንነት አገር፤ አገርም ማንነት ነው ለመነሻ …

መርህ መራሽ አገር ትውልድን ቀርፆ አገር ለማሰረክብ ዋንኛው መንገድ ነው። መርህ ተከታይ ትውልድ ፈተናን የመሻገር አቅሙ ብልህ ነው። 

መርህ ብዙ ዓይነት ነው። መርህ ሃይማኖታዊ፤ መንግሥታዊ፤ ባህላዊ፤ ማህበራዊ፤ ብሄራዊ፤ ፖለቲካዊ፤ ትውፊታዊ፤ ወጋዊ፤ ሙያዊ፤ አህጉራዊ፤ ሉላዊ፤ ልማዳዊ ሊሆን ይችላል። መርህ እንደ አማኞች የሃይማኖት ዶግማ እዮራዊ ነው። 

መርህ እንደ ገሃዳዊ ዓለም ደግሞ ሰዋ ሰራሻዊ ግን ህጋዊ ነው። መርህ የህግም መንፈስ አለበት። በመርህ ውስጥ ሥርዓት በማከብር እና ባለማክበር አፈጻጸሙ ይለካል።

መርህ በጹሁፍ፤ በምልክትም ሊገለጽ ይችላል። አሁን ይህ © ምልክት የባለቤትነትን መብት ገላጭ ነው። መኪና በማሸከርክርም መርህ አለ በምልክት። የተከለከሉ፤ የተፈቀዱ ነገሮች በምልክትም ይኖራሉ ሉላዊም ብሄራዊም። 


የሰው ልጅ ምልክቶችን ሲይ ህግ መተላላፉን ተግ ያደርገዋል። ዘበኛ ኖረ አልኖረ ምልክቱ ራሱ ዘበኛ መርህ አስጠባቂ ነው። ማስጠንቀቂያም ማሳሰቢያም ነው። በዬትኛውም የኑሮ ዘርፍ መርህ አለ። 

መርህ ህብረተሰቡ ከተስማማበት ያልተጻፈ ሊሆንም ይችላል። ለምሳሌ ታላቆች ሲመጡ መነሳት የኢትዮጵውያን ባህል ነው „ኖር“ የሚለው ቃል ደግሞ ለአክበሮቱ የሚሰጥ ምላሽ ነው።

የህግ ባለሙያዎች ላይስማሙበት ቢችሉም እኔ ግን ኢትዮጵያ በተጻፈም ባልተጻፈም ህግ ሁለቱም በጥምረት የሚተገበሩበት አገር ናት ባይ ነኝ። እንዲያውም ከተፃፈው ህግ ይልቅ ያልተጻፈው ህግ የበለጠ ተጽዕኖ ፈጣሪ ነው። ህዝቡ ፈቅዶ ተስማምቶ ስለሚያደረግው አፈፃፀም ላይ ካለምንም ህግ አስከባሪ፤ ካለምንም ወጪ ተግባራዊ ይሆናል። የጣሰም ህዝብ ፊቱን ያዞርበታል። 

በመርህ ከሚተዳደሩት ሰውኛ ድርጅቶች ወስጥ አንዱ ፓለቲካ ነው። ፖለቲካ በቀላል አገላለጽ በመንግሥት ሥራ ተሳታፊነትን አምልካች ጽንሰሃሳብ ነው። በተደራጀ ሁኔታ ህዝብ ለመምራት የሚቻለው ንድፈ ሃሳቡን መዋቅራዊ በሆነ ውቅር ነው። 

ንድፈ ሃሳቡን ለማስፈጸም ደግሞ የተደራጀ አካል አስፈላጊ ነው። አሁን በአብዛኛው  ዓለም አገሮች ፖለቲካን ለመምራት የፖለቲካ ድርጅቶች ይፈጠራሉ። አንደ መረጡት የመንግሥት አደረጃጃት ፌድራላዊ ይሁን አህዳዊ።
የፖለቲካ ድርጅት ለመፍጠር ከሁሉት በላይ የሆኑ ዓላማ እና ግብ ያለቸው ሰዎች ይፈጥሩታል። 

አብሶ በሶሻሊስቱ ርዕዮት በዴሞክራሲያዊ ማዕካላዊነት የእዝ ሰንሰለት መርህ ነው ፓርቲዎች የሚደራጁት፤ የሚመሩትም። ይህ የእዝ ሰንሰለት የግል ሆነ የቡድን ነፃነት ተጫኝ ነው። 

ከመርህ አፈጻጻም ይልቅ ቀጭን ትዕዛዝ የተሻለ አማራጭ አቋራጭ መንገድ ሆኖ ስለሚገኝ ተማራጭ ነው። ጉዞውም አንባገናናዊ ዝንባሌ ያለው ነው።

ኢትዮጵያ እንግዲህ ለ50 ዓመት የዳከረችበት መንገድ ይህ ነው። የማዝነው አሁን ይህ አሰራር አብሶ በኦህዴድ በቀደመው መግለጫ ላይ ተናደ በሚል እፎይታ ላይ ብዞዎቻችን ነበርን። ኦህዴድ ብሄራዊ አቅም እንዲኖረው የተገንበት መሰረታዊ ምክንያትም ያን ወሳኔ ብሄራዊ የማድረግ አቅም እንዲያገኝ ከመፈለግ ነበር።

አሁን ከሰሞናቱ የማዬው ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ፈጦ እዬታዬ ነው። ሰሞኑን ኦህዴድ/ ኦዴፓ ጉባኤ አካሄዷል። አዳዲስ ማዕከላዊ ኮሜቴ እንደመረጠ አዳምጠናል። 

እንደ ወትሮው ቢሆን ጉዳያችን አልነበረም። አሁን ከሆነ ነፍስ አላቸው ብለን የምናምናቸው ወጣት መሪዎች ወደፊት ከመምጣት ጋር የሚታዩ ለውጦች እና ያለውን ዕምቅ አቅም በማዬት ልናደርግ የሚገባውን ሁሉ አድርገናል። 

ከሁሉ በላይ ልባችን አውርሰናል። መንፈሳችን ያለ ምንም ቅደመ ሁኔታ ሸልመናል። ስለዚህም የእኛ ብለን ሁሉን ነገር ጊዜ ሰጥተን እንከታታለን።
አንድ የማዕከላዊ ኮሜቴ ተማራጭ ለመሆን የጉባኤ አባል መሆን ይጠይቃል።

የጉባኤ አባል ለመሆን ደግሞ ከመሠረታዊ ድርጅቱ በምርጫ ለወረዳ ጉባኤ መወከል ይኖርበታል፤ የወረዳው ጉባኤ ምክር ቤቱን ሥ/ ቁጥጥሩን / ኦዲቲንጉን ይምርጣል፤ ምክር ቤቱም ሥ/አስፈጻሚውን ይመርጣል። በዚህ መልክ ውክልናው ከታች ተነስቶ ወረዳ ዞን እያለ ክልል ይደርሳል፤ የቀጥታም ውክልና ቢሆን ከታች ተነስቶ እዬተወከለ እርኮነችን ማለፍ ግድ ይለዋል።

የክልሉ ጉባኤ ሁለት ትልልቅ አካላትን ይመርጣል አንዱ ማዕከላዊ ምክር ቤትን ሲሆን ሌላው ቁጥጥሩን / ኤዲቲንጉን ይሆናል። የክልሉ ምክር ቤት ተሰብስቦ የድርጅቱን ዕለታዊ ተግባር የሚከውኑት ሥ/ አስፈጻሚ አካላት ይርጣል። 

ሥ/ አሰፈጻሚው ተጠሪነቱ ለማዕከላዊ ምክር ቤት ሲሆን ማዕካላዊ ምክር ቤቱ እና የቁጥጥር/ የኦዲቲንግ አካሉ ግን ተጠሪነታቸው ለክልሉ የአባላት ጠቅላላ ጉባኤ ይሆናል። 

ጉባኤው እስኪ ሰበሰብ ድረስ የጉባኤውን ተግባር ማዕከላዊ ምክር ቤቱ እና የቁጥጥር/ የኢዲቲንግ አካሉ ጉባኤውን ተክተው ይሠራሉ፤ ማዕከላዊ ምክር ቤት እስኪሰበሰብ ድረስ ደግሞ የክልሉ ሥ/ አሰፈጻሚ አካላት ማዕካላዊ / ክልላዊ ምክር ቤቱን ተክቶ ይሠራል። የሥልጣን ተዋረዱ በዚህ መልክ ይካሄዳል።

 የሥ/ አ/ የሚመረጠው በዬደራጃው ጉባኤው በመረጠው ምክር ቤት ነው።
አሁን እኔ ያልገባኝ የአቶ ታከለ ኡማ የአዲስ አባባ ከንቲባ ውክልና በምን አልፎ ማዕካላዊ ምክር ቤት እንደረሰ ሳይሆን የኦሮምያ ማዕካላዊ ምክር ቤት አባል የሆነ አንድ ሰው እንዴት የአዲስ አባባ ምክትል ከንቲባ ሊሆን እንደቻለ ነው። 

ፕሮቶኮሉ እራሱ ከዶር አብይ አህመድ፤ ከአቶ ለማ መገርሳ ቀጥሎ ያሉ ሦስተኛ ሰው ሆነው ነው በአቀማመጥ ደረጃ ያዬሁት።

ሥብስበባው የተመራው በኢሠፓ አሰራር መሰረት በፕሪዚዲዬም ነው። ስለሆነም ስብሰባ ከመምራት ባሻገር ደረጃው ግን እጅግ በላቀ ሁኔታ ከፍ ያለ እምርታ አለው። እዛው አዳማ ላይ ቢቀር ምንም አይደለም። አሁን እሳቸው የአዲስ አባባ ተጠባባቂ ም/ ከንቲባ ናቸው። በቀጣዩ ምርጫም ከንቲባ ናቸው። በዚህ አትጠራጠሩ። ድልዳሉ አሳምረው እዬሠሩት ነው። መርህ ሳይሆን ምኞት ነው እዬመራ ያለው። 

አሁን አቶ ታከለ ኡማ ተጠሪነታቸው በቀጥታ ለመረጣቸው አካል ለኦሮምያ ክልል ምክር ቤት እንጂ ለአዲስ አባባ ልዩ አስተዳደር ሊሆን አይችልም። መርሁ አያስኬድም። 

አንድ ሰው ወይ ማዕከላዊ ላይ ወይ ክልልላዊ፤ ዞን፤ ወረዳ ላይ መሰረታዊ ድርጅት ላይ እንጂ ራሱን በቻለ አካል ውስጥ ሁለተኛ ተደራቢ ተጠሪነት ያለው ሆኖ አይመጣም። ይህ በአደባባይ መርህ መጣሱን ብቻ ሳይሆን ጣምራ የሆነ ፍንገጣን ያሳያል። ወይንም በአደባባይ አዲስ አባባ ለኦሮምያ ክልላዊ መስተዳደር ርክክብ ተድርጓል።

ብልጦች ቢሆኑ ኖሮ አሁን አቶ ታከለን ኡማን ኦሮምያ ላይ የጉባኤም አባል ሆነ የማዕካላዊ ምክርቤቱም ተመራጭ ማድረግ፤ በተጨማሪም የፕሮቶኮሉንም ደረጃ ያን ያህል አያንጠራሩትም ነበር። 

በእነሱ እሳቤ አህጉራዊ ፖለቲካ የሚመራ ከንቲባ ስለሆኑ ነው ያን ያህል የፕሮቶኮል ጣሪያ የነካ የፕሮቶኮል ደረጃ የሠጡት። በፓርቲ አሰራር ወስጥ ሲነሪቲ እና የፕሮቶኮል ጉዳይ አንድ ብልት ነው። ወሳኝ ብልት ነው።

መርህ በጣም ተጥሷል። ይህን እንግዲህ ትግራይ ላይ ታይቷል፤ ኢትዮ ሱማሌ ላይ፤ አዲስ አባባ ላይ። የኢትዮ ሱማሌ ጉዳይ መርህ ቢጣስም አማራጮች ስላልነበሩ እና በፊትም በስተጀርባም ሌላ ተልዕኮ አልነበረውም። ያን ውስብስብ የሆነ ችግር ለመሳወገድ ድንቅ ርምጃ ነው። ለዛውም የ ሰብዕዊ መብት ተሟጋች።

 አዲስ አባባን በሚመለከት ግን ቁልፍ የሆነ ጉዳይ አለበት። ሰው ሳይጠፋ ነው ይህ የመርህ ጥሰት የሚታዬው። እነሱ ስልታዊ ብለው ያደረጉት አካሄዳቸውን ጸሐይ ላይ አሰጣው። ነገ እጅግ ያስፈራል።  

አሁን አዲስ አባባ በፓርቲ አደረጃጃት መርሆ መሠረት የኦዴፓ ሥ/ አ/ ነው የሚመራት። አቶ ታከ ኡማ ተጠሪነታቸው ለመረጣቸው አካል ለኦሮምያ ክልል ምክር ቤት ነውና። ሁለት ተጠሪነት የለምኑሮም አያውቅም በፓርቲ  የአደረጀጃት መርህ በዚህ መልክ ሲከወን ኢትዮጵያ ያልጥርጥር የመጀመሪያ ናት። ይህ መርህ መጣስ ሥርዓተ አልበኝነትም ነው። 

ለዶር አብይ አህመድ ካቢኔም ከመርህ የወጡ እርምጃዎች የሌጋሲያቸውን ቀጣይነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል። ይህ ቁልጭ ባለው ሁኔታ ዴሞክራሲ ማዕካላዊነት ካቢኔያቸው ውስጥ እዬተሠራበት ስለመሆኑ ወፍራሙ ማስረጃ ነው። በዚህ ላይ የተከበሩ ዶር ዳኛቸው አሰፋ ቅናዊ  ዕይታ አብይ "ከቅኖና እስር የተላቀቅ ግራ ዘመም ያልሆነ፡ የሚለውንም ድምዳሜ አፈር ድሜ ያስግጠዋል።  የአብይ ሌጋሲ በድርጃተቸው በቅድመ ሁኔታ የታሠሩበት አመክንዮ አለ እያልኩም በተከታታይ ጽፌያለሁኝ።

አቶ ታከለ ኡማ ከማንም በላይ ለእኔ መንፈስ ቅርብ ናቸው። የቅኔው ልዑል የብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/ መድህን ሥጋ እና ደም ሩህ ስለሆኑ ያ መንፈስ ለእኔ ታቦቴ ነው፤ ብዙ መከራንም አስተናግጄበታለሁኝ። ነገር ግን ከመርህ በላይ አይሆኑብኝ። ለዛውም የሳቸው ጠረን አሁን ላይ የብላቴው የለበትም። ኦነግ አቀበባል ላይ ሌላ ሰው ነበሩና። ይህን ሚኒያ ላይም አይቻለሁኝ። እኛን እንደ ወገን አያዩንም። ግን ስለምን? 

የሆነ ሆኖ አሁን እሳቸው በቀጥታ አመራር የሚያገኙት ከኦዴፓ ሥ/ አ/ ኮሜቴ ነው። በቀጥታ። ይህ ደግሞ ፈጽሞ ሊሆን የማይገባው ጉዳይ ነው። ኦዴፓ በምን ሥልጣኑ ነው አዲስ አባባን የመምራት እና የማስተዳደር ሥልጣን የሚኖረው? አዲስ አባባ በቀጥታ ተጠሪነቱ ለፌድራል መንግሥት ነው ሊሆን የሚገባው እንጂ የኦሮምያ ክልል ጥገኛ ልትሆን አይገባትም ነበር።

የሆነው ግን ይህ ነው። ከልዩ ጥቅም በላይ አቶ አዲሱ ረጋሳ እንደ ነገሩን አዲስ አባባ ራሷን በራሷ የማስተዳደር መብት የላትም ተፈጸመ። 

እኔ ብግሌ በሁሉም ጉዳይ ጥልቅ ጥልቅ አልልም። ሰውኛ ተፈጥሮኛ የመብት ጥሰቶች ላይ ነው አትኩሮቴ፤ ይህ ግን የመርህ ጉዳይ ነው። አሁን ለእኔ አኖሌ ሀውልት ፈረሰ አልፈረስ ጉዳዬ አይደለም፤ የጥላቻው ሐውልት አለመፍረሱ ነው ለ እኔ መሰረታዊ ጉዳጥ። አሁን ጡት እዬተቆረጠ ነው ያለው።

አትኩሮቴ ህሊና ውስጥ ያለው የጥላቻ ሀውልት ማፍረሱ ላይ ነው ሊታገበት የሚገባ ባይ ነኝ። የሆነ ሆኖ ኢትዮጵያ በመርህ ደረጃ ነገ ምርጫ በ2012 ይካሄድባታል ለማለት አዲስ አባባ ላይ ነገ መርህና ተስፋ ግብግብ ይገጥማሉ።

 የነገ የአዲስ አባባ ከንቲባ ምርጫ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በድርጅታዊ ሥራ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ናቸው። በአዲስ አመክንዮ መርህ ጥሰትም ተጠሪነታቸው ለሁለት ሲሆን አንዱ ከመርህ ውጪ ነው።  ሆርዚንታል እና ቨርቲካል የፓርቲ አወቃቀር ኢትዮጵያ ስለነደፈች እና ሥራ ላይ ስላዋለች እንኳን ደስ አለሽ ትባል¡  

መርህን ፈርተን ሸሽተን ተጋፍተን 50 ዓመት ተጉዘናል። በዚህ 50 ዓመት ብዙ ነገር አጥተናል። ትውልድ ባክኗል። አቅም ባክኗል። ጥሪት ባክኗል። አንድ መከላከያን እንደ ናሙና ብንወስድ ያለው ገመና ራሱ ገዳም ያስገባል። 

ብ/ጄ መላኩ ሽፈራው ጋር ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ያደረገው ውይይት 27 ዓመት በሁሉም ተቋም የነበረውን የሁለመና ብክነት ያገናዝባል። ነገስ?

አሁንም እማዬው ደግሞ እንዲያውም ከዛ ከኖርንበት በላይም የሚሄድ ጉዳይ አለበት። አሳዛኙ ነገር በእኔ ዕድሜ መሪ እንዲህ የእኔ ሲባል አይቼም ሰምቼም አላውቅም። በእኔ እድሜ እንዲህ ፍቅር በገፍ ሳይቆጠብ የተሰጠው መሪ አላውቅም ነበር። 

አሁን ያ ሁሉ አቅም እዬዋለ ያለው ለኦሮሞ ኢንፓዬር እንቤስት እዬተደረገ ነው። መርሃዊ ቢሆን ችግር አልነበረም፤ መርህ እዬተጣሰ። ያጠፋ የማይቀጣበት፤ ንጹሃን ግን በአደባባይ የሚረሸኑበት፤ በራሱ አካል የተጎዱትን የሚረዱ በገፍ የሚታሠሩበት። ግን ምንን እንመን? ማንን እንመን? መርህን ወይንስ የምሳሳለትን አብዩን ተለማ?

እኔ መርህን ይበልጥብኛል ከአብዩተለማ … የእውነት። ምክንያቱም አብዩተለማ ሰው ናቸው። እንዲህ ውስጤን ያቆስለዋል መርህ እዬጣሱ መጪ ሲሉ። መርህ ግን ራሱን ስለማይጥስ ያክመኛል። የአማራ ብሄርተኝነት አቆጠቆጠ ብሎ ስንት ያለው የአብይ ካቢኔ አሁን ባለው ግብረ ምላሽ በምኞቱ ልክ የቱ ይቀድምበት ይሆን ያሰኛል?

ሌላው በአፋሩ የህዝብ ጉባኤ ላይ ደርግ የወደቀው "ሰው ስለጨፈጨፈ ነው ነው" ነበር መግለጫው እኔ ያንንም ሞግቼ ነበር፤ እኔስ እላለሁኝ አሁንስ የንጹሃን ጭፍጨፋ መቼ ቆመ? ስለዚህ ሌጋሲው ስለመውደቁ ታስቦበታል ወይ ነው ቁም ነገሩ? ህግን መወገን ሁልጊዜም የፈተና ክምር መልበስ ቢሆንም ከህግ ጋር ወገኖ ማለፍን እመርጣለሁኝ - እኔ ሥርጉተ ሥላሴ።

እንደ ማሳረጊያ … በአንድ ጹሑፌ ላይ ፕ/ ኢሳያስ አፈወርቂ ልጃቸውን ከዶር አብይ ጋር የቀረበ ግንኙነት እንዲያደርግ  አቅደው ይከውኑታል ብዬ ነበር። በጂዳ ስምምነት ወይንም ውል ላይ ረጋ ያሉት ልጃቸው አቶ አብርሃም ኢሳያስ ተገኝተው ነበር። እርግጥ ነው በዛለ አንባሳም ነበሩ። ይህስ መርሃዊ ነውን?

 ቤተሰባዊ ግኝኑነት ተፈላጊ ነው፤ ከተደስትኩበት ትልቁ ነገርም አንዱ ነበር። የፕ/ ኢሳያስ ባለቤት ሰብዕና እስከ አሁን ከልቤ አልውጣም። መሳጭ ሰብዕና ነው ያላቸው። የታደሉ!

ብቻ እንዲህ በመሰለ አገራዊ ብሄራዊ ውል ልጃቸው የመገኘታቸው አምክንዮ ግን ግር ይላል። የሆነ ሆኖ ፕ/ አሳያስ አፈወርቂ ልጃቸውን በፖለቲካ አብሶ በኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት ላይ የተለዬ አቅም እንዲኖራቸው ከማድረግ ጋር የሥልጣን ውርርስ እና የልምድ ቅኝትም ታቅዶ የተከወነ ይመስላል። 

ቀጣዩ የኤርትራ ፕሬዚዳንት አቶ አብርሃም ኢሳያስ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን አብይን የመሆን ናፍቆት ያለባቸው ይመስላል ፕሬዚዳንቱ። እኔም ቀደም ብዬ የጻፍኩት ይህንኑ ነበር … የአብይ ሌጋሲን እንደ ትምህርት የማስጠናት …  ይብቃኝ፧

መርህ ይከበር!
የኔዎቹ ኑሩልኝ።
መላፊያ ጊዜ።

  

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።