ኑሯችን ኮንፓሳችን እና ካንፓሳችን ነው! መለመላ ያሰቀረ ሙግት - ተደመጠ በዋልታ።

የህሊናን ቁመና
መለመላ ያሰቀረ
 ሙግት።
„እግዚአብሄር፤ በጸሐይ ጮራ እንደ ደረቅ ትኩሳት፣
በአጨዳም ወራት እንደ ጠል ደመና ሆኜ በማደሪዬ
 በጸጥታ ተቀምጬ እመለከታለሁ ብሎኛልና።
ትንቢተ ኢሳያስ ምዕራፍ ፲፰ ቁጥር ከ፬ እስከ ፭“
ከሥርጉተ©ሥላሴ
 29.11.2018
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።

በማለዳ የመጀሪያው ጉዳዮ ኢትዮጵያ እና አብዩ እስተ ሌጋሲው እንዴት እንዳደሩ ማረጋገጥ ነው። አንዳንድ ቀን ከንጋቱ 5 ወይን 6 ሰ ዓት ላይ ሁሉ አያሁኝ መረጃ። ምክንያቱም በዚህ በሸር በዘለበ የፖለቲካ ፍልስፍና ቀኑንም ሌሊቱንም አላምነውም። ስለዚህም ከአዬሁ፤ ካጣራሁ በኋዋላ የምስጋና ጠሎቴን አድርሼ ወደ ዕለቱ ውሉዬ ጉዞ አደርጋለሁኝ ማለት ነው።

ዛሬ ደግሞ አንድ ሙግት አዳመጥኩኝ በቀደመው አጠራር የእኛ ልብ ውስጥ በነበረበት ወቅት  ከአብርሽ ጋራ። በ አሁን ደግሞ ከአቶ አብርሃም ደስታ ከ አረና ትግራይ ለሉአላዊነት ዴሞክራሲ ሊቀመንበር ጋር የዋልታ ቴቮዥን ሞጋች ጋዜጠኛ ጋር የነበረውን ውይይት ከውስጤ አዳመጥኩት። ዋው! ድንቅ ነበር።
„አብርሽን“ ይህን በመሰለ የነጻነት አርበኝነት  እናውቀው የነበረው።

Ungerecht (injustice) neue

አንድም ጹሑፍ ጽፌ ነበር የሁለት አገር ስደተኛ የሚል ዘሃበሻ ላይ ወጥቶልኝ ነበር፤ ይህ አጭር ፊልም ደግሞ ብዙ የሎቢ ተግባር የተከወነበት ነበር።

·       ወግና ቅኝት ተ ልዕልት ትዝብት ጋራ በቀለበት።

አሁን ወደ ቀደመው ምልሰት ይሁን ከወንድማዊ ዕሳቤ ወደ የፖለቲካ ድርጅት መሪነት ሰለሆነ አንቱ አቶ እያልኩ ጥቂት ትዝብቴን ላጋራችሁ ወደድኩኝ - በጥዋቱ።

ውዶቼ እኔ ቃል በቃል ለተነሱት ጥያቄዎች እና መልሶቻቸው ምንም ማለት አልሻም። ነገር ግን መሪነት እና የህሊና አቅም ካሊሙን ያዬሁበት ቅርፊቱን የለዬሁበት አጋጣሚ ስለሆነ በዚያ ዙሪያ ጥቅል የሆኑ ሃሳቦችን ማንሳት እሻለሁኝ። ይህቺ የፈረደባት አገር እንዴት ነ አውሎ እንምትናጥ አንድ ልባ ሥልዕል ቃለ ምልልሱ ስለሸለመን። በውነት ከልብ እንሰብላት ለአላዛሯ ኢትዮጵያ።

ሊንኩ ይኸው ነው -የጥዋቱ የበሩ።
ከአረና ትግራይ ለሉአላዊነትና ዴሞክራ ፓርቲ ሊቀምንበር ጋር
አዎያዩ ጋዜጠኛ አቶ ሥሜነህ ባይፈርስ ነው። ያው የቀደሙት ጥበብ ሰዋሰዎች እንዳስተማሩን ጋዜጠኛ የጥበብ ቤተኛ ስለሆነ ከእርሰው ይልቅ ቤተሰባዊ መንገዱን ተከትዬ አንተ በሚለው አቅራቢ ተወላጠ ሥም እጠራለሁ ማለት ነው። እሱም አይከፋብኝም ብዬ አስባለሁኝ።

ቃለ ምልልሱ ፖሊሲተኮር ነው። የፖሊሲ ነገር ከተነሳ ፖሊሲ የሌለው ግን ሥሙ የገነነ ንቅናቄም አለ። ግንቦት 7። አውራ ፓርቲ ሆኖ ለመውጣት ብዙ ርቀት የተጓዘም ፓርቲ ነው በለስም ባይቀናውም። ወደፊትም ህልሙ ይኸው ነው። እርግጥ ነው አሁንም ጠ/ሚር አብይ አህመድ የሰብሰብ በሉ መፈክር ለግንቦት 7 አውራ ሆኖ መውጣት ያግዛዋል ብዬ አስባለሁኝ፤ ፈቃደኛ ድርጅቶች ከተገኙ - በለስም ከቀናው።

ለነገሩ እኔ ፓርቲ አለ ብዬ አላሰብም፤ ምክንያቱም ፓርቲ ስሜቱ ቢኖር እንጂ የሚጠይቀው የአደረጃጀት መርህ በደጋፊ አባላት ብቻ ምርኩዝ ያደረገ ስለሆነ እንደ ሎቢ ተግባር ወይንም እንደ አንድ ኢቤንት ልንለው ከመቻል ውጪ የፖለቲካ ድርጅት ለማለት አያስችልም። አድካሚወን መንገድ ማንም መከተል አይሻም። የፓርቲ ሥራ ደግሞ አድካሚ ነው። በዛ ላይ ግልጽ ፕሮግራም፤ ደንብ፤ ፖሊሲ መርሃ ግብር ይጠይቃል። በሌላ በኩል  ደንብ የህይወት ሰነድ መሆኑን ቀርቶበት በፓርቲ ህይወት ውስጥ አስፈላጊ ሰነድ መሆኑን የማያውቅ አባል ተይዞ ማሸነፍ ጋዳ ነው።

በመርሃ ግብሩ በኩልም ግልጽ የሆነ የአጭር ጊዜ የረጅም ጊዜ ሊኖረው ይገባል። መካካለኛው ጊዜ ደግሞ አጭር እና ረጅም ጊዜን የሚያይዝ ድልድይ ወይንም ሊንክ ማለት ነው። እነኝህ ሦስት ሰነዶች የግድ በ አንድ ፓርቲ ውስጥ መኖር አለባቸው። ይህን ያወቀ አንቀጽ ባንቀጽ ማስተር ያደረገ ያጠና እሳት የላሰ ካድሬ ማፍራት ደግሞ አቀብት ነው። ከብረት ቁርጥራጭ የተሰራ ሰብናን ያለው አቅም ያስፍልጋል። አለመድከመን፤ አለመሰልቸትን ይጠይቃል ፓርቲ ህይወት ውስጥ መኖር። አንቱ የተባሉ መሪዎች እራሱ ችኩሎች ስልቹዎች ሆነው ነው የማያቸው። ሁልጊዜ አቋራጭ መንገድ ነው የመፍትሄ ምህንድሳቸው። 

ስለሆነም ይህን የሚያሟላ ፓርቲ የለም። ተነሳሽነት ያላቸው ልክ እንደ አንድ በሌላ የነፃነት ኢቤንት በመምራት ጎልተው የወጡ ሊሂቃና አሉ ከማለት ውጭ ለሁሉም የፖለቲካ ድርጅት ፈታኝ አመክንዮ ይኸው ነው። መበላለጥ የለም፤ መሸዋወድ ደግሞ ከእንግዲህ በዬትኛውም ዜጋ ቤተኛ የሚያደርግ የተቀለሰ ጎጆ የለውም። ጎጆ ፈራርሷል። 

በወጀብ በማግለል፤ በማውገዝ፤ ሠራዊት መባሰለፍ ዕውነትን ማዋከብ አይቻለምና። አሁን የደፋሮች ዘመን ነው። ገና ተቀብረው የኖሩ አቅም ያላቸው ሞጋቾች ይወጣሉ። ጨላማ ውስጥ አይደለነም አሁን። በቀጥታ በ አደራም በፋክስም መላክ እንችላላን፤ መሪ አለን መንግሥትም አለን ኢትዮጵያ ውስጥ። የሌለው ሥርዓት ነው። 

ለዚህ ደግሞ መሰረት ለመጣል በአገሬ በኢትዮጵያ ተስፋን የሚቀልቡ፤ የሚያስችሉ የህሊና አቅሞች በጥራት እዬተሠራበት ነው። ሌላው ልጅ  በአንድ ቀን ተጸንሶ፤ ተወልዶ፤ አድጎ፤ ተምሮ፤ ተመርቆ፤ ኤክስፐርት ሊሆን አይችልም። መሃን ሴትም መሃን ወንድም ደግሞ ከተገናኙ ሌላ ነው፤ የደም አይነትም አለ። የአርኤች ፋክተርም ጉዳይ አለ።

ይህን ጠ/ሚር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ  "ቃል ብቻ በቂ" አይደለም ብለው የሉላዊ አቅም ንግሥት ክብርት ወ/ሮ አና ጉምዝ ስለገለጡ በመጋቢት መጨረሻ 2010 ሞግቼ ጽፌያለሁኝ። ሂደት የሚጠይቁ ብዙ ጉዳዮች አሉ። እዮባዊነትን የሚሹ ብዙ ጉዳዮች አሉ። ይልቅ በእጅ ባለው ጉዳይ ህግ አክባሪዎች መጀመሪያ ይኮን። መታበይ ከህግ በታች ይዋል። 

ወደ ቀደመው ጉዳዬ ወደ አቶ አብርሃም ደስታ ቃለ ምልልስ ስመጣ ባይቀርቡ ይሻላቸው ነበር። የመሪነቱ ንጥረ ነገር ስሜት ብቻ ሆኖ ነው ያገኘሁት። ሌላ ነገር የለውም። መፈለግ እና በፈልጉት ልክ ሆኖ መገኘት በራሱ የሚጠይቀው የአቅም አምክንዮ ይኖራል።

እራሱ የድርጅቱ አንኳር አጀንዳ እና ግብ ከመርህ አንጻር ሲፈተሽ የተደራጀበት ዓላማ እና ንድፈ ሃሳቡ መታረቅ የሚችሉ አይደሉም። እራሱ አቶ አብርሃም ደስታ የፖለቲካ ት/ቤት መግባት ይኖርባቸዋል 
ብዬ አስባለሁኝ በሊቀመንበርነት ለመቀጠል። እስካሁን በሳቸው ዕድሜ ካሉ ሊሂቃን በዝቀተኛ ደረጃ ያገኘሁት የሳቸውን የህሊና አቅም ነው። 

የእሱን የሞጋቹን ጋዜጠኛ ጉልበታም አመክንዮ ጠገብ መጠዬቅ አልቻሉትም ሙግቱን። መውጫ ቀዳዳ፤ መፈናፈኛ ቀዳዳ አጥተው አዬር አልባ ነው የሆኑት። መተንፈሻ አጡ። መመከት በፍጹም አልቻሉም። እኔ እሳቸውን ብሆን ኖሮ ከዚህች ቀን ጀምሮ ለሳምሶናይት እና ለገበርዲን አቅም አለኝ ብዬ ስለማላስብ በፈቃዴ ቦታውን ለሚመክት አቅም እለቅ ነበር። አረና ብልጥ ሆንኩ ብሎ የሄደበት መንገድ የፌስ ቡክ ጀግንነት እና ወጣትነትን ነው። ነገር ግን ዛሬ አይደለም ብሄራዊው ሉላዊው ዓለም እራሱ የሚጠይቀው ሥልጣኔ አለ።

ወጣት መሆን ብቻውን አገር መመራት የማያስችል ስለመሆኑ ቁልጭ ብሎ የታዬበት አጋጣሚ ነበር - ለእኔ። በዚህ ሂደት የእትጌ ትግራይ ነገር እጅግ አሳሰበኝ - ከልቤ። ተፎካካሪው እንዲህ የተነሳበትን ንድፈ ሃሳብ መረዳት ቀርቶ፤ ሳይውቀው ቀርቶ አንሶ እንዴት ቀኑን ለትግራይ ህዝብ ለዛውም ከወያኔ ሃርነት ትግራይን ተሽሎ ችቦውን ሊያበራ እንደሚችል ሌላ ጋራ አለበት።

በፍጹም ሁኔታ አቶ አብርሃም ደስታ አቅሙ የላቸውም መሪ የመሆን። ውልቅልቃቸው ነው የወጣው። አንገት የሚያስደፋ አጋጣሚ ነበር። ትምክህት በእሳቸው ያላቸው ወገኖችም እርማችሁን አውጡ ብሏቸዋል አደባባይ ላይ ነጭ ለብሶ የዋለው አቅማቸው። መንጠራራት ባለ ነገር እንጂ በሌላ ከሆነ እንዲህ አድሮ ካልተገኜ ጋዳ ነው። በጣም ነው የተጋለጡት።
  
አንድ የፖለቲካ ድርጅት መሪ ቢያንስ በመላጣም በገጣባም ማምለጫ መተንፈሻ ቧንቧ ሊኖረው ይገባል። እሳቸው ግን አልቻሉበትም። አቅም አነሳቸው ብቻ ሳይሆን አቅሙም የሌላቸው ሆነው ነው በአደባባይ ነው የቀረቡት። መጋረጃ አልቦሽ ሆኑ።

ይህ መሰል ችግር በአቶ በቀለ ገርባም አይቻለሁኝ። ያውም እሳቸው የአገር ጠ/ሚር የመሆን ህልመኛ ናቸው። ራሳቸውንም መሾማቸውን በተለያዩ ገጠመኞች የሚያሳዩት ስብዕና ቃላት መፍቻ መዝገበ ቃላት መሄድ እንዳያስፈልገን አድርጎ መልስ ሰጥቶናል። አረማመዳቸው እራሱ ተቀይሯል። በሌላ በኩልም ኢትዮጵያ ያለው ህግ አይመራኝም ባይም ናቸው። ይህም ሌላ የተሸበለለ ቅኔ አለበት። የዚህ መንፈሳቸው በግልጠት ለማወቅ ሂደትን ማጥናት ይጠይቃል።

ብቻ አላዛሯ ኢትዮጵያ በሌለ የፖለቲካ አቅም እንዲህ በ80 ድርጅቶች ሃሳብ እዬተበተነ ትውልድ የሚበክንበትን ዘመን ለማስቆም እንደ ጋዜጠኛ አቶ ሥሜነህ ያለ የእውነት አርበኛ፤ የፋክት ባለሟል፤ ሞጋች ጋዜጠኛ ያስፈልጋታል። ሃርድ ቶኩ መፈራት የለበትም። መካሄድ አለበት። አቅም አለን መሪ ነን ከተባለ። በራስ ሚዲያ ሳይሆን በሌሎችም ሚዲያ ሁሉም በእኩልነት መሞገት አለባቸው።

በሉላዊ ዓለም የታወቁ የሃርድ ቶክ ጋዜጠኞች አሉ። በሲኤንኤን ሆነ በቢቢሲ የእኛው ጋዜጠኛ አቶ ሥሜነህ ባይፈርስ እንደዛ ነው። የዓይኑ ትዝብት እራሱ ቦንብ ነው። ከአንድ ብርጌድ ሠራዊት ይበልጣል። 
ዓይኑን ብቻ ውዶቼ በአሰተውሎት እዩት እስኪ። በንግግር ጥበብ  የእጅ እንቅስቃሴ፤ አተያይ ልዩ ዋጋ አላቸው። ፊድ ባክ የንግግር ጥበብ አንዱ ዘርፍ ነው።

በትዳር ህይወትም እኔ በጻፍኩት „እርግብ በር“ መጸሐፌ ውስጥ ዓይን ፖስተኛ ብዬ እራሱን አስችዬ ጽፌዋለሁኝ። ከዋልታ ቴሌቪዥን በላይ የጋዜጠኛ አቶ ሥሜነህ ባይፈርስ ዓይኑ ተጨማሪ ኮንፓስም፤ እንዲሁም የዓይን ቴሌቪዥን ሆኖ አግኝቸዋለሁኝ። ብዙ መልዕክቱ፤ ብዙ ውስጡን ገላጭ ስሜቶች፤ ብዙ ህሊናውን ገላጭ ፍልስፍናውን ዓይኑ ውስጥ ማግኘት ይቻላል።

ሌላው መግቢያው እና መከወኛው ደራሽ ያለሆኑ ብትፈልጉ አዳምጡኝ ባትፈልጉት ፈንግጡት ያልሆነ ያልተጋነኑ፤ አክብሮታዊ፤ ትህትናዊ ራስን ከፍ ያላደረገ የእንግዳ አቀባበል ቃናው ራሱ መስጦኛል። ከሁሉ የሚገርመኝ ከሥር ነው የሚነሳው። መረጃዎቹ ዝቀሽ ነው። ዝንቅ 
ነገሮች ሲገጥሙት የቀደሙ ዕይታዎችን፤ ጹሑፎችን፤ አቋሟችን፤ ቃለ ምልለሶችን ሲያመጣቸው መውጫ ያጡ ቃለ መልልስ ተጋባዢዎች ረስተናዋል ዘንገተነዋል አናስተውሰውም ብለው ይሾልካሉ። እጅግ የረካሁበት ውይይት ነበር።

የክብር ካባው በህሊና ብቃት ልክ ሲመዘን ደራጃው፤ ሥልጣኔው ገና የፖለቲካ ት/ቤት ጥሪኝ ይናፍቃል የአቶ አብርሃም ደስታ የመሪነት ብቃት። በአንድ ሁኔታ ሰው ይነሳል አክቲቢሰት ወይንም ጋዜጠኛ
 ወይንም ተንታኝ ይባላል፤ ከዛ ተጽዕኖ ፈጣሪ ይሆናል ግራ ቀኝ ወጀብ ሲመጣ ከማህል ቤት ቀጥ ይላል እንደ ስልክ እንጨት ሆነ ይቀራል።

 ስለምን? ከታች ተነስቶ የመጣ የዕውቀት አቅም ሳይሆን ወጀብ የሸለመው ዕውቅና ስለሚሆን። ከዚህ ዕውቅና በኋዋላ ቢያንስ ራስን ማሰናዳት የለም። ሙሉ ነኝ ብቁ ነኝ ስለሚሉ ጥረት አያደርጉም ተጽዕኖ ፈጣሪ ተንታኝ በታኝ የሚባሉት ሁሉ። በጣም ነው አቶ አብርሃም ደስታ የተጋለጡት እርቃናቸውንም ነው የቀሩት። ፈተና ላይ ወድቀዋል።

ከሰሞናቱ የተፎካካሪ/ የተቃዋሚ/ የተቀናቃኝ ፓርቲዎች ውይይት ላይ አንድም ቦታ ፈካ ያለ ገጽ አላዬሁባቸውም ነበር። ስሜታዊ ፍላጎት እና ተጨባጩ አልተገናኘላቸውም መሰል። ፊታቸውን ኮሶ እንዳሰመሰሉ ነው የታዩት ተጀምሮ እስኪጨረስ። በውስጣቸው ያለው ተስፋማ ጉዞ ተስፋ ቆራጭነታቸው የመጣው ትግራይ „ለሉአላዊነት“ና ዴሞክራ ፓርቲ …
"የትግራይ ሉአላዊነት"፤ ለነገሩ ሉአላዊንት ብሎ ማለት ምን ማለት ነው? ራሱ ሥሙ እኮ አገር ነን ዓይነት ነው። በጣም የሚገርም አወጣጥ ነው ሥሙ እራሱ።

ብቻ ይህ ምኞት በአንድም በሌላም እያመለጠ ስለመሆኑ ድንጋጤ ፈጥሮባቸዋል አቶ አብርሃም ደስታን። ባልጠበቁት ባላሰቡት ሁኔታ። ለውጡን የወያኔ ሃርነት አውራዎች እዬመሩት ማዬት ነበር ህልማቸው፤ ያው ሺ ሚሊዮን ጊዜ ኢህአዴግ ኢህአዴግ በሚሉት መጠቅለያ ካሊም።  

ያው የዛ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌሰቶም መንፈሰኛ ናቸው። ብቻ የፈሩት ይደርሳል ሆኗል ነገሩ። ከ እንግዲህ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ነፍስ ዘርቶ አውራ ፓርቲ ሆኖ የመውጣት ህልሙም አይታሰብም። አይደለም ወያኔ ሃርነት ትገራይ ከትግራይ የሚነሳ ማናቸውም ሃይል ይህን መሰል የ27 ዓመት ዕድል እና የህዝብ ግዞት ዘመን አይደገመም። ሊሆን አይችልም። የትግራይ ሃያልነት ዘመኑ አክትሟል። ይህን መቀበል ግድ ነው። 

ለውጡን ያመጣው ሃይል አማራ መሬት እና ኦሮሞ መሬት የተነሳው ተጋድሎ ነው። ራስን የገበረ ተጋድሎ እነሱንም ነጻ ያወጣ። የዚህ መሪ አካላት መሆን የቻሉትም ኢህአዴግም ቢሆኑ የዛው አካባቢ መሪዎች ናቸው። እነሱ ደግሞ አቅማቸውን ዓለም እዬመሰከረው ነው፤ ህዝቡም ተቀብሏቸዋል። 

የሆነ ሆኖ አቶ አብርሃም ደስታ የአዲሱ ዘምን ሰው ናቸው፤ ደም  በእጃቸው የለም የተባሉ ነበሩ። ነገር ግን እሳቸውም የረጋ የኩሬ ውሃ የፖለቲካ አቅም ነው ያላቸው። አንድ ነገር ከልብ ጠብ የሚል ምላሽ ለመስጠት አልተቻላቸውም። ይግርማል!

ከአጠቃላይ ብሄራዊ ማህበራዊ ንቃተ ህሊና ጋር መጓዝ አይደለም ስለመኖሩም ዕምነት ያላቸው አይመስልም። የህሊና ንቃተ የግል የማህበራዊ የሉላዊ አቅሙ ቁሞ አይጠብቅም። ይፈጠራል፤ ያድጋል፤ ይበለጽጋል፤ ያረጃል ይሞታል ሌላ ደግሞ ተተኪ አዲስ ሃሳብ እንደ ዘመኑ ይፈጠራል ይበቅላል ያሰብላል ወዘተ ሂደት ነው የህሊና አጥሚት። ይህን መቀበል ካልተቻለ መንጠባጠብ ነው በዬፌርማታው።

ይህ አጋጣሚ ለሳቸው አደጋ ሲሆን በዚህ በብዙ ቁጥር ለተዥጎረጎረው የፓርቲ ኮረጆ እና ኩረጃዊ ፋይዳ ግን አንድ ልዩ ምስል ሰጥቶናል። በግልጽ ቋንቋ አረና እራሱ ስለ ራሱ ፕሮግራሙ፤ ስለ ፖሊሲው ሰለ ዓላማው እና ሰለ ግቡ እንደገና፤ አዎን እንደ ገና ልብ ያለው ሌላ ሰው የመፈለግ የቤት ሥራ አለበት። 

ፖለቲካ የሃሳብ አቅምን ይጠይቃል። ያ የሃሳብ አቅም ደግሞ አዲሳዊነቱ ብቻ ሳይሆን የህዝብን ህሊና የመግዛት አቅሙ ጉልበታም መሆን አለበት። አሁን ከዶር አብይ አህመድ ጋር ማነጻጻር አይደለም ለተወሰነ ደቂቃ አብሮ ለመወያዬትም ዱካ ነው መንፈሱ። ሎጆክ የሚባል አለ፤ ፋክት የሚባል አለ፤ እውነት የሚባል፤ የነጠረ ሃሳብ የማመንጨት አቅም የሚባል አለ፤ ነገር አለ ከዚህ ውጪ ሆነው ነው ያዬኋዋቸው አቶ አብርሃም ደስታ። እንደዚህ እኔ አልጠበቅኩኝም ነበር። 

ቃለ ምልልሱ እንደ ከበዳቸው ሳሪሳራቸው ግትርትር ብሎ እራሱም ይናገራል።  በፍጹም ያልጠበቁት ሙግት ነው የገጠማቸው። መቼም „እኔን ያዬህ ተቀጣ፡ ነው የሆነው። እንደ እኔ አቅም ካለው ሃርድ ቶክ ጋዜጠኛ ጋር እችላለሁ ብሎ ጥያቄውን ከመቀበል እንደ ተጠቀለሉ ተሸፍኖ መቀመጥ በስንት ጣዕሙ። 

እኔ እራሴ ደነገጥኩኝ። ራሱ ሊቢራሊዝም ፍልስፍናውን አያውቁትም አቶ አብርሃም ደስታ። ሳይውቁት ነው የዚህ ፖሊስ ፍላጎት አራማጅ እና መሪ በትግራይ ለመሆን እዬታከቱ ያሉት። የመድረክም ማህበርተኛ ናቸው አይደል? ለዚህም ይመስላል በ አንቀጽ 39 ላይ አቋማች የተመሳሰለው። 

ኦፌኮን እና ኦነግ የ አቶ ዳውዱ መንፈስ ሲቃኝ እንደማለት ...ቃሉንም አልቀዬሩትም እንዳለ ነው የተጠቀሙት። ዋናው ፍሬ ነገር ምን ተይዞ ነው? አባይን ከነምንጩ መቆጣጠር ከሆነ በህልምም አይታሰብም ከ እንግዲህ። ለ አንዲት ቀን መንገድ ቢዘጋ፤ የጣና የ ኤልትሪክ መስመር ቢዘጋ ቀጥ ነው። ጥሬ ዕቃውም ምንጩም ማራገፊያውም አድራሻ ቢስ ይሆናል። አቅምን ማወቅ ይጠቅማል ከመንጠራራት።  

እያንዳንዱ የሰጡት መልስ እራሱ ቃለ ሥንኙ ነገር ቢነሳ አውሎ ያሳድራል። ማጣፊያ ነው ያጠራቸው። አልቻሉትም ጋዜጠኛውን ከምል አልቻሉትም የአንድ ፖለቲካ ድርጅትን መርህ ዲስፕሊና አመሰራረት ህግጋትን። ከአቃማቸው በላይ ነው። እሳቸው የፌስ ቡክ ውሎ መስሏቻል። 

ፖለቲካ ሰውን የማበጀት ተግባር ነው። በግብር ይውጣ እንዲህ በለብ ለብ መጪ የሚባልበት እልፍኝ አይደለም ፖለቲካ። ህይወቱን ለመኖር መፍቀድ ብቻ ሳይሆን በፈቀዱት ልክ የነቃ የበሰለ የሰከነ ህሊና ይጠይቃል

ይህ ችግር የሁሉም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ሚዲያዎችም ችግር ነው። ስለምን? ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን ነው አንግሠው ላይ የሚያወጧቸው። መሬት ላይ ከመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ተነሱ እንዲህ ሲባል የለም። የሹመት ንግግር የፖሊሲ ካልሆነ፤ ወይንም መጸሐፍ ሆኖ ካልቀረብ ይባላል። ወይንም እስረኞች  በአዋጅ ካልተፉቱ ወይንም ችግሮች በአዋጅ ካልተባረሩ ዓይነት ጉዳዮችን እንዳምጣለን። ስሜት ብቻ አንጂ መርህ ተኮር ጉዳዮች ላይ አትኩሮት የለም። አልኖሩበታማ፤ ከዬት ይመጣል። በዛ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ መሪ ከመሆን ምን ይሻል ይሆን? 

የዚህ ሁሉ ችግር ምንጩ መሬት ላይ በፖለቲካ ድርጅት የመስራት እድሉ መጥበብ ከሁሉም በላይ ኳች የለም። ሥልጠና የለም። ሰሚናር ወርክሾፕ ያስፈልጋል ለራሱ ለተፎካካሪ / ተቃዋሚ/ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች። የፖለቲካ ድርጅት መሪነት እኮ የሸቀጥ አከፋፋይነት ሳይሆን የሰው ልጅ ህሊና መሪነት ማለት ነው። ለዚህ ነው የፌስ ቡክ አርበኞች ተንሳፈው እምናያቸው።

መሬት ላይ ደግሞ ሞጋች ጉልበታም አመክንዮዎች አሉ። ማድመጥን፤ ማስተዋልን፤ ማጥናትን፤ ማሰብን፤ ማቀናጀትን፤ መመራመርን፤ ማደራጀትን፤ የእኔ ማለትን፤ ማቅረብን፤ ሰውን ማዕከል ማድረግን፤ ተፈጥሮን ማዕከል ማድረግን፤ ዕውነትን መቀበልን፤ ስህተትን ማመን፤ ከስህትት ለመማራ መመፍቀድን፤ ምህረትን፤ ይቅርታን፤ ምስጋና መስጠት እና መቀበልን፤ ትህትና መስጠት እና መቀበልን፤ አክብሮት መስጠት እና መቀበልን፤ መቻቻልን መቀበል እና መስጠትን፤ ታጋሽነትን የሚጠይቁ እጅግ በርካታ አመክንዮዎች አሉ።

የሚያሳዝነው ያን የተለፈበት፤ የተኖረበት መከራ እንዲቀጥል ነው አሁን በዬአቅጣጫው ሌሊት ሌሊት የሚለቀቀው ወጀብ። ለዚህም ነው እኔ ተፎካካሪ ብቻ እማልጽፈው ተቀናቃኝ / ተቃዋሚ እያልኩም እማክለው። መልክ ለማስያዝ በሚደረገው ጥረት እንኳን የሲሶ ያህል ቅንነት የለም።  ለእኔ ለዚህ ዘመን የተፎካካሪ የሚለው በትክክል ስለሚገልጣቸው የአቶ ሌንጮ ለታ አሁን የጀመሩት አዲስ ፈር ቀዳጅ ፍልስፍና ምርጥ ሆኖልኛል።

መንፈስን የሚያውኩ ነገሮች ላይ አይተባበሩም፤ ቀን የሚሉትን ሌሊት አይበጠብጡትም፤ እሳቸውም የህውከት ባለሟል አይደሉም። መንፈስን በጥርጣሬ ማህል ቤት የሚገተር ሃሳብ አያነሱም እሳቸውም ቤተኛ አይደሉም። ማነቃናቅ መሰቅሰቅ ተግባራቸው ሆኖ አላዬሁኝም። ከልቤ ነው አገር ቤት ከገቡ ጀምሮ  እምከታታላቸው።

ፍላጎታችን እልቀተ ቢስ፤ የመንፈስ አቃማችን ደግሞ የኩሬ ውሃ። ተመሰገን የምለው ምንም ይጎድላቸዋል የማልላቸው መሪዎች በትረ መንበሩን ስለያዙት፤ በዛ ላይ ኮ/ ጎሹ ወልዴ አገር ስለገቡ በምንም ሁኔታ ወጀቡ ቢያልም፤ ወጣገብ ማዕበሉ ቢበዛ የልዑል እግዚአብሄር የበቃችሁ ደወል ከግቡ ይደርሳል። ተስፈኛ ነኝ። በተረፈ ለሞጋዙ ጋዜጠኛ ለአቶ ሥሜነህ ባይፈርስ ድንግል እንድተጠብቅ አቅሜ ጸሎት ነው እጸልይለታለሁኝ። በርታ ወንድምአለም። 

ይህ በውነቱ ትውልዱን ከመከራ ማዳንም ነው። እንዲህ ዓይነት የመንፈስ ማጣሪያ ወንፊት ለአላዛሯ ኢትዮጵያ በእጅጉ ያስፈልጋታል። ወሳኝ ጉዳይ ይኸው ነው። ሥም እና የህሊና አቅም … ? ገናናነት እና የጉዞ አቅም? አገር በኮታ መለካት የለባትም። አገር የአዳዲስ ፍልስፍና ፈጣሪ ፈላስማዎች ብቁዎችን ብቻ ነው የሚያስፈልጋት። ስህተት ደግሞ ሰውኛ በመሆኑ መደጋገሙ በብልጠት ለማለፍ መሞከሩ እንጂ መኖሩ የተጋባ ነው። ሰው ሮቦት አይደለም እና። ለውጡም ፍጹማዊነትን አልጠብቅበትም፤ ሰዎች ነው ሞደሬት እያደረጉት የሚገኙት።፡

ኩሬ ሲቆይ ከጥቅም ውጭ ይሆናል። ውሃነቱ አዳኝነቱ ቀርቶ የጎጂ ባይረስ ተሸካሚ ይሆናል። ስለዚህ ወንፊታዊ ቃለ ምልልሱ ይቀጥል ባይ ነኝ። ሊቀመናብርት ብቻ ሳይሆኑ አለን የሚሉት አመራር አካላታቸው ሁሉ መፈተሽ አለባቸው፤ ካሸነፉ እኮ መሪ የመሆን ዕድል አላቸው።
ስንዴው ተንተርትሮ ተበጥሮ መለዬት አለበት። 

የዘለበ ካፖርት መሸከም ከእንግዲህ አላዛሯ ኢትዮጵያ ይበቃታል። በብልጠት ፖለቲከ ሰው አይበጅም። ኢትዮጵያ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሳይሆን ዕንባዋን ከውስጡ ያደመጠ ባለቅኔ፤ ባለተደሞ ስንዱ ሙሴ እንጂ የዝና ጎርፍ ገበርዲን አይናፍቃትም እናት አገር። ይህን ደግሞ እዮር አድርጎልናል። ተመስገን!  

ኢትዮጵያን ቁምነገር የማድረግ ዓላማ።

ኑሯችን ኮንፓሳችን እና ካንፓሳችን ነው!
ትውልዳዊ ድርሻችን በህብረት እና በአንድነት እንወጣ!
የአብይ ሌጋሲ ዓርትዓይናማው መንገዳችን ነው!
ኢትዮጵያ ታሸንፋለች!
የኔዎቹ ኑሩልኝ።

መሸቢያ ጊዜ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።