የልቅና የቅንነት አሳር።

እንኳን ደህና መጡልኝ።

የልቅና የቅንነት አሳር


„መከራን ያጸኑብሽ ባንቺ ጥፋት ደስ ያላቸው ይጎሳቀላሉ።“

መጽሐፈ ባሮክ ፬ ቁጥር ፲፪

ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
30.01.2019
እመ ዝምታ ሲወዘርላንድ።

 


                      የእኔ ድንግልዬ ትጠብቃችሁ!   

አንድ ዜና ተከታተልኩኝ። ለነገሩ እኔም ጠፍተውብኝ ነበር የሰነበትኩት ዶር ለማ መገርሳ። በተደጋጋሚ ታመሙ፤ ለህክማና ሄዱ የሚለው ዜና ሁልጊዜ ይረብሸኛል። ቅን ሰው የማያበረክተው ዕድላችን በምን ዓይነት ሁኔታ ይህን ዘመን ሊያሻግረን እንደሚችል ግራ ይገባል። 

 

አንድ ጠንከር ያለ ዘገባ OBN አቅርቧል። ታዩት ዘንድ ከሥር ለጥፌያለሁኝ። ይህን መሰል ተግባር የዛሬ ዓመት በትጋት ይሠራ ነበር ሚዲያው።

 

ጠ/ሚር አብይ አህመድ ከተመረጡ በኋዋላ ግን አቁሞት ቆይቷል። በዚህ ጉዳይ ቢተጋ ብዙ መንፈሶችን መሰብሰብ ይችል ነበር ሚዲያው። ይህን ዘመን ለመታደግ ይህ ሚዲያ ቁልፍ ድርሻ አለው። ስለዚህ ዘመኑን ሳያቃጥል በትጋት በዚህ መሰል ተግባር ላይ ቢያተኩር መልካም ይሆናል።

 

የሆነ ሆኖ ቅኑ፤ ትሁቱ፤ ለስላሳው የዴሞክራሲ አባት ዶር ለማ መገርሳ በርከት ላሉ ቀናት ከሚዲያ የሉም። መቼም ኦነጋውያን፤ ህወሃታውያን ያህል ጸረ ሰብ ደርጅቶች አስቀምጦ በመዘናገት የተፈጠረ ችግር ከኖረ እጅግ ሚያሳዝን ነው የሚሆነው።

 

ምክንያቱም እኔ እራሴ ከውጥኑ ጀምሮ ይጠነቀቁ ዘንድ በስፋት ጽፌያለሁኝ ህዳር ላይ ከ2017 ጀምሮ። ይህ መሰል ህፃፅ የሥልጣን ሱስ ብቻ ሳይሆን ሉዑላዊነትን ለመድፈር ወይንም ለማሳደፈር ከመጣ ህልም የመነጨ ነው።

 

ሁሉም የፖለቲካ ሊሂቃን ሳያስቡት ነው ይህን የመሰለ አቅም ፈጣሪ እዮር ቀብቶ የሰጠን። ከሊቅ እሰከ ደቂቅ የሆነው ሁሉ ለሁሉም ዱብ ዕዳ ነበር። በዚህ አዎንታዊ ዱብዕዳ ልዩ አቅም ጥርሱን ያልነከሰ የሥልጣን ራሮተኛ ማግኘት ይችግራል።

 

እናም በታቀደም ባልታቀደም ሁኔታ ይህን መሰል ችግር ይኖራል ብሎ መጠርጠሩ የተገባ ነው። እንደ እናት ጡት አደርጎ ፈጣሪ በባርኮቱ የሰጠን አብርሃም ወ - አጽባሃም እግዚአብሄር አምላክ ይጠብቃቸው ዘንድ በጸሎት መትጋት ይገባል።

 

የለውጥ ሃይል የሚባሉት አሁን ጅጅጋንም ጨምሯል ሁሎችም በቲም ለማ ፍላጎት ውስጥ አካል ተ - አምሳል የሆኑ መሪዎች ከምንም ነገር በላይ እራሳቸውን መጠበቅ መቅድም ተግባራቸው ሊሆን ይገባል። መኖራቸው ነው የሚጠቅመን። እነሱን ባዬን ቁጥር፤ እነሱን ባደመጥን ቁጥር ምን ያህል ትርሲት እንደምናገኝ ፈጣሪ ነው የሚያውቀው።

 

ውዶቼ ይህን ዶክመንተሪ ፊልም እስኪ አዳምጡት።

https://www.youtube.com/watch?v=8r6eh9sVQyo

በሰላምና በሳል አመራር ትሩፋት ላይ ያተኮረ ዶኩመንተሪ ይከታተሉ OBN ጥር 22 2011

 

ውዶቼ ታዳሚዎቼ እያዳመጣችሁ ግን አማኑኤል የምንሰማውን ክፉ ወሬ ከባህር ከገደል ይጥል ዘንድም መማጸን ይገባል።


የሥልጣን ጥመኞች፤ የዝና ሱሰኞች ለማንም ለምንም አይራሩም። ዓይነ ልቦናቸው የጥፋት መሳሪያ ነው።

 

መቼውንም ቢሆን አቅላቸውን ገዝተውም አይቀመጡም። መቼውንም ጥቃት ከመፈጸም አያታቀቡም። በመቻል ተይዞ ነው እንጂ መከራው ሥር ሰደድ ነው። ዘግተን መቀመጣችን እኮ ወደነው - ፈቅደነው  -ተመችቶን - ተፈጥሯችን ሆኖ አይደለም።

 

አንድ የወቀሳ፤ አንድ የትችት መንፈስ የማያስተናግድ ህሊና በዚህ መሰል እርቀት አቅም ኢትዮጵያ ላይም ዓለም ላይም ሲናኝ አለማበዳቸው እነሱ ሆነው።

 

ማወዳደርም ማማረጠም በማይቻልበት ደረጃና የክህሎት ልቅና ላይ ያለ የሙሴነት ትትርና ነው ያለው አሁን። እና ይህ ጤና ይሰጣቸዋልን? ይህን ደልደል ብለው ዋጥ አድርገው በአቅማቸው ልክ ራሳቸውን ገርተው ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል አደብ ይሰጣቸዋልን? አይታሰብም።  

 

ምክንያቱም በግርግር ፖለቲካ አፍርሶ አስጎርፎ፤ አደምኖ፤ አጨፍግጎ ተስፋን አቋራጭ ዙፋን መድፋት ነው። ከዛ በሃይል በመጫን እና በማስገደድ ተረግጦ መግዛት።

 

ይህን የሰነፎች ስራ የማይወዱት፤ አቅል የነሳቸው፤ የስልቹዎች፤ የችኩሎች፤ የወረት ፖለቲከኞች አሰፍስፈው ነው የሚጠብቁት። የረባ ሥራ እኮ አሁን የሚሠራ የለም ከአዲሱ አብን በስተቀር።

 

ከሰማይ መና የሚጠበቀው ሁለቱን በማስወገድ ወይንም ህውከት ፈጥሮ በማወክ በጫና የሽግግር መንግሥት ወይንም ሌላ የጉልበት መንግሥት መፍጠር ነው ህልሙ።

 

ምክንያቱም በውድድር ነገ መክኖ እዬጠበቀ ስለሆነ። የሥነ መንግሥት ላዕላይነት ምኞቱ አዬር ላይ ተቃጥሎ ስለነደደ አሁን ሌላ መላ፤ ሌላ ስልት ቀይሶ በዛ መቀጠል አይቀሬ ነው።

 

ስለሆነም የቲም ለማ ቡድን በማናቸውም ሁኔታ ሳይዘናጋ ራሱን መጠበቅ ማለት የ100 ሚሊዮን ህዝብ ተስፋ ማስበል መሆኑን ተገንዝቦ በብርቱ ጥንቃቄ፤ ብርቱ ራስን እና ቤተሰብን ጥበቃ መንቀሳቀስ ይኖርበታል። የሚታምን ማንም የለም። ጥርስ ንክሻው በዬጓዳው አለና።

 

ምክንያቱም አቅሙን ለመተቸት አቅም ስለሚፈትን። አቅሙን ለማጣጣል ማረፊያ ህሊና ስለጠፋ፤ አቅሙን ለማሳጣትም ሉላዊ ዓለም ሳይቀር ጆሮ ስለነፈገው በምን ይመካኝ? ችግሩ ይህ ነው።

 

ከአንደበት ልስልስና፤ ከሰብዕና አገነባብ ጥራት እና ብቃት ከመሪነት ድንግልና እና ጥበብ ጋር ውድድር ሲታሰብ ከበደ። ስለዚህ ሳንክ እዬፈለጉ እንቅፋት መፍጠር ግድ ሆነ። በጥልቀት ስታዩት ደግሞ ድምጽ አልባዎቹ እናቶች ዕንባ መቆም እረፍት እንዴት እንደሚነሳቸው ክፎወችን ማገናዘብ ይቻልበታል። የትውልዱ ብክነት ሐሤታቸው መሆኑ ከሰብ ማህበር በምን ያህል ያርቃቸው ይሆን? ፈጣሪስ እንዴት ያዝን?

 

 

                          ፈጣሪ ሆይ! ቸር ወሬ አሰማን! እባክህን?!



                                   የኔዎቹ ኑሩልኝ! መሸቢያ ጊዜ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።