የተመስገን አዬር ሻታ!
እንኳን ደህና መጡልኝ።
የተመስገን አዬር ሻታ!
„ፍለጋውም (ኢታምልክ) አለገኙትም፤
ልጆቻቸውም አልተቀበሉትም፤
ከህጋቸውም ራቁ። የከነዓን ሰዎች ይህን
አልሰመሙም፤ የቴምናንም ሰዎች አላዩም።“
መጽሐፈ ባሮክ ፫ ቁጥር ከ፲፱ እስከ ፳
ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
30.01.2019
እመ ዝምታ ሲወዘርላንድ።
ነባቢት!
· ጠብታ።
ቪንቲ ዛሬ ንፋስ አለ። ወጀቡ አዬል ብሏል። አንዲህ ዓይነት ወጀብ ለጤና መልካም አይደለም። እትጌም አትሞቅም እንጂ በመቁንን ለቀቅ እድርጋ ነበር እኩለ ቀን ጨረሯን … ግን በመቁንን ነው ...
· ሻታ …
ሻታ መዞር አለ። ሻታው የጤና ነው። እዮር የላከውን ተስፋ ጸበለ ጣዲቅ ይድረሳችሁ እናንት ግፉዕና እያለ ነው። የተመስገን ሻታ ቀን ሰጥቶት አላችሁን? እንዴት ባጃችሁ? ለመሆኑ ከወጀቡ፤ ከማእበሉ ከበቀሉ፤ ከቁርሾው የተረፋቸው የአገር ፒላሮች እንዴት ናችሁ? ሰው መሆናችሁን ያዬ ሻታ እናንተ ዘንድ ብቅ ማለቱን አዳመጥን ይላል የሰሞናቱ አዬር …
ኢትዮጵያ ከሰጣት መልካም ቅን ብርቱ ወጣት አንዱ ጋዜጠኛ ዮሴፍ ገብሬ ነው። መቼም እሱ የተፈጠረባት ቀን ቅዱስ ናት። ትመረቅ አይደል?! ትፈቀድ አይደል?! ትወደስ አይደል? ይገባታል ቅንነቷ ዘመን ያሻግራል እና።
በሰሞናተ ገናን ቅደመኝ ብሎ አስተርዮ ዋዜማ የአገር ዋርካ የሆኑ አንድ ታላቅ የአገር ባለውለታ ዘንድ ብቅ ብሎ ነበር ይህ ብሩክ ወጣት። እኔ የ ኢትዮጵያን ቀደምት ሠራዊቱን ነገር ሳዳምጥ እውነት ነው የምላችሁ እንባዬን መቆጣጠር እልችልም።
ንጹሑ አገራዊ ፍቅር በዛ ቤት ጽላት ነበር። ድንግሉ የቤተሰብ ፍቅር በዛ ቤት መቋሚያ ነበር። ንጹሑ የትውልድ ፍቅር በዛ ቤት ማህሌት ነበር።
ወጣቱ የወገን ተቆርቋሪ ጋዜጠኛው የቸርንት አንበል ልጅ ዮሴፍ ገብሬ ከብ/ ጄኒራል ካሳዬ ጨመዳ እና ከአርቲስት ውብሻው ስለሺ ጋር ቆይታ ዘንከትከት ያለ የማይጠገብ ቆይታ አድርጓል።
የነበረውን ቆይታ እኔ ሳዳመጥ አገር ቤት የገባሁ ያህል ነበር የተሰማኝ። እንዲህ ዓይነት ሰውኔቴን ውርር የሚያደርግ እና በአካል ከዛ ያለሁ ሆኖ የተሰማኝ ቀን በሳበውም ላስተውሰው አልቻልኩም። ብቻ ይህ ቀን ለእኔ ልዩ ነበር። ሠራዊታችን እወደዋለሁኝ። ሽው ይለኛል ሁለመናው። ጠረኑ አይገኝም እንጂ ይናፍቀኛል። አጋጣሚ ሰጥቶኝ ታጠቅም፤ ሁለታ ገነትም ጀግኖች አንባንም የመጎብኘት ዕድል ገጥሞኝ ነበር። ያ ድባብ ልቀቁኝ አይልም ነበር ሥርዓቱ እና ህብርነቱ።
አዬሩ ራሱ ቅጽር ግቢው ከሰፈራችን 603 ኮር ነበር በ7 ኪሎ ሜትር እርቀት ከሚገኘው አዘዞም 7ኛ ክ/ ጦር ነበር። በነገራችን ላይ ትናንት ሎዛ ማርያም የንግሥና ባዕሏ ነበር። አዘዞ ደመቅ ብሎ እንደሚውል ተስፋ አለኝ። የጥምቀት እርገት ያለው ከዛ ነው። የ አማራ ታገድሎ ግብርም እዛ ነበር።
· ሠራዊታችን የእኛ የፍቅር ቤት!
ሠራዊታችን የእኛ የልብ አውቃ ነበር። ሠራዊታችን መመኪያ አካላችን ነበር። ሠራዊታችን የእኛ ብርታት እና ጥንካሬ ነበር። ጠ/ሚር አብይ አህመድ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶን „አገር“ ብለዋታል። እኔ ደግሞ እላለሁኝ የኢትዮጵያ የቀደመው ሠራዊት „አገር“ ነበር። መኖር ነበር።
ፍቅሩ የእውነት፤ ተጋድሎው የእውነት፤ ቅንነቱ የእውነት ራሱን የገበረ፤ ራሱን በአገር ፍቅር ስሜት አንድዶ ዘመን ከዘመን የማገደ፤ ለራሱ ለቤተሰቡ፤ ለኑሮው የማይሰስት ዕንቁ ነበር።
የእኛ ጌጥ የኢትዮጵያ ቀደምት ሠራዊት የምንም ነገር ነጋዴ አልነበረም። ዞገኛም አልነበረም የኢትዮጵያ ሠራዊት። ዘራፊም አልነበረም የኢትዮጵያ ሠራዊት። ሌባም አልነበረም የኢትዮጵያ ሠራዊት። ጠፈፍ ያለ ድንግል እንጂ … አንድ ኮ/ ሥርአቱ ሲፈርስ ባለቤታቸው ጠላ ሻጭ ነበር የሆኑት ልጆቻቸውን ለማስተማር።
ሁሉም በዚህ መልክ ነበር ኑሯቸው ተበትኖ የቀረው። ለ ኢትዮጵያ የቀድሞ ሠራዊት ጥሪቱ አገሩ ብቻ ነበረች። ባንኩ ተዝቆ የማያልቅ የ አገር ፍቅር ስሜት ብቻ ነው የነበረው። ቀለሙ አንድ ነው የነበረው። ምኞቱ ሉዑላዊነትን አለማስደፈር ነው የነበረው። ዓርማው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የአባቶቹ እርስት ነው የነበረው።
ጌጣችን የኢትዮጵያ ሠራዊት በርሃ እዬገረፈው፤ መድፍና መትረዬስ እዬነጣው ከዛች የቀበሮ ጉድጓድ የሚልካት ደብዳቤ እንግሊዝ ቤተመንግስት ያለ ይመስል ጽናትን አርበኝነትን ለአገር ማገልግልን ቁርጠኝነት ያለውን ክብርና ሞገስ የሚቀድስ እና የሚያወድስ ነበር።
ወንድሜ ነፍሱን ይማረው እና የ18ኛው ተራራ ክፍለጦር የ36ኛ ብርጌድ አባል የነበረው ጀግናው ሃይልዬ ይጽፍልኝ የነበረው ብርታት እና ጥንካሬ እሰከዛሬ እዬመነዝርኩ አቆይቶኛል።
እሱን በህልሜ አሳዬኝ ብዬ ጸልዬ ሳዬው እራሱ ድጋፍ አገኛለሁኝ። በርሃ ላይ ሆኖ በሚልክልን ገንዘብም ተምረንበታል። ኑረንበታል። ተጽናንተንበታል። እሱም ለአገሩ ሉዑላዊነት ሲል እኔ ድፍት ክንብል ልበልላት እና አፋቤት ላይ ቀርቷል። የ አክስቴ ልጅም 19ኛው ተራራው ክፈለጦር ይርግዬም አልተመለሰም።
እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ቤት ልጅ ገብሯል። ወንድም ገብሯል። ትዳር ገብሯል። ኑሮውን ገብሯል። አብይ ሆይ! በሚለው ማመልከቻዬ የጀግና እናቶች አርበኛ ልጆቻቸው ለከፈሉት መስዋዕትነት ጡረታው ቀርቶባቸው እናመሰግናል አለመባላቸውን አውስቼ ጽፌ ነበር። አብይ የጎንደር ጌጥም ክፍል አንድ እና ሁለትም እንዲሁ የሠራዊቱ ነገር ውስጤ ነውና ጽፌው ነበር። የጎንደር እናቶችን አሳር ስጽፍ።
ስለሆነም የጀግና ብ/ ጄኒራል ካሰዬ ጨመዳን ቃለ ምልልስ በተደጋጋሚ ሳዳማጠው መንፈሴን በንጽህና ቀልቤ ነበር ያዳምጥኩት። መጽሐፉን ባገኘው እውድ ነበር። ያ የተጋድሎ ዘመን፤ ያ የአርበኝነት ዘመን ምንም ሳይሆን አገርን እንደ አገር ሉዕላዊነቷን አስጠብቆ ለመኖር የተከፈለ መስዋዕትነት ነው።
ያ መስዋዕትነት ዋጋ አጥቶ ከስሎ በኖ መቅረቱ አልበቃ ብሎ ዜጋ አይደለህም ተብሎ መኖር ደግሞ አፍ በአለው መቃብር በግዞት መኖር ነበር።
ኢትዮጵያ ለደሙላት፤ ለተሰውላት፤ ወጣትነታቸውን ለገበሩላት ትንታግ አርበኞቿ 27 ዓመት ሙሉ እቅፋን አንድትነፍጋቸው ተደርጎ ኖሯል። አሁን መልካም ዜና እዬተሰማ ነው። ያ መልካም ዜና እንደ ዜጋ ቀና ብለው እንዲሂዱ የሚያስችል የመሰባሰብ ውጥን እዬታዬ ነው። ይህ ዘመን ለራሱ ወርቅ ሐብል ያስፈልገዋል።
ያ ሌት እና ቀን በጉድብ፤ በበርሃ፤ በቃጠሎ፤ በሀራሩ፤ በውሃ ጥም፤ በቤተሰብ ናፍቆት የተገረፈ ነፍስ ዋጋው፤ እንግልቱ አንደበደል ተቆጥሮበት ድፍን 27ዓመት የወጨፎ የጨለማ ዘመንን አሳለፈ። ዛሬ ቀን ወጣልህ እዬተባለ ነው። ተመስገን።
በዚህ ፍዳ ውስጥ የኢትዮጵያ እናቶች፤ የኢትዮጵያ እህቶች፤ የኢትዮጵያ ሚስቶች፤ የኢትዮጵያ አክስቶች፤ የኢትዮጵያ ልጆች አብረው ደቃዋል፤ አብረው ከስለዋል፤ አብረው አቧራ ለብሰው 27 ዓመት ኑረዋል። የአገር ጀግና እቃ ተሸክሞ ለመኖር እንኳን አልተፈቀደለትም ነበር። መኖር በእርቦ ተሸንሽኖ በባርነት ለመኖር ሳይፈቀድለት ያ የዳጥ ዘመን አለፈ ሌላው እንዳለፈ ሁሉ …
ውዶቼ እኔ እንደነገርኳችሁ በተለያዬ አጋጣሚ ሠራዊቱን የማግኘት ዕድሉ ስለነበረኝ የነበረው ዲስፕሊን፤ የነበረው ህሊናዊ ክህሎት፤ ብቃት እና አቅም፤ የነበረው ቅናዊ ትትርና ቃላት አይገልጸውም። ድርሳን ነው።
አሁን በቅርቡ የጄ/ ብርሃኑ ጁላ ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ ሳዳምጥ እጅግ ነው ያዘንኩት የደነገጥኩትም። የእኛ ሠራዊት ብቃት ይህ ነው ተብሎ መስፈርት ሊወጣል ከቶ አይችልም። እኔ ለዛች ደቂቃ እንዴት እንደጨነቀኝ። የ እኛ ሠራዊት እላፊም አይሄድም። አንደበቱ የተራመ ወገኑን ከውስጡ የፈቀደ ነው የነበረው። በዬእያንዳንዱ ሰከንድ የሚታዬው ሥርዕታት ትምህርት ቤት ነበር። ሳይንሳዊ ስልጠናውም በአገር ውስጥም በውጭም የተማረ ነው የነበረው።
እነዛ ትንታግ መኮነኖች ሰልጥነው በህሊናቸው ዳብረው ቆፍጠን ብለው ሲናገሩ፤ ሲተነትኑ፤ መግለጫ ሲሰጡ አቤት አንዴት ያለ የመንፈስ ምግብ ነበር መሰላችሁ …?
አቅም ክህሎት ችሎታ ሳይንሳዊ ብቃት በዛ ዘመን ቀረ። እርግጥ ነው በተለያዩ እርምጃዎች ትውልድ በ200 ዓመት የማያገኛቸውን አሳጥቶናል። ተደመጥው፤ ታይተው የማይጠገቡ ምርጥ መኮንኖች ኢትዮጵያ ነበራት። እንኳን ለራሷ ለአፍሪካ የሚበቃ ማሾ የሆነ አቅም ክህሎት ብቃት ነበራት።
ዕድሜ ይንሳውና የማሌ የግራ ርዕዮት ሁሉንም የመጨረስ መከራ ሁሉም ባክኖ እንዲህ ቀረ … ያልታደለች አገር ባልታደለ በተረገም ትወልድ የራስ እንደራሴነት ተነቅሎ ተኖረ …
ለዚህ ነው በሽታው የማርክሲዝም ሌኒኒዝም የግራ ፍልስፍና ንክኪ ጋር እኛን የሚተካው ትውልዱ እንዳይገናኝ፤ አብዝቶ እንዲጸዬፈው እኔ እምማጸነው።
መጨረስ፤ መፍጀት፤ መበትን፤ ማፈረስ በቀል አብቅሎ፤ በቀል አጽድቆ፤ በቀል አስብሎ በበቀል አዬር ነፍስን ማፍነሽነ? አለመታደል። በወገንህ መከፋት ደስታ፤ በወገንህ ስቃይ ሰቆቃ ድልቂያ?ማህከነ!
አሁን ሰሞኑን ተመስገን ነው የባከነው ባክኖ፤ የሞተው ሙቶ፤ በእሳት የጋዬው ጋይቶ፤ በርሃ የበላው ተበልቶ፤ አድራሻው ከስሞ የቀረውም እንዲሁ ሆኖ አሁን ለቀሪዎች በቁም ላሉት ዜጋ ናችሁ ይባሉ ዘንድ አዲስ መሰባሰብ እዬታዬ ነው። ይህ ተመስገን ነው። ቸር ወሬም ነው።
መቼም የዘመንን ቁልል መከራ እንደ ወጉ ይመሩት ዘንድ ሃላፊነት የተሰጣቸው ጠ/ሚር አብይ አህመድ ይህን ዜጋ አይደለህም የተባለ መከረኛ ማህበረሰብ እንዴት መንፈሳቸው ያስተናግደው ይሆን ቀጣዩ ጥያቄ ነው? ለአዲሱ ለውጥ መከራን ቁሞ የቆጠረ ስለሆነ አጥር እና ቅጥር ሊሆን እንደሚችልም ይሰማኛል።
ይህ ሃይል እንዲህ ቢደራጅ፤ ቢሰበሰብ የለውጡ ሃይሎች ይጥቅማሉ። ለአገር ባላና ወጋግራ ናቸውና። ከሁሉ በላይ የእነሱ ልጆች ዜጋ ባልሆኑ ወላጆች ሥር ተበድለው ስላአደጉ አሁን ከአዲስ ትውልድ እነጻ ጋር ይህን ጉዳይ ለመንፈስ ካሳ በሚሰጥ ሁኔታ በአግባቡ ከተያዘ 27 ዓመት ቢያመልጥም ለቀሪዎች ተተኪዎች ግን የአገር ክብርን ማስከበር ክብር ስለመሆኑ የመንፈስ የጽናት ሐውልት ይሠራል። የባለቤትነት ስሜትንም ይሸልማል።
በደሉ ልዘርዝርህም፤ ልበትንህም፤ ላብራራህም፤ ልተርጉምህ ቢባል የሚቻል አይሆንም። ከሳም አይችለውም። ግን ቢያንስ አገር ማቆዬትን ያህል ዕጹብ ድንቅ ነገር የለም እና ሥርዓት ባለው ሁኔታ እናመስግናችሁአለን መባል ግን የሚገባ ይመስለኛል።
27 ዓመት ህወሃት እና ደጋፊዎቹ ዘመነው የኖሩበትን አገር ኢትዮጵያ በመኖሯ ነው። መኖሯ ደግሞ በእነዚህ ጀግኖች ደም እና አጥንት ነው። አዬር ላይ ተንሳፎ ሉዑላዊነቱን የጠበቀ አገር የለምና።
የአገር ማገር ዋልታ እና ዋቢነት በደም ግብርነት ስለመሆኑ አዲሱ ትውልድ ሊማር የሚችለው እንዲህ መሰል ታሪካዊ የግድፈት ማረሚያ እርምጃዎች ነውና። የሠራዊታችን የመሰባሰብ ውጥን እጅግ ደስ ብሎኛል።
ወላጆቻችንም ከተስፋ ማጣት ማገገም ይችላሉ ብዬ አስባለሁኝ። ለሠራዊቱ ወላጆች የመንፈስ ስብራት ጥገና ያስፈልገዋል። መንፈሳቸው ህሊናቸው ተቀጥቅጧል። የኢትዮጵያ ወላጆች አርግዘው፤ አምጠው ወልደው፤ ክልትምትም ብለው አሳድገው፤ ለአገር ሉዑላዊነት ልጆቻቸውን ገብረውም አይዟችሁን ሲነፈጉ የመኖር ስንጥቃት ነው።
በዚህ ዙሪያ የተጀመረው ጎልብቶ፤ ጥረቱ ፋፍቶ በሠራዊቱ በዬትኛውም የክፍል፤ የሃላፊነት ደረጃ የነበሩ ባልደረቦች ድካማቸው፤ ልፋታቸው ተሰባስበው አቅም ይሆኑ ዘንድ ጥረት መጀመሩ ለአርበኝነት ትውልድ መሰረታዊ ጉዳይ ነው።
እያንዳንዱ የሠራዊት አባል ውሎውን ቢናገር፤ ያለፈበትን ተመክሮ ቢያወጣው ሰፊ የሆነ ራሱን የቻለ ሙዚዬም ይሆናል። ከሁሉ በላይ ቂም ይገደላል። ቁርሾ ይሞታል። ቋሳ ይቀበራል። የምህረት የይቅርታ እና የፍቅር እንዲሁም የትህትና ዘመን ፋፍቶ ንጹህ አእምሮ ይፈጠር ዘንድም የራሱ አስተዋፆ ይኖረዋል።
ሌላው የሠራዊታችን ትልቁ ትሩፋት ለቤተሰብ አገናባብ እና አመሰራረት እንዲሁም አሰተዳደር የነበረው ሥልጣኔ ልዩ ነበር። ሠራዊታችን ለቤተሰቡ የነበረው ፍቅር እና ታማኝነት ለአገሩ ከሚሰጠው ፍቅር እና ታማኝነት ጋር እኩል ነበር። ይህም በራሱ አንድ ተቋም ነበር።
ተያያዥ ምርኩዝ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ