ዜና እረፍት እና ዕድምታው በጨረፋታ በተያይዞ።


እንኳን ደህና መጡልኝ።

ዜና እረፍት እና ዕድምታው
በጨረፋታ በተይዞ።

„ሁሉን የሚያውቅ ጌታ ያውቃታል፤
ሰማይንና ምድርን የፈጠረ እግዚአብሔር
 በእውቀት አገኛት።“ መጽሐፈ ባሮክ ፬ ቁጥር ፳፮
ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
30.01.2019
እመ ዝምታ ሲወዘርላንድ።
 ነፍስ ይማር።

·       ፍታ።

ውዶቼ እንዴት ናችሁ ደህና ናችሁ ወይ? ትናንት ብቅ አላልኩም። ለሳተናው ጹሑፎቼን በምልክበት ጊዜ እሱን እንዳላጨናንቅ ስለምሰጋ በሳምንት አንዲት ወይንም ቢበዛ ሁለት ወግ ነው እምጽፈው። ያ ለጤናዬ በጣም የሚመች ነበር። እንዲህ ብቻዬን ስሰራ ግን አገሬ ሥራ ስለሆነ ካለምንም ሰቀቀን ስለምሰራ ጫና በጤናዬ ላይ እፈጥራለሁኝ። ስለዚህ አልፎ አልፎ እረፈት ራሴን አስገድጄ እወሰዳለሁኝ። በሌላ በኩልም የሃሳብ ቀንም ታቅዶ ይከወናል።

·       ማደረጀት እና መምራት። 

ስለ ማደራጀት እና የመምራት ሁኔታ ስለ ጽንሰ ሃሳቡ በጸጋዬ ድህረ ገጽ በስፋት እንዲሁም በሌላም ጉዳይ አስታክኬ ብዙ ጽፌያለሁኝ። ከሰሞናቱ ዜና እረፍት አዳምጫለሁኝ። የጓድ ለገሰ አስፋውን። ነፍሳቸውን ፈጣሪ አምላክ በአጸደ ነፍስ ያኑር። አሜን። 

ጓድ ለገሰ አስፋው የማዕከላዊ ኮሚቴ የፖለቲ ቢሮ አባል እና የድርጅት መምሪያ ሃላፊ የነበሩ ናቸው። ስለዚህ እኔ ለሠራሁበት ዘርፍ የአለቆቼ አለቃ ነበሩ። እኔ አሞኝ አልተገኘሁም ነበር እንጂ እሳቸው በተገኙበት ስብሰባ ጓዶቼ እንደ ነገሩኝ በአንድ ወቅት በድርጅታዊ ተግባራት ላይ በሰጡት ትንተና ጠንከር ያለ አቅም እንዳላቸው በአድናቆት ነገረውኛል። የነገሩኝ ባልደረቦቼ እራሰቸው ብቁ የሆኑ ናቸው። 

በስራቸው ከነበረው አካል ጋር ግን ከፍ ሲል ከህዝባዊ ድርጅቶች እና የሙያ ማህበራት ጉዳይ ሃላፊ፤ ዝቅ ሲል ከሠረተኛ እና ገበሬ ማህበራት ጉዳይ ሃላፊ  ጋር የመገናኘት ዕድሉ ነበረኝ። ከጓድ ለገሰ አስፋው ቀጥሎ ያለው ለዚህ ዘርፍ ቅርቡ ደግሞ የጓድ አቡድላዚዝ ነበሩ። የአኔ ዘርፍ የበላይ በላይ። 

በእሳቸውም ሥርም ዬማህበራቱ አደራጆች ነበሩ። መዋቅራዊ ግንኙነቱ ጤናማ መንፈስ እንደነበረው እረዳለሁኝ። ለተለያዬ ተልዕኮም አዲስዬ ብቅ ስል እሄድ ስለነበር የመምሪያው ጤና ህውከት እንደላንበረበት አሰተውል ነበር። 

በሌላ በኩልም ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር በብሄራዊ ጉባኤዎች ላይ አብረን የመሥራት ግዴታ ስለነበረብን አቅሙ መግባባቱ መስማማቱ የሚሰጠው ግብረ ምልሻ አካሉ ጤነኛ ስለመሆኑ መረጃ ይሰጥ ነበር። የዬክፍላተ አገር አደራጆች ከድርጅት መምሪያ ዘርፍ ጋር ቁጭ ብለን የመወያዬት አብሮ የመሥራት አጋጣሚው ነበርና።

ለምሳሌ የመኢሠማ / የመላ ኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበራት/ የመኢገማ /የመላ ኢትዮጵያ ገበሬዎች ማህበር/ ጉባኤዎች ሲደራጁ ሲመሩ ሲከወኑ አብሮ ይሠራል። በኢትዮጵያ ደረጃ የክ/ ኢሠፓ ኮሜቴ የሠራተኛ እና የገበሬ ማህበራት ጉዳይ ሃላፊ ሴት እኔ ብቻ ነበርኩኝ። ወጣትም። 

ይህን ሪኮምንዴሽን የሠጠኝ በአርሲ ክ/ አገር በጢቾ አውራጃ የሴቶች ጉዳይ ሃላፊ ሆኜ በተመደብኩኝ በሦስት ወር ውስጥ ነበር የአርሲ ክ/ አገር የኢሠፓ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ አጽድቆ ለማዕከላዊ ኮሜቴ ልኮት አርሲን ለቅቄ ጎንደር ከተማና ዙሪያ በተመሳሳይ ሃላፊነት ጥቂት ወራት እንደሰራሁ ይህ ሃላፊነት የተሰጠኝ። የክ/ አገሩ የጎንደሩ ኮሜቴ ሳይደነግጥ አይቀረም። ይመስለኛል። 

ብቻ የዛ የአጭር ጊዜ የአርሲ ቆይታ ሰብላማ መሆን ምንጩ ገብሬ ያነጸው መንፈስ የትም ቦታ ችግር እንዳይኖርበት አድርጎ ስላሰደገን ነበር። የበዛ ሥራ ወዳድነትን፤ ስልትን ጥበብን ትንፋሻችን አድርጎ ነው የቀዬሰው መንፈሳችን በጥዋቱ። ቀንም እዛው አንውላላን፤ ሌትም እዛው እንድራለን እዬሠራን ዓመት ይዞ እስከ ዓመት። ሰንበት የለ አውዳመት የለ።

ራሱ መታወቂያው የሆላው የስሜን ጎንደር ክ/ አገር የህዝባዊ ድርጅቶች እና የሙያ ማህበራት ጉዳይ ሃላፊ የሆንኩበት ሳይሆን የጎንደር ክ/ አገር የሠራተኛና የገበሬ ማህበራት ጉዳይ ሃላፊ የሆንኩበት አለ አብሮ ከእኔ ጋር በስደት አገር። በክ/ አገር ደረጃ የተመደብኩባቸው ሁለቱም የሃላፊነት ቦታዎች ደብዳቤዎችም አሉ አብረውኝ።
  
ወደ ቀደመው ስመለስ ለሠራተኛ እና ለገበሬ አገራዊ ጉባኤ ስንገናኝ አንዲት ቀጫጫ ግን ቀልጣፋ እና ንቁ ቀንበጥ ከ13 ተባዕት የክ/ አገራት አደራጆች ጋር ከማዕካላዊ ኮሚቴ ቀጥተኛ ተጠሪዎቻችን እና  ሃላፊዎቻችን አክሎ አብረን እንሰበሰብ ነበር። ታጠቅን የሰንደቅዓላማ አድባርን ያን ታሪካዊ የአገር አድን ትውፈታዊ ማሰልጠኛ እማውቀው ያን ጊዜ ነው። ታጠቅ የክፉ ቀን ያወጣ፤ ለሲያድ ባሬ ሎሌነት ያላስገዛን እራሱም አገር የሆነ የትውልድ ጉልላት ቅርስ ነው።
  
የአገር አቀፍ የገበሬ ማህበር ጉባኤተኞች ያረፉት ከዛ ነበር። የቡድን መሪያቸው ደግሞ እኔ ነበርኩኝ። በዛን ጊዜ ለኢትዮጵያ የገበሬዎች ማህበር ጉባኤ የገበሬ ሴት የጉባኤ አባል ሁሉ ይዤ ሄጄ ነበር። ለሴቶች ትንሽ አዳላለሁኝ የተለዬም አትኩሮት አለኝ። ካልቸገረኝ በቀር ሴቶች አቅም ከኖራቸው ቦታውን እንዲይዙ እሻለሁኝ። አጋጣሚውን አሳልፌ አልሰጠም።

ለዚህ ነው ለወጣት ንግስት ይርጋ የተለዬ ፍቅር እና ስስት ያለኝም፤ አድርጌው የማላውቀውንም እንድፈጽም የተገደድኩበት ምክንያት ይኸው ነበር ሚስጢሩ። ወደ ቀደመው ምልስት ሳደርግ ታጠቅ የገባነው ማታ ስለነበር እጅግ ፈታኝ ነገር ነበር የገጠመን አብሶ ለሩቅ ተጓዦቹ። 

ለእያንዳንዱ ጉባኤተኞች የተሟላ አገልግሎት ማግኘታቸውን መቆጣጠር የአደራጆች ሃላፊነት ነበር። በዛ ዕድሜ ነው እንግዲህ። ከዛ ባለፈ ደግሞ ጉባኤው ስለሚከውናቸው ተግባራት ደግሞ ማዕላዊ ኮሜቴ ላይ ቁጭ ብለን ለዋናው ጉባኤ አብረን የመንሥራቸው በርካታ ድርጅታዊ ተግባራት ነበሩ። ይህን አጣምሮ ለመከወን ዛሬ ላይ ሳስበው ምን ያህል በዛ ዕድሜ ያን መሰል ሁለገብ ሃላፊነት ለመቀበል አቅም እንደነበረኝ ህልም ነው የሚመስለኝ። ይህ በገበሬው ነው።

በሠራተኛው ደግሞ ሌላ የተነባባረ ሃላፊነት ነው። ሠራተኞች በቀጥታ ከክፍለሀገራት የሠራተኛ ማህበረት ተውከለው ለማዕከላዊ ጉባኤ ከሚመጡት ባሻገር 9 የኢትንደስትሪ ማህበራት በ9 አዳራሽ ዬዬራሳቸውን ጉባኤ በማካሄድ የ9 ኢንደስትሪ ማህበራትን ማዕካላዊ ምክር ቤት ለብሄራዊ ጉባኤ የሚወከሉ አካልነት ይመርጣሉ። 

በእኔ የቡድን መሪነት አብረን በ አንድ አውቶብስ እንሄዳለን የ9 የኢንደስትሪ ማህበረት አገራዊ የጉባኤ ተሳታፊዎች። ስብሰባ የሚሳተፉት ግን በዬኢንድስትሪ ማህበራቸው በተለያዬ አዳራሽ ይሆናል። በዚህም የኢንደስትሪ ማህበራት የክ/ አገሩን የወከሉ የባንክ እና ኢንሹራንስ፤ የመብራት፤ ጋዝ አና የሃይል ማመንጫ፤ የኢንደስትሪና የፋፍሪካ ከማስታውሳቸው የጉባኤ አባላት መሪዎች የሆኑ ለጉባኤም የተወከሉ አካላትም ሴቶች ነበሩኝ።

እንግዲህ በ9 የጉባኤ አዳራሽ የሚሳተፉ፤ በሌላ በኩልም በቀጥታ የተወከሉ፤ በተለያዬ የማረፊያ ቦታ ያረፉ ናቸው በዬጉባኤ አዳራሻቸው በሰዓት ደርሰው ጉባኤውን እንዲሳተፉ፤ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ፤  መወከል ካለባቸው ቦታ እንዲወከሉ ለማድረግ መራወጥ ነው።

 እንደገና በማዕከል ላለው ብሄራዊ ጉባኤ ደግሞ ዝበት እንዳይኖር ሁለመናን በተደራጀ ሁኔታ መምራት ለኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሜቴ ለሠራተኛ ማህበራት ጉዳይ ሃላፊና ለበላዩ ለዘርፉ የተሟላ መረጃ መስጥት ግድ ይላል። 10 ቦታ ማሰብ ማለት ነው።

በጋራ ሥለምንሠራ 14 አደራጆች አንዳንድ ጊዜ ውክልና ሳያገኙ ሥማቸው ለማዕከላዊ ተላልፎ ግን በውክልና ጉባኤ ላይ እንዲገኙ ያልተመረጡ ሰዎች ይገጥማሉ። ይህን አንዱ ፍስት ጠቅላላ ሁኔታውን ያናጋል። የእቅዱን መዋቅር ያፋልሰዋል። 

በዬወንበራቸው ሥማቸው ይቀመጣል፤ የሚታደሉ ነገሮች በስማቸው ነው የሚዘጋጀው፤ የመግቢያ ባጅ እንደዛው በዛው ሊስት ቅደም ተከተል ነው የሚደራጀው። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ የገበሬ ማህበራት የሠራተኛ ማህበራት ሆነው የኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና ተለዋጭ አባል የሆኑ ደግሞ የፕሮቶኮል አደረጃጃት ደግሞ በልዩ ሁኔታ የሚስተናገድ ነው።

ሌላም ገጠመኝ ደግሞ „ጎንደሮች ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋል“ እንዲሉ በሌላ በኩል አደራጆች ያቀረቡትን ተዘሎ ድርጅት ጉዳይ ያቀረቡትን አደራጆች እንዳቀረቡት ሆኖ በክ/ ሥ/አ ኮሜቴ ጸድቆ ለማዕከል ከተላለፈ፤ አዳራጁ መረጃው ከሌለው ቦታው ተነሳፋፊ የመሆን ዕድል ይገጥማዋል። 

በዚህ ላይ ጓድ አብዱላዚዝ ኮሰተር ያለ የመወስን አቅም ነበራቸው። በነገራችን ላይ ጓድ አቡድላዚዝ የዬካቲት 66 ፖለቲካ ኢንስቲቱዮት ምሥራታ እና አመራር ሰፊ ድርሻ የነበራቸው ነበሩ። እኔ እንዲያውም እዛ ነበር የማውቃቸው። በአስተዳደር ብቻ ሳይሆን የፍልስፍና መምህር አንዱ እሳቸው ሁለተኛው መምህር ደምሴ ነበሩ።

ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደረግ የክ/ ድርጅት ጉዳይ ሃላፊ በክ/ ኢሠፓ የገበሬ እና የሠራተኛ አደራጅ ያቀረበውን ጥሶ ወይንም ከአደራጁ ጋር ስምምነት ሳይፈጥር በራሱ መንገድ የራሱን ፍላጎት ለሥ/አሰ/ አቅርቦ አጸድቆ ለማዕካላዊ ከላከ በሁለት መንገድ ውድቅ ይሆናል።

ይህ ማለት ሥ/ አስፈፃሚ ላይ ሥሙን ብቻ አስወስኖ ሊስቱን ቢልክም አደራጁ ካላወቅ ውክልናው አስጠብቆ ከታች ወደላይ ላያመጣለት ይችላል መረጃ ስለማይኖረው አደራጁ፤ ሁለተኛው የፈለገው የሥ/አሰ ከሜቴ ያን ይወሰን የተቃርኖ ሃሳብ ከአደራጁ ከቀረበ ጓድ አብዱላዚዝ አደራጆቻቸን ለምስል አይደለም የምንመድባቸው ስለሚሉ ከክ/ ሥ/ ኮሜቴ ይልቅ የተመደበው አደራጅ የበለጠ ስለሚያደራጃቸው፤ ስለሚመራቸው ድርጀቶች ሰብዕና ብቃት ያውቃል ተብሎ በጽኑ ስለሚታምን የአደራጆች ሪኮመንዲሽን ዕውቅና በሙሉ ድምጽ ይለፍ ይሰጠውና እና ለክ/ ፓ ኮሜቲ እንዲያውቀው ብቻ መረጃ ይሰጠዋል። 

በዚህ አግባብ የክ/ አገር ድርጅት ጉዳዮች የመንፈስ ቅጣት ይደርስባቸዋል፤ ለአደራጆች ደግሞ የልብ ልብ ይሰጣቸዋል ማለት ነው። ደግሞም ትክክል ነው።
  
አሁን ዛሬ ላይ ሁኜ የማዕከላዊውን የድርጅት ዘርፍ ወይንም ከፍተኛ አካል የመምሪያ ሃላፊ ሳስበው ለበታች አካላቱ የአመራር እርግጠኝነት እና በራስ የመተማምን አቅሙ ሙሉ ነበር ማለት ያስችለኛል። 

በበላይ አካላችን በመመሪያችን የማዕላዊ ድርጅት ጉዳይ መምሪያ ሃላፊ ጓድ ለገሰ አስፋው በበላይነት ይመሩት ነበር። አደራጁ ሳያውቅ የክ/ አ/ የፓርቲ ሥ/ ኮሜቴ የወሰነውን አንዲህ አይነት የግድፈት ፈሰስ ሲገጥም እዛው ላይ ቁርጥ ያለ መልስ የመስጠት አቅምን አመራሩ ድርጅታዊ ማዕከላዊነት ቢኖርበትም መወሰን ባለበት ጉዳይ ግን የአደረጃጃት መርሁ ድርጅታዊ ማዕከላዊነት ማነቆ እንደማይፈጥር እኔ ገጥሞኝ አይቸዋለሁኝ።
በሌላም የዚኸው ክፍል አካል የሆነው የአባላት ምዝገባ እና ዘገባ ስልጠና ዋና ክፍል ጋርም በተለዬ ሁኔታም ግንኙነት ነበረኝ። 

ጓድ አንግዳ የሚባል ንቁ ወጣት ነበር። ስታዩት ራሱ ዲስፕሊን ነው። የእኔ አቻም በዚህ ዘርፍ በቀጥታ ይገናኝ ስለነበር ክ/ አገር የሚሠራው በፍጹም ሁኔታ ይረካበት አንደነበር ይነገረኝ ነበር። ማዕከላዊ ደውለን ተቸግረን አናውቅም። ቀልጣፋ መልስ ከሙሉ አክብሮት ጋር ነበር። በጠቅላላ ዘርፉ ጤነኛ ነበር ማለት ያስችለኛል። በቀጥታም በዬሦስት ወሩ ዘገባ እናቀርብም ነበር።

ስላለፈ በብዙ መልኩ በኮሶ ስለተጠቀለለ የነበረውን አቅም ማዬት እንዳይቻል በሃራስመንት ቢከስልም ግን አንዴት የተደራጀ ጉዳይ አንዳነበር ቃላት ከሚገልጸው በላይ ብቁ ነበር። የኢህአዴግ ያለፈውን ዓመት አስልቺ ከመርህ ውጪ የሆነ የ18 ቀን ስብሰባን በሚመለከት „ሙርቅርቅ“ በሚል አንድ ጹሑፍ ጽፌ ነበር።

የውጭ አገሩ ማንሳት አይቻልም። ምኑ ከምኑ ተሁኖ። ከጫፍ እንኳን አይረስም። አይደለም ፓርቲ ለማለት የፖለቲካ ድርጅት ለማለትም አያችልም። በመደዴ ድርጀት አይደራጅም፤ በደዴም ድርጅት አይመራም፤ በመደዴም አባላት አይመራም፤ በመደዴም ለአባልት ግዳጅ አይሰጥም። በመደዴም ውክልና ሃላፊነት አይሰጥም።

ጦርነቱ የእርስ በእርስ ስለነበረ ህዝብ የማይፈቅዳቸው መመሪያዎች በማጸደቅ እና እርምጃ በማስወሰድ ኢሠፓ ከባህር የወጣ አሳ ሆኖ ለዘር ሳይበቃ መራራ ስንብት እንደ ቅንጅት ገጠመው እንጂ አንቱ የነበሩ ልብ ሞልተው የሚያናግሩ የድርጅታዊ አቅም፤ ጥንካሬ ብርታት እና ጥንቁቅነት ነበር በድርጅታችን በኢሠፓ። 

ብዙ ሰው ውጪ አገር ሲወጣ ይሸሽጋል። ምን አሳፍሮ ነው የሚሸሸሸው? እኔ እኮራለሁኝ በዛ ነፍስ በሆነ፤ ነፍስ በመነበረው ፓርቲዬ በ ኢሠፓ ማደጌም መስራቴም። ኑሮዬን እምመራው እራሱ በዛ ጥሪት እና እርሾ ነው። ጥሪቱ አያልቅም። ጥሪቱም አይጠወልግም አይጠነዝልም። እዬሻተ ነው የሚሄደው። ከሁሉ በላይ ሠርተን አይደክመነም፤ ዝርክርኮችም አይደለንም። ኑሯችን በተሰጠን፤ በተፈቀደለን ልክ አሳምረን፤ አስውበንም እንመራለን። 

በዛን ጊዜ የእኛ አይደለም ለፓርቲው ለኢሠፓ ማዕካለዊ ኮሜቴ ይሁን ኦዲት ወይንም የቁጥጥር እና የዲስፕሊን ኮሚቴ ስብሰባ ቀርቶ ለማህበራት ጉባኤዎች አንዴት ጥንቁቅ፤ እንዴት የተደራጀ ተግባር ይከውን እንደነበር መጸሐፍ ነው ማለት እችላለሁኝ። 

አጅግ የሚገርም እጅግም የሚደንቅ ብቃት ነበር። መሰናዶው የሚገርም ነው የነበረው። በረጅሙ ነው የሚታቀደው። ሰፊ ጊዜ ተወስዶ ነው የሚጠናበት በዬአንዳንዱ ነጣላ ጉዳይ። ሲናሪዮው ቢጋሩ … ስንቱ ነገር ... 

በፈለገ ሁኔታ ጥያቄ ቢቀርብ አንጀት ጉበቱን አውጥተን ነበር ማብራሪያ የምንሰጠው። ክህነቱ አንቱ ነበር … ለዚህ ነው ውጭ አገር የሚሆነው ነገር ሁሉ ስለማይገባን ልንግባባ ሳንችል የቀረነው። በጠላት ተፈርጀንም አሳራችን ያዬነው … አሳሩ ታሰረን እንደንቀር አድርጎናል እኔ አሁንም እስር ቤት እንዳለሁ ነው የሚሰማኝ። ተጫኑን። ቀጩት። አቅም የለምና።

አሁን ተሰሞናቱ ስለ መክሊት ፈቅዶ መሰጠት ጠ/ሚር አብይ አህመድ ሲናገሩ አዳመጥኩኝ። ከካቴና ውጭ ላለ መንፈስ ይህን ቢናገሩ ያመራል። የእኔ 7 መጽሐፍቶቼ መጋዝን ያሞቃሉ፤ እርማቱ ያለቀው 8ኛው መጸሐፌ ሚሞሪ ላይ ነው ለሽ ብሎ ተኝቶል።  ተጀምረው ያላለቁ ኮንፒተር ላይ፤ በእጅ የተጻፉ በኮንፒተር ያልተገለበጡ ብዙ ሥራዎች አሉ። 

ምን አይቼ ልጨርሰው፤ ምን አይቼ ላሳትመው? ከዚህ ውጭ ስንት ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን አቋቁሞ መምራት ይቻል ነበር። ሌላው ቀርቶ ስደት ላይ ተወልደው ለሚያድጉ ልጆች የተደረጃ የባለቤትነት ተግባር መከወን ይቻል ነበር። አቅሙ ከታጠረ በዜት ታልፎ? ስለሆነም መስጠት ታስሮ እንደታሠረ መቃብር ይወርዳል። ይህን ደግሞ ይጠብቁት። ያዩታል። 

ሌላው ቀርቶ መጣጥፍ አንድ ጹሑፍ ሳይወጣ ሲቀር አቅም የለኝም ቀጥዬ በሌላ ጉዳይ ላይ ለመጻፍ። ሌላ ጊዜ ሌላ ጹሑፍ ጽፌ ለመላክ ለመጻፍ ቢያንስ 6 ወር መጠበቅ ግድ ይላል። በጅ አይልም ህሊና። ይኮረኮዳል። እህ> እህ/ እህ‘እጬጌውን መስጠት ፈቅዶ፤ ወዶ መስጠት? ከቶ እንዴት ይቻል „መስጠት“?

ቀን ላወጣቸው ለእድለኞች አብሶ ለታደሉ እናቶች በልጆቻቸው በረከት፤ በልጆቻቸው ለትወልድ የሚተርፍ ቅርስ ትተው እንዲያልፉ ለተፈቀደላቸው እነሱ ይደሰቱ፤ ለእኔይቱ ክልታሜ አሳረኛ እሙሃይ እብዬ ግን ዘመኗን ሁሉ እንዳዘነች እሷም እኔም እናልፋለን ብክነትን ተደምመንበት - በወናነት። 

እሙሃይ እብዬ አዝና ኩርምትምት ብላ ከቶ የኔይቱ ምን አጉድላ ይሆን? ይህን የመሰለ ሳሃ - መከራ - ፍዳ ተሰዳ በስደቱ ቀዬ የተበዬነባት ብላ በቆቧ ዕንባዋን አጠራቅማ እዬር ትልከዋለች …
  
አሁንም በዛ ገመና ሳይፈታ በዬአካባቢው ይፍታችሁ እንዳንባል ሆነን እንደ ተቀፈደድን እንደ ታሥረን ያለው አቅም በካቴና፤ በሰንሰለት፤ የሥማችን መቅኖ መንፈሱም ሳይቀር፤ አቅሙም ክህሎቱም እንዳሰሩን እነሱ አብሮ በመደመር መኖራቸውን አይተናል፤ በክብር በልዕልና፤ በጭብጨባ - በሽብሸባ፤ በወረብ በደመቀ ዕውቅና በሙገሳ በግርማ … በካባ በተክሊል --- 

ከአነ ቂም በቀል ቅል ቋንቁራቸው  ብቅልና ጌሾው ሃሞቱ እንደተጠነሰሰ ሳይጠመቅ - ሳይፈታ፤ ሳይፍታታ፤ የበደሉትን መንፈስ ይቅርታ ሳይጠይቁ፤ ያቆሰሉትን ሳያሽሩ እንደበታተኑት እንደተሸፉን እንደ ተሸበለሉ እንደተጠቀለሉ አሸብሽቡላቸው ስንባል፤ እግዚኦም አለን ሱባኤም ገባን። ፈቺም ፍቺም የለውም። አለመገደላችን ግን ፈጣሪን እናመስግነበታለን። ቢያንስ በ እሱ በፈቀደው በተጠራን እለት ለመሄድ ስንፈቅድ ራሳችን ከብዙ ነገር አቅበን፤ አስረን ከትረን ነው። ዘልዛለ ብንሆን አንሰነብትም ነበር። ሞታችንም ደመ ከልብ ይሆን ነበር። ይህን የምጽፈው ከምር ነው - ኑዛዜም።  

ወደ አዲሱ ፍልስፍና ምልስት ስናደርግ እንዴት አድርገን አለፍ አድርገን ነገ በምን መልክ ለመስጠት „መስጠትን“ እንተርጉመው „የመስጠትን ፍልስፍና ራእይ በምን ቀመር ቤተኛ ይኮን“ ? መልስ የለውም። ድፍን --- ድንብልብል ጠፍጣፋ ---- ልሙጥ ነው። ለመልሱ ጥንዝሉ ውይብ ድንኳኑ ማዕልተ ሌሊቱ ጥቁር በጥቅርሻ አቅላማት የተጠቆረ ነው። ሥማችን ያነሳ እኮ ወንጀለኛ ነው። እንኳንስ ጹሑፋችን ያወጣ፤ ለዚህ እኮ ነው ሳተናውን ጀግናዬ እምለው። ሁሉ ቦታ ማለፊያ የለም ተቆልፏል። 

ወደ ቀደመው እንደ አባቶቼ ስመለስ በድርጅት ጉዳይ መመሪያችን የነበረው አቅም እኔ ግድፈት የምለው፤ ክፍትት የምለው፤ ዝበት የምለው አንዳችም ነገር አልበረም። በጣም የተደራጀ ህሊና ነበር።

ፓርቲውን ያፈረሰው ዓለም አቀፍ በሆነው የዘመኑ ባህሪ ለውጥ እና አገራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች የማድመጥ ማዕላዊነት አቅም ገራራ መሆን እና ጦርነቱ የሰርገኛ ጤፍ የመሆኑ ሚስጢር ነው እንጂ የድርጅቱ አቅም ማጣት አይመሰለኝም። ከዛው አብረው የነበሩት እኮ ናቸው አሁን እንደምሰማው ኦነጎች ነን ብለው የውስጥ አርበኞች አብረው የተጣመሩት። አሁን ለውጡ ላይ ያለው መከራም ይኸው ነው። እነሱው ናቸው አሁንም እያንገረገቡት የሚገኙት። 

·       የመክሊት ልዩነት። 

በሌላ በኩል ለስኬት አለመብቃትን እኔ በግሌ ሳስበው ክ/ አገር ላይ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊዎች ከሰው ሰው ሊለያይ ይችላል። ከመክሊት መክሊትም እንዲሁ። የድርጅት ሰውነት እኔ በሙያ ብቻ አለካውም ሥጦታም ነው የሚል አቋም ነው ያለኝ። አድራጅነት መክሊትም ነው። ለቁንጥንጥ፤ ለችኩል፤ ለወረተኛ፤ ውጤት ተሎ ለማዬት ስክንት ለጎደለው ሰብዕና ሆነ ከላይ ከላይ ለሚፈላ የቱማታ ቤተኛ፤ በስሜት ለሰከረ መንፈስ አይሆንም።

ሥልጠናውም ቢኖር፤ የመመደቡም ዕድል ቢኖር። የድርጅት ሰው ሰውን አምጦ የመውለድ ሰብዕና ይጠይቃል። አብዝቶ መቀመጥን፤ አብዝቶ ማሰብን፤ አብዝቶ መቀዬስን አብዝቶ ምህንድስና ይጠይቃል። እውነት መሆንንም። ማደራጀት ጥበብ ነው ለእኔ። መንፈስን እንጂ አካል አይደለም እና እምታደራጀው። ለድርጅት የተፈጠሩ ሰብዕናዎችም ፈጣሪ የሰጣቸው አሉና። ተለይተው ነው የሚፈጠሩ፤ ስልቹዎች ቂመኞች፤ ጥድፈኞች አይደሉም ጸጋው፤ ክህሎቱ ያላቸው። በመናድ በማፈረስ ሳይሆን በማጠናከር፤ በመግንባት ላይ አትኩሮታቸው። 

በብሄራዊ ደረጃ ማዕከላዊ ላይ ወጥነት የነበረው ሙሉ አቅም ነበር። ዝም ብሎ ምደባ የለም። ሥልጣና አለ። በአዳዲስ መመሪያዎች ላይም ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስት ቢሮዎች ይኖራሉ ማብራሪያ የሚሰጡ በእያንዳንዱ ቅፅ ሰነድ ላይ … ሰውን አብቅቶ መፍጠር፤ ክህሎቱን አበጅቶ መቅረጽ እኔ በፓርቲዬ የኢሠፓ ሰፊ አትኩሮት የነበረው መሆኑን ነው እሚገባኝ።

በተደጋጋሚ ጊዜ እንደገለጽኩት እንደ ጓድ ገመድህን በርጋ አይነት ሙሉሰው ያገኜ ዕድለኛ ክ/ አገር ደግሞ መተከል ነበር። ለዚህ ጎንደር፤ ጅማ፤ ሚዛን ተፈሪ ዕድለኞች ነበሩ። ጓድ ገ/መድህን በርጋ የአገር ውስጥ ንግድ ሚ/ር ቋሚ ይሁን ምክትል ቋሚ ተጠሪም የነበር ይመስለኛል፤ የሠራ አክላቱ ድርጁ የሆነ የመንፈስ ሰነድ ነው። ተፈጥሮውም ድርጅት ነው። በማዬት ነው ሰውን የሚመርጠው። ከመረጠ በኋላ መንፈሱን ያረብበታል።

የእሱ ተፈጥሮ የረጋ ድንጋጌ ነው። ህገ ድርጅት። ድንጋጌው ደግሞ የሰውን ሙሉ አካል ለተፈለገው ተልዕኮ አሳምሮ ዘመን ተሻጋሪ አድርጎ፤ በተሟላ ስብእና  በእርግጠኝነት በቋሚነት መንፈስ የሚቀርጽ። ገብሬ እንዴት ሰብዕናን ይገነባ እንደነበር ዛሬ ሳስበው ጥበብ ነው። የልብ አምላክ ዳዊት ምስባክ አዬነትም ነው።

በዛ ድርጅት ውስጥ ትልቁ የድርጅቱ ተልዕኮ ሰብዕናን በሁሉም መስክ አብቅቶ ማስከን ነበር። እርግጥ ነው እንደ የሚመደቡት አካላት ብቃት ተፈጥሯዊ መክሊት ይለያያል። ጎንደር በዚህ አረገድ ዕድለኛ ነበር። አብሶ እኔ እድለኛ ነበርኩኝ። ከእነዛ የአገር ዕንቁዎች ጋር ለመሥራት መታደሌ እንደ ስለት ልጅ በምታይበት የመንፈስ ቤተኝነት ጭምር መሆን በራሱ ራሴን የሰጠኝ ሽልማቴም ነው። 

እርግጥ ነው ጓድ ገ/መድህን በርጋ ሲቀዬር ጫን ያለ ችግሬ ከእሱ ጋር ሠርቼ ከሌላ ድርጅት ጉዳይ ጋር ለመሥራት ከፍ ያለ ቻሌንጅ ነበረብኝ። አንድ ጸሐፊ ስለ ጠ/ሚር አብይ አህመድ የሳይንስ እና የቴክኖሎጂ ሚ/ር በነበሩበት ጊዜ አብረው ሠረተኛ ሆኖ እዛ ሠርተው እንዴት እዛ ሲለቁ ራሳቸውን ከብቃት ጋር ያገኙበትን አጋጣሚ እና ከሌላ ጋር ለመሥራት የገጠማቸውን ፈተና ገልጸው ነበር። ጓድ ገ/ድህን በርጋ ሲለቅ እኔም የገጠመኝ ያን መሰል ግዙፍ ፈተና ነበር። በዛ ላይ ወጣትነቱ ሲታከል ከባድ ፈተና ነበር። በወጣትነት የግድ የማይቀሩ ሰብዕናዎች ይኖራሉና።

ደግነቱ ጓድ ዘርጋው አስፈራ ነበር፤ ኮ/ አሰፋ ሞሲሳም እንዲሁም ማዕከልም ላይ ባለደራዎች ነበሩልኝ፤ ብዙም ሳይቆይ ጓድ ገዛህኝ ወርቄ አንደኛ ጸሐፊ ሆነው መጡልን፤ ከሳቸው ጋርም ጓድ አባባ በዳዳ የእኛ ዘርፍም ባይሆን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጉዳይ ሃላፊ ሆኖ ከባሌ ወደ ጎንደር መጡልን እና በላይም በግራ በቀኝም መጠለያ መንፈሴ አገኜ ቢያንስ …  አቤት የሚባልበት ኖረ … የሚያደምጥም፤ ምክር የሚጠዬቅም።

ወደ ቀደመው ምልስት ሳደርግ በዛ በተደራጀ ፓርቲ ውስጥ አቅሙ ሳይባክን ቢቀር አገር ትጠቀም ነበር። አሁን ጠ/ሚር አብይ አህመድ እንዳደረጉት አፈራረሱም በስልት፤ አገናባቡም በስልት ቢሆን አኗኗርም ያምርበታል፤ አሟሟቱም ያምርበት ነበር። መጠዬቅም ካለ በአግባቡ ማንም ከህግ በላይ ስለማይሆን መጠዬቅ ሲገባ ብትን ብሎ ያ ሁሉ ተነግሮ ተዘርዝሮ ተጽፎ የማያልቀው የአንድ ሁለት ሦስት ትውልድ ብቻ ሳይሆን የዘመናት እርሾ ፍርስርስ ብሎ ባክኖ ቀረ …

አሁን እኔ በናሁ፤ በኤል ቲቢ በዋልታ ቴሌቪዥን ሞጓች ጋዜጠኞችን ሳይ በዘመነ ኢሠፓ ባክነው የቀሩ ጋዜጠኞችን አስብ እና ይህ የማስተዋል አመራር ባይኖር እናንተንም እኮ እናጣችሁ ነበር እላለሁኝ። 

እዚህ በስደት ከወጡ በኋላ እራሱ ስንት ጋዜጠኞች ነው መክነው እንዲቀሩ የተደረጉት። ማጥፋት፤ ማውደም፤ መደርመስ የማሌ ፍልስፍና ስንቅ ነው፤ ለዚህም ነው አሁን አቅል ነስቶት እየበጠበጠ፤ አቃቂር እያወጣ  ያለው …

በዘመነ ህወሃት በዛው በተለመደው መንገድ በመጓዝ የአጤዎቹ እና የደርግ ጠቃሚ እርሾዎች በቤንዚን ተርከፍክፈው በወል በበቀል እና በበታችንነት ስሜት ተቃጠሉ። በሰሞናቱ የተርሚናል ምርቃት ላይ „አባቶቻችን“ ሲሉ ጠ/ሚር አብይ አህመድ እንባዬን አላስብኩትም ዱብ ዱብ ሲል …  እንኳንም ለዚህ አበቃን። አባቶቻችን ተከበሩ ማለት ታሪካችን ተከበረ ማለት ነውና። ታሪካችን ተከበረ ማለት ዘመንና እና ትውልድ የፈቀደላቸውን የቀከወኑ ድንቆችም ተከበሩ ማለት ነው። 

ማልቀስ አለብን ራሳችን ለመቅበር፤ ራሳችን ከኋላ ቀሮች ተርታ ለማሰለፍ ከግብታዊነት ጋር ዘመን ከዘመን መፋት ተስኖን መዋለ መንፈስ፤ መዋለ ንዋይ አንዲህ ስናባክን መኖራችን ለድህነታችን መፍቀዳችን … ለድቀታችን መፍቀዳችን ራሳችን ያበጀነው ስለሆነ።   
በዚህ ውስጥ አንግልቱም፤ የአቅም ብክነቱም ከደርግ ሥርዓት ህወሃት ሳይማር ስለደገመው ትውልድ በተቃርኖ፤ በጥላቻ፤ በቂም፤ በቁርሾ፤ ምህረትም ይቅርታም የመማርም ጸበል ሳይረጭ የበቀለ - የጸደቀ - ያሰበለ በሙሉ ባልተወለደ አንጀት ተነቃቃለ። መከነ።

አሁን ከዚህ እንውጣ ሲባል ደግሞ በፈተናዎቹ መሃል ያን ጥሶ ለመውጣት ቅን ካፒቴን ሲገኝም የታዬው፤ የሚታዬው ውቂ ደብልቂ ያን ያዬ ከዛ ያልተማረ ከምን ተፈጠርን ያሰኛል። ቀድሞ ነገር አንድ ድርጅት በወጉ አደራጅቶ ማዝለቅ ያልቻለው ሁሉ ይህን የዘመን ቁልል ደበሎ መከራ ለተሸከመ መንፈስ ተጨማሪ ጫና በመፍጠር ያዋክበዋል። ለመሆኑ - በማፍረስ ለጸደቀ ነፍስ መገንባት ምኑ ነው? ትውልድ ማትረፍስ?ቅርሰ ውርስ የመንፈስ ድንግልናን መታደገስ?
  
ሞት ህመም ጭንቀት የበላቸው ስንት ወገኖች ናቸው። አሁን እኔ አብሮ አደግ ጓዴ ኤርትራ ነበር። የህዝባዊ ድርጅቶችን የሙያ ማህበራት ጉዳይ ሃላፊ ነበር። መጀመሪያ የወጣቶች ጉዳይ ነበር፤ ከፌድራሊዝም በኋዋላ ደግሞ ኤርትራ ራስ ገዝ ስትሆን የዛ የህዝባዊ ድርጅቶችና የሙያ ማህበረት ጉዳይ ሃላፊ ነበር ጓድ እንግዳ ወርቅ ተክሌ ይባላል። ጎንደር ተወልዶ ያደገ ኤርትራዊ ነው። በእናቱም በአባቱም በዚህ ፍርሻ ምክንያት ሞተም ዳነም አለም የለም ምንም ነገር የለም።

ታላቅ ታላቅ እህቱ በኢህአፓ ጎንደር ላይ ተረሽናለች፤ እሱ ደግሞ በኢሠፓ እንዲህ ሆኖ ሳያገባ ሳይወልድ በቃ አድራሻ አልባ ሆኖ ቀርቷል። ሁልጊዜ አስበዋለሁኝ። እዬዬን እናቱን ሳስብ ምን ሆነው ይሆንም እላለሁኝ … በዬዘመኑ ልጅ መገበር።

ያው እኔ ፈንገጥ ያሉ ባህሪያት ስላሉኝ ሥራ ልብስ ካኪ እማስመጣው ከኤርትራ ነበር፤ ሲሰፋም በሞድ ነበር። ካኪውን የሚልክልኝም እንግዳ ነበር። በመንፈስ ሁልጊዜ አስበዋለሁኝ። ሞትን ማወቅ መታደል ነው። አሁን ጓድ ለገሰ አስፋው በሥጋ ተልይተዋል። ይህ መታደል ነው። ቁርጥ የታወቀ ነገር። የእንግዳ ነገር ግን ሞተ ዳነ የለም። በቃ ያ ጥንቁቅ ርጉ ስክን ያለ ወጣት ባክኖ ቀረ … ለእናትም የመዋለ ዕድሜ የዘመን ህማማት ... 

ይህን የምጽፈው ዛሬ ያሉ የኢህአዴግ ሠራተኞች ልብ እንዲኖራቸው ነው። ሠራዊት አዛዦች የሚባሉትም ከመታበያቸው ዝቅ ብለው ህዝብን ባከበረ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ ነው እማስሰበው የ ጀ/ ብርሃኑ ጁላ አያያዝ ስለማይመርበት። ለውጡንም እያገዙት ሳይሆን እዬገዘገዙት ነው። በሰላ ፋስ እዬተረተሩት ነው „እዛ አካባቢ ድሮም ሽፍቶች ነበሩ“ ማለት ጦርነት ያስነሳል። መነሻን ማወቅ ይገባል። የዛሬ ወንበር ደግሞ ነገም እንደሚታጣ ማወቅ ይገባል። ዘድቆ የተፈጠረ ወንበር የለም። ብቻ በ እናንተ ሰሃ ታች ያለው በርሃ ላይ ወድቆ የሚኖረው ደግሞ እንደለመደበት ለማኝ ሆኖ እንዳይቀር ማሰብ ይገባል ...

ዶር አብይን የመሰለ ጤናማ መንፈስ ያለው ከዚህ መሰል እረግረግ መሰስ አድርጎ በስልት ያወጣ ዓራት ዓይናማ ሰጥቷቸዋል ለህወሃት ዘመን የሠራዊት አባላት አዛዦች መኮንኖች፤ ካድሬዎች ተባባሪዎች፤ አጋራቾ። የድምጽ አልባዎችን የኢትዮጵያ እናቶች ዕንባ ያዬ፤ ያደመጠ አምላክ ፈቅዶ የሰጠው ምርቃት ነው። ይህን አክብሮ በጥንቃቄ መያዘ ደግሞ ይገባል። በስተቀር አውሎው የት በዬት እንደሚመጣ አይታወቅም .. በልክ መያዝ።  

ይህን ምርቃት በወጉ መያዝ አቅቶ የሚታዬው መተራመስ እና ያዙኝ ልቀቁኝ ፈጣሪን በጦር የመውጋት ያህል ነው። ለወጡ ቢቀለበስ የጉለሌውም፤ የመቀሌውም፤ በዬምሽጉ የሚያነኩረውም አድራሻ ቢስ ነው የሚሆነው። „እዩኝ እዩኝ ያለ ገላ ደብቁኝ ደብቁኝ“ ነው የሚያሰኘው … 

እኔ እኮ ወደ ጫካ ስወጣ በጎንደር ቁስቋም በር የሰው እራስን ውሻ ይዞት አይቻለሁኝ። እንደ ቅጠል ነበር የረገፈው ህዝብ። በሰማይም በምድርም … አይበቃም ወይ ህዝብ በባሩዱ ማለቅ፤ በካቴና መጠርነፍ? ያ ምኑ ይናፍቃል?
  
የደርግ ሥራዓት ሲያከትም በጭንቀት ያለፉት ቤት ይቁጠረው። ምጥ ላይ የነበሩ እናቶች ልጁ ተወልዶ እነሱ አልፈዋል፤ ለዚህም መምህር ሙሉዬን ልጅ ጎርባቾቦን ማቀረብ ይችላል።

በጭንቀት በሽተኛ ሆነው የቀሩት ቤት ይቁጠረው … አካል ጉዳተኞች የባዕድ አገር ጦር ቢማርክ የማይደርስ መከራ ተሸከመው፤ በዜግነታቸው አፈረውና ተሸማቀው ተኮማትረው ቀርተዋል። ልጆቻቸውም የሥነ - ልቦና ተጠቂዎች ሆነዋል። ዜጋ ያልሆነ አባት እናት እንዴት አድርጎ ልጁን ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነህ ብሎ ማሳደግ ይቻለዋል? 

ከላይ ከላይ ከመፍላት ሰከን ብሎ ያለፈውን መከራ ማድመጥ ብቻ ሳይሆን አቅጣጫ የለሽ ኩዴታ ቢገጥም ምን ሊኮን ይቻላል ብሎ ማሰብ ይገባል … ልብ ይስጣቸው በስውርም በግልጽም ለውጡን ለመቀልበስ ለሚተጉት። ለውጡን አቅሙን ለመስበር ቀን ከሌት ለሚታትሩት። 

በነገራችን ላይ ያን መሰል አጋጣሚ ቢኖር ኖሮ አብይ የሚባል ሰውም ተጠያቂ ሆኖ የካቴና እራት ነበር የሚሆነው። ዓለምም ከ100 በጎ አሳቢዋ አንዱን ጤነኛ አሳቢ ታጣ ነበር። ሉላዊው ዓለም እራሱ እንደ አንድ የመንፈስ ቴራፒ እያዬው ነው ባልተጠበቀ ዘመን ያልተጠበቀ አዳኝ መንፈስ ኢትዮጵያ ላይ በመከሰቱ።

ሌላው ሥልጣኑን ቢያገኝ ኖሮ መፍረስ የድሉ መባቻ ስለሆነ ጠ/ሚር አብይ አህመድ ሆኑ ሌሎችም እንዲሁ የካቴና እራት ነበር የሚሆኑት። ለዛውም ለግራ ፖለቲካ ብቁ ሰው አንጡራ ጠላት ነው። ፎቷቸውን መለጠፍ እንዴት ወንጀል እንደነበር አይተውታል። ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነውን“ መደገፍ አይደለም አያይዙ በዚህ ዙሪያ አስተያዬት መጻፍም የሚያስወግዝ ነው የነበረው። ቋጠሮ ድህረ ገጽ ይህ ገጥሞት ምላሹን ራሱ ሳነብ ውስጤ ጭስ እያለ ነበር።

ይህን መስል አግባቢ አቃፊ አዬር ማግኘት የተቻለው የህወሃት ዘመን በቀስታ እና በእርጋታ ፍርሰቱ ንደቱ በጥበብ ስለተያዘ ብቻ ነው። ለዚህም ነው ጠ/ሚር አብይ አህመድ ቀደም ባለው ጊዜ እኛ ያጣነው ዊዝደም ነው ብለው በአጽህኖት የገለጹት። ጥበብ ፍለጋም በግል እንደጣሩ እኔ አስባለሁኝ።  

ሌላው አንድ ሥርዓት ሲፈርስ ብዙ ነገር ነው የሚወድመው። በጓዶቻችን መሃል የነበረው ፍቅሩ እንዴት ባክኖ እንደቀረ። ሴራም ሸርም የለም አልነበረም ማለቴ አይደለም የማሌ ርዮት አጥሚቱ ስለሆነ ነበር በተደራጀ ሁኔታ።

ነገር ግን እምንግባባ ሰዎች ደግሞ ፍቅራችን ልዩ ነበር። እኔ ለሠረተኛ ማህበራት፤ ለመምህራን ማበር መሪዎች ጋር ስለ ጋብቻ የጠዬቁኝ ሰዎች በግልጽነት አጫውታቸው ነበር። ለቤተሰቤ ግን አልናገርም። ጫና ስለሚያበዙብኝ ይህን ከሰሙ።

ረጅም የሆነ ዘለግ ባለ ጊዜ በቀለም ትምህርት ዘልቆ ለረጅም ጊዜ የመማር ፍላጎቴን እንዳያጨናጉልብኝ ስለምሰጋ፤ በተጨማሪም ጋብቻ አጀንዳዬ ስለአልነበረም ውሹን ቤት ውስጥ እንዲነሳብኝ ፊት አልሰጥም ነበር። 

እናም ለወላጆቼ ሸሽጌ ለማህበራቱ አመራር አካላት ግን እንሱን አቅርቤ እንደ ራሴ ስለማዬቸው አወያያቸዋለሁኝ። ይህ ቤተሰባዊ ስሜት ከሚመሩት ጋር መፍጠር ልዩ ስጦታ ነበር። ቀጥተኛ የሆነ መስመር ይፈጥራል። መታመን የመሰለ አቅም እና ሃይል የለምና በመሪና በተመሪ ማህል። የፖለቲካ ሊሂቃን ትልቁ ችግርም ይኸው ነው የመታመን አቅም የላቸውም። 
  
እናቴ የዛን ጊዜዋ ቆንጅዬ የዛሬ መንኩሲያዋ እብዬ ከጫካ ሰመለስ ያለችኝ „ድርጅታችሁ መፍረሱ ሳይሆን እኔን የሚያሳዝነኝ ፍቅራችሁ፤ መተሳሰባችሁ፤ መተዛዘናችሁ፤ መጠያየቃችሁ፤ አንተ ትበስ አንቺ ትብሺ መበላላችሁ መፍረሱ ናድ ማለቱ ነው የሚያሳዝነኝ ነበር ያለችኝ።“

አገር ሲፈርስ መንፈሳዊ ሃብት ሁሉ ነው የሚፈርሰው። በውነቱ ማፈረስን ለሚመኙ እሱን እንደ ጣዖት ለሚያምልኩ ደካሞች አማኑኤል ማስተዋል ይስጣቸው። ካልፈራረስ ለውጥ የለም በእነሱ ቤት። ሌላው አጋጣሚን ሌላ ሃይል አግኝቶት ቢሆን የአማራ የህልውና የማንነት ተጋድሎ እና የኦሮሞ ንቅናቄ ታሪክ ይቀማ ነበር።

ይህ የለውጡ ተጋድሎው የመንፈስ አጣባ ላይ ነው አትኩሮቱ። ያ ደግሞ የቱማታ የጀንበር ተግባር አይደለም፤ በሌላ በኩል አብነት ሆኖ በሁሉም ዘርፍ መገኘትን ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ ልዑል እግዚአብሄር ሰጥቶናል። ብናውቅበት፤ አለማወቃችን ብናውቀው፤ አልመብለጣችን ብንረዳው እኛ የሌለን፤ በአማራር ዘመናችን ሞክረነው አስበነው የማናውቀውን ሁሉ መልካምነትን፤ ቅንነትን፤ ግልጽነትን እያሳዬን ነው እዮር በምርቃቱ አማካኝነት … ለዛውም በስክነት፤ ለዛውም በማስተዋል፤ ለዛውም በመቻቸል … ለዛውም እርጋ ባለ ክህሎት …  

ልብ ይስጠን ፈጣሪ። አሜን!




                            የኔዎቹ ኑሩልኝ! መሸቢያ ጊዜ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።