ዘመን ያላዳነው ቅምባ።

እንኳን ደህና መጡልኝ።
„በክፉዎች ምክር ያልሄደ በዋዘኞች
ወንበር ያልተቀመጠ፤ እሱ የተመሰገነ ነው።“
መዝሙር ፩ ቁጥር ፩

ዘመን ያላዳነው ቅምባ።
ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
16.02.2019



ውዶቼ እንዴት አላችሁልኝ። ደህና ባጃችሁ? እንዴት ናችሁልኝ አዱኛዎቼ። እኔ ልዑሌ ፈጣሪዬ ክብሩ ይስፋ በሙሉ ጤንነት ላይ እገኛለሁኝ። ደህንነተኔ የጠያቃችሁ ክብሮቼ ደህና ነኝ። ግን ድንብልብሏ ከቶ እንዴት ሰነበተች? አላዛሯ ኢትዮጵያስ?

መቼም ብዙ ነገር በዚህ 15 ቀን እንደ ተከወነ እና አንደገጠመ አስባለሁኝ። መንፈሴ ከአገሬም ሆነ ከግራጫዋ ፕላኔታችን ጋር ቢሆንም ጥሞና ጊዜ ላይ ስለነበርኩኝ በተዘጋ ገሃዳዊ ዓለም ግን እና ባለ መንፈሳዊ የፀጋ ትፍስህት አብሮነት አድርጌ ቆዬሁኝ። ተመሰገን።

ዛሬ እጅግ ማልጄ ነበር የተነሳሁት። እትዬ ንግሥትም ፍንትው ብላለች። ብቻ እህታችሁ ትንሽ ዞር ዞር እንያልኩኝ ትንሽ ነገር ለማዬት ለማድመጥም ሞከርኩኝ። ያው የሳተናው ነገር ነፍሴ ነው። 

ከቶ እናት እንዴት ሰንብቶ ይሆን ብዬ መጀመሪያ በፍጥነት ከፍቼ ያዬሁት የጥንት የጥዋቱን ቤቴን የሳተናውን ነበር። ደህና ነው። ያለፈኝ እንዳለፈኝ ሆኖ አዳዲስ ጹሑፎችን አነበብኩኝ። እሱን ሳተናውን ደህና በማግኘቴ በውነቱ ደስ ብሎኛል። አማካይ ስለሆነ። ትንፋሽም። ይኑርልን። ልፋቱን የሚመዝን አምላክም ልጆች ካሉት ይበርክለት ይቀደስለት፤ ትዳርም ከኖረው በረከቱን ሁሉ በስፋት ይለግስለት። እማከብረው ድህረ ገጽ ነው።

እውነት ምን ብትምር ይሆን ዘመን ከዘመን እንዲህ ሊያልፍላት ያልቻለ የሚል ፈታኝ ነገር ግን በውነቱ ገጥሞኛል። እናላችሁ ዕውነት ምን አለ ተምር ብትሆን አልኩኝ። ተምር በልጅነቴ ጀምሮ አውቃለሁኝ። እስልምና ሃይማኖትን የሚያምኑ የሥጋ ዘመዶቼም የልብ ጓደኛዬም ሞሚና ስለነበረች በእጅጉ ተምር ጋር እንደ አሳ ዘይት ተዛምዶዬ በልጅነት በርታ ያለ ነበር። እናቴም እብዬ አብዝታ ተምር ትወድ ነበር የዛሬን ባላውቅም።

የሆነ ሆኖ እውነት በአገሬ በኢትዮጵያ ተምር የሚሆንበት ዘመን መቼ ስል ራሴን ሞገትኩት? ተምር ሁለገብ ፈዋሽነቱን አንድ ሰሞን ዘሃበሻ በጤናዳም አምዱ ላይም አስነብቦን ነበር። ምን አለ አሁን ሁሉም ተምርን ፈላጊ ቢሆን እላለሁኝ። የፆም መሻሪያ ነው ለእስልምና እምነት ተከታዮች። ሚስጢሩን ሊቀ ሊቃውንቱ የእስልምና አቦ እድምታ ነው የሚሆነው። 

ተምር ሉላዊም ነው። እውነትም ፈላጊ አፈላላጊ አንባሳደር አጣ እንጂ አውነትም ተፈጥሮውም፤ ህግጋቱም፤ መርሁም ሉላዊ ነበር። እውነት እኮ ዶግማ ነው - ለእኔ። የማይለበጥ፤ የማይጣፍ፤ እንደ ቁሮ የማይቆረር፤ የማይሸጥ፤ የማይለወጥ። ግን እማዬው - እምሰማው - እምታዘበው እውነት ላይ ሲደረስ ማረጥ ሆነ።

ዘንበል ቀና በሚለው በፖለቲካ መኖር ውስጥ አንዱን ወግነን ስንፋለጥ፤ ሌላውን አውግዘን ሲንጣረብ፤ አንዱን ጣሪያ አስነክተን ስናሞግስ፤ አንዱን ደግሞ ድብዛውን አጥፍተን ስንብጠለጥል፤ አቅም ያላቸው ደግሞ እውነት ቀን እንዳይወጣለት አሳደው ሲያከሰሙ፤ በባዶ ተስፋ ንፋስ ተከተለን ስንወጃወጅ ዘመን እኛን ጥሎን እያለፈ፤ አብሮ መኖር መርገምት ሆኖ እዬባሰብን አለን ይኸው እንዳለን። መብሰል አልቻልነም። ሁልጊዜ ጥሬ። ጥሬ እኮ ይኮመድዳል አይደል? በኮምዳዳ መኖር ተሸንግለን ተረጀ።

ጮርቃ ለመብል ያልደረሰነት መሆኑ አውስቼ እኔ እውነትን በሸሸሸን ቁጥር ትውልድን በማትረፍ እረገድ ያለው ድርሻ ልኬቱን ወቄቱን ለቅኖቹ ልተዎው። የእኔ የቤቴ ታዳሚዎች በቤቴ ሲገኙ ምንም ግድ የማይሰጣቸው፤ እኔኑ ተከትለው በኮሳሳዊ ጎጆዬ ቅንነትን ሰነቀው ወገናችን - እህታችን - የአገራችን ልጅ ብለው ስለሚታደሙ ሚዛናማ መሆናቸው እምነቴ ጽኑ ነው።

የሚገርመው መሪዎች የሚባሉት ትናትን የት ላይ ነበርኩ? ዛሬስ የት ላይ ነኝ? ነገስ የት ላይ እሆናለሁ? የሚለውን የተደሞ ፈተና ለማለፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት ስታዘበው ደግሞ ፈተናው አንጥሮ ራሴኑ ያፋጠኛል።

ከቶ ዕውነት ማን ዳው፤ ማን ጠበቃ፤ ማን ጥግ፤ ማን ሁነኛ ይሁነው? በተናደ ቤት ውስጥ ዝናብ ያስጥለኛል ብሎ ያን የሙጥኝ ማለትስ ስለምን ይሆን? እሚታዬ ጽግሽ /ጢጢዬ/ ይህን መሰል ነገር ሲገጥማት „ብልሃት የሌለው ቅላት“ ትለው ነበር።

ዘመን ሲነሳ፤ ዘመን ፊቱን ሲያዞር፤ ዘመን የደረስንበትን ሲንደው፤ ዘመን ያሰበነውን ቢና ጢናውን ሲያወጣው ስለምን ይሆን ብሎ ራስን ለመፈተን አለመተጋት ቀጣዩንም ተደርማሽ እንዲሆን ያደርገዋል። ይህ የናፋቀው፤ ይህው ሽው ያለው አዲስ መንፈስ እንዳለ ደግሞ ከሳተናው ካገኘሁት ጥልቅ ተንታኝ ጹሑፍ ማንበብ ቻልኩኝ።

የትናንት ፍርሰት፤ የትናንት ንደት፤ የትናንት ውድቀት፤ የትናንት ድቀት ማን ማንን ተከትለ፤ ማንም ማንን ተጠግቶ፤ ማን ማንን አምኖ፤ ማን ማንን ተስፋ አድርጎ በኖ - ተኖ - ባክኖ አይሆኑ ሆኖ ቀረ የሚለውን ልብ ጠፍቶ አሁንም እውሃ ወቀጣ እንደሆን አንድ ልባም ጹሑፍ ትዝብቱን አጋርቶኛል። ጸሐፊውን ከልብ በአክብሮት አመሰግናለሁኝ። 

ከሁሉ የሚገርመው የትውልዱ ብክነት ባለቤት ማጣቱ፤ ሁነኛ ማጣቱ፤ ባሊህ ባይ ማጣቱ ነው ድንቅ ያለኝ። አሁንም ዙሮ ዙሮ ወቀን … /ወቅን በወገራ አውራጀ በዳባት ከተማ አቅራቢያ የሚገኝ ተራራ ነው/

የተስፋ ክኒን አይደለም ሌላውን ካንሰርን የሚፈውስ እንደሚሆን ተስፋ አለኝ። የትኛውም ህመም ብዙውን ጊዜ የጭንቅላት ጨዋታ ስለሆነ። አሁንም እኔ ተስፈኛ ነኝ። ተስፋ የህይወቴ አንጎል ነው። በማናቸውም ተግባሮቼ ላይ መርሄ ተስፋ ነው። የመጀመሪያው መጸሐፌ ተስፋ ነው፤ ስድስተኛው መጸሐፌም የተስፋ በር ነው፤ ጸጋዬ ደህረገጽም ላይም ተስፋ ራሱን ችሎ፤ የሎሬት ተስፋም እንዲሁ ለልጆች ሁለት መምሪያ ነበር። ከሥምም እንደ ተስፋ የምወደው የለም። ከቃልም።

ስለሆነም ነው ማናቸውንም ነገር በቅንነት ላይ ሲጀመር ተመልክቼ እምሟገትለት ተስፋ ስለማደርግ፤ ተስፋ ነው ብዬ ስለማስበውም እምቀልጥለት፤ እምፈለጥለት ተስፈኝነቴ ገደብ አልቦሽ ነው። በህይወቴ በጣም እምወደው ነገር ደግሞ ሥጦታ ነው። ለማናቸውም መልካም ነገር የአመሰግናለሁ ካርድ አይቀሬ ነው በእኔ ደብዳቤ ሁሉ የሲዊዝ መንግሥትም ይህን ያውቃል።

ስለሆነም ለአላዛሯ ኢትዮጵያም ተስፋዬ ዝልቅ ነው ሥጦታዬም ተሰፋ ነው። ግን ተስፋ መንፈሳዊ፤ ህሊናዊ ሲሆን እንጂ በሞቀ እና በቀዘቀዘ ገሃዳዊ ስሌት ተባደግ ከሆነ አደጋው ሰፊ መሆኑን ስለማውቀው አብዝቼ እፀዬፈዋለሁኝ።

ዛሬም ትናት የተገፉት እንደተገፉ ነው በአገረ ኢትዮጵያ። ዛሬም ትናንት የተገለሉት እንደተገለሉ ነው በምድረ ኢትዮጵያ። ዛሬም ትናንት የተሳደዱት እንደተሳደዱ ነው በመከረኛው እናት አገር። ዛሬም የክት እና የዘወትር ልጆች አሏት የምትገረመው አላዛሯ እናታችን። አይመረም ወይ?!

በአላዛሯ ኢትዮጵያ ውስጥ ትናንት እታዘብ እንደነበረው ዛሬም የሞቀለትን ለቀማ አለ። የደላውን፤ የተመቸውን፤ እውቅናውን የጎለበተው ብቻ ነው ዜጋዬ ሲባል ብቻ ነው እኔ እማዬው እና እምታዘበው። ይህ ለሥርጉትሻ ህሊና ባዕድ መንገድ ነው። 

እና እኔ ሥርጉተ ሥላሴ በተደራጀ መዋቅር ተገልዬ የኖርኩት እኔ እንደ ተገላዮች መሬቴ ላይ እንአሉት ምንዱባነው ወገኖቼ ብሆን ብዬ ሳስበው የተለዬ የአያያዝ ጥበብ እንደሌለ ማሰተዋል ችያለሁኝ። "ሚዛን ለራስ ነው" ይላሉ ጎንደሮች ሲተረቱ። ሚዛኑ ያገለለ ወይንም የተጫነ ነው። የነፃነት ትግል ዛሬ በጥዋቱ ይህን መሞረድ ካላቻለ ነገስ ሲባል? ውሃ ያዘለ ተራራ ነው። ሸክምን ሸኝቶ ሌላ ጫን ያለ ሸክምን ማጨት በ አማጭነት ካሰለፉት አማካሪም እንዳሻ መሸከም። 

ይህ መቼም ለዛውም ፈጣሪውን ለሚያመልክ እምነት ላለው፤ ሃይማኖት አለኝ ለሚል፤ እውነት ላለው፤ ማተብ ላለው ነፍስ ከቶም ይመቻል ብዬ አላስብም። እንዲህ የተዛባ አያያዝን እና ከጥበብም ከስልትም ያፈነገጠ ጠዬም ያለ ለዛሬ ሲታይ ስንቅ ሁን ተብሎ ሲገደድ፤ ለነገ ደግሞረ እራስን እያበለዘ የሚሄድ የህሊና ሪህ ይመስለኛል። ሥጋ የሚገዛን ከሆነ ሚዛን የማያስተዳድረን ከሆነ ነገም ጥቁር ነው። ጥቁር የሚለውን ለጊዜው ተስፋኛ ነኝ እና አሻሽዬ ግራጫ ነው የሚለውን ልውሰድ።

በጣም ተዛነፍ የሆኑ ጉዳዮች እያዬሁ ነው በሁሉም ዘርፍ። እንደ ድሮው ቁስል አልልም - ዛሬ ላይ። ስለምን ብትሉኝ መረገም ነው ወደሚል አዲስ ፈለግ፤ ደግሞ ዝንባሌ እያደረበኝ ስለሆነ። በዛ ብሩህ ተስፋዬ ውስጥ እንዲህ ወዘተረፈ ህፃጽ ሳዬ እና ሳስተውል ደስ እንዳይለን፤ ደስታችንም ሙሉ እንዳይሆን መረገማችን ማስተዋል ችያለሁኝ እና።

ብዙ ነገሮች ተቀላቅለዋል - ክፋቶች፤ ሴራወች፤ የቆዩ ቁርሾዎች በማገርሸት፤ የናጠጡ አድሎዎች፤ የተተበተቡ ሸሮች ተቀይጠዋል። የራስ ተሰማ ናደው ዘመን ድገም እያለ መሆኑን ዛሬ ሳይሆን ባለፈው ዓመት በስፋት ጽፌበታለሁኝ።

የክፉ መንፈሶች ቅልቅሎች ደግሞ ተስፋ እንደገና እንዲጠነዝል እያደረገው ነው። አቅም መሰብሰብ፤ አቅም ማከማቸት ቀላል መስሎ ታይቷል አሁንም እንደላፈው ጊዜ አብዞ እንደ ዲያስፖራው ፖለቲካ። ሌላው ሲነድ፤ ሌላው ሲያፈርስ ምን ያህል ለዛሬ ቀን እንዲደርስ ፍዳችን ያዬን፤ ስንት ማስጠንቀቂያ የደረሰን ባተሌዎች እናውቀዋለን። ባሊህ ባይ የሌለን የትውልዱ ዬዘመኑ ብክነት ያሳረረን ቅኖች ለፍተንበታል። 

ነገር ግን በስንት ፍዳ የተሰበሰበ አቅም ሲናድ ግን የቅጽበት ጉዳይ ነው። የተነቀነቁ ነገሮች እያዬሁኝ ነው። ይህ ዋዛ ሊመስል ይችል ይሆናል ዛሬ ላይ። ዛሬ ላይ ዓለምም እዬሰገደ ስለሆነ። ነገር ግን ሁሉ የደረሰበት ሌላው የማይደርሰበት ምንም አመክንዮ የለም። ትእግስት ሲያልቅ ፍቅር መሰደዱ ግድ ይላል።  መደፈረስ መጉሸት የዕጣ ጉዳይ ሳይሆን የአያያዝ ጥበብ መዛባት ችግር ነው። 

አብሶ በህሊና ተመሽጎ ያለ የሚያስማማ አንድ ጥላሽት ነገር አለ። ያን ዘመን ደርምሶታል ቢባልም ግን እንዲያገረሽ ዕድሉን ባለ ዕድሉ ስለሰጠ አልፎት የመጣውን የአሸናፊነት ጸጋን ያጎናጸፈውን በረከት ባለድሉ እዬጠቀጠቀው እንዲያውም አሳልፎ ሲሳዩን እዬሰጠው እንዳለ አስተውላለሁኝ። ይህ መቼም ሙልጭ ያለ ጅልነት ነው። የመንፈስ ሃብትህን ለሌላ ፈቅደህ አሳልፈህ መስጠት ከምን ስለምን ተፈጠርክ ያሰኛል?ማህከነ! 

እኔ ተስፋ የምለው የመንፈስ ትንሳኤን ነው። መንፈስ ሊድን የሚያስችለው በቁሳዊ ዳንኪራ እንዳልሆነ ስለማምን። ለእንዱ ንግሥና የምትሰጠው አላዛሯ ኢትዮጵያ ለሌላው ሞት ሰንቃ ትጠብቀዋለች፤ ለአንዷ እናት ልዕልና ላይ የምትኮፈስ አላዛሯ ኢትዮጵያ ለሌላው ማቅ ሲሆን አሁንም አሁንም አሁንም የመንፈስ ድቀት ዳግሚያ ውልደቱ ነው የሚሆነው። አላዛሯ ኢትዮጵያ የድምጽ አልባዎቹን እናቶች እንባ እኩል እያስተናገደች አይደለም። 

ሌላው ልግስና ማለት የራስህን ለሌላው ስትሰጥ ነው። ነገር ግን የራስን ሳይሆን የሌላውን፤ ያልተወለደውን መስዋዕትነት አሳልፎ የመስጠት እና የመሸለም ደግሞ አዲስ ታሪካዊ እርምጃ ላይ አላዛሯ ኢትዮጵያ እንዳለችም እያስተዋልኩኝ ነው። እግዚኦ!

ስለሆነም እውነትን በኢትዮጵያ ምድር ሳስባት ብርድ ብርድ እያለኝ ነው። ዘመን ያላዳነቅንባ ዛሬም እዬዘፈነ ነው። ዘመን ያላዳነው ቅንባ ዛሬም እያፎለለ ነው። ቅንባ እንደ ትናንቱ ዛሬም ይለፍ ተሰጥቶት የራሱን ወደ እግር የእግሩን ወደ ራስ እያደረገው ነው። ዝብርቅርቅ አድርጎ በውዞታል። አጅሬው ማፈረስ እንጂ መገንባት አልተፈጠረለትም፤ አልተሰጠውምም። የተጠጋው ሁሉ ኩሸት ነው። ይናዳል። አይበቅልም። ጠንዝሎ መራራ ስንብት ያደርጋል ወይ ደግሞ ተተርትሮ ህልፈቱን እንጦርጦስ ይልካል።

መሪ ሆነህ የምትመራውን ህዝብ መክሊት መመርመር ሲሳንህ ያን ጊዜ የመንፈስ ውድቀትህ ነጋሪት መለከት ልዩ ምልክት ስለመሆኑ ልብ ያስፈልገሃል ማለት ነው። መገዛት ካለበትም ከልባሞች ነጋዴዎች መንደር ሲያስፈልግ በችርቻሮ ሲያሻም በጀምላ መሸማማት ነው አዲስ ልብ ከማስገጠም መግዛት ይሻላልና።

ቅንባም ቅንባ ነው። የሚጎሰጉሰው ያገኘውን ሁሉ ነው። ብቻ እሱን ሐዋርያ የሚያደርግ ጭድ ይሁን ሙጃ በቃ ቅራ ቅንቦ መሰባሰብ የተፈጠረበት ነው። ቅንባ ሆዱን የሞላ ሁሉ እሱ ዘመዱ እሱ ወገኑ እሱ ጳጳሱ ነውና። ነገ ደግሞ ጤዛ ነው። ወይንም የሳሙና አረፋ፡፤

ቅንባ በቃኝን የማያውቅ አሳማ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ሲረገዝ አባቱን ሲወለድ እናቱን ቡጭቅጭቅ አድርጎ የሚገደል እፉኝት ስለሆነ ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂ ትልም የለውም፤ ተደግሞ አያውቅምና። ይሉኝታ የሚባል የለውምና ካስጠጋው ጊዚያዊ መጠለያ ተንጣሎ ሽርክት ምርክቱን እዬመራረገ የተጠገባትን ሰልልስሎ ፈነቃቅሎ ድራሹን አጥፍቶ በፈረሰ ታዛ ከትከት ብሎ እዬሳቀ ብቅ ይላል።

ያስጠጋውንም፤ ቀን ጠብቆ ብትክትክ አድርጎ ብል የበላው ጨርቅ አድርጎ በትኮት ይቀራል። ዛሬ ላይ ለሁሉም በቅብ መረገድ ሊታይ ይቻል ይሆናል። ዛሬ ላይ መነጠፍ ሊኖር ይቻላል። ግን ውሎ አያድርም። እስስት ተፈጥሮው የቅንባው አይፈቅድለትም እና።
ሁሉ ነገር ይደፈራል በኢትዮጵያ መኖር ውስጥ የማይደፈረው እውነት ብቻ ነው።  

የኔዎቹ ለጥ ብዬ የጸጋ ስግደት ለቅኖቹ ሰግጄ መሸቢያ ጊዜን ተመኘሁላችሁ። ኑሩልኝ። መኖራችሁ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለዛች ለጠይሟ ለአላዛሯ ኢትዮጵያም ቅኖቹ ይኑሩላት። ኑሩልን ለሁላችን!

„በክፉዎች ምክር ያልሄደ በዋዘኞች

ወንበር ያልተቀመጠ፤ እሱ የተመሰገነ ነው።“ 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።