ከታሪክ ማህደር፤ ኮርያ /ከጸሐፊ መስፍን ማሞ።/
እንኳን ደህና መጡልኝ።
ከታሪክ ማህደር፤ ኮርያ
“እግዚአብሄር አለኝ፣
--- አንተ ልጄ ነህ። እኔ ዛሬ ወለድሁህ።
መዝመረ ዳዊት ፪ ምዕራፍ ፯
ጸሐፊ መስፍን ማሞ ተሰማ
ሠላም ለናንተ ይሁን!
መቼም የኢትዮጵያ ታሪክ እንደ ሳይንስ የሚያመራምር እንደ ድንቅና ውስብስብ ልቦለድ ታሪክ ውሉን ለማግኘት ታሪኩ የሚመስጥ በዚህች ምድር ላይ ሌላ መሰል ታሪክ ያለው ሀገር ይኖር ይሆን? በ1950ዎቹ (እአአ) ኢትዮጵያ የምትደዳደረው በዘውዳዊው (ሞናርኪ) ሥርዐት ኢኮኖሚያዊ መሰረቷም ፊውዳላዊ። ያም ሆኖ ከራሷ ጂኦግራፊያዊ ክልል አልፋ አህጉራዊና ዓለም ዓቀፋዊ ተቀባይነትና ግዝፈት ያላት ሀገር - ገራሚ ነው!! ለማንኛውም ኮርያ እንዝመት፤
ዘመኑ ከ1950 እስከ 1953 (እአአ) ነው። የኮርያ ጦርነት። በኪም ኢል ሱንግ የምትመራዋ ሰሜን ኮርያ በሲንግማን ሪህ የምትመራዋን ደቡብ ኮርያ ወረረች። ሰሜኖች ኮሙኒስት ደቡቦች ካፒታሊስት ሥርዐት ተከታዮች። ከሰሜን ኮርያ ጎን ቻይና እና ሶቪየት ህብረት በግንባር ቀደምትነት ሲሰለፉ ከደቡብ ኮርያ ጎን ደግሞ አሜሪካና የምዕራብ ዲሞክራሲ ሀገራት ተሰለፉ።
በዘውዳዊው የግርማዊነታቸው መንግሥት በፊውዳላዊ ኢኮኖሚ የምትደዳደረው ኢትዮጵያችን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ነበረች። እነሆ ከተመድ መሥራች ሀገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ኮሙኒዝምን ልትዋጋ ከዲሞክራሲያዊ ሀገራት ጎን ተሰለፈች። በ1951 (እአአ) ቃኘው ሻለቃ ጦር ወደ ኮርያ ዘመተ።
እነሆም በሩቅ ምሥራቁ ጉደኛ ጦርነት ተዓምረኛ ተዋጊዎች የተባሉት የቃኘው ሻለቃ ጦር የኢትዮጵያን የጀግኖች ማማነት በደማቅ የደም ቀለም በዓለም ዐውደ ውጊያ አስፃፈ።
ቃኘው ሻለቃ ጦር በዚያ የጦር ዐውድ በተለያዩ የጦር ግንባሮች 238 (ሁለት መቶ ሰላሳ ስምንት) ጊዜ ከሰሜኖቹ የተባበበረው የኮሙኒስት ጦር ጋር ገጥሞ ተዋግቷል።
አስደናቂውና ኮሙኒስቱንም ሆነ ዲሞክራሲውን ግንባር ያስደመመው ቃኘው በየትኛውም የጦር ዐውድ ተሸንፎ አለማወቁ ነው!!
በኮርያ ጦርነት ኢትዮጵያ ከስድስት ሺህ በላይ ሠራዊት ያሰለፈች ሲሆን በጦርነቱም 121 (አንድ መቶ ሃያ አንድ) የጦር አባላቷን ህይወት ስትገብር 536 (አምስት መቶ ሰላሳ ስድስት) ቁስለኞች ሆነውባታል።
በጦርነቱ ማብቂያ ከአሜሪካ ወገን ሆነው ከተዋጉት ሃያ አንድ ሀገራት መካከል ሁሉም በኮሙኒስቶች እጅ የወደቁ ምርኮኛ እስረኞች ሲኖሯቸው አንድም ምርኮኛ ያልተያዘባት ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ ናት። አኩሪ ነው!! ለዚህም ነበር የዚያ ዘመን የጥበብ ሰዎች የኮርያን ዘማቾች ሲያወድሱ <አጨደው ከመረው ወቃው እንደ ገብስ፤ የኢትዮጵያ አርበኛ ኮርያ ድረስ> በማለት የዘመሩላቸው።
አዎ! <ሰኔና ሰኞ> ተጋጠሙና በለስ የቀናው ወያኔ ኢህአዴግ በ1983 አዲስ አበባን ሲቆጣጠር <የጠላት ጦር> በማለት በትኖት ለረሀብና ለልመና የዳረገው ይህንን የኢትዮጵያ ጦር ነበር።
ኢትዮጵያ ዛሬም በተፈጠሩና በሚፈጠሩ ጀግኖች ልጆቿ በነፃነት፤ በአንድነትና በክብር ትኖራለች!
በታኞች ራሳቸው ይበተናሉ! ኢትዮጵያ መቼም አትበተንም!!
የካቲት 2011 ዓ/ም (ፌብሩዋሪ 2019)
ሲድኒ አውስትራሊያ
ማስታወሻ።
ውዶቼ ጸሐፊ አቶ መስፍን ማሞ ጹሑፉን የላኩት ሰንብቷል። ነገር ግን እኔ ባለመኖሬ ምክንያት ዘግይቷል። ስለዚህም ታላቅ ይቅርታ ለጸሐፊ መስፍን ማሞ እጠይቃለሁኝ። ጹሑፉን እራሱ ያገኘሁት ዛሬ አሁን ነው። ኢሜሌን ስከፈት። ኑሩልኝ የኔዎቹ በጣም መሳጭ እና ሐዋርያ ጹሑፍ ነው። እጅግ አድርጌም ጸሐፊውን ከህሊናዬ ልብ አመሰግናቻዋለሁኝ። ይኑሩልን።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ