#ከውስጥ ማድመጥ እና ስኬቱ።

#ከውስጥ ማድመጥ እና ስኬቱ።

 
 
ከሥር ደግሜ ፖስት ያደረኩትን ጹሁፍ ምክንያታዊነት ልገልጥ ነው። ተያያዥ ጉዳዮችም ይነሳሉ።
በ21/10/2022 የፃፍኩት ዕውነት እኔ ሲዊዝ ሆኜ በስብሰባው ያገኜሁትን ፊድባክ ነበር። ውስጥን ያላገኜ ድካም ስለታዘብኩኝ።
ትናንት 23/10/2022 እዛው ስብሰባ ላይ ዬነበሩ፣ ባለ 7 ነጥብ ዬአቋም መግለጫውን አብረው አዘጋጅተው ያነበቡ የስብሰባው ታዳሚ ደግሞ እንዲህ ይላሉ በEMS። ሙሉውን እናንተው አዳምጡት።
 
"……… ስህተት ነበር። ሳነበው አንድ ደቂቃ ዬማይሞላ ነበር። 7 ነጥብ ነበረው። ያ እንዳይተላለፍ የተሸማቀቅኩበት፣ እና ዬሆንኩትን፣ ዬተሰቃዬሁትን ስቃይ፣ ቴሌቪዥን ላይ አለመተላለፋን እስካይ ድረስ፣ እግዚአብሔር ምስክሬ ነው። እዛ ላይ ያሉት ልጆችም እንደዛው። ምክንያቱም አላሸነፍናቸውም። ብዙወቹ ፊታቸውን ሸፍነው ነው ዬሚታዩት። ……" (አቶ ጌታነህ ከበደ ከቄራ አዲስ አበባ)
ሊንኩ ይለጠፋል።
 
EMS Eletawi Sat 22 Oct 2022
 
ማሸነፍ ልብን ነው። ልብ ከሸፈተ ድልድዩ ሰባራ ይሆናል። በዛው በህወሃት ህገ - መንግሥት፣ በህወሃት አሰባሳቢ ሎጎ እዬተመሩ ድርጅቱን ማውገዝ ዬፋደሰ ነው። እራሱ ማዕከላዊ መንግሥቱ የሚመራው በህወሃት መንፈስ ነውና። ታጥቦ ጭቃ።
ይህም ሆኖ በፍግፍግ፣ በማቃለል አያያዝ የታነፀን ልቦና መርታት ጋዳ ነው። ህወሃት አንፆታል። የህወሃት ፖለቲካ ጣዖትነት አይደለም በትግራዋይ በኢትዮጵያም፣ በመላ ዓለምም መንፈሱ አለ። 
 
እሱን ገድሎ በአዲስ መንፈስ የሚመራ የፖለቲካ አቅም፣ አቅመኛም አላዬነም። ከተቃዋሚ በለው፣ ከተዋኃጅ፣ ከመሪውም።
በኢህአዴግ በውራጅ አባላት እና አካላት መዳከር። እነ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ እነ አቶ አለምነህ መኮነን፣ እነ አቶ ደመቀ፣ እነ አቶአባዱላ ገመዳ፣ እነ ወሮ ሙፍርያት ካሜል? ነጮችም ዓይነታ ህወሃታውያን ይምሯችሁ የሚሉት ለዚህ ነው። ዬሚሞግቱት።
ይህም ሆኖ አሁንም በተዝረከረከ ሂደት አዲስ አበባ ያለውን ትግራዋይ በፍቅር ለመርታት ሳይቻል በባዕቱ የሃሳብ ትጥቅን አሟልቶ ልብን ዬሚያሸንፍ አዲስ ርዕዮትን ይጠይቃል።
 
እራሱ በዬከተማው የተካሄደው ህዝባዊ ስብሰባ በደርግ፣ በህወሃት ዘመን ዬነበረ ሶሻሊስት ርዕዮትን የተከተለ ነበር። በከተሞች ዬነበሩት ተናጋሪወች አዲስ አበባን ጨምሩ ምክትል ከንቲባወች ነበሩ። ድርጅታዊ ሥራ። ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት። ዬሆነ ሆኖ እነ ጋዜጠኛ ፍረወይኒን ለምን ተፈሩ?
 
ይህ በዚህ እንዳአለ አዲሱ የቲም ሲሳይ አወያይ ህወሃት እንኳን በባዶ እጁ ነው ዬሚወያዬው የአማራ ተደራዳሪ ግብረ ኃይል ምን አለው ሲል ይጠይቃል። መላሹ ጋዜጠኛ ፋሲል ዬኔአለም ጊዜ አናባክን ርባና ለሌለው ብሎ ይመልስ እና ጉዳዩን ያነሳል ይጥላል። ዬሰነፍ ሴት ቡሆዕቃ ትርክርክ ነበር። አቅም አለን።
 
ህወሃትን ዬሸኜው ዬኤርትራው የትጥቅ ትግል ወይንስ ሰላማዊ የተደራጀ ትግል ጣለው? የግለሰቦች ያልታሰበ የቆረጣ ተጋድሎ ነበር ዬሸኜው። ያን ጊዜም አንባሳደር ሱዛን ራይዝ፣ ያንጊዜም ዶር ቴወድሮስ አድኃኑም ነበሩ።
 
ከሥልጣን ማግሥት የዲፕሎማሲው ማህበረሰብ አቀባበል ለእናንተ ከወንዝ ዳር የታፈሰ አሽዋ ይሆናል? ምን አልባት ለእሳቸውም።
ለመሆኑ ውጥንቅጣቸው በወጣበት፣ ለኖቬል በታጩበት፣ ዬአመራ አመራር አካላት ፍጅት እና ተያያዥ ጉዳዮች በነበሩበት፣ ለምን ይሆን ዶር አብይ በድንገቴ እስራኤል ገብተው ያደሩ? ለዛውም እጅ መንሻ ይዘው? ለምንስ ይሆን የአውሮፓ ህብረት ፕሬዚዳንት ዶር ኡርዙላ በድንገቴ ኢትዮጵያ ዬተጋበዙት? ለዛውም ሹፌርነቱን ጠቅላይ ሚሩ ያስኬዱት።
 
በዛው ሰሞን ተመድም ስብሰባ ነበረው። ለጉባኤው ዬተወከሉት ፕሬዚዳንቷ ነበሩ። ያነበቡት ኢትዮጵያን ነበርን? ያነበቡት ዶር አብይ አህመድን ነበር። 
 
ለምን እንደዛ ተገደዱ? ለዚህ እንዲረዳችሁ የቅኔው ልዑልን ዬብላቴ ሎሬት ፀጋዬ ገ/ ገብረ መድህን አስተምህሮ እለጥፋለሁኝ። ከተጋሩ ጋር ዬሚያያዝ አይደለም። ስለምታጣጥሉት የአማራ አቅም መንገድ መስመር ቢቀይስላችሁ ነው።
 
ዝም ዬምንለው ድንኳን ሰባሪው ፖለቲከኛ በአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ስለሚበዛ፣ ጠላፊው ማን እንደ ሆን ስለምናውቅ፣ ያለፈው አቅም ያፈሰስንበት የኦነግ ሠርግና መልስ መሆኑን ስላዬን ዛሬም አሰፍስፎ ያለው ማን እንደሆን አስኳሉን ስለምናውቅ ብቻ ነው።
ሌላው የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትን በተደሞ ማመከር ስላለብን። እንጂ አቅሙ አለን። አታቃሉት። አታጣጥሉት፣ የአማራን የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ። ሙሉ አቅም አለን። ተቋማዊ የእናንተም ግሎባሉ አቅማችሁ ባዶ እጁን ገብቶ ተጠላይ፣ ተጠማኝ መሆኑን ታውቃላችሁ። ግለሰቦች እዩኝ እዩኝ የማይሉ ሙያ በልብን መከወን ይችላሉ። 
 
ዬአማራ መንፈስ ተቋም አልቦሽ መሆኑ ጠላፊው፣ የውስጥ አርበኛው ስላለ እርግጠኛ አይደለሁም። የተለካ፣ የተፈተነ አቅም ግን በእጅ እንዳለን ልነግርህ እወዳለሁ ለዕለቱ ኢኤምኤስ አወያይ። 
 
በተረፈ የህወሃትን መንፈስ ታቅፎ፣ የእሱን ውራጅ እያገላበጡ፣ እያሸጋሸጉ ይህን ያህል መታበይ፣ መንጠራራት አያስፈልግም። ዬሃሳብ ጥራት ነው የህዝብን ህሊና አጽንቶ የሚያረጋጋ። 
 
ውሽልሽል፣ ጥግንግን፣ ዝልግልግ ሲፈነዳ፣ ሲወታተፍ፣ እንዲያም ሲል በተደራጀ ቀውስ ስጋት እዬተቸበቸበ አገር አይመራም። ነዳላ።
አሁንም ትግራይ ውስጥ አይደለም በመላ ዓለም ያለውን ተጋሩ ህሊና ለማሸነፍ ዬሚችል ብቁ ዬሃሳብ አቅም አምጣችሁ ውለዱለት ይምራን ለምትሉት ሥንክሳር አገዛዝ።
 
ስለ ተደራጀው የአማራ ግብረ ኃይል ዬተወሰኑት እኔ ለሌላ ጉዳይ ቀድሜ ሪኮመንድ ያደረግኳቸው ቢሆንም ለጊዜው ዝምታ ይሰነቃል። ዬአማራ ተሳትፎ በድርድሩ እኔ ይኑር ብዬ ከፃፍኩ ስንት ጊዜው ነው። ከሰባት ወር በላይ ነው።
 
በአማርኛም በጀርመንኛ ጽፌዋለሁኝ። የቀደመም ተቋም ይሁን ሰው የለም። አልነበረም። እኔ ሳነሳው ሥሜ ሳይነሳ ከቤቴ ያለ ሰው በራሱ እስታይል ያቀርበዋል። ግን ታዛቢወች አሉ። በዝምታ ቀለም የሰከኑ። 
 
የሆነ ሆኖ አሁን ያለው የኃይል አሰላለፍ ዝንቅንቅ ስለሆነ በሁሉም መስክ እራስን ቆጥቦ መራመድ ይገባል። አቅም ለማን? አቅም ለምን? ስሌት። 
 
የእኔ ክብሮች የቀደመው ዕይታዬን፣ ከስብሰባው የታደሙት የአቶ ጌታነህ ከበደን ዕይታ ታገናዝቡት ዘንድ ተለጥፏል። መልካም ቀን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
24/10/2022
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ፍቅር ሲያልቅ ትዕግሥት ይሰደዳል።
ትዕግሥትም ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል።
~~~~~~~~~±±±±±~~~~~~~~~±±±±~~~~~
 



 
"ድብ ያለ የተጋሩ ህዝባዊ ስብሰባ በአዲስ አበባ።"
"ዬቤትህ ቅናት በላኝ።"
ርቀቱ ይፋ ሆኖ ይታያል። የኦነግ መራሹ ኦህዴድ ሰሞኑን ለትግራይ ህዝብ አንድ ስብሰባ በአዲስ አበባ አካሂዷል። ዬስብሰባው ጭብጥ እና የተሰብሳቢወቹ ውስጥ ግን አልተገናኜም። በጣም ዬተራራቀ ሆኖ አይቼዋለሁኝ። ቅድመ መሰናዶው እንብዛም ነው።
በተለይ አዲስ አበባ ተውልዶ ላደገ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዬኢትዮጵያዊነቱ አመክንዮ ለድርድር አይቀርብም። የአዲስ አበባ ሰው ግሎባልም ነው። ሃሳቡም ስልጣኔውም ልዩ ነው።
ዘመን አሜኬላ አበቀለ እና በክ/ አገር መጠራራት ቀርቶ በዞግ ሆነ መለያው። ያም ሆኖ አዲስ ልጆቿ ዬማይናወጥ አቅም፣ የማይታወክ አቋም አላቸው። ዬተጋሩ ልጆችም በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ይታያሉ።
ከአራት ዓመት ወዲህ ብዙ ነገሮች አልፈዋል። እላፊ ዬሄዱ አገላለፆች ከመሪ ጁምሮ። ከንቲባ አዳነች አበቤ የዛሬ ዓመት "ፈንግጡት ሰባራዋ ወፍ ሳትቀድማችሁ የሚል ዕድምታ ያለው ንግግር አድርገዋል። ምላሹ አሳንጋላ ነበር። የሰው ልጅ ሊሸከመው ዬማይችል። ያን ምሬት ያመጣውግድፈቱ ነበር።
ከንቲባዋ ያን ሲሉ ቤተኛቸውን ትተው፣ ዘንግተው እረስተው ነበር። አሞኝ ስለነበር ለ45 ቀን አልነበርኩም እንጂ በልኩ ይነገራቸው ነበር። ህግ ተከብሮ፣ ሥርዓት ተይዞ። ትርፍ ነገር አይገባም። ዕዳ ከሜዳ ስለሆነ። ለወጣቶችም ሊታሰብ ስለሚገባው። ጠቃሚም ስላልሆነ። የሃሳቡን አመክንዮ ስለሚያትረከርከው።
ዬሆነ ሆኖ።ስክነት። አዲስ አበባ ከንቲባነት ግሎባል ድርሻ አለው። አህጉራዊ ሚና አለው። አዲስ አበባ የኗሪወቿ ብቻ ሳትሆን የዓለም የዲፕሎማቲክ መናህሬያም ናት።
ያው የሳሙና አረፋው የፌንጣ ፖለቲካ አደብ ነስቶ ይኮረኮዳል እንጂ የአዲስ አበባ፣ የቬይና፣ የጄኔብ፣ ዬኒወርክ ከንቲባወች ስታንደርዳቸው እኩል ነው።
በአፍሪካ ደረጃም ሲታይ ዬአፍሪካ ህብረት መናገሻ ከተማ ናት አዲስ አበባ። አዲስ አበባ፣ የዓድዋ፣ የማይጨው፣ ዬካራማራ ዬድል መሰብሰቢያ ቋትም ናት። ቅኝም ይሁን እጅ አዙር ቅኝ ግዛት ቅስሙ በዓለም የተሰበረበት መናኽሪያም ናት። የጠይም ዳያመንድ ሉላዊ ርዕሰ እጬጌ።
በሳይንሱም የሰው ልጅ መገኛ የሉሲ መናገሻ ከተማ ናት። አዲስ አበባ ልኳን አሳንሶ ቶሬ ላይ እንዳለው ዬአሰቃቂ ዬግድያ እና ዬመፈናቀል አናርኪዝም ተውኔት ዕሳቤ ለአዲስ አበባ ነዋሪ የመብራት ቆጣሪ ሁንልኝ ማለት ዬተገባ አልነበረም።
ከዛም ያለፈው "የፀጉረ ልውጥ" ፖለቲካ ሃሞት የሆነ ጉዳይ ነው። ህወኃት 47 ዓመት ሙሉ ፀንሶ ዕውን ያደረገው ጣሊያን ቀብሮት ዬሄደው ፈንጅ ተፈፃሚነቱ ስለደላው በዞጉ ትግራዋይ ለሆነ ሁሉ ዕዳ ከሜዳ አሳፍሶታል። እንጂ በአገር ምስረታ፣ በመንግሥት አደረጃጀት፣ በመንፈሳዊ ኃብታት አንቱነቱ ደማቅ ነው።
በህወሃት የሥልጣን ስቃያዊ አግላይ ዘመን የትግራይ ህዝብ ዝምታ የውጩም የአገር ውስጡም የወገን መከፋት ጫን ተደል ዬሆነ ረቂቅ መከፋትን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ አሳድሯል። አይታይም። አይጨበጥም። አይዳሰስም። ግን ለምፁ አለ። ይፋ ይቅርታ ስላልተጠዬቀበት። በዚህ መሃል ነው ጦርነቱ የተነሳው።
ህወሃት የትናንቱ ላይበቃ በጦርነቱ በአማራና በአፋር በሥልጣን ዘመኑም፣ ከዛ ቀደም ዬሆኑትንም የሥልጣኔ ውጤቶች አመድ አስግጦታል። የዶር አብይ አህመድን ቁንጫን መወጣጫ ይህ ህዝብ ነበር።
በዚህ መሃል በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ለሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ቀላል ጊዜ አልነበረም። ጦርነቱ ትግራይን፣ አማራን፣ አፋራን፣ በቀሉም እንዲሁ ድቀትን አምጥቷል። መቅኖ አሳጥቷል።
ጦርነቱ ከመነሳቱ አስቀድሞ ከጦርነት ዬሚታፈሰው አመድ እና በቀል ነው ብዬ ነበር። የሆነውም ይኽው ነው። ጦርነቱ ብቻ ሳይሆን የጥላቻ ዓይነት እና ጥቁር ስኬቱን ታዝበናል።
አፋን ሞልቶ ሁሉም ቦታ እኛ አለን ሲል ህወሃት ለትግራይ ልጆች አልራራም። ሚሊዮኖች በተለያዬ ከተማ ይኖራሉ። ሲቆጣጠርም ትጉህ ተሳትፎ ዬትግራይ ልጆች አድርገዋል። ደሴ፣ ሽዋ ሮቢት ይህ ተደምጧል። ይህ ለፖለቲካ ትክክለኝነት ተብሎ ይለፈኝ ሊባል አይገባም። ጥፋት ነውና።
በዶር አብይ መንግሥትም ህወሃት እዬገፋ ሲሄድ በጅምላ በአንድ ካንፕ ዬማሰባሰቡም ሁነት ነበር። በዚህ ሁሉ ውስጥ ከጉዳዩ ጋር ንክኪ ዬለላቸውን ጥሞና ወስዶ የማጣራት ተግባር ብቻ ሳይሆን የመንከባከቡም ጉዳይ ያን ያህል ነበር። ሰሞኑን አንድ መምምህር ሰው ራበን ያሉትም ከዚህ አንፃር ነው። የሆነው ሁሉ ለሰሚውም፣ ለፍርድም የቸገሩ በዝምታ ያለፍናቸው በርካታ ቀናቶች ነበሩ።
አሁን ከሦስተኛው የህወሃት ጦርነት በኋላ የትግራይ ልጆች ሰላማዊ ሰልፍ በአንዳንድ ከተሞች፣ ስብሰባ አዲስ አበባ ላይ ነበር። ስብሰባው የውስጥ ሐዲዱ ዬጠና አልነበረም። #ያረገረገ ሆኖ ነው ያገኜሁት።
ጊዜያዊ መከፋት፣ ጊዜያዊ ሳቅ፣ ጊዜያዊ ደስታ አፍለኛ ነው። የታመቀ መከፋት፣ ሐሴት፣ ደግሞ ዘላቂ ነው። ጊዜ ይጠይቃል። ሐሴት ከደስታ በላይ ነው።
በዛ ስብሰባ ያዬሁት መከፋት አለ። ዬሰብሳቢወች ደጋግሞ ህወሃትን ማንሳት መጣል እና ዬደከመ አገላለጽ ስብሰባውን ድብ እንዲል አድርጎታል። ቀዝቃዛ ስብሰባ ነበር። ሬሳ የሚሸኝበት ያህል እንኳን አቅም አልነበረውም።
በስብሳው ውስጥ የተለያዩ ሃሳቦች ተነስተዋል። ምስሎች ግን ከሃሳብ በላይ ይገልፃሉ። ፋና ላይ ስለአለ እዩት።
አንዲት አንስት መልካቸው እንዳይታይ ይታገሉ ነበር። በጣም። ፍላጎታቸውን አላገኙም ማለት ነው። በትክክል ውስጠ ገብ ገለፃ አልተደረገም። ድሪቶው አገላለፅ ህወሃትን አሁንም ቅድምም መነሳቱ ብቻ ነበር።
ብዙም ተሰብሳቢ አልነበረም። በተለይ መድረኩ በረዶ ነበረ። ትንታጓ ጋዜጠኛ ፍረወይኒንም አላዬኋትም። በስብሰባው ዬቀረበ ሎጅካዊ ገለፃ አልነበረም። ያልተገናኜ የሃሳብ ገብያ ነበር። እንኳን ለጉዳዩ ባለቤት ለአልፎ ሄጅም የማይሆን ማኔጅመንት ነበር እኔ ያዬሁት።
ተሰብሳቢወች ሰንቀው ዬተመለሱት አንዳች ነገር አለ ብዬ አላስብም። እራሱ ለእኔ ዬስብሰባው ዓላማ እና ግብ አልገባኝም። ትርፋ ምን ነበር?
ዬህወኃት ፖለቲካ፣ የቀደምት የተጋሩ ሊሂቃን እና ሊቃናት ፖለቲካ፣ እና መሪ ፖለቲከኞች አመክንዮ በተርቲም የቡና ውሎ የሚፈታ አይደለም።
ዬህወኃት ፖለቲካ ከሶሻሊዝም ከአልባንያ፣ ከፍጅት ከስታሊን ቅኝት፣ ከቅኝ ገዢወች ከጣሊያን፣ እና ከጨካኞች ዬህይወት ልምድ የተቀዳ ነው። በዛ ላይ ዞጋዊነት ምርጥ ዘረዊነትም አለበት። ልታቃልለው አትችልም። አላዬሁህም አልሰማሁህም ልትለው አትችልም።
በደርዙ፣ በልኩ በቂ አትኩሮት ሰጥቶ በህሊና ውስጥ የተገነባው ዬአዳኝነት መንፈስን መካች ሃሳብ አምጦ መውለድን ይጠይቃል። ለፕሮፖጋንዲስቶች የማይመች የፖለቲካ ዕይታ ነውና። ተያያዥ ጉዳዮችም ትብትብ ናቸው። ዘመንንም ጠጥተዋል።
የኢትዮጵያን ሠራዊት ምርኮኛን በውሻ መርዝ መግደል፣ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ያደረጉትን ተጋሩን ሳይቀር በግፍ ከጎንደር ዬአማራ ህዝብ ጋር የፈጁበት ሁነት፣ የ27 ዓመት የአገዛዝ ዘመን እና የዜግነት ክብር፣ የአሁኑ ጦርነት እና ኪሳራው ሲመዘን በለብ ለብ ገለጣ ዬሚደፈር አልነበረም።
በግሎባሉ ዓለም ኢትዮጵያን ፈተና ውስጥ የጣለው ዬዲፕሎማሲ ሞገድም አለ። ትናንት የመምህር አብርኃም ደስታ ቲውተር አካውንቱ ላይ ዬፃፈውን አንብቤ፣ አስተያዬት ሰጪወችንም ታደምኩበት። ገርሞኛል።
የሰው ልጅ የክት እና ዘወትርዓለም እንዳላት የታዘብኩበትም ዘመን ነው። ለዚህ ነው ተመድ እንደገና መደራጀት አለበትም እምለው። ሰው ስለሰው በተደራጁት ተቋማት ማዕከልነቱ አክትሟል። በምክንያታዊ ጉዳይ ሳይሆን ሳቢያዊ ላይ የማይፈስ አቅም ዬለም።
እርግጥ ዛሬ አቶ አብርኃም ደስታ ሻል ያለ ሃሳብ አቅርቧል። የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ሮል ሞዴልም ነበር። ሁሌ ከአንደበታቸው የማይወጣ።
ይህን ያነሳሁት እራሱን የቻለ ግሎባል ቻሌንጅ የሚያመጣጥን የፖለቲካ አቅምን ይጠይቃል እያልኩ ነው። አዲስ አበባ ላይ ያዬሁት የከበደኝ የኦዲዬንሱ ምላሽ ትግራይ ላይ ብዬ ሳስብ ገዘፈብኝ ክብደቱ። ጥራት፣ ጥንቃቄ፣ በቂ የህሊና መሰናዶ የሚጠይቁ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ፊትለፊት ይጠብቃሉ።
ዬተደራጀ የሃሳብ አቅም ይጠይቃል። የዕለት ደራሽ ምግቦች፣ ሸቀጣ ሸቀጦች፣ መዳህኒቶች ብቻ ሳይሆኑ ህሊናን የሚያሰናዱ የዕውነት አመክንዮዊ ዬሃሳብ አቅም አምጦ መውለድን። ይቻላል ወይ አይመስለኝም።
ምክንያቱም ህወሃት ያበቀላቸው ችግኞች የግንዱን ፖለቲካ ምራኝ ብለው፣ ያን ታግለው ህዝብን የራስ የማድረግ አቅም ከዬት ይሸመታል? አሉ የሚባሉ የኦነግ፣ የኦህዴድ፣ የብአዴን፣ የደህዴን ሊቃናት የህሊና ምርታቸው ማሳ የህወሃት ማኒፌስቶ ምንጭ ፖሊሲው እሱ በእሱ ነውና።
ስብሰባው በቂ መሰናዶ ይጠይቅ ነበር። በሳል ሚዛናዊ እና ሰዋዊ ፀጋ ዬተሰጣቸው አመክንዮዊ ገላጮች ያስፈልጉት ነበር። ብቻ "ዬእነ ቶሎ ተሎ ቤት" ሆነ እና የልብ የማያደርስ ሆነ። ጦርነቱ ከቀጠለ ስሜን ኢትዮጵያ ወጣት አልባ ትሆናለች። ቅርሱ፣ ውርሱ፣ ታሪኩ፣ ሥልጣኔው በባሰ ሁኔታ ይማቅቃል። ይህ ሁሉ ፍርጥርጥ ብሎ ሊገለጥ ይገባ ነበር።
ሌላው ሚዲያወች የሚቀጣጥሉት መከራ ሸክም ነው። የበለጠ ይጫናል። ህወሃትን በሥሙ ጥሩት። ቤተ - መንግሥት ኦነግ የለንም? በሚር መሥሪያ ቤቶች ኦነጎች ዬሉንም? መከላከያ ውስጥ ኦነጎች ዬሉም?
ቤተ - መንግሥቱ በህወሃት ህገ መንግሥት አይደለም ወይ ዬሚተዳደረው? አቶ ወንድም አቤ ቱኩቻው "ህገ - መንግሥታችን" ሲል ውዷ ሳቄ ፈነዳች።
ያ ፀረ አማራ፣ ፀረ ኢትዮጵያ፣ ፀረ ዜግነት፣ ፀረ አንድነት ህገ - መንግሥት ነበር አቤን ያሰደደው፣ በዛ ህገ መንግሥት ነው እንደ ገና ዛሬ ደጋፊ ዬሆነው። ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
የባለሥልጣን ሽግሽግ፣ የዞግ ለውጥ ብቻ ነው ያለው። ዬተጋሩ ሊሂቃን ተሸኙ ዬኦሮሞ ሊሂቃን የሚኒሊክ ቤተ - መንግሥትን ተረከቡ።
ዬሚያጣላ ምንም ነገር አልነበረውም። እንኳንስ ጦርነት የሚያስከፍት። ሁለቱም ኦነጋዊው ኦህዴድም ህወሃትም ዬሄሮድስ መለስ ዜናዊ የሙት መንፈስ ምርኮኛ ናቸውና። ኢትዮጵያ ዬምትመራው በሄሮድስ መለስ ዜናዊ የሙት መንፈስ ነው፣ አሁንም።
ዬማይመጥን ስብሰባ ከማድረግ መተው ይመረጣል። መካች አልነበረም። የግብር ይውጣ ሂደት ነበር ያዬሁት። ይህ ደግሞ ለቀጣይ ጠቃሚ አይሆንም። መሠረት አስይዞ መጀመር ያስፈልጋል።
መሠረቱዕውነት፣ መርህ እና ፋክት ሊሆን ይገባል። ትውልድ በዬዘመኑ የሚመተርበት እንቆቅልሽ ሊፈታ ይገባል። ዛሬም የተረገዙ ነፍሰጡር ገመናወች ስለማይም።
በመጨረሻ ቃለ ምልልስ ላይ እባካችሁ ተጠንቀቁ። በተለቀቁ ቦታወች ምንም ቃለ ምልልስ አታድርጉ። የኃይል አሰላለፋ ዝንቅንቅ ነውና። አረበኛ መሬ ወዳጆ በጀርባ ሊመታ ነበር። ነገም ዬሚሆነው አይታወቅም።
ትናንት ከEMS ዕለታዊ ዜና አንድ ካህን ያደረጉት ቃለ ምልልስ ነበር። ጠያቄው መልሱን እራሱን መልሶ ይጠይቃቸዋል። እሳቸው እሱ ያለውን ይደግሙለታል። ተፈጥሮው የነጠፈበት ነበር።
የእኔ ስጋቴ ነገ ለእኒህ ካህን ማን አላቸው ነው። ቃለ ምልልስ ለሚሰጡ ወገኖች ማንም ጥግ ዬላቸውም። የትኛው ወገናቸው ጥቃት እንደሚፈፅምባቸውም አይታወቅም። አስፈላጊም አይደለም።
ዝምታ የሰፈነበት ኦፕሬሽን በዛው ቢዘልቅ ነው ዬሚሻለው። ህዝብን ለድጋሚ የበቀል ሰቆቃ አይዳረግ። ለፕሮፖጋንዳ ተብሎ ሰው አይለቅ። ዝም በሉ እስኪ ቻሉት። ጦርነቱ እኮ የእርስበርስ ነው።
ሌላው ተግባር እንዲመሰክር መተው ይገባል። ለጥቃት ህዝብን አታጋልጡ። ምርጫውን ለትግራይ ህዝብ ይሰጠ። የሚጠቅመውን ይምረጥ። መቼም ጥቅሙን የሚፃረር ተጠቃሚ አይኖርምና። ከጠቀማችሁት ይመርጣችኋል፣ ካልጠቀማችሁ አንሻም ይላል። የነቃ ህዝብ ነው።
ዬሰው ህይወት እና ፕሮፖጋንዳ ይለይ።
በፎቶው ውስጥ ያለውን ግብረ ምላሽን ለኩት። እግዜአብሔር ይስጥልኝ። አሜን።
 

 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
21/10/2022
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።