#ኢትዮጵያ "ጋለሞታ" አይደለችም። አበስኩ ገበርኩኝ! ስለአገላለፁ። "ህግ ተላላፊወችን ጠላሁኝ።" #ኢትዮጵያ የማንም "ውሽማም" አይደለችም። ማህከነ። "ለአንደበቴ ጠባቂ አኑርልኝ።"

#ኢትዮጵያ "ጋለሞታ" አይደለችም። አበስኩ ገበርኩኝ! ስለአገላለፁ።
"ህግ ተላላፊወችን ጠላሁኝ።"
#ኢትዮጵያ የማንም "ውሽማም" አይደለችም። ማህከነ።
"ለአንደበቴ ጠባቂ አኑርልኝ።"
 

 
ይኽው ሊንኩ።አገር ከበለጠባችሁ፤ ዬጊዜ አታሞ ካልረታችሁ።
የአሁን ዋና ዋና መረጃዎች!DereNews Oct. 19 2022 #derenews#zenatube#Ethiopiannews#
ኢትዮጵያ "ጋለሞታ" ስትባል፣ ኢትዮጵያ "ዬማንም ተወሻሚ" ስትባል አይጎረብጥም፣ አይቆረቁርም? ስለማን የምን ንጥረ ነገር ይሆን ዬሚተነፈሰው?
ውስጣችን ለእናታችን እንዲህ ሸካራማ፣ ኮረኮንችማ፣ አሜኬላ በቀል። ከእናት አገር ጠረን ዕለታዊ ሰብዕና በልጦብን ይሆን?
ኢትዮጵያ ከቅኔም፣ ከስዋሰውም አልፋ እና ንራ ኢትዮጵያ #ሰማያዊ #ምስባኽክ ናት።።።።።።።።።።።።። ቫወልም ናት። አናባቢ። ኮንሰነትም ናት ተነባቢ።
ጎንደር ላይ ሲዘንብ የባጀው የዲን በረድ አሁን ኢትዮጵያ ላይ ደግሞ መጥቷል። በተለይ "ኢትዮ" ብላችሁ ምንም ተቋም የምትከፍቱ፣ የምትጀምሩ ወገኖቼ በልኳ ለመሆን እሰቡበት።
ኢትዮጵያ ረቂቅ መንፈስ ናት። የራሷ ዬሆነ አንጡራ ማንነት ያላት የድንቅነሽ ድንቅ ናት። ዲስፕሊኑን የመጠሪያዋን ዬሚመጥን፣ የሞራል አቅም ይጠይቃል። የአውራ አገር መጠሪያ ነውና። ዬማይፋድስ፣ ዬማይነጥፍ ፏፏቴ ሥም ነው ያላት ኢትዮጵያ አገራችን።
ይህን ብዬ ዬፃፍኩት በ2014 ደጉ ዘሃበሻ እና ደጉ ሳተናው ላይ ነበር። በፀጋዬ ራዲዮም በተደጋጋሚ አቅርቤዋለሁኝ። በቅርቡም ጹሐፋን በንባብ ዩቱብ ቻናሌ ለጥፌዋለሁኝ። ሊንኩን አስቀምጣለሁኝ።
ገናናው የኢትዮጵያ ረቂቅ መንፈስ አሸናፊም ነው። ዬትም መቼውንም። ዬኢትዮጵያ መንፈስ አገራዊ ብቻ አይደለም ግሎባልም ነው። ከኢትዮጵያ ዬሚነሳው ወጀብ፣ ንፋስ፣ ጦሮም ዓለምን የማካለል አቅም አለው።
ኢትዮጵያ ለእኔ አገር ብቻ አይደለችም። አቅሟ፣ ክህሎቷ፣ ግርማ ሞገሷ #አህጉራዊ ነው። እኔ እንደ አኽጉር ነው እማያት። በዬትኛውም ወጀብ፣ በዬትኛውም ጊዜ፣ በዬትኛውም ሁኔታ ሚስጢሯ ኃያል ነው።
የዓለምን የመንግሥታት ድርጅት ቀልብ ስቦ ቁጭ ብድግ የሚያደርጋቸው እስትራቴጂ ጠቀሚታዋ ብቻ ሳይሆን ተዝቆ ዬማያልቅ የቀደምትነት ጣዝማ ጠገብ የመንፈስ፣ የውርስ፣ የቅርስ፣ የዕውነት፣ ዬታሪክ ዝቀሽ ማህለቋ ነው።
ኢትዮጵያ "ጋለሞታ" አይደለችም። በፍፁም። ኢትዮጵያም እንደ መፀዳጃ ቤት ማንም የሚቀመጥባት "የሚወሽማት" አይደለችም። በፍፁም። ተሳህለነ!
#ፍቺ ከግብታዊነት፣ ከግንፍልፍል ዬፀዳ።
"#ጋለሞት" አብዝቼ ዬምጠዬፈው ነውረኛ ቃል ነው።
"#ውሽማ" እጅግ አብዝቼ ቅፍፍ ዬሚለኝ ቃል ነው።
"#ቁሪንዲዳ" ይህንም ነፍሴ ይጠዬፈዋል።
"#ሸርሙጣ#ሴተኛ አዳሪ" ይህን ቃልም አልወደውም።
እነኝህ እና መሰል ጠያፍ ቃላት ከመደበኛ ዬአማርኛ ቋንቋ ቢወጡ ፍላጎቴ ነው። ከዚህ ቀደምም ጽፌበታለሁኝ። ዬአማርኛ ቋንቋ እንደ ጀርመንኛ ቋንቋ ዲታ ነው።
መጣኝ ቃል በብዛት አለ። ዬአማርኛ ቋንቋ ያሰበለም ነው። ዬአማርኛ ቋንቋ ለቅኔ የተፈጠረ ቋንቋ ነው። ልሳኑ ሳቢ ነው። ቋንቋውን የማያውቁት ሁሉ ሊያደምጡት የሚፈቅዱት ወለላ ቋንቋ ነው። ይጣፍጣል። ይጥማል። ይመስጣልም።
ሲሳይ ሞልቶ ዬተትረፈለት ዬአማርኛ ቋንቋ መፍቻው ዝቀሽ ነው። አሁን ለምሳሌ ላነሳኋቸው አቻ አግባቢ ሥንኛትን መጠቀም ይቻላል።
ዕውነቱን ብነግራችሁ እነኝህን ጠያፍ ቃላት ስጽፍ ቅፍፍ እያለኝ ነው። ከግምት ያወርዳል። ከሚዛን አውርዶ ይፈጠፍጣል። ከእሳት እንደገባ ፕላስቲክ ያኮፈታትራል።
ነገረ ኢትዮጵያ ሆነና እና ግድ ሆነ።
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"
1) "ጋለሞታ" አግብታ ዬፈታች፣ ለማግባት ያልፈቀደች፣ ጋብቻን የሸሸች፣ ዬትዳር አጋሯ በሞት ዬተለዬ፣ ተብሎ ሊገለጽ ይችላል።
2) "ውሽማ" ዩተመሰጠረ ፍቅረኛ፣ ቅምጥ፣ የተከደነ የፍቅር ግንኙነት ሊባል ይችላል።
3) "ቁሪንዲዳ" አፍሪካውያን ጥቁር ነን። ጠይም ማለት ይቻላል። ከጠይም ከበረታ ቡኒ ማለት ይቻላል።
4) "ሴተኛ አዳሪ" በፆታዋ የምትተዳደር፣ ፆታዋ ዬዕለት ገቢዋ ዬሆነ ማለት ይችላል። "ሸርሙጣ" ለሚለውም #አመንዝራ ዬሚለው ይሻላል። ሁሉም መኖር የሰጠው እና ባለመመቸት ዬመጣ ዬግዴታ ዕጣ ፈንታ ነውና።
"ጋለሞታ" ዬሚለው ጠያፍ ቃል "ውሽማ" ተከትሎ ዬሚመጣውው "ሸርሙጣ" ይሆናል። ሂደቱን በቁሙ ስንተረጉመው።
"ጋለሞታ" + "ውሽማ"= "ሸርሙጣ።" በእኔ አገላለጥ አመንዝራ።
ይህ ለአንድ ሰብዕና ለወ/ሮ ሃመርውኃ ወይንም ለወ/ት ሀሌታው ሀ ሲሆን እንኳን ይከብዳል። እጅግ ይከብዳል።
ኢትዮጵያን ያህል፣ ባለ ልቅና ክብርት፣ አደበሙሉዑ፣ ዬዊዝደም ቅድስት፣ ዬብቃት ልዕልት፣ ዬምንግዜም ንግሥት፣ አገር "ጋለሞታ" ያገኜ "የሚወሽማት"= ተከታዩ ባይጠቀስም "ሸርሙጣ" ይመጣል።
ይህን ዬተናገረው አቶ ኤርምያስ ለገሠ ዋቅጅራ ቁንጮው የፖለቲካ ተንታኝ ዬሚኒሊክ ቴሌቢዥን፣ የጽዋ ሚዲያ፣ የቤተሰብ ሚዲያ፣ ዬአባይ ሚዲያ፣ አሁን ከስሟል ዬአውሎ ሚዲያ፣ ዬርዕዮት ሚዲያ፣ የኢትዮ 360 ሚዲያ አንደበተ ነው።
አንድ ጊዜ አቶ ኤርምያስ ስለ መጀመሪያ ልጁ ዬኢትዮጵያዊነት ስርፀት ዬፃፈውን ደጉ ሳተናው ላይ አንብቤው ነበር። አባትነት እንዲህ ነውም ብዬ ነበር። ማህተሙም ከውስጤ በቅሏለኝ።
ልጁንም በስስት በዜና ዛሬም እወዳታለሁኝ። ዛሬ ትልቅ ሆና ይሆናል። ይህን ኢትዮጵያ ከፍና ዝቅ ያደረገ፣ ርህርህና ቢስ አዋራጅ ዬወላጅ አባቷን ገለፃውን ስትሰማ ምን ትታዘበው ብያለሁኝ። ዬዛሬ ልጆች ብስል ናቸው።
አቶ ኤርምያስ ለገሠ ዋቅጅራ ያ ሁሉ ዘመን የደከመበት፣ አሁንም ዬሚደክምበት እንዲህ ላለች ኢትዮጵያ ነውን? እናት ትዳር ባይኖራት፣ ልጅ አሳድግ ብላ አይሆኑ ብትሆን፣ ብትጠቁር - ብትከሳ፣ ብትጎሳቆል፣ ቢርባት - ቢጠማት እንኳን #ሽቅብ "ጋለሞታ" ተብላ ልትሰደብ፣ ልትዋረድ፣ ቀን ዘንበል ቢልባት፣ ልትቃለል አይገባትም። ፈፅሞ።
ሰሞኑን የሩህሩሁን አርቲስት የአቶ ማዲንጎ አፈወርቅን ደግነት ከቃለ ምልልሶቹ ሳዳምጥ ሰነበትኩኝ። አንድ ትውልድ የሆነ ኃይለ ቃል አገኜሁኝ። "ለወላጆቼ መልስ ሰጥቼ አላውቅም።"
እንዴት የታደለ፣ የተባረከ ልጅ ነበር? ይህ እራሱ ተቋም ነው። ወንጌሉም "እናት አባትህን አክብር" ይላል። ባላገኝህም ውዱ አርቲስት ማዲንጎ አሳዳጊህን ይባርከው። የቃሉን ሕይወት ኑረኽዋል።
እኛ ያላከበርናት እናት ኢትዮጵያ ማን እንዲያከብራት ይፈለጋል? ባለ ቅኔወቹ ጎንደሮች "ባለቤት ያቀለለውን አሞሌ ባለ ዕዳ አይቀበለውም" ይላሉ።
ያለው ነገር ሁሉ ዬእኛ የራሳችን ዳንቴል ነው። የውጮቹ ሚዛን ያጡት ተመጣጣኝ፣ ሚዛን ዬሚያስጠብቅ ሥራ ስላልተሠራ ነው።
ከአገዛዙ ውጬ የሆነ ክብሯን ዬሚያስጠበቅ፣ ዬጉዳቱን ልክ በልኩ ዕውቅና ዬማሳጣት፣ የፈንግጪው ጉዳይ ሆኖ እንጂ ቢሠራበት ዕውነት ላይ ሚዛን ፍትህ እንዲሰጥ ማድረግ በተቻለ ነበር።
ሁሉም የአገሩ አንባሳደር ነው። ትንፋሻችን ያለው ኢትዮጵያዊ ተብለን፣ በዓለም የታወቀች አገር ስላለን ነው። የእናት አገር ልዕልና እንዳይዳፈሩት ማድረግ፣ ማስደረግ ከእያንዳንዱ በግል፣ ከሁሉም በጋራ የሚጠበቅ ግዴታ ነው።
እያንዳንዱ ውጭ የሚኖር ቢጠላትም፣ ቢያዋርዳትም፣ ቢያቃላትም ሥሙ ኢትዮጵያዊ ነው። ትውልደ - ኢትዮጵያዊ ነው ዬሚባለው። የፈለገ ቢያንገሸግሽው።
ኢትዮጵያ ያገኜ "ቢወሽማት" ኖሮ ዛሬ ኢትዮጵያ ሥሟም ሁለመናዋም ሌልኛ ይሆን ነበር። የአፍሪካ አገሮችም ነፃነታቸውን አያገኙም ነበር።
አንድ ቦንብ ዬሆነ ሃሳብ ላቅርብ። ኢትዮጵያ የዓለምን የዘመን ፖለቲካ የቀዬረች #ዩንቨርስ ናት። ሙሉ ግሎባል ዘመን የመቀዬር ዕምቅ አቅም አላት እመቤት ኢትዮጵያ የጠይም ዕንቁወች ምድር።
ዓለም ጠይም ዳያመንድ መሆኑን ተገዶ ዬተቀበለው በኢትዮጵያ የመንፈስ አቅም ነው። ቃና ናት ለሰውኛ፣ ለነፃነት፣ ለአህጉር ህብረት፣ ለዓለም አንድነት ቀለም ናት፣ ሸማ ናት፣ ጌጥ ናት፣ በራስ ዬመተማመን አስኳል ናት። ቅመም። ጽዑሚት። ተደሟዊት።
ኢትዮጵያ ሥሙ ኃይለ ቃሉ እራሱ ተፈሪ ነው። ኢትዮጵያ "አሽንፋ" አታውቅም ሲባልም ሰምቻለሁኝ። ግጥም አድርጋ አሸንፋ ኢትዮጵያዊ ዬሚል ማንነት ቀርፃለች። ፈጥራለች። ዓለምን አስደምማለች።
ኢትዮጵያ ዬሚባል አገር በዓለም ካርታ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዩንቨርሥም ሥሟ ፃድቅ ነው። ኢትዮጵያ ተሸንፋ አታውቅም። ሁለመናዋ አሸናፊ ነው።
እኔ ስላልኩት አይደለም ስለአሸነፈች ነው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ተብለን ተሰደን እንኳን መኖር የምንችለው። ባታሸንፍ ወይ ዬሞቃድሾ፣ ወይ ዬኢጣሊያን፣ ወይ ዬእንግሊዝ፣ ወይ የፖርቹጊዝ፣ ወይ የኡቱማን ቱርክ ፓስ ነበር ዬሚኖረን። ቅንጣት የእኛነት የማንነት እንጥፍጣፊሚ ባልኖረን።
ዛሬም ትንፋሻችን ዬሚደወረው ኢትዮጵያዊ ተብለን ነው። ተቋማችን ኢትዮጵያዊ ተብሎ ነው ህጋዊ ዕውቅና ዬሚያገኘው። የምንሠራበት ቋንቋም ኢትዮጵያዊ አማርኛ ቋንቋ ነው። ተጽዕኖ ፈጣሪነቱ ከኢትዮጵያ የሚቀዳ ነው።
አኗኗራችን ያው ኢትዮጵያዊ ማዕዛ እና ለዛ ያለው ነው። ዕውነትን መጨቆን፣ በዕውነት ላይ ዲስክርምኔሽን መፈፀም ለሰው ይቅር ለፈጣሪ ፀጋ አይሆንም። ምርቃት ሲነሳ ልጥ መሆን አለና። #ስጦነት
ኢትዮጵያ ዬአዬር ፀባዮዋ እራሱ ለመዳህኒት ዬሚታዘዝ ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሥርዓት ጥልቀት እና ምጥቀት በራሱ በቂ ነው። እያንዳንዷ ዬተዋህዶ ተደሞ ዕፁብ ድንቅ ነው። ከሌላ ተዋህዶ ዬማይገኙ የፍጽምና ልዕልና አለን በቤታችን።
በዓውዳችን። በመንበራችን። በባዕታችን። ዬራሳችን የሆነ ዘይቤ ያለን ሕዝቦች ነን። አናፍርበትም። በራስ የመተማመን አቅማችን በቂ ነው። የተቀዳው ከፏፏቴዋ ልዕልት ኢትዮጵያ ነው። 

 
ኢትዮጵያ ሳይንስ ናት።
ኢትዮጵያ ፍልስፍና ናት።
ኢትዮጵያ ዩንቨርስ ናት።
ኢትዮጵያ ዬፊደል ገበታ ናት።
ኢትዮጵያ ፓን አፍሪካኒስት ናት።
ኢትዮጵያ ሉላዊ ናት።
ኢትዮጵያ የአውሮፓ ሥልጣኔ በኽረ ናት።
ኢትዮጵያ ነፃ አገር ናት።
ኢትዮጵያ ቀደምት ናት።
ኢትዮጵያ ዬኪነ ጥበብ ዓውደ ምህረት ናት።
ኢትዮጵያ የራሷ የፊደል ገበታ፣ የፁሁፍ ታሪክ ያላት አገር ናት።
ኢትዮጵያ መኖር ለማኗኗር ጥበብ ያላት አገር ናት።
ኢትዮጵያ ከዓለም ተለይታ ዬ13 ወራት ባለፀጋ ናት።
ኢትዮጵያ ሁሉም ለሰው ልጅ፣ ለእንሰሳ፣ ለዕፅዋት፣
ከአበባ እንኳን ብሔራዊ አበባ አድዮ አላት። ለፍጥረታት ዬሚያስፈልጉ ነገሮች ሁሉ ያላት አገር ናት። ኢትዮጵያ ዬሰው መፈጠሪያ ዬሉሲ እናት ናት፣ በሳይንሱ።

 
ይህ "ከጋለሞታ" ያገኜ "ከምትወሸም" እናት ይገኛልን? ከነተፈጥሯዋ ደምቃ ሰልታ የበቃች አገር ናት። ይህ ዬሚያስበረግጋቸው ሊበውዟት ይሞክራሉ። ሩቅ መሄድ አይቻላቸውም። መዳከር ካልሆነ።
ሰሞኑን በመንግሥት ሚዲያ ስማዳ ስይቴ ጠፌ ዬሚገኝበት የጋይንት አውራጃ አንድ ወረዳ ነው። ጋይንት ሦስት ወረዳወች አሉት። ታች ጋይንት፣ ላይ ጋይንት እና ስማዳ።
ከዛ ውስጥ አንድ የእስልምና ዕምነት ታሪክ ሳይ ነበር። ቤተ መቅደሱ ውስጥ የአድያም ሰገድ እና የበቁት ዬእስልምና አቨው ምስል አለ። በአንድ ላይ። ይህ ጥንታዊነት፣ መቅድምነት ረቂቅነት በወርቅ፣ በዕንቁ፣ በአልማዝ በምን መሸመት ይቻል ይሆን?
መዝነው አቶ ኤርምያስ ለገሰ ዋቅጅራ። ዬምትበሳጭበት ነገር ይኖራል። ፈልገህ ያላገኘኽው ነገር ይኖራል ለኢትዮጵያ ልጇ ነህና መከፋትህ አይደንቅም።
ግን እናትህን እንዲህ በመዳፈር አይሆንም። ተዳፈርካት። አቃለልካት። የአሮጌ ዬማበሻ ጨርቅ ያህል ክብር ነሳኃት። ክብሯን ትቢያ አልብሰህ፣ በጫጭቀህ መቃብር ላከው።
ተው እንጂ። ክብር፣ ኩራት፣ ማዕረግ ነሽ ማለት ይቅር። ግን እንዴት ለቀጣዩ ትውልድ እንዲህ ታስተምራለህ? በብዙ ነገር ብትገርመኝም ይህ ግን በፍፁም ሁኔታ የሰራ አከላቴን እንደ ዱባ ዬቀረደደው ጉዳይ ነው።

 
#ህይወት የጥያቄ እና #የመልስ ጭማቂ ናት።
ህይወት ማሳዋ ጥያቄ እና መልስ ነው። በዚህ ውስጥ ፅንሰት አለ። መወለድ አለ። ፈተናም በቡፌ ይኖራል። መወጣት መውረድ አለ። ፈተና ከታላቅ አገር ቀርቶ አንተ በህይወትህ ስንት አስተናገድክ አቶ ኤርምያስ?
ለእኔ ኢትዮጵያ 80 ዞግ አላት ብዬ አላምንም። 110 ሚሊዮን ዞግ ነው ያላት። ከዥንጉርጉር በላይ ነው የእኛ ነገር። ግን አንድ ዕውነት አለ። ዬደነገለ ተፈሪ መንፈስ ያላት እናት አገር አለችን። ኢትዮጵያ! የፀዳች። ያልተበከለች። ንጽህት። ያልባለቀችም።
#የሆኖ ሆኖ።
ከዚህ ቀን በኋላ ከህብራዊው ሰንደቋ፣ ባህሏ፣ ትውፊቷ፣ ታሪኳ ጋር እንዴት እና እንዴት ልትኳኋኑ ይሆን? አክብሮታዊ ጥያቄ ነው ለአቶ ኤርምያስ ለገሠ ዋቅጅራ።
"ዬጋለሞታ" "የተወሸመች" እናት ሥም አስቀድሞ ተቋማችሁን ማስቀጠል ይቻል ይሆን? እምታሳፍር እናት ታይልን ትሏት ይሆን አስቀድማችሁ? "#ኢትዮ" ' 360' " ያስኬዳል? ስፈረው።
ሰርክ እምትጎናፀፈው ሰንደቋስ "የጋለሞታ፣ ያገኜ የሚወሽማት" የባለቀ አይሆንብህምንም? ባህላዊ ልብሷ፣ የአኗኗር ዘይቤዋ፣ አክብረው የሚታደሙልህ አድማጮችህ ሁሉ "ዬጋለሞታ" ልጆች አይሆኑብህምን?
አንተ የውጩን ሚዲያ፣ የአማራን ፋኖ፣ የኢትዮጵያን እንብርት ነገረ አዲስ አበባን ፖለቲካ በአማካሪነት እንዳለህ ነግረኽናል። በተዘዋዋሪ መሪ ነህ። እነኝህን ሁሉ ወላጅ አልባ እራስህ አደረግካቸው። ይብላኝ ለገራገሩ ዬአማራ ፋኖ። ለነገሩ ከአንተ እጅ ወድቆ ምን ተራፊ ነገር አለና? ዕንቁ ይሁን ብራንድ????
ይሆነ ሆኖ እኔ እምጽፈው በ100 ሺህ የሚቆጠር ቤተኛ አለህ፣ እና እኔ ለእነሱ ሚዛን ጠብቀው እንዲራመዱ ለማድረግ ነው የፃፍኩት።
ሰማይ እና መሬት ቢገናኝ፣ ፀሐይ ብርኃኗን ብትነፍግ ኢትዮጵያ "ጋለሞታ" ሆና አታውቅም፣ አትሆንም።
ቅድስት አገር ኢትዮጵያ "ውሽማ" ዬማንም ሁና አታውቅም፣ አትሆንምም። ከዚህ ተከትሎ ዬሚመጣው መተዳደሪያዋ በፆታዋ ዬመሆን ጉዳይ ይሆናል። እንደ አገላለጽህ። አንተ ባትለውም ዬሂደቱ ዬአገላለፁ መድፊያ ግን "ሸርሙጣ።" ይሆናል። ገድፈኃል።
ያሳዝናል ዬሚለውን ቃል እማልጽፈው ሰብዕናህን ለረጅም ጊዜ ወስጄ ስላጠናሁት ነው። ከስምንት ዓመት ላላነሰ። በአቶ ጃውር መሐመድም ያለ ቢል አላዝንም። ይህ እንዲሆን ግድ ዬሚሉ አመክንዮች አሉና።
የውስጥነት ተባደግ ዬሌለባት እናት አገር ኢትዮጵያ ባንታደል እንጂ ከመሬት በላይ ብቻ ሳይሆን በከርሰ ምድርም ተዝቆ የማያልቅ ዓይነታ አንጡራ ሐብት አላት። ለሁላችን አንፈራሶ በፍቅር፣ በሐሴት የሚያኖር። ትምክህት አይደለም። ዕውነት ነው።
የሥርዓት መምጣት መሄድ፣ የትውልድ መምጣት መሄድ፣ የዘመን መምጣት መሄድ የራሱ ዬሆነ ዑደት አለው። ስበት እና ግጭቱ ይፈጥራሉ ቅይጥ // ውጥንቅጥ /// ዝልግልግ/// ክስተት።
ከፍም - ዝቅም - /// ሰፋ - ጠበብም፣ ለብ~~~ ሞቅ ~~~ ፍል ~~~ ዬመሆን ጉዳይ። ያ ዬእኛ ብቻ ችግር አይደለም። ይገጥማል።
እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት ከተለዬች በኋላ ስንት ጠቅላይ ሚር ሾመች? የአሁኗማ 60 ቀንም የደፈኑ አይመስለኝም። አውሮፓ ህብረት ዬራሽያን እና የዩክሬንን ጦርነት ማኔጅ ማድረግ ቻለን?
ራሺያ ስንት ማዕቀብ አስተናገደች? ስንት ውግዘት ደረሰባት? ስንት ገደብ ተጣለባት? እና ልጆቿ "ጋለሞታ ተወሻሚ" ይሏታል? አይሏትም። ፈጽሞ። ሞራላቸው ላንቁሶ አይደለምና።
ራሺያውያን በመከራዋ ጊዜ ከጎኗ ይቆማሉ። ጥቃት ማውጣት ባይችሉ በፀሎት ይረዷታል። ዓለም ፊቱን ስለዞረባት ፈጣሪም አይዞርም። ማዕከሉ ዕውነት እና መርህ አለና።
ያን ታግሦ፣ አመጣጥኖ ትውልድን ከምቀኝነት፣ ከቅናት፣ ከቂም፣ ከገለማ በቀል፣ ከጥላቻ በወጣ አስተምኽሮ በማይደፈር የጽናት መንፈስ መገንባት እንመራለን ባሉ ትናንት፣ እንመራለን በምትሉት ዛሬ ባሉት የፖለቲካ ሊቃናት፣ የፖለቲካ ሊሂቃን ዬክህሎት እና ፃዕዳ ዬሞራል አቅም ይወሰናል።
የሚታዬው የውድቀት ይሁን የመነሳት ሁኔታ "የተዘራው ነው የታጨደው።" ያልተዘራ አይበቅልም።
እንዲያውም እኮ ጦርነቱን "ህግ ማስከበር፣" ሂደቱን "ኢትዮጵያዊ አብርኃም ሊንከንን እንጠብቅ' እያልክ ስትሰብክ ነበር። ለዛውም ዬኔታ አቻምያለህ ታምሩን ጠይቀኽዋል እኮ።
መዋለል በግል ይሁን ትውልዱ ቋሚ ባልሆነ ፍላጎት ማባከን ዕዳ ከሜዳ ነው። ጠቃሚው ነገር አመጣጥኖ መጓዝ ይመስለኛል። ይህም ይሁን ማህፀን አይረገምም።
ሁሉን - ሁና፣ ሁሉን - ሰጥታ ሳይደላት አስተምራ፣ አሹማ፣ አስከብራ፣ ሺህ ደጋፊ አስችራ፣ ፈጥኖ ደራሽ ወገን ደጋፊ ሰጥታ አቆላምጣ፣ ሴት ልጇን ሰጥታ ዓይንን ለዓይን አብቅታ፣ መንበር ላይ ላወጣች አገር ውለታው፣ ወረታው ቢቀር አትዘለፍ! አትቃላል! መስቃ አትስማ!
የአቅመ ቢስ ስብስብ ቀድምቷ ሉዓላዊት አገር ተጎታች አድርጓታል። ተፅዕኖ ፈጣሪነቷ ግን ዓለም በሙሉ በአንድ ቃል ዬሚመሰክረው የወርቅ እንክብል ዕውነት ነው። ዛሬም።
ኢትዮጵያን አትዳፈሯት፣ ቅጣቷን አትችሉትም እና። ሰወች ነው የሚመሯት ከእነሱ ጋር እስጣ ገባው መቀጠል ነው። ዋስ ጠበቃ ከሌላት እናት አገር ኢትዮጵያ ቅባዓ ግን መንፈስም፣ አካልም፣ ሁለመና ሊገራ፣ ሊቀጣ ይገባል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም ሁሉም ዓይነት ችግር አለ። ሁሉም አይነት ድሎት አለ። አቅላችን ውጥን፣ ህሊናችን ጥብቆ ካላደረግነው።
ዬትውልድ አደራ ተረክቦ በማስረከብ ደግሞ መሪ ነን ዬሚሉት፣ #ዬምትሉት አንተን ጨምሮ ድርሻ እንጂ የኢትዮጵያ ባዕት፣ ብትን አፈር፣ መልካዕምድራዊ አቀማመጥ ጉዳይ አይደለም።
ዛሬም ስለ ኢትዮጵያ ይመሠከራል፣ ብትደክምም፣ ብትዝልም፣ በፈተና ብትዋጥም ልዑቅ #ላቂያ ናት። ዘለግ ያለች፣ እሸት ሁልጊዜ እንዳሸተች የምትኖር። ሁለመናዋ ሳቢ፣ ጠረኗ ጣፋጭ ማንጠግቦሽ።
ሰጪዋ አንድዬ መዳህኒት ዓለም ነው። አብዝቶ ሰጥቷታል። ከብረት ቁርጥራጭ የተፈጠረች ናት። ኢትዮጵያ ትናንትም አሸናፊ ናት። ዛሬም አሸናፊ ናት። ነገም አሸናፊነቷ ይዘልቃል። ከነገ በስትያም ታሸንፋለች።
ለምን? መሠረቷ የፈጠራት አምላክ፣ አላህ አለላት እና። የታምር፣ የገድል፣ የትንግርት አገር ናት። ተስፋችን በአምላካችን።
አንቺ ስስቴ ነይልኝ በሞቴ
ዳብሽኝ ልዕልቴ
የዘላላም ንግሥቴ
የምስባዕክ ዕውነቴ
ኢትዮጵያ እመቤቴ።

 
ዬማከብራችሁ ቅኖች ዬምለጥፋቸውን ጠረኖች ጠጡልኝ፣ ብልሉኝ።
ኢትዮጵያዊነት የደሜ ዕምነት ሥነ ሕይወት!
Feb 12, 2021
ኢትዮጵያዊነት የመንፈስ ንባብ ነው … ለእኔ!
Jan 29, 2021
ኢትዮጵያዊነት የደሜ ዕምነት ሥነ ሕይወት!
Jan 29, 2021
የአፍሪካ አንድነት ምስረታ እስከ አፍሪካ ህብረት ድረስ ያለው ታሪካዊ ክስተትና የኢትዮጵያ ድርሻ ዕድምታ።
May 28, 2019
"ለአንደበቴ ጠባቂ አኑርልኝ!" (ንጉስ ዳዊት በመዝሙሩ:)
ትውልድ ሆይ ኢትዮጵያ አገራችን ብፅዕት የሰናይ አልፋ ኦሜጋ ናት!
እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
፣20/10/2022
ልዕልት ኢትዮጵያ በደማቅ ክብሯ ትለመልማለች።
እቴጌ ኢትዮጵያ ሳይንስ ናት።
እመቤት ኢትዮጵያ ፍልስፍና ናት።

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።