ዬሰባዕዊ መብት ተሧጋቹ አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ይናገራሉ። እማከብራቸው ሰው ናቸው። በጠሚር አብይ አህመድ አሊ ብርቱ ተስፋ ነበራቸው። ዛሬስ??
ከሊቀ ትጉኃን አቶ ኪሩቤል ዘለዓለም ዬተገኜ ነው።
//////…………///
"ጠቅላይ ሚንስቴሩ በአንድ እጃቸው ላይ እንደ በረዶ እየቀለጠች የምትመስል አገር ይዘው በሌላ እጃቸው በእንዲህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ባለች አገር ስለሚኖር ተደማሪ ትውልድ መጻፋቸው ግራ ቢገባኝ ነው ብእሬን ያነሳሁት። እኚህ ሰው ሌላ እኛ የማናውቃት፣ መሬት ላይ የሌለች፣ እሳቸው በምናብ ፍንትው ብላ የምትታያቸውና የሚያስተዳድሯት ኢትዮጵያ የምትባል አገር አለቻቸው ይሆን አስብሎኛል።
ካልሆነ ግን አንድ ያልተገለጠልኝ ነገር አለ ማለት ነው። እንዴት እንደበረዶ እየቀለጠች ያለች በምትመስል አገር ውስጥ አንድ አገርን አስማምቶና አረጋግቶ፣ የሕግ የበላይነትን አረጋግጦ፣ ሰላም አስፍኖ፣ ሙስናን አመንምኖ፣ ኢኮኖሚውን አረጋግቶ፣ ግጭትና ጦርነትን አስወግዶ፣ ሰብአዊ መብቶችን አክብሮና አስከብሮ አገር መምራት ያቃተው ሰው እንዴት ሊበለጽግ የሚችልና ራዕይ ያለው 'ተደማሪ' ትውልድ መፍጠር ይችላል? የሚለው ጥያቄ እንዲሁ በአእምሮዬ ሲመላለስ ከረመ።
ለእኔ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ እና ግብራበሮቻቸው፤ ህውሃቶችን ጨምሮ እራሳቸውን ችለው አገር የመምራት ብቃት እንደሌላቸው የተረዳሁት ገና በጊዜ የነገሮችን አያያዛቸው አላምር ሲለኝና አንዳን የሚፈጽሟቸውን ፖለቲካው ፋውሎች ደጋግሜ ማጤን ስጀምር ነበር። ደጋግሜ ስወተውት የቆየሁትም ሁለት መሠረታዊ የሆኑ እና ኢትዮጵያን ወደተሻለ አቅጣጫ ሊያመሯት የሚችሉ የለውጥ ጊዜ እርምጃዎችን አከናውና ማለፍ አለባት ከሚል እሳቤ ነበር።
1ኛ/ አገሪቱ በብዙ ግፍና ጭካኔ የሞላቸው የመብት ጥሰቶች ውስጥ አልፋ ስለመጣች ገና ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የሽግግር ወቅት ፍትህ ሂደት የግድ ያስፈልጋታል የሚል ውትወታ ነበር። ይሄን ሃሳብ ባነሳን ቁጥር ጠቅላዩና አጃቢ ካድሬዎቻቸው አንድም ሆን ብለው፤ አለያም ገሚሱ ከግንዛቤ ማጣት የሽግግር መንግስት ይቋቋም ያልን በማስመሰል ሃሳቡን ሲያምታቱትና ሲያጣጥሉት ቆዩ።
2ኛ/ ሁለተኛው ደጋግሜ አነሳ የነበረው ነገር ይችን አገር ጠቅላዩ ብቻቸውን "መደመር" በሚል ተግባር የራቀውና መረት ላይ ያለውን ተጨባጭ እውነታ ያላገናዘበ የቅዠት ፍልስፍና ሊመሯት አይችሉም። ስለዚህ የግድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ባለድርሻ አካላት የመከሩበት የጋራ አገራዊ ራዕይና ፍኖተ ካርታ መቅረጽ፣ አገራዊ መግባባት መፍጠር፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ነጻነት መስጠትና በሕገ-አራዊት ስትመራ የቆየችውን አገር ሁሉም ኢትዮጵያዊ የመከረበትና የተሳተፈበት ሕገ መንግስታዊ ሥርዓት መፍጠር ያስፈልጋል የሚል ነበር።
እንደውም የዛሬ ሦስት አመት 'አሻጋሪውንም የሚያሻግር ብሔራዊ መድረክ ያስፈልጋል' የሚል ሀሳብ የያዘ ዘለግ ያለ ጽሑፍና ምክረ ሀሳቦችም አቅርቤ ነበር።
የሆነው ሆኖ ጠቅላዩም ሆኑ አገሪቱ እጃቸው ላይ የወደቀችባቸው ብልጽግናዎች ከላይ የተነሱትን ሁለቱንም ሃሳቦች ሥልጣናችንን ያሳጡናል ወይም የፈላጭ ቆራጭነት አቅም ይነፍጉናል በሚል ስጋት ሊሆን ይችላል ወደ ጎን በመተው አገሪቱን በደመ ነፍስ በሚመስል ሁኔታ ይዘው ለመጓዝ ወደሚያስችላቸው የሥልጣን መደላድል ላይ ብቻ አተኮሩ።
የ2010ሩ ምርጫ ለአገሪቱ ሰላም እና መረጋጋትን ከማምጣት ይልቅ ትልቁ እንዲያሳካ የተፈለገው ነገር ለገዢው ፖርቲ የሥልጣን መደላድል ሕጋዊ ገጽታ ማላበስን ሆነ። የኢትዮጵያን ጊዜ ጠገብ ችግሮች እና እራሱም የአብይ አስተዳደር የፈለፈላቸውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች 'መደመደረ' በሚል ግራ የገባው የግል ፍልስፍና ለመፍታት መጽሐፍ ማሳተምና እሱን አገሪቱ የምትመራበት ሰነድ በማድረግ የአገሪቱ ችግሮች ሁሉ የመፍቻ ቁልፍ እንደሆነ አድርጎ የማሰብ ቅዥት ውስጥ ሲገባም ነገሩ ስላላማረኝ ጠቅላዩ ወደ 'ብልጽግና ተኮር አንባገነናዊነት ወይም Benevolent dictatorship' እያቀኑ ይመስላል የሚል ስጋት አዘል ምልከታዬን የዛሬ ሦስት አመት ግድም በሌላ ዘለግ ያለ ጽሑፍ አቅርቤ ነበር።
እንደኔ ግምገማ ጠቅላይ ሚንስትሩ እንደ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰብ እና ፖርቲያቸው እንደ አገዛዝ ሥርዓት ከላይ ያነሳኋቸውን ሁለት መሠረታዊ የሆኑ የሽግግር ጊዜ ውሳኔዎችን ወደ ጎን በመግፋታቸው የተነሳ ኢትዮጵያን ወርቃማ እድሎችን አስመልጠዋታል። በዚያም የተነሳ ይመስለኛል አገሪቱ ባለፉት አራት አመታት ታይተውና ተሰምተው የማይታወቁ የመከራና የስቃይ ናዳዎችን ስታስተናግድ ቆይታለች።
በጠቅላይ ሚንስትሩ የአስተዳደር ድክመት፣ አቅም ማነስ እና አንዳንዴም ከልክ ባለፈ ዳተኝነታቸው የተነሳ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን የከፈሉትን እና ዛሬም እየከፈሉ ያሉትን መስዋዕትነት ዘርዝሮ መጨረስ ባይቻልም ዋና ዋናዎቹን ግን መጥቀስ ይቻላል።
+ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል ግጭቶች እንዲበራከቱ እና ለመቶ ሺዎች ሕይወት መጥፋትና ሚሊዬኖች ከቀያቸው ተፈናቅለው በየመጠለያ ስፍራው ለርሀብ፣ እንግልትና ስቃይ እንዲዳረጉ ምክንያት ሆነዋል፣
+ በማንነት ላይ ያተኮሩ ጥቃቶች፣ ጭፍጨፋዎች፣ ማፈናቀሎችና ግጭቶች እንዲበራከቱ እና የሕግ የበላይነትን ማስከበር ያቃተው አመራራቸው ሕገ ወጥ ቡድኖች እንዲበራከቱም ምክንያት ከመሆንም አልፎ ባሳየው ለዘብተኝነት ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
+ የአገሪቱ ሉዓላዊነት ታይቶም፣ ተሰምቶም በማይታወቅ ሁኔታ አደጋ ላይ እንዲወድቅ አድርገዋል። ዛሬ ብርጭቆ መልሰው ከሚያጋጩዋቸው የሰሜን ጓደኞቻቸው ጋር የጀመሩት የሥልጣን ፍትጊያ ከቁጥጥራቸው በመውጣቱም አገሪቱን ለሁለት አመት ለቆየ የለየለት ደም አፋሳሽ ጦርነት ከተዋታል።
+ ጦርነቱን ባልንጀሮቻቸው የህውሃት ጓዶች ቢጀምሩትም በሕግ ማስከበር ስም ጠቅላዩ ጦርነቱን የመሩበት መንገድ የኢትዮጵያን ሕዝብ ያሳሳተ፣ በሕዝቦች መካከል ዘላቂ ቅራኔን ያተረፈ፣ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች እልፈት ምክንያት የሆነ፣ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሴቶች መደፈር፣ ለበርካታ ከተሞች መውደም፣ ለሕዝብ ተቋማቶች መፍረስ እና አገሪቱም ለከፍተኛ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ዳርገዋታል። ጁንታና ሽብርተኛ የሚለውን ነጠላ ዜማ ሁሉም ካላዜመ አገር እንደከዳ የሚቆጠርበትን የወከባ ዘመንም አሳልፈናል። (የጦርነቱ ነገር ሲነሳ ትላንት ፖርላማ ላይ ቀርበው ስለ ሕውሃት ወደ ቅዱስነት የተጠጋ ሰላም ፈላጊነት ሊያስረዱን የዳዳቸው የጠቅላዩ አማካሪ አቶ ሬድዋን የዛሬ ሁለት አመት፤ ጦርነቱ በተጀመረ አንድ ወር ግድም በኢሊሌ ሆቴል የሲቪክ ማህበራትን ሰብስበው ስለ 'ሽብርተኛው' ህውሃት የሰጡንን ትንታኔ ሳስታውስ ፕሮፌሰር መስፍን 'ማፈር ድሮ ቀረ' ብለው የቀድሞዎቹን ኢህአዴጎች የገለጹበት መኔገድ ትዝ አለኝና ይች አገር በምን አይነት ሰዎች እጅ ነው የወደቀችው አልኩ)
+ በዚህ የሽግግር ወቅት በተፈጠሩ የእርስ በርስ ግጭቶች፣ የሰሜኑ ጦርነት፣ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል በተፈጠሩ ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ዘግናኝ ጥቃቶች እና በብዙ አካባቢዎች በተነሱ የውስጥ ድንበር አከላለልና የአወቃቀር ጥያቄዎች የተነሳ ወያኔ አሳስታው የነበረው የአብሮነት፣ የመተሳሰብ እና አገራዊ ስሜት ተበጣጥሶ ዜጎች በብሔርና በሃይማኖት ጎራ ተቧድነው እርስ በርስ እንዲገፋፉ፣ አንዱ ሌላውን እንደጠላት እንዲያይ፣ እንዲፈራረጅ፣ በማንነት ላይ ላነጣጠሩ እልቂቶች እንዲዘጋጅ የጠቅላዩ ደካማና መድሎ የተሞላው አስተዳደር ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
+ ግማሽ ሊባል የሚችለው የአገሪቱ ክፍል በተለያዬ ታጣቂ ሃይሎች በየቀኑ የሚታመስበት፣ አጣዬን እንደ ምሳሌ ብንወስድ ቢያንስ ለዘጠነኛ ጊዜ በታጣቂዎች ጥቃት ሰለባ የሆነችበትና ከተማዋ ለተደጋጋሚ ውድመትና ዝርፊያ እንድታስተናግድ የተገደደችበት፣ በርካታ የመንግስት መዋቅሮች የተፋለሱበት እና በአንዳንድ አካባቢዎችም ስርዓት አልበኝነት የነገሰበትን ሁኔታ ለመፈጠሩ የጠቅላዩ አስተዳደር የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል።
+ የአገሪቱ አውራ መንገዶች በመንደር ጉልበተኞች ለቀናት እየተዘጉ ዜጎች በገዛ አገራቸው ውስጥ ከቦታ ቦታ በነጻነት እንዳይንቀሳቀሱ የተደረገው በዚህ የአስተዳደር ዘመን ነው።
+ እጅግ የተዳከመ ማዕከላዊ መንግስት፣ እርስ በርስ የሚፎካከሩ፣ የሚፈራሩ እና አልፎ አልፎም የሚጋጩ፣ አንዳንዴም ሕገ መንግስቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ ተግባራትን የሚፈጽሙ፣ የራሳቸውን ጡንቻ ያፈረጠሙ የክልል ጉልበተኞች የተፈጠሩት በብልጽግና የአገዛዝ ዘመን ነው።
+ የጅምላ ጭፍጨፋዎች፣ አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ወንጀሎች የበየቀኑ የሚፈጸምበት፣ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በጠራራ ጸሀይ ዜጎችን በእሳት ሲያቃጥሉና በድንጋይ ወግረው ሲገድሉ፣ በግፍ የገደሏቸውን በዶዘር በጅምላ ሲቀብሩ የታየበት የሰቆቃ ዘመን ቢኖር ያለፉት አራት አመታት ናቸው።
ዛሬ ኢትዮጵያ የቶን እሳት ላይ ተጥዳ በብዙ መከራዎችና ሰቆቃዎች እየተለበለበች ያለች አገር ናት። ርሀብ፣ የኑሮ ውድነት፣ ጦርነቱ ያስከተለው ምስቅልቅል ሁኔታ፣ በብዙ ክልሎች የሚታየው የሰላም እጦትና አለመረጋጋት፣ የከፋ የአስተዳደር በደል ያስከተለው የዜጎች የኑሮ ዋስትና ማጣት ጠራራ ጸሀይ እንዳረፈበት በረዶ በመቅለጥ ላይ ያለች አገር አስመስሏታል።
ወደ አምስት ሚሊዬን የሚጠጋ የአገር ውስጥ ተፈናቃይ ባለበት፣ ቦረናን ጨምሮ በርካታ አካባቢዎች ዜጎች ለርሃብ ቀተጋለጡበት፣ በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች እጅግ በርካታ ትምህርት ቤቶች በመውደማቸው ምክንያት በሚሊዬን የሚቆጠሩ ሕጻናት ትምህርት ቤት መሄድ ባለመቻላቸው የትምህርት ኢደት መስተጓጎሉን በራሱ በመንግስት ሚድያ በሚነገርበት አገር ጊዜ አግኝተው መጽሐፍ የከተቡት ጠቅላዩ የመጽሐፍ ሽያጩ ገቢ ሶፉመር ዋሻን ለማደሻ፣ አዲስ አበባ ስታዲየም መገንቢያና ወዘተ... እንዲውል መናዘዛቸው ይበልጥ አስደምሞኛል። ለጠቅላዩም ሆነ ለመሰሎቻቸው የሰው ዋጋ ስንት ይሆን? የአገሪቱን ችግሮች በምን ደረጃ እንደሚመዝኑም ያሳዩበት አጋጣሚ ይመስለኛል።
ለማንኛውም በሚሊዬን የሚቆጠሩ ህጻናት በሜዳ ላይ በወደቁበት፣ በየመጠለያው በታጎሩበት፣ ከትምህርት ገበታቸው እንዲርቁ በተደረገበት፣ ትምህርት ቤታቸው በጦርነት በጋየበት፣ በአናታቸው ላይ ታንክ በሚያጓራበት፣ በድሮን ጥቃት አይምሯቸው ውስጥ ሰቆቃ በሞላበት፣ ርሃብ አለንጋ እየተገረፉ ባሉበት በዚህ አስጨናቂ ወቅት 'የተደመረ ትውልድ' የሚል መጽሐፍ መጻፋቸውስ ምን ይባላል። የእርሳቸው የመጽሐፍ ድምር ውስጥ እነዚህ ሚሊዮኖች ተካተው ይሆን?
ለማንኛውም ቢዘገየም አሁንም ቅዠት ከሞላው የመደመር ፍልስፍና ተሻግረን ኢትዮጵያን ከገባችበት አደገኛ እና አስፈሪ ቅርቃር ለመታደግ፣ ሕዝቧንም ከገባበት ስቃይና መከራ ለመገላገል እውነተኛ የሆነ ብሔራዊ ምክክር፣ ተጠያቂነትን፣ ፍትትን እና እውነትን ያማከለ የሽግግር ፍትህ ያስፈልጋታል። የሽግግር መንግስት አላልኩም፤ እውነተኛ የሆነ እና ከፖለቲካ ፍጆታ ያለፈ የሽግግር ፍትህ ትፈልጋለች።
እሳት ላይ ተጥዳ እንደ በረዶ እየቀለጠች በምትመስል አገር ብልጽግናም ሆነ ተደማሪ ትውልድ መፍጠር አይቻልም።"
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ