ጭምቱ ለሁሉም አልጋው አማራ። "ኢትዮጵያዊነት ሱሴ" ምን ያህል አቅም እንደፈሰሰለት፤

 

ማዕዶተ ሰባዕዊነት ለዛውም በሰንበት።
ዕለተ ሰንበት ማዕዶተ ርትህ ሰባዕዊነት።
በከበቡሽ የቁራሽ እንጀራ ብራና
በቢሆነኝ የተብራራ ብራ
በሰብለ ህይወት አዝመራ
ለራህብ የሚራራ።
„የሰው ልብ መንገድን ያዘጋጃል
እግዚአብሔር ግን አካሄዱን ያቃናለታል።"
(ምሳሌ 16 ቁጥር 9)
• ጭምቱ ለሁሉም አልጋው አማራ።
 

 
ዘመን - ተዘመን፤ ወቅት - ተወቅት፤ ሂደት - ከሂደት፤ ታሪክ - ከታሪክ፤ ትውፊት - ተትውፊት፤ ዓመት - ከዓመት፤ ወራት - ተወራት፤ ሳምንት - ተሰማንት፤ ቀን - ተቀን አንድም ዕለት ወቀሳ አብርቶለት የማያውቀው የአማራ ህዝብ መከራውን ተሸክሞ ኢትዮጵያንም ከእነመከራዋ ተሸከሞ አለ እንዳለ። ትናንትም ዛሬም። በአማራ ሥም የተደራጁት ሁሉ የሚታገሉት ለኢትዮጵያኒዝም ነው።
በኦሮሞ፤ በአፋር፤ በትግሬ ወዘተ … ሥም የተደራጁት ደግሞ ለራሳቸው ማህበረሰብ ነው። ጠቀመም ጎዳም። አማራ ሲደራጅ ኡኡ! ተባለ። የተደራጀበትን ዓላም ግብ አይደለም መከራውን ማስታገስ ሳይችል የኢትዮጵያን መከራ ለመሸከመ ቆረጥ ቆረበበትም። ጎዳናውን በዛ ጠረገ።
 
የኦሮሙማ አስተዳደር ተቀምጦ „ኢትዮጵያን አትንኳት?“ ከአማራ ድርጅት የሚወጣ የወል ድምጽ ነው። ይህን ሚስጢር የሚያነብ፤ የሚተረጉም፤ የሚያመሳጥር አቅም ያለው ሙሴ እስኪመጣ ድረስ ድሉን አማራ አይገኝም። አማራን በልኩ የተረዳ ተቋም የለም።
አማራ አማራ ሆኖ መታገሉን እራሱ ፈጽሞ አላወቀበትም። አልገባውም የተደራጀበት ዓላማ እና ግብ አያውቀውም። ያለበትን ወቅትም ማንበብ አልቻለም። አናባቢ ዲክሽነሪ ያስፈልገዋል። ለዚህ ነው እኔ የአማራ ቀን አልተጸነሰም እምለው።
 
አማራ ለደቂቃ ኢትዮጵያዊነትን አኩርፎ፤ በትውፊቱ ጀርባውን ሰጥቶ፤ ከእናቱ ጸጋ አፍንግጦ ታይቶ አይታወቅም። አልጋው አማራ የኢትዮጵያን ሰንደቁን ሲያ ወከክ ይላል። ሰንደቁ ኦክስጅኑ ነው። ኢትዮጵያ የደም ሴሉ። „ኢትዮጵያዊነት ሱሴ“ ሲመጣ ወከክ ሆነ ሁላችንም። ከረባቱ፤ ጃኬቱ ትንሽ የሰንደቁ ቀለም ካለም በቃ አማራ ያ የጽድቅ ጉዞዬ ነው ይላል። ፈጣሪ የቅንነቱን አይቶ ሰው ይስጠው። አሜን።
 
ፊት ለፊት ወጥቶ አማራው የረሳውን አማራ ቅብ ያልሆነ ድንግል ኢትዮጵያዊ ወገን የሚታገልለት ነፍስ ይፍጠርለት ፈጣሪ። አሜን። የእኔ የዘወትር ጸሎት ይህ ነው። የአማራ ማንኛውም ድርጅት የተደራጀበትን ዓላማ ስቶ ሌላ አጀንዳ ከፈቀደ በተናጠል የሚያደርገው ትግል ከምንም አይደርስም።
 
አማራ አሰባሳቢው ሞቶ ሊሆን ይገባ የነበረው የአማራ ተጋድሎ መርኽ ነበር። ሌላ ማንፌስቶም አያስፈልገውም ነበር የሐምሌ 5/22/ የመስከረም የባህርዳር ተጋድሎ ነበር ልኩ መከራውን ተቋቁሙ የመከራውን ድምዳሜ የሚያስገኝለት። ግን አልሆነም።
ጭምቱ አማራ እዬሞተም ሞቱን ደግፎ ሰልፍ ይወጣል ውጭ አገርም አገር ውስጥም። የሚገርመው በዚህ ዘመን ገዳዩን፤ ጨፍጫፊውን ኦሮሙማን ደግፎ ግድያው ጣፍጦኛል እና ቀትልበት ብሎ በአደባባይ ይወጣል። ሰልፍ ሲወጣ ኦሮሙማ ሊያው፤ ሊያቀርበው የማይፈልገውን፤ አብዝቶም የጠዬፈውን የኢትዮጵያን ሰንደቁን ለብሶ ነው። 
 
የኢትዮጵያን መለያ፤ ክብር፤ ማዕረግ ሰንደቁን እያነደደ፤ ሰንደቁን እዬደረመሰ፤ ሰንደቁን ለተጠዬፈ ድውይ የአብይዝምን መንፈስ ጨርሰኝ ብሎ፤ ክብሬን አዋርደህ ቅበረው ብሎ፤ ሰልፍ መውጣት ዕብደት ነው። ለእብደቱ ጎንድ ተ/ኃይማኖት ያስፈልጋል። ለኃጢአቱ ደግሞ ንስኃ።
በዬሰከንዱ የሚከዳው አማራ አሁንም የጭቃ እሾሁን ኦሮሙማን ደግፎ ይወድቃል ይነሳል። ግርባው ብአዴን ጨምሮ። ኦሮሞሙ ጨርሶ ውጦ ሲያጠናቅቀው ያን ጊዜ ያውቀዋል። 500ሺህ ዲሞግራፊ አዲስ አበባ ላይ ሲከውን ለእሱ መሆኑ አልገባውም። ነግረንም። አስረድተንም አድማጭ የለም። አጀንዳም አይደለም።
 
ወደ አዲሱ መንደር የተዛወረው ኦሮሞም ቢሆን ከቀዬው ሲነቀል ሰባዕዊነቱ ተጠብቆ አይደለም። በግፍ ነው። ፈቅዶ አይደለም በጭቆና ነው። ለዚህ ለምታዩት የኮረጆ ዳንኪራ።
 
የሆነ ሆኖ ማናቸውም ዓይነት በአማራ ህዝብ ላይ የሚደርስ ጥፋት፤ ውድቀት፤ መደርመስ፤ መጨፍጨፍ ዕውቅና ቀርቶ መስማት የሚይፈልገውው የዶር አብይ ሌጋሲን ለማስቀጠል የሚተጋው አማራ ሆኖ ስታዩት መቼ ልብ ሊያገኝ እንደሚችል የአማራ መከራ መጨረሻው አይታወቅም። 
 
ከግፉ በጥቂቱ።
 
"ኢትዮጵያዊነት ሱሴ" ምን ያህል አቅም እንደፈሰሰለት፤
ኢህዴግ ስብሰባ ላይ ሙሉ የብአዴን የምክር ቤት አባላት ሙሉ ድምጻቸውን ለኦህዴድ እንደምን አንዳበረከቱ፤
የፌድራሉን ሸክም አማራ መሬት ላይ እንደምን እንደተስተናገደ፤
ኦህዴድ ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ መንግሥታዊ ቁልፍ ቦታውን ሁሉ ሲያገፍፍ አንድም ጠያቂ ማጣት።
"የሰበሩንን ሰብረን በሰበሩን ቦታ የአገሪቱን ዋና ከተማ ተቆጣጠርነ" ሲባል ልብ አለመግዛት?
በህወሃት እና በኦህዴድ ጦርነት የተከፈለው መስዋዕትንት ህወሃትን አማራ ባይመክተው ምን ሊሆን እንደሚችል የነበረውን ዕውነት መካድ፤ መታስም፤
በዬሰልፉ የአማራ ልጆች ለሞታቸው "አብይ መሪያችን" እያሉ ሲያደነቁሩን አልቦሽነቱ ሲታሰብ?
ከቀን አንድ ጀምሮ የአማራ ልጅ በሁሉም መስክ መንጠራውን ስታዳምጡ፤
አሁንም ምንጠራውን ደግፊ ወክዬ እወዳዳራለሁ ሲባል ስትሰሙ፤
በፓርላማ አማራ በጦር ወንጀለኝነት ሲከሰስ፤
አማራ አይሞቀው አይቀዘቅዘው። ለ እሱም አልመሰለው። ለእሱ ኢትዮጵያ እሱ እሱ አልቆ ሞቶ ከተረፈች ሠርጉ ነው። ሙሉ አማራ ምጥጥ ብሎ ሌላ አዲስ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ላይ ቢፈጠር አጀንዳው አይደለም።
አማራ ከሞተ በኋላ፤ ከተነቀለ በኋላ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ወይንስ (ሱማሱ) ሱማሌ - ወ -ሱዳን (ኤሱ) ኤርትራ - ወ - ሱማሌ (ኤሱ) ኤርትራ - ወ - ሱዳን ወይንም(ሱኤሱ) ሱማሌ ወ - ኤርትራ- ወ ሱዳን እንደምን ቅይጥ፤ እንደምን ቅጥ አንባር የጠፋባት አገር ኢትዮጵያ ልትሆን እንደምትችል አላሰበውም አማራ። ሱማሌ ስል መቋዱሾን ሱማሌ ማለቴ ነው።
አማራ እራሱን ለማዳን የሚያደርገው ቁርጠኛ ተጋድሎ ነበር ኢትዮጵያን ሊታደግ፤ ሊያተርፍ በተፈጠርበት ልክ ሊያስቀጥል የሚችለው። አይደለም ኢትዮጵያ የመካከለኛው ምስራቅ አፍሪካ፤ አፍሪካ ቀንድ ሆነ አፍሪካ ሊንድኑ የሚችሉት።
ምክንያቱም በሁሉም አማራ የእንኳን ደህና መጣችሁ ይትብኃል ስላለው ጋብቻው፤ ጉርብትናው፤ ጽጌው፤ ሰንበቴው፤ ማህበሩ፤ እድሩ ሁሉም ቦታ ቅመም ነው። ይህን መረብ በጸና መሰረት አስይዞ መታገል ይገባ ነበር። ግን የተጋድሎ ሚስጢሩም፤ መክሊቱም ፈሰሰ።
• የኢትዮጵያ ገጠሮች በአማራ ሞት በግሎባል ታወቁ።
በዬትኛውም ቦታ የሚሳደደው አማራ ወይንም የአማራ ውስጥ የሆኑ ማህበረሰቦች ናቸው። ሰብዕዊነት ተጠቀጠቀ። ሰባዕዊነት ተጨፈለቀ፤ ሰባዕዊነት ታረደ፤ ሰባዕዊነት በግፍ ተከተከተ፤ ሰብዕዊነት ተፈጸመ ማለት ይቻላል።
አማራ በኢትዮጵያ በስልት፤ በግልጥ፤ በዓዋጅ፤ በተደራጀ ሁኔታ እያበቃ ይገኛል። ይህም ሆኖ ለገዳዩ ሞዝበልድ አልጋ ሆኖ ተሸክሞ፤ ድልዳል ሆኖ አቅሙን ያለ ገደብ ሹሞ ሸልሞ እያለቀ ይገኛል አልጋው አማራ።
የትኛውም ተቋም ይደራጅ፤ ይወጥን የፈለገው ዓይነት ነገር በኢትዮጵያዊነት ሥም፤ በብሔራዊ ሰንደቁ ሥም ከሆነ አማራ ግንባሩን አያጥፈም። ሄዶ ይማገዳል። ሄዶ ይቆሰቆሳል። ለእሱ ግን የምናዬው ነው።
በጣት የሚቆጠሩ በድንግልና ሲቆረቆሩ፤ ሲተጉ፤ ሲወድቁ ሲነሱ አሁን ከሆነ እኔ አያለሁኝ። እሸት የሆኑ ነፍሶች። ይህም ተመስገን ነው። ከቀስት እንድን ዘንድ የተሰጡን ስለሆኑ አክብረን ልንይዛቸው ይገባል። ቢያንስ በጸሎት ልንደግፋቸው።
እንኝህ ነፍሶች ለእኔ ብፁዕ ናቸው። ብፅዕና ሰባዕዊነት ነው። ሰው መሆን መቻል ነው ብጽዕና። በአማራ ህዝብ ላይ የተደቀነው ግዙፍ አደጋ ብሄራዊ ብቻ ሳይሆን ሉላዊም ነው። ይህን አውቆ ቀደም ብሎ ተግባር ይጀመር ዘንድ እኔ ብዙ አሳስቤያለሁኝ። እስራኤሎች የተጓዙበትን መንገድ እንከተል ዘንድ በትህትና አሳስቤያለሁኝ። ዓለም ፊቱን ካዞረብን ስደቱም መኖርን አያጸድቀውም ብዬ ብዙ በጣም ብዙ ጥሬያለሁኝ። ለመስማት ፈቃዱ እንኳን የለም።
አሁን አሁን ጠንከር ብለው የወጡ ነፍሶችን አያለሁኝ። ያው አንድ ቀን ደግሞ አጤ ዝናቡ ዶር አብይ አህመድ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ጃኬት ለብሰው „እኔም አማራ ነኝ“ ብለው ወጥተው ማዘናገቱን ካልዳሩት ካልኳሉት በስተቀር። ወይ ሉዕካቸውን ልከው ካላደነዘዙት በስተቀር። ዘመኑ አልገባንም። አሳቻውን አጤ ዝናቡን ዶር አብይንም አላወቅናቸውም። ፈጽሞ።
መሬት ላይ ያለ መታረድን፤ መገፋትን፤ መሳደደን እያዬህ እንደምን ማይክ ታምኖ አማራ ትጥቁን ይፈታል? አሁን እኮ ያ ጠንካራ የአማራ ተጋድሎ ጽናት፤ ብርታት የለም። ለብ ያለ ጠይም መንፈስ አደንዝዞታል። አፍዞታል። ለዛውም በጋመ ፈተና ላይ አማራ ተቀምጦ። ያሳዝነኛል ነገረ አማራ።
ዘመኑ ባልሆነው የሚኖረው አማራ መሪ ሃሳቡን ከግብ የሚያደርስለት አቅም ገና አላገኜም። በያዝ ለቀቅ የህልውና ተጋድሎ ለግብ አይበቃም። ከጽናትም በላይ ከብረት ቁርጥራጭ የተሰራ ሰብዕናን ይጠይቃል። አዲስ አበቤ አግኝቶ ነበር አቶ እስክንድር ነጋን፤ አቶ ስንታዬሁ ቸኮልን። ግን ካቴና ሆነ ስንቃቸው።
የሆነ ሆኖ ተግተው በአማራ ጉዳይ ይሠሩ የነበሩት ሁሉ የሚጫናቸው መንፈስ አገሬ ነው። አገርም ሰው ሲኖር ነው። ሃይማኖትም ሰው ሲኖር ነው። ትውልድም ሰው ሲኖር ነው። ሰንደቅ ዓላማም ሰው ሲኖር ነው። ሰው አልባ ምኞት - ራዕይ - አገር - ሃይማኖት - ታሪክ - ቅርስ - ውርስ የለም። ፍላጎታችን ምድረ በዳ ላይ ነው።
አገርን በዬዘመኑ ለደረሰባት መከራ ሁሉ ግንባር ሆኖ ተጋፍጦ አይዞሽ ያለው ጭምቱ፤ አልጋው አማራ እና የአማራ ትውፊቶች፤ ታሪክ ሁለመና አደጋ ላይ ናቸው። አደጋ ላይ መሆናቸው ስታውቁ ኢትዮጵያም አደጋ ላይ ሞሆኗን ትረዳላችሁ። አማራን በማዳን ነው አገርን ማዳን የሚቻለው።
አገራዊነት ሰባዕዊነት ከነጠፈበት አገራዊነት እራሱ አልተፈጠረም። ደፍረው „እኔ አንድ አገር ወዳድ ዜጋ ነኝ“ የሚሉ ነፍሶች በአማራ ሰቆቃ፤ በአማራ መከራ፤ በአማራ ፍዳ ውስጥ እራሳቸውን ያገኙት ብቻ ናቸው አገር አዳኝ፤ ፈውስ ሊሆኑ የሚችሉት። ሙሴም!
አማራ ለይ እዬደረሰ ያለውን ሁለገብ መከራ ለመጋፈጥ ሰውነት በቂ ነው። ሰው መሆን መቻል፤ ማስቻልም። ሰው መሆን መቻልም፤ ማስቻልም ያልቻለ ነፍስ አገራዊ ሊሆን አይችልም። አገራዊነትም አልገባውም።
አገር በሰወች ማህብር የተሠራ ቤት ነው። ለዚህ ነው ማህበረ ሰብ የሚባለው ህዝብ። አገር ሰው ነው። ሰውም አገር ነው። አሁን ቅርስም፤ ውርስም፤ ተፈጥሮም እንሰሳትም እዬነደዱ ነው። የሳተ ጎመራ ጊዜ ላይ ነን። ሥርዓተ አልበኝነት ነግሷል። እና እንደምን በምን ሁነት መኖርን ማኖር ይቻል ይሆን? ነብይ ፍለጋ ላይ ነኝ።
እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
28.03.2021
ጎዳናዬ ሰብዕዊነት ነው!

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።