Enforced Disappearance) "በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣው ሰዎችን አስገድዶ የመሰወር (Enforced Disappearance) ድርጊት በአፋጣኝ ሊቆም ይገባል
"በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣው ሰዎችን አስገድዶ የመሰወር (Enforced Disappearance) ድርጊት በአፋጣኝ ሊቆም ይገባል
...
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ አካባቢዎች እየጨመረ የመጣውን የአስገድዶ መሰወር (Enforced Disappearance) እና ተይዘው የሚገኙበት ሁኔታ ሳይታወቅ በእስር ላይ የሚገኙ (Incommunicado Detention) ሰዎችን ጉዳይ ሲከታተል ቆይቷል።
አብዛኛውን ጊዜ የዚህ ድርጊት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው፣ ከሥራ ቦታ ወይም ከመንገድ ላይ የሲቪልና የደንብ ልብስ በለበሱ የመንግሥት ጸጥታና ደኅንነት ሠራተኞች ያለ ፍርድ ቤት የመያዣ ትእዛዝ ተይዘው ከታሰሩ በኋላ ወዳልታወቀ ስፍራ እየተወሰዱ እንዲሰወሩ የተደረጉ ሲሆን፤ ከፊሎቹ ከተወሰኑ ቀናት፣ ሳምንታት ወይም ወራት መሰወር በኃላ የተገኙ መሆናቸው የተገለጸ ቢሆንም፣ ሌሎች ይህ መግለጫ እስከተሰጠበት ጊዜ ድረስ በግዳጅ እንደተሰወሩ የቀጠሉ ናቸው።
ከእነዚህ ተጎጂዎች መካከል የተወሰኑት ሲያዙ በወንጀል ተጠርጥረው የሚፈለጉ መሆኑ ተነግሯቸው ወደ መደበኛ ፖሊስ ጣቢያ ከተወሰዱ በኋላ የተሰወሩ ሲሆን ከፊሎቹ ደግሞ ምንም ሳይነገራቸው በጸጥታ ኃይሎች ተወስደው የተሰወሩ ናቸው፡፡
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “ይህ አስከፊ የሆነ የአስገድዶ መሰወር ድርጊት በአስቸኳይ እንዲቆም መንግሥት አስፈላጊውን ጊዜያዊ እና ዘለቄታዊ እርምጃዎች ሁሉ እንዲወስድ፣ የተሰወሩ ሰዎች ሁሉ በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁ፣ በተሰወሩበት ጊዜ ሁሉ የተፈጸሙ ድርጊቶች ላይ የተሟላ ማጣራት ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም ችግሩ የደረሰበትን አሳሳቢ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ሀገር አቀፍ ገለልተኛ አጣሪ የሥራ ቡድን በማዋቀር የድርጊቱ ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ማፈላለግ እና ፍትሕን ማረጋገጥ ይገባል” በማለት አሳስበዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም “መንግሥት የአስገድዶ መሰወር ወንጀል ሰለባ ለሆኑ ሰዎች መፍትሔ መስጠቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህንን ወንጀል ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመከላከል ይረዳ ዘንድ፤ ሁሉንም ሰዎች ከአስገድዶ መሰወር ለመጠበቅ የተደረገውን ዓለም አቀፍ ስምምነት (International Convention for the Protection of All Persons from Enforced Disappearance) ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ተቀብላ እንድታጸድቅ ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል።"
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ