ዬተረጋጋ ሥርዓት የሚፈጠረው በዊዝደም እንጂ በግልቢያ አይደለም። ቦጅጃው የቋንጃ የኢትዮ ፖለቲካ እና አጤ ሂደት??? #ትናንት ፈርሶስ ዛሬ አለን ማለት ይቻል ይሆን? ተፈቅዶ በፈራረሱ ትናት እና ዛሬ ላይስ #ማግሥትን ማስላት ይቻል ይሆን???
ዬተረጋጋ ሥርዓት የሚፈጠረው በዊዝደም እንጂ በግልቢያ አይደለም። ቦጅጃው የቋንጃ የኢትዮ ፖለቲካ እና አጤ ሂደት???
#ትናንት ፈርሶስ ዛሬ አለን ማለት ይቻል ይሆን?
ተፈቅዶ በፈራረሱ ትናት እና ዛሬ ላይስ #ማግሥትን ማስላት ይቻል ይሆን???
ረዘም ያለ ፁሁፍ ነው። ትንሳኤን ለሚያልሙ ምራቃቸውን ለዋጡ የኔወች የተጣፈ ነው።
ውቦቼ እንዴት አደራችሁልኝ? በአራቱም ማዕዘን በማደምጣቸው ህውከት በሚንጣቸው፤ መረጋጋት በተሳናቸው አመክንዮ ዙሪያ ጥቂት ነገሮችን ላነሳሳ ፈቀድሁ። እንሆ ………
#እኔ ስል …… እንዲህ ………
ሂደት ሽግግር ነው። ሂደት የዘመን ልውውጥ ነው። ሰከንክም፦ በረገግክም ሂደት በራሱ ህግ እና ሥርአት ይሄዳል፤ ይተማል። ሂደት ጎዳናውን ያውቃል። በሂደት ውስጥ #አናርኪዝም ዬለም። ግጭቱ በሂደት ህጋዊ ሥርዓታዊ ጉዞ እና ሂደትንን ቀድመን እንቆጣጠረዋለን በሚሉ ዕብን መንፈስ አናርኪዝም ጉዞ ነው። የግጭቱ ስበት እና ስበቃ በመሃል አናርኪዝም ስላለ ስኬቱ ውድቀት፤ ጉም እና ትቢያ ማፈስ ይሆናል።
የሰው ልጅ እራሱን የሚመራበት ሥርዓት እና ህግ ሊኖረው ይገባል። በግሉ ማለት ነው። ያ ሥርዓት እና ህጉ ከብሄራዊ፤ ከሉላዊ ህግ ጋር ግጭት ሳይፈጥር ተስማምቶ ይሄድ ዘንድ ሂደትን ማጥናት፤ ሂደትን ማወቅ፤ ሂደት ለዘመኑ የደነገገውን ድንጋጌ ማወቅ። ዕውቀቱን ዕውቅና መስጠት ያስፈልጋል።
አንድ ሰው ተቋም ነው። አንድ ሰው ሚስጢርም ነው። ሚስጢርነቱንም ተቋማዊነቱንም መመራት፤ በቅጡ ማሰተዳደር የሚቻለው ሥርዓት መከተል ሲቻል ብቻ ነው። የሥርዓት ጥሰት የሂደትን መፋለስ ሳይሆን የሚፈጥረው የትውልድን አደራ እና ራዕይን ያፋልሳል። ሂደት በራሱ መርህ፤ በራሱ እውነት እዬተጓዘ #እደርተዋለሁ፤ ወይንም እደልዘዋለሁ፤ ወይንም አሸጋሽገዋለሁ፤ ወይንም ኢንጂነሪግ እሰራበታለሁ ብትለው ያስፈነጥርኃል።
እራሱን የገራ ሰብዕና ሂደት እና መርህን አጣጥሞ ብቻ ሳይሆን #አዋህዶ አካል ተአምሳል አድርጎ፦ በወጀብ መሐል እንኳን ወጀብን የመቋቋም አቅም እና ክህሎት ሊኖረው ይችላል። ያ #የቻለው አመክንዮ ዬሂደትን ሥነ ምግባር እና ዕሴት መሸከም የቻለው አመክንዮ ለዬትኛውም ተቋም መሪነት ያበቃዋል። መሪነት እራስን መግራት ነው። መሪነት እራስን ማረም ነው። መሪነት እራስን መግዛት ነው። መሪነት እራስን ለመርህ፦ ለህግ እና ለድንጋጌ ማስገዛት ነው። መሪነት አገልጋይነት ነው።
አገልጋይነቱ በመርህ እንዲመራ መፍቀድ ነው። መሪነት በሃሳብ ጥሻ ለጥሻ መሽሎክሎክ አይደለም። መሪነት ጠረጴዛ ላይ በተዘረጋ ግልጥ የመርህ ድንጋጌ ውስጥ ከፍቶ አቅም ፈጥሮ ያን አቅም በሥርዓት መምራት እና ማስተዳደር ነው። እንጂ የድብብቆሽ እንካ ስላንትያ አይደለም መሪነት። ቀድሞ ነገር ድብቆች ለዬትኛውም ተቋም አይበጁም። ጉድጓድ ለቀበር ብቻ። መሪነት ፍንትው ፏ ያለ የተስፋ ጣዝማን ዬሚቃኝ ግልጥ እና ቀጥተኛ፤ ሃሞተ ኮስታራ እና ንቁ ሰብዕናን ይጠይቃል። የተጫኑ ይመስል በትንፋሽ የሚናጡ ለዛ ለዞወችእንኳን ለብሄራዊ ለራስም ጋዳ ነው።
አንድ ተቋም ወይም ድርጅት ከአንድ አገር ህገ መንግሥት የተቀዳ በዛ ላይ የሰከነ የራሱ ደንብ ይኖረዋል። ማንም ሰው ከአንድ አገር ህገ መንግሥት በላይ አይደለም እና። የሆነ ሆኖ የፖለቲካ ድርጅት ከሆነ ማኒፌስቶ እና መሪ ዕቅድም ይኖረዋል። ያም አገሪቱ በምትመራበት አውራ የህጎች ሁሉ ዬበላይ በሆነ ህገ መንግሥት ይመራል።
#ጋራ።
ተቋም በግል እና በጋራ ነው የሚመራው። ሁሉም በጋራ፤ እያንዳንዱ በግል ድርሻ አለው። መሪነት ቲም ሊደርነትም ነው። ቲም ሊደሩ ላፀደቀው ደንብ ለመገዛት ኑሮውን የሚመራበት መርህ ድንጋጌ በቅድሚያ ሊኖረው እና በዛ ሥርዓት ውስጥ ሊሰክን ይገባል። ከተቋም መሪነት በፊት እራስን መመራት መለማመድ ግድ ነው። መቼም ፋንታዚ መርህ ነው ተብሎ ለሙግት እንደማይቀርብ ተስፋ አደርጋለሁ።
አንድ ውጥን ወይንምጥንስስ ሂደት ከዜሮ ይነሳል። አንድን ያስከትላል። ሁለት ቀጣዩ ነው። ሦስትም ቅደምተከተሉን ጠብቆ ይመጣል። 1 ……… 2 ……… 3 ……… 4 ……… 5 ……… 6 ……… 7 ………ወዘተ። ከዜሮ ተነስቶ አስር ደረስኩ ከሆነ ሂደቱን ያልጠበቀ ስለሆነ በመሃል ያሉ የህይወት ልምድ እና ተመክሮ ስለሚዘለሉ የተበጣጠሰ እና የተበተነ ይሆናል። ፍልሚያው በተደራጀው የሰከነ ዬሂደት ጉዞ እና እንደ ፌንጣ ከሚዘል የህውከት ጉዞ ጋራ ግጭት ይፈጠራል። ግጭቱ ብዙ አመክንዮወችን ይደረምሳል።
ለዚህ ነው በብጥቅጣቂ ብልጭ ድርግም በሚሉ ኩነቶች ላይ ሰፊ አትኩሮት፤ በመሰረታዊ የችግሮች መነሻ እና መድረሻ፤ እያንዳንዱ በሚፈጠረው ግዙፍ ችግር እራሱን ችሎ በሚፈጠሩ ጅረቶችም ከአቅም፤ ከቁጥጥር በላይ እዬሆኑ በግንዱ ወይንም በሥረ መሠረቱ ችግር ላይ ሳይሆን በደራሽ እና በጭፍጫፊ ችግሮች ልክ የለሽ ጊዜ ባክኖ ዬኪሳራ አፓርትመንት ዘመን ከዘመን የሚታነፀው።
#አንድ ምሳሌ በጭላንጭል ላንሳ ………
በዚህ አምስት ዓመት ሥርአቱ ትክክል አይደለም ብለው የሚታገሉ ነበሩ። ትክክል ነው ብለው የሚደግፋ ነበሩ። ሁለቱም ትክክል ናቸው። አለን በሚሉት ዕውነት። ነገር ግን አንዳንዱ ሲጀመር አብሮ ያልጀመረ፤ ሌላው በዬወራቱ በነጠብጣብ ዬተለዬ ይኖራል። ሁሉም ግን ሂደት የሰጠውን ጉዞ አያዳምጥም። እንደመጣ ዘው ነው። ግጭቱ ይህ ነው።
ይመስለዋል ሁሉም መንግስታዊ አገራዊ ውድቀት ብቻ አድርጎ። ሁሉም በድርሻው ልክ #መውደቁን አያስበውም። #ውድቀት #የሚጀምረው #በተሳትፎ #ውስጥ ከነበረው ሁሉ ጋርም ጭምር ነው። የሚገርመው በውድቀት ከብካቢነት ውስጥ የነበረው በትረን መመኜቱ ነው። በሌላ በኩል ቀድሞ የሞገተውም በሥርዓት ጥሰት ሂደት ጉዞ ጋር የግጭት ሰለባ መሆኑ ነው። በማህል ሁሉን አጥተን ቁዘማ????
ይህን መቀበል ይጠይቃል። ተስፋ ጥግ የሚያጣውም ለዚህ ነው። ህወኃት እንዲወገድ ስንሰራ ተተኪ አቅም አልነበረም። ዕዱሉ ለበላህሰብ ተሰጠ። ህውሃትም 27 ዓመት አረረ መረረም የሠራውን እራሱ ሰክኖ ባለማሰብ አነደደው። አሁንም ስልጣን ሲያስብ ወደ ሥልጣን ከመጣበት ዘመን ጋር የማይንፃፀር ቻሌንጆች እንዳሉ አያውቅም። አዲስ ኃይል አልፈጠረም። የደከመው እና የሰለቸው የተስፋ ማጣት የሚንጠው ድርጅት ይዞ ልፊያ ላይ ይገኛል። ተፎካካሪ፤ ተቃዋሚ፤ ተዋህጁም አድብቶ ጠበቀም አልጠበቀም አሸንፎ የሚወጣበት የፖለቲካ አቅም ጋራ ሆኗል። አደራ መጠጊያ አጥቶ የወወሌ ገበታ ላይ ነው።
ዬሚገርመው አሁንም ቦጅቧ ጃ የቋንጃ ፖለቲካ ላይ ተሁኖ ማግስትን ቀርቶ ዛሬን ማሰብ እንዴት ይቻላል ተብሎ አጀንዳ አልሆነም። ትናንት ፈርሷል። ምን ያልፈረሰ ነገር አለ? የብድሩ ዕዳው ሳይከፈል ትናንት የተበጀው ሁሉ ተገንዟል። ዛሬም እዬፈረሰ ነው። በትናንት ፍርስራሽ እና በዛሬ ፍርስራሽ መሃል ማግሥት በምን ይጠንሰስ???።
ቢያንስ እራስን መውቀስ፤ ከቆሸሸው የክህደት አዟሪት መውጣት እንዴት ያቅት??? የተሰባሰበ ተቋም ቀርቶ ሃሳብ የለም። አሁንም በመናድ ውስጥ ተሁኖ ቦክሱ ቀጥሏል። እኔ የማይገባኝ ጠቡ ምን እንደሆነ ነው? የትኛው ሰብዕና? የትኛው ተቋም ፃዕዳ ሆኖ??? ከሁሉም የሌለን የዕንባ ጉዳይ አሳስቦን የምንደክመው ስንታዘብ ብስል ከቀሊል፤ ተከሌ እከሌ ይሻላል የሚል ፍሬ ነገር የለም። ኢትዮጵያን ቁም ነገር የማድረግ ተልዕኮ እንዲህም፤ እንዲያም አይደለም።
እንጡሩብ በሚዘሉ ፕሮፖጋንዳወች እና ፕሮፖጋንዲስቶች #ትነት እና #ትንታ ትውልድም አገርም አይገነባም። እራስን ሳያጠኑ፤ አቅምን ሳይመጥኑ የሚደረግ ማናቸውም ጉዞ ትርምስ፤ ግርግር እና ፍርሻ ይሆናል ስኬት ይህ ነው ከተባለ¿¿¿¡¡¡ ሥም እና ዝና፤ ሽልማት እና ዬተከታይ ብዛት አቅም አይሆንም። አቅም ከእራስ የሚገኝ የዕውቀት ሃብት ነው።
ኢትዮጵያ #ሥርዓት ናት። ኢትዮጵያ #ህግ ናት። ኢትዮጵያ #ፍልስፍና ናት። ኢትዮጵያ #ዩንቨርስ ናት። መንፈሷ ኃያል ነው። ኃያልነትን ለመምራት ከራስ የጀመረ ጥራትን ይጠይቃል። ጥንቃቄ ይሻል። ለመምራት ብቻ ሳይሆን ለመመራትም ፈቃድ ይጠይቃል። #ፈቃድ ቀላል ቃል ነው። የሦስት ፊደላት ቅምረት። ግን በፈቃድ ውስጥ ያለ እሺታ፤ ይሁንታ፤ ታላቁ የፍቅር ተፈጥሮ አንከር ነው።
ለክርስትና አማንያን "በመጀመሪያ ቃል ነበረ። ቃልም እግዚአብሄር ነበረ። ቃልም እግዚአብሄር ሆነ።" እያንዳንዱ ቃል የተፈጠረበት የራሱ ማንነት፤ ዬራሱ ተደሞ፤ የራሱ ጥሪ እንደ እኔ እንደ እርስወ አለው። እምነት ያለው፤ ሃይማኖት ያለው በቃለ ወንጌልም ሆነ በቁራዓን ድንጋጌወችን እፈፅማለሁ ሲል፤ እሱን እራሱን ለሚመራበት፤ ሂደት እራሱን ለሚያስተዳድርበት ኩነት፤ በእጄ ለተቋሜ አዘጋጅቸዋለሁ ለሚላቸው ልዩ ልዩ ሰነዶችም መገዛት መፍቀድ፤ ይለፍ መስጠት ይገባል።
ዜሮ ላይ መሆንን መቀበል ያስፈልጋል። ማንም በኢትዮጵያ ፖለቲካ #ከዜሮ #በላይ የተራመደ ዬለም። "ኢትዮጵያን አድነናል" ብሎ መታበይም አያስፈልግም። እራስን ማድመጥ የተሳነ ሰብዕና ተሸክሞ ማዳን አይታሰብም እና።
መማር፤ መመራመር እኮ ተሽሎ መገኘት ነው። ተሽሎ ለመገኘት ቢያንስ የተፈጥሮ ድንጋጌወችን ሂደት የሚመራባቸውን መቀበል ያስፈልጋል። #ተጠውራ በጀት የምትይዝ አገር፤ #በመቀለት እዮቤል ቤተ መንግሥት ግራ ቀኝ ካልሠራሁ እያለ የሚገለግል ሥርዓት "የነቀዘ ስንዴ አያስፈልገኝም" ሲል ይደመጣል። በመደበኛ መጓጓዣ ቀርቶ ቻርተር ይታዘዛል። አመት ይዞ እስከ አመት ግብረሰላም እና የፋሽን ትዕይንት ይቀልጣል፤ የፕሮሚ ጉዞ እና ጥበቃው፤ የሆቴል ውሎ እና አዳሩ ኢትዮጵያ ቅንጡውን ሞናኮን የተሆነ ያስመስላል። ይህ ሁሉ ዝክንትልትል ተሸክም በብጣቂ ነገር ሁለመና ይቃጠላል። ሁሉ ነገር ይደቃል።
እንሆ ዛሬ ምክንያታዊ አመክንዮ እዬተዘለለ በሳቢያ ላይ በመዳከር እራሱን ችሎ ሊቆም ያልቻለ ማህበረሰብ ኖረን። ይህ የሚያስመካም፤ የሚያስፈነጥዝም አይደለም። ይልቁንም አንገት የሚያስደፋ እንጂ።
ድል ስኬት የያዙትን አጠናቆ፤ ግድፈትን አርሞ፦ ህዝብን አማክሮ እና አድምጦ ለቀጣዩ ስኬት በአቅም ልክ፤ አቅምን ቆጥቦ አቅምን በቅጡ ማስተዳደር ነው። ስኬት ቅምጥ ፍላጎትን አሽኮኮ አድርጎ፤ ህዝብን እያምታቱ ከድህነት ወለል በታች ማባከን አይደለም። ወይንም ይህን ብክነት ከብክቦ ገበርዲን እና ከረባት እዬቀያዬሩ፤ ፋሽን እያሳዩ በውድቀት ኦርኬስተር አብሮ መዳነስ አይደለም።
#መሪነቱም #አልታወቀበትም። የህልመኛ ማት ተትረፍርፏል በተዥጎረጎረ ሥያሚ። ጠያቂም የለም፤ ለመጠዬቅም ፈቃድ የለም። የሰው ልጅ ከኢንሴክት በታች ሰርክ ይታጨዳል። የሰው ልጅ ቄራ ተከፍቷል። ይህ አንገትን ቀና ያደርግ ይሆን? ይህ ይሆን አገር ማዳን? ይህ ይሆን የህዝብ አገልጋይነት????
#አደራም ባለቤት አልቦሽ ነው። እራሱን ያልገራ ሰብዕና ብስልም - ቀሊልም፤ ቅንጣትም - ግዙፍም ኃላፊነትን ተቀብሎ ሊመራ፤ ሊያስተዳድር ፈጽሞ አይችልም።
ተስፋ አያልቅም። ተስፋ አይቋረጠም። ተስፋችን አምላካችን ነው። አምላካችን በስክነት፤ በመረጋጋት ውስጥ ለሆኑ ጥቂት ስኩን መንፈሶች ሲል መልስ ይሰጥበታል። ከሂደት ጋር ሳይጋጩ፤ ከሂደት ጋር እንካ ስላንታያ ሳይገጥሙ፤ ከፈላው ጋር የማይፈሉ #ትነቶች ያልሆኑ ባለ አደቦች በፀሎታቸው፤ በድዋቸው ኢመርጀንሲ ሩም ያለችውን እማን እና መሪ፤ ሙሴ፤ እረኛ አልባ ለሆነው ህዝባቸው በረከት ይሆናሉ።
ኢትዮጵያ በአንድ ቀን አልተሰራችም። ኢትዮጵያ በአንድ ምሽት አልተበጀችም። ኢትዮጵያ የሂደት ዕንቁ ስኬት ናት። ሂደት ሠርቷታል። ሂደት ይጠብቃታል። ከመስመር የወጡ ማናቸውም ሁነቶች በተፈጥሮ ህግ ይዳኛሉ። በዬትኛውም ክስተት መደናበር አያስፈልግም። ጊዜ ታሪክን ለባለታሪኩ ያስረክባል።
ታሪክ የሚሠራው በቀደመ ህዝብ ነው። በዛ ዘመን በኖረ ህዝብ መኖርም በጥበብ ይበጃል። በሌላ በኩል የተበጀን ለመናድ በሚካሄደው ፍልሚያ እራስም መናድ እንዳለ ሊታወቅ ይገባል።
#ክወና ፈጣሪዬ ሆይ!
ሁሉ ይቻልኃል። ሁሉንም ነህ። ታያለህ ትሰማለህም። ዬንስኃ ጊዜ ሰጥተህናል። ከውድቀታችን እንማር ዘንድ ለሰጠህን ፈቃድ ተመስገን ኤልሻዳይ።
ክብሮቼ ደህና ዋሉ። ደህና ቆዩኙ። ሙሉ ምስጋና በዘንካት አክብሮት።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
09/06/2023
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት ስለራሱ አይሰንፍም።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ