የህሊናችን ቤተኛ ሊሆኑ የሚገባቸው ወገኖቻችን በማንኛውም ሁኔታ ማሰብ ይገባል።
የህሊናችን ቤተኛ ሊሆኑ የሚገባቸው ወገኖቻችን በማንኛውም ሁኔታ ማሰብ ይገባል።
" ጎለመስሁ አረጀሁም፤ ፃድቅ ሲጣል፦ እህል ሲለምንምአላዬሁም"
(መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፴፮ ቁ ፳፭)
ወገኖቻችን ሲታሠሩም ሲፈቱም የራሳቸው ምልከታ ሊኖራቸው ይችላል። የአቋም ለውጥም በማንኛውም ጊዜ ሊያመጡ ይችላሉ። ይህን መጠበቅም ብልህነት ነው። ከሁሉ ሊቀድም የሚገባው ጉዳይ ግን #ሃሳባቸው፤ #ዓላማቸው #ሊሞገት እንጂ #ሊታሰርም ሆነ ሊገደል ወይንም ጥቃት ሊደርስበት አይገባም ብሎ መሞገት ከእያንዳንዳችን በግል ከሁላችን በጋራ የሚጠበቅ ብሄራዊ ግዴታ #ይመስለኛል።
ሌላው ለአብዛኛው ህዝብ የሚሆን ስኬት ለማዬት ያለተበቃው ሥርዓት፤ zየተቋማት ግንባታ፤ አደረጃጀት ላይ በሳል የሆነ የጥናት እና የምርምር ተግባር በትጋት አለመሠራቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ መስዋዕትነቱን፤ ድካሙን የሚመጥን ስኬት አልተገኘም። ብዬ አስባለሁ። ዛሬም ዓውዱን ስታዩት ይሄው ነው።
በደራሽ ጉዳይ ተቋማት ሲገነቡ ታያላችሁ። በደራሽ ጉዳዮች ላይ የኃይል አደረጃጃት አሰላለፍ ታያላችሁ። ይህ ደግሞ ዘላቂ መፍትሄ አስገኝ አይሆንም። በቅርቡ እንኳን ግፋዓን ሰብሳቢ ያን ትተው አዲስ የፖለቲካ ድርጅት ከፋኖ አዲስ የጎመራ ንቅናቄ ጋር እንደመሠረቱ፦ የዚያም መሪ እንደሆኑ አዳምጫለሁ። ብሄራዊ የፖለቲካ መሪነትም ወደ ፋኖ ሰላማዊ ዝውውርንም አስተውያለሁ። የፋኖ ንቅናቄ ባይጎመራስ??????
#በምልሰት መገበር ዬዕውቅናውን አድራሻ።
ግዙፋን ብናይ የሻብያ እና የደርግ ጦርነት፤ የሱማሌ እና የኢትዮጵያ ጦርነት፤ የባድመ ጦርነት፤ የዶር አብይ መንግሥት እና የህወሃት ጦርነት እስከ ደቡብ አፍሪካው ስምምነት ይህ መንግሥታዊ ሁነት ሲሆን፦ ከኢህአፓ እስከ ቅንጅት ባለፈም እስከ ኢዜማ ያለውን የአደረጃጀት ሂደቱንና ስኬቱ እና ትውልድ የማትረፍ አቅሙ፤ የተሰውቱ ወገኖቻችን እና ቤተሰቦቻችን ሁኔታ፤ የመስዋዕትነቱ አድራሻ እና ዕውቅና ስታዩት በአመዛኙ ትርፋ #ዕንባ፤ ጧሪ ጠዋሪ ማጣትን፤ የባሊህ ባይ ድርቀትን እናስተውላለን። የ97ቷን ዕንቁ ሽብሬ ደስአለኝን ዛሬ ማን ያስታውሳታል??? ስኬቱ መረሳት ነው። ምክንያቱም ያ ሁሉ የተከፈለ መስዋዕትነት ዛሬን ማዳን አልችል ብሎ ኢትዮጵያውያን #በዜግነት #ከማይታወቁበት፤ #ለህልውናቸውም #ዋስትና ያጡበት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። ዓውዱ በፍርሃት ተውጧልም።
ነፃነት ተዘርፏል። ሥልጣን ላይም ላለው፤ ለደጋፊውም ለሞጋቹም ህይወት በፍርኃት ሰቀቀን ላይ ነው። አንድ የአገሬ ልጅ ሰሞኑን ዕቃ ተሸክሜ መንገድ ላይ አገኜኝ። እና ሊረዳኝ ፈቀደ። እኔ ግን አልፈቀድኩም። ለዛውም በቅድስቴ ምድር ሲዊዘርላንድ። ዶር አብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ ምሽት ወጥቼ አላውቅም። ማህበራዊ ኑሮም ማዕቀብ ተጥሎበታል። ጥንቃቄ ያተርፋል እንጂ አያከስርም የሚል መርህም ስላለኝ። ነፃነታችን እራሱ ኢመርጀሲ ክፍል ውስጥ ነውና።
#ድካም እና ስኬት ስለምን ተራራቀ።
ለምን? የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚመራው #ደራሽ እና #ሰበር ሁኔታ ስለሆነ። "ኢትዮጵያ ሱሴ ናት" ያስከፈለው መስዋዕትነት ተዘንግቶ ዛሬም በቀላል አቀራረብ ተበውዘው ለሚቀርቡ ቅብ አገላለፁች አንጋፋ እና በሳል ተንታኝ ነን የሚሉት፤ ናቸውም የሚባሉት እዛው መልሰው ለመነከር ዳር ዳር ሲሉ ስመለከት አሁንም፤ ዛሬም ኢትዮጵ ያለባትን መከራ የመረዳት አቅሙ ግልብልብ መሆኑን እረዳለሁኝ። የችግሩ መነሻ ነጥብ በግልብልብ ክስተት ወይንም ዲስኩር ይጠቀለላላል።
ሌላም ምሳሌም ላንሳ። ፋኖ የአማራ ህዝብ ትራድሽናል ዘብ አደር ነው። አብሮት የኖረ ነው። ፋኖን እንደ ፖለቲካ አካል ወስዶ በማኒፌስቶው ያስገባ የለም። የፋኖ ንቅናቄ ሲነሳ ግን ጡጧቸው የሆነ የፖለቲካ ድርጅቶች ተመልክቻለሁ። ለዚህም ነው እኔ በተዕቅቦ ያለሁት። በፋኖ ሆነ በጠቅላላ የአማራ ፖለቲካ ስተጋበት እንደነበርም ይታወቃል። መከራውንም ስታገል።
የሆነ ሆኖ ፋኖ ባይነሳስ ኖሮ የዛሬ የፖለቲካ ድርጅታቸውን ድምጽ የቀዬሩት ምን ይሆኑ ነበር? የሚገርመው ይህ ወቅትም እንደ አለፈው #የተጋድሎ #ዘመን #ይረሳል። የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ የጎንደር ፋኖ በአርበኛ ጎቤ አማካኝነት ደጀን ነበር። ተገብሯልም። አርበኛ ጎቤ ምንም ያልጎደለበት የትዳሩ የደረጀ ከፍ ያለ ትጉህ ለኑሮው የማያንስ፤ ኑሮው ያማረ፤ የሠመረ ነበር። አርበኛ ጎቤን የራስ ለማድረግ ብዙ በጣም ብዙ ትርምስም ነበር የፖለቲከኞች።
አርበኛ ጎቤ ፋኖ ነው። ፋኖ የሚመራው #በጎበዝ #አለቃ ነው። ፋኖ የፖለቲካ ድርጅት ከነመፈጠሩም አያውቀውም። የገበሬው በሃል ነው። እራሱ የጎበዝ አለቃ የሚለው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዕውቅና የተሰጠው አልነበረም። ለመጀመሪያ ጊዜ ቃሉን የተጠቀሙት አቶ ተክሌ የሻው ነበሩ። ድርጅታቸው ሞረሽም ምንም ዓይነት ገፊ ሰበር ዜናን የተጠለለ አልነበረም።
በራሱ ጊዜ ችግርን ቀድሞ የተደራጄ ተቋም ነበር። ተቋሙ በተቋቋመበት ዓላማ ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ ልክ እንደ ኢሠመጉ የመቀጠል ዕድሉ ሰፊ ነበር። #ለጋ ክስተቶች ሳይጠኑ ወደ ፖለቲካ ድርጅት መቀዬራቸው፤ ቢጠኑም በተቋቋሙበት ዓላማ ፀንተው ቢቀጥሉ ለኢትዮጵያ ተስፋነት ተስፋ ይሆኑ ነበር። ምክንያቱም የአገር ሉዓላዊነት በልዕልና የሚቀጥለው በተቋማት አደረጃጀት ጥራት እና በመሪ ብቃታዊ ተመክሮ ነውና።
ሁለተኛ ባልደራስንም ስናይ የተቋቋመው በሲቢክስ ተቋምነት ነበር። ቢቀጥል #ፓን #አፍሪካኒስት ላይ ቢተጋ፤ ዛሬ ባለቤት የለላቸው ብዙ በጣም ብዙ ኢትዮጵያዊ ክስተቶችን በሰከነ የዲፕሎማሲ ትግል ድጋፍ በገፍ ይሆን ነበር።
ይህ ቢቀር እንኳን ቢያንስ መስዋዕትነቱን መቀነስ፤ የፍላጎት ዕውቅና ማግኜት፤ በተቋም ግንባታ ዘላቂ ትጋት ተስፋን አርቆ የማዬት ዕድሉ ይኖር ነበር። ባልደራስ በሲቢክስ ሀ ሲል በጥዋቱ የገጠመውን የገዘፈ ፈተናውን አውቀዋለሁ ፕሮፖጋንዲስት አያስፈልገኝም። ግን በፖለቲካ ድርጅት ካስገኜው ይልቅ በሲቢክስ ተቋም ቢቀጥል አህጉራዊ አቁም፤ የአማካሪነት አቅሙ፤ የተደማጭነቱ የውሃ ልክ የትውልድ በሆነ ነበር። አመሠራረቱ በገፊ ሁነት አነሳሽነት ቢሆንም።
መሰዋት ካልቀረ ለሥርዓት ለውጥ ምስረታ አይከን በሆኑ የተቋማት ግንባታ እና ቀጣይነት ላይ ሊተጋ ይገባል ነው የሃሳቤ ዛቢያ። የተከበሩ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን ለሁለት ጊዜ ምርጫ ድል ያበቃው የተቋማት ግንባታ ጥረት እና ጽናት ነው። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ይህ #የማይደፈር #የሚፈራም ግን #ያላባራ የዴሞክራሲ ግንባታ ምኞተኝነቱ እና ጥማቱ ግን ውርስም ቅርስም ሆኗል። መመኜት ማለም ብቻውን ለግብ አያበቃም። ዴሞክራሲ ያጣው ሁሉ በቅድሚያ ዴሞክራሲን በራሱ ህይወት፤ በራሱ ተቋም ሁኖበት አስተማሪ ሊሆን ይገባል። ራሱን የገሰፀ፤ ያረመ፤ እራሱ የታረመ ንግግር የማድረግ አቅሙ እንኳን ጮርቃ ነው ፖለቲካው።
ዛሬ በእስር የሚንገላቱት ወገኖቻችንም ነገ ይረሳሉ። #የሚረሱት ዛሬም በህይወት እያሉ ነው። ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የታገሉ እኮ እንደ ጀግና አይታዩም። የአርበኛ ቤተሰብ ደሞዝም አይከፈልም። ለምን? የኢትዮጵያ ፖለቲካ መሪው ደራሽ #ክስተት ነውና።
መድከም ካልቀረ፦ መሰዋት ካልቀረ ዛሬን የሚያሳድር፦ ነገን በክብር የሚያስቀጥል ተግባር ላይ ሊተኮር ይገባል። ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ሙሁራን ብቻ ሳይሆኑ #በፀጋቸው ሙሉ አቅም የተሰጣቸው ኢትዮጵያዊ ዜጎችን ሁሉ በቅንነት ፈቅዶ እና ወዶ ማሳተፍ ይገባል።
#አግላይነት፤ #አጋ፤ አንጃ፤ ቡድነኝነት የዞግ ፖለቲካ የሚጠዬፋ ሁሉ መለያ ነው። ኢትዮጵያን ተስፋ ማድረግ ከዚህ ዲሪቶ ጉዳይም መነጠል ይገባል። በዚህ ዘርፍ መዳን አለመቻሉ ብዙ ድሎች መላጣ፤ ልሙጥ እንዲሆኑ ሁኗል። አሁንም በዛ መንገድ ከሆነ፤ ከልብ መቀራረብ ከሌለ ልብ እና ኩላሊትን የሚመረምረው አምላክ ቋንቋችን ይደበላልቀዋል። አልተመቸነውምና።
ሴራ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ እንደ ፍልስፍናዊ ዕውቀት የሚታይ ገመና ነው። ርህርህና ነው ፍልስፍና ሊሆን የሚገባው። አብሮነት ነው መርህ ሊሆን የሚገባው። አንቺ ትብሽ አንተ ትብስ ነው ጎዳና ሊሆን የሚገባው። አለን? የለንም። ግን እንመኛለን። የምኞታችን ባለአንጃ እራሳችን ነን። አንድ መሰዋት፤ አንድ ለካቴና መብቃት የለት ዜና ብቻ ነው። ያ አቅም አጀንዳነቱ ቀጣይ አይሆንም። ለወርት የሚዲያ ዲኮሬሽን።
የሆነ ሆኖ በማፍሰስ የሚታወቀው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ነዳላው ብዙ ነው። በነዳላው ልክ መገበር ሲታከልበት የነገን ተስፋ አንገት ያስደፋል። በስክነት፤ በእርጋታ ውስጥ ወረተኛ ሳይሆኑ በሩቅ አስቦ በሥርዓታዊ ጉዞ ህልምን ለማሳካት መታተር የትውልዱ ተግባር ሊሆን ይገባል። ሁሉን ነገር ሥልጣን ካለው መንግሥት፤ ወይንም ከፖለቲካ ድርጅቶች ሊጠበቅ አይገባም።
ከራስ መጀመር የችግር መፍቻ ቁልፍ ነው። በተለይ ትርፍ ንግግር፤ ማቃለል፤ ማጣጣል ከሁሉ ቀድሞ ሊታረም የሚገባ ነው። ለዚህም ነው ንጉሥ ዳዊት "ለአንደቤቴ ጠባቂ አኑርልኝ" ያለው። በማቃለሉ፤ በማጣጣሉ፤ በዘለፋው ውስጥልዕልት ኢትዮጵያም እንዳለችበት ሊታሰብ ይገባል። እናትን አሻቅቦ መናገር ትውፊትም፤ ትሩፋትም አይደለም። አክብሮ መሞገት፤ ተከባብሮ መታገል ይገባል። ማዕዳችን ያቺው ኢትዮጵያ ናትና።
ክወና ቀላሉን ሳንደፍር የከበደውንማ????
ያዘኑትን ማጽናናት፤ ለታሠሩት ጠበቃ መሆን ማን ያዘን???? ሼር ማድረግ እንኳን ብርቅ ነው። ሰውነት እዬሸሸን ይሆን???
ክብረቶቼ እንዴት አደራችሁልኝ። በደራሽ ዜናወች አትዋጡ። በዘለቄታ ተግባር ላይ ትተጉ ዘንድ ትለመናላችሁ። ካቴና ላይ ለሚገኙት አወቅናቸው አላወቅናቸውም አይዟችሁን መንፈግ አይገባም። ኑሩልኝ። እግዚአብሄርም ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉትሻ
13/05/2024
ጊዜ ራዲዮ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ