ቋንቋን የቻለ ሁሉ የአንድ አገር ፖሊሲን መተርጎም ይችላልን?

 May be a doodle of 1 person and text

#ቋንቋን የቻለ ሁሉ የአንድ አገር ፖሊሲን መተርጎም ይችላልን?

 

" እኔ ችግረኛ እና ምስኪን ነኝ፦

ጌታ ግን ያስበኛል፥

አንተ ረዳቴ እና መዳህኒቴ ነህ፤

አምላኬ ሆይ አትዘገይ።"

(መዝሙረ ዳዊትምዕራፍ ፴፱ ቁጥር ፲፮)

 

 

ሰሞኑ ዘለግ ያለ የፖለቲካ ሃሳቦችን የያዘ የአሜሪካ አቋም በአንባሳደሩ አማክኝነት ተገልጧል። እንግሊዘኛ ቋንቋ የቻለ ሁሉ እፍታውን በጥድፊያ በራሱ የፖለቲካ ዝንባሌ ተንትኖታል። አንደኛ ችኮላው ገርሞኛል። ሁለተኛው ሁሉም ተንታኝ ሆኖ መቅረቡ አስደንቆኛል። ዲፕሎሚሲያዊ ጉዳዮች ተደሞን፤ አንክሮን አብዝተው ይሻሉ።

 

#ተዚህ ላይ ወግ ቢጤ እምር አለኝ።

 

እኔ በአማርኛ ቋንቋ 7 ዓመቴ ጀምሮ ክትትሉ አለኝ። ትጋቱም እንዲሁ።

 

#ምክንያት

 

ወላጅ አባቴ አቨይ መምህር እና የቤተ መፀሐፍት ኃላፊ ስለነበር፤ ለእኔም ልዩ የህሊና እንክብካቤ ያደርግ ስለነበር አማርኛ ቋንቋን የኦክስጅን ያህል ሰውነቴ ይጠቀምበታል። እናላችሁ ከሁለት ሳምንት በፊት የቅኔውን ልዑል የብላቴ ሎሬት ፀጋዬ / መድህን ራዲዮ በሲዊዘርላንድ ዙሪክ ከተማ አለኝ። በወር ሁለት ጊዜ በዕለተ ሃሙስ 15.00- 16.00 ሰዓት በአማርኛ ቋንቋ በበዛ ጥንቃቄ እና ጥራት 16 ዓመት እዬሠራሁ ስላለ በቀጣይ የብላቴውን የሎሬት ግጥም ሙሉ ፕሮግራም ልሥራበት ብዬ ጀመርኩላችሁ።

 

ዕውነት ልንገራችሁ አማርኛ #ቋንቋዬን የቤተሰቤ የአፍ መፍቻ ቋንቋን፤ እንደ ነፍሴ እምወደውን ቋንቋ ማንበብ አቃተኝ። "እሳት ወይ አበባ" የመጽሐፋም ዕርዕስ ነው። ወጣቶች ኢትዮጵያ ላይ ትወና እዬሠሩበት መሆኑንም ተከታትያለሁ። እናላችሁ እሱን መቅድም ላድርግ ብዬ ፈተነኝ፤ አሸኝ፦ ገመደኝ። በጣም ነው የከበደኝ። ለእኔ አማርኛ ቋንቋ ቅኔን ማንበብ የከበደ ለሌላውማ እንዴት ሊሆን ነው ብዬ መደዴ ትምክህታችን ጋር ተፋጠጥኩኝ።

 

እና አማርኛ ቋንቋ የቻለ ሁሉ የአገሬ ፖለቲካ ተንታኝ፤ አለፍ ሲልም የፖሊሲም ተርጓሚ ሆኖ ያለፍንበትን ዘመን በምልሰት ቃኜሁት። እንኳንስ በእንግሊዘኛ ቋንቋ፦ ፖለቲካ ፖሊሲያዊ ሚስጢር እርስበርስ ተዋደው እና ተዋህደው የተገኙበት የታሰበት ማብራሪያ ቀርቶ። እንደ ቃተኛ እንጃራ ወዲያው ነው ሚዲያወቹ ሁሉ በሽሚያ የተጣዱበት። እንደ ተራ ንግግር የለት ትንተና ሆኖ ሲቃጣ ግርም አለኝ። ሊጠና ይገባው ነበር። የሙያው ባለቤቶች ዕድሉ ተሰጥቷቸው ግብረ መልሱን አክለው ሊታደሙበት ይገባ ነበር። የሠርግ ወይንም የግጥግጥ ውሎ አልነበረምና።

 

ቋንቋ ፕሮፌሽናል አስተርጓሚ አለው። ሙያም ነው። በኢትዮጵያ ቋንቋዊ አስተምህሮ ፊደላት እንኳን ድርብ ከሆኑ አግባባቸው የተለዬ ነው። በተለምዶ በስዱ እንዳክረበታለን እንጂ ንጉሥ፤ ፀሐይ፤ ሐሤት፦ ሥራ፦ ዐይን ወዘተ በፊደላት ሚስጢራዊ ባህሪያት የተያዙ ናቸው። በቤተክህነት ሥም እራሱ የሆሄያት ጥንቃቄ ከሌላቸው በስኬት ረገድ፤ በጤና ረገድ ሳንክ ይገጥማል ይባላል።

 

ጋዜጠኛ ሳዲቅ የድምፃችን ይሰማ ጋዜጠኛ እና የፖለቲካ ተንታኝም ነበር። ዛሬ እንዲህ ድብዛው ሊጠፋ። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ የመንበረ ሥልጣን ንግግራቸው ስለ ድምፃችን ይሰማ ዕውቅና የለውም ንግግሩ ብሎ ሲፎገላ ነበር። በወቅቱም የመሪ ንግግር የፖሊሲ ፍንጣቂ ቢኖረውም ግን ለለቱ የቀረበው ዘገባዊ ሳይሆን የኪዳን ውል መዋዋያ የመነሻ ሃሳብ ማስተዋወቂያ ነበር።

 

ትናንት በነበረው የአሜሪካ ኢንባሲ ታሪክን መነሻ አድርጎ በኢትዮጵያ ውስጥን ገላጭ ንግግር እፍታው የመንግሥት ዩቱበሮችን አስፈንጥዞ ነበር። በተለኝ ነገረ አማራ ፋኖን የሚመለከተው ዕድምታ። የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ መንግሥት በከፋኝ ዕይታውን ሲያጋራ ደግሞ ቆዝመዋል። ይህ ስክነት አልቦሽ ትርምስም ነው አልቦሽነትን እያሳለበን ያለው። ለሞላው ጊዜ ምን ያጣድፋል? ተጣድፈን ምን አሳካን? ለዛውም በጀቷ በብድር የተንጠለጠለች አገር እያለን።

 

የሆነ ሆኖ ችግሩ ጥድፊያው ነው። ምን ያስቸኩላል። የአንድ አገር መንግሥት ለዛውም ባለ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ባለቤት አገረ አሜሪካ ድምጽ ተግታን ይጠይቅ ነበር። አብዝቶ ማድመጥን ይሻም ነበር። የቋንቋ አስተርጓሚወች አይችሉትም። የሚችሉት በሙያው ዕውቀቱ፤ ልምዱ፤ ተመክሮው ብቃቱ ያላቸው፤ የዬትኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል ያልነበሩ፤ አካልም ያልሆኑ #የዲፕሎማቶች ተግባር ነበር። ሽሚያው ግን ይህ ነው አይባልም።

 

ብዙ ጊዜ አንከር ሚዲያ የሚቀርቡ አቶ ጥላሁን አዳሙ ስክነታችው ይመስጠኛል ከዕውቀታቸው በላይም፦ ተመክሯቸው ወጣትነቱ ካልተጫነው እሳቸው ቢተረጉሙት ድንቅ ነው። እዬጠበቅኩ ነው። የአንከር ሚዲያ ባህል ሙያተኞችን ማሳተፍ ተግባሩ ስለሆነ። ሌላው እንደ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዓይነት ባለሙያወችም ናቸው ይህን መሰል ጉዳይ ደፍረው ሊተነትኑት የሚችሉት በቁጥብነት። በኢትዮጵያ ፖለቲካ በሁሉም የሙያ ዘርፍ ሁሉም ተንታኝ ነው።

 

ጉሮሮ ያለው ሁሉ ተናጋሪ ሊሆን አይችልም። ጉሮሮ ያለው ሁሉ ሳቢ እና ማራኪ ድምጽ ላይኖረው ይችላል። ድምጡ አሮጌ ቆርቆሮ የሆነ የሚዲያ ባለቤት፤ ዜና ዘጋቢ ከሆነ ዜናው ቢያስፈልገኝም እኔ አላዳምጠውም። ውስጤ እንዲቀበለው እምሻው ቃና አለና።

 

በፖለቲካ ትንታኔም እንደዚሁ ነው። ድምፁ፤ ልማርበት የምችለው ልኬታ አስልቼ ነው ጊዜ እምሰጠው። ዛሬ ደግሞ አማራጩ ሰፊ ነው። ፊትም ቢሆን ድምጽ የመጀመሪያ መሥፈርቴ ነው። ሞናትነስ ዬሆኑ፤ ተናግረው ያልጠገቡ አውያዮችንም አላዳምጥም። በተለይ ተጠያቂ አስቀምጠው እነሱ ጀምረው ሙሉ ጊዜውን ተንሰራፍተው የእንግዳን የዕውቀት ማሳ የሚሻሙትን አላዳምጥም። ፕሮፖጋንዲስትም ስለማያስፈልገኝ።

 

#እንደ መከወኛ።

 

ፋኖን በሚመለከት በዲፕሎማሲው ዘርፍ የተሠራው ሥራ ደረጃውን አይቻለሁ። በውጭ የሚገኜው ሁሉ ጄኒራል፤ ሁሉ ኮነሬል፤ ሁሉ ሻለቃ እና ሻንበል፤ የኦፕሬሽን መሪ እና አቅጣጫ ነዳፊ ሁሉ የት ሂዶ ይሆን????? ብለናል እኔ እና ብዕሬ።

 

አወንታዊነት ይሰነቅ። ውጤትም ስኬተም በፈቃደ እግዚአብሄር እና በትጋት ይገኛል። አግንኖም አከስሶም ማዬት አይገባም። ለደስታም ትንሽዬ መደርደሪያ ያስፈልጋል። ምክንያት …… ደስታው ባይገኝ ተስፋ ቆራጭነት፤ ደስታውም ቢገኝ ሌላ ደስታ ሲገኝ ቦታ እንዳይጠፋ፤ ከሁሉ በላይ ግን ደስታ ሲበዛ ህግ መተላለፍን ባለፈም ምርቃት ስለሚያስነሳ። ልባም ተግባር ሲከወን እንደ ቄጤማ አይነሰነስም። ህሊና ያላቸው ክድን አድርገው ይይዙታልና። ውዳሴ አጀንዳቸው አይደለምና። ልታይ ልታይንም ይጠዬፋታልና። በልክ መኖር መርሃቸው።

 

"ልክን ማወቅ ከልክ ያደርሳል" ይላሉ ባለቅኔወቹ ጎንደሬወች።

ውዶቼ ደህና አምሹልኝ። አሜን።

 

ሥርጉትሻ

17/05/2024

ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።