#ቀይ ሽብር በኢትዮጵያ ተጀምሯል።
"ከንቱ የከንቱ ከንቱ ሁሉ ከንቱ"
(መጽሐፈ መክብብ ምዕራፍ ፩ ቁጥር ፪)
#ጠብታ።
ሰማዕቱ አቶ አወቀም በመኖሪያ ቀበሌው በጨካኙ የሄሮድስ አብይ አህመድ አሊ ነፍሰ በላወች ተረሽነዋል። ይህን የእኛ አቤል ሰማዕቱ ንገረው አዲስ በአይኑ ተመለከተ።
#የመከራ ደወል!
ሰማዕቱ ንገሩው አዲስ የ13 ዓመት ታዳጊ ወጣት ነው። ታዳጊው ወጣት የ4ኛ ክፍል ተማሪ ነው። ሰማዕቱ፣ ተማሪው እና የበግ እረኛው ንገረው አዲስ እንደ ልጅ ተጫውቶ የማያውቅ፣ በቁም ነገር ላይ የሚያተኩር፣ ለጎረቤቶቹ በሙሉ ታዛዥ፣ ፍፁም ታታሪ እና ትጉህ እንደ ነበር ቤተሰቦቹ ለስላሳዋ ጋዜጠኛ ላቀረበችው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ አዳምጫለሁኝ።
#አሰቃቂው ሂደት።
ንገረው የእኛ አቤል በጎቹን በመጠበቅ ላይ ነበር። ጨካኞቹ የመንግሥት ኦነጋዊ ታጣቂወች ወደ ቀዬው ዘልቀው አቶ አወቀ የተባሉትን ነዋሪ "ፋኖ ነህ" ብለው ነፃ እርምጃ ይወስዱባቸዋል። #ቀይ ሽብር ማለት ነው። ንገረው ይህን ያያል።
ይገድሉኛል ብሎ ይሸሻል የሚወዳቸውን በጎቹን ትቶ ሸሸ። ቤቱ ይርቅበታል። እሱ ይሮጣል፣ ገዳዮቹ ይከተሉታል። ንገረው በአቅራቢያው ካለው ጎረቤት ቤት ገብቶ *ቆጥ ላይ ይሸሸጋል። የልብኑ ምት እሰበው።
ይህ አስጨናቂ ጊዜ ለብላቴናው ምን ያህል መርግ እንደሆነ እሰቡት። በተለይ ልጆች ያላችሁ። ብቻውን ነው። ወላጆቹን አልባ ጦርነት የተከፈተበት።
ልክ ቤተ እስራኤሎች ይሳደዱ እንደነበረው ነው የሆነው። በህይወት አለመኖሩ እንጂ ቢተርፍልን ኖሮ የአና ፍራንክ ታሪክ በባዕታችን ይደገም ነበር።
የቤተ - እስራኤል ልጆች እንደሚሳደዱት ነው የአማራ ልጆች እዬተሳደዱ ያሉት። ጭንቅላት ሳይሆን ህሊና ከኖረን። ጭንቅላትማ ድንቢጥም ወፍ አላት።
*ቆጥ ማለት ከፍ ብሎ እንደ ፎቅ ቤት ውስጥ የሚሠራ አልጋ ማለት ነው። መስክ ላይም እህል ሲደርስ ወፎችን ለመከላከል ይሰራል።
ጨካኞቹ የሄሮዶስ አብይ አህመድ አሊ #ፋሺስት ወታደሮች ከተሸሸገበት አውጥተው ግንባሩን፣ ብብቱን በጥይት እንዱ ጨርቅ ሰውነቱን በታተኩት። በድፍረት ገደሉት።
ይህን የሰሙ ቤተሰብ ተጣድፈው ሲደርሱ በኩራት "እኛ ነው የገደልነው፣ ምን ታመጣላችሁ፣ ብንፈልግ አንተንም እንገድልኃለን ብለው ዝተዋል።"
ካሉምንም ተጠያቂነት ሄደዋል። ለአካባቢው አስተዳደር ለማሳወቅ አጎቱ ቢጠይቁም ዕውቅና አልተሰጣቸውም።
ምን ዋስትና አለ? ባለቤት ለሌለው ህዝብ። ምን ዋስትና አለ ስልትም ጥበብም ላነሰው ዝብርቅርቅ የአማራ ዬፖለቲካ ሁኔታ። ምን ዋስትና ይኖራል ብትን አፈር ለተነፈገ ህዝብ?
መከራውም፣ ድንጋጤውም፣ ዕንባውም፣ ሰኔል እና ቹቻውም #አልጎረበጠን። ጥንቃቄ አልባ በምንለቀው ዲስኩር እንሆ ምንም የማያውቁ ንጹኃን፣ ለፍቶ አዳሪወች ዙሪያቸው በሰቀቀን ቲፍ አለ።
መኖራቸው በስጋት ጉም ተሸበበ። እያሉ አስተማማኝ የመኖር ዋስትና አጡ። መጠጊያ ተስፋ እንሆ እራቃቸው። እኔን አፈር ልብላ።
የውሻ ያህል የአማራ ደም የማንም ጉዳይ ሊሆን አልቻለም። ቢሆንማ ስንት ጥበብ፣ ስንት ጥንቃቄ፣ ስንት ስልት ተፈጥሮ ህዝባችን ከሞት ባዳን ነበር።
ይህ ታሪክ አንድ የፋክት መድብል ይወጣዋል።
ሰሞኑን በተፈላጊው ጊዜ አቶ ጃዋር መሐመድ ስትራቴጅካዊ ቃለ ምልልስ አድርጓል። እሱም የፖለቲካ ድርጅት አለው። ድምፁ ተናፍቆ ይሁን ጥሞ፣ ጥሞ ይሁን ሻክሮ በ21 ደቂቃ ውስጥ ከ300 ሺህ በላይ አድማጭ ነበረው። እኔ ሳደምጠው። አሁን ሚሊዮን ገብቷል።
ጥሞና፣ መጨመት ብዙ ነገር ያድናል። በብዙም ያተርፋል። ብልህነት ይህ ነው። መሪነትም ይህ ነው። ለዓላማው በጥንቃቄ መጓዝም ይህ ነው። ብዙ መስዋዕትነትን ይቀንሳል።
ለኢትዮጵያ ዝልዝል ፖለቲካ አንድ አዲስ የመማሪያ፣ መመሪያዊ ታሪክ ሰርቷል። "ለማድመጥ ጊዜ ይኑረኝ ብዬ ነው" አለ። እኔም የምለው ይህን ነበር።
ሰሚ ባገኝ ይሁሉ ቀውስ አይኖርም፣ ቢኖርም ዘግይቶ ስለሚመጣ በሃሳብ የተደራጁ ወጣቶች በረጋ መንፈስ ተስፋችን በቅጡ እያደራጁት፣ እዬመሩት አዲስ ምዕራፍ እዬሰጡት ስለነበር በቂ የመተንፈሻ ጊዜ ይኖራቸው ነበር። ዛሬ ጅምራቸው አይደለም ስለ ህይወታቸው መትረፍ ነው እያሰብን ያለነው።
ዕድልን በቅጡ አለማስተዳደር ትርፈ ቢስ ኪሳራ ነው። ኪሳራው የግል ቢሆን ምንም አልነበረም። እንዲህ የሚሊዮን ተስፋ ባይገበርበት። ብዙ ሰው እኮ የአንጀቱን ሃዘን መሸከም አቅቶት ታሟል። ረቂቅ ነው።
የእኛ አቤል ሰማዕቱን ንገረው አንድ እሱ ብቻ የተሰዋ እንዳይመስላችሁ፣ የዛ ቀበሌ ልጆችም፣ የአጎራባች ቀበሌ ልጆች በመንፈስ ሥነ - ልቦናቸው ተቀጥቅጧል። ለመቀጣጫም ነው እንዲህ የሚሠሩት። የአማራ ልጆች መኖርን እንዲፈሩት ማድረግ የኦነግ ዓይነተኛ ፖሊሲ ነው።
ለዚህ ተጠያቂው ሥርዓት ያጣው፣ አናርኪዝሙ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ፋክክር ያመጣው ጦስ ነው። ለገዳዮች፣ ለአሸባሪወች፣ መተዳደሪያው ቀውስ ለሆነው ለገዳ ሥርዓት አቅም ሰጡት። በይፋ ነው ቀይ ሽብር የተጀመረው።
የአማራ ህዝብ የጨመተ፣ የሰከነ፣ አብዝቶ የሰጠው፣ ፍፁም ቻይ፣ ፍፁም ታጋሽ፣ አርቆ አሳቢ ስለሆነ ብቻ ግፍ ተሸክሞ ምላሹን ሳይሰጥ በዝምታ ውስጥ ረግቷል።
ነገስ? አንድዬ ኤልሻዳይ አምላክ ይመልሰው። የአማራ ልጅ ቀጣይ ተስፋስ? ምን አለን? ማን አለን? አማኑኤል ይመልሰው።
#ፎቶው ከሪፖርቱ ላይ ስለወሰድኩት ጥራት ላይኖረው ይችላል። የእኛ አቤል ሰማዕቱ ንገረው አዲስ በቀይ የተከበብ ነው።
ለቤተሰቦቹ መጽናናትን እመኛለሁኝ። ሰማዕቱ ግን ማኒፌስቷችን ሊሆን ይገባል። ከፈቀዳችሁ።
እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
ኑሩልኝ። አሜን።
ደህና እደሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergite©Selassie
02/06/2022
መኖርህን ለማስከበር ዘመንን አድምጥ!
ትውልድ ይቀጥላል፣ ሥልጣንም ይሰወራል።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ