መጥኒ ለአንቺ ኢትዮጵያ።

 

መጥኒ ለአንቺ ኢትዮጵያ።
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"
ክብሮች እንዴት አደራችሁ? ልዕልት ኢትይጵያስ እንዴት ነሽ?
ስድብ፤ ክብርን መገሰስ፤ ማዋረድ ከዬት የመጣ መከራ ይሆን? ከሊቅ እስከ ደቂቅ የታረመ አንደበት #መነነ። ይህ አሳረኛ ትውልድ ተፈርዶበታል። ስድብን እንዲያጠና፤ በስድብ ሪከርድ እንዲሰብር ይፈለጋል። ስድብን ትውልዱ አጥንቶ ባለ መዳያም እንዲሆን። ለዛም እንዲተጋ። መዘለፍ፤ መቀርደድ እንደ መልካም ነገር አናባቢም ተነባቢም አስተርጓሚም ተተርኋሚም አይደለም። ስድብ ማዋረድ እራስን ይሸረሽራል። 
 
ከዚህም ባለፈ የቅኔ ያህል ስድብ ዘለፋ ክብር ተሰጥቶት አመሳጣሪም ያስፈለገው ይመስላል። እግዚኦ ነው። እራሱን በመሪነት ያስቀመጠ፤ ወይንም ያስቀመጠች ማንኛቸውም የስድብ የፊደል ገበታነትን መፍቀድ የተገባ አይመስለኝም። የትውልዱን የሞራል ግንባታ ያጫጫል። አማርኛ ቋንቋ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ለሆነው ማህበረሰብ ይሁን ላልሆነውም በስድብ፤ በዘለፋ የሚገኝ #ብቃትም #ላቂያነትም የለም። ኑሮም አያውቅም። ለትውልድ የሚሠራ ከሆነ የታረመ፦ ቁጥብ ያስተዋለ ሰብዕና ያስፈልጋል። በተለይ ወጣት ሆኖ ጊዜ ወደ መሪነት ካመጣው አላስፈላጊ ከሆኑ ከወጣትነት ሥነ - ምግባሩ ጋር መፋታት ይኖርበታል። ሊገራም ይገባል። "ቁመው የሰቀሉት ቁጭ ብሎ ……" እንዳይሆን። 
 
ቢያንስ በመከራ ውስጥ በፈተና ውስጥ ላለ ማህበረሰብ ጥላ፤ ጋሻ የሚሆን መንፈስ መከራው እራሱ ትህትናን ስለሚያጎናጽፈው እራሱን ዝቅ አድርጎ አቅሙን ማፋፋት ይገባል። የሰው ልጅ ክቡር ነው። ፈጣሪ አላህ አክብሮ ቀድሶ መርቆ ነው የፈጠረው። ማንም ይሁን ማን፤ የትኛውም ክፍለ ዓለም የሚኖር የአለም ዜጋ በሰውነቱ #ሊከበር ይገባል። በውነቱ ገበሬም መሆን ሊቃለል አይገባም። "በማን ላይ ቆመሽ እግዚርን ታሚያለሽ" ነው።
 
ገበሬ ስልጡን ነው። መሬትን አናግሮ አሳምኖ ልግሥናዋን በአግባቡ ተጠቅሞ ትንፋሽ የሚዘራ ባለሙያ ነው። ሲዘለፍ አደምጣለሁ። አለመማር ወንጀል አይደለም። በሌላ በኩል #ዕውነትን ደፍሮ መግለጥም ግድፈት አይደለም። በማንኛውም ሁኔታ፤ የትም ቦታ በሁሉም ጊዜ ዕውነት ዕውነት መሆኑን መቀበል ግድ ይላል። ለዕውነት ፕሮፖጋንዲስት አያስፈልገውም። ለዕውነት አጃቢ አይሻም። ዕውነት ቢደፈር የኢትዮጵያ ዕንባ ማበስ በተቻለ ነበር።
ለቀጣዩ ትውልድ ቢያንስ አክብሮትን፤ ደፋሩን ዕውነትን ለማውረስ እንትጋ። ቢያንስ #ስድብ #እንደ #አንድ #የፖለቲካ #ርዕይ አድርገን #ትውልዱን #ገደል #ለገደል አንምራ። አማርኛ ቋንቋ ዲታ ነው። ሙግትም፤ ማብራሪያም ቢያስፈልግ አማርኛችን ጉልበት አለው። በጣም የደረቀ ግን በስሎ በዝግታ የደረቀ ለማለት #ቃ አለልን። የልብ ሳቅን ለመግለጽ #ፏ አለ። ከተፈጠረው በላይ ተለጥጦ ለተከፈተ #ቧ፦ ከተለመደው ውጭ ለዘገዬ #ዳ ………
የአማርኛ ቋንቋ አቅም ሳያንሰው ስለምን #ዘለፋን ቅደመኝ እንደሚባል አይገባኝም።
 
 እንዲገባኝም አልሻም። ስድብ፤ ዘለፋ ገባኝ አልገባኝ ስድብ ምን አፍርቶ ምን አስብሎ አይቼ? ዘለፋ፤ ስድብ #መኃን #የነጠፋ ናቸው። ከፍግም በታች ነው ዘለፋ እና ስድብ።
ዘለፋ እና ስድብ የፖለቲካ አጋር ለማድረግ ሲታሰብ እንደ መርኽም ሲታይ ይገርመኛል። ትውልዱ ይህንንም ውረስ እዬተባለ ነው። ተው። ዘለፋ ስድብ የዕውቀት ዘርፍ አይደለም። ዘለፋ ስድብ ቀለመ ቢስ አልቦሽ ናቸው።
 
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
03/06/2024
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።