ከአማራ ክልል ውጭ የሚኖሩ አዲስ አበባን ጨምሮ ስቃያቸው ሊወከል ይገባል። #አንሰበርም #አንሰብርም። #አማራነት #ይከበር። #አማራነትም #ያክብር።
ውዶች የቤታችን ታዳሚወች
ውቦች እንዴት አደራችሁ?
ግርማ ሌሊቱ እንዴት ነበር። ተመስገን ነግቶ ተገናኘን።
"የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሄር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ" ትንቢተ ዘካርያስ ነው እንዲህ የሚለን ……
" የሠራዊት ጌታ እግዚአብሄር እንዲህ ይላል፦
ስለ ጽዮን ታላቅ ቅናት ቀንቻለሁ።
በታላቅም ቁጣ ስለ እርሷ ቀንቻለሁ።"
(ትንቢተ ዘካርያስ ምዕራፍ ፰ ቁጥር ከ፩ - ፫)
ከአማራ ክልል ውጪ የሚኖሩ የአማራ ልጆች ሚሊዮን ናቸው። ሚሊዮኖች የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚ፦ የማህበራዊ ኑሮ፦ የሃይማኖት ዕውቅና ያለው ውክልና የላቸውም። ኑሯቸው #ግዞት ነው ማለት ይቻላል። በአገራቸው ውስጥ 33 ዓመት ተሰደው ኑረዋል። የትኛውንም የግፍ ጽዋ ስንቅ ኑሯቸው፤ አሳርን መገፋትን መገለልን መጠለያቸው አድርገው። በራሳቸው የፊደል ገበታ አይማሩም። ልማር ቢሉም እንደ ወንጀል ስለሚታይ ይቀጣሉ። ይገለላሉ። ከባዕታቸው በግፍ ይፈናቀላሉ፤ ይሰወራሉ፤ ይገደላሉም። #ሁነኛ የላቸውም። በኢትዮጵያ ተፈጠሩባት ግን መብት አልባ ግዴታን ብቻ በጫና ሲኮመኮሙ ኖሩባት። ይመርጣሉ ግን አይመረጡም። በአቅማቸው ያሉበትን በዓት ተግተው ያለማሉ፤ ግን ይቀጡበታል እንጂ አይሸለሙበትም።
ለዚህ ነው ዛሬ የአማራ ወጣቶች እኛ ታላላቆቻቸው በዕድሜውም፤ በተመክሮውም በመቆዬታችን #ለዘብ አድርገን በምናያቸው ክስተቶ የሚበሳጩብን። ይገባቸዋል። አንድም ወጣትነታቸው ያስገድዳቸዋል። ሁለትም መከራው የገዘፈ እና የሰው ልጅ ከሚሸከመው በላይ ሆነ። ስለዚህ ቢበሳጩ ቢከፋቸው ሊሰማን አይገባም።
የሆነ ሆኖ በማናቸውም ሁኔታ ነገረ አማራ ሲነሳ ሽዋ፤ ጎጃም፤ ጎንደር ወሎ ሲባል እሰማለሁ። አዲስ አበባ 50+ አማራ ነው። ወኪል ያስፈልጋዋል። በኦሮምያ፤ በቤንሻንጉል ጉምዝ፤ በሱማሌ፤ በድሬ፤ በማህል ኢትዮጵያ፤ በደቡብ፤ በሲዳማ፤ በአፋር፥ በትግራይ በሲዳማ ያሉ የአማራ ልጆች በትልሞች፤ በተሳትፎ ውክልና ሊታሰቡ ይገባል። መከራው ጠንቶ የኖረ በእነሱ ላይ ሲሆን በተሳትፎ፤ በውክልና በዘመነ ኢህአዲግም፤ በዘመነ አብይዝም ውክልናው #ልሙጥ ሆኖ በራሱ በአማራው የማንነት እና የህልውና ተጋድሎም ዬተገለሉ ናቸው። ስለሆነም ይህ ግድፈት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ታርሞ ድምፃቸው የሚሆን ወኪል ሊኖራቸው ይገባል።
በአራቱም መዓዘን በተወጠረው በኢትዮጵያ በዓት እንደማይቻል አውቃለሁ። እንኳንስ ከክልሉ ውጪ ተቆርምሞ በተሰጠውም መቆሚያ መቀመጫ አጥቶ ህዝባችን በድሮን እና በባሩድ ሲታሸድ ነው የባጀው። ዛሬም አላባራም። ነገር ግን ውጪ አገር ላይ ጥንስሱ ሊጀመር ዕውን ሆኖም ሊተገበር ይገባል።
በመልካም ነገርም ቢሆን ምስጋና ቢኖር፤ ሽልማት ቢኖር፤ የአብሮነት ሴሪሞኒ ቢሆን ጎጃም፤ ጎንደር፤ ወሎ ሽዋ ብቻ ሊባል አይገባም። ከክልሉ ውጪ ያለ አማራወች ድሬ እና አዲስን ጨምሮ ውክልና ሊኖራቸው ይገባል። ስቃዩን የተሸከሙ 33 ዓመት እነሱ ውክልና ግን የለም። ይህ ከፍ ያለ #ግድፈት ስለሆነ ሊስተካከል ይገባል።
ከአማራ ክልል ውጪ ያሉ አማራወችን በማሰባሰብ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ (ካፒቴን) በቲም ገዱ ዘመን ሞካክሮት ነበር። ያ ቅምሻ ሆኖ ነው የቀረው። ሙከራው እንዳይደረጅ ዬአብይዝም ቀውስ አነቀው። ቢያንስ ውጭ አገር በሚደረጉ ማናቸውም ኢቤንቶች ከክልሉ ውጪ የሚኖሩ አማራወችን የሚወክል ወኪል ማደራጀት እና ህጋዊ ዕውቅና መስጠት ያስፈልጋል። መሪነት #አሰባሳቢነት እንጂ አንዱን ጥሎ አንዱን አንጠልጥሎ ሊሆን አይገባም።
እንዲያውም አሁን አሁን የማዬው ለትልቅ የኃላፊነት እርከን መንፈሴ ያጫቸው፤ ደፍሬም ሌት ተቀን ሞግቼ ለሚያደምጡኝ አሳውቄም አንቱታን የተጎናፀፋት መንደር ፍለጋ ላይ ሆነው አይቻቸዋለሁ። በውነቱ ውስጤም ቆሳስሏል። ሲሆን ሲሆን ከፍ ያለውን ፓና አፍሪካኒዝም ላይ መሆን ሲገባ ከአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎም ነጥሎ ለተፈጠሩበት ባዕት ብቻ ለመሆን መትጋት? የክብሩ ባላቤት እኮ መላ የአማራ ህዝብ ነበር። በእሱ ስም ነው ማዕረጉም፤ ሞገሱም የተገኜው። ሹመትም ሽልማትም ቢሆን በገፍ በተሰዋው የአማራ ሰማዕታትት ትክሻ ነው።
#ሆኖ ከክልልሉ ውጪ የሚኖሩ አማራወች ባሊህ ባይ ያስፈልጋቸዋል። ቁስለቱ ሊሰማን ይገባል።
በዘመነ ህወሃት የተጨፈጨፋት እኮ እነሱ ናቸው። ደራ ላይ እራሱን በእሳት አቃጥሎ ሰማዕትነትን የተቀበለ #መምህራችን ነበር። ቢረሳ ቢረሳ እሱ ይረሳን? የባሰውን በርደን ስለተሸከሙ እነሱ #አማራ #ነኝ ለማለትም ቅንጣት ጊዜ አያጠፋም። ዘመናይ አይደሉም። ቅልጣንም ትውር አይልባቸውም። ሲታገሉም ከውስጣቸው፤ ከልባቸው #በድንግልና ነው። መታመንንም ታማኝነትንም አያስከፋም። ጠንካሮንም ናቸው። ለምን? መከራ ጠጥተው፤ መከራ ተመግበው፤ መከራን ተጎናጽፈው ስለኖሩ። ለዛውም ከሱናሜው ከተረፋ እንጂ ብቅ ባሉ ቁጥር እዬታነቁ አሳራቸውን ሲዩ ነው የኖሩት። አፓርታይድ ትናንት አልነበረም፤ ዛሬም የለም የሚሉ ፈጣጣወች አሉ። አለ እንጂ። አንድ ሰው የፖለቲካ ውክልና ካልተሰጠው እኮ አፓርታይድ በዛ አገር ውስጥ አለ ማለት ነው።
ትግሉን ጥልቅ እና ሁለገብ ዕይታን ያገናዘበ የሰከነ፦ የበሰለ ሊያደርገው የሚገባም የመለሲዝም ዶግማ አማራ ላይ ጭካኔውን በፐርሰንት ማውጣት አይቻልም። ቢያንስ መለሲዝም ድርጅቱ ስለሚፈርስ አማራ የለም ካለ አማራ አለ ብሎ ያምን ይሞግትም ነበር ሙሁራንን። ማንኛውም ነፃ አውጪ "አማራ ጨቆነኝ" ብሎ ስለሚደራጅ ማለቴ ነው። የለም አማራ ካለ ድርጅቱ ህልው አይሆንም።
ሌላው ስውሩ መከራ አማራ አለ ብለው የማያምኑ ሊቃናት መኖራቸው ነው። ይህ #የመስፍኒዝም ተከታይ ድርጅቶች ሁሉ ይህን እንደ ዕውነት አድርገው ይወስዳሉ። ሰሞኑን አወያይ ቤቲ ይህንን አስረግጣ ስትናገር ሰምቻለሁ። በመስፍኒዝም ዶክትሪን ያሉ የተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶችም በዚህ #ሰላቢ ዕሳቤ የተረቱ ናቸው። እንደ እኔ ዕይታ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አማራ አለ ብለው ያምናሉ ብዬ አላስብም። ማህል ላይ እዬወላወሉ እንዳሉ ይሰማኛል። የደንቢ ደሎ የተሰወሩ ተማሪወችን አስመልክተው "ተማሪ ብሄር" የለውም ያሉትም ከዚህ ዕሳቤ ተነስተው ነው። ይህ በንግግራቸውም፤ በሹመት አፈፃፀማቸው ያዬሁት ዕውነት ነው። በአመዛኙ የሥልጣን ውክልና የሚሰጡት #ውህድ ማንነት ላላቸው አማራወች ነው። በዚህ ጉዳይም እሚያሳስበኝ ስለለ እመለስበታለሁ።
የሆነ ሆኖ ሽዋ፤ ጎጃም፤ ወሉ ጎንደር ብላችሁ በምታዋቅሩት ሁሉ ቢያንስ በእናንተ ህሊና ከክልሉ ውጪ ያሉ አማራወችን የማሰብ፤ የውክልና አክሰሱን የመፍጠር፤ የሚዲያ ዕድልም የማመቻቸት ወሳኝ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ አምናለሁ በፍፁም ልቤ እና ህሊናዬ። እንዲያውም ለእኔ ከእናታቸው ማህፀን ጀምሮ አሳራቸውን ላዩ ወገኖቼ የበለጠ ጅራፋ ይሰማኛል። የእነሱ መጠለያ ተገፋችም// ተገለለችም ኢትዮጵያ የሚለው ታላቅ ረቂቅ መንፈሳዊ ፀጋ እና አላህ እግዚአብሄር ብቻ ናቸው። እኛ እንኳን ተስፋ ልንሆናቸው አልቻልንም።
በጥቅሉ የአማራ ፖለቲካ ስንቁ ርጋታ፤ ቀኖናው ሁልአቀፍ፤ ዶግማው መከራው ሊሆን ይገባል። ጉዞው ማስተዋል የዘለቀው፤ በፍፁም ታጋሽነት እና አብሮነት የለመለመ ዊዝደም መሆን አለበት። ጉዞው ደራሽ ነገሮች የማያስበረግጉት፤ ደራሽ ጉዳዮችን ለሪፈረንስ ብቻ ይዞ ሩቅ ዓላማ እና ግብን ለማሳካት ብልህነት በብስልት አዋህዶ ሊሆን ይገባል። ለአማራ የትግል መንፈስ ግልፍተኝነት፤ ለብ ለብ፤ ላይላዩን፤ ገረጭራጫነት፤ አግላይነት፤ አይበጁትም። ፈጽሞ። ህሊናውንም መንፈሱንም ሰፊ ማድረግ ይኖርበታል። በቃላት ጢባጢቦሽ የማይርድ ተቋም ያስፈልገዋል። ከሁሉ በላይ የተጋድሎው መንፈስ ተናዳፊ ሳይሆን ተግባቢ እና ማግኔታዊ ሊሆን ይገባዋል። ትግሉ የዱላ ቅብብሎሽ ወይንም የጫጉላ ሽርሽር አይደለምና።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ነገ በሌላ ዘለግ ባለ ጉዳይ እንገኛለን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
06/06/2024
#አንሰበርም።#አንሰብርምም።
#አማራነት #ይከበር። #አማራነት #ያክብርም።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ