እኔ እራሴ በዚህ ፁሁፍ ተደምሜያለሁ፨ የደጉን አማራ ሁለንትናዊ አቅም ማኔጅ የሚያደርግ መሪ ነው የጠፋው። ሙሴ አልባ ተጋድሎ ሰማዕትነት ብቻ።

 

የደጉን አማራ ሁለንትናዊ አቅም ማኔጅ የሚያደርግ መሪ ነው የጠፋው። ሙሴ አልባ ተጋድሎ ሰማዕትነት ብቻ።
"እንደ ጠቢብ የሆነ ሰው ማን ነው?"
(መክብብ ፰ ቁጥር ፩)

 
 
እንዴት አደራችሁልኝ? አላችሁልኝ?
የአማራን አቅም የሚሻማ በሽ ነው። በአማራ አቅም የሚጎመጅ በሽ ነው። ዬአማራን አቅም የሚዘርፍ በሽ ነው። የአማራን አቅም ለራሱ ፍላጎት ኢንቤስት ለማድረግ የሚወራከብ ወዘተረፈ ነው።
የኦሮሞ አቅም፣ የተጋሩ አቅም፣ የሱማሌ አቅም፣ የጋንቤላ አቅም፣ የደቡብ አቅም፣ የአፋር አቅም፣ የቤንሻንጉል አቅም ወዘተ በራሱ ጊዜ ካለ ማንም አዋኪ እና አዋካቢ በልጆቹ ይመራል፣ በራሱ ልጆች ይደራጃል፣ ይተዳደራል። ጠብ የምትል የአቅም ነቁጥ የለም። ጠበል።
የአማራ አቅም ግን የሌላው ሳንጃ ተሸከሚ ነው። ለሌላው አንጋች እና አጋች እና አሳጋጅ ጥቅም ብቻ ነው።
የአማራ ልጅ ሰኞ ይፀነሳል፣ ማክሰኞ ይወለዳል። እሮቡ ትምህርት ቤት ይሄዳል። ሃሙስ ለፈተና ይቀመጣል። አርብ ዩንቨርስቲ ይገባል። ዕሁድ ይመረቃል። ሰኞ ለሞት ይሰናዳል። የአማራ ልጅ ሱቅ ከምንገዛው ዕቃ እንኳን ያነሰ ዕውቅና አይሰጠውም።
የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የአማራን አቅም ሲያጩ፣ ሲሟጥጡ ባላሳደጉት ልጅ፣ እንዲት ፔና ያልገዛ፣ በባለንብረትነት ባለቤት ሆነው ልባቸውን ነፍተው የፖለቲካ ድርጅት ይፈጥራሉ። በአንድ ቀን ደርሶ እሸት ቅመሱ የሚል ማገዶ ህዝብ አላ። አማራ ደግዬ፣ ቅንዬ።
በተዥጎረጎረው ስማቸው ልክ ፔስቲ ያላወጡበትን ልጅ አገልጋያቸው አስደርገው ማገዶ ያስደርጋሉ። ልጁ የተጎዳበት ፖለቲከኛ አላውቅም።
የአማራ ልጅ እኔ ገጠሩን በአደራጅነቴ ዘመን በእግሬ ኳትኜ፣ አቀበት ቁልቁለት ወጥቼ ወርጄ፣ ወንዝ ተሻግሬ ሙላትን ተጋፍጬ፣ ሰኔሏ ላይ መደብ ላይ ተኝቼ አውቀዋለሁኝ ጓዳውን፣ አሳሩን፣ መከራውን።
ሌሊት ለብሷት የሚያድራትን ለብሶ ነው ቀን የሚውለው። ዝናብ ከመታበት ማታ ዘረጋግተን በእጃችን ይዘን ልብሱን እናደርቀዋለን። ለብሶት የሚተኛ ስሌለው።
ተማሪ ከሆነ በወይራ፣ በግራር፣ በአባሎ እንጨት ብርሃን የትምህርት ቤት ሥራውን ይሠራል። ያጠናል። ያን ለዘዝ ያለ እራፊውን ተከናንቦ። በማግስቱ እሩቅ በእግሩ ተጉዞ አንጀቱን አስሮ ይማራል።
በዛ ጭንቅ ተወልዶ አድጎ፣ ተርቦ ተጠምቶ፣ #የኢትዮጵያ #ፖለቲካ #ሊኳንዳ ቤቱ የሚቋቋመው በአማራ ልጅ ነው። ይህ ዕውነት ለ50 ዓመት ተሠራበት።
በተለያዩ አዳዲስ ታጋዮች #በመሰለብ። በዬዘመኑ የመራራው ስንብት የቅንጅት መንፈስ መጣ ይባልለታል ለአማራ ንቅለት። ዛሬም ቀጥሏል።
የአማራ ልጅ የእኔ የሚለው አቅም የለውም። በአቅሙ አያዝም። ይቀራመቱታል። ለአንድ ልጅ እድገት አንድ ኪሎ እህል ያዋጣ ያለ ይመስል።
አቅሙ የሌሎች ንግሥና፣ የማያውቃቸው ልዕልና፣ የማያዝኑለት ዕውቅና ማገዶ ነው። ለምን? አማራ መሪ አግኝቶ ስለማያውቅ #የአጥር ወይን፣ የአጥር ኢንጆሪን ስለሆነ አላፊ አግዳሚው እዬሸመጠጠ #ያራግፈዋል። ይመለምለዋል። ለመልማዮችም የግንባር ሥጋ ያደርገዋል።
ለአማራ ህዝብ መከራ መፍትሄም፣ መድህንም ሊሆን የሚችል አንድም የተደራጀ አለን የምለው የፖለቲካ ፓወር ያለው፣ ሞጋች ጎዳና አይታዬኝም አሁንም። ሁልጊዜ ሽሚያው የአማራን አቅም #ለቅምጥ ፍላጎት ኢንቤስት ስለማድረግ ነው የሚመከረው፣ የሚዘከረው።
አያደራጁትም፣ ወጥተው ወርደው የበላውን በልተው ችግሩን አይጋሩለትም። የመፍትሄ ጎዳና አይቀይሱለትም። እህሳ? እሱ እራሱ ተገብሮ በሚሰበስበው አቅም በኮፒ ራይት ሲቧከሱ እሱ ለተጨማሪ ውጪ ነፍስ፣ ግቢ ነፍስ አሳሩን ያያል። ጥርስ ውስጥ ይገባል። በማያውቀው ነገር ሰማዕትነትን ይቀበላል።
የአማራ ህዝብ መከፋቱን፣ እራህብ ጥማቱን፣ ጉስቁልናውን ችሎ እንኳን ሰላሙን ነሱት። አቅሙን ፍለጋ በሚደረገው #የእርስ በእርስ የፖለቲካ ድርጅቶች ፋክክር ልጆቹ ወጥተው መግባት ተሳናቸው። ለዚህ #ተጠያቂነትም#ኃላፊነትም የሚወስድ አንድስም እንኳን የለም። ማን ተፈርቶ? የአማራ ደም የውሻ ደም ነው።
ይቅርታ የሚጠይቅም ዬለም። ሁሉም ብፁዑ ነው። ሁሉም ከሰማዬ ሰማያት የወረደ ቤተ - መቅደስ ነው። ሁሉም አይከሰስም፣ አይወቀስም።
የአራተኛ ክፍል ተማሪ፣ የ13 ዓመት ህፃን ልንገረው አዲስ ተሳዶ በመንግሥት ወታደር ተቀጥቅጦ በባሩድ ሲገደል መነሻ ምክንያቱ ላይ ምንም ጥናት አይደረገም። አጥፊውም ጠፊውም ተወቃሽ ነው።
የአማራን አቅም በመሻማት ውስጥ ለሚመጣ ቀውስ፣ ለሚታዬው አናርኪዝም ተጠያቂው ማን ነው? ለዚህ መልስ ለመስጠት በሰከነ፣ በረጋ ሁኔታ በልባምነት ዜሮ ላይ ቆሞ ዕውነትን መፈለግ ይገባል።
አጥፊው ከጠፊው በላይ ወቃሽ ነው። አጥፊው ከጠፊው በላይ ቅዱስ ነኝ ይላል። በዜት ተገብቶ ስህተቱ ይታረም?
የሰኔ 15/2011 መከራ እንዳይደገም፣ አቅማችን እንዳይባክን፣ አቅማችን ተጠቂ እንዳይሆን፣ አቅማችን ጎራ ለይቶ እርስ በእርሱ እንዳይፋለም፣ አላስፈላጊ ቅራኔ ውስጥ አቅማችን እንዳይቀረቀር፣ #ተስፋችን #እንዳይደርቅ፣ ራዕያችን እንዳይጠወልግ፣ ምኞታችን ጉዞው እንዳይስተጓጎል ማኔጅ ለማድረግ በውስጡ የለንም። አብሰንት።
አዲስ ስህተት በአዲስ በርዥን መፈፀም ሰውኛ ነው። በዛው መንገድ ተጉዘህ አዲስ ጉስቁልና፣ አዲስ መታነቅ፣ አዲስ የጉዞ መጓጎል እንዴት ልትፈጥር ትችላለህ? ዕብንነት።
አያያዙን ሳዬው #የማስተዋል #ተፈጥሮ #የዘለለን ይመስለኛል። ስለሆነም ለቅሷችን ይቀጥላል፣ ፍሬ አልቦሽ መባተላችን ይቀጥላል፣ #አልቦሽ ቀኖቻችንም እያሾፋብን ይደረደሩልናል።
ለምን? የአማራን ትንታግ አቅም ለአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ብቻ የሚመግብ ተፈሪ ማንነት መፍጠር አልቻልንም።
ይህን ተፈሪ ማንነት የሚመራ ሙሴም አላገኜነም። ያ ቢሆን አቅማችን እንዲህ ያገኜ እዬዘረፈ፣ የህዝባችን ተስፋ መንገድ ላይ ተጨንግፎ ወይንም ሰላላ መላላ ሆኖ ባልቀረ ነበር።
የአማራ አቅም #መንፈሱ #ኃያል ነው። ግን ልጆቹ ከእቅፍ እዬወጡ የባሩድ፣ የገጀራ፣ የገጀሞ፣ የድንጋይ፣ የዲሽቃ፣ የእሳት፣ የመትረዬስ እራት ሲሆኑ ማዳን አልቻለም።
እንደ አማራ ማሰብ ማለት በዚህ ዝብርቅርቅ፣ አንዱን ይዞ ሌላውን በመጣል አይደለም። በጥቃት ላይ ሌላ ጥቃት በመደረብም አይደለም። ተጨማሪ አዳዲስ ኃላፊነት በአማራ ህዝብ ላይ በማሸከም፣ በማንዶልዶል አይደለም።
በማሸነፍ ላይ ማሸነፍ፣ በማስበል ላይ ማስበል፣ በማብቀል ላይ ማጽደቅ ቢኖር ነበር። ኪሳራ ማሸነፍ አይደለም።
በጠራ መስመር፣ በጠራ የኃይል አሰላለፍ አማራን እንደ ህዝብ ማዳን ቀርቶ በነፍስ ወከፍ እራስን ለማዳን እንኳን አልተቻለም።
ቢቻልማ ኖሮ በሁለት ሳምንት ብቻ በባዕቱ ከ5000 ሺህ በላይ ለካቴና፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ታፋኞች፣ ቁጥራቸው በውል ያልተመዘገቡ ሰማዕታትን ታቅፈን ኤሉሄ ባላልን ነበር።
በዬዕለቱ በሚፈለፈል አዳዲስ ቅንጅት በለው ድርጅት ምክንያት የአማራ ልጅ ሰብሳቢ አጥቶ፣ መሪ አጥቶ፣ ማስተዋል በነሳው የኢትዮጵያ ፖለቲካ የቀራንዮ፣ የቀረመት፣ የቄራ ሰለባ ሆነ።
ከአማራ ውጪ አንድም ዜጋ ካለ አግባብ ህይወቱ አያልፍም። ቅኑ፣ አማኙ አማራ ግን የመጣ የሄደውን ሲያስተናግድ በእሱ ግብር ሌላው መኖሩን ያጣጥምበታል።
የአማራን አቅም የራሱ ብቸኛ ማዕከል ለማድረግም የሚታትረው ከሊቅ እስከ ደቂቅ ነው። ይህ ሁሉ መራኮት ምክንያቱ አማራ አቅሙን አማክሎ በአንድ ሴንትራል እዝ አማራ በሚል ኃይለ መንፈስ የሚመራለት መሪ አለማግኘቱ ነው። ገሩ አማራ አቅሙን ለአቅሙ ባለመመገቡ የሌላ ገበታ ማሞቂያ፣ መዳሪያ መኳኳያ ሆነ።
የአማራን ጉዳይን እንመራለን የሚሉ ደራሽ ታጋዮች የአማራ ህዝብ ለጣምራ ተልዕኮ እንዲተጋ ኃላፊነትን ከማነባበር፣ ከመጫን እራሱን እንዲያድን ቢያበረታቱት፣ ቢያደራጁት ይመረጣል። ትናት ለኮረጆ ዕውቅና እፍ ግብ ሲሉ ያዬናቸው የሚዲያ ደንበኛ ሰብዕናወች።
የአማራን አቅም #እያዘረፋ ለተጨማሪ መከራ እና ሰቆቃ የአብርኃም በግ ከሚያደርጉት፣ ከሚያስደረጉት። "እራስ ሳይጠና ጉተና ነው" እማዬው ነገር።
እድገት ማለት ለእኔ በጀመርከው መስመር ስኬትን ማስመዝገብ መቻል ነው። ስኬት አልቦች ዕድገት መመኘት የአልቦሽ ድርድር ነው። ቤት ሳይፀዳ የጓሮ አበባ ፋይዳ ቢስ ነው ለእኔ። የመምራት አቅም በስኬት ይለካል።
#ቅኔው ጎጃም አማራነቱን በሥርዓት ስላስተዳደረ የተወካዮች ሸንጎ ላይ ባለ አምስት ወንበር ሆኗል። ያ ድል የተገኜው የተቋም አይደለም። የተቋም አቅም ቢሆን ሌላ ቦታም ተመሳሳይ ውጤት ይገኝ ነበር።
#ዋርካው የጎጃም ዬአማራ ህዝብ እራሱን መርቶ፣ እራሱን በራሱ አደራጅቶ፣ ወስኖ ያስገኘው በረከት ነው። ጥበብ ነው። ልቅና ነው። ስኬት ማለትም ይህ ነው። ልጆቹም ጥርት ያለ አቋም ያላቸው፣ ጠፈፍ ያሉ ናቸው። ይህን አቅሙን ዬሽሚያ ማራቶን ነው እኔ በወርኃ አስተርዬ በ2014 እኢአ ያዬሁት ትርኢት።
የሆነ ሆኖ የአማራ ህዝብ እራሱን ለማዳን ያለው ብቸኛ መንገድ አቅሙን ለአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ በቅጡ አደራጅቶ፣ በማስተዋል መምራት ይኖርበታል። ይህ ከዬትኛውም አካል ጋር ውል ሊፈጽምበት የሚገባ አመክንዮ ሊሆን ይገባል።
ከቤተ - ተጋሩ፣ ከቤተ - ኦሮሞ፣ ከቤተ - አፋር፣ ከቤተ - ሱማሌ፣ ከቤቴ - ጋንቤላ፣ ከቤተ - ጉምዝ ሊማር ይገባል። የሱማሌ ካቢኔ ትንታጎች እንደምን በጥራት እንደተደራጁ በጥልቀት ማጥናት ነው። የተስፋ አበባ ነው ያሰበሉት።
የአማራ ህዝብ ቢያንስ እስከ ዛሬ አላግባብ ያፈሰሰው አቅም ምን ያህል ቤቱን ከመቃብርነት እንዳላዳነው በእርጋታ፣ ጥሞና ወስዶ መርምሮ አቋም ሊወስድበት ይገባል።
እራስን - መምራት፣ እራስን - ማስተዳደር፣ የራስ ጌታ - እራስ መሆን። #የራስ #እንደራሴነት የሰው ልጅ ሲፈጠር የተሰጠው ፀጋ ነው።
ስለሆነም የአማራ ህዝብ ፀጋውን ሳያባክን #እራስ ጠቀም የማድረግ ኃላፊነት እና ግዴታ ይኖርበታል። ሚስጢሩ ድልን እንዲሰንቅ የማድረግ ብልህነትን ፊደል መቁጠር ይጀመር።
ይህን ሲያደርግ አይደለም አገር በቀል ድርጅት የውጩም ያከብሩታል፣ ዕውቅና ይሰጡታል፣ አጀንዳቸው ይሆናል። ተፈላጊም ይሆናል። "ልብ ያለው ሸብ" ይላሉ ጎንደሬወች ሲቃኙ። "ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋምን" ያክላሉ ቅኔውን።
የአማራ ህዝብ መልሶ መላልሶ በወደቀበት እረግረግ መዛገጥ የለበትም። ሞቱን፣ ጉዳቱን የሚጠግን፣ የሚክስ እንጂ። #ሙትልኝማ የሁሉም የአቅሙ ሟጣጮች ጎዳና፣ ቅዬሳ እና ሎጓቸውም ነው።
እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
02/06/2022
የመምራት አቅም #በስኬት ይለካል።
No insights to show

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።