ሃሳብ መኖርን ያበጄ የሰማይ ፀጋ ነው። ሃሳብን ማደራጀት ከዕለት መኖር ይነሳል። የሰው ልጅ ሚስጢር ነውና። እኛን እንሁን። የአላዛሯ ኢትዮጵያ ልጆች በሚስጥራችን ልክ እንሁን። ልመና።
ሃሳብ መኖርን ያበጄ የሰማይ ፀጋ ነው። ሃሳብን ማደራጀት ከዕለት መኖር ይነሳል። የሰው ልጅ ሚስጢር ነውና።
እኛን እንሁን።
የአላዛሯ ኢትዮጵያ ልጆች በሚስጥራችን ልክ እንሁን።
ልመና።
"እግዚአብሄር በአንድም በሌላም
ይናገራል ሰው ግን አያስተውለውም።"
እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ ስለምን አምላኳን ፈጣሪዋን "ከሰይጣን ጋር ታረቅ ብላ ሞገተች?" ይህ ጥሪያዋ ገድሏን ካነበብኩ ጊዜ ጀምሮ ይጠራኛል። አላዛሯ ኢትዮጵያ ውስጧ እራስ እግሩ ዕንቁ። ግን አፈሰስነው።
ተቋም ሲፈጠር፤ ወይንም የተፈጠረ ተቋምን ለመምራት #የሃሳብ #ጥራት እና #ብቃት ይጠይቃል። ለመኖሩ ሃሳብ የሌለው ማለቴ ሃሳቡ ሊኖር ይችላል ግን ያልተደራጄ፤ አዋኪ፤ #ገርባባ፤ ተርገብጋቢ፤ #ቅጽበታዊ፤ የሚያረገርግ፤ ተጣዳፊ፤ ተጣጅ፤ አማሽ ከሆነ ባክኖ ይቀራል። በመኖር ውስጥ ዙሪያ ገብ ፈተናወችን ለማለፍ ስለሚያዳግተው። ተሸናፊም ይሆናል።
የኢትዮጵያ ተቋማት የማይፀኑትም ጎርፍ ላይ ይነሳሉ፦ ማዕበል ሲመጣ መቋቋም ስለሚሳናቸው ምራቅ ይሆናሉ። ወይንም የሳሙና አረፋ።
አስቦ የሚነሳ መኖር ግን ከራሱ አልፎ የሚሊዮኖች #መዳኛ መሠረት ይሆናል። በብዙ ማይል ርቀት ውስጥ ሆነን ያ የተደራጀ ሃሳብ ይዞ የተነሳ ሰብ ዕይታ የታመመውን፤ የተንገላታውን፤ መተንፈሻ፦ መፈናፈኛ ያጣውን መንፈሳችን ይፈውሰዋል። #ያጽናናዋል። #አይዟችሁ ይለናል።
የሰው ልጅ #ህሊና በምግብ እና #በመጠጥ ብቻ አይኖርም። የሰው ህሊና #በጥሩ መንፈስ መኖርን ይሻል። ይመኛል። ይፈልጋል። በፈለገ ርቀት ይሆን ተመሳሳይ መመሰጥ ያላቸው ሰብዕናወች ፍላጎታቸውን ሲያገኙ ውስጣቸውን ይሰጣሉ። #ሚስጢራቸውን ያጋራሉ።
የጨመቱም ቢሆኑ "በይበቃኛል" የሚኖሩ ቢሆኑም። አምሳያቸውን ሲያገኙ ካለ ምንም የዕድሜ፤ የፆታ፤ የዕውቀት ደረጃ፤ የሃይማኖት፤ የቀለም ልዩነት፦ ወዘተ መስመሩ ይዘረጋል። ታውቃላችሁ ቤተሰቦቻቸው እንኳን ሳያውቋቸው የሚኖሩ ልጆች እንደሚኖሩ። በምን ቋንቋ ይግባቡ?
የሰው ልጅ ሲፈጠር #ለሚስጢር ነው። ሰው በራሱ #ሚስጢር ነው። እስቲ አፈጣጠሩን እንሰበው። ረቂቅ እኮ ነው። በመታደላችን ውስጥ ህግ ባንተላለፍ ከደስታ በላይ ሐሤት ስንቃችን በሆነ።
በሐሤት እና በደስታ መሃል ልዩነት አለ ሁልጊዜ እላለሁኝ። ሐሤት ቋሚ እና ዘላቂ መንፈሳዊ እና ገኃዱ ዓለምን የሚያገናኝ። ደስታ ግን ጊዜዊ የገኃዱ ዓለም ክስተት ብቻ ነው ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ ሰው በተፈጥሮው ልክ ቢሆን ሐሤት መዳፋ ላይ በሆነ ነበር። ስለ ደስታ ካነሳሁ ዘንድም አበክሬ ደጋግሜ እምነግራችሁ ደስታችሁን መጥኑ። ለምን?
1) ሌላ ደስታ ሲጨመር መደርደሪያ እንዳታጡ።
2) ደስታችሁን የሚቀናቀን ክስተት ሲፈጠር ተስፋ ቆራጭ ሆናችሁ እንዳትታመሙ።
3) እግዚያብሄር አላህ ልክ ካለፋችሁ ስለሚከፋ ምርቃታችሁን እንዳያነሳ።
ወደ ቀደመው እንደ አበው።
በተለምዶ ኮከቤ ገጠመ ሲባል ትሰማላችሁ አይደል። የውስጥ መገናኜት #ቅኔ ነው። ዛሬ #መሐሌት ላይ የተገኜሁ ያህል ተሰማኝ። መልካም ሰወች #የብሥራት #ዜናወች ናቸው። መልካም #ዜና ጋር ቆዬሁኝ። መልካም ዜና ለእኔ #ትውልድን #በማዳን #ተግባር ላይ #መትጋት ነው። እነኝህ ለእኛ #ሽልማቶቻችን ናቸው። እነኝህ ለእኛ #ፀጋወቻችን ናቸው። እነኝህ ለእኛ #ዘውዶቻችን ናቸው።
ክፋ ነገር አብሮን አልተፈጠረም። ስንፈጠር ጎዝጉዞ የሚቀበለን ግን ክፋ ነገር ነው። ለምን? ክፋ ነገርን የሚቋቋም ተቋም ዓለማችን ስለ አልሠራች። ትጋቴ ያ ዕውን እንዲሆን ነው። አንድ ዩቱብ ቻናል አለኝ። በዛ ላይ የተጋ። ግን በጥልቅ ሃዘን ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ ቆመ። አሁን ቲክቶክን ፎርማቱን ለዛ ጀምሬዋለሁ።
በቀጥታም ባይሆን ከእኔ መንፈስ ጋር የሚቀራረቡ መነሻቸውን እያዬሁኝ እጽናናለሁ። እበረታታለሁም። ትውልድ መዳን አለበት። ትውልድ በተፈጠረበት ሚስጢር ልክ እንዲሆን ግን ሥራ ይጠይቃል። በዚህ ዙሪያ ለሚታትሩ #ሊቀ #ትጉኃን ምን አለኝ እና ንፁህ ልቤን ከመስጠት ውጪ። በቃ እኔኑ እሰጣቸዋለሁኝ።
መኖራችን አጭር። በአጭሩ ሕይወታችን የክፋት ድሪቶ፤ የበቀል ቡተቶ፤ የምቀኝነት ዝክንትል፤ የጭካኔ ብርንዶ??? ለምን? በፍቅር ተሰርተን እራሳችንን ለማፍረስ የምንጥር የሚስጢራችን መንጥሮች። ታላላቆች አልሠሩትም። ግን እኛ አቅም አለን። ለዛ እንትጋ። ቢያንስ ቅን እንሁን። ቢያንስ ክፋ ነገርን በውስጥ ሴብ አናድርግ። እራስን ማዳን የትውልድ የማህበረሰብ ይሆናል። ሂደት ነው እና።
ፈቃድ መስጠት የወሳኝነት አቅምም // #አቅልም ነው። መልካምነት በራሱ የምሥራች ነው። በልጅነቴ ዝምተኛ ነበርኩ ይባላል። መምህሩ እና የቤተ መፃህፍት ኃላፊው አባቴ አበይ ዝምተኛ ነበር። እናቴ ደግሞ ሳቂተኛ የበሞቴ ልዕልት የእሽታ ንግሥት ነበረች። ወደ ቀደመው ምልሰት ሲሆን የአጎቴ ባለቤት መልካምሰው ትለኝ ነበር። መልካም ሰው የምትለኝን መልሼ መልካሜ እላት ነበር።
አክስቴ ደግሰው ትለኝ ነበር። እኔም ደግዬ እላት ነበር። ያን ጊዜ ያለኝን ሁሉ እምሰጥ ፍፁም ለጋስ ነበርኩ ይባላል። ዓለማችን ክፋነትን የሚቋቋም ተቋም ቢኖራት መልካምሰው // ደግሰው ሆኜ እንደ አፈጣጠሬ እዘልቅ ነበር።
ሞጋች ሁኜ ሰውን አላስከፋም ነበር። ምንም እንኳን እምሞግትበት የእኔ የምለው ዕውነት እና መርኽ ቢኖረኝም። እምታገልለትም #ዕንባ ይቁም ነው። ሥልጣን ክብር - ሙገሳ - ውዳሴ - ፋይናንስ አጀንዳወቼ አይደሉም።
ለብዙ ትጉኃን መንገድ ስጠርግ፤ ስደለድል ኖርኩኝ። ዞር ብሎ የሚጠይቅ ባይኖርም። አንገተቢስ ቢሆኑም። የራስ ዝና አፓርትመንት ላይ ቢጣደፋም። አሁንም ዕንባ ይቁም የምተጋበት መሥመሬ ነው።
ለነገሩ ኢትዮጵያ የከበደችን ለሁላችንም ነው። ጥቂት በጣም ጥቂቶች ግን እምዬ ያልከበደቻቸው መሆኗን አያለሁኝ። በዚህ እጽናናለሁ። የአይዟችሁ አርበኞች ናቸው እና። ቢያንስ በፀሎት ቢታገዙ ምኞቴ ነው። በመልካምነት ላይ ለሚተጉ ጀግኖቼ።
ልጅነቴ በደግነት በትጋት በማድመጥ በዝምታ ላይ ያተኮረ ነበር። ለዚህ ነው ሃሳቤ ጋር ስምም የሆነውን ፎቶ የለጠፍኩት። በዚህ ዕድሜ የነበረ ትጋት፤ የነበረ ቅልጥፍና ልዩ ነበር። ዝምታው አሁንም አለ። ግን እቴጌ ብዕሬ ሳለች ተናጋሪ አደረገችኝ። ሲዊዚሻ ዝግ ሆኖ እንጂ የወጣልኝ ተናጋሪም ነበርኩኝ።
በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የንግግር ጥበብ ኮርስ ይሰጥ ነበር። እኔም ታድዬ ከዚህ ከፎቶዬ ዕድሜ ባነሰም ዕድሜ ለ40 ፔሬድ በአንድ ፔሬድ ለሁለት ሰዓት ያህል በመደበኛ ተምሬያለሁኝ። ሠርቼበታለሁም። ግን ሲዊዝሻ እና ታለንት?
ንግግር ፀጋ ነው። የላይኛው በረከት። ክህሎቱን በስልጠና ማግኜት ይቻላል። ስምንተኛ ያልታተመ መጸሐፌ ላይ አለ። ስለ ንግግር ተጥፏል መድረክ ጉስቁልቁል ሲል ስለማይ። ሞናትነስ የሆኑ ስብሰባወች ማፍሰስም ናቸው። ሰው ያለውን አጥቶ የሚመለስበት።
ብቻ ስለንግግር የተከተበበት መጠሐፌ ይታተም አይታተም አልተወሰነም። የወግ ሥብስብ ነው።
ሲጠቃለል ስለ መልካምነት በአዕምሮ ላይ የሚሠሩ ሁሉ ለእኔ ማህሌቴ፤ የምሥራወቼ ናቸው። ህሊና ቡርሽ ያስፈልገዋል እና። አዬሩም እኛም ተበክለናል በክፋነት። የተፈጠርንበትን የላዕላይ ሚስጢራዊ መንፈስም እያፈሰስን ነው። ወደ ተፈጥሯችን እንመለስ እምለውም ለዚህ ነው። ወደ ጤናችን እንመለስ። እኛን እንሁን።
ህግ የጥቂት ባለሙያወች ብቻ ሊሆን አይገባም፨ ህግ የማህበረሰብ ሙያ ሊሆን እንዲችል ዓለማችን ስትራቴጂ ልትነድፍ ይገባል፨
ክብረ ሰው ሲፈጠር ለመልካምነት ውስጠ ብርኃን ሆኖ ነው። ክብረ ሰው ከክፋ ነገር ጋር ፈቅዶ ሲዋህድ ውስጠ ጽልመት ይሆናል። እዮራዊ ምርቃቱም ይነሳል።
https://www.youtube.com/watch?v=cBce7c69vsk&t=45s
ዓለማችን ለፍቅር ተፈጥሯዊ መልካምነት ካሪክለም ልትነድፍ ይገባል። ህግም የጥቂት ባለሙያወች ሳይሆን የማህበረሰብ ሙያ ይሆን ዘንድ ልትተጋ ይገባታል።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
23/07/024
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት ጋራጅ አያስፈልገውም።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ