«በኦባማ የዓመቱ ምርጥ መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ የተካተተው ዲናው መንግሥቱ ማነው?» BBC

 

«በኦባማ የዓመቱ ምርጥ መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ የተካተተው ዲናው መንግሥቱ ማነው

 

https://www.bbc.com/amharic/articles/cdr01lgv4xlo

5 ሰአት በፊት

«የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ 2024 ምርጥ መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ ካካተቷቸው መጻሕፍት መካከል የዲናው መንግሥቱ 'Someone Like Us' ይገኝበታል።

ኦባማ እአአ 2019 የዲናውን 'How to Read the Air' የተባለ ልብ ወለድ የዓመቱ ምርጥ መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ አስገብተዋል።

ኦባማ በምርጥ መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ የሚያስገቧቸው መጻሕፍት በአብዛኛው መነጋገሪያ ይሆናሉ። ብዙዎች የኦባማን ዝርዝር ተከትለው መጻሕፍቱን ማንበባቸውንም ይናገራሉ።

የኦባማ የዓመቱ ምርጥ ሙዚቃዎችም በተመሳሳይ ተደማጭነት ሲያገኙ ይስተዋላል።

በአውሮፓውያኑ 2021 ኦባማ የዓመቱ ምርጥ ብለው ከሰየሟቸው ሙዚቃዎች መካከል የቴዲ አፍሮ "አርማሽ" የተሰኘው ሙዚቃ መካተቱ ይታወሳል።

ኢትዮጵያዊ-አሜሪካዊው ዲናው 'All Our Names' 'How to Read the Air' እና 'The Beautiful Things That Heaven Bears' የሚሉ ልብ ወለዶችን አሳትሟል።

ዲናው የሁለት ዓመት ልጅ ሳለ ነበር ከቤተሰቦቹ ጋር ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ የሄደው።

ጋዜጠኛ ሳለ ስለ ዳርፉር ጦርነት፣ በሰሜን ኡጋንዳ እና በምሥራቅ ኮንጎ ስለነሩ ግጭቶች ጽፏል። ለኒው ዮርክ ታይምስ፣ ለርፐርስ፣ ለግራንታ ጄን፣ ለሮሊንግ ስቶን፣ ለዎል ስትሪት ጆርናልና ሌሎችም መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

በፈጠራው ዘርፍ የላቀ ብቃት ላሳዩ ባለሙያዎች የሚሰጠው ማክአርተር የገንዘብ ሽልማትን ጨምሮ በናሽናል ቡክ ፋውንዴሽን 35 ዓመት በታች ተሸላሚ ከሆኑ አምስት ደራሲያን አንዱ ነው።

ጋርዲያን የሚያዘጋጀውን 'ጋርዲያን ፈርስት ቡክ አዋርድ' የላናን ሊትረሪ ፌሎውሺፕ እንዲሁም ሎስ አንጀለስ ታይምስ የሚያዘጋጀውን 'አርት ሰዲንባውም አዋርድ' ተሸልሟል።

እአአ 2010 40 ዓመት በታች ያሉ 20 ደራሲያን ዝርዝር ውስጥ ኒው ዮርከር ጋዜጣ አካቶታል።

ዲናው የመጀመሪያ ዲግሪውን የሠራው ጆርጅታውን ሲሆን ሁለተኛ ዲግሪውን ከኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ አግኝቷል።

ኒው ዮርክ ታይምስ የመጻሕፍት ዳሰሳ 'All Our Names' የተባለውን መጽሐፍ የገለጸው "እያንዳንዱን ገጽ በጉጉት በፍጥነት ትገልጡታላችሁ። ስትጨርሱት ደግማችሁ ማንበብ ትፈልጋላችሁ" በማለት ነበር።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ይሠሩ የነበሩ አባቱ በቀይ ሽብር ጊዜ ነበር ጣልያን ለሥራ በሄዱበት ጥገኝነት የጠየቁት። ከሁለት ዓመት በኋላ ዲናው ከእናቱና ከእህቱ ጋር ወደ አሜሪካ አቅንተው ከአባታቸው ጋር ተገናኙ። ቤተሰቡ መጀመሪያ በኢሊኖይ ግዛት ከዚያም በቺካጎ ኖሯል።

የመጀመሪያ ልብ ወለዱ በአሜሪካ 'The Beautiful Things That Heaven Bears' እንዲሁም በዩናይትድ ኪንግደም 'Children of the Revolution' በሚል ርዕስ ታትሟል።

ሰፋ እስጢፋኖስ የተባለው ዋና ገጸ ባህሪ በደርግ ጊዜ ወደ አሜሪካ ተሰዶ የሚገጥመውን ሕይወት ያስቃኛል።

በዋሽንግተን ዲሲ ጥቁር አሜሪካውያን በብዛት የሚኖሩበት ሰፈር ሱቅ የከፈተው ስደተኛው ከሌሎች ሁለት አፍሪካውያን ስደተኞቹ ጋር በመሆን የስደት ሕይወትን፣ ማንነትን፣ አገርንና ሌሎችም የሕይወት ውጣ ውረዶችን ሲጋፈጡ ልብ ወለዱ ያስነበብባል።

ሁለተኛው ልብ ወለዱ 'How to Read the Air' የኧርነስት ጌይንስ ሽልማትን አግኝቷል። ስደተኞች በአሜሪካ የሚገጥማቸውን ሕይወት በማሳየት ረገድ ልብ ወለዶቹ ተጠቃሽ ናቸው።

'All Our Names' የተሰኘው የዲናው ልብ ወለድ በአሜሪካዊት እና አፍሪካዊ መካከል ያለ የፍቅር ታሪክ ነው። ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ ኤንፒአር፣ ቦስተን ግሎብና ሌሎችም መገናኛ ብዙኃን የዓመቱ ምርጥ መጽሐፍ ብለውታል።

ኦባማ 2024 መነበብ አለባቸው በሚል ከጠቀሷቸው መጻሕፍት መካከል አንዱ የሆነውና በቅርቡ የታተመው የዲናው ልብ ወለድ 'Someone Like Us' ከኢትዮጵያውያን ስደተኞች የተወለደ ልጅ ስለ ቤተሰቡ ታሪክ ለማወቅ የሚያደርገውን ጥረት ያስቃኛል።

ማሙሽ የተባለው ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊ ዋና ገጸ ባህሪ የሚኖው ፓሪስ ሲሆን ጋዜጠኛ ነው። እናቱ የምትኖርበት ቨርጂኒያ ከተመለሰ በኋላ ነው የቤተሰቡን ውስብስብ ታሪክ የሚረዳው።

ዲናው በጆርጅታውን ዩኒቨርስቲ፣ በብሩክሊን ኮሌጅና ሌሎችም ተቋማት ሥነ ጽሑፍ አስተምሯል። በብራድ ኮሌጅ የሥነ ጽሑፍ ክፍል የፕሮግራም ዳይሬክተርም ነው።

በአፍሪካውያን ስደተኞችና በአሜሪካ የሚገጥማቸውን ሕይወት በማስቃኘት ታዋቂ ከሆኑ ጸሐፊዎች መካከል በዋናነት ይጠቀሳል።

የማንነት ጥያቄ፣ ዘረኝነት፣ ራስን መፈለግና የስደተኞችን ውስብስብ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሕይወት በሥራዎቹ ያሳያል።»

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።