#ናፍቆቴ #ሰላም ነው።
"የሰው ልብ መንገድን ያዘጋጃል፦
እግዚአብሄር ግን አካሄዱን ያቃናለታል።"
(ምሳሌ ፲፮ ቁጥር ፱)

#ልጆች ቁጥር አንድ ሰላም አፍቃሪ ናቸው።
#እናቶች ሰላምን አጥብቀው ይሻሉ።
#አብራክ የሰላምን ዋጋን ከልጆች ፍቅር ጋር አዋህዶ ይመለከተዋል።
#ማህጸን የፊደል ገበታው ሰላም ነው።
እጽዋት በትክክል #መተንፈስ የሚችሉት ሰላም ሲኖር ብቻ ነው።
የቤት ይሁን የዱር #እንሰሳት ተፈጥሯዊ የአኗኗር ዘይቤያቸው የሚቀጥለው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው።
#ተራሮች ፈንጅን አጥብቀው ይጸየፋታል።
#ምድር የአዬር ድብድባን እንዲነሳባት አትፈልግም።
አፈር በቦንብ መቃጠሉን አትሻም። ያንገሸግሻታል።
#ኮረብታወች ጆሯቸውን ጭው የሚያደርገው የድሮን ድብደባ አይናፍቃቸውም።
ወንዞች በሮኬት #የጉዞ ፀጥታቸው ይደፈርስ ዘንድ ሽው አይላቸውም።
#አዝዕርት በሰው አጥፊ መርዝ እድገታቸው እንዲጨናገፍ አይፈልጉም።
#አዬር በኒኩሌር ቦንብ እንዲታወክ አይሻም።
#ሳይንስ ጦርነት አይፈልግም።
#ዊዝደም ከጦርነት ጋር ፍቅር የለውም።
#ሃሳብ ጦርነት እርጋታን የሚቀማ ዘራፊ መሆኑን ጠንቅቆ ስለሚገነዘብ ይጠላዋል። ሰላም እንደ እኔ ይናፍቀዋል።
#ፍልስፍና ሰላም ጋር በተክሊል ተጋብቶ መኖርን ይፈቅዳል።
ዕውቀት ለሥልጣኔ ሰላም ወሳኝ #ቁምነገር መሆኑን በጽኑ ያምንበታል።
ተፈጥሮ/// --- ተፈጥሮውን የሚያስቀጥልለት #ሰላም ብቻ ስለመሆኑ ያምንበታል።
#የሃይማኖታዊ ዶግማ እና ቀኖና የሰላም ፍሬ ነገር ወሳኝ ጉዳያቸው ነው።
#መኖር ከሰላም ጋር ውህድ ማንነት ያለው የፈጣሪ የአላህ ሥጦታ ነው።
ኪነ - ጥበብ ሰላም #ኦክስጅኑ ደጄሰላሙ፤ ዓውደ ምህረቱ ነው።
ተማሪወች በህይወታቸው ከሚናፍቃቸው #አንከር ጉዳይ ሰላም እና ሰላማዊ አዬር ብቻ ነው።
ሥልጣኔ ዕድገቱ በውድመት መሻገትን አይሻም።
የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች፤ ውድ ቤተሰቦቼ ……
እኔ ከለጠፍኩት ፎቶ #ባነሰ ዕድሜ ሥራ ላይ ሆኜ፤ ተማሪም ሁኜ፤ ታዳጊ ወጣትም ሆኜ፤ ወጣትም ሆኜ የጦርነት መልከ ቁመናውን አውቀዋለሁኝ። የተወለድኩበት በዕቴ ልዕልት ጎንደር የጦርነት ቀጠና ብቻ ሆና ነው የማውቃት። ስለሆነም ተስፋዬ አሮ፤ የመማር ምኞቴ ተኮማትሮ የዕውቀት መሻቴ ዶክኮ ዘለቀ። የወጣልኝ አንባቢ እና ሰቃይ ተማሪ ነበርኩኝ። በጦርነት ምክንያት ቤተሰባችን ተበተነ፤ ህልሜ አይሆኑ ሆኖ ቀረ።
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ጭራሽ #ሳይታሰቡ ኦሮምያ ላይ እዬሠሩ ነበር ስጋቴን በደጉ ሳተናው ድህረ ገጽ ላይ የገለጽኩላቸው። "እህልዋ" ጎንደር ድጋሜ የጦርነት ቀጠና እንዳይሆን። እንዲያውም አንባቢወች "ምን ስልጣን አላቸው እና" ብለውኝ ነበር። ቢያንስ በኢህአዴግ ስብሰባ አንድ ድምጽ ይኖራቸዋል ነበር መልሴ።
ምክንያቴ በከተማ አስተዳደር ጎንደር ላይ እሳቸው በመሩት ስብሰባ ላይ በጎንደር ጉዳይ ቀና የሆነ ዕሳቤ ያለው #ቀንጣ ሊሂቅ በዘመነ ህወሃት እሳቸው ብቻ ስለነበሩ፥ ተስፋ አድርጌባቸው ነበር እና ነው ያን ማሳሰቢያ የፃፍኩት። በፍፁም ሁኔታ "እናትዋ" ጎንደር እኔ በአደኩበት የጦርነት መከራ ውስጥ እንዲህ በድጋሜ ይነከራል የሚል ያን ጊዜ ምንም ሃሳብ ባይኖረኝም። ከፋኝ ያለው ሁሉ ወደ ጎንደር ዱር ገደል እንደሚያማትር ስጋት ስለነበረኝ ነበር ያን ሃሳብ ያነሳሁት።
ጠቅላይ ሚር አብይን እኔ መከታተል የጀመርኩት ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚር እያሉ ነበር። በውነቱ ያ ተስፋ ያደርኩበት አብይዝም በህይወት የለም። በንግግር - ለዛም፤ በንግግር - ቃናም፤ በተፈጥሯዊነት - ዕሳቤም ሆነ ለእናቶች ባለ ትሁት ዕይታ ፈጽሞ እንዲህ አልነበረም። የተገለበጠ አዲስ ማንነት ነው ጠሚር ከሆኑ በኋላ ያዬሁት። #እናቶችን፤ ህፃናትን #በድሮን????
አመዛኙን የዛን ጊዜ ንግግር ቀድቸዋለሁኝ። ለምን ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ያን ሰዋዊ የንግግር ሰብዕናን በውዘው በዚህ የጭካኔ መንፈስ ውስጥ ሊዋኙ እንደቻሉ የፈጠራቸው አማኑኤል ይወቀው። የሆነ ሆኖ ቢያንስ አሁን ከዚህ ሁሉ ውድመት በኋላም የአገር ውስጡ የባሩድ ነዲድ ፀጥ ሳይል፦ ሌላ ከጎረቤት ጋር እያቆጠቆጠ ያለውን የግራ ቀኙን የጦርነት #መንኮራኩር ዋዜማ አጥብቄ እቃወማለሁኝ። ቀደም ብዬ በሌላ የወግ ገበታዬ እንደገለጽኩትም ለእኔ ወፈፌነት ወይንም ዘለግ ሲል እብደትም ነው።
ጠሚር አብይ አህመድ ንቀቱንም፤ ማቃለሉንም፤ ማጣጣሉንም ተወት አድርገው ከዬትኛውም ወገን ጋር በቅንነት፤ በንጽህና ለመነጋገር መፍቀድ ይኖርባቸዋል። እንዲህ ሁሉ ነገር እንደ ተበተነ ያልታሰበ ነገር ቢፈጠር ይህ ህዝብ ምን ይሆናል ብለው እንደ መሪ ሊያስቡ ይገባል። ማንኛችንም ዕድሚያችን በመሃረብ ቋጥረን አልያዝነውም እና።
በሌላ በኩል የራሳቸውን ብቻ ሳይሆን "ላም እረኛ ምን አለ" ብለው ሊያዳምጡ ይገባል። ከአንድአፍታው ከአቶ አማኑኤል ይልቅ እኛን ቢያዳምጡ ይበጃቸዋል። ያተርፋቸዋልም።
ለመሆኑ ጥሞና ላይ የሚሆኑት መቼ ነው ዶር አብይ አህመድ አሊ??? ለራሳቸው እራሳቸውን ለማረም ይሁን ለመገሰጽ ጊዜ ሊኖራቸው ይገባል - ትእዛዝ አይደለም ማሳሰቢያ ነው --- የባተሌዋ። ሁልጊዜ ቀውስ፤ ሁልጊዜ ስጋት ማስበል፤ ሁልጊዜ ሽብር፤ ሁልጊዜ ጦርነት፤ ሁልጊዜ ሬሳ ማፈስ፤ ሁልጊዜ አካላቸውን ያጡ፤ ተስፋቸው እምሽክ ያሉ ወጣቶች ማዬት ሊናፍቃቸው አይገባም። ፈጽሞ።
በፖለቲካ እስረኞች በኩልም የእናቶች፤ የሚስቶች፤ የልጆች፤ የእህቶች፤ የትዳር ሰላም መታወክ እንደ አንድ የአገር መሪ አጀንዳቸው ሊሆን ይገባል። ምን ይጠቅመኛል ብለው የነፍስ ወከፍ ኑሮ መበተን እንደሚገፋበት በፍፁም አይገባኝም። መሪነት ለህዝብ የመኖር ዋስትና ማረጋገጥ እንጂ ስጋትን መደገስ ሊሆን አይገባም። ህዝባችን በፍርሃት ምጥ ውስጥ ነው የሚገኜው።
በኢትዮጵያ አንድም የፖለቲካ እስረኛ ሊኖር አይገባም። የአገር ውስጥ ጦርነቱ ሊቆም ይገባል። ሰላም ሊፈራ አይገባም። ሰላምን መድፈር አትራፊ ነው። ወይንም ያቋቋሙትን የሰላም ሚር የጦርነት የቀውስ አምራች ሚ/ር ይበሉት። ከጎረቤት አገር ጋር ያለው የጦርነት ወላፈንም በረድ ሊል ይገባል።
የኔ ቅኖች እንዴት አደራችሁ - ዋላችሁ? ኑሩልኝ። አሜን።
ቸር አስበን፦ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
12/03/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
በቃ ጦርነት!
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ