#እርህርህናዬን #አልወቅሰውም።
አገር እያለሁኝ ከቤተሰብ ጉዳት ከደረሰ ለተጎዳ ሳይሆን እሷ ምን ትሆናለች ነው ጭንቁ። እግዚአብሄርን ባገኜው የምጠይቀው ውስጤ በምን #እንደተሠራ እንዲነግረኝ ነው። ስልክ እማልወደውም፦ እማላነሳውም በፍራቻ ምክንያት ነው። የቤቴ ደወልም በጣም ነው የሚቀፈኝ። ውጭ አገር ለሚኖሩ ቤተሰቦቼ የሚልኩልኝን ዕቃ በአደራ ደብዳቤ እንዳይልኩ ሁሉ ነው እምነግራቸው። የቤቴ ደወል በፖስተኛ እንዳይጨናነቅ። የሆነ ሆኖ ፈንጠዝያ አያጓጓኝም። ፈንጠዝያም ውስጥ ኑሬ አላውቅም። የምመርጠው ከተቻለ ጸጥታ። …
… ካልሆኑም ጉዳት በደረሰበት አካባቢ መገኜት እና የድርሻዬን መሞከር ነው። በምሞክረው ውስጥ ብቻ #ሐሤት አገኛለሁኝ። ሐሴት ከደስታ በላይ ነው በእኔ ፍልስፍና። ለነገሩ የአደኩበት ቤተሰብ በልደት #ነዳያን #ድንኳን ጥሎ #አደግድጎ ታጥቆ #ከሚያደግፍ ከሊቀ ሊቃውንታት ደጋግ ቤተሰብ ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን የተፈጠርኩበት ዕለት እና ሳይንቲስቶች የሚሉት የደም ዓይነቴም ሊሆን ይችላል በተጎዳ አካባቢ ብቻ ህሊናዬ እንዲያተኩር የሚሆነው። ለዚህም አምላኬን አመሰግነዋለሁኝ፦ ይህን ስለሰጠኝ። እጅግ ብጎዳበትም።
ከተሰደድኩኝ አንድም የቤተሰብ መርዶ በቅጡ ነግሮኝ የሚያውቅ ደፋር የለም። ህልሜን አምናለሁኝ። በህልሜ ራሴን አርድቼ የሃዘን ጊዜዬን በመጨመት ይከወናል። ከሠርግ ቤት - ሃዘን ቤት፤ ከወል የፌስታ - መሰናዶ የታመመ መጠዬቅ ይቀናኛል። ይህን ፈጣሪዬ መርቆ ስለሰጠኝ አመሰግናለሁኝ። ብጎዳበትም ግን የውስጤ እርካታ ምንጩ ይህ በመሆኑ #ርህርህናዬን #መቼውንም #ቢሆን #አልወቅሰውም። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ተጠለፋ ሲባል ከ2 ወር በላይ ጥቁር ለብሻለሁኝ። ሥማቸውን አንስቼ አላውቅም።
ጅልነት ይባል ምን አላውቅም ጥቁር መልበሴ። ሰው ሁሉ ይደነግጥ ነበር። አንድ ቀን በልጅ መሳይ ሚዲያ የታገለላቸው ማን እንደነበር ሲገልጹ #ክህደታቸውን አስተውያለሁኝ። ሚዲያ ላይም በአደባባይ የፃፈ፦ ህወሃትን የሞገተ የኔን ያህል አላየሁም። አልነበረም።
ድርጅታቸው እራሱ በብዕር የእኔን ያህል አልሞገተም። ሚዲያወቼም ተግቶበታል። አጭር ፊልምም ያዘጋጀሁበት አመክንዮ ነበር። ለነገሩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ #ጫጭቶ - ጫጭቶ፤ ሳስቶ ሳስቶ #ኮስምኖ ሳያተርፍ ተንሳፎ የሚቀረውም ክህደት ማሟሻው ስለሆነ ነው።
ወደ ቀደመው የመነሻ ሃሳቤ ስመለስ ፖለቲካ ውስጥ በመደበኛ ሠራተኝነት ሥሰራም #ርህርህናን ጨብጬ ነው። ለዚህም ነው ችግር ስሰማ ፈጣን ምላሽ እምሰጠው። ዳር ድንበር የለውም ለአዛኝነት። ማን ይፈጽመው ማን? ብቻ የሰው ልጅ በሰው እጅ ጭካኔ ሊፈጸምበት አይገባም ነው መርሆዬ። ቅድመ ሁኔታም አላስቀምጥም #ርህርህናዬን ለሚጠይቅ ማናቸውም ክስተት ፈጥኜ ብዕሬን አነሳለሁኝ። መተንፈሻ ቧንቧዬ ብዕሬ እና ብራናዬ ናቸው እና።
ልጅ እያለሁ ሌሊት እነሳ እና የበሞቴ ልዕልቴን፦ የእሽታ ንግሥቴ እብዬን እናቴን፥ እህት እና ወንድሞቼን ጉንብስ ብዬ ትንፋሻቸውን እጠጣ ነበር። ነግቶ በሰላም እስክንገናኝ ድረስ አላምናቸውም ነበር። ወደ አቨይ አባ ዝምታ አባቴ ስሄድም ሌሊት ባልደፍርም ግን ጥዋት ቀድሜ እማገኜው እኔው ነበርኩኝ። የተሠራሁበት ዘሃ ግራ ባውቀው ምንኛ ደስ ባለኝ ነበር።
በዬትኛውም ዓለም የሚሠሩ ጭካኔወች ያስከፋኛል፦ እንኳንስ በአገሬ የሚከወኑ ጉዳዮች። የሰው ልጅ በፈጣሪ አምሳል ተሰርቶ ጭካኔን ከተባበረ የፈጠረውን አምላኩ ላይ #እንደሚጨክን ነው የማምነው። ጭካኔው ማንም ይፈጽመው ማን መቅደም ያለበት ተበደልኩ የሚልን ሰብዕና ዕንባ ማዳመጥ ቀዳሚው ተልዕኮ ሊሆን ይገባል። ስለዚህም መቼውንም ቢሆን፤ በማንኛውም ጊዜ ቢሆን የተሳሳተ ሊሆን ይችላል፤ ለዚህኛው ለዚኛው ፐርፐዝ ብዬ ደንበር እምሰራለት አመክንዮ ፈጽሞ የለም። ርህርህናዬ ይቀጥላል።
ውስጤ ስለተጎዳ በሃኪሞቼ ምክር እማላያቸው፤ እማላዳምጣቸው ጉዳይ ቢኖሩም ተቆራርጠው በዜና የሚቀርቡ ጉዳዮች ካዳመጥኩ ግን ወጥቼ ዕንባን መጋራቴ አይቀሬ ነው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ በጋሜዬ የጀመርኩት ሆኖ ሁልጊዜም ግን አዲስ ነው። #ትብትብ ነው።
ለዳኝነትም አስቸጋሪ ነው። ለዚህ መሰል የኢትዮጵያ ፖለቲካ የምርመራ ጋዜጠኛ ወይንም የህግ ባለሙያ ጋዜጠኛ መሆንን ይጠይቃል።
እኔ የሠራሁበትም፤ ኮርስ የወሰድኩበትም በመጋዚን ዝግጅት እና በራዲዮ ጋዜጠኛነት ነው። ስለዚህ በህዝብ ጎልቶ እና ጎልምሶ በወጣው ወቅታዊ መረጃ ማተኮር ግድ ይላል። በተለይ አንቱ በተባሉ ሚዲያወች ላይ አና ብሎ የወጣን የመከፋት መረጃና አላውቅህም ልለው አልችልም። ለዛውም በውስጡ የሚሊዮን ሴቶች የስጋት ምንጭ የሆነውን፥ በባህላችን ተደፍሮ ለአደባባይ የማይበቃውን "#የመደፈር" ጉዳይ በወል ዕንባ ታጅቦ ሲቀርብ ርህርህናዬ ማድመጡን፤ ማስተናገዱ የተገባ ነው። በዚህ መልክ በዬጊዜው በጉልበት የሚደፈሩ፤ ማስፈራሪያ የሚደርስባቸው፤ የሚሳቀቁ ሴት እህቶች፤ ሴት ልጆች አሉኝ እና።
ይህ አስገድዶ የመድፈር መከራ በህግ ፊት ቀርቦ ህጋዊ ቅጣት ያገኝ ዘንድ እተጋለሁኝ። ሰው በግፍ ታግቶ የሰው ልጅ በገንዘብ እንደ ሸቀጥ በጅምላ እና በችርቻሮ የሚሸጥ እና የሚለወጥበት #የባርነት ሥርዓትም ይቆም ዘንድ እተጋለሁኝ። ቦኮሃራሚዝም ሃራም፤ አክ እንትፍ ይባል ዘንድ እተጋለሁኝ። ተመርጫለሁ የሚል መንግሥት የሴቶችን የመኖር #ዋስትና የማረጋገጥ አቅም ሊኖረው ይገባል እንጂ የእኔን አብሮኝ የተፈጠረውን ርህርህና ልወቅሰው፥ ልነቅሰው ፈጽሞ አልችልም።
ወላጆች ልጆቻቸውን ለመንግሥት አደራ ሲሰጡ፤ መንግሥት አደራውን ሊወጣ ይገባል። ይህ መብቱ ሳይሆን ግዴታው ነው። በዚህ አጋጣሚ በርህርህና ዘርፍ ነጥራ የወጣችውን እህቴን የሚዲያ ባለሙያዋን ጋዜጠኛ ሉላ ገዙን ከልቤ አክብሬያታለሁኝ። በምንም ይሁን በማንም ዕንባን መጋራት፦ የሲቃ ቤተኛ መሆን ጥልቅ የሆነ የእናትነት ሚሥጢር ነው እና "እግዚአብሄር በአንድም በሌላም ይናገራል ሰው ግን አያስተውለውም" የሚለው ቃል እንደ ተፈጸመ ይሰማኛል። የዕንባ ጠበቂ የሚባል፦ የሴቶች የህፃናት እና የወጣቶች የሚባሉ ተቋማት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉ አዳምጣለሁኝ። እነኝህ መሰል ተቋማት ሊመሩ የሚገባቸው በወ/ሮ ሉላ ገዙ ዓይነት ሩህሩህ ሰብዕና ሊሆን ይገባል።
በዚህ አሳቻ ዘመን ያላዬነው፥ ያልሰማነው፤ ያላስተዋልነው የጭካኔ ዓይነት የለም። ገራገርሯ ወት አስምራ ሹምዬን የሰባዕዊ መብት ተሟጋች አመለጠች ተባለ፤ ቃለ ምልልስ ተደረገላት፦ በታገቱ ልጆች ተግተው የሚሠሩት እንኳን #ሳት ብሏቸው ሥሟን አንስተውት አያውቅም። እኔ በዕንባ ጉዳይ እንዴት የሚለውን ጥያቄ ማንሳት አልሻም። ግን ወጣቷ በምን ሁኔታ ትገኛለች? አዘውትሬ እምጠይቀው ጉዳይ ነው። እሷም እናት፤ እሷም ቤተሰብ አላት እና።
በሌላ በኩል በወቅቱ ሰፊ ድጋፍ የነበረው ኢትዮ 360 ሚዲያ የደንቢ ዩንቨርስቲ ተማሪወች ላይ የደረሰው ጉዳት መረጃው እንዳለው ገልፆ ነበር። የቡራዩም እንዲሁ። በወቅቱ መረጃው ሳይታፈን ቀርቦ ቢሆን ኖሮ በሰሞኑ የብርቴ ክስተት ፍንትው ያለ የተጠረገ ጎዳናን ማያት ያስችለን ነበር። በጣም ከባዱ ነገር የሰው ልጅ ተሰውሮ ሲቀር ነው። #የቀበረ እኮ ዕድለኛ ነው።
በዘመነ ደርግም በትውልድ የማይተካ እነ ሊቁ ሚኒስተሩ ጸሐፊ እና ደራሲ፤ ገጣሚ እና ባለቅኔ አቶ በዓሉ ግርማ እና ከአንድ ቤተሰብ አራቱን ወጣቶች አጥተናል። የወልቃይት፥ የጠገዴ ጠለምት ማይጠምሪ፤ የአድአርቃይ እና የራያውም ተመሳሳይ የታሪክ ብልዛት ነው። በጦርነቱም በትግራይ፤ በአፋር እና በአማራ ክልል በሴት እናት፤ በሴት እህት፦ በሴት አክስት የደረሰው መከራ #ጠቀራዊ ታሪካችን ነው። ይህን የእኔ እንድለው የሚያደርገኝን አጤ ርህርህናን ዛሬም ወደፊትም አልወቅሰውም።
እራሳቸውን መውቀስ ያለባቸው ለምታልፈው አሮጌ ጨርቅ የምድር ኑሮ፦ በዚህ መሰሉ ብሄራዊ የጭካኔ ገመና የተሳተፋት ናቸው። በድርጊታቸው ሊያፍሩ፤ ሊሸማቀቁ የሚገባቸው። በሌላ በኩል አብይዝም መንግሥት ነኝ ካለም ቆፍጠን ብሎ በተሰጠው ወንበር ላይ ቁጭ ብሎ #አስተዳደራዊ ተግባርን ሀ ብሎ እንዲጀምር እንነግረዋለን። አብይዝም እግሩን እንጂ ወንበሩን ለምን ይፈራዋል።
አዘውትሮ መሄድ መጓዝ ብቻ። አሳቻው ዝርክርክ እና ዝልግልግ አመራር ነው ቀልባችን እረፍት ነስቶ እያባተለን የሚገኘው። ዕውነትም ፍዳው ጠና። በጠቅላላ የሁነቱን ውሃ ልክ ስለካው ኢትዮጵያን እዬመራት የሚገኜው ሞተሩ መንፈስ #አናርኪዝም ነው። ወላጆችን #ልጅ አልባ፤ ልጆችን #ወላጅ አልባ ያደረገው ጨካኙ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታማሚ ነው እና ሃኪም ያስፈልገዋል። ሃኪሙ ደግሞ ርህርህና ነው።
መዳህኒቱ ሰውኛነት ነው። ማኒፌስቶው ተፈጥሯዊነት ሊሆን ይገባል። የተፈናቀሉት ረመጥ ጉዳይ ልፃፈው ቢባል ምን ብራና ሊበቃን።
በነገረ ብርትሽ ጉዳይ ሁሉንም መረጃ #አዳመጥኩት - በጥሞና። አዬሩን የሞላው ጭካኔያዊ መንፈስ ነው። ሴቶች ጥበቦች እንጂ ተንኮለኞች አይደለንም። ታማኝነት ለሚታማነው ለፈጣሪያችን ለአላኃችን እንጂ ለዬትኛውም የፖለቲካ ፍላጎት ሊሆን አይገባም። በተለይ ሴቶች ሚዲያ ላይ ከወጡ ሰባዕዊነት እንጂ ሴራዊነት አይጠቅማቸውም። ሴረኝነት አሰር እና አረም ሙጃ ነውና።
ሴረኝነት እናትነታቸውን ይፈገፍገዋል፤ እዮራዊ ምርቃታቸውንም ያስነሳል። ሴቶች ቅድሚያ እራሳቸውን ሴት ሆነው መፈጠራቸውን ያክብሩ፤ ያስከብሩ። ሴቶች የሚመሯቸው ሚዲያወችም ሁሉም እናት አለው፦ እኔም የሁሉም እናት ነኝ፦ ልጆች የማህበረሰቡ ልጆች ናቸው ብለው ሊነሱ ይገባል። "ረፈረፈው አራገፈው" ከሚል ዘገባም ሊቆጠቡ ይገባል። የህዝብን መንፈስ በሽብር ከሚነጡ እርዕስ አፃፃፍ እና ቀለም አመራረጥም ላይ ቱኩረት ሊደረግ ይገባል። የሚዲያ ሰውነትነት ከመንግሥት በላይ ተጠያቂነት እና ኃላፊነት አለበት እና። በእኛ ግን ልቅ ነው የሆነ። መንፈሱ ይጋረፋል።
ሰው የሚሰጠው ክብር፤ ሽልማት፤ ሹመት የሳሙና አረፋ ወይንም ምራቅ ወይንም ጤዛ ነው። ልዑል እግዚአብሄር እናት አድርጎ፦ ጉልላት አድርጎ የፈጠረን ሴቶች ከምድራዊ ሹመትም፤ ሽልማትም የበለጠ ነው። በተለይ ጭካኔያዊ ሃሳብ እዬተፈታተነ ከሆነ ጥሞና መውሰድ ይገባል። ብዙ መንፈሶች እርምጃ ይወሰድ ዘንድ የሚያኮበኩቡ ናቸው እና። የሰው ልጅ የጀንበር ሥራ ወይንም የእጅ ሥራ ዳንቴል አይደለም እና። ሰው ሆኖ ተፈጥሮ፦ በተፈጥሮ ላይ መጨከን ፈጣሪ አምላክን፤ አላህን አሻቅቦ መፈተንም ነው።
የፖለቲካ ሥልጣን ሆነ ውዳሴ ገብያ ነው ይፈታል። የሰውን ተፈጥሮ አክብሮ መነሳት ግን እዮራዊ ነው። "ህግ ተላላፊወችን ጠላሁ" ይላል ንጉሥ ዳዊት በመዝሙሩ። ፍላጎትን ለማሳካት በግልጽ እና በቀጥተኛ መንገድ ህገ እግዚአብሄርን ሳይዳፈሩ ሊሆን ይገባል። ክስተቷ ብርቴ ጉዳይ ብዙ ጥልቅ ጥናትን የሚጠይቅ ሆና አግኝቸዋለሁኝ። የሆነው ሁሉ ከቅጣት በላይ ነው እና ለቀጣይ ሰላሟ ሁሉም ኃላፊነቱን ቢወስድ ምርጫዬ ነው። ክስተቱ ጋዜጠኛ ወ/ሮ ሉላ ገዙን ግን ሰጥቶናል ብዬ አስባለሁኝ። የአንገት ሳይሆን የአንጀት መሆንን ነው እኔ ያስተዋልኩት።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ውዶቼ ክብረቶቼ ሩህሩህ ሁኑ እና ተወቀሱበት። ምርቃታችሁ በበረከት ይሞላል።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
28/03/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ርህርህናን የፈጠርክ የሰጠህ አምላክ የተመሰገንክ ነህና ቅዱስ እግዚአብሄር ሆይ! አመሰግንኃለሁኝ። አሜን።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ