ፈላስፊት ኢትዮጵያ የባህር በርም፤ የወደብ ፍላጎቷንም ለመግለጽ #የማንም #ፈቃድ አያስፈልጋትም!
የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች እንዴት አደራችሁ፤ እንደምንስ ዋላችሁ? በብዙ ብሄራዊ ጉዳይ በጣም ዘለግ ላለ ጊዜ ማድመጥን ብቻ ፈቅጄ #ሳደማምጥ ባጀሁኝ። አቅም ማፍሰስ ለትርፍ እና ለስኬት፤ #ለመደማመጥ እና ለትውልድ ተስፋ እርካብ ካልሆነ አቅምን ቆጠብ አድርጎ ማስተዳደር እንደሚገባ በጽኑ እያመንኩበት መጥቻለሁኝ። በተለይ የግለሰብ ሰብዕና ግንባታ ላይ ጊዜን ማባከን የተገባ አለመሆኑንም በከብት ግባት ተረድቻለሁኝ። ምስጋና ቀርቶ የተማገድንለት ሰብዕና ለሰባዕዊነት ጋሻ ለመሆን አለመትጋት ለባተሌወች ዱላ ነው። ተቀጥተንበታል። አይደገምም።
እኔም ሆንኩ ቤተሰቦቼ በአገሬ ኢትዮጵያ በጎንደር ከተማ ተወልደን ስናድግ፤ እኔ ሥራም በያዝኩበት ወቅት ኢትዮጵያ ሁለት ወደብ እንደ ነበራት አውቃለሁኝ። #አሰብ እና #ምጽዋ። በየትኛው ዘመን እንደተሠራ ባላውቅም ጎንደር ደብረብርኃን ሥላሴ ፊት ለፊት ካለው የእመቤታችን አድህኖ ሥዕል #ጁቡቲ የኢትዮጵያ አካል እንደነበረች ያመለክታል።
በዘመነ ህወሃት በእጃችን የነበሩ ሁለት ወደቦች ለኤርትራ አገርነት ተሰጠ። የባህር ሃይሉም ጉዳይ በዝም ብሎ ተቋጬ። ወደቦችን ለማልማት የተከፈለው ዋጋ ይሁን፤ የመርከቦች ዕጣ ፋንታ አቤቱ ህወሃት ከኤርትራ መንግሥት ጋር በምን እንደቋጨው መረጃው የለኝም። የሆነ ሆኖ በዘመነ ህወሃት ለኢትዮጵያ የወደብ አማራጭነት ተነስቶ ሁሉም ለኤርትራ መሰጠቱ ብቻ ሳይሆን፦ ስለ ወደብ ማንሳት የሚያሳስር፤ የሚያስቀጣም ነበር። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ምን አስበው እንደ ሆነ ባላውቅም ስልጣን እንደያዙ የባህር ኃይል ጥንስስን የማፋፋት ተግባር ፈጸሙ። ባህር ሳይኖር የባህር ኃይል?
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ፍጥረተ ነገራቸው #ድንገቴ ነውና ከዕለታት በአንድ ቀን ኤርትራ መጓዛቸው ተደመጠ። የኤርትራ መንግሥትም ግሩም የሆነ አክብሮታዊ አቀባበል አደረገ። ያው የኤርትራ እና የእኛ ነገር ቤተሰባዊ ነውና ተነፋፍቆ የተገናኜ ቤተሰብ እኔን አክሎ በሐሤት ተሞላ።
ነገር ግን ስለሁለቱ መሪወች ንግግር ይሁን ስምምነት የምናውቀው አንዳች ነገር አልነበረም። በሻብያ እና በኢሠፓ በነበረው ረጅም ጦርነት በዬቤታችን አካሎቻችን አጥተናል። ስምምነቱ ከዚህ አንፃር ምን እንደነበረ? በስምምነቱ ሊገኝ የሚችለው ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊ፤ ባህላዊ ትርፎች በሥርዓት ተደራጅተው ዋጋ የከፈለው ህዝብ እንዲያውቅ አልተደረገም ነበር። ይህ ፖለቲካዊ የገዘፈ ግድፈትም ነበር። የኢትዮጵያ ህዝብ ግዴታውን ከመጠየቁ በፊት መብቱ ሊከበርለት ይገባል።
ይህ በዚህ እንዳለ በ2024 የአውሮፓውያን አዲስ ዓመት ዕለት እንደ አገር ዕውቅና ከሌላት ከሱማሌ ላንድ ጋር አንድ ውል ፍርርም #በድንገት አያን ከአብይዝም መንግሥት ጋር። የአማራ ፋኖ ንቅናቄ ፈክቶ በነበረበት ወቅት። ከዛ የአፍሪካ ቀንድ በዚህ አመክንዮ ምክንያት ሞቅ ደመቅ ወደ አለ ፖለቲካ ተሸጋገረ። በድጋፍም፤ በተቃውሞም ጉዳዩ ተጧጧፈ። ለሱማሌ ላንድ ፖለቲካ #ፏ ያለ የዕውቅና በር ከፈተ። የስምምነቱ ጠብታ ግን እድገት ሳያገኝ ተሸበሸበ። በመሃል የአንካራ ዲክላሬሽን ተከተለ።
ኢትዮጵያን እንደ ስጋት ያዩ አገራት ህብረት ፈጥረው ስለነበር የአንካራው ዲክላሬሽን በአገረ ሱማሌ እና በአገረ ኢትዮጵያ የነበረው ውጥረቱን ረገብ አደረገው። የኢትዮጵያ የወደብ ፍላጎት ጥንስስ ግን ሂደቱን ቀጠለ። ተመስጥሮም ይሁን አደባባይ እያሰኜው "ወደብ የባህር በር" የሚሉ ፖለቲካዊ መሻቶች በኢትዮጵያ ህዝብ ህሊና አጀንዳ የመሆን አቅም አገኙ።
ይህ ያልተመቻቸው ጎረቤት አገራትም በጥምረት የሃሳብ ዓውድ ማበጀታቸውን ቀጠሉ። መሪ ተዋናዮዋ #ግብጽ ናት። ይህ በጥድፊያ እና በተደጋጋሚ የመሰብሰብ እና የመመካከር ሂደት ከብልጽግና የካድሬ ሚዲያወች ባሻገር፥ ለኢትዮጵያ ስጋት መሆኑን ፍዙ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሂደት ለዓለማቀፋ ማህበረሰብ በተለይም ለተመድ ማሳወቅ ይገባው ነበር። በሰነድ። በግልጽ እና በአጭር መረቅ በሆነ ቁምነገራዊ ሃሳቦች ተከሽኖ።
ኢትዮጵያ በምንም ታምር ቀይ ባህር አካባቢ #መተንፈስ አይገባትም በሚል የተደራጄ ጉዳይ እዬተከወነ፦ ኢትዮጵያ የእሷ በኽረ ጉዳይ አድርጋ እንብዛም አላዬችውም። ………እንጂ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ የባህር በር፤ የወደብ መሻቷ ያስከተለውን ጫና በተገቢው ጊዜ #በሳል ተግባር ልትከውንበት ይገባ ነበር። ለአፍሪካ ህብረት ጸሐፊነት እጩ በማቅረብ እና ለማሸነፍ መትጋትም ሲገባት አጀንዳዋ አልነበረም። ይህ ዕድል በራሱ ያመለጠ #መላጣ ሁነት ነበር።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስተሩን ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴን አንስቶ ፕሬዚዳንት ከማድረግ ይልቅ በልምዳቸው፤ በተመክሯቸው እና በእርጋታቸው ብቁ ተፎካካሪ እንዲሆኑ ማስቻል ሲገባ፤ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስተርነት ማንሳት ብልህ ፖለቲካ አልነበረም። ይህም ከሆነ አንባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን (ከፕሬዚዳንትነት) ውጭ ጉዳይ በማድረግ የአፍሪካ ህብረት የበቃ ልምድ እና ተመክሮ ቀደምት ዲፕሎማት #ሴት እንዲመራው ለማድረግ ቢጣር ዓለም፤ አህጉራችን አፍሪካ እና ኢትዮጵያ በእጅጉ ይጠቀሙ ነበር።
በሌላ በኩል የአህጉራችን ፖለቲካ ገጽም ህብራዊ ቀለማም ይሆን ነበር። እናታዊነት ዊዝደም ዘለግ ያለ ጸጋ ነውና። በወቅቱም ጽፌበታለሁኝ። የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የእመው እና አበው ዊዝደምን ንቀው ስለሚያሳልፋት የፈካው ዕድል ተዳፈነ። ይህ በብዙ ለኢትዮጵያ ሁለገብ መሻት ረቂቅ አቅም መጋቢ ይሆን ነበር። ብዙ እብጠቶችን የሚያስተነፍስ። በርካታ የጓጎሉ ሴራወችን #የሚያልም ልቅና ይሆን ነበር። ያን የመሰለ ዕድል ሳይታሰብበት ባክኖ ቀረ። እኔም አዘንኩ።
ወደ ቀደመው ሃሳቤ ስመለስ ትልሟን ኤርትራን ከኢትዮጵያ ለመነጠል ሁለመናዋን ገብራ ያሳካችው ግብጽ የወደብ፤ የባህር በር ጥያቄ በኢትዮጵያኒዝም ዳግም ትንሳኤው እንዳይሳካ ጥረቷን ቀጥላለች፤ ወደፊትም ትቀጥላለችም። ግብጽ የኢትዮጵያ ዋና ተፎካካሪ አገር ናት። በአባይ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ የዓለም የዲፕሎማሲ አራተኛ መዲና አገር መሆኗ፤ የአህጉራችን የእማማ አፍሪካ መናህሪያ መሆኗ፤ የጥቁር ህዝቦች የተስፋ ምድርነቷም፤ የኢትዮጵያ መንፈስ የተፈሪነት ጣዕም፤ በነፃነት ዙሪያም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ፤ ኢትዮጵያ ለነፃነት ወዳድ ህዝብ ዓርማ መሆኗ ለግብጽ የሚመች አይደለም። ስለሆነም ግብጽ የኢትዮጵያን ማንኛውም የመሻት ፍላጎት የማቀጨጭ ህልሟ የማይመክን ነው።
በአባይ ጉዳይ አንድ ጊዜ ሳዳምጥ በአስተርጓሚ ኢትዮጵያ አባይ ግድቧን አቁማ "#ዝናብ #ታጠራቅም" የሚል ከአንድ የግብጽ የፖለቲካ ሊቅ ሳደምጥ በጣም ነው የሰቀጠጠኝ። ድፍረቱ። ለኢትዮጵያ ህይወት የንድፍ አባት የግብጽ ፍላጎት መሆኑ። ይህን እንደ ዜጋ ብቻ ሳይሆን ፍትህ እና ነፃነት ለሰው ልጆች ያስፈልጋል ብለን ለምንሞግት ሁሉ ጉዳያችን ሊሆን ይገባል። መማር የመብት እና የግዴታ ጣሪያ እና ግድግዳ ካላሳወቀ ጨለማነት ይሆናል።
ኢትዮጵያ #መተንፈስ ትፈልጋለች። ባህርማዶ ተሻግረው ብዙ አገሮች ቀይ ባህር ላይ ድርሻ ሲኖራቸው፤ የነበራትን ያጣች አገር እኔም እፈልጋለሁ ብላ ማወጇ በራሷ ልጆች መኮነኑ #እርግማን ይመስለኛል። እስከ አሁን ባለው ሁኔታ አብይዝም ወደብም፤ የባህር በርም መሻቱን የሚያመለክቱ ጠረኖች እንጂ ወደ ጦርነት የሚወስድ ነገር እኔ አልሰማሁም። ስለ ባህር በር ሆነ ስለ ወደብ ትንፍሽ ልትል አይገባም ከራሱ ከኢትዮጵያ ዜጋ መስማት ግን ይከረፋል። ማስፈራሪያ ሆነ። ይገርማል። ኢትዮጵያ ከህዝቧ በስተቀር የማንንም፤ የዬትኛውን አገር መንግሥት ፈቃድ አያስፈልጋትም ምኞቷን፤ ተስፋዋን እና መሻቷን ለመግለጽ። ሙሉ መብት ኢትዮጵያ አላት። ቀደምት ሉዓላዊት አገርም ናት። የፋሺዝምን ቅስም ሰብራ ድልን የተመገበች።
በሌላ በኩል ዕለታዊ መጠለያ ለማግኜትም "እኛ የባህር በር፤ የወደብ ጥያቄ አናቀርብም" የሚል አንድ ቃለ ምልልስም አዳምጫለሁ "መታፈር በከንፈርን" የዳጠ። ይህ ኮንፊደንሱ የላመበት መንፈስ ዕይታ ነው። የበታችነትም ስሜትም ነው። ስንት ልፍስፍስ ፍላጎት እና ምኞት እንዳለ ይፋ ያደረግልን አቶ ሂደት ይመስገን። አሜን። እኔ እማይመቸኝ የሌላን ሉዓላዊ አገር መንግሥትን ማንጓጠጡ፤ ትርፍ መናገሩ፤ ህግ መተላለፋ እንጂ የኢትዮጵያ የመብት ደረጃ ወሳኝ እራሷ ኢትዮጵያ ናት።
እኔ እንዲያውም የባህር በርን፤ ወደብን በሚመለከት ከብልጽግና ካድሬወች ጥገኝነት አመክንዮውን አፋቶ፦ ሙያዊ፥ የተደራጄ ተቋም ፈጥሮ ማስጠናት፤ የተደራጄ ተግባር መከወን የሚገባ ይመስለኛል። ጉዳዩን ከተናጠላዊ፤ ከስሜታዊነት፤ ከኮፒራይት ሽሚያ፤ ከሰብዕና ግንባታ ማህደር አላቋ ኃላፊነት እና ተጠያቂነት ሊሰማው የሚችል ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት፤ ህግ፤ ደህንነት፤ የውኃ ፍልስፍና ሙያተኛ፤ በደንበር ጉዳይም ፕሮፌሽናል የሆኑ የሰከኑ፤ የዬትኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባልም አካልም ያልሆኑ፥ ብቁ ሰብዕና ያላቸው ኢትዮጵያውን የሚያሳትፍ መሪ #ተቋም መፍጠር የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ተቋሙ በአብይዝም ዘመን እንዳዬናቸው ለፎቶ ሸው ብቻ ተደራጅተው እንደፈረሱት እንዳይሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል። አርቲፊሻል ሁነቶች ሁልጊዜ መንገድ ላይ ነው የሚቀሩት።
#በሌላ በኩል ከቁጥርም፤ ከግምትም ገብተው የማያውቁ ሦስት ዕንቁ አካላት አሉ።
1) ሳይለንት ማጆሪቲው፦
2) በፀጋቸው፦ በተሰጥዋቸው ልቅና ያላቸው መንፈሶች። ሊሂቅ የሚባሉት።
3) ገራገሩ የኢትዮጵያ ገበሬን ጨምሮ ልዩ የተመሰጠረ አቅም አላቸው። ኢትዮጵያ እነሱን በስፋት የሚያቅፍ አዲስ ሥርዓት ልትፈጥር ይገባል።
በዘመነ ኢሠፓ የሆነውን ላጫውታችሁ። ጓድ ኮነሬል መንግሥቱ ኃይለማርያም ለሥራ ጉብኝት ወደ አንድ የገበሬወች አምራቾች ህብረት ሥራ ማህበር ያመራሉ። በዛ መንደር ሥራ እንዲረዱ ከኮርያ የመጡ ነበሩ። ፕሮጀክቱ #የሩዝ ምርትን ወረታ ላይ ማልማት ነበር። ሥሙ ጠፋብኝ ትጉህ ወጣት ነበር ሊቀመንበሩ፤ የኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሜቴም ተለዋጭ አባልም ነበረ። እና የኢትዮጵያ መሪ ጓድ ኮነሬል መንግሥቱ ኃይለማርያምም ውስጣቸው የከበደውን ቃል አወጡ። ያም "ቋንቋው እንዴት አደረጋችሁ?" ብለው ፈገግታ ሳይቆጥቡ ገበሬወችን ጠዬቁ። ሊቀመንበሩም ቀልጠፍ ብሎ "ጓድ መንግሥቱ አሁንማ #ሚስጢር እያወጋን ነው" አላቸው። እንደ መርግ የከበዳቸው ሸክም በዛው ቅጽበት ሲሟሽሽ ይታይ ነበር። ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ኃብት ብቻ ሳይሆን አልባሌ በምንላቸው ወገኖቻችን ተዝቆ የማያልቅ የመንፈስ ዲታነትም አለ።
ለዚህ ነው እኔ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባለተሰጥዖሊሂቃንን እና ገበሬውን ሊያሳትፍ የሚችል የፖለቲካ ውክልና መስመር ይዘጋጅ የምለው። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ገና 100 ቀን ሳይሞላቸው ነበር ያሳሰብኩት። ህወሃት ብዙ የማይታዩ የኢትዮጵያኒዝም ፈርጥ ይትባህሎችን ቀብሯል። ለድል ያበቃው ገበሬ ሆኖ፦ ገበሬው ግን ከፖለቲካው ተሰርዟል። አንድ በቅርቡ በሰማሁት ቃለ ምልልስም "እኛን ለድል ፋኖ ካበቃን በኋላ ወደ ግብርናው ይመለሳል" የሚል የከሳ ኮሳሳ ኢጓዊ ዕሳቤም አዳምጫለሁኝ። የሚገርመኝ ይህን #ልም ዕሳቤን የተሸከመ መንፈስ ይምራኝ ብሎ የሚገበር ገበሬ መኖሩ ነው።
የከፋው - ይክፋው - ከፈቀደው።
የተቆጣም - ይቆጣ - ካሰኜው።
የተበሳጨም - ይበሳጭ - ለጨጓራው ካልራራ።
የአፈነገጠም - ያፈንግጥ - ከጠቀመው።
ያኮረፈም - ያኩርፍ - ዳሽን ከንፈር ካሰኜው።
ኢትዮጵያ መብቴ ነው ብላ መሻቷን መግለፆዋ ማንም ማዕቀብ ሊጥልበት አይገባም። ከማንም ፈቃድ መጠዬቅ አይጠበቅባትም። የኢትዮጵያ ዓዋጅ ብዙ ህዝብ አለኝ። ነገር ግን ወደብ እና የባህር በር ያስፈልገኛል። እናንተ ይህ የተፈጥሮ ጸጋ ያላችሁ ተረዱኝ እና ተከባብረን እንጠቃቀም ጥያቄዋ ፍትኃዊ፤ የተገባ ነው። እርጋታ ስክነት ግን ያስፈልገዋል። በሳል አትኩሮት እና ክትትልም ይሻል።
ይህ ጉልላታዊ ጉዳይ ካድሪያዊ ሁነት ሳይሆን ሙያዊ ቲም ያስፈልገዋል እንጂ ጥያቄው #የነፃነትም ጥያቄ ነው። ነፃነትን አጣጥማ የተፈጠረች፤ በነፃነት የኖረች አገር ስለነፃነት ፕሮፖጋንዲስት አያስፈልጋትም። በዚህ መስመር እዬተንጠባጠበ የሚቀር ከኢትዮጵያኒዝም ፌርማታ ሊኖር የሚችል መንፈስ ይኖራል። የራስ ውሳኔ ነውና ሊከበርለት ይገባል።
የራሷ የሆነውን፤ የራሷ የነበረውን ትህትናን አስቀድማ ተጨማሪ ዋጋም የሚያስፈልግ ከሆነም እንነጋገር፤ እንመካከር ማለቱ የተገባ ነው። ለአፈፃፀሙ እና ለሂደቱ ሁሉም ያለውን ቢያዋጣ ትውልድ ይጠቀማል። መሻታችን ነገን ለማን? ለነገስ ምን ተኮር ሊሆን ይገባል ነው። ዛሬ ባይነሳ ነገም ቀጣዩ ትውልድ ያነሳዋል። ማንነት ተኮር ጉዳዮች የጊዜ ደንበር የላቸውምና።
እርግጥ ነው ወደብ አልባ የሚኖሩ የአደጉ አገሮች አሉ። ለምሳሌ ሲዊዘርላንድ። እምዬ ሲዊዝ ያን የሚያካክስ ጥበብ ግን አላት። እራሱ ሰላሟ ከመንፈስ ብክነት፤ ከእድገት መስተጓጎል፤ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያላት ስምማዊ ሂደት፤ የሰከነው ቲም መር መንግሥታዊ አደረጃጀቷ እና አመራሯ፤ ተቋማዊ ጽናቷ፦ ለተፈጥሯዊነት፤ ለሰዋዊነት የምትሰጠው ልዩ አትኩሮት፤ ፈርኃ እግዚአብሄር ተሰጥዖዋ ለዓለም ህዝብ የትምህርት ካሪክለም ሊሆን የሚችል ነው። ሥልጡን ህሊና ሥልጡን ትውልድ ማፍራቱ አይቀሬ ነውና። ስለሆነም ወደብ ሳይኖራት ሁሉ ያላት አገር መሆን ችላለች። ምርቃቱ በዝቀሽ ከድርጊቷ መልካምነት የተገኜ ነው።
ኢትዮጵያ ግን የተቋምም፦ የቲም መር ፖለቲካ የላትም። ፖለቲካው ቂም፤ በቀል፤ ጥላቻ ጦርነት ገብ ብቻ ሳይሆን የትሩፋት ተከታታይነት ሳይሆን የነቀላ ፍቅር ነው ያለው። ይህም ስለሆነ የነበረን በመቀናነስ ተዚህ ተደረሰ። ኢትዮጵያ የከበደችን ለሁላችንም ነውና።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ደህና እደሩልኝ። አሜን።
ሥርጉ©ተሥላሴ
Sergute©Selassie
07/05/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት ጋራጅ አያስፈልገውም።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ