ጎንደሮች ምከሩ። ማስተዋልን ዘክሩ።

 

ጎንደሮች ምከሩ። ማስተዋልን ዘክሩ።
 
"አቤቱ በመመስገኛህ ቦታ በጽርሐ አርያም
ሆነህ እኛን በዓይነ ምህረትህ ተመልከት።"
(መጽሐፈ ባሮክ ምዕራፍ ፪ ቁጥር፭)
 
የእኔ ክብር ቤተሰቦች እንዴት ሰነበታችሁ? ሰንበት እንደምን አለፈ? እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ ደህና ነኝ። እናንተም ደህና ሁኑልኝ። አሜን። በጣም ዘለግ ያለ ጹሁፍ ነው። 
 
 May be an image of 1 person and smiling
……… እንሆ ዛሬ ………
 
በእቴጌ ጎንደር ዙሪያ ትንሽ እል ዘንድ ፈቀድኩኝ። በ2014 እአአ በደጉ ዘሃበሻ እና ደጉ ሳተናው የጎንደርን ተሳትፎ በሙሉ ልባቸው በተቀበሉ ድህረ ገጾች በ፬ ክፍል ስለ ጎንደር ጽፌ ነበር። የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይንም አንድ ቀን ሊፈነዳ የሚችል የተዳፈነ ቦንብ እንደሆነ ኮልሜ ነበር። ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ በኽረ ብሄራዊ ዓለም ዓቀፋዊ አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል።
 
ምን ለማለት ነው ይሄ? አስፈላጊ ሲሆን እቴጌ ጎንደርን በሚመለከት ይጣፋል ለማለት ነው። ስለ ጎንደር ሲፃፍ፤ መልካም ሲነገር የሚከፋቸው እንዳሉ አውቃለሁኝ። እነሱም ፕሮ - ህወሃቶች ናቸው። አንድ ግለሰብ፤ አንድ ተቋም፤ አንድ ሚዲያ ተግቶ በፀረ ጎንደርነት ከሠራ ያ አካል ፕሮ - ህወሃት መሆኑ አስተርጓሚ አያስፈልጋችሁም። ፕሮ - ህወሃት ሆነው ኢትዮጵያኒዝም መለያችን የሚሉትም፦ ጎንደርን ከልባቸው ፈግፍገው፦ ፍቀው ስለመሆኑ ልብ ልትሉት ይገባል። ስለምን? ጎንደር ትቀደምልኝ የሚለው ኢትዮጵያን ስለሆነ፤ የኢትዮጵያ ምልክት ነኝ የሚል ሁሉ ከጎንደር መንፈስ ጋር ግብግብ ፈጽሞ አይገባም እና።
 
#የቅኔው የጎጃም ህዝብን በሚመለከት።
 
ጎንደሬ ነኝ የሚል ሁሉ በማስተዋል ሊራመድ የሚገባው የጉዞ ቅያሴ፦ የቅኔው ጎጃምን ማገዶነት ስለጎንደር ከውስጡ በዶግማነት ሊቀበል ይገባል። በዛ በጠቆረ፤ በዛ በጎሼ፤ በዛ ኮረኮንቻማ ህወሃት መረሽ ዘመን " ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳሽ." ብሎ እንደ ክርስቶስ እራሱን የሰጠው መላው የጎጃም ህዝብ በነቂስ ወጥቶ አደባባይ ላይ ድምጹን ብቻ ሳይሆን መኖሩን ቀራንዮ፤ ጎለጎታ ያደረገ ብልህ ህዝብ ነው ቅኔው ጎጃም። #ጎወች የጣና እና የአባይ ተክሊላዊ ጋብቻ ብቻ ይተረጉማቸዋል። ይህን ያመሳጠረ ህዝብ መቼውን ቢሆን የጉዞ፤ የመኖር መርኃዊ ማኒፌስቶ ሊሆን ይገባል።
 
የሊሂቃን ገጭ - ገው ይኖራል። ግን ይህ የሊሂቃኑ ገጭ ገው ተፈጥሯዊ ውህድ እኛነታችን ላይ ሳንክ በፍፁም ሊፈጥር አይገባም። እኔ አልደረስኩበትም ቤተሰብ እንደነገረኝ ግን ባህርዳርም፤ ከወሎ ሃይቅም የጎንደር ግዛትም እንደነበሩ ሰምቻለሁኝ። በሌላ በኩል የጎንደር ሊቃናት፤ የጎንደር ሊሂቃን አጤ በካፋን ጎጃም ድረስ ሄደው የአባትህን ዙፋን ተረከብልኝ ብሎ በትህትና ጠይቆ፤ ዕውቅና ሰጥቶ አጤ በካፋ እና እናታቸውን ክብርት እቴጌ ማርያማዊትን በክብር፥ በግርማ፥ በሞገሥ ወደ ጎንደር አምጥቶ ያነገሰ ኢጎን የሰበረ ዊዝደም ነው የጎንደር መንፈስ።
 
በኢትዮጵያ የነገሥታት ታሪክ ውስጥ ብጡሏ የንግሥት ምንትዋብ ታሪክ መሠረት የአጤ በካፋ የትዳር አጋርነት ስለመሆኑ በብልህነት እሰቡት። የተሰጠን ፀጋ፤ የቆዬልን በተግባር የፈካ ትውፊት ከጊዚያዊ የፖለቲካ ፍላት በላይ ነው። በሁለቱም ወገን የሰከኑ፤ የተረጋጉ በፈርኃ እግዚአብሄር፤ በፈርኃ አላህ መንፈስ የተቃኙ ሊቃናት እና ሊሂቃን ያስፈልጋሉ። ግልቢያ ለዊዝደም ስለማይጠቅም።
 
ግድፈት ሰው ሆኖ አለመፈጸም ሰውነትን የሚቀንስ ይመስለኛል። ይህ የእኔ ፍልስፍና ነው። ሰው አልሳሳትም ብሎ ሲያስብም፤ ሲመፃደቅም አይመቸኝም። ሰውነት ከሚገለጽባቸው በኽረ ጉዳዮች አንዱ ግድፈት ነው። ግድፈትን አዳምጦ ማረም ደግሞ ብልህነት ነው። ስለሆነም ሁሉም ላፒስ፦ ቡርሽ ሊኖረው ይገባል ውስጡን የሚያጸዳበት። እናም እንደገና የሚወለድበት የብሥራት ቀን ሊኖረው ይገባል። በሌላ በኩል ደግሞ በተመሳሳይ መንገድ መሰል ግድፈት ላለመፈጸም እራስን ማብቃት ይጠይቃል።
 
የውስጥ ጽዳት ከቅናት፤ ከምቀኝነት፤ ከበቀል እራስን ማራቅ የውስጥ አብዮትን ይጠይቃል። ይህ በፈቃድ የሚከወን በራስ እርምጃ እራስን የማዳን ወሳኝ ጉዳይ ይመስለኛል።
 
ከሁሉ በየዘመኑ የተከፈሉ መስዋዕትነቶችን፤ የተከወኑ የዊዝደም ስክነቶችን በጥንቃቄ ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ የየሰከንዱ አስተምኽሮ ሊሆን ይገባል።
 
ይህን ንዑስ እርዕስ ከመቋጨቴ በፊት የቅኔው እንቡጥ ዶር ቴወድሮስ ካሳሁን በዛ ግራጫማ ዘመን የጎንደርን መንፈስ እንደ ታቦት የከበከበት ደፋር እና ጥልቅ ምጡቅ ቅኔ፤ ያስከፈለው መስዋዕትነትም በህሊና ሙዳይ እንደ ታቦት ተቀርፆ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊሸጋገር ይገባል። ኑርልን አጤ ቴዲ አፍሮ፤ በዘመኑም አጤ አስቻለው ፈጠነም ጣዝማነትህ ፈውሶኛል። እግዚአብሄር ይስጥልኝ አሜን። በእነኝህ በቅኔው የጎጃም ህዝብ፤ በቴዲአፍሮ፤ በአስቼ በሦስት አመክንዮች ጉዳዬ ወጥ አቋም ሊኖረን ይገባል። ውስጣቸውን ለጎንደር መንፈስ የፈቀዱ ሽልማቶቻችን ናቸውና።
 
"#ኑ ጎንደርን እንሞሽር ሞቶ።" ያስነሳው ንቅናቄ ……
 
ይህ ቃለ ምህዳን ብልጽግና ሠራሽ አይደለም። በዛ ልክ የተነተኑ፤ የበዬኑ፤ ያቃለሉ ወገኖቼን አይቻለሁኝ። እኔ ሙሉ ዕድሜ ላይ ነኝ። ሳድግም ሙሽራዋ ጎንደር የሚለውን ስንኝ እዬሰማሁ ነው ያደግኩት። በጥበብ ዘርፍም ከጎንደር አመሠራረት ታሪክ ጋር የተጣበቀ ሳይሆን እንደ ቀይ የደም ሴል ውህድ ማንነቷ ነው ለጎንደር ሙሽርነት። ትውፊቷ ስለሆነ ይህን ትውፊት መከብከብ የተገባ ነው። ትውፊትን ማስቀጠል በቁስ ብቻ ሳይሆን በመንፈስም ነውና። 
 
የእኔ 7ቱ መጸሐፍቶቼ አገላለፆቹ በሙሉ በትውፊቴ ልክ ነው። መፃፍ ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ ሙሽራ ቃላትን ለአደባባይ ማብቃት ግዙፋ #ፕሮጀክቴ ነው። እንደ ጥሪዬም ነው የምቀበለው። በሌላ በኩል ሙሽራዋ ጎንደር የሚለውን ቃል ስሰማ የሰራ አካላቴ ቋንቋ ልዩ ዜማዊ ቃና አለው። ያናግረኛል፤ ያወያዬኛል፤ ያጽናናኛል፤ አይዞሽ ይለኛል፤ ብቻዬን እንዳልሆንኩ ይተረጉምልኛል፤ በባዕቴ መንፈስ ውስጥ እንደ ሰከንኩ ያመሳጥርልኛል። ሐሤት አገኝበታለሁኝ።
 
ሁልጊዜ በሐሤት እና በደስታ መካከል ልዩነት እንዳለ አበክሬ እገልፃለሁኝ። ደስታ ጊዜያዊ እና ሰው ሠራሽ፤ ሐሤት ግን ሰማያዊ እና ቋሚ እንደሆነ አምናለሁኝ። ስለሆነም ሙሽራዋ ጎንደር ልሳኑ በራሱ ለእኔ ሐሤቴ ነው። መቀጠሉ ቁምነገሬ ነውና።
 
በዚህ አጋጣሚ በጎንደር ጥላቻ አይቼበት የማላውቀው ጋዜጠኛ መሳይ መኮነን "ማን ሊያገባት ነው ጎንደር የምትሞሸረው" ሲል ዕርዕስ ሰጥቶ አይቻለሁኝ። እኔ ልመልስልህ ወንድም ዓለም ጎንደር የዕድሜ ልክ ሙሽራ ናት። ጎንደር በድንግል እና አግብታ የኖረች ሁልጊዜም እሸት መንፈስ ያላት በዓት ናት። ጎንደር ፈትም፦ ባል ፈላጊም ሆኖ በዘመኗ አታውቅም። 
 
ባለቤቷም #ዓጤ #ዊዝደም ይባላል። ዊዝደም በመዳፋ ያለ ግርግር፤ ግብግብ፤ ዝልግልግ፤ ዝርክርክ፤ ጥድፊያ፤ ቅናት እና ምቀኝነት፤ በቀል እና ጥላቻ እንዲሁም ጎርፍ ግጥሙ ያልሆነ መንፈሷ ነው። የጀመረውን በትኖ/ ወይንም በትና እንደ ፌንጣ በሚዛለል የፖለቲካ፤ የማህበራዊ ትርምስ ውስጥም ልባሟ ጎንደር አትነከርም።
 
የፎቶ ሸው፥ ከንቱ የውዳሴ ትርምስ፤ የአሬንሻታ ኳኳቴ የማያሰኛቸው አንገተ ደፋታ ልጆቿ ገድል እና ታምርን "በሙያ በልብ" እዬከወኑ ጥቃቷን ያወጡላታል። ያ ከእነሱ አልፎ ለሌላውም ሹመትና ሽልማት ያስበቃል። እቴጌ ጎንደር ከየትኛውም የመኖር ሚስጢር ቋት በላይ ናት። ልጆቿ በሚጥሩት ልክ የተሰጣቸውን ለብሄራዊነት እንዳያውሉ በዬፌርማታው ማነቆ አለ እንጂ የዊዝደም ልጆችማ አሏት። ማጫቸው ዊዝደም ነው ልጆቿ፤ ጥረታቸው አንድ ጥይት ሳይተኮስ፤ አንድ ቤተሰብ ሳይጎዳ፤ አንድ የአገልግሎት ተቋም ሳይታመም በዝምታ ውስጥ ዕንቁ ስኬትን ያሰክኑታል።
 
ይህ ለጨዋታ ማሟያ እንዳይመስልህ ልጅ መሳይ መኮነን። ከሠራዊት በላይ በቀንጣ ባተሌ የሚከወኑ ዝልቅ እና ሰብላማ ተግባራት አሉ። ፀጋው ክስተታዊ ነው። በእኛ ተፈጥሮ እዩኝ እዩኝ የለም። የወረትም አይታሰብም። ምንጊዜም ዝንፍ ስንል በዓታችን እንድትሳቀቅ ስለሚሆን እንጠነቀቃለን። ጎንደር ለእኔ ዩንቨርስቲዬ፥ የፊደል ገበታዬም ናት። ምግባሯ በሞራል የጸደቀ - የሚያጸድቅም ነው። 
 
የሆነ ሆኖ ማይክ የያዘ፤ መድረክ ያለው ሁሉ አሻቅቦ እቴጌ ጎንደርን ሲዳፈሯት ይገርመኛል። አንድ ፔና ገዝቶ ያስተማረን፤ አንድ ሜትር ጨርቅ ገዝቶ ያለበሰን፤ አንድ ወር የሚመግብ ቀለብ የሰፈረልን ያለ ይመስል ለማገዶነት፤ ለአንጋችነት፤ ለመቃጠል እና ለመንደድ፤ እንዲሁም ለመማገድ እና ምድር ውስጥ ለማርጀት ደግሞ ግዴታው ጫን ተደል ነው። 
 
ጎንደርን ለመምራት፤ ጎንደርን ከጎን ለማሰለፍ የሚጠይቁ ጥልቅ #ዲስፕሊኖች አሉ። አይደለም በስማ በለው ተወልደን፤ አድገን፤ ተምረንባት፤ ሥራ ተቀጥረን፤ አደራጅተን እና መርተንም እሷን #አንጋጠን ለማዬት አንደፍርም። ያለልክ የተሰፋ ጥብቆም፦ ሽብሽቦም ስለማያሰኜን። "ልክን ማወቅ ከልክ ያደርሳል" ዶግማችን ነውና።
 
ዕውነቱ ጎንደር #ትዘልቃለች! ጎንደር ኢትዮጵያንም #ታዘልቃለች!
 
#ጎንደር ዛሬ፤ ጎንደር ነገ፤ ጎንደር ከነገ በስትያ ቀጣይነቷ የፈጣሪ የአላህ እንጂ ሰውሰራሽ አይደለም።
 
ቀዳማይ እመቤትነት ለጎንደሬወች ብርቃችን አይደለም። የተሰጠን ፀጋችን ነው። ቤተ - መንግሥት መግባት ብቻ ይሆናል የሚታዬው። አይምሰላችሁ እንደዛ። በተማላ ኑሯችንም በዓታችን አስከብረን፤ መሠረት ያለው ምግባርም፤ የተባ ተግባርም ከውነን ተከብረን ነው እምንኖረው። ደልዳሎች ነን። በውነቱ እንቅለልም ብንል አያምርብንም። አልተሰጠነም፤ አልተፈጠርንበትም፤ አላደግንበትም እና። ደርባባወች ነን። ድልድል የሚል የሴት ሥም መጠሪያ ሥያሜ ጎንደር አላት። የጨዋ ሰፈሯ ድልድል ላቀው። እራሷን ስታመሳጥር።
 
ምን እንዳለን፤ ምን እንደ ተሰጠን፤ ምን እንደሚፈቀድልን፤ ምን ደግሞ እንደማይፈቀድልን የመብታችን እና የግዴታችን ጣራ እና ግድግዳ አሳምረን ጠንቅቀን እናውቃለን። ከማንኛውም ሰው ጋር በሚኖረን ግንኙነት የተክለፈለፈ እንዲሆን አንፈቅድም። በቆይታችን በሰከኑ ሁነቶች ሰክነን፤ ስንለይም ያተረፍነውን ስክነት ጥበቃ አድርገንለት በእሱ ሐሤታችን በማስቀጠል ነው። ቂም እና በቀል ጥዩፍ ነው በአስተዳደጋችን።
#ፈላስፊት ኢትዮጵያን በሚመለከት ለክብሯ በሚመጥን ሁነት ሁሉ እኛን ማስገኜት፤ ክብሯን ሆነ ልዕልናዋን በሚነኩ ቅንጣቶች ደግሞ ሃራም ባዮች ነን። ቤተሰቦቻችን በቤታችን ውስጥ ሲያሳድጉን ወተታችን አድርገው የሚያሳድጉን የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ነው። 
 
#በሳይንቲስቷ ኢትዮጵያ ላይ ቂም ይዘን፤ አኩርፈን እንድናድግ ተፈቅዶልን አያውቅም። ፈጽሞ። 
 
ስለሆነም እርምጃችን ይሁን እንቅስቃሴያችን፤ ተስፋችን ይሁን ምኞታችን በልካችን ተከርክሞ በሥርዓት ተኮትኩቶ ያደገ ነው። ሥርዓት፤ ህግ፤ ደንብ የሰማዩም ይሁን የምድሩ ገዢያችን ነው። ሥርዓተ አልበኝነት ግጥማችንም አይደለም። እርግጥ ነው ከቅንጣቱ እስከ ገዘፈው የመኖራችን ሂደት ሳንክ አይለቀነም። እንቅፋት ሸማችን ነው በነፍስ ወከፍ። ይህን በጎንደር ላይ በሚወርደው ማዕት ማዬት ይቻላል። እኛ ግን ያደግንበት በራስ የመተማመን ክህሎታችን በቂ ጥበቃ ሰለሚያደርግልን ዝንፍም፤ ዛልም ብለን አናውቅም።
 
በዚህ በጠቀስኳቸው የሕይወት ፍልስፍናወች ውስጥ ፈቅደው መኖርን የመረጡ ጎንደሬወች እንዳሉ ሁሉ፦ ክብራቸውን ጥለው መጭ የሚሉም ይኖራሉ። መጨረሻቸው ግን አያምርም። ከአባት አደሩ ይትብኃል ማፈንገጥ የገደል ግጥም ነውና።
#የፕሮ ህወሃቶች ሂደት እና ስኬት።
 
ስለ ህወሃት ከልጅነት ጀምሮ የማውቀው፤ የታገልኩትም፤ የሞገትኩትም፤ በፈቀድኩት፤ በምፈልገው ሁኔታ በኃይል፤ በጉልበት ሳይሆን ህወሃት ወዶ እና ፈቅዶ መንበረ ሥልጣኑን በሰላም መልቀቁ ለእኔ የሰማይ ትንግርት ነበር። ያን የሰማይ ትንግርት መንከባከብ፤ ጥበቃ ማድረግ፤ ለሥጦታው ዕውቅና ሰጥቶ ማክበር ይገባኝ ስለነበር፦ ህወሃትን በሚመለከት በ፯ ዓመታት ውስጥ ለስለስ ያሉ ከሦስት ያላልበለጡ ጹሁፎች ብቻ ነበር የፃፍኩት። ወደፊትም ዕምነቴ ያ ነው።
 
ህወሃት ምክንያታዊ በሆነ አመክንዮ ከጎንደር ጋር ፋክክር አለበት። በዚህ ምክንያት ጎንደር በስኬት ጎዳና እንድትሆን አይሻም። ያው ተፎካካሪ መንፈስ ስላለው። ይህም ተፈጥሯዊ ነው። ብዙ እርር ኩምትር የሚያደርግ፦ የሚያነጫንጭ አይመስለኝም። አንዱን ቅንጣት ኩነት ባነሳ ፋሲል ከነማ ለህወሃት የእግር ኳስ ቲም ብቻ አልነበረም። ከዛ ይዘላል። ከዛ ይዘልቃል። ግን ከጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ዘመን የእርዳታ የማሰባሰብ ጊዜ በኋላ ፋሲል ከነማ የት ገባ???
 
ወደ ቀደመው ምልሰት ሲሆን በብዛት እና በስፋት ያለው የትግል መስመር ከመሼ የታዘብኩት ፕሮ - ህወሃት፤ ፕሮ - ኢህአዴግነት ነው። የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ውስጥ ዳጥ እና ምጡ ክስተት ይህ ነው። ፕሮ - ህወሃትነት እና ጎንደሬነት???? #መታረቅ፤ ምህረት መፍጠር አንዱ ትርጓሜው ነው፤ ሌላው መገራት ሁለተኛው ትርጓሜው ነው፦፦፦፦፦፦፦፦ ይችላሉ ወይ? ፋኖነት ከህወሃት ጋር ተቃቅፎ የአማራን የማንነት እና የህልውና ዘላቂ መፍትሄ ያስገኛል ብሎ ማሰብ ፀሐይ - ጨረቃን፤ ጨረቃም - ፀሐይን ይተካካሉ ማለት ነው። የጎንደር ሊቃናት እና የጎንደር ሊሂቃን በማስተዋል መምከር፤ ማስተዋልን መዘከር ያለባቸው ከዚህ ዕንቁ የሚስጢር #ጓል ተነስተው ሊሆን ይገባል። በተለይም ዕውነተኛው የአማራ ፋኖ በጎንደር። 
 
የፋኖ ንቅናቄ በጎንደር ለጎንደር ከተማ ልዩ ጥበቃ፤ ልዩ ጥንቃቄ ሊያደር ሲገባ ጎንደር ከተማ ላይ ነበር አብሪ የነበረው። አመራሩ ከዬት እንደፈለቀ ሻለቃ ዳዊት ከሰጡት መግለጫ አዳምጫለሁኝ። ያ መንፈስ በጎንደር ልክ መጥኖ???? ጎንደር የጀንበር ከተማ አይደለችም። የዓለም ዓቀፍ ፖለቲካ ህሊና የሆነች አናት ናት ጎንደር። በጎንደር ጉዳይ ላይ የፋንታዚ ልዑል መሪ አያስፈልግም ነበር። ብልህ ቢገኝ። ውጭ አገር የተቀመጡ እስከ ዶክትሬት የደረሱትም ቢሆን ለጎንደር ምን አድርገውላት ይሆን ጎንደር መቋዲሾ እንድትሆን የበዩንት??? በውነቱ እንደ ዕምነታቸው ንሰኃ ሊገቡ ይገባል።
 
በሌላ በኩል ስክን ያለው ፋኖ ምሬ ወዳጆ እንደምን ለእናት ደሴ፤ ለኮንበልቻ፤ ለሐይቅ፤ ለወረባቡ፤ ለወልድያ ልዩ ጥበቃ እንዳደረገ፤ የአበው እና የእመውን ዊዝደም እንዳላፈሰሰ ሳስተውል ዕውነትም ዋርካ ብያለሁ። አንድም ብሄራዊ አጽዋማትም አልተስተጓጎሉም። ፍስካቸውም ማቅ አለበሰም። ብሩክ አስተዋይ መሪ። 
 
ላልጠፋ ዱር እና ገደል? ላልታጣ የተፈጥሮ ጉድብ እና ዋሻ የጎንደር ከተማ ህፃናት፤ ሴቶች፤ አዛውንታት፤ ሆስፒታል ውስጥ የነበሩ ህሙማን፤ ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪወች፤ ጎንደርን አምነው ልጆቻቸው በጎንደር ዩንቨርስቲ እንዲማሩ የፈቀዱ የኢትዮጵያ እናቶች አደራ፤ የአብነት ተማሪወች፤ የረመዳን እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አፆማት፤ የሱባኤ ሥርዓታት፤ የምህላ ይትበሃል፤ ትውፊታዊ አርምሞ ሁሉ በስጋት ጅራፍ እንዲቀጡ፤ እንዲሸማቀቁ፤ እንዲርዱ፤ ከባዕታቸው እንዲነቀሉ ማድረግ እና ማስደረግ ህወሃት በጦርነቱ ወቅት አልሞ ያልተሳካለት ቧ ባለ ፈቃድ የተከወነለት መከራ ነበር። ህወሃት በጎንደር መሰቃየት አትርፎበታል። ይህ የፕሮ - ህወሃቶች ስኬት ነበር። 
 
ጎንደር አንድ የሳቅ ቀን አላት። ሰሞነ አስተርዬ። አንደኛው የጥምቀት በዓል ወደ 28 ጊዜ የአዬር በረራ ነበረው። በአውቶብስ ቢቻል ከዛ በላይ በሆነ ነበር። የገብሬ ጉራቻ መስመር ሰላም ቢያገኝ በኩንትራት መኪኖችም ብዙ ወገኖች ዕድል ይከፈትላቸው ነበር። ያም ሆኖ በአውሮፕላን የቻለው ወገን ተገኜ እና ሳቁን ዳሩት - ኳሉት። ያን እቦታው ተገኝቶ ለማደፍረስ ያደባ መንፈስ በዕለቱ ነበር። እኔ ውስጤ በስጋት ይርድ ነበር።
 
ያ መንፈስ እንግዳ በዓል ለማክበር የመጣን የጎንደር ወጣቶች ተቆጥተዋል ተብሎ እንዲመለስ አስደርጓል። ዘገባውንም እነርሱ ነበር የሰሩት። ማን ይሆን ምን ለጎንደር ህዝብ እንግዳ ክብሩ ነው። ያ ትውፊት ተጥሶ ተጠቅጥቆም፤ ሃግ የሚልም ጠፍቶ በሩ የተዘጋባት ተመላሽ እንግዳ ኖራት እቴጌ ጎንደር ሲባል አብረን ማፈር ይገባናል። ጠያፍ እርምጃ ነበር። ሁነቱ በቀል ጠነሰሰ እና የወይብላ ማርያም ልጆች ተገበሩበት። አንገት የተሠራው አዙሮ ለማያት ነው።
 
በዛው ሰሞን የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ጋር ሰፊ እሰጣ ገባ ነበረው። ለዛ ደግሞ ቅድስታችን ዘመን ናት እና እራሱን የቻለ ያወቀ፤ በበቃ ሚስጢራት የተካነ ተቋም አላት። እሷን እተካለሁ ማለትም አይገባም ነበር። ቤተክርስቲያናችን የራሷ ዶክትሪን አላት። እመ እዮቢት ለራሷ አታንስም።
 
ይህን ያደረጉ ወጣቶች ጽዋ ሚዲያ ላይ ቀርበው ሲያስረዱ ሰምቻለሁኝ። ጎንደር የአብርኃም ቤት ናት። እንግዳ የሚናፍቃት፤ እንግዳ የምትወድ፤ ለእንግዳ ልዩ ክብር እና ማዕረግ ያላት እናት ሆና፦ ይህ ፈቃዷ ባልሰከነ ስሜት ተስተጓጎለ። ቅሬታም አጨ። እኔ ሳድግ የገና በዓል ነዳያን ድንኳን ተጥሎላቸው በቁርጥ እና በጥብስ እንዲገድፋ ይደረግ ነበር በአብርኃሙ በእነመላከ ብርኃናት ዓውደ ምህረት። ይህ ልዩ ትውፊት መንፈሱ ነው የተጠቀጠቀው።
 
የሆኖ ሆኖ የጥምቀት በዓሉ እንደምንም ተከበረ። ግን ያ ድምቀት፤ ያ አጓጊ ሂደት አልተደገመም። ለዛውም የጥምቀት በዓል በዩኒስኮ በተከበረ በዓመቱ ነበር ይህ የሆነው። ቁልጭ ባለ አማርኛ የህወሃት ፈቃድ ደልደል ብሎ ተፈጸመ። ይህንን ነው የጎንደር ሊቃናት፤ የጎንደር ሊሂቃን በማስተዋል ሊመረምሩት የሚገባው።
 
አስተርዬ በጎንደር የሰናይ፤ የብሥራት፤ የምስራች፤ የትዳር፤ የቱሪዝም፤ የቤተሰባዊነት፤ የንግድ፤ የባህል፤ የታሪክ፤ የእብሮነት፤ የእቅፍቅፍ፥ የትሩፋት፤ የፍቅር ተፈጥሮ ፍካት መገለጫ ነበር። ግን "ነቅናቂ ሳለ ማን ጥሩ ይጠጣል" ሆኖ ማዕረጉን አስገፈፋት። ባለዋቂ ሳሚ ፈንታዚ አራማጆች። 
 
ይህንኑ ቅራኔ እንዲያመረቅዝ ያን ቀንበጥ ታይቶ የማይጠገብ ሙሽራ ወጣት ናሆሰናይ እና አበኔዘር የጥምቀቱ ሳይጎረብጥ ሌላ ውሽልሽል ፕሮጀክት ተሰርቶ ጎንደር እና አዲስ አበባ፤ ጎንደር እና ማዕከላዊ መንግሥት ያመረቀዘ ቅራኔ ውስጥ እንዲገቡ ታቅዶ ተከወነ። ይህ ለጎንደር አዲስ ትውልዳዊ ተስፋ ይጠቅማልን? ዳኙት! 
 
ህወሃት ዕድል አግኝቶ ጎንደርን ቢቆጣጠር ከዚህ በላይ የታቀደ መሰሪያዊ ተግባር ይፈጽማልን? አቤቱ ህወሃት ምንም ወጭ ሳያወጣ ነው ጎንደር ከተማ እና ተስፋዋ ከእሳት እንደገባ ፕላስቲክ ኩምትርትር እንዲል የሆነው። 
 
በሃሳብ ሙግት እኮ እኔ የጠሚር አብይ አህመድን መንግሥት እኮ እሞግታለሁኝ። አይደለም? ግን ቅንጣት የጎንደር ትውፊትን በሚፈትን፤ ህዝቧን ፈተና ውስጥ በሚከት፤ ጎብኝወቿን በስጋት በሚንጥ ምልከታ እና ድርጊት አይደለም። 
 
እስኪ ይሳካላችሁ ብዬ ላስብና፥ የሚመጣው ጠቅላይ ሚኒስተር ማን እንደሆን፤ ካቢኒወቹ እነማንን እንደሚያካትት? እርግጠኛ የሚያደርግ ምን አላችሁ?
 
/በየዘመኑ - ማገዶነት፤/
/ በዬዘመኑ - አንጋችነት፤;
/ በዬዘመኑ - ቃጠሎነት፤/
/ በዬዘመኑ ለስጋት ድግሥ ማሰናዳት አይሰለቻችሁም? ----- አይደክማችሁም?
 
 ለመሆኑ የጎንደር መንፈስ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኢሊት ስለጎንደር ምን እንደሚያስብ እምታውቁት ሚስጢር አለን? ይህ ዘመን የሰጠን ሚስጢር ቢኖር እስከዛሬ የተማገድንላቸው ፖለቲከኞች የማናውቃቸው መሆኑን ነው። አናውቃቸውም የኢትዮጵያን ፖለቲከኞችን። ዕውነቱ ይህ ነው። ስለሆነም ስለነሱ ተብሎ #የሚቃጠል ዕድሜ፤ የሚነድ ንፁህ መንፈስ፤ የሚሰቃይ አቅም፤ የሚባክን ክህሎት ሊኖር ፈጽሞ አይገባም።
 
///ትናንት ለእነ እከሌ፤///
/// ዛሬም ለእነ እንቶኔ/// ……… ጎንደር ተማገደች፤ ነገስ ለየትኛው እንቶኔ --- ማን ለመገበር? ማንን -- ለመማገድ ተዘጋጅታችሁ ይሆን? የኢትዮጵያ ፖለቲካ እርካታ ቢስ ነው። ነገ ደግሞ ከፋኝ የሚል ሲመጣ ያው ጎንደር ለእርድ ትሰናዳለች። መጥኒ………
 
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትንተናውን እዩት፤ የደም ፍላቱን ለኩት። በአመዛኙ ቅናት ነው። የተሻለ አማራጭ ተቋም ቀርቶ የተሻለ ሃሳብ ምርቅ ነው። ይህ በሌለበት መኖርን መገበር??? 5ሚሊዮን የአማራ ልጆች ከትምህርት ገበታቸው መስተጓጎል፤ የሚማሩትም በስጋት ውስጥ ለመማር መገደድ??? ፈቅዶ እና ወዶ ኋላቀርነትን ማጨት - መዳር እና መኳል ያውም በማጫ ነው። ዕውቀት እንደምን ማዕቀብ ይጣልበታል? ብርኃን ወይንስ ጨለማ የቱ ይሻላል?????
 
#ሚዲያ እና እቴጌ ጎንደር።
 
በዘመነ ህወሃት ጋዜጠኛው፤ ሚዲያው፤ ጸሐፍቱ በርከት ያሉ የጎንደር ተሳትፎ ነበረባቸው። እነሱም ቢሆኑ የጎንደር ሊቃናት እና ሊሂቃንን የሚከበክቡ፤ እገዛ የሚያደርጉ፤ ቀና እንዲሉ የሚደግፋ አልነበሩም። ማዶ ማዶ የሚያተኩሩ እንጂ። በአብይዝም ዘመን ደግሞ #ተለሞጠ
ስለሆነም ፕሮ - ህወሃት ሚዲያወች የሚያስቡት ሙሉ ፓርላማ፤ ሙሉ የፌድሬሽን ምክር ቤት፤ ሙሉ የቤተ መንግሥት አማካሪ፤ ሙሉ ካቢኔ፤ ሙሉ ምክትል ሚኒስተር፤ ሙሉ የመንግሥት ሚዲያ፥ ሙሉ የብልጽግና ከፍተኛ አመራር ከቁንጮ እስከ ታች ድረስ በጎንደር ሊቃናት የተሞላ ተደርጎ ነው፦ ጎንደር ቁሚ ተቀመጭ ስትባል ውሎ የሚታደረው። ያለው መንፈስ ቃር ነው። ይህንን የሚመክት ሚዲያ ጎንደሮች የላቸውም። ለምን???
 
አንድም ከሌላ በዓት የተፈጠረ የብሎጽግና ሹም፥ ሊቅ ሲወቀስ፤ ሲነቀስ ሲብጠለጠል አትሰሙም። ከሆነም በስሱ ነው። የጎንደር ልጅ ግን በነቂስ እዬታደነ ፍዳውን ያሳዩታል። ብልጽግና መሆን እኮ መብት ነው። ብልጽግና አለመሆንም መብት እንደሆነው ሁሉ። የዴሞክራሲ ፍልስፍና መብት እና ግዴታን አጣጥሞ መቀበል ነው። የማይመች ሃሳብን ታግሶ መቀበል፤ እና ሞግቶ በፋክት ብልጫ መውሰድ ነው። ይህ የለም። የሚገርመው የኢትዮጵያ የአዬር ጠባይም እንደ አብይዝም ነው የሚታዬው። የሥርዓቱን ድክመቱን ነቅሶ አውጥቶ መሞገት ይቻላል። 
 
አንድ ከሌላ በዓት የተገኜ ጋዜጠኛ በሰባዕዊነት ከተጋ ዱላ ይሰናዳል ለአንድ ጎንደሬ ጋዜጠኛ የብልጽግና አገልጋይ ተብሎ። በሌላ በኩል ደግሞ ትጋት ያላቸው አራት ዓይናማ የጎንደር የሰባዊ መብት ሞጋቾች ብልሆች ደግሞ ይሳደዳሉ። እቴጌ ጎንደር ደመ መራራ ናት። እንደ ሰውም በጽኑ የሚቀናባት መሆኗን የተረዳሁት ከበፊቱ አሁን ነው። ዘመኗ ሁሉ ሰላም እንድታጣ የሚሠራባት ባዕት ብትኖር ጎንደር ናት። ፈጣሪ አላህ ይጠብቃት እንጂ ……… ጎንደር ሰው የሚኖርባት፤ ጎንደር መኖር የሚሰለጥንባት በዓት መሆኗን መቀበል የተሳናቸው ሰብዕናወች አያለሁኝ።
 
 አብዛኞቹ ሞገስ በአማራ ተጋድሎ ያገኙ ናቸው። ለዛ ያበቃቸው የሃምሌ 5ቱ የጎንደር አብዮት ነው - ቢያውቁት።
ጎንደር ለአማራ ትግል የከፈለችው መስዋዕትነት፤ ጎንደር በዘመኗ ሁሉ ስትገበር መኖሯ ዕውቅና የሚሰጠው እንብዛም ነው። ይህ ከሆነ የጎንደር ሊቃናት፤ የጎንደር ሊሂቃን በአደብ ሊመክሩበት ይገባል። ለማንኛውም ተሳትፎ ጎንደር የማታስፈልግ ከሆነ የጎንደር ልጆች ከአምላካቸው ጋር ሊመክሩ ይገባል። የራሳቸውን መንገድ መፈለግ ዘመን የጠዬቀው በኽረ ጉዳይ ይመስለኛል፤ 
 
#በአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ በማገዶነቷ ልክ ጎንደር ምን ተጠቀመች?
#ከሃምሌ 19/2010 ዓም ጀምሮ እስከ ፋኖ ንቅናቄ 2017 ድረስ ሊቃናቷ ተለቅመው ተመነጠሩ።
#ዕድገቷ ተስተጓጎለ።
#የቱሪዝም ፍሰቷ ተጨናገፈ።
ሳቋ ፍሰኃዋ -----ተጉላላ።
ተስፋዋ ---- አጎፈረ።
ምኞቷ --- ጎሽቶ አጎረፈ።
 
የሚፈለገው በጥልቀት ስታጠኑት ህወሃት ማረኝ ብላ እቴጌዋ አደግድጋ ከጨካኟ ሥር ምህረት ትጠይቅ ዘንድ ነው እዬተሠራበት የሚገኘው። ቁልጭ ያለው ፋክት ይህ ነው። ቅንነት የሚገዛን ሰብዕናወች የሰጠነው ድጋፍ ሁሉ ለጎንደር ክስመት፤ ለህወሃት እንደገና መንሰራራት ጉዝጓዝ ነው የሆነው። ሽልማቱም --- ዕውቅናውም። 
 
#ዘመቻ እከሌ በጎንደሬ ህልፈት ነው የሚታለመው። 
 
ቀዝቀዝ ሲል ማሟቂያ የጎንደሬ ደም ፍሰት -- ይታጫል። የሚገርመው መስዋዕትነቱ የጎንደር ሆኖ የፊት ሽፋን አዬር ላይ ኃይላት የሚደረገው የሌላ ፋኖ መሪ ነው። የሚገርመው ተግባራቸውን አጽድቀን፦ እንደታቦት ከብክበን ጉልላት ያደረግናቸው መንፈሶች ይህን ሲፈጽሙ ስታዩ --- ታዝናላችሁ። ቢያንስ መገበሩን ዕውቅና መስጠት ከተሳነ፦ የጎንደር ማገዶነት --- ለማን? ስለማን --- ተብሎ መጠዬቅ የጎንደር ሊቃናት፤ የጎንደር ሊሂቃን እንደምን አቃታቸው? ይህ ጨምተው ሊመክሩበት የሚገባ በኽረ ጉዳይ ነው። ጥሞናም ሊወስዱ ይገባቸዋል --- ጎንደሬወቹ። 
 
እዚህ ላይ አንድ መራራ ሃቅ ልገልጽ እፈልጋለሁኝ። የተከበሩ ኮነሬል ደመቀ ዘውዱ ፋኖን ተቀላቅለው ቢሆን ኖሮ፦ እስከ አሁን ድረስ በህይወት እንዲኖሩ አይፈቅድላቸውም ነበር። እሳቸው በማስተዋል ስለሚራመዱ፦ ራዕያቸውም እሳቸውም እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ ህልው ናቸው። ተመስገን። አመዛኙ መንፈስ የህወሃትን ግብ ለማሳካት ነው። ህወሃት በምድር ማን ከህይወት እንዲሰረዝ ትፈልጋለህ ቢባል "ሁሉም ቀርቶብኝ ጭምቱን ኮነሬል ደመቀ ዘውዱን" እንደሚል እሙን ነው። ልብልክም ነው።
 
በስሱ የአማራን ጥያቄ ለማስመለስ ይባል እንጂ፤ ወሳኙ ጉዳይ ጉልህነትን ለማግኜት ከኮነሬል ደመቀ ዘውዱ የአማራ ፒላርነትን ለመዝረፍ ለፋክክር የታለመ ክስተት ነው እያስተዋልኩ ያለሁት። ጎንደር አልገባትም፤ አልተረዳችም። ክብርን ፈቅዶ ለመግፈፍ መፍቀድ ምን የሚሉት ጅልነት ይሁን???? በጋመ ቋያ እንደ በሳት ተፈትኖ የፈለቀውን የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ህሊናን ትቶ ሌላ?? የፋክክሩ ምክንያት አቶ ጃዋር መሃመድ (ሃጂ) የማህበራዊ መሰረቱ ባለካስማነት የፈጠረው ፋክክር ነው ይህን ስሜት የወለደው። ሰው በሰራው ስኬት አርቲፊሻል ቦይ ፈጥሮ መፍጨርጨር -- ያስተዛዝባል። ይህን ዕውነተኞቹ የጎንደር ፋኖወች ከውስጣቸው ሆነው ሊመረምሩት ይገባል። አጤ ዊዝደምን አክብረው ይጥሩት። ማን በማን ሊተካ??? 
 
ሰማዕቱ ዶር አንባቸው መኮነን ሦስት ወር ሰላም አላገኙም። ዶር ገዱ አንዳርጋቸው ሳሉ ጸጥ ያለው ሁሉ በዶር አንባቸው ጊዜ ነጋ ጠባ ጉዞ ከአዲስ አበባ ወደባህርዳር ነበር። ማዕከላዊ መንግሥት ጥርጣሬ እንዲያድርበት ምቹ መደላድልን ማን አበጀው? ከዛ ጎንደር ልትማር ስላልቻለች ቀይ ሽብር በጎንደር ይነግሥ ዘንድ ተፈቀደ። "በሞኝ ክንድ" እንዲሉ።
 
ምን ሲባል የጎንደር ፋኖ ከሁለት፤ ከሦስት ይተረተራል? ለማን - ተብሎ? የጀግና ጎቤ መንፈስ እንደምን በእናንተ የልዩነት ሰቅ ይሰቃያል???? ጎንደር አንድ አህቲ ፀጋ እና መንፈስ ነው ያላት። ይህን መተላለፍ አይገባም። "ሸማ በዬዘርፋ ይለበሳል" ብሂላችን የት ገባ??? ሁልጊዜ የደከሙበትን መጠሪያ በብላሽ አሳልፎ መስጠት? ልብ በማስተዋል ከቀደምቶቹ ቢቀዳ ጥሩ ነው። 
 
የሚገርመው የትጥቅ ትግል እዬመራህ፤ ሰላማዊ ታጋይ ነኝ ቧልትም አለ። የወደመው፤ የደቀቀው መንፈስ ከግምት በላይ ነው። በዬትኛውም ዘመን ከገጠመው ድቀት በላይ ነው የሆነው። የሰሞኑን የሻለቃ ዳዊትን ቃለ ምልልስን አዳምጡት። የእስክርቢቶ ቀፎ የተሰበረ ያህል ህመም የለበትም። ሊጠዘጥዝ ፦ሊቆጠቁጥ ይገባል፥ ለማይዘልቅ ድርጅት እና መንፈስ አብሮ መሥራት ያ ሁሉ ውድመት ጋር መተባበር። የደብረ ኤልያሱን መከራ ከውስጣችሁ አስቀምጡት። የጥሪት ቅርስ ነው የተቆራረሰው። መቼውንም የማይገኝ።
 
ሰሊጥም ፍርደኛ ነው። በዘመነ ህወሃት ለግብይት ሲጓዝ አቤቶ ሰሊጥ በቁሙ አልነደደም። አሁን ወደ አማራ ክልል በጊዚያዊነት ባለው ለምለም በዕት የተመረተውን ሰሊጥ በቁሙ ማንደድ ማን ደስ ይበለው ተብሎ ይሆን? የጎንደር ሊቃናት፤ የጎንደር ሊሂቃን በአደብ ከልባችሁ ሁናችሁ ምከሩ፤ ዘክሩ።
 
ሰሊጥ አጤ ነው። አፋን ከከፈተ ግብዓተ መሬቱን ይፈቅዳል። እጅግ ጠንቃቃ ገበሬን ይጠይቃል። አንድ ጎንደሬ ወልቃይቴ በሰሊጥ መኽር ወቅት እናትህ ሞተች ቢሉት፦ የሰሊጥ አጨዳ ላይ ነኝ ነው የሚለው። ቤተሰቦቻችን ሰሊጥን አምርተው እዛው እቤታቸው ዘይት ማውጫም የነበራቸው፤ ግራ ቀኝ ትራክተር፤ የቤት መኪና ላንድሮበር ወዘተ የነበራቸው ትጉኃን ስለነበሩ ነው። ጥበበኞችም ስለነበሩ ነው። የትውፊት ጥበቃውንም የእኔ ብለው ስለሚቀበሉ ነው። ይህን ውርስ ማስቀጥል ከእያንዳንዱ በግል፤ ከሁሉም በጋራ የሚጠበቅ የመዋለ ዕድሜ አመክንዮ ሊሆን ይገባል። ጎንደሬ እና ------- ቱግታ? ጎንደሬ እና ፍላት አይመጣጠኑም። በማስተዋል መራመድ ያስፈልጋል። አንደበትም መታረም፤ ድርጊትም በማስተዋል እንዲራመድ መምራት ይገባል።
 
ስለተፈለገ፤ ስለተወደደም አይደለም የእቴጌ ጎንደር አውራነት እና ዋርካነት። #ጎ መነሻ ሥያሜ ሲሆን ትንግርቱ የእዮር ነው። ለአገር መጠሪያነት ጎንደር ቅብዓዋ ከእዮር ነው። የህወሃት የቅናት ምንጭም ይኽው ነው። በአንድም በሌላም የጎንደር እና የአካባቢዋ ለላም ሲታወክ ለህወሃት ሠርጋ እና መልሱ ነው። ይህን ማሳካት ከህወሃት በላይ ህወሃትነት ነው። 
 
ጎንደር መሬት የሚያበቅለው አዝዕርት፤ ፍራፍሬ፤ ቅመማቅመም ሁሉ ይገኝባታል። ጥጥ ሳይቀር፤ እጣን ሸንበቆ ጨምሮ፤ የቅባት እህል፤ የቤት እና የዱር እንሰሳት፤ የእንሰሳት ተዋፆ፤ ከንብ ማር እስከ መሬት ጣዝማ፤ የተፈጥሮ ልምላሜ ፀጋ አላት። ጎንደር ደጋ፤ ወይና ደጋ ቆላም አላት። ጎንደር ወንዞች እና ሃይቆችም፤ ተራራ እና ኮረብታወችም አሏት። አእዋፋት በዓይነት አሏት። አሳም መደበኛ ምግቧ ነው። ጎንደር በጸሎት ሂደትም ዘመናትን የሚያመሳጥር ይትባህል አላት። ክርስትና፤ እስልምና፤ እስራኤላዊ እምነቶች ተነጣጥለው ሳይሆን በተፈጥሯቸው ልክ ተዋህደው ዘመናትን አድዮ አድርገው አስቀጥለዋል።
 
ጎንደር በሴቶች ሙያ አውራ ናት። በእጅ ጥበበብም እንዲሁ። ዓራት ዓይናማ ናት ጎንደሪና። ሌላ ቦታ የማይገኙ የጎንደር ብቻ የሆኑ የልባምነት ልኬታ አለ። መዋቢያ የጎንደር የፀጉር አቆራረጥ፤ የአለባበስ ግርማ ሞገስ፤ የአኳኳል ትውፊት ከዘመኑ ቢበልጥ እንጂ የሚያንስ ኩነት የለም። ሳውና የጎንደር ነገስታት ወለባ ትውፊት ነው።
 
የህሊና ስልጣኔም ቢሆን ለዛው ጎንደሬያዊ ሆኖ ከሌላው በዓት የማያንስ አቻዊ አቅም አለ ብዬ አምናለሁኝ። የጎንደር ልጆች ለማዶች ግን በመቆጠብ የሚከውኑት ይመስለኛል። ጎንደር ሁሉ ዘመዴ ዓይነት ነው። ጎንደር የሚገባ ሰው ለደቂቃ የእንግድነት ስሜት አይሰማውም። አዬሩ አይፈቅድም። አንድ እንግዳ ሰው በህይወቱ አደጋ ቢደርስበት ሁሉም ሃዘንተኛ፤ ሁሉም ጥቁር ለባሽ ይሆናል።
 
ጎንደር አዲስ ጎረቤት ሲመጣ ቡና ተፈልቶ ይጠራል። እንደገባም ማንቆርቆሪያ ጠላ፤ በገንቦ ጠላ ተይዞ ይኬዳል። ሰው ሲወልድ አስር እንጀራ በወጭት ዶሮ ወጥ ተሠርቶ ይወሰዳል። ሃዘን ሲሆን በተለይ በባላባቶች ከሆኑ ሞሰባቸውም፤ የወጭት ወጣቸው፤ ጠላቸው የተለዬ ነው። 
 
ጎንደር ለረጅም ጊዜ በአገረ መንግሥትነት መቆዬቷ እራስን፤ ሃሳብን አደራጅቶ የመምራት ረቂቅ ጥበብ ለጎንደሮች አብሮ አደጋቸው እንዲሆን አድርጎታል። ሳያውቁት የመሪነት ክህሎት አብሯቸው ያድጋል። ለዚህም ነው ጎንደሬ ሊቅ እዬታደነ በዬዘመኑ የሚረሸነው። በዘመነ ኢህአፓ፤ በዘመነ ኢዲዩ፤ በዘመነ ደርግ፤ በዘመነ ከፋኝ፤ በዘመነ የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር፤ በዘመነ ህወሃት፤ በዘመነ አብይዝም፤ በዘመነ ፋኖይዝምም ከሞት ጋር የተጋባው የጎንደር ሊቅ ነው። የጎንደር ሊሂቅ ነው። 
 
የተከበሩ ጄኒራል ፈንታ በላይ፤ የተከበሩ ሜጄር ጄኒራል ነጋ ተገኝ በ100 ዓመት ትውልድ የማያገኛቸው ዕንቁወች ናቸው። ለአገር ቀርቶ ልቅናው ለአህጉርም የሚበቃ ነበር። በሁሉም ቃለ ምልልስ ስለሁለቱ ሊቃናት የድርሳን ያህል ነው ምስክርነቱ። እናት ዓለም ጎንደር የተመሰጠረ ልቅና እና ልዕልና ለህሊና መግባ ታሳድጋለች። 
 
በዘመናችን አንድ ከዚህ ግባ የማይባል ዐረፍተ ነገር የጫጫረ የሌላ በዕት ልጅ በአፍታ መንበር - ይታጭለታል። ሚዲያው ሁሉ አብዮት ያካሂዳል ለሰብዕና ግንባታ። ሽልማት ይጎርፍለታል። በጥልቅ ብቃት ልቅና እና ልዕልና ትጋቱ ዘመን የማያደበዝዘው ተግባር የከወነ ጎንደሬ ግን ተቀብሮ እንዲኖር በጽኑ ይሠራበታል። ራሱ ጎንደሬው ለጎንደሬው ፀጋ ቀናዕይ አይደለም። አንድ ሁለት ተጽዕኖ ፈጣሪ ቀንቷቸው ከወጡ፤ ለአንድም ጎንደሬ ብቃት ከለላ አይሰጡም። ትካቸውን አይፈጥሩም። ይህ ሊታረቅ ያልቻለ የዘመን እንቆቅልሽ ነው። 
 
አንድ ሰሞን አስራት የሚባል የአማራ ድምጽ ሚዲያ ነበር። ለሚዲያው የጎንደር ብቁወች አጀንዳው አልነበሩም። የተረሱትን፤ የተዘነጉትን፤ ባን የተደረጉትን ጎንደሮች ሽፋን ሰጥቶ አቅማቸው ህዝብ ጠቀም እንዲሆን ሳይሰራበት ግብዓቱ ተፈጸመ።
 
በጎንደሬ ሊቃናት፤ ሊሂቃን እንደዬ ፆታቸው የተሰጠ ጸጋ አላቸው ከዋርካ እናታቸው ቅብዓ ጋር አብሮ አደግ የሆነ። ያ አገር ጠቀም እንዲሆን ተሰርቶበት አያውቅም። ብርቅ እና ድንቅ የሚሆነው በለታዊ ክንውን ላይ ያተኮሩ ድንገቴ ሰብዕናወች ብቅ ሲሉ፥ ጎልተው እና ደምቀው እንዲወጡ ይደረጋል። ሰርክ መኖራቸውን ለተበደሉ እና ለተገፋ የሚማገዱ ግን ጎንደሬወች ከሆኑ መጥፊያቸው ይታጫል። በግልጽም በስውርም ያለ ድካም ተዳፍነው ይቀሩ ዘንድ በትጋት ይሠራበታል። በዚህም ዙሪያ ልብ ተህሊና የተሰጣቸው የጎንደር ሊቃናት እና ሊሂቃን የተበተኑ ሚስጥራታቸውን ለመሰብሰብ ጉዞ ይጀምሩ። 
 
ፕሮፌሰር ዶር ማለደ ማሩ እንደምን ያን የዕውቀት ማዕከል ወጥነው ለዚህ እንዳበቁት ሃኪም ዩቱብ ዕውነቱን ሸልሞናል። እኒያ ታላቅ ሰው በህይወት እያሉ መንገድ መሰዬም፤ የምስጋና ቀን ማደራጀት ይገባል። ጊዜን መሻማት። የጎንደር ሙሽርነት አንዱ መለኪያ ድርጊት ነውና። ተማሪ እያለሁ፤ ሥራ ላይም ሆኜ አውቃቸዋለሁኝ። ድንቅ ቅኔ ሰብዕና ያላቸው በ100 ዓመት የማይገኙ ዋርካ ናቸው ፕሮፌሰር ዶር ማለደ ማሩ። ለሁሉም እኩል አክብሮት እና ትህትና ያላቸው ጉልላት። እራሳቸው የትምህርት ካሪክለም ናቸው። እባካችሁን በእሳቸው ዙሪያ ፍጠኑ! በተለይ የጎንደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት።
 
#በቃችሁ! ሰርክ የምትዘነጣጥሏት ጎንደርን ---- አትዳፈሯት።
 
…… ቢያንስ መገፋቷን፤ ቢያንስ ማገዶነቷን፤ ቢያንስ መገበሯን ክብር ዕውቅና መስጠት ቀርቶባት፤ በየሚዲያችሁ እዬነቀሳችሁ እያወጣችሁ የጎንደር እናት አምጣ የወለደቻቸውን ልጆቿን - አትቀጥቅጡ። አታንጓጥጡ። ጎንደርን - ልቀቋት! መብት አላት ያሻትን ወስና እንደ አሻት ለመኖር። ለእናት ክብር ይኑራችሁ።
 
ያ ሁሉ ፋኖ ተሰማራ እንደ ቼጉቢራ እኮ እቅፍ ድግፍ አድርጋ፤ ተቀብላ፤ መንገድ መርታ አሻግራ፤ ስንቅ ጎጆ ሆና፤ ሽሽግ ክውን አድርጋ ወደ ሱዳን አሸጋግራ ከዛ ወደ አደጉ አገሮች ተሂዶ ፕሮፌሰር፤ ዶክተር፤ ትዳር፤ ኢንቬስተር የተሆነው በልዕልት ጎንደር የእናትነት ትዕግሥት እና አርምሞ ነው። የሁሉም እናት ናት ጎንደር። ኢትዮጵያ እራሷ ላመስግንሽ ጎንደር የሚል መሰናዶ ሊኖራት ይገባል።
 
ጎንደር ከፋኝ ያሉትን ስታስጠጋ በደርግ፤ የኢትዮጵያን ሠራዊት የቆሰለ ስታስታምም ከፋኝ ባሉት ታጣቂወች በግራ ቀኝ ተቀጥቅጣለች። ጎንደር ይህን ሁሉ መከራ ታግሳ ነው ኢትዮጵያ የቀጠለችው። ከተከፋ ጎን ቆማ የተማገደች ናት እቴጌ ጎንደር። አንድም ሰው ሲያመሰግናት፤ አንዳችም ነገር ለጎንደር ውለታ ሲደረግላት ሰምቼ አላውቅም። ጎደሪና የልብ አድርስ፤ እሩህሩህ፤ እንስፍስፋ የሰብዐዊ መብት ዓራት ዓይናማ ተሟጋች ኮከብ በዓት ናት። ሽልማት ያስፈልጋታል የዘመን ምርጥ ናት እና። እራሷም ዘመን። የበሞቴ ልዕልት፤ የአፈርስ ሆን ንግሥት፤ የአይዟችሁ አጽናኝ አብነት ናት ጎንደርዬ። 
 
አሁን ይበቃታል ተዋት። በተለይ ህወሃት ተኮር ሚዲያወች ከራሷ ውረዱ። የእናንተ የዩቱብ በጅሮንድ በጎንደር ጥላቻ፦ በጎንደር ንቀተ እና ምቅኝነት አይሁን። ባመዛኙ ያላሰባችሁት ክስተት ታሪክ ተደገመ እና ያ ነው የሚያብተከትካችሁ። ከጥላቻ ውስጥ የማግስት የአብሮነት ብርኃን የለም። ተስፋን አትታገሉ በቂም እና በበቀልም ዘመንን አታሰቃዩት።
 
ሃሳብ ካላችሁ አብይዝምን በአመክንዮ ሞግቱ። ለነገሩ የማንነት ቀውስም ይመስለኛል ከጎንደር ጋር ይህን ያህል ቲካቲካው። እግዚአብሄር ይማራችሁ። አሜን። እኛ ጎንደሬወች ግን ስትታሰሩ፤ ስትንገላቱ አብረን ነው ክልትምትም ያልነው። ያው እናንተ ማተበ ቢስ ሆናችሁ እንጂ።
ሌላው ቀርቶ የደርግ ሥርዓት ሲያበቃለት ከኤርትራ፤ ከትግራይ የተበተነውን ሠራዊት የጎንደር ህዝብ እስከ ወለቃ፤ እስከ ኮሶዬ፤ እስከ አንገረብ ድረስ ተጉዞ በግፍ ባዶ እጁን የተባረረውን የኢትዮጵያ የሠራዊቱ አባል እና ቤተሰቡን በፍቅር ተቀብሎ ያስተናገደ ህዝብ ነው።
 
በነፍስ ወከፍ እሱ እና ቤተሰቡ ከመሬት እዬተኙ ክብሮቹን አክብሮ አስተናግዶ በፍቅር የሸኜ፦ በቁሙ የጸደቀ ህዝብ ነው የጎንደር ህዝብ። ከእኛ ቤት አባት እና ልጅ የሲዳሞ ቤተሰቦች ተገናኝተዋል። እናት እና ሚስትም ከሲዳማ ድረስ መጥተው ከእናቴ ጋር ተዋውቀዋል። ጎንደር ጉልላት የኢትዮጵያ ውስጥነትም ናት። ጎንደር የህክምና ማዕከል ልጆቹን ሲያስመርቅ ቤተሰቦቻቸው ከሌላ ክፍለ አገር ሲመጡ ተቀብሎ፤ የቤት ውስጥ መሰናዶ አዘጋጅቶ ያስመርቃል። ጎንደር ከሚስጢር በላይ ናት እናኑ፤ እናናዬ። 
 
ኤርትራውያን ከህወሃት ጋር የነበራቸው የጫጉላ ሽርሽር ተጠናቆ ወደ ኤርትራ ሲመለሱም በጎንደር የተጓዙት በደማቅ አቀባበል፥ በልዩ እንክብካቤ፥ መስተንግዶ ተደርጎላቸው በፍቅር ተሸኝተዋል። ይህን አውስትራልያ የሚኖረው ጋዜጠኛ ሰናይ መስክሮታል። ጎንደር የነበሩት ሲሸኙም የጎንደር ህዝብ እንስፍስፏን እናቴን ጨምሮ ንብረታቸውን ክውን አድርጎ በአግባቡ እንዲደርሳቸው አድርጓል። በአብይዝም መንግሥት እና በህወሃት ጦርነት መኖራቸው የታወከ፤ የተጎዱ እና የተፈታው ሠራዊት ጎንደር በፍቅር እና በክብር ተቀብላ አስታማ፤ አልብሳ፤ አስተናግዳለች። ያውም በኮረና ዘመን። ይህ የሰማይ ፀጋ እና በረከት ዘመን ከዘመን እያሸተ የቀጠለ የዊዝደም መክሊት የኢትዮጵያም የእዮር ስጦታ ነው። ጎንደር ለኢትዮጵያ ምርቃት ናት። 
 
ህወሃት ገሥግሶ ሲመጣ የቅራቅር ህዝብ እና ታጣቂ ህወሃትን መክቶ ተስፋውን አምክኗል። ጎንደር ከሚስጢር በላይ ናት። ጎንደር ኃላፊነትን እና ተጠያቂነትን ስትከውን በተባ ክህሎቷ ነው። በሥርዓት። እራሷ ጎንደር የመርህ መሰላል ናት። 
 
አሁን ደግሞ በዳግም የኤርትራ በርኃ ያ ናፈቀን የሚሉ መንፈሶች ጋር አብሮ እፍታ ምን ለማግኜት? ማንን ለማትረፍ ይሆን? በዚህ እልህ የአብይዝም ሥርዓት ለጎንደር ሊያመጣ የሚችለውን ጫናም በማስተዋል መርምሩት። እንደ አባት አደሩ ጥሞና ውሰዱ። ዕውነቱን ብነግራችሁ ፍፃሜው #አልቦሽ ይሆናል ግንባር ብላችሁ ጎንደርን እንዳስገበራችሁት ከንቱ ህልም። ፍፃሜው #ፀፀት ይሆናል። ከስኬት መንፈስ ጋር ሳይሆን ከኪሳራ መንፈስ ጋር የሚያገናኝ ሰባራ ድልድይ ነውና። 
 
የአገር መሪነት ክህሎታዊ አቅም የለም።
ስክነት - የለም።
ተመክሮ - የለም።
ቅብዓም - የለም።
የማደራጀት ፀጋም የለም።
 
ያለው ቅናት - ቅጽበታዊነት እና ፋንታዚ ብቻ ነው። ዘለግ ባለ ዝምታ ውስጥ ሆኜ የገመገምኩት ዕውነት ይህው ነው። በጨመተ አስተውሎት የደረስኩበት ማጠቃለያ ይኽው ነው። የዕቃ፤ የሸቀጥ፤ የነገሮች መስዋዕትነት ይሁን፦ የሺ ዘመናት የጎንደርን መጨመት ተደሞ እዬተደፈረ፤ ጥቃት እዬተፈፀመበት ነው። ጎንደር በነገር ወጨፎ እዬተጨቀጨቀች ነው። ነገሩ ሁሉ ያለአዋቂ ሳሚ ወይንም እሚታዬ ጽግሽ እንደምትለው ብለኃት የሌለው ቅላት ነው።
 
ስለሆነም ጎንደር ከምሥረታው ጀምሮ ኢትዮጵያን ጨምሮ የዓለም ሊቃናት፤ ሊሂቃን በጥበብ ያበጇት እንጂ የአንድ ጀንበር ዳንቴል አይደለችም። አንድ ዘለላ የጎንደር መንፈስ ብዙ ድርሳን ያጽፋል። ብታውቁበት፦ ብታስተውሉት። በአደብ እና በጥምና ዘመኑን በልቅናችሁ ልክ ፈውስቱ። የትውልድ ስቃይ የእኛው ዘመን ይበቃ ነበር። ህዝባችን እና ትሩፋታችን ተሰቃዩ።
 
ዕውነተኛ የአማራ ፋኖ በጎንደር --- ጎንደሬነትን ከዊዝደሙ ጋር አወያዩት። እያንዳንዱ ንቅናቄያችሁ ለህወኃት አቅም ይመግባል ወይ ብላችሁ መርምሩት። እኔ እንደ ባይታዋር ዝም ብዬ ነው የኖርኩት። ዛሬ ልላችሁ እምሻው ቁም- ነገር የፕሮ - ህወሃት አጥሚት እና አጋፋሪ ላለመሆን እሰቡበት ነው ጭብጤ። ብቁ መሪወቻችሁን እየገበራችሁ እስከ መቼ? የጎንደር ዓራት ዓይናማ የፋኖ ቀንዲሎች እኮ ተመነጠሩ። ሚስጢሩ ከህወሃት ጋር ለሚደረገው ጋብቻ ጎንደሮች አሻም ይላሉ ተብሎ ነው። 
 
ለነገም ከጎንደር መሪ? እእ አይታሰብም። የተከለከለ መንገድ ነው። ተመስጥሮ ተቀብሮ ያለ አመክንዮ። በዘመነ ህወሃት መራሽ የአማራ ክልል አንድም ጎንደሬ ፕሬዚዳት፤ የአገርም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር ሆኖ አያውቅም። አይታሰብም። በዘመነ አብይዝም ለሦስት ወሩም ለሞት የታጨ ነበር። ለሦስት ወር እንኳን አቅል፦ አደብ አልነበረም። ከእነ ቲሙ አፈር ተደገሰለት። አፈር ሆኑ ቲም ሰማዕቱ ዶር አንባቸው መኮነን። ይህን ማመሳጠር እንዴት ያቅታል???? ለማን - ተብሎ ይሆን ሁለት ዓመት ሙሉ የጎንደር ህሊና ለባሩድ የተፈቀደው? ለምንስ - ተብሎስ? እሰቡበት። እሰቡበት።
 
ለጎንደር አደቧ፦ ጥሞናዋ ነው የሚበጀው። ያላዬችው መገለል፤ ያላለፈችበት የፈተና ቡፌ የለም እና። ይህን ስል በሚያስከፋ ሁነቶች ዝምታ ይንገሥ እያልኩ አይደለም። ጎንደር ለሰባዊ መብት ቤትነቷን በጥበቧ ልክ ልትወጣ ይገባታል። ያን ደግሞ ልጆቿ እዬሰራንበት ነው። ከድብልቅልቁ ሆነ ከሁከቱ፤ ከከንቱ ውዳሴው ሆነ ከኳኳቴው የሌለንበት እትብቷ በሥርዓት፤ በህግ እና በደንብ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ብዕራችን እና ብራናችን እዬተጋ ነው። ስንሞግት ንቀን፤ ዘንጥለን አዋርደን አይደለም። አክብረን እንጂ። በእኛ ቤት "አንተ እና አንቺ" አይደፈርም። አቃሎ ገንጥሎ ማዬትን ጎንደሬነታችን አይፈቅድም። አማራነታችንም ይለፍ አይሰጠነም። ኢትዮጵያዊነታችንም በጅ አይለንም። ስለሆነም አክብረን እንሞግታለን። 
 
ከፋኖ ንቅናቄ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ትንግርት የፖለቲካ ትርፍ ነበር ለአማራ ህዝብ። አንድ ሰው ሳይሰዋ፤ አንድ አማራም ሳይገበር። የአንድ ከተማ መንፈስ ሳይታወክ፤ እንደ ቄጤማ ሜዳ ላይ ያልተነሰነሰ ልዩ ድል። ሚስጢር ጥበቃ ይሻል እና ለፎቶ ሾው አልተፈቀደም። የሆነ ሆኖ ጦርነት አትራፊ አይደለም። አቤቶ ጦርነት አተረፍኩ ካለ፤ የሚያተርፈው ቂም እና አመድ፤ ጥላቻ እና በቀል ብቻ ነው። ጦርነት የእኔ መንገድ አይደለም። በቃ! ጦርነት ጎዳናዬ ነው። እጅግ የማከብራቸው ቅዱሱ የካቶሊክ ሃይማኖት ፓትርያርክ አባት ፍራንሲስ የኑዛዜያቸው ዕርገት "በቃ! ጦርነት" ነው። ተመስገን ብያለሁኝ። ትልም ሲባረክ። 
 
ከአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ በፊት ዛሬ ልካቸው የለም ብላችሁ እምትሟገቱላቸው ሰብዕናወች ጎንደር እንዴት አደርሽ? እንደምን ዋልሽ? መልካም ምሽት፤ ደህና እደሪ ብለዋት ያውቃሉን????? ስለ ፋኖ ጽፈው ሞግተው ያውቃሉን? የፋኖ ንቅናቄ ከመፈጠሩ በፊት ፋኖ የሚል ቃል አንደበታቸው ላይ ሰምታችሁ ታውቃላችሁን??? 
 
እኔ ሁልጊዜም ተጎዳ ብዬ ከማስበው ጎን ስለምቆም ከ15 ዓመታት በላይ የተጋሁበት መሰረታዊ አመክንዮ መስዋዕትነትን መቀነስ እንጂ ማባዛት አልነበረም። የእናት ዕንባ ሊቆም ይገባል። ያዬሁት ግን ሙሉ ጊዜ ተገበርልኝ የሚል የማይጠረቃ የኢጎ ስካር እና ካንሰር ነው። በምርጫ ተወዳድሮ የተሸነፈ መንፈስ በጠበንጃ በሌላው ግብር??? 
 
ገና ሳይወጠን ከእስር መለቀቅ ጋር የፃፍኩት ፋኖን እመራለሁ እንዳትል ብዬ በድፍረት ጽፌያለሁ። ለዛ የሚያበቃ የተፈጥሮ አቅም እንደሌለ አሳምሬ አውቃለሁ። ህዝብ አደራጅ ነው የነበርኩት። መምህሮቼ ደግሞ የአገር መሪነት አቅም የነበራቸው የዘመን አደቦች ነበሩ። አስቀድሜ በትህትና ስለ አሳሰብኩኝ ጸጸት የለብኝም። ጦርነትንም ጎንደር ከተማ ተወልጄ አድጌ ደጋፊ ልሆን በፍጹም አልችልም።
 
ብዙ የተደከመላቸው፤ በብዙ ሰብዕናቸው የተገነባላቸው ወንድም እና እህቶች ተው ሲባሉም አያደምጡም። ጆሮ አልባ፤ አደብ ለነሳው መንፈስ መታከት ደግሞ አይገባም። የመምራት የማደራጀት አቅሙም ሆነ የመሪነት ቅባውም ነጠላ ነው፥ የለም። በየእርምጃው መፍረክረክ። ፈርሶ መሰራት፤ ተሠርቶ መፍረስ። ሃሳብ ለመግለጽም ጋዳ ነው። ከልብ የሚገባ ጠብ የሚል የንግግር ጥበብም የለም። መሪነት ዓራት ዓይናማ ተናጋሪነትንም ይጠይቃል። 
 
እና ምን ታምኖ? ምን ሊያተርፍ ይሆን የጎንደር ማገዶነት? በበሰለ ህሊና ሲሰላ ጎሌራ ከተማ ላይ ከመደበኛ ሠራዊት ጋር እንደምን ይታቀዳል??? ለህዝብ ለሰላማዊው ነዋሪ ዲል ያለ መከራ ማጨት፤ ጽልመት መከመር። ዘመን ከዘመን የጎንደር እናትን ጥቁር ለባሽነትን አልሞ ማስፈፀም ማንን አተረፈ? አቤቶ ህወሃትን። ዕውነተኛ የጎንደር ፋኖወች ከዋርካው ምሬ መማር ይበጃል ልላችሁ እሻለሁኝ።
 
የጎንደር እና አካባቢያዊ አዬር በባሩድ ሊታወክ አይገባም። ኮሶዬ፤ ወለቃ፤ ደፈጫ፤ እንፍራዝ፤ ጯሂት፤ ማክሰኝት፤ ጠዳ፤ ደንቢያ፤ ጎርጎራ፤ አዘዞ፤ አዬር ማረፊያ፤ ወረታ፤፦ ደብረታቦር እና አካባቢው ጥበቃ ይሻሉ። የተኩሱ ንጠት ቅርስን ይበጠብጣል። ዋርካው ምሬ ጥንቃቄ ያተርፋል እንጂ አያከስርም መርሄን አመሳጥረህልኛል እና አመሰግንኃለሁኝ። 
 
ጎንደራዊው መንፈስ የበዛ ጥሞና፤ በርከትከት ያለ ተደሞ፤ ዝልቅ አደብ እና ስክነትን የአባት አደሩን ሊከተሉ ይገባል። ይህ ሁሉ መገበር ከዋጋ የቆጠረላችሁም አንድም አካል የለም - ዛሬ። ነገማ ትዝም አትሏቸውም። አመድ አፋሽነትም የተሰጠን ይመስለኛል። ያ ታይቶ የማይጠገብ ወጣት ናሆሰናይ ተረሳ እኮ???
 
በሌላ በኩል የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ትጥቅ ፍቱ ብይን መርግ እና ቆባ የሆነ ፖለቲካ ውሳኔ ነው። ሊታረም ይገባልም። ገና ጠሚር አብይ አህመድ 100 ቀናታቸውን ሳይደፍኑ እኔም ዜጋ ከሆንኩ በሚል ዘለግ ያለው ጹሁፌ የተፈጥሮ ዘብ አደሩን ገራገር በሚመለከት ብልህነቱን አጠይቄ ልዩ የመንፈስ ጥበቃ ያደርጉለት ዘንድ አብክሬ ጽፌያለሁኝ።
 
የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ጆሮ አልቦሽ ናቸው እና ሳያዳምጡ አፈሰሱት። የፋኖ መከፋት ምንጩ ይህም ነው። ለጎንደሬ ትጥቅ መፍታት ቀበቶ አልቦሽ ነው። ሚስትም አያገኝ ትጥቅ የፈታ። መታጫው፤ መዳሪያ መኳያው፤ ድንበር ማስጠበቂያ መከታው ነው ትጥቁ። እያንዳንዱን መንደር በመንግሥት ሠራዊት ማስጠበቅ ከባድ ግዴታ ነው። የፈቀዱ፤ ማህያ የማይጠይቁ ቅኖችን ገፍቶ ምን ለማትረፍ እንደ ታሰበ የአማካሪ እጥረትም ነው። የኢትዮጵያ ደንበሮች በፈቀዱ ዘቦች ነፃ አገልግሎት ካስማነት ነው የቆዬው። 
 
በጠቅላላ በአማራ ሥነ - ልቦና ልዩ የጥሞና ጊዜ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ የሚያስፈልጋቸው ይመስለኛል። አማራነት ፍልስፍናው ጥልቅ ነው። ማጥናት ያስፈልጋል። ከማቃለል - ማክበር፤ ከማጣጣል - ዕውቅና መስጠት፤ እንደ አልባሌ ከማዬት አቅርቦ መንፈሱን ማወያዬት ያስፈልጋል። በመሪነት ውስጥ የክት እና የዘወትር አያስፈልግም። በኽረ አጀንዳው የአማራ ጉዳይ በተጠለ፤ በተገለለ፤ በተናቀ ቁጥር፤ እንዲሁም በተጫኑት ቁጥር ኢትዮጵያዊነትን ለማስቀጠል መርግ ይሆናል። የአማራ መንፈስ አቅሙ በቀላል ካልኩሌሽን የሚደመደም አይደለም -----------። 
 
ትርፍ ንግግር፤ መስቃም ሊታረም ይገባል። " ጃውሳው" ይሰቀጥጣል። አማረነት ይከበር!
 
ማህበራዊ መሰረቱን ያጣው ሁሉ ስለምን ወደ አማራ መንፈስ ይተማል? ቅኑ ገራገሩ አማራ ሁሉም አለውና። አማራን የሳተ፤ መንፈሱን ያስከፋ ስኬቱ ውሽልሽል ይሆናል። ትንቢት አይደለም። አቅም አቅም ያለው ዊዝደም እንደሚሻ ለማጠዬቅ እንጂ። እርግጥ ነው ለአማራ ተሳትፎ ሻሞ ቢኖርም የአማራ ልጅ ቁልፍ የመሪነት ቦታ እጮኝነት ግን ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ኢሊት ምጥ ነው። ይህንን ጉዳይ የአማራ ልጆች በአስተውሎት ሊመረምሩት ይገባል። 
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን። 
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
5/05/2025
 
ስለ ትንፋሽዋ ጎንደር ቅንነታቸውን ለሚመግቡ ወገኖቼ ሁሉ ምስጋናዬ ከልብ፤ አክብሮቴም ከህሊናዬ ነው። ኑሩልኝ። አሜን።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?