#ራህብን ለመግለጽ ሌላ "#ራበኝ" ከማለት ሌላ ቋንቋ ይኖረው ይሆን?
እንዴት አደራችሁ ማህበረ ቅንነት? ደህና ናችሁ ወይ?
#የአብይዝም መንግሥትስ?
የኢትዮ ሰላም ሚዲያ ባለቤት ልጅ ቴወድሮስ አስፋው ከሚያነሳቸው በርካታ ጉዳዮች ላይ #ሦስት ጉዳዮች እኔንም ሞገቱኝ እና ሃሳቤን ላጋራ ወደድኩኝ። ለመነሻነት ይህ ይሁን እንጂ ተያያዥ ጉዳዮችም ሊነሱ ይችላሉ።
የሆነ ሆኖ በአመዛኙ ከሁለት ዓመት ወዲህ #ቅይጥይጥ ክስተቶች ከመበራከታቸው የተነሳ በብዙ ክስተቶች ላይ ጥንቃቄያዊ ጉዞ ላይ ነው የባጀሁት። የኃይል አሰላለፋም ተለዋዋጭ ባህሬ መኖሩም። ስለሆነም የአቅም መግቦቱ እና ስኬቱ ለማን? የሚለውን በጥልቀት ማየት ያስፈልግ ስለነበር ተግታን መርሄ አደረኩኝ። ያ ጥንቃቄ ለእራሴ የውስጥ መንፈስ ቅዱስ መዳህኒት ሆኖልኛል።
ሰማይ ዝቅ ምድር ከፍ ቢል ቅንጣት አቅም የህወሃትን ተስፋ እንደገና በሚያለምልም አዟሪት ውስጥ መግባት በቁም ሬሳ የመሆን ያህል ይሰማኛል። ከመሼ እየታየ ያለው ሂደት ይህን እንደሚያመሳጥርም እዬታዘብኩ ነው። አቤቱ ህወሃት ለሚናፍቃቸው ወገኖቼ አቅም ብጣቂ አላዋጣም። ፈጽሞ። አቤቱ የሴራ ካፒቴኑ ህወሃት እና #አኞ ፖለቲከኛው ናፍቆኝ አያውቅም። ወደፊትም አይናፍቀኝም። ግድፈት፤ ሂደት፤ ወቅትና ዘመን ሊያስተምረው የሚችል ድርጅት አይደለም እና።
በሌላ በኩል የበዛው ቅንነቴ ስለ ወገኔ የምሰጠው ምስክርነት ሆነ ማገዶነት ጊዜ ራዲዮሎጂ ነውና የግለሰብ ሰብዕና ግንባታው ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ተጨማሪ ችግር አምራች እንጂ የመፍትሄ ጎዳና ሆኖ በተጨባጭም አላገኜሁትም። ብዙ የሚሰቀጥጡ ጉዳዮች እራሳችን መስክረንም፤ ተማግደንም መንበር ላይ ባወጣናቸው ሰብዕናወች ተጽዕኖ ፈጣሪነታቼው ፈውስ ሳይሆን ሸክም ሲሆን በዘመኔ አየሁኝ። በሰባዕዊነት ብቻ በሚደረጉ ድጋፎች የሚገነባ የግል ሰብዕና ሁልጊዜም "ቁሞ የሰቀሉትን ቁጭ ብሎ ማውረድ" እዬቸገረን መሆኑም በኽረ ጉዳዩ ይህ ይመስለኛል። ሙሉ የአቅም መግቦት የተደረገለት ሰብዕና ዕድሉን ሲያገኝ ተጨማሪ ፈተና የመሆን ጉዳይ እጅግ አሳሳቢው ጉዳይ ነው። ስለሆነም ጥንቃቄያዊው ጉዞ መሆንም የነበረበት፤ ያለበትም ያ ይመስለኛል።
የሚቆጠቁጡ፤ የሚያርገበግቡ፤ አቅጣጫውን የሚያፋፍሙ፤ ወይንም የሚያሰውሩ ሂደቶችን በጥሞና ማዬት ይገባል ብዬ አስባለሁኝ። ይህ ለህዝባችን የውስጥ መረጋጋት እና ሰላም መሰረታዊ ነው ብዬም አምናለሁኝ። ጉዳትም ይቀንሳል፤ መስዕዋትነቱን ያመጣጥናል። የመፍትሄ አቅጣጫወች ላይም #መጫንን ያስቀራል።
በብዙ በመንፈስ ዲክታተር የሆኑ ተጫኝ ሃሳቦች ወዘተረፈ ናቸውና በኢትዮጵያ ፖለቲካ። አይታወቀውም እንጂ በሚዲያ፤ በአክቲቢዝም ላይ ያሉ ሰብዕናወች #ተጫኝ ሃሳባቸውን ሲያቀርቡ #የዲክታተርነትን መንፈስ ቅረበኝ እያሉ እንደሆን የሚያስቡት አይመስለኝም። አንድ ሚዲያ በስጨት ብሎ፥ "ለምን ወጣቶች ከተማ ውስጥ ይታያሉ? ሁሉም ያለውን ይዞ ዱር ቤቴ ይበል" ሲል እሱ ዝንጥ ካለው ዕልፍኙ፤ ዘመን ካለው አገር ሆኖ፤ የራሱን ቤተሰቦችም ውጭ ውጭ እያለ ለሌላው፤ አማራጭህ ዱር ቤቴ ይሁን ብሎ ሲወስን #ዲክታተርነት መሆኑ አይታዬውም። የዲክታተርነት መሻት እጮኛነት እኛንም እዬጎበኛኜን እየፈተነንም ነው እንደማለት። ጥቂት ወጣቶች ከተማ መታየት ያንገበግባቸዋል። አንድ ፔና፤ አንድ ራፊ፤ ቁራሽ እንጀራ ያላቀረበ። ዘረፋም ነው። ባልደከመበት የልጅ አስተዳደግ ሙሉ ዘመኔን በፖለቲካ የኃይል አሰላለፍ እንደ ሽንብራ ቂጣ እኔ ስገላበጥ ምኞቴ ይሳካ ዘንድ #እረርልኝ።
በሌላ በኩል ሂደት እያጓጓዘ እንካችሁ የሚሉ አዳዲስ ሁነቶችን ወይንም ክስተቶችን #ቀና አድርጎ በአስተውሎት #በቅንነት ማዬት ይገባል። ለበደሉ ተጨማሪ ጭነት ማከል የሚገባ አይመስለኝም። ወይንም ምንጊዜም ተከሳሹ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ነውና ስንት ሊቃናት በመደበኛ ሚኒስተርነት፤ በአማካሪነት ለተሰማሩለት መንግሥትም ይህን መንገድ አንተ አላየኽውም እና እኔ ልገዝ በማለትም ክስተቱን በማሳጣት ረገድ መትጋትም የማስተውለው ስንጥር ገጠመኝ ነው። ይህ ሂደት እና ምርጫ ከሰባዕዊነት አንፃርም ለህዝብ ዘላቂ የውስጥ ሰላም ትጋት ላይ ጫና ይፈጥራል።
ለምሳሌ አንድ በመንግሥት እስር ላይ የሚገኝ፤ ሳይታሰር ትሞግተው የነበረውን ሰብዕና ሲታሰር ሙሉለሙሉ የሙግትህን አቅጣጫ ማቋረጥ ይገባል። በእሱ ሥር ያሉ ቤተሰቦችን፤ የትውልድ ተስፋ የሆኑ ልጆቹን ወዘተ ግምት ውስጥ ማስገባት ይገባል። የታሳሪ ወገንህን እስር ጊዜውን የሚያቀል እንጂ #የሚያጠብቅ ሁነት መፍጠር የተገባ አይደለም። በሌላ በኩል ብልጽግናን አምነው አገር የገቡ ወገኖችህ አንተ የምታውቀው የቀደመ ሚስጢር ካለም ቆጥቦ መያዝ ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሥልጣን ይያዝ አይያዝ ረመጥ ነው። በግራ ቀይ ላርባ ይጋረፋል። ለወገንህ አንተም #ደህንነቱ ነህና ጥንቃቄ ያስፈልጋል።
የብዙ ወገኖች የጥቃት መስመር የሚቃኜው ለሰባዊነት፤ ለዕውነት፤ ለተረጋጋ የህዝብ ሰላም እንሰራለን በሚሉ ትጉኃን ምክንያት ሊሆን ይችላል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሥልጣን ላይ ይኮን፤ ለሥልጣን በሚደረግ ትግል ውስጥ ቂም፤ ጥላቻ፤ በቀል እና ግለት ባህል ነውና በብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። እራስን መግዛት። አንደበትን መቆጣጠር ይገባል። ዕውነት እንኳን ቢሆን እንዳላዩ ማለፍ ወይንም ዝምታን መመገብ ይገባል። ሳይሠራ ይቅር። እርግጥ ነው ዛሬ የህይወትም፤ የዕውቅናም ይሁን የተጽዕኖ ፈጣሪነት ፈሰሱ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ መትጋት መሆኑን ባውቅም።
ልጅ ቴዲ ኢትዮ ሰላም የሃኪሞች ጥያቄ "#ራበን" "ሆድ ለመብላት፤ አንጀቴን በላህው በላኽው" እንደማለት አድርጎ አቅሮቦታል። መብታቸውን በቀጥታ እንጂ የህዝብን ስሜት በሚነቀንቁ ኃይለ ሁነቶች ሊሆን አይገባም ባይ ነው። ከዚህ ሃሳብ ጋር ትንሽ እንቆይ።
1) "#ራህብ" የአንድ ሰው ወይንስ ተጠያቂነት እና ኃላፊነት ያለው የነፍስ ወከፍ።
1.1) አንድ የጤና ባለሙያ እናት፤ አባት ወይንም አሳዳጊ ይኖረዋል። እህት ወንድምም።
1.2) አንድ የጤና ባለሙያ ትዳር ወይንም እጮኛ፤ ልጅ ወይንም የሚያሳድገው የዘመድ ልጅ ይኖረዋል።
1.3) አንድ የጤና ባለሙያ በማህበራዊ ኑሮው ሰርግ ይጠራል፤ ሚዜ ሊሆን ይችላል፤ የራሱ የቅርብ ቤተሰብም የሚዳር ሊኖረው ይችላል።
1.4) አንድ የጤና ባለሙያ የራሱ ቤተሰብ፤ ጎረቤት፤ የሥራ ባልደረባ፤ ቤተዘመድ ወዘተ ሃዘን ሊደርስበት ይችላል።
1.5) አንድ የጤና ባለሙያ የራሱም ልጅ ሊታመምበት፤ ወይንም የጨረሰው ኮርስ ከኖረው ምርቃት ሊኖርበት ይችላል።
1.6) አንድ የጤና ባለሙያ እራሱም ሊታመም ይችላል።
1.7) አንድ የጤና ባለሙያ የተጎሳቆሉ ታማሚ ወገኖቹን ሊረዳ የሚችልበት የግዴታ ገጠመኝ ሊኖርበት ይችላል። የልጅ ተክሌን ዩቱብ ቻናል ብታደምጡት ምኞቴ ነው። መዳህኒት ለመግዛት በሽተኞች አለመቻል፤ ወይንም መግዣ መጉደል፤ ወይንም መዳህኒቱ አገር ውስጥም ላይኖር ይችላል። ሃኪሙ በመዳፋ ባለው ኪሱ ይወስናል።
1.8 አንድ የጤና ባለሙያ በብሄራዊ ደረጃ ግዴታዬ ነው ብሎ በሚያስበው የተሳትፎ አንባም ፍላጎት ሊኖረው ይችላል። በመዋጮ ፈቅዶም ይሁን በመንግሥት ተጠይቆም ሊሳተፍ ይችላል። መጸሐፍ ግዙ፤ ለልማት አዋጡ፤
1.9) መንገድ ላይ ያልሆነ የወገን ችግር ገጥሞ ያን አይቶ ማለፍ የማይችልበት ገጠመኝ ይኖራል።
1.10) አንድ የጤና ባለሙያ በተዋህዶ ልጅነት አስራት፤ በኰራት፤ ወይንም በእስልምና መኖር ለከበዳቸው እገዛ ማድረግ የአጽዋማት ግዴታ ስለመሆኑ በእስልምና ሃይማኖትም አለ።
1.11) የኢትዮጵያ ዓውዳመቶች እራሱን ጠና ያለ በጀት ይጠይቃሉ።
1.12) አንድ የጤና ባለሙያ በግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሊሳተፍ ይችላል ወዘተ። ወዘተ።
አንድ ሰው ኖርኩ የሚለው በዚህ መሰል ተፈጥሯዊ፤ ማህበራዊ ሁኔታወች ማለፍ አለበት። መኖር ይህን ካጣ #ልሙጥ ይሆናል። ለልሙጥ ህይወት ደግሞ የሰው ልጅ አልተፈጠረም። ስለሆነም አንድ የጤና ባለሙያ በአቀደው የህይወት መስመር ብቻ በጀቱን መምራት አይችልም። በመኖር ውስጥ ባሉ የውዴታ ግዴታወች መሳተፍ የመኖርን አቅም ያሳሳል።
የመኖር አቅም ሲሳ ደግሞ እራስን ማኖር ይከብዳል። ከባዱ ፈተና ሊለምን አፍሮ ለራሱም ጉሮሮ ሲሳን ነው። ጉሮሮ ማርጠቢያ ከሌለ ራህብ እራሱን ዓውጆ ከች ይላል ቤተኛ ይሆናል። እህል ቢኖር ማጣፈጫው፤ ማጣፈጫው ሲኖር ጋዙ፤ ጋዙ ሲኖር ትራንስፖርቱ፤ ትራንስፖርቱ ሲኖር አልባሳቱ፤ አልባሳቱ ሲኖር የቤት ኪራዩ፤ የቤት ኪራዩ ሲኖር የመብራት እና የውሃው፤ ይህም ሲገኝ ድንገቴ ገጠመኞች ወጪን የሚጠይቁ ሁነቶች ሊከሰቱ ይችላልሉ። መኖር እራሱን የሚገልጽባቸው ሁነቶች ሁሉ ወጪ ናቸው። ከጸሐይ ከንጹህ አየር በስተቀር። ለዛውም ትንፋሽ ላጠረው ክፍያ የሚጠይቅ ኦክስጅን ይጠይቃል።
ዘርፈ ብዙ መስተጋብሮችን የያዘው ጥያቄ የአንድ ሃኪም ብቻ ሳይሆን የማህበረሰቡን ውስጥነትም፤ የመኖርን ሚስጢራትም ያካተተ ስለሆነ ነጥሎ ማቅረቡ፤ አቃሎ፤ ወይንም አጋኖ፤ ወይንም አዝሎ ማቅረብ በፍጹም አይገባም።
2) ሁለተኛ ልጅ ቴወድሮስ ያነሳው የጤና ባለሙያወች " "#ልዩ ነን" ብለው ያስባሉ ወይንም ያምናሉ።"
ይህም የሚያስኬድ አይመስለኝም። የጤና ባለሙያ "ልዩ ነን" ብለው ቢያስቡ ………
2.1) ጋብቻ የሚፈጽሙት ከሙያ አጋራቸው ከአቻቸው ብቻ ይሆናል።
2.2) ምንም ዓይነት የሃይማኖት ሥርዓት ላይ አይሳተፋም ነበር። ህዝብ በጤና ባለሙያነት አልተመረቀምና።
2.3) ምንም ዓይነት ማህበራዊ አገልግሎት ላይ አይገኙም ነበር። ዕድር፤ ቁቤ፤ ማህበር፤ መረዳጃ ማህበር፤ በሃዘን በደስታ፤ የጸሎት፤ የድዋ ሥርዓት ላይም።
2.4) የተለዬ የጤና ባለሙያወች መኖሪያ አንባ በመሥራቴ ላይ ይተጉ ነበር።
2.5) ሰባዕዊ እና ተፈጥሯዊ ሁነቶች ላይ በጉልህ አይሳተፋም ነበር።
2.6) አብሮ አደግ ጓደኛ የሚይዙም በርካቶች ናቸው። በኢትዮጵያ ያልተፃፈለት ድንጋጌ ቢኖር የጓደኝነት ውሎ እና እስትንፋስነት ነው።
2.7) በአስተዳደር፤ በሚኒስተርነት፤ ወይንም በመምሪያ ሃላፊነት፤ ወይንም በመምህርነት ለመሳተፍ ፈቃደኛ አይሆኑም ነበር።
የዛሬውን የኢትዮጵያ የሃኪሞች የአኗኗር ዘይቤ አላውቅም። አብዛኛው የጎንደር ከተማ ተማሪወች ያቺ ህልማችን የእዮር ገነት አድርገን የምናስበው የጤና ባለሙያነት ነበር። ምክንያቱም ሃኪሞች ሮል ሞዴሎች ስለሆኑ። ያን እያዬን ስለምናድግ።
በእኔ ዕድሜ አንዲት ነርስ ሲስተር መለሱ ተሰማ ሹፌሯን አግብታ፤ አስተምራ ዶክተር አድርጋዋለች። የእሷ እናት የመነኩሲት ጣይቱ የእስልምና እምነት ተከታዩን ጋሼ ዶር መልኬን አግብታለች። ተቋሙም ሹፌሩን ለታላቁ ልዕልና የህክምና ባለሙያወች ቁንጮ አብቅቶታል። ይህ ትንግርት ለትውልዱ ትሩፋቱ፤ የፈካ ታሪኩ ነው። አሁን በቅርቡ ነው የጋሼ ዶር መልኬን በሥጋ መለየት የሰማሁት። መጽናናትን ለሁሉም እመኛለሁኝ። የሠፈራችንም ሰው ስለሆነ ታሪኩን ጠንቅቄ አውቃለሁኝ። ከእለታት በአንዱ ቀን እኔ በመራሁት ስብሰባ ላይ ተገኝቶ የሰጠኝ ዕንቁ ሃሳብ የሙሉ ዕድሜዬ ሽልማት ነው።
ለእኔ ለሥርጉተ ሥላሴ የጤና ባለሙያ ንጹህ የሰባዕዊ መብት ተሟጋች ነው ብዬ አምናለሁ። ጥሪውም ተግባሩም ሰውኛ እና ተፈጥሮኛ ስለሆነ ከዚህ ጸጋው አፈንግጦ ይኖራል ብዬ አላስብም። ይህ ዩንቨርሳል ሰውኛ ተፈጥሮኛ ጸጋ ውጪ ወጥቼም እጅግ ከምረካበት ግሎባል ጉዳዮች አንዱ የሃኪሞች ወጥ የሆነ፦ ልዩ፦ ልባዊ የርህርህና ስጦታ ነው። የእኔ ሃኪሞቼ #መላዕኮች ናቸው።
በዚህ ዙሪያ ልጽፍ አስብ እና የትኛው ቃላት የውስጤን መሻት መግለጽ ይችላል ስለምል ብቻ አልፃፍኩትም እንጂ ሃኪም ብርሃን፤ ሃኪም ተስፋ፤ ሃኪም አጽናኝ፥ ሃኪም ቤተሰቤ፤ ሃኪም አጋር ነው። የትርታ አጋር። ሃኪም ሰውነትን የተቀበለ - ሰውነትን ያከበረ - ሰውነትን ያነበበ- ሰውነትን የተረጎመ - ሰውነትን ያመሳጠረ ልዩ ሽልማታችን ነው ብዬ ነው እማምነው። ጭንቅ ባላችሁበት ደቂቃ ከፈጣሪ፤ ከአላህ በታች የሃኪሜ ቃል ለእኔ ትንፋሼ ነው። በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ በነበርኩባቸው ጊዜያቶች ሁሉ ሃኪሞቼ ከጎኔ አልተለዩም።
አንዲት ስደተኛ የሥራ ባልደረባዬ ሲዊዝን ለመልቀቅ ብዙ ጊዜ ታስብ ነበር። ልጅ ልትወልድ ሃኪም ቤት ትገባለች። ከዛ ሌሊት እሷ እንቅልፏን ጨርሳ ስትነሳ ልጇ በሃኪሟ ደረት ላይ ተኝታ አገኜቻት። ከዛ በኋላ የሌላ አገር ስደተኝነት አምሮቷ መከነ። ይህን ያደረገው ኃይለ ሚስጢር የሃኪምነት ጥሪ አቅሙ እዮራዊ መሆኑ ነው። ማቃለልም፤ #መዳፈርም የሚገባ አይመስለኝም።
እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ ጥሪ ይዞ ይወለዳል። እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መልዕክት ይዞ ይወለዳል። እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መክሊት ይዞ ይወለዳል። ሃኪምነት ጥሪን በተባ ተግባር ለማስጌጥ ዕድል የሰጣቸው ባለ በረከቶች ናቸው - ለእኔ። ጋውኑ እራሱ ሳስበው ተስፋየን ያፋፋል። ፃዕዳ።
3) "ሙሉለሙሉ ሥራ የማቆም አድማው የማነው?" ለሚለውም እራሱ በዚህ መልክ ከመቅረቡ ጀምሮ የተገባ ነው ብዬ አላምንም። በተጨማሪም በዚህ ስበብ ለሚፈጠረው ቀውስ ለሃኪሞች የሰጠው የኃላፊነት ጫን ያለ ጫናውን በሃኪሞች ላይ ነው ያደረገው። ለመፍትሄ ከሆነ ጥረቱ ግራ ቀኙን በአክብሮት ሊያገናኝ የሚችል ጤነኛ ቀለበት ማሰናዳት ይገባል፤ እንጂ ………
ከዚህ ጋር አያይዞ "የሚጮኽላቸው" ስለላቸው ወገኖችን አጣምሮ ያቀረበበት መንገድም በእሱ ዕድሜ ላሉት የፖለቲካ ግንዛቤ እና ዕይታ ንጽህናውን በመጠበቅ እረገድ ስስ ሁኔታ ነው ያዬሁበት። በሌላ በኩል "የሚጮኽላቸው" ለሌለው እኮ ነው ሙሉ ዕድሜያችን የገበርንበት። ትናንትም ይሁን በቅርቡ የእሱ ከእስር መለቀቀ የእኛ ጥረት እና ትጋት የከወነው ቁም ነገር ነው። እስር ቤት ሆነው የመታከም አቅም ለሚያንሳቸውም ኢትዮጵውያን ልግሥናቸው አንቱ ነው። ውጭ አስወጥተው ያሳከሙ የተግባር ዲታወች ትናንትም ነበሩ፤ ዛሬም አሉ አባ፤ እማ መስጠት ኢትዮጵውያን።
ስንቱ ይዘረዘራል ብራናውስ ብዕራዊ ቀለሙስ ይችለዋልን? እኔ እንዲያውም እንደምን ብንፈጠር ይሆን ለሰከንድ መንፈሳችን ካገራችን ጋር ኢትዮጵውያን ብዬ ሁሉ አስባለሁኝ። ከዚህ የ193 አገሮች ዜጎች ይኖራሉ። መረጃው ትንሽ ቆዬት ቢልም። እንደ ኢትዮጵውያን በአገሩ ጉዳይ፤ በህዝብ ጉዳይ ሊቀ - ትጉኃን አይቼ አላውቅም። ወጣትነታችን ጥሎን እብስ ያለው፤ ብዙ ዕድሎቻችን አጥፈን ለህዝባችን እፎይታ መትጋታችን፤ ማገዶነታችን ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ በመሆን ነው። ከፈጣሪ የተሰጠን ጸጋም ይመስለኛል።
ህዝባችን መኖራችን ነው። ህዝባችን ናፍቆታችን ነው። ህዝባችን ተስፋችን ነው። አለን የምንለው የህዝባችን መከፋት አጀንዳችን ብቻ ሳይሆን መርኃችን መኖራችን በማድረጋችን ነው። ስለዚህም ለጤና ባለሙያወች ድምጽ በመሆን ረገድ የተለመደ ተግባራችን ነው እየከወን የምነገኜው። ራህብ በድርቅም፤ በተፈጥሮ አደጋም፤ በጦርነትም ይመጣል። ለዛም እኛ ኢትዮጵውያን ስስታም አይደለነም። በአቅማችን ልክ እንደ ጥሪያችን የድርሻችን እንወጣለን። ለጥሪያችን #ፕሮፖጋንዲስት በፍጹም አያስፈልገነም።
በብዙ ታጋሼ ነው አንዳንድ ሚዲያወችን እማዳምጠው። ፕሮፖጋንዲስ ሚዲያወችን የብልጽግና ይሁን የተቃዋሚ አላዳምጥም። በሃሳብ ጉዳይ ሚዛናዊ የሆነ፦ ትውልድ ጠቀም አጀንዳወችን የሚያነሱ ሚዲያወችን ነው እማደምጠው። እማይመቹኙን ሚዲያወች ይበልጥ ማድመጥ እፈቅድላሁኝ። በሌላ በኩል ልማርባቸው የምችላቸውን መሰናዶወች በተለይ ከትውልድ ተስፋ ጋር ቀና ዕይታ ያላቸውን ዝግጅቶችንም አዳምጣለሁ። ለማዳመጥ ሙሉ ትዕግሥቱ አለኝ። ይሄኛውን የልጅ ቴዲን ግን አቅም አጣሁኝ። እና አቋረጥኩት።
አሁን ባለው ያለየለት ቅይጥይጥ የኃይል አሰላለፍ ማንም ሰው የመረጠውን መስመር መከተል ሙሉ መብት ነው። የእኔ ግዴታ ይህንን መብት ማክበር ነው። አክብሮ መሞገት ግን አይቀሬ ነው። ካዳመጥኩኝ። ካዳመጥኩኝ ወይ ከፔጃቸው ላይ ወይ ከራሴ ፔጅ ላይ እንዲህ ይፃፋል። ምንም የማልላቸው ሚዲያወች ስለማላዳምጣቸው ነው። ህዝብን ከስጋት ለማዳን አቅጣጫው አይመቸኝም። እርዕስ ምርጫው፤ የሚጠቀሙበት ቀለም ሁሉ ለህዝብ የውስጥ መረጋጋት በእጅ ባለው ሁነት መጠቀም እንደምን ያቅታል።
በጉዳት ላይ ንጉሥ ሆይ! ይህን አላዬህውም እና እኔ ላስታውስህ አንተም #ትሬኮላታውን አጠባብቅ የሚገባ አይመስለኝም። ለአገርም መፍትሄ አያመነጭም። ሙሉ ፯ ዓመት ጭንቀት በቦንዳም፦ በችርቻሮም ሲቀና ተስፋ አብሮ ተጎሳቁሏል። በግራ ቀኙ የፖለቲካ ፍልሚያ። በሚዲያወች ዘርፍ ይሁን በፖለቲከኞችም ያለው አቋም መሃል ላይ ነን የሚሉ አንድም የህወሃት ፍቅረኞች ሲሆኑ ሌሎች ትናንሽ እርማት አድርጎ ራሱን ሳያሳጣ ብልጽግና እንዲቀጥል የሚሹ ናቸው። ግራቀኙ ለአማራ ህዝብ ንቅናቄም ደጋፊነታቸውን ቢያሳዩም መዳረሻቸው አፍቅሮተ የኢሃዴግ ቤተኞች ለዘላለም እንዲገዙ፦ እንዲነዱ የሚሹ ናቸው።
ጥርት ባለ የተቃውሞ አስላለፍ ውስጥ ስር ነቀል ለውጥ የሚሹ፤ አብይዝም የመፍትሄ አካልነቱን ፈጽሞ የማይቀበሉ፤ ዓላማ እና ግባቸውን የቀረጸ የተፃፈ ድንጋጌ የሌላቸው፤ አገር ቢረከቡ በዬትኛው ርዕዮት እና ፓሊሲ ህዝብን ሊመሩ እንደሚችሉ ግልጽ የሆነ አቅጣጫ ያልነደፋ፤ የተሰባሰበ መሪ ሃሳብ እና አካልም ያላደራጁ ዜግነትን የጸነሱ ናቸው። ማንኛውም ዓይነት ንቅናቄ ቢችሉ መምራት ካልቻሉ መግፋትን የሚያዘወትሩ ናቸው። ይህን አበጥሮ እና አንተርትሮ ለትውልድ ተስፋ የትኛው አቅጣጫ ይበጃል የሚለውን መለየት ብቻ ሳይሆን አቅምንም በአግባቡ ማኔጅ ማድረግን ይጠይቃል።
በሌላ በኩል በገዢው ብልጽግና የተሰለፋትም ቢሆኑ መንገድ እና ህይወት እኛ ነን የሚሉ ናቸው። ኢትዮጵያ በብልጽግና ሱናሜ ውስጥ ናት በብርሃን ታጅባ ለአፍሪካ አብነቷን ቀጥላለች ባዮች ናቸው፤ ሁሉም በራሱ ፍላጎት ልዕልና እንጂ የዛሬ ፶ ዓመት የነበረው የገበሬ ህይወት ዛሬም ከዛው ነው። ነገስ??? ……
ሌላው ከልጅ ቴዲ ጋር የማይያዘው የጤና ባለሙያወቼ ጉዳይ በግል ተቀጣሪነቱ እና በመንግሥት ተቀጣሪነቱ ያለውን ሁነትም ሰፍቶ የታዬበት ትንተናም አዳምጫለሁኝ በሌላ ሚዲያ። በመንግሥት ያለውን ኃላፊነት ያቆሙ፤ በግሉ ግን ያላቸውን የትርፍ ጊዜ ሥራን ያላቆሙም የህክምና ባለሙያወች እንዳሉ ሲገለጽ ሰምቻለሁኝ። በዚህ ዘርፍ መረጃው ግልጽ ሆኖ ስላልወጣ የማውቀው ባይኖረኝም ሃሳቡ ግን የመንግሥትን ጫና የሚያጠናክር ነው። መንግሥት ሆይ! ይህንንም ዳኜው ዓይነት ይመስላል።
ኢትዮጵያ በጠራ ፍላጎት ራዕይና ግብ ሰውኛነትን፤ ተፈጥሯዊነትን ታስቀጥል ዘንድ ቀናነት እና ቅንነት በግልም፤ በጋራም በሚመሩ የሚዲያ ተቋማት ሊኖሩ ይገባል። ኃይል ያለው ከመንግሥት ስለሆነ እኛ በምንጠቋቁማቸው ስንጥሮች ተበዳዮች ይበልጥ እንዳይበደሉ ብርቱ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል።
አብይዝም ከአክቲቢስትነት፤ ከካድሬ ገፋዊ ሥምሪት፤ ከእልህ፤ ከታዳጊ ወጣትነት ባህርያት ሆነ ከኮበሌያዊ ፋክክር እና እልህ ወደ ምራቁን የዋጠ፤ ወደ አዳልት ደረጃ የሚያሸጋግር የፖለቲካ አቅም ሊኖረው ይገባል። አብይዝም በህወሃት ላይ ያለው የታጋሽነት ሁነት በሌሎችም አገራዊ፤ ብሄራዊ፤ አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ቢደጋግመው ያተርፋል እንጂ አይከስርም።
የሃኪሞች ጥያቄ ግሎባል አቴንሽን ሊያመጣ ይችላል። ለእኔ ከአፍሪካ ቀንድ ውጥረት በላይ የሆነ ክስተት ነው። ስለዚህ በጣም ንጹህ፤ ብልጥ ያልሆነ ብልህነት፤ ፌካዊ ያልሆነ ዕውነታዊነት፤ ጊዜያዊ ያልሆነ ዘላቂ ለትውልድ ሊበረክት የሚችል የፖሊሲ ንድፍ እና ብሩህ ንቅናቄ መንግሥት እራሱ ሊያደርግ ይገባል። ማሸነፍ በድርጊት እንጂ በካቴና ሊሆን አይገባም። አልፎም ድብደባ እንዳለም ሰምቻለሁኝ። ከሁሉም የአብይዝም ፕሮጀክቶች በላይ ይህ የህክምና ባለሙያወች ጥያቄ በልኩ ጥርት ያለ ወሳኝ አቋም እና በሳል መፍትሄ የሚጠይቅ ነው። የነፍስ ነገር። የህይወት ነገር። የትርታ ነገር። የትንፋሽ ነገር አውራ ጉዳይ ነው።
ብልጽግና በዚህ መሰል ግሎባል ጥያቄ የካድሬ ስምሪት አያዋጣም። መኖርን ለማትረፍ ቅንነት እና ቀናነት ይሰነቅ። ፍጥነት ከማስተዋል ጋር ሊዋህዱም ይገባል። የአብዛኝ ጥያቄ ገዢ ሊሆን ይገባል።
ይህን ንቅናቄ የሚያስተባብሩትም ሥራ ባላቆሙ የሙያ ቤተሰቦቻቸው ፍረጃውን በፍጥነት ሊያቆሙት ይገባል። ሁሉም መብት አለው። ተመቸኝ የሚሉ መኖራቸው የሚጠበቅ ነው። የነሱ የማህበራዊ ህይወት ምስቅልቅልም የራሳችን ብለው ሊቀበሉት ይገባል ባይ ነኝ። የብልጽግና አባላት ፓርቲያቸውን ተቃውም ሊወጡ አይችሉም። መርሁ አይፈቅድም።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ህዝብ 20 // 39/// 50// 100// ሚሊዮን ሳለም የሚተጋው ጥቂት ነው። ተጠቃሚው ደግሞ ያልተሳተፈው መስዋዕትነት ያልከፈለው ነው። አሁን ድሎተኞች አዲስ ገቦች ናቸው። ሚኒስተር የሆኑትን እራሱ ብዙወችን አናውቃቸውም። ወደፊትም የሚነዱ ጥቂቶች የሚለየልሙ ብዙወች ናቸው እና። ሁሉንም ነገር በቅድሚያ በአውንታዊነት ማዬት ይገባል። መፍቻው #ቅንነት ነውና።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን፤ አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ