ጥንቃቄ በማስተዋል ቢሆን ……
ጥንቃቄ በማስተዋል ቢሆን ……
ሃኪም ቀስብለው ተራምደው አያውቁም ችግርን ለመፍታት፤ ለህይወት ለመድረስ መጣደፍ ነው። ይህ ጸጋ ግሎባልም ነው። ጥሪያቸውም ነው። #ብሩኮች።
"ቤት በጥበብ ይሠራል፤
በማስተዋል ይጸናል።"
(ምሳሌ ምዕራፍ 24 ቁጥር ፫)
የኢትዮጵያ ሃኪሞች እጅግ ሐዋርያ ከሆነ ትዕግሥት በኋላ፤ ዕውነት የሆነ ጥያቄያቸውን ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ለአብይዝም መንግሥት አቅርበዋል። ጥያቄው ትክክለኛ እና ዕውነትን የገለጠ አቤቱታ ነው። ነገር ግን ጥያቄው አቅጣጫውን ስቶ ካለስኬት ተዳፍኖ ጉዳት አምራች እንዳይሆን ብርቱ ጥንቃቄን ይሻል።
"ጠቢብ ሰው ብርቱ ነው፤
ዓዋቂም ሰው ኃይሉን ያበዛል።"
ከሃኪምነት በላይ ምድራዊ ልቅና ያለው የለም የሚል እምነት አለኝ። ከእግዚአብሄር በታች ሩኃችን በህክምና ባለሙያወች መዳፍ ላይ ነውና። ለእነሱ በምንም ሁኔታ ፕሮፖጋንዲስት አያስፈልጋቸው። ለገኃዱ ዓለም የሩህ መሪ ናቸውና። አዛኞች፤ አጽናኞችም። አይደለም ስለራሳቸው ስለእኛም የቅዱስ ሩፋኤል ሥልጣን የተሰጣቸው ናቸው እና። ፀጋቸው ሰማያዊ። ጥሪያቸው ሰባዕዊ ነውና። በአቤቱታቸው ላይም የጋመ ነዲድ፤ ወይንም እንክርዳዳ መቀዬጥ የተገባ አይመስለኝም። ታቅዶም ይሁን ሳይታቀድ። አቤቱታቸው #ንጽህናውን የጠበቀ ድንግል ነውና ምንም ቅጥያ ፍላጎት ሊቀጣጠልበት አይገባም።
#ሦስት ጉዳዮችን ለማጣቀሻ አቀርባለሁኝ።
1) ታስታውሱ ከሆነ በአንድ ወቅት አዲስ አበባ ከተማ ላይ "ለመስቀሉ እሮጣለሁ" የሚል መንፈሳዊ መልዕክትን በቅድስና የያዘ መሰናዶ ተጀመረ። እራሳቸው ሠርተው አቅም #መፍጠር የተሳናቸው ፖለቲከኞች፤ ቲ ሸርቱን አሰርተው መሪው እኛ ነን የማለት ያህል ማህበራዊ ሚዲያውን ናጡት። እና ምን ሆነ? ያ ቅዱስ መንፈስ #ለጥርጣሬ #ተጋለጠ እና ታገደ።
ቅድስቷ በበረከቷ የምትበርክበት ዕለትም ታጠፈ።
2) በሌላ በኩል የወልቃይት የጠገዴ፤ የጠለምት፤ የአዳርቃይ፤ የአድረመጥእና የራያ ጉዳይም #ዓለም ዓቀፋዊ አጀንዳ ነው። በደራሽ ስሜት እና በአብይዝም ዘመን በበቀሉ መሻቶች ጋር ሊዳበል በፍጹም አይገባም። ይህ አንከር ጉዳይ ለዬትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ወይንም ንቅናቄ ሊሰጥ የሚችል አጀንዳ #በፍጹም አይደለም። በአነሳሱም በዬትኛውም ዘመን በአገር ውስጥ ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተሰናዱ የሰላማዊ ሰልፍ ይዘቶች በፍፁም ሁኔታ የተደራጄ፤ የህዝብን ሁለመናዊ ጥያቄ በቅጡ አድሬስ ያደረገ፤ ልብን እና መንፈስን በአኃቲነት የገዛ፤ ያስተዳደረ፤ የተበተነን መንፈስ የሰበሰበ ታሪካዊ ክስተት ነበር። የህዝብን የማህበራዊ ንቃተ ህሊናም የገለጠ ብቁ ክስተት።
የንቅናቄው ሂደት በእድገቱም ሆነ በይዘቱ በልዩ ሁኔታ ልቅናን የተቀናጄ ስለሆነ በማስተዋል ሊታይ የሚገባው በኽረ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያኒዚም መለያዬ መጠሪያዬ የሚል ፖለቲከኛ ሁሉ ከእራሱ ጋር ታርቆ በጥልቀት ሊያስብበት የሚገባ ካስማ ፖለቲካም ነው። ህወሃትን ለማዳን ይህን ጥያቄ ማግለል ትናንትም ዘጭታ ፈጥሮ ከመንበሩ ነቅሏል፤ ነገም ዘጭታ ያመጣል። ለቀኑ ቀን የፈቀደለት ተሰጥዖ ነውና። አቅም ጠፍቶ፤ ትዕግስት ተሰዶ፤ ያደራጁትን በትኖ በግርግር ፖለቲካ ልዳኝህ ቢባል አይሆንም። ጥያቄው በተፈጥሮው ነጥሮ የወጣ አህጉራዊ ጥያቄ ሆኗል እና። ስለሆነም ባለኮፒራይቱ እኔ ነኝ ማለትም አይችልም።
ስለሆነም " ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳሽ " ከምንም ጉዳይ ጋር ሊነካካ የማይገባው የኢትዮጵያ #ሉዓላዊነት፤ ባለፈም #የአፍሪካ ቀንድ፤ እና #የመካከለኛው ምስራቅ አፍሪካን ፖለቲካ ገጸባህሪ ሊለውጥ የሚችል #ጉልላታዊ አመክንዮ ሆኗል። ከፍ ያለ የፖለቲካ አቅምነቱ #ዘመን ሸልሞታል። ስለሆነም ይህን ጉዳይ #ኮፒራይት ውስጥ ማስገባት የተገባ አይደለም። ለቀቅ አድርጉት። መሰናክል አትፍጠሩበት። ሌላ ጣጣ ይዞ ደግሞ አዲስ የመገበር የሽብር ኢንሴክት ሊፈጥር አይገባምና።
አወዛጋቢ የተባሉ በዓቶችን በሚመለከት ትርፍ እና ኪሳራው ዝልቅ ስለሆነ መንፈስን አርጋግቶ ብልህ ልቅና እና #ዊዝደም ይመራው ዘንድ መፍቀድ ይገባል። አቅመ ቢስ መንፈሶች የያዙትን እስኪ አሳምረው ለመምራት እና ለስኬት ያብቁት። እያዬን ኦኮ ነው። በተለይ በማንኛውም ሁኔታ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ሆነ፤ ከህወሃት አቅም ጋር ተዳብሎ የሚገኝ መንፈስ ይህንን ካስማዊ ጉዳይ እመራለሁ ብሎ #ዳዴ ቢል ቅንጣት ስኬት ፈጽሞ አይኖረውም። ኪሳራ እና ውርዴትን ለመቀለብ ከመፍቀድ በስተቀር። በእልህ ብዙ ነገር ከመበላሸቱ በፊት ያላዋቂ ሳሚ ሁነቶች ሊታረሙ ይገባቸዋል።
3) የኢትዮጵያ የፈውስ ማዕከል የሆነው የሃኪሞች ንቅናቄን በሚመለከትም አቅጣጫውን ለመቀዬር ብዙ ሁነቶችን አስተውላለሁኝ። ለዕውነተኛው ጥያቄ በድሪቶ ጠቅልሎ እሳት ውስጥ የመጨመር ያህል ይሰማኛል ጥያቄያቸውን ከተፎካካሪ ሃሳቦች ጋር መለጠፍ። ጥያቄውን ለፖለቲካ ፍጆታ ለማወል መፎካከር የተገባ አይመስለኝም። የኢትዮጵያ ሃኪሞች እርኃባችሁ ይቀጥል ካልሆነ በስተቀር ……
አንድ ሰው ነፃነቴን እሻለሁ ብሎ ሲታገል፤ ሌላው የሚያደርገውን ማናቸውም ንቅናቄ #ነፃነት ሊሰጠው ይገባል። አሁን ያለውን የአብይዝም ሥርዓት ለመነቅነቅይሁን አስገድዶ ጫና ለመፍጠር የራስን አቅም ጠንስሶ፤ አደራጅቶ እና መርቶ ለስኬት ማብቃት እንጂ ዜጎች ከራህብ ጋር ተፋጠው፤ የመኖር ዋስትናቸው አደጋ ላይ ሆኖ መንፈሳቸው በጭንቀት እዬተናጠ ለእኔ ፍላጎት ተማገዱልኝ #ጭካኔ ነው። ጸረ ሰባዊነትም ነው። ደፍረን ክንንቡን ስንገልጠው።
እዬሆነ ያለው ለሃኪሞች ሰላማዊ ጥያቄ መፍትሄ ሰጪ ሳይሆን #የስጋት ምልክት ሆኖ፤ ሃኪሞች እዬታደኑ ለካቴና እንዲዳረጉ፤ ጥያቄው ህገወጥ ነው ተብሎ በር እንዲዘጋበት የሚያደርግ ሁነት ነው እኔ እምመለከተው። ሁሉን ነገር ከፖለቲካ ጋር ማነካካት፤ ማያያዝ የተገባ አይደለም። የኢትዮጵያ ባተሌ የህክምና ባለሙያወች ጥያቄያቸው የሥልጣን ሹምሽር አይደለም። ፈጽሞ። መኖሬ መኖር አቃተው። ስለሆነም መኖሬን የሚያስቀጥል የኢኮኖሚ አቅም እና የደህንነት ዋስትና ይሰጠኝ ነው። ንጹህ፤ ቅን፤ ቀና ጥያቄ ነው።
ይህን ጥያቄ አሻክሮ፤ ወይ #አጎድጉዶ የአገር እና የመንግሥት ችግር #አማጭ እንዲሆን መነካካት የሚገባ አይደለም። ተጨማሪ ችግር ይፈጥራል። ተጨማሪ ስጋት ያመርታል። ተጨማሪ ጫና ይፈጥራል። ተጨማሪ #ጥርጣሬ ይፈጥራል። ስለሆነም የሃኪሞች ቅን ጥያቄ #ደባል ፍላጎት ሊመረትለት አይገባም። ተዋቸው! የተማሩ እኮ ናቸው። የህይወትም ሰባዕዊ መሪም መርኽም ናቸው ሃኪሞች።
በማንም፤ በዬትኛውም ተቋም ይሁን ግለሰብ ፈቃድ ያልተፈጠረ ንጹህ ጸዓዳውን የሃኪሞችን ጥያቄ እባካችሁ ተውት። በራሱ መንፈስ በቅሎ፤ ጸድቆ ስኬትን ያበቅል ዘንድ ፖለቲከኞች ፈቅዳችሁ እና ወዳችሁ #ምህረት ስጡት። ጥያቄያቸው የታመቀ፤ የታፈነ ይሆን ዘንድ መንገድ ጠራጊ ላለመሆን በማስተዋል ማሰብ ያስፈልጋል።
በተለይ ሰፊ ተከታይ ያላችሁ ሚዲያወች "ሁሉ ተፈቅዶልኛል፤ ሁሉ ግን አይጠቅምም።" የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መርኽን ብትፈቅዱለት። በሁሉ ነገር ላይ፤ በሁሉ ክስተት ላይ ፖለቲካዊ ምኞትን፤ ፍላጎትን ለመጫን መቻኮል፤ በስውሩ ለእኔ ለሃሳብ ሳይለነት ዲስክርምኔሽን ማወጅ ይመስለኛል። ይህ ደግሞ የአቤቱታውን ግሎባል አቅምም ይጫነዋል። ቅኑ አቤቱታ ወደ ፖለቲካዊ ፍላጎት አመክንዮውን ለማሸጋገር ከተጣረ። ይህ ደግሞ ለቀጣዩ ለሃኪሞች ተስፋ የትምህርት #ዕድልም ሆነ፤ የሥራ ዕድል ስጋትን ያጫል።
በሌላ በኩል የከፋው፤ የተጨነቀ፤ የባሰው ወገን በራሱ መንገድ አቤቱታውን እንዳያቀርብ እንዲህ ብባልስ ብሎ ስጋት ውስጥ እንዲያዋኝ ማድረግ ለእኔ #ጭካኔም ነው። የዕውነት ጭካኔ ነው። የአብይዝም መንግሥት ልብ ቢያገኝ፤ ለጥያቄው ዕውቅና ሰጥቶት ብሄራዊ መፍትሄ ይሰጠው ዘንድም ክፍት ቦታም ያስፈልጋል። መሞከር፤ መሞከር፤ ደግሞ መሞከር ……… ጥያቄው ከህግ በላይ ልሁን ያለ አይደለም። እናቱን አሻቅቦ አልተናገረም።
#በጥልቀት ……
መተንፈስ ያቃታቸው የሃኪምን አስቸኳይ እገዛ የሚጠይቁ ሚሊዮን ወገኖቻችንም ጉዳይን የእኔ፤ የእኛ ማለት በተቃዋሚውም ሆነ በገዥውም የአብይዝም መንግሥት፤ ዕውቅና ሊሰጠው ይገባል። ችግሩን በግብር ይውጣ፤ የትም አይደርስም ብሎ እንደ አልባሌ ማዬት አይገባም። ግሎባል የመሆን አቅሙ ጠንካራ ነውና። በዬትኛውም ዓለም ሙያው ወጥ እና ዕውቅ ነውና።
የሃኪሞች ድምጽ ሆነ፤ ይህን ጉዳይ የሚመራው ማንኛውም አካል አቤቱታውን በጥንቃቄ እና በማስተዋል ሊመሩት ይገባ። ንግግሮች፤ ማብራሪያወች፤ ስልጋኖች በጥንቃቄ፤ በማስተዋል አሰናድቶ መምራት ያስፈልጋል። ለቃላት ለፊደላት ሁሉ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል።
የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጥንቃቄ ይጠይቃል። ሳያስቡ ቀርቶ ታስቦበትም ዳጥ እና ምጥ ነው። ቅጽበታዊ መሻቶች ለስኬት አያበቁም። ጉዳት ነው መደምደሚያወች። እራስን ችሎ የራስን ሃሳብ አፍልቆ፤ ተቋም ፈጥሮ በራስ ባለቤትነት የሚመራ መንፈስ መፍጠር ብልህነት ነው። በሌላው ንጹህ መንፈስ ተዳብሎ ግን #ይኮሰኩሳል።
አንድ ሰሞን የመርካቶ ነጋዴወች ንቄናቄ ነበር። ፈላ ……… ፈላ ……… ተንተከተከ ……… ይለያል ጉዱ ተባለ። የተጎዳ ተጎድቶ - ሰከነ። ተግ አለ። አሁን በሃኪሞችም ጉዳይ ማፍላትም፤ ማብረድም የባለቤቶች ይሆን ዘንድ #ነፃነቱ ሊሰጥ ይገባል ነው የእኔ በኽረ ጭብጥ። ከጉዳቱ በኋላ ዞር ብሎ የሚያዬው የለም ---- ና። በዘመነ ህወሃት ደራ ላይ ራሱን በቤንዚን ያነደደ መምህር ነበር። በወቅቱ የትግል ማጋጋሚያ ነበር። አሁን ያን ሰማዕት ትዝ ብሎት የሚያውቅ ተቋምም፤ ይሁን ግለሰብ፤ ሚዲያም የለም።
የትኛው መንገድ ነው ለንጹሁ ጥያቄ መፍትሄ ሊያስገኝ የሚችለው? የትኛውስ መንገድ ነው መሰናክል የሚፈጥረው? ችግሩን የተሸከሙት ባለቤቶች እንዲወስኑበት ነፃነት መስጠት ያስፈልጋል። ስኬት ስክነትን እና ማስተዋልን ይጠይቃልና።
ሸበላ ሰንበት። አሜን።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
10/05/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ