አብሶ በትምህርት ዘርፍ #ዛሬን #ሳያመልጥ መሻማት ነገን #ያበጃል። ዛሬ አጀንዳ ሲሆን ነገ #ያበራል። ነገ በዛሬ #የተባ ድርጊት ብቻ ነው የሚገኜው።

 

አብሶ በትምህርት ዘርፍ #ዛሬን #ሳያመልጥ መሻማት ነገን #ያበጃል። ዛሬ አጀንዳ ሲሆን ነገ #ያበራል
ነገ በዛሬ #የተባ ድርጊት ብቻ ነው የሚገኜው።
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 May be an image of 1 person and grass
 
በአገሬ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ነክ ጉዳዮች፤ ለዛውም በአማርኛ ቋንቋ ፕሮፖጋንዲስት አያስፈልገኝም። ከጋሜየ እስከ ሙሉ ዕድሜ ተዘለቀበት እኮ። የሠራሁበት እኮ ነው። በሌላ በኩል እያንዳንዱ ሰው በራሱ ህሊና የመጠቀም ሙሉ መብት አለው። በክራይ፤ በወለድ አገድ እስካላያስያዘው ድረስ። ሙሉ ዕድሜየን ነፃነቴን ለማንም ለምንም አሳልፌ ሰጥቼ አላውቅም። እኔን ሆነ ህሊናዬን አከራይቼ አላውቅም። የፈለገ አገረ ገዢ ይሁን። የፈለገ ሚሊዮኖች ይከተሉት። በሌላ በኩል ደግሞ እኔ ጎርፍ አምጥቶ ደለል የሠራብኝ ሴት አይደለሁም። ወይንም አብይዝም ሲመጣ አብሬ መጥቼ #ደራሽ ፖለቲከኛም አይደለሁም። ህሊናየንም ለማንም አከራይቼ አላውቅም። 
 
በፊት ለፊቴ፥ ይሁን በጀርባየ የማስከትለው የሌላ አካል ወይንም ተቋም ወይንም የግለሰብ ፍላጎት እና አጀንዳም የለም። #እኔ እኔ ብቻ ነኝ። በቃ! እኔ እማስበው ከውስጤ የፈለቀ ሃሳብን ነው ሼር እማደርገው። በሌላ በኩል አንድም ቀን የእኔን ግራ ቀኝ ዩቱብ ቻናል፤ ብሎግ፤ ፌስቡክ፤ ራዲዮ ፕሮግራም ሳብስክራይብ፤ ሼር ላይክ አድርጉ ብየ አላውቅም። ወይንም #ፈንድ አድርጉልኝ፤ #ዶኔት አድርጉ ብየ ጠይቄም፤ አስቸግሬም አላውቅም። ለምን? ነፃነቴን አብዝቼ እሳሳለትአለሁኝ።
 
የማስበውን በነፃነት የሚያስገልጸኝ ይኽው መስመር ብቻ ነው። በሌላ በኩል የሰውን ልጅ ፈቅዶ ያድርገው እንጂ እኔ ልጫነው አይገባም የሚል ሙሉ እምነት አለኝ። ፌስቡክ ላይ ሼር እንድታደርጉ እጠይቃችሁ የነበረው በእስረኞች ጉዳይ ለዶር ዳንኤል በቀለ ስጽፍ ብቻ ነበር። ያም እንዲዩት እፈቅድ ስለነበር።
 
#ውስጤ የሚለኝን ፈርቼ ወይንም ተሸማቅቄ አላስቀረውም። ገልጬ እነግራችኋለሁኝ።
 
እኔ ፖለቲካን በስማ በለው ሳይሆን፤ ከገበሬው ጋር፤ ከከተማው ነዋሪ ጋር፤ ከወጣቶች ሴቶች ጋር፤ ከሙያ ማህበራት ጋር አብሬ በመኖር የተማርኩበት ዘርፍ ነው። አየር ላይ ይሁን ሞገድ ላይ አልነበረም መነሻዬ። ቋሚ የፖለቲካ ሠራተኛ መሆኔ ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያ ደግማ ልታገኛቸው የማትችል ዕንቁ እንደ ጓድ ገብረመድህን በርጋ የወቅቱ የአገር ውስጥ ንግድ ሚኒስተር ቋሚ ተጠሪ የነበረ፤ እንደ አንባሳደር ወንድወሰን ኃይሉ፤ በሚሊተሪውም ከፍተኛ የኮር አዛዦች፤ የሆለታ ገነት አስተዳዳሪወች እና ሌሎችም ወዘተ በስስት ኮትኩተው እንደ ልጃቸው ነው ያሳደጉኝ። ጥርት ኮለል ያለ ታሪክ ነው ያለኝ።
 
ወደ ሚዲያ ስመጣም እራሳቸው ክስተት የሆኑ ዓለም ዓቀፍ ጋዜጠኞች ናቸው ያበቀሉኝ። የገጠሩ፤ የከተማው፤ የጫካው፤ የእስር ቤቱ፤ የስደቱ፤ የተለያዩ ብሄራዊ እና ዓለም ዓቀፍ፤ ኢቤንቶች፤ ጉባኤወች፤ አጫጭር ኮርሶች እና ሰሚናሮች የራሳቸው የሆነ ዕውቀት፤ ተመክሮ እና ልምዳቸውን አጋርተውኛል። እኔ ሁልጊዜ ተማሪ ነኝ። መማር ደግሞ ዩንቨርስቲ ብቻ አይደለም። የትም ቦታ፤ በማንኛውም ጊዜ መማር ለፈቀደ ሁሉም የመኖር ገጠመኝ የዩንቨርስቲ ደጀሰላም ነው። 
 
ቀደምት የፖለቲካ ሊቃናት እየተከታተሉኝ፤ እያረሙኝ ኮትኩተው ነው ያሳደጉኝ። አሁን እማየው ነገር ቢጠቅም ኖሮ እኔም አበረታታው ነበር። ግን አይጠቅምም። ትምህርት ውጤቱ የሚታየው በረጅም ጊዜ ጥረት ነው። ዛሬ አይታይም። ስለሆነም ልጆች ዕድላቸው እንዳያመልጣቸው በትምህርት ገበታቸው ላይ መገኜት አስፈላጊ እና መሠረታዊ ጉዳይ ነው። የአማራ ልጆች በየዘመኑ በሚነሱ የፖለቲካ አለመግባባቶች ዕድላቸውና ተስፋቸው ሊገበር አይገባም ባይ ነኝ። 
 
ነገ የአማራ ልጆች መሪ እንዲሆኑ ከተፈለገ፤ ፊልድ ማርሻል፤ ጄኒራል፤ ኮነሬል እንዲሆኑ ከታቀደም፤ ዛሬ ትምህርታቸው ላይ አትኩሮት እንዲያደርጉ ማድረግ የትውልዱ በኽረ አጀንዳ ሊሆን ይገባል። እንዲያውም እኔ በዘርፋ ለአዲስ ገቦች የአማራ ፖለቲከኞች ቦታ ለቅቄ በዝምታ ነው የቆየሁት። ብዙ ግሎባል ትጋቴም በጸጥታ ነው የባጀው። መጋፋትም መሻማትም ግጥሜ አይደለም። እንዲያውም ለእኔ የእረፍት ጊዜ ነው የሰጠኝ። እስኪ የአማራ ፖለቲካ በአዲስ አቅም ይድላው በሚል አቋም ጸንቼ ነው የቆየሁት። መገፋፋት መፎካካር አልወድም። በዚህ ሂደትም የማገኘው ብጣቂ ነገር፤ የማጣውም ምንም ነገር አይኖርም። ትውልዱ ስለሚያሳዝነኝ ብቻ ነው በነፃ በራሴ ጊዜ እና ወጪ እምተጋው። ነገም ልሙጥነት ስለሚያስፈራኝ። 
 
"#አትማሩ" የትውልድ ያልሆነ፤ የትውልድም የማይሆን።
 
ልጆች ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ ደህንነታቸው የሚያሰጋ ከሆነ፤ ወጀቡን ዝቅ ብሎ ማሳለፍ ይገባል። ከዛ በተረፈ ግን ልጆች መደበኛ ሥራቸው መማር ነው። ልጆችን ከተፈጠሩበት ጸጋ ማራቅ ኩነኔ ነው። በእኛ ዘመን "#የአትማሩ" የኢህአፓ መፈከር ስንት ሳይንቲስት፤ ስንት ፈላስፋ፤ ስንት አስትሮኖመር፤ ስንት የህክምና ባለሙያ ሊሆን የሚችል ወጣት አጉል ቀረ???
 
በሁለቱም በደርግም ባሩድ፤ በኢህአፓም አልቋል። በዛ ፍርሃት ውስጥ እየተጨናነቅን ያደግን ደግሞ ከፊሉ አቋርጧል፤ ከፊሉ ተሰዷል። የተሰደደ ሁሉ #አይቀናውም። ስደት ብዙ ትብትብ መከራ አለበት። አካሉ የጎደለ አለ። ወደ ሌላ አገር ለመሻገር በተደረገው ጉዞም ገጠር አግብተው ወልደው እዛው የቀሩ አሉ። የተሳካላቸው ደግሞ እንደ ፕሮፌሰር ዶር ብርሃኑ ነጋ ከስንት ዘመን ድካም በኋላ የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስተር ሆነዋል። ይሄ ስለተማሩ የተገኜ ብቸኛ መፍትሄ ነው። ኢህአፓ አገር ውስጥ "አትማሩ" ያለውን መፈክር ውጭ አገር ላይ ስደተኛ አባላቱን ይሁን አካላቱን፤ በተለያዬ ምክንያት የተሰደዱትን ወገኖቹን "አትማሩ" ብሎ አላገደም። የቀናቸው ሳይንቲስት እስከ መሆን ደርሰዋል። ከዚህ የሂደት ከውድቀቱም ሆነ ከትርፋ ብራና ትውልዱ ሊማር ይገባል።
 
በተለይ ጎንደር በዘርፋ እጅግ የተጎዳ ነው። ጂኦ ፖለቲካል አቀማመጡ "ከፋኝ" ላለው ሁሉ መጠጊያ ስለሚሆን። ያ "አትምሩ" ዘመቻ የጠቀመው የለም። በወቅቱ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ልጆች ማስጠንቀቂያ ይደርሳቸዋል። ስለሚፈሩ አይሄዱም። ዕድሜያቸውም አብሮ ይጓዛል። የወጣትነት ዘመናችን ጋር የተላለፍነው ብዙወቻችን እኮ በዚህ ነው።
 
በዛ ዘመን ሰላማቸው ሳይነካ የተማሩት አቶ ኃይለማርያም ደስአለኝ ሳይሰደዱ በሰላም ተምረው ትምህርታቸውን ጨርሰዋል። ዩንቨርስቲም ዕድሉን ተጠቅመው የአገር መሪ ጠቅላይ ሚር መሆን ችለዋል። ደቡብ ላይ "አትማሩ" ትናንትም አቅም አልነበረውም፤ ዛሬም አቅም አላገኜም። አቶ ኃይለማርያም እሳቸው ከደቡብ ናቸው። የዛሬ አለመማር ከ20/25 ዓመት በኋላ የፖለቲካ ውክልናው አማራ ክልል አሁን ካለው #በባሰ ይሆናል። ዘለግ አድርጎ ይህን ማየት ይገባል። 
 
ፖለቲካ እልህ ሳይሆን ብልህነትን ቢመገብ ለትውልድ የሚሆን ስኬትን ያጎናጽፋል። ፖለቲካ የሚያመዝነውን ትርፍ ላይ በመትጋት ሊሆን ይገባል። ትምህርት አትራፊ ክስተት ነው። ዕውቀት እኮ ነው መኖራችን ያሰለጠነው። አሁን እምንገናኝበት የማህበራዊ ሚዲያ መድረክ እኮ ሥልጣኔው ከትምህርት፤ ከዕውቀት የመጣ ነው። ልዩ የአለም ክስተት ላይ ነው እምንገኜው። ከጨለማ ብርሃን፤ ከግራጫማ ብርሃን ይበልጣል። ዕውቀትን ማግለል እና ማስገለል ጨለማን እና ግራጫነትን መፍቀድ ነው። መማር መኖርም ነው። መኖር ይጨልመው ምን ዓይነት ፈሊጥ ነው። እሰቡበት። 
 
ለፖለቲካ ፋክክር የቀለም ዕውቀት ሙሉ አቅም ይጠይቃል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚመራው በቀለም ዕውቀት አዋቂወች በባለ ዲግሪወች ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ በተፈጥሮ አዋቂ፤ በእግዚአብሄር ሙሉ ጸጋ የተሰጣቸውን አያስጠጋም። ውክልናም የላቸውም - ሊሂቃን።
ዛሬ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ኃላፊነት ለማግኜት ምን ያህል ድግሪ አለው? ምን ያህል የአገልግሎት ጊዜ አለው? ከየትኛው ዩንቨርስቲ ነው ዲግሪውን ያገኜው? የየትኛው የዞግ አባል ነው? የሚለው ከምኞት ጋር ተያይዘው የሚቀርቡ ሞጋች ጥያቄወች ናቸው ጠረጼዛ ላይ ያሉት ሞጋች ዕሳቢወች።
 
በሌላ በኩል ለአህጉራዊ ይሁን ለዓለም አቀፋዊ የሥራ ዕድልም ይህ ወሳኝ ጥያቄ ይከተላል። አይደለም ከትምህርት እራስን አግልሎ ይዘው የተገኙት እንኳን አማራ + ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ከሆኑ ይጠረጠራሉ። አይታመኑም። #ይገለላሉ። ይህም ቢሆን ተስፋን ለሚሰንቅ አንድ ንቅናቄ ይዞ መገኜት፤ ሆኖ መገኜት ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገም ዕውቅና ያለው የዕውቀት መረጃን አሟልቶ መገኜት ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም። በስተቀር ተስፋ ይለሞጣል። 
 
በሌላ በኩል ለወላጆችም ጫና ነው። በዚህ የኑሮ ውድነት። አንድ ተማሪ 7ኛ በሚሆንበት ጊዜ የአንደኛ ክፍል ተማሪ ከሆነ፤ 12ኛ ክፍል በሚሆንበት ጊዜ የ7ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን ያለውን የመኖር ጫና እሰቡት። መኖር ሞናትነስ እና ተስፋ ቢስ ይሆናል። በ7 ዓመቱ የአንደኛ ክፍል ተማሪ መሆን የሚገባው በ14 ዓመቱ የአንደኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን አስሉት? ዩንቨርስቲም ሲገባ እንዲሁ ነው የሚሆነው።
አባት እና ልጅ ወይንም ታላቅ ወንድም እና ታናሽ ወንድም ይሆናሉ በአንድ ክፍል አብረው የሚማሩት። ይህ ደግሞ በራሱ የዕድሜ ከፍነት እና ዝቅነት እራሱን የቻለ የማንነት ቀውስ ያመጣል። የሥነ - ልቦና ጥቃትም ሊያመጣ ይችላል። አይደለም በዓመታት ልዩነት በወራት ልዩነትም ብዙ የማይገጣጠሙ፤ የማይመጣጠኑ የባህሬ #ክፍተቶች ይኖራሉ።
 
ለየትኛውም ደረጃ መሪ የሆነ ሰብ ይህን አርቆ ማሰብ ያስፈልገዋል። ጉዳትን ቀንሶ ጥቅም የሚያበዛውን መንገድ መምረጥ ቢጠቅም እንጂ አይጎዳም። ላም እረኛ ምን አለም ቢደመጥ መልካም ነው። ተምሮም እኮ ተማሪ ከፈለገው ደረጃ የመድረስ ዕድሉ ጠባብ ነው በዞግ ሥርዓት ዘመን። ለቤተ - መንግሥቱ ቀረብ ያሉ የዞግ አይነቶች አሉ በጥርጣሬ የሚታዩ እና የተገለሉም አሉ።ይህ ለ30 ዓመታት የታየ የሃቅ እንክብል ነው። 
 
ስለሆነም ይዞ መሞገት እንጂ በባዶ እጅ መሞገት ለስኬት አያበቃም። ቢያንስ ያለውን ጠባብ እድልም በራስ ፈቃድ መዝጋት የተገባ አለመሆኑ ሊታመንበት ይገባል። ዕውቀትን ማግለል ብልህነትም አይደለም። ሙሉ 7 ዓመት በታቀደም ይሁን ባልታቀደም ሁኔታ በአማራ ክልል የመማር ማስተማሩ ሂደት #ተስተጓጉሏል። ጓጉሏል። በዚህ ከቀጠለ ለነገ የአማራ ህዝብ የፖለቲካ ውክልና ጥያቄ የበለጠ መንገዱ ይዘጋል። 
 
ሌላው ልብ ብላችሁ ካስተዋላችሁት የብዙ መግለጫወች፤ ትንታኔወች፤ መሻቶች በአብይዝም ካቢኔ ወይንም የፓርላማ አባላት፤ ወይንም በሠራዊቱ ላይ ያተኮረ አይደለም። አንድ ሰው ጠቅላይ ሚኒስተሩ እና የቅርቦቻቸው ጥቂት ሰወች ተገለው፤ ሌሎችን ግን ከእነ ሙሉ አቅማቸው ለመቀበል ነው ያለው የይለፍ ፈቃድ ሥነ - ልቦና። ለምን? ትምህርት እንደፋብሪካ ዕቃ በገፍ የሚመረት የጀንበር ስኬት አይደለምና። በሌላ በኩል ይዞ የመገኜትን ዕንቁ ገጠመኝ የሚተካ ምንም ነገር እንደለለ ያጠይቃል። 
 
በእኛ ዘመን የእኛ በዕት ጎንደር በትግል ረመጥ ሲርመጠመጥ ጸጥ ብሎ ትናንት ደቡብ ስለተማረ ህወሃት ሥልጣን ሲይዝ ሰፊ ዕድል አገኜ። ደቡብ ህወሃትን - አልታገለም። ደቡብ ለህወሃትም ስንቅ - አላቀበለም። ግን በዘመነ ህወሃት ለጠቅላይ ሚር ደረጃ የደረሰው ደቡብ ነው። ህወሃት መንበሩን ሲለቅም ደቡብ ይህ ነው የሚባል የጎላ ሚና አልነበረውም። ግን በጉልህ በዕድሉ ተጠቃሚ የሆነው የላመ የጣመ ዕድል ባለቤት የሆነው ደቡብ ነው። እራሱ የሲዳማ ክልልነት ጥያቄ በክብር ነው የተመለሰው። 
 
ደቡብ በሚደንቅ ሁኔታ በዘመነ አብይዝምም አሁንም እየተማረ ነው። ይህ ሂደት ውጤቱ ዛሬ አይታይም። ነገር ግን ለዛሬ 15/20/25 ዓመታት የፖለቲካው ውክልና የደቡብ በጉልህ ዕድሉን እንዲያስቀጥል ያደርገዋል። እኔ በፖለቲካ ህይወት ውስጥ ፊደል ከቆጠርኩበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ደቡብ የከፈለው #መስዋዕትነት ጉልህ የሆነ አላየሁም። በየዘመኑ ግን የዕድል በረከት ይዘንብለታል። ይህን ከልብ ሆኖ በማስተዋል መመርመር ይገባል። 
 
የአማራ ህዝብ #መስዋዕትነትን የሚመጥን ዕድልን ለማሳካት እኩል ሁሉንም የህይወት ዘርፎችን የመከወን ጥበብ ይጠይቃል። ዛሬ ያልተማረ የአማራ ልጅ፤ ነገ የአገር መሪነት ይሁን፤ ከዛ ያነሱ ዕድሎችን ለማግኜት ጋዳ ይሆንበታል። ስለዚህ ልጆች የዛሬ ዕድላቸው #ታጥፎ ነገ ተስፋቸውን እንዳያጡ ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ ማበረታቱ የተገባ፤ ወቅታዊ፤ ዊዝደማዊ፤ መሠረታዊ ጉዳይ ነው። 
 
አንድ ሚዲያ ላይ ያደመጥኩትን ላስታውሳችሁ። የተወሰኑ ወጣቶች አንድ አማራ ክልል ከተማ ላይ ታይተው ስለነበር " ወጣቶች ምን ይሠራሉ ከተማ ላይ፤ ለምን ጫካ አይገቡም?" ብሎ ደፍሮ ሲናገር ሰምቸዋለሁኝ። የእሱን ሙሉ ቤተሰብ እንዳይጎዳበት ከአገር ያስወጣ ሰብዕና ነበር ይህን የሚናገረው። የእሱ ክልል ጸጥ ረጭ ብሎ እየተማረ እኮ ነው አሁን። አብዛኛው ቁልፍ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥልጣንም ለደቡብ የተሰጠ ነው። መዳር መኳሉ። ስኮላርሽፑ ዕድሉ ሁሉ በስምረት ደቡብ ላይ እየተከወነ ነው።
 
አብዛኛው ቁልፍ ቦታ የሚመሩትም የእሱ ክልል የፖለቲካ ሊቃናት ናቸው። በነፃነት ትግሉ ዘመን አንዳቸውንም ሥማቸውን ሰምተን አናውቅም ከፕሮፌሰር ዶር ብርሃኑ ነጋ በስተቀር። አይደለም በከፋው ጊዜ በኢትዮጵያ ሱሴ ነው አጭር ቆይታም የጎላ ተሳትፎ እኔ አላየሁም። የሆነ ሆኖ የአማራ ልጅ የ30 ሚሊዮን ህዝብ ፍላጎት አስፈፃሚነት ይሸከም የሚባለው ገዳዳ ዕሳቤ ለእኔ አይጥመኝም። ሁልጊዜ እኔ እማየው "በሞኝ ክንድ ጉድጓድ ሲለካ" ነው። ይህ ሁነት ከልብ መመርመር ይገባዋል። እስከ መቼ ማገዶነት? ማገዶነቱም ማንን ለማስተረፍ ? ተብሎ ሊታሰብበት ይገባል። #ብልህነት ለምን፤ ስለምን ያቅታል? ስሜታዊነት አንዲት ስንዝር ወደ ስኬት አያዳርስም።
 
አሁን ዱር ቤቴ ያለውን የፋኖን ንቅናቄ በአብዛኛው የሚመሩት እኮ #የተማሩ ናቸው። በገፍ የሚሰውትም የተማሩት ናቸው። የሆነ ሆኖ የትኛውም የትግል ዓይነት ከዕውቀት ጎን መቆም እንጂ ዕውቀትን ተፃሮ ሊቆም አይገባም። ከግሎባሉም ዓለም ጋር፤ ከዲጂታሉ ዓለም ጋርም መገናኛ ድልድዩ ትምህርት ነው። ይህን ከስሜታዊነት በጸዳ ሁኔታ አደብ ገዝቶ መመርመር፤ መወሰን እና ወደ ድርጊት ማሸጋገር ይገባል።
 
በኢትዮጵያ ከኦሮሞ የፖለቲካ ሊቃናት ቀጥሎ ያለው የአብይዝም የቁልፍ የሥልጣን ተዋረድ በደቡብ እጅ ነው - ዛሬ። ለምን? በየዘመኑ ደቡብ ለነፃነት ተጋድሎ የሚያዋጣው አቅምን መዝኑት። ከድል በኋላ የተማረ፤ መስፈርቱን ያሟላ ሲባል ደቡብ ከች ይላል። ዕድሉን ሁሉ ይጠቀልላል። በዘመነ ህወሃትም የደቡብ ሊቃናት በፖለቲካ ሥልጣን ተጋፊነት አይጠረጠሩም፤ በዘመነ አብይዝም የደቡብ ሊቃናት አይጠረጠሩም። ስለዚህ ከቤተ- መንግሥቱ ጀምሮ ያሉት ቁልፍ የኃላፊነት ቦታወች ለደቡብ ተስጥቷቸዋል። ተምረውም፤ ይዘውም ስለተገኙም ነው። የደቡብ ህዝብ የሚያቅጠለው ጊዜ ለትግል ብሎ የሚያጠፋው ቅንጣት የጊዜ ሰሌዳ የለም። የደቡብ ሊቃናት ለናሙና ቢሳተፍ እንኳን ከፐርሰንት ሬሾ በታች ነው። 
 
ነገም በዚህ የፖለቲካ የውክልና ፋክክር ውስጥ ለመገኘት ዛሬን #ልሙጥ አለማድረግ ይገባል። ብልህ መሆን ይገባል። ተምሮ መሞገት ወይንስ ሳይማሩ ተስፋን መጠበቅ? የትኛው ነው አዋጪ???? አንድ ሰው ዕድሉን ሲያገኝ ብቻውን አይደለም። ቢያንስ በአማካኝ አምስት ሰው ይጠቀማል። አንድ ሰው ዕድሉን ሲያጣ ቢያንስ በአማካኝ አምስት ሰው ዕድሉን ያጣል። ይህን ቁጥር ከፍ አድርጋችሁ ወደ 10/15 20 ስታሳድጉት የተጠቃሚው ቁጥር ይበረክታል ወይንም የተጎጂው ቁጥር ይጨምራል።
 
#ማስላት ያስፈልጋል። 
 
የትግል ጊዜ ነው አልበላም- አልጠጣም፤ አለብስም - አልተኛም፥ እግዚአብሄርን - አላህን አላመልክም አይባልም። ልክ እንደዚህው ሁሉ የትግል ጊዜ ነው ተማሪወቻችን በሰላም ወጥተው እንዲገቡ ጥበቃ እናደርግላቸዋለን፤ ጠንክረው ተግተው ተምረው በሁሉም ዘርፍ ብቁ ሆነው እንዲወጡ ከእኛ የሚያስፈልገው እገዛ እናደርጋለን የሚል የጋራ ስምምነት ሊኖር ይገባል።
 
ኢትዮጵያ ሙሉዑ እንድትሆንም በአንድ እግር በመራመድ ብቻ ስኬት አይገኝምና ይህ በኽረ ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል በብልጽግናው መንግሥትም። ስለዚህ ከአማራ ክልል የሚወጡ ትንታግ ልጆቿ ያላቸውን የመንፈስ ሃብታት ኮትኩቶ አሳድጎ ኢትዮጵያን ሙሉዑ እንድትሆን መትጋትም የብልጽግና መንግሥት ግዴታ ይሆናል።
 
ይህ ደግሞ ለሰላም በታማኝነት ቆርጦ መወሰን፤ በተግባርም መገኜትን ይጠይቃል። የቀለሙ ደብዛዛነት ስኬትን አያመጣም። የቀለሙ ጥቁሩ ወይንም ቢጫው ተጫኝነትም ስኬት አይሆንም። የቀለሙ ብሩህነት ህብራዊነት ሲኖረው ብቻ ነው የሚገኘው። መገለሉ ሆነ ማግለሉ አንዱን ማህበረሰብ፤ ሌላውን ማህበረሰብ እንዳሻህ ሁን ብሎ እቅፍ ድግፍ፤ ጥግት እምንን መፍቀዱ ኢትዮጵያን ሙሉዑ አያደርጋትም። በፍጹም።
 
ለሁሉም አንድ ዓይነት ጸጋ የለም። ለዚህ ነው አሻራችን ኮፒ የለለው። ኢትዮጵያ ለሚለው ኃይለ ቃል ሁሉም ዓይነት ቀለማት በህብረት ተመጣጥኖ ሊቀመር ይገባል። ከጥርጣሬ ይልቅ ማመን፤ በመታመኑ ውስጥ ያለውን ንጥረ ነገር አክብሮ መገኜት ይጠይቃል። ይህ ይቻላል። በእጅ ያለ ነው። ፈቃዱ ከኖረ። 
 
የሆነ ሆኖ ይዞ እና ሆኖ መገኜት ጠቃሚው ጎዳና ነው። ስሜታዊነት ለእኔ #ምራቅ ወይንም የሳሙና #አረፋ ነው። ስሜታዊነት ብዙ ረቀቅ ያሉ ጤናማ መንፈሶችንም አውዳሚ ነው። ስሜታዊነት ያዬለበት ትግል ይሁን መኖር ለትውልድ አይበጅም። ስሜታዊነት አንድ ጊዜ ተኩረፍርፎ ረብ የሚል ነው። ይልቅስ ተረጋግቶ ነገን ማሰብ ያስፈልጋል። ነገ በዛሬ ድርጊት ብቻ ይወሰናል። ዛሬ ያልተማሩ ልጆች ነገ የኢትዮጵያን የመሪነት ዕድል ማግኜት ፈጽሞ አይችሉም። ዛሬ ሳያመልጥ መሻማት ነገን ያበጃል። 
 
የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች እንዴት አደራችሁ፤ እንደምን አረፈዳችሁ፤ እንደምንስ ዋላችሁ። ለመማር ለሚፈልግ ሁለመናው ያስተምራል። "ለምን" እንዲህ ወይንም እንዲያ ሆነ የሚለው ቃል በራሱ ጊዜ ሰጥተን ብናወያዬው ብዙ እንማርበታለን። አይደለም ህይወቱን ኑረንበት ተመክሯችን በነፃ በምናቀናው ዜጎች ሃሳብ ቀርቶ።
 
 
ይህ ፔጅ ቅንጣት ዘለፋን አያስተናግድም። ጥላቻንም - አያበረታታም። ጥላቻ ጥላቻን አይፈውሰውምና። ጥላቻ ጸረ ሰውነት ነው። ጥላቻ ጸረ ሰውነትነቱ መቀበል ሆነ ማስፋፋት፤ የሰው ልጅን መርቆ ቀድሶ የፈጠረውን ፈጣሪን አላህንም መታገል ነው። በሌላ በኩል የእኔ ፔጅ ቅጽበታዊነትን አያሞጋግሥም። ብዙ ንቅዘቶች አሉበትና። የፋንታዚ አቶወችንም አይከበክብም። ቁጥር ሥፍር ያላቸው የማህበረሰብ ጉዳቶችን ያስከትላልና። ክፋ ሃሳብ እና ክፋትን አያባብልም። ዳጥ እና ምጥን መፍቀድ ነውና። ህግ ተላላፊነትን አብዝቶ ይጠየፋል። ዳኝነት የህሊና ብስለት ስኬት ነውና። ሁልጊዜ በእያንዳንዱ ሰብ ህሊና ውስጥ የዳኝነት መንበር፤ የችሎት አደባባይ አለና።
 
ይህ ፔጅ የገሃዱ ዓለም እና የመንፈሳዊውን ዓለም ህግጋትን፤ ድንጋጌወችን #ተራጋጮችንም አያሽሞነሙንም። ለብሄራዊ ለአለምአቀፋዊ ህግጋት ተገዢ ነው ሃሳቤም ማዕዴም። ልብ አምላክ ዳዊት "ህግ ተላላፊወችን ጠላሁ" ህግ አክባሪነት ያለው ሰብዕና ህግ ሰውነትን ስለሚያስከብር ነው። ለእኔ ፶ (50) ቅኖች በቂወቼ ናቸው። ለዚህም ነው ተከተሉኝ ብዬ እማላስቸግረው። ለነገሩ እኔ የምጸፈው ለለት አይደለም። ለነገ፤ ለነገ ተወዲያም አስቤ ነው። ዩቱብም ላይም እየሠራሁ ነው እማስቀምጠው ለነገ በስትያ። የራሱ ህሊና ያለው ሰው በራሱ ህሊና ይዘዝ። ደንበር አለ። ወሰን አለ። እኔ አለቃ የለኝም። የራሴ አለቃ እኔው እራሴ ነኝ። የእራሴ እንደራሴው እኔ ነኝ። 
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
24/09/2025
ጥላቻን ጥላቻ አያክመውም። በፍጹም!
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።