«በሞኝ ክንድ ጉድጓድ አይለካበትም።» "የውክልና ጦርነት" አይኖርም አሉ።
«በሞኝ ክንድ ጉድጓድ አይለካበትም።»
ብዙ ጊዜ ሃሳባቸውን ሲለዋውጡ ስለማያቸው ልብ የሚያስጥል ባይሆንም፣ አሁን ላለው የቀንዱ ውጥረት ግን ጠቃሚ ውሳኔ ነው። በትክክል ገብቷቸው ይህን አቋም አጽንተው ከቀጠሉበት " በሞኝ ክንድ ጉድጓድ አይለካበትም? ኢትዮጵያዊው ብሂል ዘመን ሰጠው ማለት እችላለሁኝ። አንድ የአገር መሪ፣ ወይንም የአንድ ንቅናቄ መሪ በዓቱን ከጦር ሜዳነት መከላከል ብልህነት ነው።
ይህ ዜና ከጸና ለኢትዮጵያ የምሥራች፣ ለግብጽ ግን መርዶ ይመስለኛል። የግብጽ የፖለቲካ ሊቃናት ኮተት እያሉ የሚድሁበት መንጠላጠያ ፍላጎታቸው አንኳሩ ኢትዮጵያን መፎካከር፣ የአፍሪካ መሪ ሆኖ ለመውጣት ማለም ነው። አባይ ምክንያታዊ የመንፈስ ማረፊያቸው ቢሆንም ፋንታዚያቸው ግን የአፍሪካ አንከር መሆን ነው። የእኔ መረዳት እንዲህ ነው።
ሥርጉትሻ 2025/09/24
«የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ኢትዮጵያ እና ግብፅ በአገራቸው ውስጥ እንዲዋጉ እንደማይፈቅዱ ተናገሩ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በአገራቸው በሰላም ማስከበር ላይ የሚሰማሩ የኢትዮጵያ እና የግብፅ ወታደሮች ወደ ግጭት ሊገቡ የሚችሉበት ምክንያት እንደሌለ በመግለጽ "የውክልና ጦርነት" አይኖርም አሉ።
ፐሬዝዳንቱ ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ላይ እንደተናገሩት በሁለቱ አገራት መካከል "በሶማሊያ ምድር" የሚካሄድ ጦርነት እንደማይኖር እና ሶማሊያም ይህንን እንደማትፈቅድ አሳውቀዋል።
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው ላይ ኢትዮጵያ እና ግብጽ በሶማሊያ ውስጥ ግጭት ውስጥ ሊገቡበት የሚችሉበት ዕድል እንደሌለም ተናግረዋል።
ሁለቱ አገራት ወደ ግጭት መግባት የሚፈልጉ ከሆነ በራሳቸው ሊዋጉ ይችላሉ ያሉት ፕሬዝዳንቱ "ነገር ግን በሶማሊያ ምድር የሁለቱ አገራት ሠራዊት የሰፈሩት ቦታ ተቀራራቢ ስላልሆነ" ለግጭት የሚያበቃ ዕድል የለም ብለዋል።
በግብፅ እና በኢትዮጵያ ወታደሮች መካከል በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቀት መኖሩን የገለፁት ፕሬዝዳንቱ "ግብፅ ኢትዮጵያን ለመረበሽ የምትፈልግበት ምክንያት አይታየኝም። ኢትዮጵያም በሶማሊያ የሚገኙ የግብፅ ሰላም አስከባሪ ኃይልን ለመረበሽ የምትፈልግበት ምክንያት አይታየኝም" ብለዋል።
የኢትዮጵያ እና የግብፅ ወታደሮች ሶማሊያን የጦርነት አውድማ የሚያደረግ "የውክልና ጦርነት" ማድረግ እንደማይቻል ሶማሊያም ይህ በግዛቷ እንዲከናወን እንደማትፈቅድ አሳውቀዋል።
ፕሬዝዳንት ሐሰን አገራቸው ለአስርታት በተካሄደ ጦርነት መሰላቸቷን እና ተጨማሪ አዲስ ጦርነት እንደማትፈልግም አክለው ተናግረዋል።
"የራሳችን ችግሮች አሉብን። የራሳችን ጦርነቶች አሉብን" በማለትም ሌሎች አገራት እዚህ መጥተው በላያችን ላይ እንዲዋጉብን አንፈልግም በማለት "ያ ፈጽሞ አይሆንም" ብለዋል።
የፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መንግሥት፤ በአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ ውስጥ የሚሳተፉ አገራት 11,000 ወታደሮች እንደሚያዋጡ የገለፀው ባለፈው ዓመት ነበር።
ተልዕኮው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት በጸደቀበት ስብሰባ ላይ የሶማሊያ ተወካይ ባደረጉት ንግግር፤ በስምሪቱ የሚሳተፉ ወታደሮች ድልድል የተወሰነው በሁለትዮሽ ስምምነት እንደሆነ ገልጸው ነበር።
በአገሪቱ በሰላም ማስከበር ከሚሳተፉ አገራት መካከል በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ቅራኔ ውስጥ የገቡት ኢትዮጵያ እና ግብፅ ይገኙበታል።
የኢትዮጵያ ሠራዊት በሶማሊያ ውስጥ ሰላም ለማስከበር ከተሰማራ ሃያ ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ ግብፅ ጦሯን ለዚህ ተልዕኮ የላከችው ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ በገባችበት ባለፈው ዓመት ነው።
ኢትዮጵያ በታኅሣሥ 2016 ዓ.ም. ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የባሕር በር ስምምነት ከሶማሊያ ጋር አንድትቃቃር አድርጓት ነበር።
ሁለቱ ጎረቤታሞች ለአንድ ዓመት ያህል ባለመግባባት ውስጥ ከቆዩ በኋላ በቱርኩ ፕሬዝዳንት አቀራራቢነት አንካራ ላይ በተደረገ ውይይት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
የአገራቱ መሪዎች ከስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ስምምነቱ ለወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ የባሕር መተላላፊያ በር እንደታገኝ የሚያደርግ ነው ሲሉ እምነታቸውን ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መካከል የወደብ አገልግሎት ጉዳይ ንግግር እየተደረገበት መሆኑን ጠቅሰው "ገና መቋጫ እንዳላገኘ" ጠቅሰዋል።
"ኢትዮጵያ የሶማሊያን ወደብ ብትጠቀም ችግር የለብንም" ሲሉም ተናግረዋል። የአሜሪካው ሴናትር ቴድ ክሩዝ ዶናልድ ትራምፕ ለሶማሊላንድ ዕውቅና እንዲሰጡ መጠየቃቸውን በተመለከተ የተጠየቁት ፕሬዝዳንቱ "ይህ የአፍሪካ ኅብረት ቻርተርን የሚጥስ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተርን የሚጥስ ነው። ሶማሊላንድ የሶማሊያ አካል ናት" ብለዋል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው ላይ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው እስላማዊ ታጣቂ ቡድን አልሸባብ በተደጋጋሚ የግድያ ሙከራ እንዳደረገባቸው ተናግረዋል።
አልሸባብ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለአምስት ተከታታይ ጊዜ በሞቃዲሾ እና በጦር ግንባሮች ላይ የግድያ ሙከራ እንዳደረገባቸው እና የመጨረሻው ሙከራ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ እንደነበረ ለቢቢሲ አስታውሰዋል።
ምንም እንኳን ቡድኑ ፕሬዝዳንቱን ለመግደል ያልተሳካ ሙከራ ቢያደርግም እየተዳከመ መሆኑን ገልጸዋል። ሶማሊያ "በአሁኑ ሰዓት የዓለም አደገኛ አሸባሪዎች" ሲሉ የጠሯቸውን አልሸባብን እና አይኤስአይኤስን በተለያዩ አውደ ውግያዎች እየተፋለመች መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ ይህም ከፍተኛ የደኅንነት ተግዳሮት መፍጠሩን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ተግዳሮታቸው የአገሪቱን ጦር መገንባት እና እግረ መንገድ ጦርነት ማካሄድ መሆኑንም አንስተዋል። ባለፉት ሦስት ዓመታት ከአሸባሪዎች ጋር በሚያደርጉት ጦርነት በርካታ ውጤቶችን ማግኘታቸውን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ "በርካታ ከተሞች እና አካባቢዎች ከአልሸባብ ነጻ ሆነዋል" ብለዋል።
ነገር ግን አሁንም አልሸባብ የተወሰኑ "የገጠር አካባቢዎችን" እንደሚቆጣጠር አልሸሸጉም። "ከበፊቱ ጋር ሲነጻጸር አልሸባብ ተዳክሟል" ያሉት ፕሬዝዳንቱ የገንዘብ ምንጩን ለማድረቅ "በርካታ የባንክ አካውንቶችን እና የሞባይል ገንዘብ ዝውውሮችን ዘግተናል" ብለዋል።
ባለፈው ዓመት የሰኔ ወር የአሜሪካ መንግሥት የበርካታ የአፍሪካ አገራት ላይ የጉዞ ገደብ ከጣለባቸው አገራት መካከል አንዷ ሶማሊያ መሆኗን እና በወቅቱም አገራቸው "ለሽብርተኝነት ምቹ የሆነች" ተብላ መገለጿን የተጠየቁት ፕሬዝዳንቱ አገራቸው በዚህ መልኩ መገለጿን ፈጽሞ እንደማይስማሙበት ገልጸዋል።
"ለሽብርተኝነት ምቹ የሆነች የሚባለው ሽብርተኝነትን እየተዋጋን ባይሆን ነበር" ሲሉም አገራቸውን ተከላክለዋል። አገራቸው ከ32 ዓመታት በኋላ የተጣለባት የመሳሪያ ግዢ ማዕቀብ መነሳቱን፣ ከአውሮፓውያኑ 1972 ወዲህ የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ያልሆነች አባል መሆኗን፣ የ5 ቢሊዮን ዶላር የዕዳ ስረዛ ማግኘቷን እና በዓለመ አቀፍ እና በቀጣናዊ ድርጅቶች ውስጥ መሳተፍ መጀመሯን በመጥቀስ "ይህ ሁሉ የሆነው አልሸባብን እያሸነፍን ስለሆነ ነው" ብለዋል።»

አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ