#የማይከብደው #ባይከብድ #ስለትውልድ።
#ምዕራፍ ፲፯
* ሰላም ለምን ይፈራል?
** ስለሰላም መትጋት ስለምን ይሸሻል?
*** ስለሰላም መሆን እንደምን ያቅታል? ሰላም በኽረ አጀንዳችን ስለምን አልሆነም?
****በተለይ በትረ ሥልጣኑን ለያዘ አካል ሰላምን ማስፈን ለምን ይቸግረዋል?
#አይዋ ጦርነት አተረፍኩ ካለ፦ የሚያተርፈው የተቃጠለ ጠቀራማ አመድ እና በቀል ብቻ ነው ።
በሰላም ጉዳይ ሙሉ ኃላፊነቱን ሊወስድ የሚገባው ሥልጣን ላይ የሚገኝ የማንኛውም አገር መንግሥት ሊሆን ይገባል? ጦርነት ታቅዶም ይሁን ሳይታቀድ አትራፊ ክስተት አይደለምና። ጦርነት የሰቆቃ እና የዋይታ፤ እንዲሁም የውድመት #አንበል ነው። ይህ አሰቃቂ ክስተት እንደአይከሰት ጉዳዩን ወደ አገራችን ስወስደው ሰፊ ኃላፊነት ያለበት #የብልጽግና መንግሥት ነው። ወደ ጦርነት የሚወስዱ አቅጣጫወችን በሰላም ገርቶ ትውልድን #የማበርከት ኃላፊነት አለበት የብልጽግና መንግስት።
የብልጽግና መንግሥት #ኮበሌያዊ የእልህ ጉዞውን አቆሞ (ትዕዛዝ አይደለም ትሁታዊ ዕይታ ነው።) ምራቁን የዋጠ፥ የጉልምስና ባለፈም የአዛውንት ተግባራትን ሊፈጽም ይገባል። ዘወትር - ጦርነት፤ ሰርክ የሞት ዜና፤ ሁልጊዜ የስጋት ዓውድ እሰከ መቼ? እኔ #የምክክር ኮሚሽኑ ተግባሩ የሰርክ ሊሆን የሚገባው ብየ የማስበው በሰላም ዙሪያ አቀራራቢ ሃሳቦችን በማመንጨት ከፋኝ ብለው #ዱር ቤቴ ካሉት ወገኖቻችን ጋር ከጫካው ኦነግም ይሁን ከፋኖ ጋር #ቅን የሆኑ ውይይቶች የሚደረጉበትን ዓውደምህረት መፍጠር ይገባው ነበር ባይ ነኝ። ከሰላም በላይ የላቀ የህይወት፤ የመኖር፤ የሥልጣኔ በኽረ አጀንዳ የለም። የምክክርኮሚሽኑ አጀንዳ ለማሰባሰብ ባህር ማዶ ከመዝለቅ በፊት ይሁን በኋላ ይህ አጀንዳ መሪ ሊሆን ይገባል።
ከሁሉም አጀንዳ በፊት የሰላም ኃሳብ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ባይ ነኝ። #የማይከብደው #ከብዶ ዘመን - ከዘመን፤ ወራት - ከወራት፦ ትውልድ ከትውልድ ዘወትር መርዛማውን ባሩድን ማዕደኛ ማድረግ የተገባ አይደለም። በምንም - ሁኔታ፤ በየትም ቦታ ከሰላም በላይ #ሥልጣኔን፤ ቴክኖሎጂን ሊያስቀጥል የሚችል ክስተት የለም።
ለዛውም በዓለም ተለይታ #የሰላም #ሚኒስተር ለተደራጀላት ኢትዮጵያ ሰላም ባይተዋሯ፤ ሰላም በጎሪጥ የምታየው ክስተት ሊሆን አይገባም ነበር። ግን ኢትዮጵያዊው የሰላም ሚኒስተር ትርታው አለችን? ይተነፍሳልን? ያን ያህል መዋቅር ተዘርግቶለት፤ በገፍ ባለሙያ ተመድቦለት፤ ባጀትም እየፈሰሰለት ምን አሳካ ይሆን? እንደ አንድ ኢትዮጵያ ዜጋ እኔ በግሌ የምጠዬቀው ጉልላታዊ ጥያቄ ነው።
የዓለም የሰላም ሎሬት ተሸላሚ መሪ ያላት አገር ኢትዮጵያ የሽልማቱ ዕውቅና ከተሰጠበት ዕለት ጀምሮ ትጋቱ፤ አቅጣጫው፤ መርኃ ግብሩ፤ ጉዞው ሰላም እና ሰላማዊነት በሆነ ነበር። ኢትዮጵያን የሰላም #የፊደል ገበታ በማድረግ አብነትነቷን ድርጊት ላይ ማዋል በተገባ ነበር። አንድ ቤተሰብ ውስጥ መጋጨት፤ መኮራረፍ፤ መበዳደል ሊፈጠር ይችላል። ግን ያን በስክነት የእኔ ብሎ፤ በውስጥ - ስለውስጥ ተጨንቆ እና ተጠቦ አክብሮም ከፋኝ የሚሉ ድምፆችን ማድመጥ ይገባ ነበር።
በጥቂቱ ታቅደውም ይሁን ሳይታቀዱ የተጀማመሩ ጉዳዮች፤ #ለሙከራ ተብለው የተፈቀዱ ሁነቶች ሁሉ ዛሬ ገንግነው እንዲህ አስቸጋሪ ደረጃ አይደርሱም ነበር። በወቅቱ፤ በሰዓቱ ሁነቶችን ከማጣጣል፤ ከማናናቅ፤ ምን ያመጣል በማለት የቅጥል ሥም ሰጥቶ አንኳስሶ ከማየት ይልቅ፥ በበዛ መችል ውስጥ ሆኖ አትኩሮትን መደልደል ይገባ ነበር።
ቅን መካሪ ወይንም አማካሪ መኖር ብዙ ብስጭቶችን ማርገብ፤ የተለያዩ ተስፋ ቆራጭነቶችን አባብሎ ተስፋን መመገብ ይቻል ነበር። መሪነት እኮ ማድመጥን ለተመሪው መመገብ ነው። ይህ ባለመሆኑ ህዝብ በእጅጉ ተጎዳ። ለለት - ከፈን፤ ለለት - ጉርስ፤ ለለት - መጠለያ ያልበቃ ህዝብ ተይዞ፤ በአፍሪካ ካሉ ደሃ አገሮች #ከመጨረሻወቹ ተርታ ያለን አገር ይዘን ለሰላም አለመትጋት የብልህነት ጎደሎነት ነው ለእኔ።
ጦርነት እኮ ሁሉንም የህይወት ዘርፍ የሚበትን፤ የሚያቆስል፤ ጥሪት አልቦሽ የሚያደርግ፤ የተፈጥሮን አትኩሮት የሚቀማ፤ ባካና የሚያደርግ፤ የሚወደደውን የሚያሳጣ፤ የሁለመና ዘራፊ #ግራጫማ ክስተት ነው። በጦርነት ቅንጣት ትርፍ የለም፦ አይኖርምም። በፍጹም። አይዋ ጦርነት አተረፍኩኝ ካለ የሚያተርፈው ሁልጊዜ እንደምጽፈው አመድ እና በቀል፤ ጥላቻ እና ጭካኔ፤ ቂም እና ውድመት ይሆናሉ የአይዋ ጦርነቴ ትርፋ ትርፎች።
1) ሰላም ቆራጥ ሰብዕናን ------ ከጦርነት በላይ ይፈልጋል።
2) ሰላም ብቁ ዓራት ዓይናማ የሰላም መኮንኖችን ይሻል ---- ከጦርነት በላይ።
3) ሰላም የጨመቱ ሰብዓውያን መሪወችን ---- ይመኛል።
4) ሰላም አርቆ ለትውልድ የሚጨነቁ ትንታግ ብልሆች ---- ይናፍቁታል።
5) ሰላም ከእኔ ይልቅ እኛነትን የሚያስቀድሙ የድርጊት #ሐዋርያትን -----ይፈልጋል።
6) ሰላም ሊቀ ትጉኃን ተፈጥሯዊነት #የጠለቃቸው ምርቆችን----- ያሰኜዋል።
7) ለሰላም የዊዝደም ባለሙያዋችን እንጂ የፋንታዚ - ፋንታዚወች ልኩ ሊሆኑ በፍፁም አይችሉም።
ለሰላም - ስለሰላም ለሚያስብ ደግ ፍጡር ከአንድ ቡቃያ የቤት ውስጥ ማስዋቢያ አትክልት ውስጥ አንዷ ቅጠል ብትቀነጠስ ይሰማዋል። ለምን? የዛች ቅጠል የልምላሜ ዘመን ሲቀጭ ለዓይኑ ይሰጥ የነበረው ውበት ስለሚቀንስ። ከዚህ ላይ በቅርቡ የገጠመኝን መምህራዊ ዕድል ላጋራችሁ ወደድኩኝ።
በግንቦት ወር መግቢያ አንዲት የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ግድ የሚሰጣትን ወዳጄን ከቤቴ ጋብዤ ነበር። ሲዊዛዊቷ ደግዬ ጋር ሻይ እየተገባበዝን ንብ መጣ እና ለብርጭቋዋ እንግዳ ሆነ። ቀስ አድርጋ በማንኪ ወዲያውኑ አወጣችው። ከአጠገቧ ያለውን ሶፍት አውጥታ አንጥፋ ሲንፈራፈር ለነበረው ንብ ደረሰችለት። እኔ በጥሞና እየተከታተልኩኝ ነው።
……… እና ያ ድንገቴ የደረሰበት ዕድለኛው ንብ ህይወቱ ቀጥሎ እስኪበር ድረስ ሙሉ አትኩሮቷን መገበችው አደጋ ለደረሰበት ንብ። የጀመርነው ጨዋታም ጠብቅ ተብሎ ቁሞ እየጠበቀን ነው። እኔ ገርሞኝ እየተከታተልኩ ነው። እሷ የአንድ ንብ ህይወት አላግባብ ከመቀጨቱ በፊት #የማዳን ተግባር ላይ እየተጋች ነበር።
ደግነቱ ሻዩ በረድ ያለ ስለነበር ንቡ ብዙም አልተጎዳም ነበር። የተደረገለት የሪከበሪ መልካምነትም ልዩ ነበር። ጥቂት ልፍስፍስ፤ ከብለል ካለም በኋላ እየፈነጠዘ፤ እየተፍለቀለቀ ፈጣሪያውንም እያመሰገነ ከነፈ። በጣም ትልቅ የተፈጥሯዊነት ትምህርት ቤት ነበር - ለእኔ። በውነቱ ይህን የድርጊት ገጠመኝ ለሰጠኝ እግዚአብሄርም ውስጤ አመሰገነ። ከሁሉም ከድምጽ አልቦሾቹ ከኢትዮጵያ እናቶች ጎን ሁልጊዜም እንድቆም ለረዳኝ፤ መንገዱን ላመቻቸልኝ ፈጣሪየን አመሰገንኩት።
እንዲህ ለአንድ ንብ ህይወት ከምትጨነቅ ውድ አንስት ጋር ያገናኜን አምላኬንም አመሰገንኩኝ። ሥልጣን የሚባለውን ነገር በጣም መጠየፌንም በራሱ አመሰገንኩት። የኢትዮጵያ የሥልጣን እርከን እርካቡ በአመዛኙ በጀቱ ጭካኔ ሆኖ ስለማየው። በነገራችን ላይ ንብ የታደለ ሥለሆነ ለአዲስ ትውልድ ሁለመናውን ፈቅዶ የማስረከብ አቅም ያለው ፍጥረት ነው። ህብራዊነቱም አንቱ ነው።
#የጦርነት ውርርስ አያስፈልገንም።
ከትናንት - በስትያ የኢትዮጵያን ታሪክ ስንፈትሽ የእርስበእርስ ጦርነት ነበር። ዛሬም ኢትዮጵያ በጦርነት ውስጥ ናት። ነገም ይህን የጦርነት ድግግሞሽ ለማስቀጠል ያለው ሽርጉድን በዝምታ አስተውላለሁኝ። ሞቅ ያለ የጦርነት ዓውድ ሲኖር #ፍልቅልቅ፤ ፍንክንክ የሚሉ የሚዲያ ሰወችንም የእነሱ …… አያለሁኝ። ውስጣቸው ለሰባዕዊነት ምንኛ ይሆን? የሆኖ ሆኖ ……
* እናታቸው?
** አባታቸው?
*** እህት እና ወንድሞቻቸው?
**** አክስት እና አጎቶቻቸው?
***** ትዳራቸው?
****** ልጆቻቸው…… የቤተሰቦቻቸው መጠቃት ቢሆኑ ያን ያህል #ይቧርቁ ነበርን???
******* ይህን ያህል የሠርግ ያህል ፍንድቅድቅ ይላሉን???
ጦርነት አሳዛኝ ክስተት እንጂ የሠርግ እና የመልስ፥ የግጥግጥ ወይንም ቅልቅል አይደለም። ጨካኙ ጦርነት የሁለመና መራራ እጅግም ጎምዛዛ ክስተት እንጂ ያን ያህል ከውስጥ የኮለኮሉትን ያህል ፍንክንክ የሚያስደርግ ክስተት አይደለም - ጦርነት። ጦርነት ውስጥ የሚሆነው ወገን እራሱን ለማዳን ወይንም ለመከላከል ሊሆን ይችላል።
ሌላው ግን ከውስጡ ሊያዝን እንደ ዕምነቱ ምህረት፤ ይቅርታ፤ እርቅ እንዲወርድ መጸለይ እንጂ እንደ የፍቅር ተውኔት ትዕይንት ጦርነት ሆኖ ያን ያህል የሚስፈነድቅ ሊሆን ባልተገባ ነበር። ሰው ሆኖ ተፈጥሮ የደም ፍሰትን ለዛውም የሰው ልጅን መናፈቅ የጎደለ የህሊና ክፍል ያለ ይመስለኛል። አሰቃቂ፤ አስጨናቂ ክስተት የሙዚቃ ኮንሰርት አይደለምና።
እራሱ የጦርነቱ ዓውድ ባዕቱ በእነሱ ባድማ ቢሆን ይህን ያህል ፌስታቸው፤ ሠርግ እና መልሳቸው ይሆን ነበርን ለጦርነት ፌስተኞች? አይምሰላችሁ የእኔ ክብሮች፤ የሥርጉትሻ ፔጅ ታዳሚወቼ፤ መከራውን የተሸከመው ከእነሱ የሥጋም የመንፈስም እርቀት ተሰልቶ ነው ውቂደብልቂው እንዲደላው የሚዲያ ሙሉ ሽፋን የሚሰጠው።
ይህን በግራ ቀኙ ደጋፊወች፤ ፈፃሚ እና አስፈፃሚወች በኩል ያለውን የፋክክር ጉዳይ እሰቡት እና የአንድ ንብ ነፍስ ለማትረፍ ሙሉ አትኩሮት የሰጠችውን የእንግዳየን የተፈጥሯዊነት ልክ መዝኑት። እንዲህ ዓይነት ሰብዕና ትውልዱ ይኖረው ዘንድ የማይከብደው ሳይከብደን ወደ ሰላም እናቀና ዘንድ ሁላችሁንም በትሁት ልቦና በአክብሮት እለምናችኋለሁኝ።
#እርገት ይሁን።
ለቀጣዩ ትውልድ *በቀልን በጦርነት አፋፍቶ፤ ** ቂምን በጥላቻ አለምልሞ ከማውረስ ይልቅ፤ ሰላምን *** በደግነት አሳምሮ፤ **** ቅንነትን በህብራዊነት አስውቦ፤ ***** አጽናኝነትን በአይዟችሁ አጎምርቶ፤ ****** ሰዋዊነትን በመሆን አስውቦ፤ ******* ተፈጥሯዊነትን በእኛነት አስጊጦ ማስረከብ ከእያንዳንዳችን በግል፤ ከሁላችንም በጋራ የሚጠበቅ ፈቅደን፤ ወደን እና አስመችተንም ልንቀበለው የሚገባ የአደራ ማዕዳችን ሊሆን ይገባል። ትዕዛዝ አይደለም። ኧረ ምን በወጣኝ። ትሁታዊ የውስጤ መሻት ነው።
በባዕታችን በኢትዮጵያ *አየሩ - ታውኳል። ዕጽዋት -- ተረብሸዋል። መሬት ** ኡኡታ ላይ ነው ያለችው። *** የቤት እንሰሳት ይጨንቃቸዋል። **** የዱር እንሰሳት ይሰደዳሉ። ***** አብሶ ሰሜናዊው ባዕት ቋያነቱ ቀጣይ ከሆነ *የማያልቅ የለም። *** የማይጠናቀቅ አይኖርም። በጠርሙስ የሞላ ውሃ ስትጠጡት እንደሚያልቅ ሁሉ ዘርም *** ይነጥፋል።
ጥይቱ፤ ድሮኑ መርዝ ነው የሚተፋው። መርዙ ደግሞ የነገን ልሙጥነት ይገልጣል። ዘር አልባነት።ተተኪ አልባነት። የመከነ ባድማ። በሌላ በኩል በምስራቅ ኢትዮጵያም ሰሞኑን የሰማሁት ዜናም ይህውን መከራ ያጨ ነው። በእጅ ያለ፤ የሚቻል ነገር አቅቶ ነው፦ ህዝብ ወልዶ - መሳም፤ አምርቶ - መመገብ፤ በድህነቱ ላይ ሰላሙ ተነፍጎ የሚገኘው።
ሁላችንም ጦርነት የለለባት ኢትዮጵያን እንናፍቅ ዘንድ በትህትና አሳስባችሁአለሁኝ። ይህም ብቻ ሳይሆን የሱዳን የእርስ በእርስ የሥልጣን ሽሚያ ጦርነት፤ የጋዛ እና የእስራኤል እጅግ አሰቃቂ ጦርነት እንዲቆም፤ የዩክሬን እና የራሺያ ጦርነት እንዲያከትም እንደ ግሎባል ዜግነታችን ቢያንስ በጸሎት መረዳዳቱ፤ በብሄራዊ ደረጃ ይሁን በግሎባል ደረጃ የሚካሄዱ የሰላም ጥረቶችን በማበረታት ልንተጋ ይገባል ባይ ነኝ። ኑሯችን ምጥን፤ ቆይታችን አጭር ነውና ከሰላም ጎን መቆሙ ዕውነተኛው ጎዳናችን ሊሆን ይገባል ብየ አስባለሁኝ።
ግን የሥርጉትሻ ፔጅ ቅን ታዳሚወች እንዴት አደራችሁልኝ። ኑሩልኝ። አሜን።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
30.09.2025
ሰላም ለተፈጥሯዊነት!
ሰላም ለሰብአዊነት!
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።


አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ