ፈላስፊት ኢትዮጵያ ሆይ! አማኑኤል አባቴ #ከመፈንቅለ #መንግሥት ሙከራም፤ ስኬትም ያውጣሽ። አሜን።

 

ፈላስፊት ኢትዮጵያ ሆይ! አማኑኤል አባቴ #ከመፈንቅለ #መንግሥት ሙከራም፤ ስኬትም ያውጣሽ። አሜን።
 
"እግዚአብሄር ገርና ትሁት ልቡናን አይንቅም።"
 
#ምዕራፍ ፲፯። 
 
በፖለቲካ ህይወቴ ከሚያሰጉኝ ጉዳዮች ትልቁ መፈንቅለ መንግሥት ነው። 
 
 May be an image of 1 person, headscarf, hospital and text that says 'H'
 
 
#ምክንያቴ በስሱ።
1) መንፈቅለ መንግሥቱን የሚያደርገው አካል ምን ገጽ? ምን ባህሪ? ምን የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚ አቅም፤ ምን የፖለቲካ አቋም እንደሚያርምድ ድፍን ነው። ሥም የለሽ።
 
2) መፈንቅለ መንግሥቱ በግል ወይንስ በወል እንደምን ሊፈጸም ይችላል ለሚለውም መገመት አይቻልም። ፎርም የለሽ ነውና።
 
3) #ፈንቃዩ ቢሳካለት ለለት የሚገባው ቃል እና እዬቆየ እያከረረ ሊሄድ የሚችለው ፖለቲካዊ አቋምን መተንበይ አይቻልም። 
 
4) የመፈንቅለ መንግሥቱ ባለቤት ማንን #ጠላት አድርጎ እንደሚነሳ አይታወቀም። ስለዚህ ያልተሰናዳው ተጠቂ እጅግ የሚሰቀጥጥ ኢሰባዊ እርምጃ ሊደርስበት ይችላል። 
 
5) የመፈንቅለ መንግሥቱ ተጠሪ #ከወገቡ በላይ #ሰውኛ፤ ከወገቡ በታች #ምንኛ ሊሆን እንደሚችልም ዝግ ነው። 
 
6) ይህም ብቻ አይደለም #እስር ቤት የሚገኙ ወገኖቻችን ላይ ሥልጣን ላይ ያለው የብልጽግና መንግሥት ይሁን፤ የመፈንቅሉ አስተናባሪ ሊወስድባቸው የሚችለው እርምጃ እና የደህንነታቸው ዋስትና አሁን ካለው የከፋም ሊሆን ይችላል። የፖለቲካ እስረኞች ለፈንቃዩም፤ ለተፈንቃዩም ለግራ ቀኙ እንደ ስጋት ስለሚታዩ። ጥቃቱም ባለቤት አልቦሽ ሊሆን ይችላል። በሰው እጅ ያሉ ከአዲስ አበባ ጀምሮ በሌላው ክልል በትናንሽ ከተሞች የታሰሩ ፖለቲከኞች ዕጣ ፈንታ ጨለማ ነው። 
 
7) ሌላው ሥርዓተ አልበኝነት አገር ሲመራ የወህኒ ቤት #ደረቅ ወንጀል ፈፃሚወች ዕድል ቢያገኙ፤ በቀሉ ምድራችን የከፋ የደም መሬት ሊያደርጋት ይችላል። እርቃኗንም ልትቀር ትችላለች - በሁለመናዋ። 
ስምንት) የመፈንቅለ መንግሥቱ ሂደት #ሰዓቱ አይታወቅም። በማንኛውም ጊዜ ሊከወን ይችላል። ቀን ከሆነ ሥራ የሄዱ፤ ትምህርት ቤት ያሉ ልጆች፤ ለገብያ የወጡ፤ ጉዞ ላይ ያሉት ሁሉ አድራሻ ቢስ ሊሆኑ ይችላሉ። እናት ልጄን እንዳለች፤ ልጅም እናቴ እንዳለ በተቀራረበ ርቀት የትራጀዲ ትዕይንት ሊኖር ይችላል። አይደለም መፈንቅለ መንግሥት ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ባህሬ ይለወጣል። ጭካኔ ይመራል።
 
9) ቂም እና በቀል #አና ባለበት በኢትዮጵያ የዞግ ፖለቲካ ምን ዓይነት የሰላ ፋስ እና መዶሻ ለህዝባችን ስቃይ እንደሚያወርድ አይታወቅም። ይህን በሰላም በተከወነ ሽግግር አይተነዋል። ወገናችን ተገድሎ ተዘቅዝቆ ሲሰቀል ሻሸመኔ ላይ። ታስሮ ተገድሎ አካል ሲነድም አይተናል። መራር ታሪክ። አብረን እንፈር እምለው እኔ ከዚህ ላይ ነው።
 
10) ሆስፒታል ያሉ፤ ምጥ ላይ ያሉ፤ በኦክስጅን ህይወታቸው የቀጠለ፤ አዛውንቶች፤ አካላቸው ሙሉዑ ያልሆነ ሁሉ የቀጥታ ተበዳዮችም፤ ተጎጅወች ሊሆኑ ይችላሉ።
 
11) ተፈጥሯዊ መረጋግት በይፋ ይሰደዳል። ሁሉም ደንጋጣ፤ ተሸባሪ፤ ብስጩም ሊሆን ይችላል።
 
12) መፈንቅለ መንግሥቱ ብስጭትን ጎርሶ ስለሚመጣ፤ ሊፈጽም የሚችለው የበቀል እርምጃን መገመት አይቻልም።
13) የማግሥት ተስፋ #ድንብርብሩ ሊወጣ ይችላል። መንፈሱ ማረፊያም ሊያጣ ይችላል።
 
14) መፈንቅለ መንግሥት የኢትዮጵያ እናቶችን ዕንባ ቢያስቀጥል እንጂ ዕንባ ፈዋሽ ፈጽሞ ሊሆን አይችልም - በጉልበተኞች ማህበር።
 
15) ለመፈንቅለ መንግሥት ቅርብ የሆነ አክሰስ ያለው የታጠቀው ኃይል ነው። በታጠቀው ኃይል መሃልም የመግባባት ስኩን፤ ርጉ #ስምረት በድንገቴ ዱብ ዕዳ ገጠመኝ ማግኜት ስለማይችል፤ ሌላ መራራ የመጠቃቃት ገጠመኝ ሊከሰት ይችላል። ሁሉም እናት አለው። ለእናቶች የፍዳ ጫና ማከል ይሆናል።
 
16) በመፈንቅለ መንግሥት ከጥቃቅኑ እስከ ገዘፈው ብሄራዊ ጉዳይ አድራሻ የለሽ ሰቆቃ ህዝባችን ለማስተናገድ ሊገደድ ይችላል።
 
17) በዕድሉ #ህወሃት ተጠቃሚ ቢሆን? ሻብያ ታካይ ቢሆን የባሰ ገጠመኝ ኢትዮጵያን እና ህዝቧን ሊገጥማት ይችላል።
 
18) አሁን እኮ እንደ ቀደመው ጊዜ ሽሽግ፤ ሽጉጥ ተብሎ ወጀብን ማሳለፍ የሚቻልበት ሁነት የለም። የት ይኬዳል? ሁሉም በዞግ ቋያ ላይ ነው ያለው። ወጥቶ መመለስ ቀርቶ፥ ከቤት እየተወሰደ እገታው - ግድያው - መደፈሩ - መሰወሩ #አና ብሏል። መንግሥት ባለበት አገር። መንግሥት ሲሰናበት ደግሞ የችግሩን ግዝፋት እና የአሳሩን መጠኑን ስፋት ለኩት።
 
ባሳለፍነው የአብይዝም ዘመን ሁልጊዜ በሌለ ነገር፤ #ማጫጫን#ማጫጫስ ተፈልጎ ይመስለኛል "የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተደረገብኝ" በሚል አሰልቺ ዕሳቤ በገፍ ለጥቃት የተዳረጉ ወገኖች ነበሩን፤ በተለይ የአማራ ሊቃናት ላይ። የአብይዝም ሥርዓት ከምርጫው በኋላ ይህን ስጋቱን ያስታገሰ መስሎኛል። አሁን ደግሞ ይህ ጉዳይ አገርሽቶ በጉልበታም ወጀብ ተከስቷል። የአሁኑ አቅም ያለው ይመስላል። ሰብሰብ ያለ ምኞትም #በጠቃጠቆ እታቱ ዥግራ እያለ ነው።
 
#እጅግ አሰቃቂ ከንቱ ክስተት ምኑ ይደገፋል?
 
መፈንቅለ መንግሥት #ጥቁር ለብሰህ፤ አይንህ #ተዘግቶ ወደ ቋያ ተወርወር የማለት ያህል ነው - ለእኔ። የታመቀ የቁርሽ ጥማት አለ። በማንኛውም ሁኔታ መፈንቅለ መንግሥት ለአገር ከሂደቱ ታሪክ ጀምሮ፤ ለህዝብ፤ ለትውልድ፤ ለአደራ የማይሆን ከንቱ የሆነ #አሰቃቂ ክስተት ነው። ስለሆነም አቋሜ ቁልጭም ጥርት ያለ ነው። ለሳይንቲስቷ ኢትዮጵያ መፈንቅለ መንግሥት #ስቅለቷ#ሲኦሏ ቢሆን እንጂ ትፍስህቷ ሊሆን ፈፅሞ አይችልም ባይ ነኝ።
 
በሌላ በኩል መፈንቅሉን የሚመራው ኃይል መላ ኢትዮጵያን በአንድ ጊዜ ሊቆጣጠር ስለማይችል፤ በየከተማው የሚገኘው ህዝባችን ከአሁን በከፋ እና በጎመዘዘ ሁኔታ ለጭንቀትና ለጥቃት ይጋለጣል። የሚያፈነግጥ ክልልም ይኖራል። በተለይ ደቡብ ላይ የራሳቸው አዲስ ክልል የተሰየመላቸው አብይዝምን ደግፎ ሊነሳ ይችላል። ወጥ አመራር፤ ማዕከላዊ የርቃ ቆፍጣና መመሪያ ለመስጠትም ሊያዳግት ይችላል። በሌላ በኩል ገንዘብ አላቸው ተብለው የሚገመቱ ተቋማትም ይሁኑ ግለሰቦች ጥሪት አልባ በአንድ ጀንበር ሊሆኑ ይችላሉ። መንገድ አደርም ሊሆኑ ይችላሉ።
 
በተጨማሪም በሃይማኖት ተቋማት ከእስከ ዛሬው የከፋ ሰቆቃ፤ መራቆት፤ ደግመው የማይገኙ ቅርስ እና ውርሶች ሊወድሙ ይችላሉ። አድህኖ ስዕላት፤ ቅዱሳን አልባሳት እና የእኛነት መገለጫወች በሙሉ ዕጣቸው ገሃነም ሊሆን ይችላል። በተለይ ቀደምትነትን የሚገልጹ ምስክር ቅርሶችም አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ።
 
በብዙ ሁነት በመፈንቅለ መንግሥት ከሚገኝ ትሩፋት ዬልቅ ኪሳራው፤ ውድመቱ፤ አመድነቱ፤ እልቂቱ የከፋ ይሆናል። እርምጃወች አረመኔያዊ ሊሆኑ ይችላሉ። በሌላ በኩል ኢትዮጵያን ያህል በመንግሥት አመሠራረት ታሪክ አንቱ የተባለችውን ያህል በዚህ ጥቁር ታሪክ #መለሰኗ ሌላው የሚጠዘጥጥዝ የውስጥ ህመም ይሆናል።
 
ዓለም ዓቀፋ ማህበረሰብ እንደ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ሂደቱን እጁን አጣጥፎ ይመለከተዋል ብየ አላስብም። ዕውቅናም የሚሰጠው አይመስለኝም። በሌላ በኩል የአፍሪካ ህብረት መቀመጫውን ለመቀየር ሊገደድም ይችላል። ይህ ደግሞ የሞት ያህል ከባድ ውርዴት ነው ለፓን አፍሪካኒስቱ ለኢትዮጵያኒዝም ቀንዲላዊ አቅም። ግብጽ እና ወዳጆቿ የሚመኙትን በራስ እጅ መስራት ለእኔ የህሊና ህሙማንነት ነው። የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ይሁን ስኬቱ በኢትዮጵያ ዕድሜ ዘመኗን ባካበተችው የነፃነት ዕንቁ ገፆዋ አብነትነቱ ላይ ጠቀራ ስለሚያለብሰው።
 
አለም ዓቀፍ ማህበረሰቡ በስምምነት የተፈነቀለውን ሥርዓት ብልጽግናን ከመለሰ፤ በመፈንቅሉ ዙሪያ የተሳተፋት ሁሉ ሌላ አሰቃቂ የበቀል እርምጃ ሊወስድባቸውም ይችላል። ብልጽግናን የሚያስቆመውም ኃይል አይኖርም። በሂደቱም ለፈንቃዩ ጥልቅ ጉድጓድ ምሶ ቀብሮት ሊሄድ ይችላል። ሁልጊዜ እንደምለው ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድን፤ አቃሎ፤ አኮስሶ ማየት ጠቃሚ እንዳልሆነ ሳስገነዝብ ኑሬያለሁኝ። እሳቸው ያልተሳተፋበት ማናቸውም ሙከራ የ100 ዓመት መከራን ሊያሸከም ይችላል። #አታውቋቸውም#አሳቻ ናቸው። በሙያቸውም ሰላይ። 
 
መፈንቅል አድራጊው ራዕዩ እና ግቡን ቀርጾ ሳይሆን በደም ፍላት፤ ወይንም በቅጽበታውያን ውሳኔ ሊከወን ስለሚችል ማግስትን ለመተንበይ አይቻልም። የመዝለቁም ነገር አስተማማኝ አይሆንም። በራሱም ላይ ሌላ የአንጃ ቅርንጫፍ ሊፈጠር ይችላል። ስጋት፤ ጥርጣሬ፤ ጭንቀት አሁን ካለው በከፋ ሁኔታ ይቀጥላል። በሌላ በኩል ድርጁ የሆኑ የታጠቁ ኃይሎችን ዱር ቤቴ ያሉት ፋኖ እና የጫካው ኦነግ ሚና እንዲህ ይሆናል እንዲያ ነው ብሎ መተንበይም አይቻልም። 
 
ምን አልባትም ባለመሳሪያዋች ይለይልን ብለው አዲስ ግንባር ሊከፍቱ ይችላሉ። ህዝቡ ከስቃይ ወደ ስቃይ፤ ከዕንባ ወደ ባሰ እንባ፤ ከጭካኔ ተሰምቶ ወደ ማያውቅ ጭካኔን ተሸከም ሊባል ይችላል። በዚህ የኑሮ ውድነት ኢኮኖሚውን ማረጋጋት ሳይቻል ይቀር እና በዘርፋም ከፖለቲካው ባላነሳ ሥርዓት አልበኛ የሆነ የገብያ ገጠመኝ ሊፈጠር ይችላል። ይህን የኢኮኖሚ ባለሙያወች ይቀበሉት አይቀበሉት ባላውቅም፤ ህግ እና ሥርዓት ከቁንጮ ከተጣሰ በየዘርፋ ስርዓተአልበኝነት አንቱ ማለቱ አይቀሬ ነው። ሥርዓተአልበኝነት ምህረት የለሽ ነው። የሚያስተርፈው ነገር አይኖርም። 
 
በሰላም በፈቃድ ህወሃት መንበሩን ለቆ እንኳን የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ቀን ብሄራዊ በዓላትን በሰላም ወህ ብሎ አክብሮ አያውቅም። እንኳንስ የማይታወቅ ኃይል የመራው ንቅናቄ?
 
ማስተዋል፤ ማስተዋል። ሰክኖ ማሰብ በእጅጉ ያስፈልጋል። መኖር ሥልጣኔውን ከሚያስተጓጉል አለቅት ሃሳቦች ጋር ላለመወዳጀት የሚያስወስነው ከከፋው በጣም የከፋውን ማስቀረት፤ ለዛ አቅምን ቆጥቦ ማስተዳደር ይጠቅም ይመስለኛል።
 
#እርገት ይሁን። 
 
ለእናቴ ለኢትዮጵያ፤ ለሚናፍቁኝ ለድምጽ አልባወቹ የኢትዮጵያ እናቶች እምመኜው የልጆቻቸውን አለም በሰላም እና በፍሰሃ ድህነታቸውን ችለው እንዲያገኙ ነው። ልጆቻቸው እንዳይገደሉ፤ እንደወጡ እንዳይቀሩ፤ እንዳይሰወሩ፤ እንዳይታገዱ፤ እንደ ዕቃ እንዳይሸጡ እንዳይለወጡ፤ እንዲማሩ፤ እንዲዳሩ እንዲኳሉ። ይህ ምኞቴ ይሳካ ዘንድ ብዕርና ብራና ትጋታቸው ይቀጥላል። እናቶች የናፈቃቸውን። ልጅ የልጅ ልጅ እንዲዩ ነው የተረጋጋ ሰላም እና ስኩን የሆነ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት። አቤቱ ብልጽግና የኮበሌነት ባህሪውን ተግ አድርጎ ወደ ተረጋጋ አዳልት የፖለቲካ መሥመር ለመግባት ሊወስን ይገባዋል። የእኔ ድንግል ከቀጣይ ውስብስብ መከራ ኢትዮጵያን ትጠብቅልኝ። አሜን።
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
25/09/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።