19.11.2020 ረመጥ ነው ወልቃይትወጠገዴ።
ረመጥ ነው ወልቃይትወጠገዴ። እፍታ። በድጋሚ ለጥ ብዬ እጅ እነሳለሁኝ። ህወሃት ከድል እስከ ውድቀቱ የጎንደር ሁነት ምን ነበር የሚለውን የነበርኩበትን በምልሰት ቅኝት አቅርቤያለሁ። ማንበብ ፀጋቸው ለሆኑ ወገኖቼ፣ ታሪክን እንደ አግባቡ ለሚያዳምጡ፣ ለሚይዙ ወገኖቼ፣ በጭልፋ ፕሮፖጋንዳ የወልቃይትጠገዴ ጉዳይ ላይ ለሚያላግጠው የኦዳ ሥርዕዎ መንግሥትም ነገረ ሥራው የሳሙና አረፋ ነውና ውስጤን ያይ ዘንድ የፃፍኩት ነው። ልቀት። የወልቃይት እና የጠገዴ ጥያቄ ከአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ዘመን መባቻ ብቻ የሚመስላቸው አሉ። ህወሃት ጫካ ሆኖ ሲወስን ከህወሃት ጋር የነበሩ የጠገዴ፣ የወልቃይት ልጆች አፈንግጠው ወጥተው በለመዱት ዱር ገደል ሲታገሉ ነበር። ውጭ የወጡትም ለአንዲት ሰከንድ ከተጋድሏቸው ዝንፍ አላሉም። በዘመነ ህወሃት ረጅሙ ተጋድሎ ጋር የዘለቅን በርካታ ጎንደሬዎች የህሊናችን ሞተር እርስታችን ነው። ይህ ሊታወቅ ይገባል። ውስጣችን የማይበርድ ረመጥ አለ። የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ሲነሳ አቶ አሥራት አብርኃ የገብያ ግርግር ሲሉት ወጥቼ ቅጥ አስይዠዋለሁ። ማንነት ሸቀጥ አይደለም በገብያ ህግ የሚተዳደር። ድፍረታቸው ልክ ስላልነበረው ነበር ወጥቼ የሞገትኳቸው በደጉ ሳተናው ድህረ ገፅ። ኢሳትም ሳቢያ እያለ ሲያላግጥ፣ ግንቦት ሰባትም የነፃነት ኃይል ተጋድሎ እያለ ሲለነቁጥ ልካቸውን እንዲይዙ የብዕር ቦንብ ተልኮላቸዋል። ጠቅላዩ ወደ ሥልጣን ሳይመጡ ጭምጭምታ ሳይኖር በዝርዝር ለዛን ጊዜው የኦህዴድ ሥራ አስፈፃሚ የፅህፈት ቤት ኃላፊ፣ ለዛሬው ጠቅላይ በስክነት አስረድቻቸዋለሁኝ። የወልቃይትወጠገዴ ጉዳይ አገር በማስቀጠል ጉዳይ ምክንያታዊ ነው። ገዢ መሬት ነው። ህወሃት ሞተ ተብሎ ማወጅ የሚቻለውም ይህ ርስት ወደ ባለቤቱ ሲመለስ ...