#አብይዝም እና ሥነ - መንግሥታዊ #ፕሮቶኮል።

 

#አብይዝም እና ሥነ - መንግሥታዊ #ፕሮቶኮል
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።"
 
 May be an image of one or more people, people smiling, scarf and eyeglasses
 
#ምዕራፍ ፲፰።
 
ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት ማለቱ ብቻ በቂ አይደለም። 
 
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ለፕሮቶኮል ሥርዓት የሚመቹ #መሪ አይመስሉኝም። በፕሮቶኮላዊ ዲስፕሊን ሥር ለመንቀሳቀስም የሚፈቅዱ አይመስለኝም። ይህን ለ፱ኛ ዓመት ዋዜማ ላይ ከሚገኘው የመንግሥታቸው አፈፃጸም ሂደት ግብረ መልስ ያገኜሁት መረጃ ነው።
 
ቀድሞ ነገር በአብይዝም #ፕሮቶኮል ሙያ እንደሆነ አብይዝም ይቀበለዋል ብዬ አላምንም። ለአፍሪካው ስብሰባ መሪወች አቀባበል ሲደረግላቸው አንዲት ሴት አይቻለሁኝ። ይህ በተቋም ደረጃ ይሁን አይሁን አላውቅም። ወይንም የአፍሪካው ህብረት አዘጋጅቶ ይሁን አላውቅም።
 
የሆነ ሆኖ አንድን አገር እንደ መንግሥት #ሊያቆመው#ሊያጸናው፤ ሊያስከብረው ከሚችሉ በኽረ ጉዳዮች መካከል #ሥርዓት ወሳኝ ጉዳይ ይመስለኛል። በአብይዝም ዘመን የፕሮቶኮል ሹም የሚባልም ሰምቼ አላውቅም። በደርግ ጊዜ የኮነሬል መንግሥቱ የፕሮቶኮል አገልግሎት የሚሰጡ ደልደል ያሉ ፍጹም ታማኝ ሴት እንደነበሩ አስታውሳለሁ። ይህ በተዋረድ በክ/አገር፤ በአውራጃ እና በወረዳ በጽህፈት ቤት አገልግሎት ሥር ይመራ ነበር። 
 
አቀማመጥ #በሲነሪቲ ነው። ዝንፍ የለም። አለባበስም በስብሰባ #ደማቅ ሰማያዊ ካኪ፤ በመደበኛ ሥራ ካኪ ቀለም እና ድብ ያለ ድባ ነገር ይለበሳል። እኔ አመጸኛ ነገር ነበርኩኝ። ቅዳሜ እና እሁድም፤ ዓውድ ዓመታትም ሥራ ላይ ስለነበርን በእነኝህ ቀናት ካኪ አለብስም ነበር። የተለዬ ልብስ ለብሼ ነበር ቢሮ እምገባው። ትርፍ ሰዓቴ ስለሆነ።
 
እራሱ ካኪውን በፋሽን ዲዛይን ነበር አስፍቼ እምለብሰው። ካኬወቼን እማስመጣውም ከአስመራ ነበር። በስብሰባ ቀን ግን #ደማቅ ሰማያዊ የግድ ነው። በፋሽን ማሰፋትም አይፈቀድም። ለመክፈቻ ንግግር፤ ስብሰባ ለመምራት ለሴቶች አገር ባህል ቀሚስ ይፈቀድ ነበር። ለዛም ቢሆን ሂደቱ በፕሮቶኮል መሪው ሥርዓት ውስጥ ማለፍ ግድ ነበር። በተፈለገ ጊዜ ወደ ስብሰባ ቦታ አይኬድም። ሰዓቱን መጥኖ ጉዞውን የሚፈቅደው የፕሮቶኮል ሹሙ ነው። ልክ #በሰዓቷ ከተጋበዝንባት ቦታ መድረስ ታቅዶ የሚከወን ሥርዓት ነበር። አይደለም ብሄራዊ ላይ።
#ወደ ቀደመው ጉዳዬ ስመለስ ……
 
በዘመነ አብይዝም የአገር መሪወች ሲመጡ አቀባበሉ #ወጣ ገባ ነው። የአገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስተሮችም አቀባበልም ቢሆን እንዲሁ ወጣ ገብ ነው። ለአንዱ #ሙሉ፤ ለሌላው #እኩሌታ፤ ለሌላው #ሢሶ፤ እንዲያም ሲል #እርቦ ልብ - ክብር - ማዕረግ ይመደብለታል።
በፕሮቶኮል፤ በዲፕሎማሲ ጉዳይ በይፋ አንዱ ልጅ ሌላው #የእዳሪ ልጅ ሊሆን አይገባም። ለአንዱ ከፍ ያለ አቀባበል እና አቀራረብ ለሌላው ዝቅ ያለም ሊሆን አይገባም። ይህ ወጥ ያልሆነ ሁነት የተፈጠረው በዘመነ አብይዝም፤ የኢትዮጵያ ሥርዓተ - መንግሥት የፕሮቶኮል አገልግሎት ዕውቅና ስላልተሰጠው ይመስለኛል።
 
በፖለቲካ ሁነት ለምሳሌ ሲነሪቲ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ይህን የሚያስተካክለው እራሱን የቻለ የፕሮቶኮል ቢሮ እና ግልጽ የሆነ መመሪያ ሲዘጋጅ ነው። ለምሳሌ ወሮ ሙፍርያት ካሜል እና ከንቲባ አዳነች አበቤ ታች የነበሩት ከንቲባ አዳነች አበቤ ናቸው። ስለዚህ ቀድመው ሊቀመጡ የሚጋባቸው ወሮ ሙፍርያት ካሜል ሊሆኑ ግድ ይላል። ከዲያቆን ዳንኤል ክብረት እና ከአቶ አደም #ፋርህ ዲያቆን ዲንኤል ክብረት በሲነሪቲ ይቀድማሉ አቀማመጡ የሚደራጀው በዚህ ቅደምተከተል ነው። ወዘተ …… ነገረ ፕሮቶኮል እራሱን የቻለ አርት ነው። 
 
በዲፕሎማሲ #የኩርፊያ ጉዳይ ቦታ የለውም። ሊኖረውም አይገባም። ይህ ሁኔታ ባለፋት ፰ዓመታት እኔ የተከታተልኩት ክፍተት ነው። የጀርመን መንግሥት ካንስለር ኢትዮጵያ ሲሄዱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስተሩ አቶ ደመቀ መኮነን ሥልጣን ላይ ነበሩ። እሳቸው እንኳን አልተቀበሏቸውም። በሲነሪቲ የሚበልጡት ምክትል ሚር አንባሳደር ብርቱካን አያኖም አልነበሩም። እኛ እንኳን እማናውቃቸው ም/ የውጭ ጉዳይ ነበሩ። ለኃያሉ ጀርመን???? እንዲህ እና እንዲያ ………
 
……… ጀርመኖች ይህን እንደ አልባሌ ያዩታል ተብሎ አይታሰብም። በዓለም ዓቀፍ ፖለቲካ፤ ኢኮኖሚ፤ ባህል እና ትውፊት የፊት ረድፈኛ ናቸው ጀርመኖች። የልዕልት ዶር አንጊላ ሜርክል አገርን #ዝቅ ያለደረጃ መስጠት የተገባ ፈጽሞ አልነበረም። 
 
በሌላ በኩል ለአረብ ኢምሬት፤ ለጣሊያን፤ የዛሬን አያድርገውና ለኤርትራ መሪወች ደግሞ እራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስተሩ ይቀበላሉ፤ ለአንዳንዱ የፈረስ እጀባም አለ፤ ሲያስፈልግም ጠቅላይ ሚኒስተሩ እራሳቸው #ሹፌር ሆነው ልባዊ አቀባበል ያደርጋሉ። ይህ ተዛነፍ አያያዝ የአገርን ሉዓላዊ ክብር ይሸረሽራል። 
 
በውጭ ጉዳይም ሚር ደረጃ ቢሆን፤ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚር አቀባበል፤ አያያዝ በዛች ጠባብ የቡና ክፍል የነበረው ሁነት ይገርመኝ ነበር። ይህ ሁሉ ተዛነፍ የሚታየው ተገቢው ተቋም በተገቢው ጊዜ ሊቋቋም ባለመቻሉ ነው።
 
አንዱን አቅርቦ ሌላውን ማራቅ የኢትዮጵያን ቀጣይ ትውልድን ዋጋ ያስከፍላል። በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ያላባራ ፈተና ውስጥ አጠገብ የሚሆን ሁነኛ አቅም ያለው አገርም #ያሳጣል። በዲፕሎማሲው ዘርፍ ኢትዮጵያ የምትፈልገው ድጋፍ፤ ድምጽ ሲጠየቅም ይሁንታ ለማግኜት #ያዳግታል። 
 
ብዙ ክፍተቶች ነው ያሉት። እኔ ጉዳዬ የነገ ትውልድ የዲፕሎማሲ አራጣ ከፋይ እንዳይሆን ጥንቃቄ ሊደረግ ስለሚገባ ነው። አሁን የሰሞናቱ በጣሊያን አፍሪካ ሁነት፤ የኢትዮቱርኪ ግንኙነት የአቀባበል ፕሮቶኮል ደረጃውን እዩት። ለጣሊያን ጠቅላይ ሚር የተደረገው አቀባበል፤ ለቱርኪ ፕሬዚዳንት የተደረገው አቀባበል በአንድ ሰሞን ነበር ደረጃውን መዝኑት። ኢትዮጵያ በሁሉም መስፈርት ነው #በዓለም አደባባይ ለግምገማ የምትቀርበው። 
 
የጠቅላይ ሚር ጉዞም ሲሆን #እግረ መንገድ ይህንንም፤ ያንንም ተብሎ ባይሆን ጥሩ ነው። ክብርን ይቆራርጣል። ማዕረግ ይጣስ ዘንድ ሁኔታ ያመቻቻል። ለምሳሌ #የባቲካን ሥርዓተ ሁነት አዲስ ምዕራፍ ላይ ስለነበር፤ የምዕራፋ ማዕደኛ ለመሆን፤ በእግረ መንገድ፤ ጣሊያንም፤ ፈረንሳይም ጎራ ልበል ዓይነት ሁነት አይቻለሁኝ። በፍጹም ሊሆን የማይገባ ነበር። 
 
ባቲካን ደርሶ መመለስ ይቻል ነበር እኮ። እያንዳንዱ አገር የራሱ የጊዜ #ሰሌዳ አለው። እንደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ "የሰበር" ተጠቂ አይደለም ፖለቲካቸው። ስክን #እርግት ያለ ነው። እርግጥ ነው ተጽዕኖ ፈጣሪነት እና መሪነት ባመጣው ጣጣ የአውሮፓ ፖለቲካ በዘለንስኪዝም ምክንያት ብዙ ፈተና እያስተናገደ ቢሆንም። እራሱ ብዙ የአውሮፓ አገሮች የሶሻል መዋቅራቸውን እንደገና እንዲያደራጁ ተገደዋል በዩክሬናውያን የመኖር ፈተና። ይህ የማይታይ ክስተት ነው። 
 
የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች ዛሬ ዘለግ ላለ ጊዜ ዛሬን አብረን ቆዬን። እግዚአብሄር ይስጥልኝ። ሰላማዊ ምሽት እመኝላችሁለሁኝ።
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
 
ኑሩልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
19/02/2026
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።