የኢትዮጵያ Mastermind ለመሆን የተሰለፋ አገራት እና የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ መጥኖ የመነሳት መቅኖ አስፈላጊነት።
የኢትዮጵያ Mastermind ለመሆን የተሰለፋ አገራት እና የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ መጥኖ የመነሳት መቅኖ አስፈላጊነት።
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።



#ምዕራፍ ፲፰
ብዙ በጣም ብዙ ሁነቶች በኢትዮጵያ ሰሞኑን ተስተናግዷል። በላይ በላይ ፋታ አልቦሽ ሁነቶችን ሳይ በ2010 እኢአ ስደት ላይ የነበሩ ኢትዮጵውያን፤ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ አገሮች ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ ይጓዙ ነበር። ፖለቲካው ገና #ችግኙ ከፈልነት ሳያልፍ የገነገኑ ሁነቶችን እንደምን ማኔጅ ማድረግ እንደሚቻል እራሱን የቻለ አካልም ሳይኖር የነበረው ዲል ያለ ሁነት ይገርመኝ ነበር። ጎንደሮች ባለቅኔ ናቸው። ይህን መሰል ሁነት ሲገጥም "ራስ ሳይጠና ጉተና" ይሉታል።
ሰሞኑን ያዬሁትም አብይዝም የ፯ ዓመታት ልምድ ቢኖረውም፤ በጎኑ ማን አለ እራሱን የቻለ ተብሎ ሲታሰብ አንድ ሁለት ሊኖሩ ቢችሉም ብዙው የአብይዝም ቀጥተኛ መንፈስ ጥገኛ ነው። ከንቲባ ጽህፈት ቤትን፤ ጠቅላይ ሚር ቢሮን፤ ውጭ ጉዳይ ሚኒስተርን ለናሙና ማንሳት እችላለሁኝ።
አብዛኛው የሁለመና ሁነት የአብይዝም መንፈስ ጥገኛ ነው። ይህ ደግሞ አደጋው ብዙ ነው። እንጂ፤ እንጂማ በዚህ ወላፈን ውስጥ የማይቀርበትን አንዱን ኢቬንት ከውን፤ ለሌላው በቂ ጊዜ ሰጥቶ፤ አስታግሶ ፤ ሳይጠዳደፋ፤ ትንፋሽም ሰብስቦ ማስተናገድ ይገባ ነበር።
-------------- የገረመኝ ደግሞ፤ በዛ ሁነት ሰንብተው ጠቅላይ ሚኒስተሩ ትናንት ወለጋ ነበሩ፤ በ100 ቀናት ውስጥ ዶር ለማ መገርሳን እና እሳቸው የተሞገቱበት ደንቢደሎም በጉብኝቱ ተካታ ተመልክቻለሁኝ። ያን ጊዜ ጽፌበትም ነበር ስለ ነገረ ደንቢደሎ፤ ሊዮዋቸው እንኳን ፈቃደኞች አልነበሩም። አኩርፈው ነበር የተቀበሏቸው።
ብቻ፤ አወን ብቻ ……… ለምንድን ይሆን ይህ ሁሉ ጥድፊያ????
#ምዕራፍ ፲፰።
1) የአንካራው ዲክላሬሽን ማጫ ነበር። የቱርክ መንግሥት ሱማሌ ላይ ለሚኖረው አራጊ ፈጣሪነት፤ የሱማሌን አቅል አአጋግቶ፤ የኢትዮጵያን ፍላጎትን ጠርንፎ ወይንም #ቀፍድዶ የእራስን ፕሮጀክት ለማሳካት የታለመ ነበር የአንካራው ዲክላሬሽን። ……… ይህ ከተቻለማ እኔስ ምን ያንሰኛል የኢትዮጵያ ህሊና መሪ ብሆን የቱርክ መሠረታዊ በኽረ ጉዳይ ይመስለኛል። አሁናዊው የቱርክ ተነሳሽነት። አቅምም፤ ጉልበትም ያለው መንግሥት ነው ቱርክ።
ቱርክን በሚመለከት በኢትዮጵያ "የዝም አንልም" የእስልም እምነት ንቅናቄ፤ አንድ የቱርክ ዘመናዊ ሰብዕና ያለው ወዳጄ ስለ እስልምና ዕምነት አንዳንድ መርኾችን ስጠይቀው፤ በተጨማሪነት የቱርክ መንግሥት በየአገሩ ሊያሳካ የሚፈልገውን ፕሮጀክት አክሎ ነግሮኝ ነበር። ዘሃበሻ ላይም ስሜቱን ጽፌው ነበር። የኡቶማን ቱርክን የመመለስ ፕሮጀክት ተግቶ እየሠራበት ስለመሆኑ አጠይሞ ነግሮኝ ነበር።
1) የአንካራው ዲክላሬሽን የምን #የባህር በር? የምንስ ወደብ? በሚል ኢትዮጵያ በሱማሌላንድ የአጨችው ፍላጎት - መከነ። በዚህ ካሳነት የቱርክ መንግሥት ለፈጸመው ውለታ እኔ ነኝ ያለ የፕሮጀክት ጠቃሚ ንቅናቄ ሱማሌ ላይ ጀምሯል የቱርክ መንግሥት። በአንካራው ዲክላሬሽን ሱማሌ እና ቱርክ አትርፈዋል። ኢትዮጵያ በምንም ነው ከፖለቲካ ውድድሩ የወጣችው።
2) የሰሞናቱ የቱርክ ጉዞ አቀባበሉን ተመሌክቻለሁኝ። መግለጫውንም - ተከታትያለሁኝ። የአቀባበሉ ፕሮቶኮል የሌሎች የአገር መሪወችን በተቀበሉበት ልክ ወይንስ ያነሰ ወይንስ በትክክሉ የሚለውን ለመመርመር ሞከርኩ። በዘርፋ ልጽፍበትም እራሱን አስችዬ እፈልጋለሁኝ። ከአንድ የዩቱብ ሰብዕ ጋርም ስሟገትበት ነበር። የሆነ ሆኖ የቱርክ መንግሥት ቁንጮ በሚመለከት አቀባበሉ ደረጃውን የጠበቀ ነበር ወይ? ይህ ለቱርክ መንግሥት ይመቻል ወይ? ይመጥነዋል ወይ? መዝኑት።
ጋባዡ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ መሆናቸው ገርሞኛል። ብዙ ክፍተት ሊያመጡ፤ ሊፈጥሩ የሚችሉ ፖለቲካዊ ክስተቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ። የሆነ ሆኖ የብልጽግና ፖለቲካል ፓርቲ ደጋፊወች ኢትዮጵያ እንዳተረፈች ሲያዘክሩ አዳምጫለሁኝ። እኔ ግን አዲስ ልምራሽ የሚል መንፈስ ነው የተገነዘብኩት። ሉዓላዊነትን አስረክቦ የዕንቁ ሥጦታ ለዕኔ ምንም ስለሆነ። የቱርክ መንግሥት የኢትዮጵያ Mastwrmind ለመሆን በድፍረት የገለጸበት አጋጣሚ ነው እኔን የገባኝ። ይህ ደግሞ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ፈቃድ ልሰጠው የማልፈልገው ጉዳይ ነው።
#የቱርክ መንግሥት በአንድ ድንጋይ ከሁለት በላይ ተልዕኮ ለማሳካት የቻለበት አጋጣሚ ነው።
2.1 የአንካራው ከሱማሌላንድ ጋር የነበረውን ሁነት አመከነ።
2.2 ኢትዮጵያ በቀጠናው ላይ የጦርነት መሻት እንዳላት እና ይህን እንድታቆም ቀጭን ትዕዛዝ ሰጥቷል። በቀጥታ የምን "የአሰብ" ወደብ ዓይነት ነው ዕድምታው። ዝግትግት ብለሽ ተከርችመሽ ተቀመጪ ነው ትእዛዙ። #ወዮም! ብትሞክሪያት አለበት። ጦርነቱ ባያስፈልግም የፖለቲካ ውሳኔ ግን ከቱርኪ ኢትዮጵያ ፈቃድ የምትጠይቅበት ቅንጣት ሁነት ሊኖር አይገባም ነበር።
ወደፊትም የቱርክ መንግሥት የአዛዥነት የመብት እንጥፍጣፊ ሊኖር አይገባም። የእነኛ ኮስታራ እመው እነ አቨውን የአርበኞቻችን አጥንት ከመቃብር አውጥቶ #መጠቅጠቅም ነው። እርግማንም ነው። የቱርክ መንግሥት ድፍረት ግን በእጅጉ ገርሞኛል። አዛዥ ናዛዥ ልሁን ብሎ ነው የቀረበው። ቅንጣት ፍርፋሪ ኢትዮጵያን የወገነ መንፈስ አላየሁም። ለመንፈሱ እርካታ ተብሎ ያዬሁት ሁነት ይገርማል።
የኢትዮጵያ የመንግሥት መርሆ ምንድን ነው? እኛ እማናውቀው ነገር ይኖር ይሆን???? ይህን ሁነት በጅጅጋ ጉዞ ለሱማሌ፤ እና የጁቡቲ መንግሥትም መሰል አቀራረብ ነበር። የቱርክ መንግሥት ቢቆላማጥ፤ ቢቀማጠልም ሁነቱ ከሁሉም በላይ አገር ለሚል ኢትዮጵያዊ ዜጋ ገጠመኙ በንቃት ልንከታተለው የሚገባ ሆኖ ነው ያገኜሁት። እራስን አሳልፎ መልጠት ከአገር በላይ??? ምን አለና።
2.3 ሌላው የእስራኤል ወደ ስትራቴጂክ ቦታ ብቅ ማለት የውስጥ #ቁስለት ለቱርኪ መንግሥት ፈጥሯል። በአንካራው ዲክላሬሽን መክኖ ወደ ጋርቤጅ የተጣለው አመክንዮ አቋራውን እርግፍ እርግፍ አድርጎ የእስራኤል መንግሥት ሳይሽኮረመም፤ በድፍረት የማንንም ይሁንታ በግልጽ ሳያስፈልገው የመጀመሪያው ለሱማሌላንድ የአገርነት ዕውቅና ሰጥቷል። ተከታታይ ተግባራትንም በአደባባይ እየፈጸመ ነው። በጀርባው የእስራኤል መንግሥት ቤቢዬ የሚል ገዢ ገናና መንፈስ ስላለው።
በዚህ ዘርፍ ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ሚና እንዳይኖራት እና ማናቸውንም #የቀና፤ የዳበረ ግንኙነት ከእስራኤል ጋር እንዳታደርግ ህሊናን የሚያስር ዋ! ብትሞክሩት ነው የተባለችው።
በሌላ በኩል እስራኤል በሰጠችው የአገርነት ዕውቅና ላይ ኢትዮጵያ #ማጣፈጫ የፖለቲካ አቅም እንዳታቀርብ፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ በሚገኝ የለሰለሰ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ጥቅማ ጥቅም ማዕቀብ ተጥሏበታል።
ይህም ብቻ አይደለም ለሱማሌላንድ የአገርነት ዕውቅና ልዩ ማዳበሪያ የሆነችው ኢትዮጵያ፤ መንገዱን የጠረገችው ኢትዮጵያ፤ በዘርፋ ቀጣይ መስመር እንዳትዘረጋም የተስፋ አንገቷ #ስቅለት ታውጆበታል።
እኔ ሳስበው የቱርክ መንግሥት ኢትዮጵያ በቱርክ ስር #በኮንፌደሬሽን ያለች አገር ያደረገ፤ ደፋር እና ይሉኝታ ያጣ፤ ዓይን ያወጣ ፈጣጣ እና ተጫኝ ሁነት ነው ያዬሁት። የቱርክ መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ ባይጋበዝ ይህ ሁሉ የጣጣ ጫና ባልመጣ ነበር። የብልህ አማካሪ፤ ብልህ ምክሮችን የሚያደምጥ መሪም የሚያስፈልገው እንደነዚህ ዓይነት #ዝልኝ አመክንዮችን ከመምጣታቸው በፊት ማስቀረት ይቻል ነበር።
2.4 ከዚህ ባለፈ ማህበረ - የአረብ ኢምሬት አባልነትሽን እቴጌ ኢትዮጵያ አስታግሰሽ፤ ከእኛ ሥር እጅም፤ እግርም የሌለው ድንቡልቡል አገር ሆነሽ ከብለል፤ ከብለል ስናደርግሽ አቤት ወዴት በይ ነው። ፍጥጫው ይህ ነው።
2.5 በዚህ ጉዞ ውስጥ ኤርትራም፤ ግብጽም፤ ሱማሌን በጽንሰት ተሰንቀው፤ ኢትዮጵያ ካለምንም የቅርብም፤ የሩቅም አጋር አገር የሌላት፤ በወና ዲፕሎማሲ፤ የከሰረ ሂደትን ታስተናግድ ዘንድ ብርቱ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ቱርክ መንበር ላይ ሆኖ፤ እግርጌ ግብጽ፤ ኤርትራ፤ ሱማሌ ተፈቅዶላቸው፤ ኢትዮጵያ #ጋርደን ጠባቂ ትሆን ዘንድ ብይን ነው የተሰጠው።
ይህን ለፍፁም #ተገዢነት አሻም! ይህን ለፍጹም #ባርነት አይሆንም! ይኽን ለፍጹም #የበታችነት እንብኝ! የምንል ሚሊዮን ጭምት ልጆች እንዳሏት አጤ ቱርክ ሊሂቃኑ የተገነዘቡት አይመስለኝም። እኛ ባርነት አላሳደገንም። ኢትዮጵያ እንደ ሱማሌ፤ እንደ ግብጽ የቅኝ ግዛት እርሾ #አላበቀላትም። በቀደምትነት፤ በገናነት፤ በሰማዩም በምድሩም ልቅና እና ልዕልና አንቱ የሆነች ፈላስፋ አገርን ታሪክ ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል ከጉብኝት በፊት። አገረ ቱርክም የራሷ ልዑቅ ታሪክ ቢኖራትም እኛን መንፈሳችነን፤ ጸጋ እና በረከታችን ከሥር ለመንዳት ማሰብ ግን የማይቻል ነው። እሚበጀው መከባበሩ፤ መደማመጡ፤ ልክን አውቆ በልክ መጓዙን ነው።
ትናንት በግብጽ የተፈጠረች ኤርትራም ምኞቷ እኔ ለኢትዮጵያ ህሊናሽ ልሁን ባይ ናት፤ ግብጽም ይኽን እኔ ካፒቴን ልሁን ነው የሚያንደፋደፋት፤ አቤቶ ቱርኪ መንግሥት መሻትም በዚህው መስመርተኛ እንደሆነ እያስተዋልኩ ነው። ሦስቱ የኢትዮጵያ Mastermind እንሁን ባዮች ተፎካክረው ማን እንደሚያሸንፍ ይታያል። አረብ ኢምሬትም፤ ሳውዲም ይህ ህልም የላቸውም ብዬ ላስብ አልፈቅድም።
#እና።
አሁን ነው ቁጭ ብሎ የኢትዮጵያ ሊቃናት የኢትዮጵያን የፖለቲካ አቅም ከጅዋጅዊት አውጥተው ለቀረመት የተሰናዳችውን አገራቸውን ክብር፤ ልዕልና እና ልቅና ለማስጠበቅ የእመው እና የአቨውን #ዊዝደም ናልን ሊሉ የሚገባቸው። አብይዝም ቢሆን ተስምንት አቅጣጫ ውጥረት ላይ ያለውን የኢትዮጵያ አዬር ከማባከን ማሳረፍ። አየሩ ወህ ይል ዘንድ ሊፈቅድ ይገባል። ሊቃናቱም ጥሞና መውሰድ ያለባቸው ይመስለኛል። #ተግታ። በቅንጥብጣቢ ሁነቶች በመሳብ ሉዓላዊ አገርን ክብርን ማስነካት አይገባም። አገር አገር ነው። #መጠሪያ። አገርን ከእነ ማዕረጓ ለማስቀጠል ፋይዳው ፋይዳ አትራፊነቱ በጥሞና ሊፈተሽ ይገባል።
ለየትኛውም አገር ይለፍ የሚሰጠው ከሉዓላዊነታችን በላይ ሊሆን አይገባም። የዲፕሎማሲ ግንኙነት ልካችን ሊደፈጥጥ አይገባም። እራስ ጋብዞ ዝቅ ብሎ፤ ጎብጦ ከመሄድ ተቆጥቦ ክብሩን ማስጠበቅን ማስቀደም።
ሌላው መልስ ከመስጠት በጥቃቅን ጉዳይም #ዝምታን መምረጥ። ምክር ማድመጥ። "ላምረኛ ምን አለን" ቁብ መስጠት። አየር ላይ እንዲህ አወዛጋቢ ወሳኝ ጉዳዮች ሲገጥሙ፤ በይፋ፤ በአደባባይ አውጥቶ ህዝብ ተወያይቶ ድምጽ እንዲሰጥ በማድረግ ዳታ በመሰብሰብ መሾፈሪያውን በዳታው ፈቃድ ልክ የአብዛኛው ፍላጎት ያረፈበትን አመክንዮ #በገዢነት ተቀብሎ ሥራ ላይ መዋል በእጅጉ ያስፈልጋል።
#የመከወኛ መግቢያ ለስንዴ ባለነዶቹ።
ለብልጽግና ደጋፊወች፤ ካድሬወች፤ የሚዲያ ባለቤቶች የፓርቲው ፍላጎትን ከሉዓላዊነታችን በላይ እባካችሁ #አታንጠራሩት። እንደ ፖለቲካ ድርጅት ገና ለጋ ጮርቃ እና ብዙ መርህ ገብ ዲስፕሊኖች ክፍተት ያለበት ድርጅት ነው አቤቱ ብልጽግና። የመወዳደሪያ ምልክቱን ሲወስን በሳል የትርጉም ዳሰሳ እንኳን ማድረግ አልቻለም፤ ባለፈው ተሎ ሊሰበር፤ ተሎም ብርሃኑ ሊከትም፤ ሊቃጠልም የሚችል አንፖል ነበር። ዛሬ ደግም "ነዶ።" ጽፌበታለሁኝ።
ብልጽግና የልምድ፤ የተመክሮ፤ የአደረጃጀት ችግር አለበት። ስለሆነም ግድፈቶቹን ማረሙ ነው የሚጠቅመው። …… እንጂ እርምጃው ሁሉ ቅዱስ አድርጎ መቀበሉ #አያጸናውም። አያሳድገውም። የቱርክ መንግሥት አስኳላዊ ፍላጎት በተከታተልኩት ልክ የሚያስፈነጥዝ አልነበረም።
የተከበሩ የቱርክ ፕሬዚዳንት ፕሬዚዳንት ረጅብ ጣይፕ ኤርዶዋን ከሉዑካኖቻቸው ጋር ፈላስፊት ኢትዮጵያ አገሬን ለሁለተኛ ጊዜ ሄደው ስላዩ አመሰግናቸዋለሁኝ። በሌላ በኩል ግን መብቷን #ሊጫኑ ያቀረቋቸውን ሰም ለበስ ፖለቲካዊ ሁነቶች አልተመቹኝም። ይህ ፎቶ ፕሬዚዳንት ረጅብ ጣይፕ ኤርዶዋን በመሬት መንቀጥቀጥ ህዝባቸው አደጋ ሲደርስበት የነበራቸው ሁነት ነው።
አንጀታቸው #ሩህሩህ ይመስለኛል። ይህ መታደል ነው። አከብረዋለሁም። የሶርያን ስደተኞች በከፋቸው ጊዜ ከጀርመን መንግሥት ለቀረበላቸው ስደተኛን ሼር የማድረግ ጥያቄ ይሁንታቸውንም ከሰብአዊነት አንፃር ስለማየው የማከብረው ነው። ለዚህ ትልም የጀርመን መንግሥት ጠርቀም ያለ ድጎማ አድርጎ ነበር። ለሶርያውያን ዕንባ ጀርመን እናት መሪ አገኜ እና ብዙ ህይወት ተረፈ።
*** ከዚህ ብዙ የቱርክ የገብያ ማዕከሎች አሉ። በገብያም፤ በሥራ ቦታም የቱርክ ዜጎች ትጉህ እና ሰብዕዊ ሆነው ነው የማያቸው።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergure©Selassie
19/02/2026
ዕውነት ወጌሻ አያስፈልገውም።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ