19.11.2020 ረመጥ ነው ወልቃይትወጠገዴ።

 

ረመጥ ነው ወልቃይትወጠገዴ።
 No photo description available.
እፍታ።
በድጋሚ ለጥ ብዬ እጅ እነሳለሁኝ። ህወሃት ከድል እስከ ውድቀቱ የጎንደር ሁነት ምን ነበር የሚለውን የነበርኩበትን በምልሰት ቅኝት አቅርቤያለሁ።
ማንበብ ፀጋቸው ለሆኑ ወገኖቼ፣ ታሪክን እንደ አግባቡ ለሚያዳምጡ፣ ለሚይዙ ወገኖቼ፣ በጭልፋ ፕሮፖጋንዳ የወልቃይትጠገዴ ጉዳይ ላይ ለሚያላግጠው የኦዳ ሥርዕዎ መንግሥትም ነገረ ሥራው የሳሙና አረፋ ነውና ውስጤን ያይ ዘንድ የፃፍኩት ነው።
ልቀት።
የወልቃይት እና የጠገዴ ጥያቄ ከአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ዘመን መባቻ ብቻ የሚመስላቸው አሉ። ህወሃት ጫካ ሆኖ ሲወስን ከህወሃት ጋር የነበሩ የጠገዴ፣ የወልቃይት ልጆች አፈንግጠው ወጥተው በለመዱት ዱር ገደል ሲታገሉ ነበር። ውጭ የወጡትም ለአንዲት ሰከንድ ከተጋድሏቸው ዝንፍ አላሉም።
በዘመነ ህወሃት ረጅሙ ተጋድሎ ጋር የዘለቅን በርካታ ጎንደሬዎች የህሊናችን ሞተር እርስታችን ነው። ይህ ሊታወቅ ይገባል። ውስጣችን የማይበርድ ረመጥ አለ።
የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ሲነሳ አቶ አሥራት አብርኃ የገብያ ግርግር ሲሉት ወጥቼ ቅጥ አስይዠዋለሁ። ማንነት ሸቀጥ አይደለም በገብያ ህግ የሚተዳደር። ድፍረታቸው ልክ ስላልነበረው ነበር ወጥቼ የሞገትኳቸው በደጉ ሳተናው ድህረ ገፅ።
ኢሳትም ሳቢያ እያለ ሲያላግጥ፣ ግንቦት ሰባትም የነፃነት ኃይል ተጋድሎ እያለ ሲለነቁጥ ልካቸውን እንዲይዙ የብዕር ቦንብ ተልኮላቸዋል።
ጠቅላዩ ወደ ሥልጣን ሳይመጡ ጭምጭምታ ሳይኖር በዝርዝር ለዛን ጊዜው የኦህዴድ ሥራ አስፈፃሚ የፅህፈት ቤት ኃላፊ፣ ለዛሬው ጠቅላይ በስክነት አስረድቻቸዋለሁኝ። የወልቃይትወጠገዴ ጉዳይ አገር በማስቀጠል ጉዳይ ምክንያታዊ ነው። ገዢ መሬት ነው።
ህወሃት ሞተ ተብሎ ማወጅ የሚቻለውም ይህ ርስት ወደ ባለቤቱ ሲመለስ ብቻ ነው። በዚህ ጉዳይ ልቡ የማይሸፍት ድውይ የግንቦት 7 ካድሬ ጎንደሬ ብቻ ነው። ያው ስልብ ምርኮኛ ስለሆነ ከቁጥር አይገባም።
ተመስገን የሚያሰኘው ጎጃም ዋርካው ደም ገብሮበታል። ዓለም አቀፍ ዕውቅናም አለው። ዬአውሮፓ የጀርባ አጥንት ለህወሃት ፊት የነሳው በነገረ ወልቃይትወጠገዴ ነው። ውሽልሽል እንዳይመስላችሁ። የበሰለ ተግባር ተከውኖበታል።
የፈለገ ካድሬ ለኦዳ እጅ ይስጥ፣ ምርኮኛ ሊሆኑ ያልፈቀዱ ሚሊዮን ነፍሶች እንዳሉ ሊታወቅ ይገባል። በጦርነት ባይሆን ምርጫዬ ነበር። ኢትዮጵያ በተሰጣት መክሊት ልክ መሪ ስሌላት በምናዬው ቀውስ ውስጥ እንገኛለን።
አሻምተኛ።
ከአጤው ዘመን መውደቅ ጋር ጎንደር የሁሉም አሻምተኛ ቤዝመንት ነበር። ቋራ፣ ማጠቢያ፣ በለሳ አርባያ፣ ላይ እና ታች አርማጭሆ፣ ቆላ ወገራ፣ በዬዳ ጃናሞራ፣ ወልቃይት ጠገዴ፣ የህወሃት፣ የኢህአፓ፣ የኢዲዩው፣ በስተመጨረሻም የኦህዴድ።
ደርግ ሲወድቅ ደግሞ የከፋኝ፣ የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር። በኋላም የግንቦት 7 የአዬር ላይ ቀቢሰ የሞገድ ተስፋ። በውጭም በአገርም ቢሆን ቀላል የማይባል ጎንደሬ በዘመኑ ተጋድሎ ሁሉ አንቱ ተግባር ከውኗል።
ፀሀፊ፣ ጋዜጠኛ፣ የሰባዕዊ መብት ተሟጋች፣ ፖለቲከኛ፣ በዘመኑ ቋንቋ አክቲቢስት። ስደትም የበላው ይኽው ህዝብ ነው። ነጭ ሽብር እና ቀይ ሽብርም እንዲሁ። ህወሃትም ድቅቅ ያደረገውም።
በተለይ የህወሃት የወልቃይት ጠገዴ ወረራ በውስጡ ረመጥ ያልፀነሰ ጎንደሬ ይኖራል ብዬ አላስብም። የማንነት ጉዳይ ተፈጥሯዊ እንጂ በገብያ ህግ የሚመራ አይደለም እና። ከህወሃት በዬጊዜው ድል ላይ ሆነው ሁሉ ያፈነገጡ ቤተሰቦች አሉኝ። ህወሃት አስሮ ያንገላታቸው።
የኦዳው ቤተ - መንግሥትም የሚከተክተውም፣ ጥቃት አውጪውም ይኽው መከረኛ ህዝብ ነው። ያሳዝነኛል። ደመ መራራ፣ ሁልጊዜ ማገዶ።
ምልሰት።
ህወሃት ድል እዬተሳካለት ሲመጣ ወገራ እና ስሜን አውራጃ መልቀቅ ግድ ነበር። የወገራ አውራጃ ዳባትን፣ የስሜን አውራጃን ደባርቅን መንግስት ለቀቀ። ትንንሽ ከተሞችንም። በቆላው በኩል የወገራ አውራጃ ክፍለ አካል የሆነውን ሰቲትንም። የሰቲት መለቀቅ እጅግ ዘግናኝ የሆነ ታሪክም አለው። አፈፃፀሙ አሳዛኝ ነበር። ህዝባችን ተንገላታ።
ይህ የሆነው ጎንደር ላይ የነበረው የሰራዊቱ ክፍለ ጦሮች፣ ኮሮች፣ ተጠባባቂ አካላት መሰናዶ ሙሉው ወደ ማህል አገር እንዲሄድ በማዕከላዊ መንግሥት ስለተወሰነ ነበር።
ስትራቴጂኳ ጎንደር ባዶዋን ቀረች። ስለዚህ በአገሬው አቅም ለመመከት ኃይልን አሰባስቦ አቅምን ሳይበትኑ መዋጋት ግድ ስለነበር የወገራ እና የስሜን አውራጃዎች ተለቀቁ።
ህወሃት ትግራይ ቀድሞ ስለተለቀቀለት መጠነ ሰፊ ጥቃቱ አሸወይና ሆነለት። በደቡብ ጎንደር የደብረታቦር ውጊያ ለረጅም ጊዜ ታግሎ ተረታ።
አንፃራዊ ሰላም የነበረው በጎንደር ዙሪያ፣ በላይ እና ታች አርማጭሆ፣ በጭልጋ ወረዳ ነበር። በስሜን ጎንደር ከነበሩት አራት አውራጃዎች ውስጥ የቀሩት ሁለት ብቻ ነበሩ። ጎንደር ዙሪያ አውራጃ እና ጭልጋ አውራጃ።
እራሱ ፌድራሊዝሙ ክፍለተ ሃገራትን ስሜን ደቡብ እያለ የከፋፈለው ለአማፃዊ ቦታ የማመቻቸት ስትራቴጂካል የፖለቲካ ውሳኔ መሆኑ አሁን ላይ አስተውለዋለሁ። የእርስበርስ ጦርነት መከራው ይህ ነው።
ድል ሚስጢር ነው። ሚስጢሩ ለጠላት እጅ ቀድሞ ይደርስ ስለነበር ሽንፈት አይቀሬ ሆነ። የተማገደው ትውልድም ከስሎ ቀረ። ሰማዕት እንኳን አይባሉም።
የጎንደር አዬር ማረፊያ ነገር።
አዬር ማረፊያችን ዳኮታ ማሳረፍ አይችልም ነበር። እናም የአዬር ማረፊያ ነዋሪዎች እንዲነሱ ቀደም ብሎ ተወሰነ።
አስታውሳለሁ እዛም አስተባባሪ ነበርኩ በአንድ ቀን መሰረት ተጥሎ፣ ቆርቆሮ ለብሶ፣ የመጀመሪያ ምርጊቱ ተጠናቆ ብዙ ቤቶች በዚህ መልክ ተሰርቶ የአዬር ማረፊያ ቤተሰቦች ከሚያውቁት፣ ከለመዱት እትብት መንደራቸው ተነቅለው አዲስ ቦታ እንዲሠፍሩ ተደረገ።
የጦርነት ጊዜ አደብ የሚባል የለም። ጊዜ የለም። ለዚህ ነው እኔ አሁን በጣም ቁጥብ የሆንኩት። ጦርነት ሁሉን ይሻማል።
በነገራችን ላይ የአዬር ማረፊያ፣ የአዘዞ እና የጡሮታ ሠፈር ቀበሌ 3 ነዋሪዎች አብዛኞቹ የወታደር ቤተሰቦች ናቸው። ህብራዊነታቸውም ጉልህ ነው። የአኗኗር ዘይቤያቸውም ሥልጡን እና ማህበራዊነቱም የላቀ ነው።
የቀደመውም የጎንደር ሥልጣኔ መሠረቱም መጣችሁብን ሳይሆን መጣችሁልን ስለሚያነግሥ ጎንደር ዘመን ከዘመን የጎንደር ልቅና በልዕልና የሆነበት አመክንዮ የዚህ የይትባህል ትሩፋት ባለፀጋ ስለሆነ ነው።
ጎንደር ውስጥ አንድም ሰው ከዬት መጣህ? ኃይማኖትህ ምንድን ነው ተብሎ ተጠይቆ አያውቅም። ፈፅሞ።
ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ እነኛን ከአዬር ማረፊያ ያነሳናቸውን ወገኖቻችን መኖር ፈርሶ አዲስ መንደር የተመሠረተው፣ እኛም ከዛው እያደርን እዬዋልን አቧራ ለብሰን የተጋነው አንቶኖብ ሠራዊት አምጥቶልን ጎንደርን ኢትዮጵያን ይታደጋል በሚል ነበር።
አሳዛኙ ተውኔት።
ማዕከላዊ መንግሥት ኮነሬል መንግሥቱ ሳያውቁ ጎንደር ያለው ሠራዊትን አሟጦ ሲወስድ ጎንደርን ለህወሃት ለማስረከብ ስለመሆኑ ባለፈው ጊዜ የ603ኛ ኮር አዛዥ የነበሩ ከፍተኛ መኮነን ከሰጡት ቃለ ምልልስ ተረድቻለሁ።
ጎንደር ላይ ህወሃት አከርካሪው ተመቶ ቢሆን ኖሮ ሁሉም ነገር በቁጥጥር ሥር ይውል ነበር። ጎንደር ቅባዓ አለው እምለውም ለዚያ ነው።
ጎንደር ላይ የሚነሱ መንፈሶችን በጥንቃቄ፣ በአክብሮት ዕውቅና ሰጥቶ መያዝ ካልተቻለ የረጋ መንግሥት ህልም ነው። ፈጣሪ አላህ ከዛ ባዕት የሚጠብቀው የመንፈስ ማረፊያነት ያለም ይመስለኛል።
ባለፈው አመት ጥጋበኛው ጠቅላይ ሚኒስተር ጦር አውርድ ብለው ልጆቹን መፍጀታቸው ላይበቃ ጦር ሲያዘምቱበት ጤናቸውን በጣም ተጠራጠርኩኝ። አስቀድሜ አበክሬ ነግሬያቸዋለሁ። ለከንቱው ግንቦት 7 እንዲሁ።
ወደ ቀደመው የደርግ ሽንፈት …
ተጣበን፣ ተጣበን በቀረችን አንድ ዕድል አዬር ማረፊያው ተሳክቶለት አንቶኖብ አሳረፈ። ያ ሁሉ ህዝብ ተፈናቅሎ አንድ ጊዜ ብቻ። የመጣው ግን ስንቅ ጭኖ ነበር። የኢትዮጵያ መርዛማ ፖለቲካ ጢባ ጢቦሽ ይኽው ነው። ጎንደር በነፍስ ውጪ ግቢ ላይ ኦክስጅን ነበር የሚያስፈልጋት። ሠራዊት።
ህወሃት ከኢህዴን ጋር ሆኖ ደንቀዝ ላይ ከባድ መሳሪያ ይለቃል። በቀጥታ ያነጣጠረው እዛ ላይ ነበር። በፈጣሪ እርዳታ ባገኜነው ዕድል ሠራዊት ሊላክ ሲገባ ለአጋሰሱ ስንቅ ልከናል የሚል የራዲዮ መልዕክት መጣ። ለአማፅያኑ ጎንደር ሲገባ ስንቅ እንዳይቸግረው።
የሚያሳዝነው የአዬር ማረፊያ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀያቸው መነቀል ዋጋ ቢስ ሆነ። የበለጠ ህሊናን እንደ ዱባ የሚቀረድደው ለእነኝህ ምስኪኖች ካሳ ለመክፈል፣ የበለጠ የሎጅስቲክስ አገልግሎት ሳይሟላ ነበር ጎንደርን አማፅያኑ የተቆጣጠረው።
በዛ በነበረውም አንድ ዕድል ሠራዊት ተልኮ ቢሆን ስንቁን የጎንደር ህዝብ ይችል ነበር። ይህም ብቻ አልነበረም። ደንቢያ በር ነፃ ቀጠና ነበር። አዬር ወለድ ማቅረብ ይቻል ነበር። አልሆነም። ይህ ከታወቀ በኋላ ነበር ጓድ ገዛህኝ ወርቄ ኮማንድ ፖስታቸውን ከማህል ከተማ ወደ ሌላ ቦታ የቀዬሩት።
ጓድ ገዛህኝ ወርቄ የስሜን ጎንደር ኢሠፓ ፅህፈት ቤት ተጠሪ፣ አቶ ሽፈራው እንቁባህሪ ዋና አስተዳዳሪ ነበሩ። አብዝቶ እርጋታውን የሰጣቸው መሪዎች ነበሩ።
በመጨረሻም ዕድሉ እዬጠበበ ሲመጣ ኮማንድ ፖስቱ ወደ ላይ አርማጭሆ ትክል ድንጋይ ሲዛወር ቢሮ የቀረነው ጥቂት ሰዎች ነበርን።
ያን ያደረጉበት ጥበብ ጓድ ገዛህኝ ወርቄ እና አቶ ሽፈራው ዕንቁባህሪ ጎንደርን ለማዳን ነበር። ጦርነቱ ከተማ ውስጥ ሆኖ አገልግሎት መስጫ ተቋማታ፣ ታሪካዊ ቅርሶች ጉዳት እንዳይደርስባቸው በማሰብ ነበር። ልቅና በልዕልና።
አዲግራት እና ደንቀዝ።
የሰሞኑ አዲግራት ሆነው ህወሃቶች ተኮሱት የተባለው የርቀት መሳሪያ እና ጎንደርን ሊይዙ ሲሉ ደንቀዝ ላይ ሆነው ያቀዱት ትልም የጎንደር አዬር ማረፊያን ለማጥቃት ነበር። ታሪክ እራሱን ደገመ። ግን ህወሃት የጎንደርን ቅስም መስበር አለመቻሉን ጥንትም ሆነ ዛሬ ያውቀዋል።
የታሪክም ውርዴ ነው። ያበላ፣ ያጠጣ፣ ገመናን ክውን አድርጎ የያዘን ወገን እንዲህ አይነት እያገረሼ የሚነሳ በቀል አለመታደልነት ነው። የጎንደር ሆነ የባህርዳር ህዝብ በቁጭት ተነሳስቶ እንደ እነሱ እንሰሳዊ ተግባር ፈፅሞ የፖለቲካ ዲፖ ለማግኜት ነው።
ጦርነት ከፍቶ የተፈናቀለው፣ ሰርክ የሚያልቀው ነፍስ አልበቃ ብሎ ነው ይህ የዕብድ ሥራ ደግሞ በ30 ዓመቱ የተደገመው።
የዛን ጊዜ ያሸነፋበት ሚስጢር የጎንደር አዬር ማረፊያ መያዝ ነበር። የጅልነታቸው ጅልነት እንጥፍጣፊ እነሱን ሊያስብ በማይችል የሥነ - ልቦና ድቀት በቀል፣ እልህ ቢወልድ እንጂ ትርፍ ሊያስገኝ የማይችል እርምጃ ነበር።
ትንሽም ተበትኖ ለሚኖረው ተጋሩ አለማሰብ ጭራቅነት ነው። አንድ የተበሳጬ ነፍስ ብዙ ጥፋት ሊያደርስ ይችላል።
ለዚህ ነው ከሁለት ወር በፊት ህወሃት የኩሬ ውኃ ነው ብዬ የፃፍኩት። መቼውንም ይህ ድርጅት ሰውኛም ተፈጥሮኛም አይሆንም።
ይህን ዝልብ መንፈስ እሸከማለሁ፣ አስቀጥላለሁ ብለው ጠቅላዩ መወሰናቸው ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የውርደትም፣ የመከራም አርኬብ ነው።
የላዩን እንጂ የታቹ እንዳለ ይቀጥላል እያሉን ነው። ለነገሩ በሳቸው ድርጅት ውስጥ ያለው መከራም ያልተነካ ነው። "እባብ ለእባብ ይተያያል ካብ ለካብ" እንዲሉ።
የታችኛው የህወሃት አካል ይቀጥል ሲሉ አዲሱን ምርጫም ተቀበልወታል ማለት ነው። ዝልግልግ። ከህወሃት እርሾ አያስፈልግም ጥበብ ላለው ህሊና።
ያው ሁሉም እንኩቶ ስለሆነ ግን ከዚህ ላቅ ያለ ነገር አይጠበቅም። ጠቅላዩ ልካቸው ይኽው ነውና። ለአቅመ አዳም ያልደረሰ የመሪነት አቅም መከራው ወዘተረፈ ነው።
የጎበዝ አለቃ ተጋድሎ ጎንደርን በማዳን ንቅናቄ።
ታስታውሳላችሁ የአማራ የህልውና የማንነት ተጋድሎ ሲነሳም በአንድ ተፈጥሯዊ እዝ ሥር እንደምን ፈጥኖ እንደ ደረሰ ይታወቃል። ትውልዱም አይቶታል።
ቀደም ያለው መንፈስ ትውፊቱ በውርርስ ነው። ይህ የተነሳሁበት አንኳር ነጥብ ነው። ከህወሃት ያፈነገጡ ጀግኖች አርበኛ አበጄ በለው በሚል መሪያቸው በወልቃይትወጠገዴ ጥቃት የሚያወጣ ተጋድሎ ያደርግ ነበር።
ይህን ሃይል በአገር ይትብኃል አስማምቶ፣ አግባብቶ የስሜን ጎንደር አስተዳደር አብረው ይሠሩ ዘንድ በህጋዊነት ተቀበላቸው። በሰላም ገቡ።
በማዬት ብቻ የአቅማቸውን፣ የቁርጠኝነታቸውን ልክ ማወቅ ይቻል ነበር። ወደ ጎንደር ሲገቡ የእኛ ቢሮ እና አስተዳደሩ ፊት ለፊት ስለሆነ በተለይ የእኔ ቢሮ ለማዬት ምቹም ስለሆነ ሳያቸው ቆፍጣና፣ የቆረጡ፣ ትንታግ ነበሩ። የሥነ - ልቦና አቅማቸው መለኪያ ወቄት አልነበረውም። ትዕዛዙ በኮማንድ ፖስት ይሰጥ ነበር።
ጎንደር በሦስት ዙር ቀለበት ጉድብ ተሰርቶ ቀደም ብሎ አገ -
ሬው ጥበቃ ሲያደርግም ነበር። ሥልጠናም ተሰጥቷል። አያያዙ ያላማራቸው ጓድ ገዛህኝ ወርቄ ቀድመው ነበር ይህን የሠሩት። ያው እቴጌ ጎንደር በዬዘመኑ የጦር ቀጠና ናት እና።
አጤውም ሲወርዱ አሻም ብሎ ዱር ቤቴ ያሉት ጎንደሮች ነበሩ። ነፍሳቸውን ይማረው እና በሻ / አጣናው ዋሴ አማካኝነት። ጀግና ነበሩ። ዓራት ዓይናማ። ከተሰደዱበት ሱዳን አፍኖ አምጥቶ ህወሃት ነው የገደላቸው።
ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ ደርግ ሲፈረካከስም የ18 ቀኑ እልህ አስጨራሽ የመከላከል ገድል የተሠራው በእነኛ ትንግርተኛ የጎበዝ አለቆች በሚመሯቸው ጀግኖች እገዛ ነበር እንጂ ደርግማ ቀድሞ ጎንደርን አስረክቦ ነበር።
ማህበረ ምዕመኑ ቀጥ ብሎ ምህላውን አደባባይ እዬሱስ ላይ ያካሂድ ነበር። ልክ እንደ ዛሬው። ጎንደር ጭስ ነበር የምትመስለው። ጦርነት ክፋ ነው። ሁለመናን ይቀማል። መኖርን ይነጥቃል።
ሴቱ ስንቅ በማቀበል፣ ተባዕቱ በግንባር ጎንደሬ ተፋለም። ያን ጊዜ በከተማ ውስጥ ህወሃት ሰላዮችን በገፍ አሰማርቶም ነበር። በሁሉም ዘርፍ ጥረቱ ቢጠናከርም አልሆን ሲል መልሶ ለማጥቃት በጓድ ገዛህኝ ይመራ የነበረው ኮማንድ ፖስት ወደ አርማጭሆ ጫካዎች አመራ። ስትራቴጂካል ማፈግፈግ ነበር የተወሰደው እርምጃ።
ይህ የሆነው ህወሃት አዬር ማረፊያን የተቆጣጠረ ጊዜ ነበር። በሰማይም ገጠር ላይ የማጥቃት እርምጃ ነበር። ብዙ ነገር ተፈጥሯል።
ዛሬ ህወሃት የደረሰበት ከበባ ታሪክ እራሱን ደግሞ እሱ ልክ ጎንደርን ከቦ እንዳጠቃው እሱም ቀለበት ውስጥ ሆነ። ይገርማል።
ጥበብ ቢኖራቸው የመቀሌን ከተማውን ማዳን በመዳፋቸው ነው። ይህ ሁሉ ህዝብ እንዲህ የሚማገደው 400 ለማይሞሉ የሥልጣን ሱሰኞች ነው። ኢትዮጵያ እማ ስትከዳ ነው የኖረችው። እከሌ ተከሌ የለበትም ለክህደቱ።
ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ ጥበበኛው ጓድ ገዛህኝ ወርቄ ኤሊኮፍተር ሲላክላቸው ህዝቡን ጥዬ አልሄድም አሉ።
ከተማው ላይ ውጊያ እንዳይካሄድም ኮማንድ ፖስቱን ወደ ላይ አርማጭሆ አዛወሩት። ጎንደር ተረፈች ከእነ ግርማ ሞገሷ። ያ ትልቅ ትርፍ አስገኝቷል።
እኔም እጄን አልሰጥም ብዬ ጫካ የገባሁት ያን ጊዜ ነበር ግን ተቆራርጠን ነበር። ለዚህም ነው ህወሃት መቀሌ ከተሸኜ በኋላ ሆነ፣ አሁን በዝርክርክ አመራር ቅጥ መጠኑ በጠፋ ወጣ ገብ አመራር ቁጥብ ሁኜ ሁኔታውን እዬተከታተልኩ ያለሁት።
ወጣትነትህን ገብረህ፣ ተማግደህ ሥልጣን ሰጥታህ መምራት ተስኖት ላንቁሶ ሲሆን ቀሪውን መንገድ መጨረስ የደካማው የኦዳ አመራር ይሆናል። ነገ ደግሞ ወጥቶ ያቅራራል። አያፍሬ የኦዳ ሹማምንት። ለነገሩ አሁንም ማገዶው ጎንደር ነው።
የሆነ ሆኖ የገዛህኝወሽፈራው አመራር ጎንደርን በአገር ቅርስነቷ እንዲቀጥል አድርጓል። ዓለምም አትርፏል። ጎንደር የዓለምም ቅርስ ውርስ ናት። በጦርነት ጊዜ ማስተዋል፣ ማድመጥ ይጠይቃል።
ጎንደር ከተማ ላይ የፈሰሰ ደም አልነበረም። ህወሃትም ማድረግ ያለበት ይህንኑ ነው። ከተማዋ መቀሌ ከእነ ክብሯ አገራዊ፣ ሉላዊ ቅርስነቷ በሚቀጥል መልክ ህዝብም ሳይጎዳ ሊሆን የሚገባውን እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል ህዉሃት። ጀብዱ ካለ አግባቡ ከሆነ ያጠፋል። ይህ ከእግዚአብሄርም የሆነ ነው።
የካቲት እና ህወሃት።
ህወሃት ጫካ በነበረበት ጊዜ የካቲት የዘረፋ ወቅቱ ነበር። በወገራ አውራጃ፣ በስሜን አውራጃ፣ በሊቦ አውራጃ መጠነ ሰፊ ወረራ የሚያደርገው የካቲት ወር ነበር።
የጎንደር ገበሬው ዓመት ሙሉ የደከመበትን አዝመራ ሙልጭ አድርጎ ዘርፎ ስንቁን የሚከዝን የካቲት ወር ላይ ነው።
ሽምቅ ውጊያ መከራው ብዙ ነው። ህዝብን ይጎዳል። አማፂው በወቅታዊ በሚይዝባቸው ቦታዎች የመንግሥት ደጋፊ የሚባሉት ቤታቸው ይነዳል፣ ንብረታቸው ይወረሳል፣ ልጆቻቸው ይታፈናሉ።
መንግሥት ቦታውን ሲያስለቅቅም መንገድ መርታችኋል፣ አማፅያንን ተቀብላችኋል በሚል ያው መከረኛ ህዝብ በገፍ ይታሰራል፣ በገንዘብ ይቀጣል። 50 ዓመት ሙሉ። ይህ እንግዲህ በወሎ፣ በትግራይ፣ በኤርትራ፣ በጎንደር የገጠመ መከራ ነው። የሚያሳዝነው አሁንም መቀጠሉ ነው።
ማፍረስ።
ህወሃት የተፈጠረበት ነው። ዕድሉን ሲያገኝ የመጀመሪያ ተግባሩ የህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋም ማፍረስ ነበር። ሃኪም ቤት፣ ትምህርት ቤት፣ መንገድ፣ ድልድይ ማውደም የተልዕኮው እንብርት ነው። አፍራሽ ድርጅት ነው።
ሰሞኑን ወደ ትግራይ የሚያስገባውን ድልድይ ሠባበረው ሲባል ስሰማ አልደነቀኝም። ጋኔል የሠፈረበት ድርጅት መሆኑን በልጅነት አውቅ ነበር እና። ታገልኩ ለሚለው ህዝብ እንዲህ አድርጎ ያሳዬው።
ህም።
ይገርመኛል። አሁንም ላምነው ያልቻልኩት ቁም ነገር ለ27 ዓመት እንደምን ባለ አዚም ህወሃት አገር እንደመራ ነው።
ቦታዎች ሲለቀቁ መልሶ በሥነ - ልቦና ለማቋቋም ስንሄድ በአይነ ምድር ማሌሊት ያሸንፋል ብለው በሰባበሩት ግድግዳ፣ ሰሌዳ፣ ባወላለቁት የወንበር ወለል ፅፈው በዓይኔ በብሌኑ አይቻለሁኝ። ቀለሙ አይነ ምድር ነው።
ያ ዝልቦ መንፈስ ከጫካ አራዊትነት እንደምን ተፈጥሯዊ ሆኖ አገር መምራት፣ የአፍሪካ ሞዴል የሆነበት ሚስጢር እስከ አሁን አይገባኝም።
የG20 አባል አገራት በተፈጥሮ አዬር መዛባት ኮፐን ሃገን በዴንማርክ ባደረጉት ጉባኤ ላይ አፍሪካን ወክለው በታህሳስ 2008 የተገኙት ሄሮድስ መለስ ዜናዊ ነበሩ።
አውሮፓ ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ ነበር እኔም ፀጋዬ ድህረ ገፅን፣ ፀጋዬ ራዲዮን መንፈስ ይዤ ወት ብርቱካን ሚዲቅሳም ታስረው ነበር ያንም ሰንቄ ከቦታው ኮፐን ሃገን ዴንማርክ በዛ በረዶ ነበርኩኝ። አባይ ሚዲያም ነበር።
ባንዳንድ ሁኔታዎች ላይ ሚዛናዊ ዕይታ ሳቀርብ "ወያኔ ትመስይኛለሽ" ያለ ዝልቦ ገጥሞኛል። እኔ ያን ያህል ስታገል ጠቅላዩ የህወሃት የነፍስ አባት ነበሩ። እኔ ሥርጉተ ሥላሴ የህወሃት ሎሌ ሆኜ አላውቅም። ሎሌ የነበረውን ኦነጋዊ ኦህዴድን መጠዬቅ ነው።
እንሰሳዊነት።
የሆነ ሆኖ ህወሃት ባፈረሱት ቦታ የምታገኙት ምልክት እንሰሳዊ ነበር። መዳህኒቱን ደፍተው ቆርቆሮውን ይዘው ይሄዳሉ። ወንበሩን ስፖንጁን ነቅለው ይወስዳሉ። አገር ሲረከቡም አሁን ኦነጋዊ ኦህዴድ እንደሚያደርገው ባንኮችን ይዘርፋሉ፣ ከተሞችን ሙሉ ለሙሉ ያወድማሉ።
አውዳሚ አገር ገንቢ ሆኖ 27 ዓመት አራጦ ሲገዛ፣ ያም አልበቃ ብሎ "ጁንታ" በሚል ሴሉን ለማስቀጠል ሲወሰን ይህቺ አገር ጥቃት አውጪ እንደ ሌላት ፍንትው ብሎ ይታያል።
መርዝ መወገድ እንጂ ጥገና አያስፈልገውም። ለነገሩ መርዝነት ከዋጠ ድውይ መንፈስ ይህን መጠበቅ ጅልነት ነው። የእባብ መርዝ ታቅፎ ነፃነት መጠበቅም ብላሽነት ነው።
ይገርመኝ የነበረው ያን ጊዜ።
አሁንም እንዳይደገም እሰጋለሁ። አውሮፕላን ለሌላቸው ሻብያወህወሃት አዬር መቃወሚያ አብሮ ይዘምት ነበር። ከባድ መሳሪያውም እንዲሁ።
እነሱ እኮ ሽምቅ ተዋጊዎች ነው የነበሩት። እዬወሰደ ደርግ መሳሪያ ያስረክባቸው ነበር። የእርስ በርስ ጦርነት መከራው ዝልቅ ነው እምለውም ለዚህ ነው።
ለሽምቅ ውጊያ የኮንቤክሽናል የውጊያ ጥበብ ደርግን ካሰናበተው ቁልቁል መከራ ሚስጢሩ ነበር። አሁንም ኦነግን ቤተ - መንግሥት አስቀምጦ የኦነግ ክንፍ ጋር የሚደረገው ውጊያ በመሰሉ ቀጥሏል።
ህወሃትም የሽምቅ ውጊያ ያደገበት ስለሆነ እንኳንስ ሴሉን አስቀጥሎ ባይቀጥልም መከራው ይቀጥላል። ደጋግሜም እላለሁ የእርስ በርስ ውጊያ መከራው ይኽ ነው። ዓለማችን ሥነ - ባህሪን መዝግቦ ከግንባር የሚለጥፍ መሳሪያ ገና አልፈለሰመችም።
ማን ምን እንደ ሆን አይታወቅም። ተከድኖ የተቀመጠው ኦነጋዊ ኦህዴድ፣ የሱማሌ ነፃ አውጬም ሌላ የተጠመደ ፈንጅ አለበት።
ለዛውም በዞግ ፖለቲካ ሲሰላ መከራው ዝልቅ ድሉም የወረት ይሆናል። በህሊና አቅም ብልጫ ካልመጣ በስተቀር። የኦዳ ሥርዕዎ መንግሥት ዘመኑን የሚመጥን ሰዋዊ፣ ተፈጥሯዊ የአመራር ሥልጣኔ አላዬሁበትም። ዕለታዊ ነው። እሳት በማጥፋት፣ በመከላከል ብቻ የተጠመደ ኩርፍርፍ ነው።
ቁንጥንጥ ነው። ዝልግልግ ነው። ትዕቢተኛ ነው። ድንገቴ ያበዛል። በትራጀዲ የሰመጠ ነው። ክህደት መርኹ ነው። መስቀኛ ነው። ቀረርቶ ያበዛል። በኮፒራይት ሽሚያ የተጠመደ ነው። ስክነት በእጅጉ ያንሰዋል። ጭካኔ መንገዱ ነው። ሰውኛ ጠረን አይቸበት አላውቅም።
የጎንደር ከበባ ለነገም ያሰጋኛል።
አሁንም በማንም ይሁን በማንም የጎንደር ቀጣይ ዕድል ያሰገኛል። በጠቅላዩ ከሁለት ዓመት በላይ በዘለቀው የሥልጣን ዘመን በሹመት፣ ቦታ በመስጠት፣ ቁልፍ ቦታ በማስያዝ ያዬሁት ቁምነገር የለም።
በማሰር፣ በማዋከብ፣ በማንገላታት፣ ጀግንነቱን በመድፈን፣ በመረሸን በጎንደር ላይ አፓርታይዳዊ ተግባር ፈፅማዋል ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ።
ወደፊትም በተለይ በአማራ ቀጠና መሰሉ ከበባ በሥነ - ልቦና ይቀራል ብዬ አላስብም። ስጋትም አለብኝ። የኦዳ ሥርዕዎ መንግሥትንም ፈፅሞ አላምነውም። የመንፈስ ትጥቄንም አልፈታም። በተጠንቀቅ ማንኛውንም እንቅስቃሴ በንቃት እና በአትኩሮት እከታተለዋለሁ።
ለአማራ ልዕልና የሰናፍጭ ቅንጣት ታክል ከጠቅላዩም ከሎሌውም ብአዴን አልጠብቅም።
አቅም ነው የሚያስከብር። አቅም ደግሞ በሞቅታ በስካር ለአራጅ ሥጦታ አይሰጥም። ለካህዲ የአቅም ጉርሻ አያስፈልግም። ፈፅሞ። በዞግ ወይንም በሌላ ሱስ የተጠመዱ ከፍ እና ዝቅ ይበሉ። ነፍሴ የሞጋሳ ጥምቀትን ትጠዬፋለች።
ወልቃይትወጠገዴ።
የወልቃይትጠገዴ ጉዳይ ዘመን ተሻጋሪ ነው። በአግባቡ ካልተፈታ ፈንጅ ነው። እሳተ ጎመራ ነው። እትብት በገብያ ህግ አይገዛም፣ አይሸጥም አይለወጥም።
ከህወሃት አፈንግጠው ጎንደርን ለማዳን የተጉት ጀግኖች ደርግ ሲረታ የጫካ ትግላቸውን ቀጠሉ። እናም የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባርን ፈጠሩ።
የዚህ ግንባር የውስጥ አመክንዮ የተከዜ የተፈጥሮ ደንበር መጣሱ ነበር። አሳዛኙ ነገር በተገባው ልክ የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር ለድል ሊበቃ ስላልቻለ መድፍ እዬረገጠ የጎንደር እና የጎጃም የአማራ ህዝብ ህወሃትን ሸኜ።
እኛም ተጋድለናል። የበላበትን ወጪት ሰባሪ ስለሆነ ህወሃት። ጎንደርን መነጠረ፣ ቀጠቀጠ፣ ቀጣ። ነገም ኦዳ መሰሉን ይከውናል። ስለዚህ በልክ መጥኖ መራመድ ይገባል። ዛሬም ለካቴና የተሰጡት የአማራ ልጆች፣ የተዋህዶ ፅላቶች ናቸው።
ህወሃትን ሸኝቶም አቅመ ቢሱ የኦዳ ሥርዕዎ መንግሥት በቅጡ ሊመራ ስላልቻለ ህወሃት እንሆ ታበዬም ገነገነ። በወልቃይት፣ በጠገዴ፣ በራያ የታሠሩትን ማስፈታት እንኳን አልተቻለም። ተፈናቃዮች አዲስ አበባ ድረስ ሄደው ሰሚ አላገኙም። ማን አቅርቧቸው።
የሚገርመው ዬኦዳ መሳፍንት ሲታበይ ባጅቶ ፈጣሪ በጥበቡ ከአማራ እጅ ጣላቸው። እጃቸውን አወጣ። ከውርዴት ታደጋቸው። ካህዲዎች ስለሆኑ ነገም ይከዱታል። ከእግዚአብሄር ከአላህ ሰይፍ ግን የሚያመልጥ የለም።
ህም። አሁንም እሱን ገኖ የወጣውን ህወሃትን ለመሥበር የጎንደር አማራ ተገበረ።
የራያን እምዘለው መሠረታዊ የተጋድሎው ነገር እንደ ወልቃይትጠገዴ ባልመሆኑ ብቻ ሳይሆን ከድል ዋዜማ ጋር ጎልቶ የመጣ ተጋድሎ ስለሆነ በቂ መረጃ የለኝም። የግፋ ደረጃም መመጣጠኑን በውነቱ አላውቅም።
ወልቃይትወጠገዴ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ጆኖሳይድ የተፈፀመበት፣ የፋሺዝም ዴሞግራፊ ዕውን የሆነበት፣ መቅድመ ሥፍራ ነው።
እዛው ጎንደር ተውልጄ ማደጌ፣ ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦቼም ተወላጆች ስለሆኑ፣ የፖለቲካ ቋሚ ሠራተኛም ስለነበርኩ ከሥሩ የሆነውን ነገር ሁሉ በስማ በለው ሳይሆን እኔ እራሴ ለአመክንዮው መስታውት ነኝ። አውቀዋለሁኝ። ስለዚህም አፌን ሞልቼ መናገር እችላለሁኝ።
ሙርቅርቁ ዬኦዳ ሥርዕዎ መንግሥት።
ሙርቅርቁ ዬኦዳ ሥርዕዎ መንግሥት አፍሪካን ተመኝቶ፣እንደ ተዝረከረከ በህወሃት ሙሉ መሰናዶ ጥቃት ሲሰነዘረበት የታደገው ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ ያሳደደው ዕውቅና የነሳው የአማራ ሙሉዑ፣ ብቁ፣ ሥነ - ልቦና ነው።
ልዙ የኦዳ ሥርዕዎ መንግሥት ጥቃቱን መክቶ ገዢ መሬቱን የተቆጣጠረው በአማራ ደም ነው። ቴሌቪዥን ላይ እዬተመጣ የሚፎገላው ያንጠራራው ሥነ - ልቦና ስለነኮተ ነው። መግለጫ የሚሰጡት ያው እነሱው ናቸውና ብጄ ቡልቲ ሆኑ ጄኒራል ብርኃኑ ጁላ።
የሆነ ሆኖ የአማራ ልጅ የሚሞትለት ዓላማ ግብ አለው። በእጁ ባበጃት አገሩ ባይተዋር ሆኖ እዬተቀጠቀጠ ነው። ዴሞግራፊ እዬተሠራበት ነው።
መፍትሄው እርስቱን ማስመለስ ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ መፍትሄ የለም። እርስቱን አስመልሶ፣ ባለቤትነቱን አረጋግጦ እንደ ቀደመው ይትብኃል ከዬትኛውም ወገኑ ጋር ተቻችሎ በፍቅር መኖር ይችላል።
ይህን ሁሉ መከራ ተሸክሞ እኮ ነው በጭምትነት፣ በማስተዋል እዬተራመደ የሚገኜው አማራ። ሲበዛ ግን ሲከር ይበጠሳል፣ ሲሞላም ይፈሳል። ነገ እንሰማለን የጨረቃ ቤቱ ብልፅግና ድል አደረገ ተብሎ ነጋሪት እንደሚጎሰመው። ርዕሰ ብሄሯም እንደሚተርኩልን።
ምክትልም፣ ዋናም ኢታማጆር ሹም ተሁኖ መግለጫው ፍሰቱን እያዬን በአንድ ልሳን እያዬን ነው። ምክትልም ሳሉ ጄኒራል ብርኃኑ፣ ዋናም ሆነው እሳቸው፣ ብጄ ቡልቲ፣ ሌላም ጄ ባጫ ደበሌ ይህ ሁሉ ድርድር በሰበረን ቦታ ሰብርነት ትርክት ወለምታ እንዳይገጥመው ጋራጅ ነው።
ከአቶ ሬድዋን ሁሴን ጋር ቢመጣም፣ ብቻ ቢኮንም መሬት ላይ ጨዋታውን እናስተውላለን።
ውራጅ።
የአማራ ህዝብ ማንነቱን ተውሶት አያውቅም። ስለዚህ ሙርቅርቁ ኦዳ ልቡን የገጠመላቸው የህወሃት ቅሪት አካል ሹመኞች የሚሰጡት ቃለ ምህዳን ተሸክሞት ይዙር። አቋቋምኩት ካለው ኮሚሽንም የአማራ ልጅ ፍትህ አይጠብቅም።
አማራ የለም በማለት በማንነት ቀውስ ከሚዳክሩት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ሆነ አዚፋ የኮሚሽኑ ስብስብ ቅንጣት ፍርፋሪ ፍትህ አይጠብቅም። ስለመኖሩም ኮሚሽኑ ትዝ ብሎኝ አያውቅም።
በበላዩ ትናንት ለደቡብ ዛሬ ለሱማሌ አቶ አባ ዱላ የተመደቡት ጠቅላዩ ለሥም ብቻ የጎለቱት ጉልት ስለሆነ ነው። የሲዳማው ህዝበ ውሳኔም በኦነጉ የጠቅላይ ሚር ጽህፈት ቤት ቁርጥ ውሳኔ ነው የተመራው።
የወልቃይትወጠገዴ ጉዳይ እሳተ ጎመራ ነው። 40-50 ዓመት ግብር የተከፈለበት። የሰው፣ የትሩፋት፣ የታሪክ፣ የቅርስ ውርስ፣ የኢኮኖሚ።
እንዲያውም ህወሃት በዚህ ቦታ ለፈፀመው ግፍ፣ ለዘረፈው ንብረት ድርብ ካሳ ይገባዋል ይህ ህዝብ። የኢፈርት መሠረት አንጡራ ጥሪቱ ነጭ ወርቃችን ነው።
ሦስቱ ነጭ ወርቆች።
ሦስቱ ነጭ ወርቆች ደበር፣ ሰሊጥ እና ጥጥ ናቸው። ሰሊጥ እና ጥጥ ካሽክሮፕ ናቸው። የውጭ ምንዛሬ አስገኝ። ሦስቱም ነጭ ናቸው።
ወደአርባ።
ደበር የማሽላ ዓይነት ነው። እንደ ጤፍ የሚቃጣው የማሽላ ዝርያ ነው። ወድአርባ ታምረኛ የማሽላ ዝርያ ነው። ማሽላው ከአፍንጫው ላይ ቀይ አለበት። ከደበር ደንበል ያለ ሲሆን ተዘርቶ ለመብል የሚደርሰው በአርባ ቀን ውስጥ ነው።
ኢትዮጵያ ወደአርባን የመሰለ የእህል ዘር አምራች ሆና መራቧ የመሪ ችግር ነው፣ እንጂ ወደ አርባ መሪ ቢያገኝ እራህብን ባናቱ ይዘቀዝቀዋል ኢትዮጵያ ምድር ላይ።
ወድአርባ የተባለውም በአርባ ቀን የሚደርስ ልጅ ለማለት ነው። ከሆድም ብዙ አይቆይም፣ አይከብድም፣ ቀላል የምግብ አይነት ነው። ለቆሎ፣ ለዳቦ፣ ለጠላ እህል፣ ለንፍሮ፣ ለእንጀራ ይሆናል። ሁለገብ ነው። ደበርም እንዲሁ።
መፍትሄ።
ህገ - መንግሥት መሰረዝ።
በአጤ ኃይለስላሴ በነበረው መልክ ወደ ክፍለ አገራት መመለስ።
ፌድራሊዝሙን በክፍለ አገር ማደራጀት።
የህወሃትወኦነግ መንፈስ ያረፈባቸውን ሰነዶች መሰረዝ።
የአዕምሮ ቡርሽ ትምህርት ቤት መክፈት። ከጠቅላዩ ጀምሮ ድውይ ነው መንፈሱ። ሰው መሆን የተሳነው።
ክወና።
የወልቃይትወጠገዴ ጉዳይ ፖለቲካዊ ውሳኔ ካልተሰጠው የኦዳ ሥርዕዎ መንግሥት ፈንጅ በራሱ ላይ እንደ አጠመደ ይቁጠረው።
የህወሃት አከርካሪም የሚሰበረው ይህ እልባት ሲያገኝ ብቻ ይሆናል። ዕብጠቱም፣ መታበዩም የሚደቀው ፖለቲካሊ የወልቃይት፣ የጠገዴ፣ የራያ ጉዳይ በአግባቡ አስቸኳይ መፍትሄ ከተሰጠው ብቻ ነው።
የዛሬ ቁልምጫ የነገ እሳተ ጎመራ ነው። ዬህውሃት መንፈስ እንዲህ በሰው ለውጥ ይወገዳል ብሎ ማሰብ ጅልነት ነው። ቂመኛ ድርጅት ነው።
ግን ግን ግርባው ብአዴን አዲሱ አለቃውን ዶር ሙሉ ነጋን መቼ ነው ካባ የሚያለብሰው? ቀይ ምንጣፍ አንጥፎስ ጉንብስ ቀና የሚለውስ መቼ ነው? የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱስ መሰናዶ ለመቼ አስቦት ይሆን ልሙጡ፣ ስልባቦቱ፣ ጣፊያው ብአዴን? እንደ ዕቃ ከአንዱ ጆንያ ወደ ሌላው ኬሻ መገላበጥ መቼስ አይሰለቸው። አይመረው።
ጦርነት ሆኖ እንጂ ጊዚያዊ ክልላዊ መንግሥት ሊቋቋም የሚገባውስ አማራ ክልል ነበር።
ምራቂ።
ይህ የወንዝ ካርታ የሚገኘው በወልቃይትወጠገዴ ነው። በውርስ ቅርስ ይያዝ ዘንድ ጠቅላዩ ስለ ሚኒልክ ቤተ - መንግሥት ጥያቄ ጠዬቅኽኝ ብለው፣ አቅማቸውን አቅርበው ሲሰልሉት የነበረውን ወጣት ሊቅ በቀላጤ ሳያባርሯቸው ለአቶ ዮናስ ደስታ በግል አንድ ማስተዋሻ ፅፌ ነበር። እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
የኔዎቹ መሸቢያ ቀን እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።