ከዶር አብይ አህመድ የውስጥ ዕንባ "እኔ ብታፈርሱኝ ምን ጥቅም አለው?“


„ውዝፍ እና ክምር አምጥታችሁ ጭናችሁብኝ እኔ ብታፈርሱኝ 

ምን ጥቅም አለው?“  „ባልቅላችሁ ፍጻሜዬ ቢሆን ምን ትጠቀማላችሁ።“



                 "ጥበብ በቀደሙ ሰዎች ዘንድ ተመረመረች።" (መጽሐፈ ሲራክ ምእራፍ ቁ፴፱ ጥር ፩)
  • መነሻ።

/ሚንስትር አብይ ዛሬ በሀዋሳ ያደረጉት አስገራሚ ንግግር Dr. Abiy Ahmed
ለማጥናት ጊዜ ያስፈልገኛል ገና እኮ ከተመረጥኩ እኮ ሁለት ወሬ ነው። !! ለእኔስ ጊዜ አያስፈልገኝም?! ውዝፍ እና ክምር አምጥታችሁ ጭናችሁብኝ እኔ ብታፈርሱኝ ምን ጥቅም አለው?“ ማልቀስ አይገልጸውም። ባለፈውም ኦቦ ለማ መገርሳ መሰሉን ተናግረው ነበር። እነሱ ታግለው ነፃነቱን ያስከበሩለት ሁሉ ሜዳ አልበቃው ብሎ ሲያብጠለጥላቸው ... ህም!

heger Werewoch - “40 ነፍሶች ይቅርታ ማድረግ በሰው ልጆችም ሆነ በፈጣሪ ፊት ጥሩ ስራ ነው” 
- የሸገር ወሬዎች
  • ውዝፍ እና ክምር አምጥታችሁ ጭናችሁብኝ እኔ ብታፈርሱኝ ምን ጥቅም አለው?“

ልብ ይሰነጥቃል። ህሊናን ከሁለት ይገምሳል። እኔ እሰከ ዛሬ የኖርኩት ይበቃኛል። ትግሌም የኢትዮጵያ እናቶች የ43 ዓመት ዕንባ እንዲደርቅ ነበር። አሁን ኢትዮጵያ ብቁ ሙሴ አግኝታለች። እናም ዕድሜዬ የቀረኝ ካለ ፈጣሪዬ ለዶር አብይ አህመድ ቢሰጥልኝ ምኞቴ ነው። እናቴንም ቢሆን ቀኑን ሁኔታውን ካገኙ አይዞሽ ይሉልኛል። እሳቸው ካዮዋት ይበቃኛል። እባክህን አምላኬ የእኔን ዕድሜ ለዚህ ቅዱስ ሸልምልኝ እና የማቱሳለን ዕድሜ ስጥልኝ። እባክህን አዶናይ!

አይዘዎት! አባ ቅንዬ ፈጣሪ / አላህ አለ፤ ድንግል አለች፤ ጻድቃን ሰማዕታት አሉ፤ እኛ ብቻ ሳንሆን ሰው አጀንዳቸው የሆኑ የዓለም ንጹሃን ሁሉ አብረዎት ነው ያሉት። የኬኒያ ህዝብ፤ የግብጽ ህዝብ፤ የኤርትራ ህዝብ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ፤ የሱዳን ህዝብ፤ የኡጋንዳ ህዝብ፤ የሳውዲ፤ የአረብ ኢምሪቶች ህዝብ እና መንግሥት፤ የተባባሩት መንግሥታት የሰብዕዊ መብት አስከባሪ ድርጅት መንፈሳቸው ሁሉ ከእርስዎ ጋር ነው። ሌሎችም ልጠቅሳቸው እማልሻቸው ለዛሬው አሉለዎት በጥሞና እዬተከታተሉዎት ነው ክፉዎችንም እያስተዋሉ ነው። 
  • አይዞዎት።

አዎን የተፈለገው ይሄው ውስጠወትን ለማቁሰል ነው። ግን ንፁሃን ጸሎት ላይ ናቸው። ጎንደር በጸሎት መትጋቱን ሰምቻለሁኝ። የተገፋ ማህበረሰብ ስለሆነም ዕድሉን እንደ 12ቱ ሐዋርያት በጸሎት፤ በሱባኤ ነው የተቀበለው። እኔም ኮርቸበታለሁኝ።

እርግጥ ነው ያው ሆደ ባሻ ስለሆንኩኝ እያለቀስኩኝ ነው ያደመጥኩት። ትርትር ብለው ቢቀሩ ነው ምኞቱ። 40 ዓመት የኖረች ዓይኗን የገረዳት ፍጡር አንድ ቀን እደሪ ብትባል እንደምን ብዬ እንዳለችው ነው። የሲዳማ ጥያቄ፤ የጉራጌ ጥያቄ፤ የወላይታ ጥያቄ የደቡብ መንግሥትን ማዕከል አድርጎ ያለመው ማን ነው? ስለምንስ አሁን ተፈለገ። አያስታውሱንም ኦቦ ለማ መግርሳ እና ዶር አብይ አህመድ መስክር ካልሆኑ እኮ የ አንድ ሰሞን ቅልጥ ያለ አጀንዳ ነበር። ወዮ የ ኦቦ በቀለ ገርባ ዓይን አንድ ነገር ይሁንናም ፉከራ ነበር፤ እከሌ የሚባል አርበኛ ካልተፈታ፤ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ካልተናሳ ምን አልተባለ አለ እና። አሁን አጀንዳው አለቀ። አጀንዳው ደቀቀ። ስለዚህ ታላመ ደቡብ ላይም ተሳካ። አሁን ቀሪው ደግሞ አፋር በጅ ካለ ሙከራ ይኖራል። ጥርስ አልባው አንበሳ ህልፈቱን ለመቀበል መንገዳገዱ የተገባ ነው። እንደ ባሎን በተነፋ የውሸት ከረጢት ገማናው አዬር ላይ አይሆኑ ስለሆነ።
  • ላመስግነህ አዶናይ!

በሌላ በኩል ደግሞ ተመስገን ልብል እስኪ። እግዚአብሄር ይመስገን ልብል እስኪ። መጀመሪያ ልቡ ውልቅ እስኪል ድረስ በዶር. አብይ አህመድ ላይ ሥራ ፈቶ ሲያባዝት የከረመው ልግመኛው ፖለቲከኛ እና ሰውኛን ማእከሉ ያላደረገው የወረቀት ጣዖታኛ ሚዲያ ሁሉ አሁን ደግሞ ወደ ቀልቡ ተመልሶ „ጀግናዬ“ ለማለት እዬዳዳው ነው። „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ወንጀል ሆኖ የአቋም ለውጥ እዬተባለ ሲብጠለጠል እንዳልነበረ ሁሉ አሁን አገር ምድሩ እሱ ሆኗል። ውስጡ ኩምትርትር ቢልም ... ቢተክንም ... 

የDW አንጋፋ እና እኛም ዓይናችን የምንለው ተናፋቂ ጋዜጠኛ አቶ ነጋሽ መሐመድ ከፖለቲካኛው ጃዋር መሐመድ እና ከዶር ደረሰ ጌታቸው ጋር በነበረው ቆይታ „ተለጠጠ“ ሲል ሳዳምጠው ምነው የጤና ብዬ ነበር። አንድ ጹሑፌ ላይ ለበስ አድርጌ አቅርቤው ነበር።

ዛሬ የዓለም ዕውቅ ሚዲያዎች፤ መጋዚኖች፤ የኢትዮጵውያን ብቻ ሳይሆን የኤርትራውያን ሚደያዎች ሳይቀሩ የዚህን ቅዱስ ሰው መንፈስ አድንቀው እዬተናገሩ እዬጻፉም ነው። የተባባሩት መንግሥታት ልዑክ ሳይቀር በሚገርም ቋንቋ እና አድናቆት በዓለም አደባባይ መስክረውታል። ኢትዮጵያ ናሙና ሆና ሌሎች አገሮች ደግሞ ተወቃሽ ሆናዋል። እኛ ዓለምዓቀፍ ሚደያ ተመቸን ብለን ስንሸነሽነው የነበረው መሠረተ ቢስ ክስ ገመና በዓለሙ ማህበር አድናቆቱ ተቸረው። ግን ሳተናው ምን ተስምቶት ይሆን? አንድ እንደ ወልዴ በድጋፍ ጸንቶ የቆመ የነበረ ሚደያ ስለነበር። 
Ethiopia: የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ እየታየ ያለዉን ለዉጥ አደነቀ።

ነገ አብይ የእኔ ነው ያልኩት መርህ ሁሉም እንደሚለው አልጠራጠረም። አብይ ኬኛም ያልኩት እንዲሁ። አብይ የኢትዮጵያ ህይወት ያልኩትም እንዲሁ … ለማውያንም የሥርጉተ ብቻ ሳይሆን የሚሊዮኖች ድምጽ ይሆናል። ጠብቁት።

ምስጋና ይግባው እና ትናንት ባተሌው ሳታናው ዕጣ ነፍሱን ሲያስተናግደው የነበረው ነገረ አብይ አሁን የሁሉም አጀንዳ ሆኗል። ሚደያው ሁሉ የተፈራው ደረሰ እና የሙሴውን ምስል ትንግርት እዬዘከረ ነው። ብቻ እኔ ፈሪ ስለሆንኩኝ ስጋት አለብኝ። ራሱ የቅዳሜው የምስጋና ሰልፍ በሰላም እስኪጠናቀቅ ድረስ እንቅልፍ የለም። ሸረኛው ወያኔ ሃርነት ብቻ አይደለም። ግራ ሁል ጊዜም ግራ ነው። ከሰውኛ የተጣለ ወረቅትኛ ስለሆነ። ለዚህ ነው እኔ ምቾት ያልሰጠኝ። ማን ምን እንደሆን አይታወቀም። አንድ አማሽ ፖለቲካኛ እኮ ነው ለረጅም አመት እንኩሮ ያደረገን። አንድ የምህረት ሰው ሲመጣ ደግሞ ጤናችን ሰጠኝ። አሁን ያ የእፉኝት መንፈስ ሊተኛ አይቻለውም። የተለመደ ነው ሲረገዝ አባቱን ሲወለድ እናቱን መግደሉ ...  
  • ልግመኛው የኢትዮጵያ ፖለቲካ። 

ሴት ተሁኖ የ  ኢትዮጵያ እናቶች መንፈሳቸው አረፈ ተብሎ አይቸግርም ለማብጠልጠል። ሴትነት እናትነት ነው። እናትንት ደግሞ ትልቅ የመክሊት ሚስጢር ነው። ሴቶች አናባያቸውን ይታገላሉ። ይገርማል። አርቆ ማዬት በእጅጉ የሚሳነው ልገመኛው የኢትዮጵያ ፖለቲካኛ እና ሚዲያ ደም ጠማኝ ሆኖ ግፋ ህውከት ሲል ካራርሞ አሁን በደቡብ እንዳሰበው „በጨንበለል ባዕል“ ደስታን በዕንባ በቀዬረበት ሰዓት፤ ለዛውም በረመዳን፤ ወያኔን ነው እያለ እሱም ከሳሽ ሆነ አርፏል። የወያኔ እጅ አለበት፤ ለዚህ ምንም ጥጥር የለውም። የሌላም እጅ አለበት ይህ ደግሞ የግልጽነት ዘመን ነው እና ተሸፍኖ ተሸጎጦ መታለፍ የለበትም። የቆጨው፤ የነደደው፤ የተቃጣለው መንፈስ ሲከረኩሩ የከራረመው ቅናት አደባባይ ወጥቶ ፊት ለፊት ገጥሟል። ግን የእግዚአብሄርን መንፈስ አሸንፎ ያሰበውን አቋራጭ ክብር እና ልዕልና አያገኛትም። ስለምን? ህዝብ የሚያውቀውን ስለሚያውቅ። አሁን ደግሞ የትነበርክ  መሪ ማለት ምን ማለት እንደሆነ በስክነት፤ በርጋት እያስተማረው ነውና።

ህዝብን ለህውከት የሚያነሳሱ፤ የተጀመረው ለውጥ አርኪ አይደለም፤ ሥር ነቀል ለውጥ ያለ ሁሉ፤ ጥያቄያዎችን ለዴሞክራሲ ነው ሲል የነበረው ሁሉ አደፍራሽ መልዕክቶችን በተገኘው ሚዲያ ሁሉ ሲያናፍስ፤ ሲበትን የነበረው ሁሉ ለደቡቡ ግጭት ተጠያቂ ነው። ተጠያቂነት እኮ ሃላፊነት መሰማት ማለት ነው። ሃላፊነት ሳይሰማን የተገኘውን ተስፋ ጨፍልቆ በመደዴ ፖለቲካ መረጋገጥም ያስጠይቃል። ከ43 ዓመት በኋዋላ የኢትዮጵያ እናቶች ትንፋሽ አገኙ ተብሎ የነበረው ርብርብ እኮ ዘመን ይፍረደው።

የደቡብ ክልሉ ከዬት እና ከእነማን ጋር እንደሚያያዝ እኮ ባለቅኔነትን አይጠይቅም። ምን በመሰለ ሁኔታ ብሄራዊ ቀኔ ብሎ በተቀበለ ፍቅር በሆነ ህዝብ፤ በሆታ እና በእልልታ የተቀበለ ህዝብ በማግሥቱ ይህን የመልካምነት ድባብ በጥቁር ጥላሸት የቀባው ማን ነው? የተባበሩት ናቸው።  ምንጩ ለምን ከማን ተነሳ? ህሊና አለን። ልብ አለን። ምንጊዜም በማመስ እና በማተራመስ ሥልጣን የሚያባዝናቸው አፉኝቶች ለማህበራዊ ኑሮም ሳንክ ናቸው። የሰው ሞት ጉዳያቸው አይደለም። የሰው እልቂት ምናቸውም አይደለም። ቆሼም እኮ ለዚህ መሰል ዓላማ የታሰበ ነበር። ስለዚህ ህዝብ ለማያውቀው ዓላማ አጋፋሪ እንዳይሆን መጠንቀቅ አለበት። ዛሬ እንዲህ ያለ የኤዶም ገነት ነፋሻማ አዬር መዳፉ ላይ አለ፤ ስለዚህ መላ የኢትዮጰያ ህዝብ አደብ መግዛት አለበት። የማያውቀው አገር አይናፍቀው። 

ክፉዎች እነሱ ብቻ በሬሳ ላይ ተረማምደው የቤተ መንግሥትን ቁልፍ ይረከቡ። ቢችሉ ማንም ይሰዋ ማንም ጉዳያቸው አልነበረም። ከዚህ ቀደም እኮ ብዙዎች ተሰውተዋል የተጎዳ ህዝብ ነው። ስለዚህ ህዝብ እንኳንስ ይህን የመሰለ ቅዱስ ከሰማይ ዱብ ሲልለት ቀርቶ የተሻለ ነገር ከመጣ የፈጣሪ ስለሆነ ብሎ ጸጋውን አክብሮ፤ ቢችል ሱባኤ ገብቶ ማብቀል፤ ማጽደቅ አለበት ተስፋውን።

ክፉዎች ቢሰጣቸውም አቅሙ የላቸውም። መሪነት መሪ ነኝ ስላልክ ብቻ ሳይሆን አዛኝነትንም ነው፤ ርህርህናም ነው፤ ጥበብም ነው። ክህሎትም ነው። መሪነት ጠብታ የደም፤ የሰላም ሁከትን መጠዬፍን ይጠይቃል። ሽግግሩ እኮ ከታሪክ በላይ ነውሂደቱ እራሱ እኮ በሥርዓት ትምህርት ተቀርፆ መጸሐፍ ተዘጋጅቶለት ልጆች እዬተማሩ ሊያድጉበት የሚገባ የመርህ ጉዳይ ነው። አሁን እኮ የፍቅር ተፈጥሮ ሥርዓተ ትምህርት እኮ ነው በሙሴው የተከፈተው።


የአንድ የፖለቲካ ድርጅትን የሥ/ አስፈጻሚን መንፈስ አንድ አድርጎ መጓዝ እንኳን አልተቻለም። ሥ/ አሰፈጻሚው ስከነትን፤ አደበን ምራቁን መዋጥን አላስተማሯቸውም። ስለዚህም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ክፍተት ሲፈጠር ነው የሚታዬው። ስለምን መሪ የላቸውማ። የነጻነት እስረኛ በብዛት ሲፈታ እኛ በሁሉም ቦታ አለን እኮ ነው የተባለው? ይህ ርህራሄ ነውን? ይህ ስለሰው መጨነቅ ነውን? ለማ ገዱ አብይ አንባቸው እና ሌሎቹም ቅኖች ተፋልመው የተገኘው ዕድል እንደ ገና ቁርሾ፤ እልህ ተባይ እንዲያፈራ? እነሱማ በአደባባይ በወኪላቸው በወ/ሮ ሙለ ገ/ እግዚአብሄር አማካኝነት ጠየቁ እኮ። ወ/ሮዋ ዛሬ ብቻ ሳይሆን የካቢኔ ሽግሽጉንም ተቃውመው ቀርበው ነበር። ለዛ ነው እኛ ማዳበሪያ የሆነው። ለዛ መንፈስ ነው እኛ ስንቅ እያቀበልን ያለነው።

አንተ እንዴት ከህዝብ የሚያራርቅ ጹሑፍ በተጨማሪነት ትበትናለህ? እንዴትስ ሰው ከእስር ሲለቀቅ እያለሁበት ስለምን ለቀቅካቸው ብለህ ትሟገታለህ? ዲስፕሊን የለም። እንዲያው ለአንድ ቀን ሥልጣኑ ቢሰጥ አገር ትዘቀዘቃለች እንኳንስ ይሄን ሁሉ መከራ መሸከም ቀርቶ። 100 ሚሊዮን ብሄረሰብ ያላት አገር ነው ያለችን። 80 ነው ያላት የሚባለው ውሸት ነው። ኢትዮጵያ ያላት 100 ሚሊዮን ብሄር ብሄረሰብ ነው። እንቅጩ ይሄው ነው። ደንቢ ዶሎ፤ የደምቢዶሎ ንጉሥ ነው ማዬት የሚሻው፤ ሌላውም እንዲሁ፤ ፈተናው ይሄው ነው፤ የሰሞኑ ግርግር ይሄው ነው። የተጠበቀ ተስፋ ነበር ቀለጠ እናም ሴራ ተቀመረ። ሊሂቁም ከዚህ ያለፈ አቅም የለውም።

ለመሆኑ ከወያኔ ሃርነት ትግራይ የተሻለው ማን ነው? ቢያገኙን ሰብስበው ያነዱናል። ብዕራችን ተፈርቶ አይደለም ታግተን የምኖረው … ስንት መከራ ነው ያሳለፍኩት እኔ እራሴ? ስንት ፍዳ ነው እኔ ያሳለፍኩት? እዛ ያለው የተቀናጣ ጋዜጠኛ አዲስ ዓይን አይቶ ሌላ ገጽ ናፈቀኝ ይለናል። ስንቱ ይነገራል። ሆድ ይፍጀው። 

ሥርዓተ ዓልበኝነት ነው ያለው። ሥርዓት ዓልበኛ መንፈስ ደግሞ ለእኛም ለቀጠናውም ለአህጉሩም፤ ለዓለሙም አይመጥንም። ቢመጥንማ ምኞታችን ነበር። ግን ሥም ብቻውን አለመሆኑን በሂደት ከሥሩ ተጥንቷል። መሪነት መክሊትም ነው። ተሰጥዖ። ከዛ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ያባለን? ከዚህስ ስደተኛውን በፍቅር ለመምራት እንደ ሃሳባችን እንደንኖር ስለምን አልተፈቀደም? አቅሙ የለም። ብልህነቱ የለም። ጥበቡ የለም። ሁሉም የለም። መካሪ እንኳን የለም። የቀደሙት እረኛ ምን አለ ብለው ያዳምጠሉ፤ የዛሬዎቹ ቤተ መንግሥት ምን አለ ነው? ያነንም ለመልካምነት ቢሆን ይሻል በነበረ፤ እንደ እብድ እኮ ነው ሚዲያ ላይ የሚያደርጋቸው። የእጅ እንቅስቃሴያቸው ሁሉ እኮ ዛር ያለበት ነው የሚመስለው። 
   
የለውጥ ፈላጊው ዕውን ለኢትዮጵያ እናቶች ዕንባ ተቆርቋሪ ቢሆን ኖሮ እኮ ይህን መሰል መሪ ቢያንስ  ለእጩነት ከቀረበ በኋዋላ በዛ ላይ ተግቶ በአጀንዳ መሥራት፤ ከተመረጠ በኋዋላም እግር እግር እዬተከታተሉ ሰባራ ሰንጠራን እዬፈለጉ መንፈስን በሰላ ፋስ ከመተርተር መንገዱን በሚያጠናከሩ ማህበረ ደራጎን በማያደክሙ ተግባራት መትጋት ሲገባ ጫና፤ የውስጥ ሰላም ማወክ አና ብሎ ተያዘ። በዓለም አቀፍ ሚዲያ ሳይቀር ለዛ ዕድል ያበቃ ነፃነትን ያጎናጸፈ መንፈስ ታረደ።
  • ሰው።

አሁን ደግሞ እኔ ሐዋራያ ነበርኩኝ ብሎ በዬጓዳው ጉድጓዱ „መደመር“ ይለናል። ብቻ መልካሙ ነገር ህሊና ስላለ ጨዋው የኢትዮጵያ ህዝብ ስለላ በዝምታው ውስጥ መልሱን ይሰጣል። አርኪቡም ይመሰክራል። አርኬቡ ላይ ድራሹ ቢጠፋ እንኳን ሌላ ሥራ የለምና ማጥፋት፤ መደመስስ ስለሆነ ብልሆች ልቅም እያደረጉ ፋይል አደርገውታል። ይህ ሁሉ ምንጩ ሰውን ስለማይወደደ የመጣ መከራ ነው። ሰውን ማዕክል ላደረገ መንፈስማ ምኑም አይከብደውም። ደግነትን፤ ርህርህናን ተስፋን ለመቀበል ተራራ አይሆንበትም ነበር።

ወረቀት ሰውን እለሰራም። „ቃል“ ነው ሰውን የሠራው። „ቃል“ ነው መዳህኒት እንጂ ወረቀት አይደለም። ወረቀት ይቃጠላል። „ቃል“ ግን ዘለዓለማዊ ነው። በዬደረስከብት ፈተና መሆን አለመታደል ነው። የረገጥከው፣ የቀረብከው ነገር ሁሉ ጦስ አምራች ሲሆን ስለምን ብሎ ህሊን መጠዬቅ ይገባ በነበረ? በመሆንህ ውስጥ በሌለ አቅም መሆነህ እያወቅከው ሁልጊዜም ባልሆነ ተስፋ ተንጣላጥሎ ሰውን ማሳሳት፤ ማታኮስም በራሱ ወንጀል ነው።

ሰውን ለማጣላት ማስገበሩ ምን ያተርፋል። ሰው አለው/ የለውም የመንፈስ ሃብት ብሎ አጋ ለይቶ ሲቧከስ ደስታ ነው። እልልታ ነው። ሜዳውም ፈረሱም ቢባል እኮ የሚቻል አይደለም። ቢሆን እማ ኖሮ ከሰማይ በታች አግዝፍን አውጥተነው ነበር። ግን ውስጡ ከሌላ ማንም ሰው ምንም አድርጎ አኮፍሶ ቢያወጣው ጊዜ እያበጠረ፤ እያንተረተረ እያንጎዋለለ መልክ ያስይዘዋል። ስለምን? ማህበራዊ ንቃተ ህሊና አዳጊ ስለሆነ። ማህበራዊ ሚዲያ የታቆረ የኩሬ ውሃ ስላልሆነ። ወቅት የሚሸልመው ሌላ ብልሃትም አለ። እድገት አለ። አንድ ቃላት ለዘመኑ አታጋይ ነው „አቸናፊ፤ አሸናፊ“ አዋጊ ቃላት ነበሩ ለዘመኑ። 

አሁን ደግሞ „ተጋድሎ“ ሆኗል። „ፈተና“ ነበር ድሮ ዛሬ „ተግዳሮት“ ሆኗል። ድሎ ዓለምዓቀፍ ነበር አሁን “ሉላዊነት“ ሆኗል። ድሮ „ምላሽ“ ነበር አሁን „ግብረ ምላሽ“ ሆኗል። ዘመን ያመጣቸው በዬአገሩ ቋንቋ መተርጎም ስላልተቻለ እንደ ሥምም እንደ ግሥም የሚራቡም አሉ „ጉጉል“ ጀርመኖች googlen / googln ብለው አግሥሰውታል  Google እንዳለ ሥም አድርገውታል። እርባታውም አርቲክሉም በመደበኛ ውስብስቡ የስዋሰው መርሃቸው ውስጥ ተካቷል። ዘሩ go ከሚለው ነው የመጣ ነው የሚሉት። ፍሰቱ ቃናው የጀርመንኛ እንደ አማርኛ ነው በጣም ረቂቅ ነው ግን አይደፈረም። አለምም ቀርቶበታል ባይ ነኝ እኔ በግሌ። ክብደቱ ሳይነሳ ማለት ነው።
ያሸነፉት እንደ ተከበሩት ልዑል ዶር አስፋው አስራተ ካሳ ዓይነቶችን ሳይጨምር። ጀርመኖችም እንደዛ ዓይነት ዜማዊ ቃና የላቸውም ዝክረ ናቸው ለጀርመንኛ ቋንቋ ልዑሉ፤ ልክ እንደ ዶር አብይ አህመድ ትግረኛ ቋንቋ ጥዑም ሳቢ ማራኪ ቃና ነው ያላቸው ጀርመንኛውን ሲናገሩት። አጅግ የሚስብ ብቻ ሳይሆን ማህሌት ላይ የቆማችሁ ያህል ነው የሚመስለው። አንድ ዓለምአቀፍ የስዕል ኤግዚቢሽን ኢትዮጵያም ነበረችበት ሲከፍቱ ነበር ያዳመጥኳቸው። የሰማይ ማህሌት ነበር የሚመስለው። እኔ ቋንቋን ድምጸቱ፤ ቃነው፤ ቅላጼው፤ ምቱ፤ ቅርጹ፤ ይዘቱ፤ ድምጸቱ ይመስጠኛል። ቋንቋ እኮ ሙዙቃም ነው። ምት አለው። 

ወደ ቀደመው ስመለስ አማራ ህልውናዬ አደጋ ላይ ወድቋል ሲል „ የአማራ ተገድሎ“ ብሎ በአደባባይ ወጣ። አዲስ ዘመን የሰጠውን ስንኝ ፈጥሮ። ያው ለቅኔው መንደር የሚመጥን ነው። ሞቱን ፈቅዶ ሞተለትም፤ ታስረለትም አካሉን ሰጠለትም፤ ታዲያ አንተ ብራስልስ ላይ ተቀመጠህ „የነፃነት ሃይል“ ለማለት አቅም የለህም። ማን ፈቀደልህ? ይሄ ነው ህዝብ እና መሪን የሚለዬው። የህዝብ ማህበራዊ ንቃተ ህሊና ቀድሟል አንተ ጀራት ነህ፤ ጅራትን በማንህሎኝነት ተቀበሉ ነው። ይሄን ጋዜጠኛው ተቀብሎ ያስተናግዳል ባላብዕሩም ባለብራናውም። ዝም መልካም ነገር ነው። ከዚህ የህዝብ የተደሞ ውሳኔ እና አቋም ውጪ እሄዳለሁ ብትል ከባህር የወጣ አሳ ትሆናለህ።
በዚህም ጠቅላላ አዬሩ ተቀዬረ። ዛሬ ብትን መሬት፤ አንዲት ነፍስ ማግኘት አይቻልም። የመንፈስ ሃብት ዋጋው ከፍ ያለ ነው። አደፍጦ የተቀመጠው ሁሉ የአብይ መንፈስ ሲመጣ አብይ ድምጼ ያለውም ለዚህ ነው። ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ነበር ህዝብ ቀን ከሌት ውጤቱን ሲከታታል የነበረ። የወረቀት ስንቀኛ ብቻ ነበር እዬቆፈረ ሲባዝን የነበረው … ለማፈረስ፤ ጠልፎ ለመጣል። እኔ እኮ ቤተሰቦቼ ሲነግሩኝ የመልዕክት ልውውጡ የ አብይ ንግግር እንደ ነበር ነው የሚነግሩኝ። ሁሎችም አክቲቢስቶች ናቸው። የሚደፈር ሃይል ፈጽሞ አይደለም። ሁሉም ማለት እችላላሁኝ ቤተሰቦቼ የ አይቲም ከፍተኛ ባለሙያዎች አሉበት ትጋታቸው ሲነገሩኝ በጣም ነው የገረመኝ። መነሻው የ አማራ ተጋድሎ ነው። የለማ መንፈስም ንጉሥ ነው ከሁለቱ አንደኛቸው ብቻ እንዲሆኑ ነበር ጸሎታችን ነው የሉት። በጣም ነው የሚደንቀኝ እኔ ... ያላችሁ ሊመስላችሁ ይችላል ግን ውስጡ የለም ቀለም የሌለው አስክርቢቶ እኔ እውነቱን ነው የምነግራችሁ ... 
  • ቅዳሜን ጠብቅ ፈጣሪ እኔ ፈሪ ነኝ እና ... 


ዛሬ ሚሊዮኖች የእኔ ብለው ሊወጡ አስበዋለኝ ቀጠሮው ለቅዳሜ ነው። ያው እኔ ፈሪ ስለሆንኩኝ በስጋት ውስጥ ነኝ። አሁንም አዋኪዎች ስለማያርፉ። የምስጋና ቀን ብለው ቅኖች ይወጣሉ መልካም ነገር ቢሆንም አጋጣሚውን ያልሆነ መፈክር ይዘው ወጥተው የሌሎችን አጀንዳ አድማቂ እንዳይሆን ስጋት አለብኝ። የሚሆነውን መተንበይ አልችልም። ደቡብ ህዝብ ያን የመሰለ ፍቅር ሲሳጥ እርፈት ስላልሰጠ ነበር የአሁኑ ዕንባ የፈሰሰው። ቅዳሜ እንኳን ቢሳካ በዛ መሪነት ሌላ ሰልፍ ቀጥዬ አዘጋጃለሁ ቢባል ሌላ ድራማ አይቀሬ ነው። ስለምን? የህዝብ ሰቆቃ ስለሚናፍቀን።
  • ቀጣዩ አዲስ ቀን። 

የሆነ ሆኖ ነገ የዓለም የሰላም ሽልማት ቢጎመዝዘንም፤ ቢመረንም ይመጣል። ዕውነት ቢደብቋት መፍለቋ አይቀሬ ነው። አንተ የወረቀት አምላኪዎችህን አሰማርተህ የፈለገህን ያህል ብትፍጨረጨር አይሆንም። ትርፉ መጋጋጥ ብቻ ነው። አንተ በጦርነት ድል አደርጋለሁ ብለህ ብታሰብው እንኳን አቅሙ እንደ ሌለህ ታውቃለህ። በመደበኛ ቀርቶ በሽምቅ እንደማትችለው። ሚዲያ ብርጌድ አይሁንምና። እውነት ተዘሎ ድል አይታፈሰም። አቅም አይፈቅድም። ይህን ደግሞ መሪዎችህ ራሱ ወጥተው ተናግረውታል። መልካሙ ነገር ሰውን ሳያምታቱ በአቅም ውስጥ መኖር ግድ ይላል። ልክን አውቆ መኖር ብልህነት ነው። ነገሩ እዬተገፋ ሲኬድ ክቡር የአቶ ሞለ አስገዶም ሠራዊት ያጥለቀልቃል አዲስ አበባ ነው ግን መሳገሪያ የለውም ባዶ ነው። አማራ ጅል አይደለም። ለሚወጋው መንፈስ አንጋችነት በቃኝ ብሏል። የዛሬ 100 ዓመትም አይሳካም። ስለዚህ ሁለመናህን አጥበህ አዲስ ሰብዕና ማምጣት ባይቻል እንኳን ያው በተለመደው መመስል እና ማስመሰል አንገትን እያቅለሰለሱ ከች ማለቱ ይበጃል።

የአሁኑ እልህ የኦቦ ሌንጮ ለታ ፓርቲ የወሰደው አቋም እና ያተረፈው የፖለቲካ ብልህነት ያመጣው መግረጭረጭ ነው። አዬሩን እንዲታወክ ለማድረግ የታሰበው። የአብይ መንፈስን ለማወክ። ኦህዴዶች ከውስጣቸው እንዲያዝኑ እና ተስፋ ቆርጠው እንዲተውቱ ለማድረግ። ወያኔ ሃርነት ትግራይ ውስጣቸውን አቁስሎ ፊታቸውን አብልዞታል እኛ ደግሞ በዛ ቁስል ላይ የአንጀት ቁስል እንዲጨመርበት አብረን እንሰራለን። ማደራጀት ቡና መጠጣት መስላችሁን?
  • የዘመን ጀግኖች የማህብራዊ ንቃተ ህሊና አድማጮች ብቁዎችም።


... ግን ጀግናው ለማ መግረሳ፤ ጀግናው ገዱ አንዳርጋቸው፤ ጀግናው ዶር አንባቸው መኮነን አብረዋቸው አሉ። 108 የአብቹ አንበሶችም እዛው ምክር ቤት ውስጥ አሉ። ኢትዮጵያ በታሪኳ በእኛ ዕድሜ ፍቅርን የደፈረ መሪ ቢኖራት ዶር አብይ አህመድ የመጀመሪያው ናቸው። ይህንስ ምነው የቅኔው ልዑል ብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/ መድህን ተነስቶ ባዬልኝ ነበር። ለዛውም በዚህ በእሱ አክቲቢስትነትም የመጀመሪያው መሪ ናቸው። ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚ/ር በነበሩቡት ጊዜ ቢሯቸው ውስጥ ነበር የሎሬቱ ታቦት፤ ወደ ኦህዴድ ሲሻገሩም ታቦታቸውን ይዘው ነበር። ለነገሩ የእሱን መንፈስ የሙጥኝ የሚል አይሸነፍም። ሚስጢር አለው። በጄኔባ የሰብዕዊ መብት ጉባኤ የተመሰጠበት ዕውነት ይህንስ ታገሉና አሸንፉ ችሎቱ ካላችሁ። የጋናን ያህል ሳይሆን ዓለም ከሄደበት መስመር በእጅጉ የተለዬ ሰውኛም፤ ተፈጥሮኛም የፍቅራዊነት መንፈስ ነው አዲሱ መንገድ … ለስላሳ እንጂ ግትር እና እንደ ጠፍር ገራራም አይደለም ... "ልብ ያለው ሸብ ይላሉ ጎንደሬዎች።"

የእኔ ቅኖች ቀንበጥ ብሎጌን ስለፈቀዳችሁ እጅግ አድርጌ አመስግናችሁለሁ። አዶናይ ይጠብቅልኝ። ድንግልዬም መንገዳችሁን ሁሉ ታቃናልኝ።

Seregute Selassie You Tube ጎብኘት አደርጉት ግን ጥያቄዬ በትህትና ነው። ትንሽ የሚከብዱ ነገሮች አሉት ግን መንፈሱ ይረዳል። ፍቅርን የሚፈራ ሸረኛ እና ምቀኛ ብቻ ነው። የልግመኛው ፖለቲከኛ ቤተኛ ብልጽግና የፍርሃቱ መነሻም መድረሻም ነው።
  • ፎቶ ከሳተናው ድህረ ገጽ የተወሰደ። 

የአብይ መንፈስ ያሸንፋል!
አብይ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ሽልማት ነው!
የአብይ የተስፋ ማግሥት ይበቅላል፤ ይለመልማል፤ ይጸድቃል!
አብይ ኬኛ!


መሸቢያ ጊዜ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።