ሃኪሙ የኢትዮጵያ ጠ/ ሚር፤

     ፍቅር ኪሎኛ አይደለም።
                                   ከሥርጉተ ሥላሴ 20.06.2018 (ከገዳማዊቷ ' ሲዊዘርላንድ።)

                 „በጎ ነገር ከጥንት ጀምሮ ለበጎ ሰዎች ተፈጠረች እንደዚሁ ክፉ ነገርም ለሃጢያተኞች ተፈጠረች“ 
                                     (መጽሐፈ ሲራክ ምዕራፍ ፴፱ ቁጥር ፳፭)

ፍቅር የቁጥር ተማሪ አይደለም። ወይንም ፍቅር በሜትር የሚመተር አይደለም። ወይንም ፍቅር በወቄት የሚለካ አይደለም። ወይንም ፍቅር በክንድ የሚሰፈር አይደለም። ወይንም ፍቅር በእፉኝ // በጭብጦ የሚመዘንም አይደለም። ፍቅር ኪሎ የለውም። በፍቅር ተፈጥሮ ውስጥ ቀመር የለም። ፍቅር መለኪያ መስፈርት የለውም።
ፍቅርን ሲያስቡት ቀላል ተፈጥሮ ይመስላል። ግን እንደ ፍቅር እጅግ ፈተኝ እና አድካሚ ተፈጥሮ የለም። ፍቅር ውስጥ በቀላል ውጣ ወረድ ወይንም በለብለብ ግጥምጥሞሽ የፍቅርን ተፈጥሮ ማግኘት ይቸግራል።

ፍቅር ችግር የሚሆነው ሰው መሆን ሲያቅት ብቻ ነው። ሰው መሆን ያቀተ ዕለት የፍቅርን ተፈጥሮ ፈተናዎችን ተራራ አክለው፤ ምን ተራራ ብቻ ውሃ ያዘለ ተራራ ሆነው ሳንሸከመው ግን በሃሳብ ብቻ የዝዝላል። ፍቅር ጀግና አይደለም የሚፈልገው ለእኔ። ስለምን? ፍቅር ራሱ ጀግና ስለሆነ።

እርግጥ ነው ጀግና ጀግና ቢፈልገው አይደንቅም፤ ግን ጀግናን ፈጣሪው ጀግና ስለሆነ ነው ፍቅር ጀግና አይደለም የሚፈልገው ያልኩት። ፍቅር ጥላቻን አሸናፊ ሆኖ ሲፈጠር ነው የጀገነው። ጀግናን የሚቀበሉ የጀግና ተከታይ ወይንም በቀረበ ትርጉም የጀግና ቤተሰብ ቢባሉ ያስኬዳል።

የፍቅር ተፈጥሮ መርሁ በማድመጥ ይወሰናል። በማድመጥ ይወሰናል ስል ማድመጥ ብቻ አይደለም እጅግ ሰፊ የአምክንዮ እርባታዎች አሉበት። ለመነሻ የሚሆኑ ጉዳዮችን ከፍቅራዊነት ዩቱቤ ላይ ስላለ ከዛ ማግኘት ይቻላል። ከሥር እለጥፋለሁኝ ምርኩዙን።

ማድመጥን ስላነሳሁኝ በፍቅር ተፈጥሮ ሰውኛ በሆነ ግንዛቤ ማድመጥ ከተለመደው ይለያል ለእኔ። እንደምን ቢሉ? ፍቅር የሚያደምጠው የራሱን ተፈጥሮ ነው። ስለምን እንደ ተፈጠረ? ስለማን እንደ ተፈጠረ? ስለምን ዓላማ እንደ ተፈጠረ? ስለምን ግብ እንደ ተፈጠረ የራሱን ተፈጥሯዊ ህግጋት አድማጭ እንደ ፍቅር የለም።
የሚገርመው የሰው ልጅ ትልቁ ችግር ራሱን ለማድመጥ ጊዜ ኖሮት አለማወቁ ነው። የእውነት ነው የምላችሁ። ሰው ሁልጊዜ የሚያጣፈው ጊዜ በራሱ ተፈጥሮ አምክንዮ ሳይሆን እሱን በፈጠሩት ሳቢያዎች አካባቢያዊ ሁነቶች ብቻ ነው። ልክ ሰሞኑን ታላቁ ኢትጵያዊ የህግ ሊሂቅ ዶር ያዕቆብ ኃ/ ማርያም ከስንት ዓመት በፊት የተወሰነን ውሳኔ ሳቢያ ላይ ወርደው ስለ አፈጸጻም ሂደቱ ላይ ሄደው ከጭብጡ አናት ሙሉ ለሙሉ ወጥተው ሲከራከሩ እንደ ነበረው ማለት ነው። 

„ሰው“ የሚለውን ስተው ቁሳቁስ ላይ ቸክለው ነበር። የባከነ ጊዜ ቢሉት ይሻላል ያን ዶር ያዕቆብ ቆይታቸውን።  የፖለቲካ ሊቀ ሊቃውነቱ ሳይንቲስቱ ዶር መራራ ጉዲናም እኛ በህይወት አናገኛቸውም፤ ስኳር በሽታ እንኳንስ እስር ቤት በተደላደለም ሥፍራ ፍዳ ነው እያልን ቀን ከሌት እናስባለን ሲፈቱ እሳቸው ያስጨነቃቸው ቆርቆሮ ነበር በዓለም አቀፍ ሚዲያ " እስከ አሁን መኪናዬ አልፈታችም" ነበር ያሉ ለዶር. ነጋሶ ጊዳዳ እኮ መኪና ገዝቶ ኦህዴድ ሰጥቷቸዋል መኪና ሳይሆን ብርቁ ለኦህዴድ "ሰው" ነው። የተጋውም ለዚያ ነው። ለነገሩ እሱ ብቻም ሳይሆን የገዱ መንፈሰም ነው። እናመሰግናለን ሲሉም አልሰማሁም። ብቻ ሳቢያ ነው ጊዜያችን ሲባለው የኖረው። ሰው በሚያተርፈው ጉዳይ አይደለም የሚባክነው። ይልቅ በባድመ ጉዳይ ዶር. መራራ ጉዲና ጥሩ ዕይታቸውን አዳምጫለሁኝ። አሁን ያለው የትግል ሂደትም የ43 ዓመቱን የጦርነት ዘመን ምዕራፍ ስለመዝጋት መሆኑ ልብ አላሉትም ፖለቲከኞቻችን። ድሉም እንዴት እንደ ተገኘ አለስተዋሉትም። የ አሁኑም ሂደት በፍቅር መስመር ቅራኔዎችን አለስልሶ ለመያዝ የተጀመረውን ስልታዊ ጉዞም ልብ አላሉትም። 

የኛዎቹን ተፎካካሪ ይሁን ተወዳዳሪ የፖለቲካ ድርጅቶችን ልብ ብላችሁ ስትምለከቷቸው አንድም ቀን በተፈጠሩበት መስምር ሲተጉ አታዮቸውም። ተከታዮቻቸው ሆኑ አባሎቻቸውም እንዲሁ ፈጽሞ በማይመለከታቸው ጉዳዮች ነው ሲባዝኑ የምትመለከቷቸው። ጊዜ ሲያባክኑ። አቅም ሲያብከኑ። ትወልድ ሲያባክኑ፤ ስለምን? የሰው ልጅ ራሱን ለማድመጥ በፍቅር ተፈጥሮ ረቂቅ ህግጋት ውስጥ ተገርቶ ስላላደገ። የሰው ልጅ ራሱን፤ ውስጡን፤ ነፍሱን ማድመጥ ከቻለ ብቻ ነው የአካባቢውን ተጽዕኖ ፈጣሪ ተወራራሽ፤ ተያያዥ ነገሮች በማጥናት፤ በማሸነፍም ከዛ ከፍ ካለ የሃሳብ ደረጃ ደርሶ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን የሚቻለው።

አሁን የዶክተር አብይ አህመድ ልቅና ይሄው ነው። ከሳቢያ ሳይሆን ከምክንያታዊ የሆነው የተፈጥሮ ማዕከል „ሰው“ ስለምን ተፈጠረ? ከሚለው ነው የተነሱት። በሰው ሰውኛ ንቃተ ህሊና ራሳቸውን አዳመጡ፤ በአቅራቢያቸው ያለውን ተወራራሽ ተፈጥሮኛ ሰንሰለትማ ሰብዕናዎችን አዳመጡ፤ በአካባቢያቸው ያለውን ዘለበታዊ ጅረትን ከሰው ጋር ንክኪ ያላቸውን አመክንዮዎች  አዳመጡ፤ አህጉራቸውን በሰውኛ ዘይቤ አዳመጡ፤ ሉላዊውን በተፈጥሮኛ ፍላጎት አዳመጡ፤ አጠኑት የእኔ ብለው አቅርበው። በዚህ ውስጥ የማድመጥ ምርምራቸው ማሰብ ማንሰላሰል ከጀመሩበት ዘመን ጀምሮ ሰውን ማዕከል አደርገው ተጉ። በእውቀት አበለጸጉት። የባከነ ጊዜ የለም። በዬጊዜው ወደ ራሳቸው ተመልሰው ጥቅምና ጉዳቱን መረመሩት አስጠግተው። ቁልጭ ያለው በሽታ ያለበትን ሰርጀሪ አደረጉ፤ እና ዕጢውን አገኙት። 

እናም ዕጢውን ለማውጣት ሲተጉ ከዛ በተቃራኒ ያለውን ቁልፍ ጉዳይ አጠኑት። ዕጢውን የሚያለመልመው፤ አለምልሎ ነፍስ የሚያጠፈውን ጉዳይ አዳመጡ ዋናው አሉታዊ እና ጥላቻ ነው ከሚል መደምደሚያ ደረሱ። አሉታ እና ጥላቻ ከቀልሃም፤ ከመድፍም፤ ከቦንብም ጣይ አውሮፕላን በላይ ሰውን ከነተጠፈጠሮው የሚያወዱም ናቸው። ማክሰል።

መዬት እና መሞከር እንዴት ጥሩ መሰላችሁ ቅኖቹ - የኔዎቹ። አሁን እኔ ዮጋን፤ ጅምን፤ ሜድቴሽንን ምን ያህል መንፈስን እንደሚጋራ የወቅኩት ራሴም ሞክሬው ነው። ሰው በሌላው ሰው ላይ የሚያውን ሞክረህ ንገረኝ ከሚል ራሱ ተሞካሪ ኦብጀክት አድርጎ ማዬት አለበት። ትርፍና ኪሳራው የሚመዘነው በራስ ላይ ራስን መፈተኛ፤ መሞከሪያ ማድረግ ሲቻል ብቻ ነው።

ስለዚህ ሙሴው ተቋጥሮ፤ ሥር ሰዶ የኖረውን ዕጢውን ከሰውነት ውስጥ ፈንቅሎ ለማስወገድ ፍቅር የሚባል የጠቅላላ ህክምና ማዕከል ከፈቱ፤ አሁን በሽተኛው ሁሉ እዬሄደ በነጣ እንዲታከም ፈቀዱ። ሜዞ አይወጣበትም። የክት እና የዘወትር አይለይበትም። ሃብታም ደሃ የለም። መሃይም ሙሁር የለም፤ ተከሌ ዘውግ ተከሌ እንቶኔ የለም …

  • እንግዲያማ ተኛስ?

የመጀመሪያው መሰረታዊ ጉዳይ እኔ በሽተኛ ወይንስ ጤነኛ ለማለት ራስን ማድመጥ ይጠይቃል። ታምሜያለሁኝ ወይ? በሙሉ ወይንስ በከፊል ብሎ ጠቅላላ ውስጥን መፈተሽ ይገባል። ራስን ለማድመጥ ሰው ከሚለው መነሳት ይሻል። ይህም እኔ ሰው ነኝ ከማለት። ሰው ከተሆነ በውስጥ ያለው ስሜት በመቀነስ ወይንስ በመደመር ላይ ሥራ በዝቶበታል ብሎ ማድመጥ። ለፈቀዱት የአብይ ኢንዶስኮፒ በመቀነስ እና በመደመር መከከል ያለውን የልዩነት መጠን ያዳምጣል። በመቀነስ ከሆነ ከመቀነስ በፊት ከመደመር ጋር ለመደመር የመቀነስ ምልክትን በሙሉ ጥርግርግ አድርጎ ወደሚያወጣው የመደመር ጠቅላላ የጤና አገልግሎት ሪፈር ይጽፋል። አዋሳ ላይ የመጀመሪያው የዬምሥራች ብሄራዊ ጉባኤ እኮ ታዳሚዎች „በርበሬ ታመመ፤ ቡና ታመመ ሲባሉ“ ሃኪሙ የኢትዮጵያ ጠ/ ሚር „አዬ እናንተ  ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያልተመመ ነገር አለና? ሁላችንም ታመናል“ እኮ ነው ያሉት።

ገራሚው ነገር 24  ሰዓት 7 ቀን አገልግሎት ስለሚሰጥ ሆስፒታሉ ማንኛውም ድውይ መሄድ ይቻላል። ውይ አንድ ነገር በኢትዮጵያ ያሉ ቀናት ለካንስ ከመጋቢት 24 ቀን 2018 ጀምሮ እኮ 8 ቀን ሆኑ አሉ። ቀን ተሌት ሳተናዎቹ ቅንኛዎች ይተጋሉ …

አዎናወጪ ሳይቀር የህክምና አገልግሎቱ ይሰጣል። ቀጥ ብሎ ጌታውን ዩቱብ መክፈት፤ ቁጭ ብሎ መታከም፤ ኪሎ አይጠይቅ፤ ትኬት አይጠይቅ፤ ሜትር አይጠይቅ በቃ በነጣ ብቻ የመፈወሻ ጠበል በዬምድጃው ይሄው አና ብሏል። ድንበር የለው፤ ክልል የለው፤ / ከተማ የለው፤ እነ ሳጅን እነ ኢስፔክተር እነ ምንትሶ ቅብጥርሶ ትውር አይሉበትም፤ ኪራይ ሰብሳቢ ሙስና የሚባል የለም ስላችሁ። በቃ ለፈቀደ ሰው መሆንን አይዋ ጉልግልሻ በሉላዊነት የተገራ መቼም ሲፈጠር ታጥቦ የፈጠረው ነው በዬቤቱ ከች ነው። ሌላም ከ አይዋ ጉግል ልብለጥ ያለ ሊመጣ ነውም ይባላል። ብቻ አይዋ ጉግል… ወዳጅነቱ በመሆን የተገኘ ነው። ዝንፍ የለ ቅርንፍ የለም።

መሆን ግን የግድ ነው እዬበሉ እዬጠጡ ዝም የጋን ወንድም አይገባም። እነዛ ክፉ መንፈሶችንዛሮችን አውሌያዎቹን እነ ሰይፈ ጨንገሬዎችን እንክርዳድ ጠላ ካልጠጡ ረፍት የማይሰጡትን ክፉ ሃሳቦችን ሁሉ ጆሮ መንፈግ በቃ አረሙ እንዳይበቅል ብልህነት ማድመጥ ብቻ ሳይሆን ባዳመመጡት ውስጥ መብቀልም ነው።

  • ፎቶ ምንጭ ከዘሃበሻ። እግዚአብሄር ይስጥልኝ ይህ ፎተ እጅግ ያስፈልገኝ ስለነበር። ለሌላ ተግባር። 
  • ፍቅራዊነት LoveIsm Sergute Selassie YouYtube.


ፍቅር ኪሎ የለውም!

ቅኖቹ የፍቅር ተፈጥሮ ቤተሰቦች ለነበረን ዘንካታ ጊዜ እግዚአብሄር ይስጥልኝ። ኑሩልኝ።

መሸቢያ ጊዜ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።