የአፍሪካ ቀንድ ታላቅ የምሥራች ቀን ዋዜማ!


የአፍሪካ ቀንድ ታላቅ የምሥራች ቀን ነው። 
የበርሊኑ ግንብ የተደረመሰበት ዋዜማ!
የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል።
   ከሥርጉተ ሥላሴ 20.06.2018 (ከገዳማዊቷ - ሲዊዘርላንድ)


                 "የሰው ልብ መንግድን ያዘጋጃል፤ እግዚአብሄር ግን አካሄዱን ያቃነለታል።" (ምሳሌ ምዕራፍ ፲፮ ቁጥር ፱) 
  • ዋዜማ።

መቼም በዬዕለቱ አበረታች ብቻ ሳይሆን አጽናኝም፤ ተስፋም፤ የምህረት መንገድም፤ የፍቅር ጉዞም ተጀምሯል። በተደጋጋሚ እንደ ገለጽኩት ፈቀደ እግዚአብሄርም ነው። ኢትዮጵያን በቀሽ ብሏታል ፈጣሪ አምላክ።
የመላ ኢትዮጵያ ህዝብ ጸሎት፤ እንባ እዬርን አንኳኳ፤ በሩን አስከፈተ፤ ፈጣሪም በቃልኪዳኑ ልክ ሙሴ ሰጠን። ይህ የፍቅር ሙሴ ጥበቡ ስልቱ ከፈጣሪው የተሰጠው ነው። በቅንነት ላገልግላችሁ ብሎ ተነሳ፤ እኛ ቅነንታችን በድርቅ ተመቶ ባንደግፈውም፤ እኛ ቅኖች ሆነን አይዞህ ለማለት አቅም ቢያነሰንም ጥንካሬው የፈጣሪ ነውና ይሄው እንደ ጥረቱ ዛሬ ታላቅ የአፍሪካ ቀንድ ሆነለት። ማዕለተ አብይ! ተመስገን!

እኔ የሚናፍቀኝ የበርሊኑ የመረቡ ግንቡ ሲናድ የኤርትራ ህዝብ እንዴት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚነጉድ ነው። ምክንያቱም የስንት ዓመቱ ውጊያ እና ውጤቱን መሬት ላይ ኑሮበት አይቶታል እና። ፍቅርን ስትቀርበው ፍቅርን ስትቀበለው እንዴት እንደሚያበራ። ፍቅርን ስትሸሸው ፍቅርን ስትገፈትረው ደግሞ እንዴት አጭር፤ ኮስማና፤ አመዳም እና ቡላ እንደሚያደርግ፤ መለዬት ናፍቆት አይደለም። መለዬት ከሞትም በላይ ነው።

ዛሬ የልደት የፋሲካ የትንሳኤ ዕለት ነው። እትዬ አልጋነሽ በሩ የተከፈተ ዕለት ጎንደር ቀጥ ብላ ሄዳ እናቴን እንደምታይ ነው። መቼም በዚህ ውስጥ ስንት የዕንባ ሲቃ እንደሚወርድ ነው። ፍቅር ጥሩ ነው። ፕ/ ኢሳያስ አፈወርቂም እንኳን ለዚህ አበቃቸው። እውነት ለመናገር ፎቷቸውን ትክ ብዬ ሳዬው ሁልጊዜ የውስጣቸው መከፋትን አዬው ነበር። ሳቃቸው እራሱ የውስጥ አለነበረም።

አሁን በደልን፤ ቁርሾን፤ ሰቆቃን ረስተው የኢትዮጵያ እናቶች ማህጸናቸው የደረቀበትን ዘመን የቻሉት ልጆቻቸው የወደቁበትን ቦታ ሄደው አይተው ለሁለቱም ህዝቦች ዕልቂት ምክንያት የሆነው የህሊና ካሳ ከፋዩ ፍቅርን ሸምተው፤ ሰማዕታቱን እኩል የሚዘክሩበት ቀን ይኖረናል። ታምረኛው የአፍሪካ ቀንድ ሙሴ ይህን ያስደርጋል። የታሰሩ እስረኞቻችንም ይፈታሉ። አብይ ኬኛ! ወንደሞቻችን ልጅ ወልድ ከሆኑም ፈልገው ይመጣሉ። ምን አልባት የሃይልዬ ልጅ እናቴ የማዬት እድል ይገጥማት ይሆናል። 

ብቻ ብቻ ሰላም ጥሩ ነገር ብቻ ሳይሆን ሰላም ንፁህ አዬር ነው። ሰላም ጥሩ ነገር ብቻ ሳይሆን ሰላም ነፍስ ነው። ሰላም ጥሩ ነገር ብቻ ሳይሆን ሰላም መኖር ነው። ሰላም ጥሩ ነገር ብቻ ሳይሆን ሰላም ሥልጣኔም ነው። ሰላም ጥሩ ነገር ብቻ ሳይሆን ህሊናዊነት ነው። ሰላም ጥሩ ነገር ብቻ ሳይሆን ሰላም እኛዊነት ነው። ሰላም ጥሩ ነገር ብቻ ሳይሆን ሰላም ጽድቅም ነው። ሰላም ጥሩ ነገር ብቻ ሳይሆን ሰላም የሰውነት እና የተፈጥሮነት አክቲቢስት ነው። ሰላም ጥሩ ነገር ብቻ ሳይሆን ሃይማኖትም ነው። ሰላም ከሌለ መስጊድም፤ ቴንፕልም፤ ቤተ እግዚአብሄርም ምኩራብም የለም።

ሰላም አገር ነው። ሰላም ብትን አፈር ነው። ሰላም ናፍቆት ነው። ሰላም ብሄራዊ ባንዴራ ነው። ሰላም ትዳር ነው። ሰላም ልጅ ነው። ሰላም ትወልድ ነው። ሰላም ዘመን ነው። ሰላም ሰላም ሰላም ሰላም ሰላም ኑርልን!

በኢሣቱ ጋዜጣኛ መሳይ መኮነን ጹሑፍ መነሻነት "የባድም ዕድምታ በሥርጉተ ዕይታ" የሚለውን አገር ቤት ያሉ ሚደያዎችም እኔ ያነሳሁዋቸውን ነጥቦች አጉልተው ተዋያይተውበታል፤ በፓርላማ ውሎም ጠ/ ሚር ዶር አብይ አህመድም እኔ ያለኩትን መንፈስ ነበር ያጠናከሩት። ብቻ በዛ ጹሑፌ ላይ እዚኸው ስለሚገኝ ለጥቃችሁ ማንበብ ትችላላችሁ ውዱቼ።
  • ያልኩት ...

„የኤርትራ መንግሥት እንደ ማንኛውም መንግሥት ጥቅሙን ተጻሮ ይቆማል ተብሎ አይታሰብም - እንደ እኔ።“ „… የተሻለ ሁለቱም በአዋሳኝ የሚኖሩት ዜጎች እንደልባቸው ወጥተው ገብተው ካለስጋት በቀደመው የአብሮነት ብሂል የሚሠሩበት ጤናማ ሁኔታ ሊፈጠር ከቻለም አንድ ነገረ ነው … በፍቅር ፍለጋ ውርዴት የለም። ፍቅር ፍለጋ ሸንፈት የለም። በፍቅር ፍለጋ የመንፈስ ትርፍ እንጂ የቁስ ብልጠት የለም። በፍቅር ፍለጋ ክብር ነው ያለው። በፍቅር ጉዞ "ቅርቃር ውስጥ መጨመር" ሳይሆን የሚቀረቅረውን ዲያቢሎሳዊ ሴራ አክሽፎ ክፉውን መንፈስ አባሮ ቅርብትን ለዕልፍ መናኘት ነው። መኖርን ነፃ ማውጣት የፍቅር ፍልስፍና ነው።“ የሚል ጽፌ ነበር።

አዎን ዛሬ ፕ/ ኢሳያስ አፈወርቂ ለሰጡት ቅናዊ አዎንታዊ መልስ ጠ/ ሚር አብይ አህመድም መልስ ሰጥተዋል። ደስ ያለኝ ደግሞ በትግረኛ ቋንቋ መልዕከቱን መላካቸው ነበር። በአንድ ጹሑፍ ላይ ስለ ቋንቋ ማወቅ ወንጀል አይደለም በሚለው ጹሑፌ ላይም ትግረኛ ቋንቋን ዶር አብይ አህመድ ስለሚችሉ በኤርትራ ህዝብ ውስጥ ገብቶ በልብ ለመጎዝጎዝ አስተርጓሚ አያስፈልጋቸውም ብዬ ነበር። ዛሬ ዋዜማ ነው፤ ግን በቀጣይ የምሥራች ቀናት የምንሰማቸው ብዙ ልብ አንጠልጣይ እና አ አመክንዮች ይኖራሉ። ቋንቋ በራሱ ፍቅር ነው። 

ቋንቋ ሳቅ ፈገግታም ነው። ስለዚህ እኒህ ሙሴያችን የጣምራ ዝግጅታቸው ሙሉዑ ነው። ለዚህም ነው „ኢትዮጵያን ቁም ነገር የማድረግ ዓላማ“ ያለው መሪ ብዬም የጻፍኩት። ሁሉም እዚሁ ላይ ሰላለ ክብረቶቼ መከታታል ትችላላችሁ። 

ብቻ ዛሬ ሌላ የምሥራች ቀንነቱ በሰሞኑ የደቡብ የህዝብ ጥፋት እና ሁከት ብቻ ሳይሆን እዛ ከሄዱ በዋላ የተሰማቸው ቁስለት የሚፈወስ የሚክስ ነው። ድርብ ጠቀሜታ አለው። ሰሞኑን ጠ/ ሚር አብይ አህመድ አዝነዋል። ብር ብለው ሄዱ ግን ሃሳቦቹ አልተመቹ መሰል በጨረፍታ አዳምጫለሁኝ። ግን መልሳቸው ፈታኝ ስለሆነ ጸበል ማለት ነው። ባለቅኔው ጠ/ ሚር ሲናገሩ ለስህተት ፈጻሚዎች ብቻ አድርጎ ራስን ከደሙ ንጹህ ነኝ ብሎ ነው ሰው የሚያዳምጠው። በእያንዳንዱ የንግግር ዘለበት እራስን አስቀምጦ ራስን መፈተሽ ይገባል ። ይሄ ለህሊና አጠባው ጉዞ በጣም ይረዳል። 

ለውጥ እንሻለን። ለውጥ እንፈራለን። ለትዳር አጋራችን፤ ለወላጆቻችን፤ ለልጆቻችን፤ ለሙያችን ንጹህ ፍቅር እንሸልማለን ለነፃነት ግን አንችልም። እንፈታተሽ ልቡ ወኔው ከኖረን። 

  • እንደ ማሳረጊያ በምልሰት .. 

የባድም ዕድምታ በሥርጉተ ዕይታ ላይ ... ሌላው ግን የኤርትራን የማቅረብ ጉዳይ ጋዜጠኛ መሳይ እንደሚያስበው ወይንም እንደሚያሰጋው በብልጠት አይደለም። „አልያም ኤርትራን ዲፕሎማሲያዊ ቅርቃር ውስጥ ለመክተትና ጊዜያዊ ድል ለመጨበጥ በሚል ብቻ የተወሰደ እርምጃ ሊሆን ይችላል“  እኔ ያልኩት "እንዲህ ዓይነት ጠማማ ሰው አይደሉም ዶር አብይ አህመድ። ምንአልባት ቅንነታቸው እና ንጽህናቸው አንዳያስጠቃቸው ነው ስጋታችን እንጂ ውስጣቸውን ላጠናው ሰው ለፖለቲካም ብልጣ ብልጥነት የሚሆን ሰብዕና የላቸውም። ያው ፖለቲካ ብልጥነትም ትንሽም ከሴራውም ከሸሩም ቀምስ ቀምስ ቀሰምም ያለ ነገር ስለሚያስፈልገው። እንደ ተፈጠሩ ናቸው። ፍቅር አለበት በተባለበት ቦታ የማይደክሙ የፍቅር ሊቀ ትጉሃን ናቸው። ቀድሞ ነገር ከሴራ የጸዳ የፖለቲካ ሊሂቅ መሪም ዓይናችን እንደናፈቀው ኖሮ አሁን ነው ለመዬት የበቃነው። ንፅህናቸውን አይቶ ነው አምላካችን ከዛ ሁሉ የውስጥ መከራ አውጥቶ ለዚህ የፈተና ጊዜ አሻጋሪ ሙሴ ያደረጋቸው - የቀባቸው። በሌላ በኩል ስለ አፍሪካ ቀንድ ያላቸው በጎ ምልከታ ይሄው ማያያዣ ምርኩዙ። ስለ ኤርትራም ያላቸው ቅናዊ ራዕይም ይሄው … የቀደመ ስለመሆኑ።"

„Dr. Abiy Mohammed ሕዝብን የሚያረጋጋ ንግግር ተናገሩ
  • የኔዎቹ በሉ ብቻ ደስታውን በዚህ ምርኩዝነት ይሁን በሉት።
https://www.youtube.com/watch?v=BQ6OMKQEca8
Ethiopia / አብይ ለኤርትራው ፕሬዚዳንት በትግርኛ አነጋጋሪ ምላሽ ሰጡ፤
https://www.youtube.com/watch?v=qGMM1bd46xs
Ethiopia: / / አብይ ለኤርትራ ምላሽ የሰጡት ከፍተኛ ምስጋና

አመስግናችሁ አለሁኝ ክብረቶቼ። ኑረልኝ እናንተን አያሳጣኝ። ሲዊዞች ለካንስ ይሄን ያህል ትወዱኛላችሁ ማለት ነው። ግርም ይለኛል። ብራስልሶች ቅኔዎች ሆናችሁብኝ። አሜሪካኖች ደግሞ የቅኔ እልፍኞች ደቡብ አፍሪካ ሳውዲ ዩክሪን ፖላንድ እስራኤል ሲወዲኖች ሲዊዲኖች መንፈሶቼ እዬገረመኝ ነው የማዬው ነገር ሁሉ ይደንቀኛል በረከቱ። ነፍስ ሆናችሁ ነፍሳችሁን ሰጣችሁኝ። ምን ልስጣችሁ? ልቤን ተሸለሙ።

ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!
መሸቢያ ጊዜ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።